Telegram Web Link
በትሕትናው ልዕልናን ላገኘ፣ ለፍጥረታት ባለው ርኅራኄ የአምላክ እናትን ለሚመስል፣ የተቸገሩትን ፈጥኖ መርዳት ልማዱ ላደረገው፣ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ፣ ደግ እና ሰውን ወዳጅ ለሆነው መልአክ ለቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ በዓል እንኳን በሰላም አደረሰን።

ቅዱሳን መላእክት በአንድ ኃጢአተኛ ወደ እግዚአብሔር መመለስ የሚደሰቱትን ያህል፣ ባልተመለሰው ኃጢአተኛ ደግሞ እንዲሁ ያዝናሉ። በአንዱ ኃጢአተኛ መመለስ የተሰማቸውን ደስታ ፈጣሪያቸውን በማመስገን እንደሚገልጹ፣ ባልተመለሰው ኃጥእ የተሰማቸውን ኃዘን ደግሞ አምላካቸውን "ማረው፣ ይቅር በለው" ብለው በመለመን ያሳያሉ። (ያዕ 5፥13) ቅዱስ ሚካኤል አሁን እንዴት እንደ ሆንን አይቶ ይዘንልን፣ አዝኖም ይለምንልን፣ ለምኖም ያስምረን!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ሕመም ትጠላለህ? እና ሕመም የሚወድ ማንን አየህ? ትለኝ ይሆናል። እሺ ምንም ዓይነት ውጋት ድርሽ ባይልብኝ ብለህስ ተመኝተህ ታውቃለህ? እስኪ አንድ ስለማውቀውን "ያለ መታመም" ሕመም ልንገርህ።

ይህ ሕመም እንደ ባለሙያዎቹ አጠራር Familial dysautonomia ሲባል ከዘረ መል ምስቅልና ጋር ተያይዞ ከብዙ መቶ ሺህ ሕፃናት በአንዱ የሚከሰት ነው። የሕመሙ ጠባይ ልክ ከዚህ በፊት እንደምናውቃቸው በሽታዎች ቀስፎ ይዞ የሚያስጨንቅ ወይም በውጋት የሚያጣድፍ አይደለም። ሕመሙ ያለ መታመም ስቃይ ነው፤ ውጋትን ያለማወቅ ድንዝዝና።  በዚህ ደዌ የተጠቃ ልጅ እጁን በስለት ቢቆረጥ፣ በእሳት ቢቃጠል አይሰማውም። ምላሱ የመረረ ወይም የጎመዘዘን ነገር አይለይም። ሌሎች በሽታዎችም አድክመው ካልጣሉት በቀር ሲጀማምሩ የሚያሳዩትን ቀላል ምልክቶች ሰውነቱ ችላ ይላል፣ ቤተሰቦቹም መታመሙን ቶሎ አያውቁለትም።(Harold S., When Bad things happen to good people, 71) እንደዚህ ያለ ሕፃን ባለመታመም ሕመም ውስጥ ሆኖ ብዙ ማጣጣሩ አይቀሬ ነው። እንዴት ያሳዝናል!

ለካስ ሲያዙ ማቃሰት፣ ሲወጉ እህህ ማለት ሌላ ጤንነኛ የመሆን ምልክት ነው? ለካስ ቆረጠኝ፣ ፈለጠኝ አለማለት እንዲህ ያስጨንቃል? 

እስኪ አስቡት እግዚአብሔር ውጋት የሚባለውን ስሜት በሰውነታችን ጨርሶ እንዳይኖር ቢያደርግና፣ በዚያ ምትክ ስንታመም እንደ ደወል የሚያቃጭል ወይም እንደ አምቡላንስ መብራት የሚብለጨለጭ ምልክት ግንባራችን ላይ ቢያስቀምጥ እንዴት እንሆን ነበር? እንጃ አሁን ላይ ለማሰብ ሁሉ የሚከብድ ነገር ይመስላል? አንድ ነገር ግን እርግጥ ነው። አሁን ላይ ያለው ሰው ከነሕመሙ፣ ከነማቃሰቱ ያምራል። እንኳን የሚቃጭል ደወል አላኖረብን። እንኳንም ባለ ስሜት ፍጥረታት አደረገን።

ውጋት መኖራችንን ወይም እየሞትን አለመሆናችንን የሚያስታውሰን አንድ ምልክት ነው። ሕይወት የሌለውን ነገር ብትመታው፣ በስለት ብትወጋው፣ ብትረግጠው ምንም አይሰማውም። ለምን? እየኖረ አይደለማ። አንተ ግን እየኖርክ ስለሆነ ነው የምትታመመው።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ኅዳር 17/ 2016 ዓ.ም
+++ የማርያም መንገድ +++

ድሮ በልጅነት ከባልንጀሮች ጋር
በየጎዳናው ላይ ስንበር ስንባረር

አባራሪው ደርሶ መንገዱን ከዘጋ
ከግራና ከቀኝ ማምለጫ ካሳጣ

ተባራሪ ምስኪን መንገድ የጠበበው
በጭንቁ 'ሚጠራት አንዲት ዋስ አለችው

የእርሷን ስም ካነሣ የጠበበ ይሰፋል
የተዘጋው ሁሉ መንገድ ይከፈታል

ቀን በጎደለበት ባገኘው መከራ
በጨነቀው ስዱድ ስሟ የሚጠራ
ማርያም እርሷ ነች ሁሉን 'ምታራራ።


ጸወን መጠጊያ ለሆነችን ለድንግል ማርያም ዓመታዊ በዓል እንኳን አደረሰን። ጭንቅ እና መከራ በተሞላ ዓለም ውስጥ ከክፋ ቀን ሁሉ የምንወጣበትን "የማርያም መንገድ" የሰጠን አምላካችን ስሙ የተመሰገነ ይሁን!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com

ቴሌግራም
https://www.tg-me.com/Dnabel
ኃጢአት ጸሎት የማቋረጥ ውጤት ነው። እውነተኛ ጸሎት ኃጢአትን የማቆም ምልክት ነው። ሰው ኃጢአትን ልምዱ ካላደረገ በቀር እየጸለየ የሚበድል፣ ከአምላኩ ጋር እየተነጋገረ የሚያምጽ የለም። አዳም እጸ በለስን የቆረጠው ከአምላኩ ጋር የነበረውን ንግግር (ጸሎቱን) በማቋረጡ ነው። ይኸውም አዳምን ጠርቶ "ወዴት ነህ?" ባለው በፈላጊው ድምጽ ተረጋግጧል።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ክርስቶስ ደካማውን የእኛን ሥጋ የለበሰው፣ ራሱን ባዶ አድርጎ በግርግም የተወለደው፣ በስተመጨረሻም እርቃኑን የተሰቀለው ለእኛ ሲል ነው። ይህ ሁሉ ትሕትና እርሱን አንዳች የማይጠቅመው ስለ ሰው መዳን ሲል ግን የከፈለው ትልቅ ዋጋ ነው። የእኛ ትሑት መሆን ከእኛ በቀር ማንን ይጠቅማል? ትዕቢተኛ መሆናችንስ ከእኛ በላይ ማንን ሊጎዳ ይችላል? ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ እንደሚባለው ክርስቲያን ለራሱ ሲል ትሑት መሆን ይገባዋል።

ትሕትና ለራስ ነው!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ራስን ማጥፋት ሌሎች ሰዎችን ከመግደል በላይ ትልቅ ኃጢአት ነው። አንተ ሌላ ሰው ብትገድል ያን ሰው በሥጋው ትጎዳው እንደ ሆነ እንጂ ነፍሱን ግን አታገኛትም። ራስህን ካጠፋህ ግን በዚህ ዓለም አምላክህ የጠህን የሕይወት ጸጋ በገዛ እጅህ ታጣለህ፣ በወዲያኛው ዓለም ደግሞ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በማፍረስህ ነፍስህን ተጠያቂ ታደርጋለህ።

አቤቱ እኔን ከእኔ አድነኝ!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
"ማርያም ሆይ፣ የሐናን ጡት እየጠባሽ ወደ ቤተ መቅደስ በገባሽ ጊዜ ያገኘሽ ያለ እናት ማደግ ያሳዝነኛል፤ ዳግመኛም በደመና የሚጫን የእሳት አበባ የለበሰ ፋኑኤል እንደ አባት ከመላእክት ጋር መናን እየመገበሽ በቅድስና የማደግሽ ምሥጢር ያስደስተኛል"

አባ ጽጌ ድንግል

እንኳን ለእመቤታችን ወደ መቅደስ የመግባት በዓል በሰላም አደረሰን!!!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com
በምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ሥራ የሠራውና በተለይ በLiturgical Theology ተጠያቂ ሊቅ የነበረው አሌክሳንደር ሽሜማን ዛሬ የዕረፍቱ ቀን መታሰቢያ መሆኑን @St. Vladmir's seminary seminary ሲያዘክር ነበር። እኔም ይህን ፎቶ ባየሁ ጊዜ አንዲት ነገር ትዝ አለችኝ ፦ በትውልድ እንግሊዛዊ የሆኑት እና በዚያው በምስራቁ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በነገረ ሃይማኖት ተጠያቂ የነበሩት አባት ካሊስቶስ ዌር (ቅርብ ጊዜ ዐርፈዋል) በአንድ ስብከታቸው ላይ ስለ አሌክሳደር ሽሜማን ሲናገሩ፣ በተማሪነት ዘመናቸው ካስተማሯቸው መምህራን አንዱ እንደ ሆነ በመጠቆም ሽሜማን ሲናገር አንደበቱ ብሪቲሻዊ ለዛ ስለነበረው "Faith"/"ፌዝ" – የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል "ፌስ" ብሎ ነበር የሚጠራው። እና አንድ ቀን

"look at my faith, my faith is an ancient faith " / "ሉክ አት ማይ ፌዝ, ማይ ፌዝ ኢዝ አን ኤንሸንት ፌዝ"
በማለት ፈንታ

" ሉክ አት ማይ ፌስ ማይ ፌስ ኢዝ አን ኤንሸንት ፌስ" አለ ብለው ነገሩን በሳቅ ያስታውሳሉ። ያው እንግዲህ የሳቁን ምክንያት ለእናንተ ትቼዋለሁ! :-)
አባቶችህን ዕወቅ ቅጽ አንድ በወንድማችን በመ/ር ዲ/ን መንክር መዓሾ ወደ ትግርኛ ተተርጉማ ለንባብ በቅታለች። ያንብቧት!
ሰው ራሱን ሳያውቅ የሚቀረው ስላልቻለ ብቻ አይደለም፡፡ ራሱን ማወቅ ስለማይፈልግም ጭምር ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ‹ራስን ማወቅ› ይዞ የሚያመጣው ጊዜያዊ ሕመም ወይም ትንሽ ስቃይ አለ፡፡ ወደ ራሳችን መመልከት ስንጀምር የማንፈልገውን ‹‹እኛነት›› በውስጣችን ልናገኘው እንችላለን፡፡ በዚህም መረበሽ፣ መቆጨት፣ ኃፍረት ይሰማን ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ስሜት ለማምለጥ ብለን ወደ ቅዠታዊ ዓለም ይሄድ ዘንድ ለራሳችን ልንፈቅድለት አይገባም፡፡ ለእኛ ከማንም በላይ ጠላት የሚሆንብን ይህ በውስጣችን የተደበቀውና ማወቅ የማንፈልገው ‹‹ስውር እኛነታችን›› ነው፡፡ ስለዚህም በጊዜ ራስን መርምሮ አፋጣኝ መልስ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
"ኃይል የሌለውን ምንኛ ረዳኸው!
ብርታት የሌለውን ክንድ ምንኛ አዳንኸው!"
ኢዮ 26፥2
2025/07/07 19:24:33
Back to Top
HTML Embed Code: