Telegram Web Link
📌ድምጻዊ ጎሳዬ ተስፋዬ እና ድምጻዊ አለማየሁ ሂርጶ ከ20 ዓመታት በኃላ የሙዚቃ ስራዎችን በአንድ መድረክ ሊያቀርቡ ነው።

በ1990ዎቹ ለሙዚቃ አፍቃሪያን ከደረሱ የሙዚቃ አልበሞች መካከል "ኢቫንጋዲ" የተሰኘው አልበም ተጠቃሽ ነው።

በዚህ አልበም ጎሳዬ ተስፋዬ እና አለማየሁ ሂርጶ በርካቶች የማይረሷቸው ተወዳጅ ሙዚቃዎችን ለአድማጮች ያቀርቡበት ነበር።

በ"ኢቫንጋዲ" አልበም የተጣመሩት ሁለቱ ድምጻዊያውን ከ20 ዓመታት በኃላ የሙዚቃ ስራዎችን በአንድ መድረክ ሊያቀርቡ እንደሆነ አርትስ ስፔሻል ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ይህ የሙዚቃ ዝግጅትም ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም አመሻሽ ላይ በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል ተብሏል።

በሙዚቃው ዝግጅቱ ላይ ከጎሳዬ ተስፋዬ እና አለማየሁ ሂርጶ ባሻገር አንጋፋው ድምጻዊ ኤፍሬም ታምሩ እና ወጣቷ ድምጻዊት ሜላት ቀለመወርቅም ያቀነቅኗል።

ለዓመታት በኖርዌይ በስደት አስቸጋሪ ጊዜ ሲመራ ቆይቶ በቅርቡ ወደ ሃገር ቤት የተመለሰው  ድምፃዊ አለማየሁ ሄርጶ ከዓመታት በኃላ ወደ ሙዚቃ መመለሱን ይፋ ያደረገበት የሙዚቃ ሥራውን ከወራት በፊት ለአድማጮች ማድረሱ ይታወሳል።

ለተጨማሪው:https://www.tg-me.com/EventAddis1
📌የድምጻዊ አንዱዓለም ጎሳ የችሎት ሂደትን የሚዲያ ባለሙያዎች እንዳይታደሙ በፍርድ ቤት ታገዱ

ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ያስቻለው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በፍቅረኛው ወጣት ሞዴል ቀነኒ አዱኛ ህልፈት ተጠርጥሮ በምርመራ ሂደት ላይ የሚገኘው የአርቲስት አንዱዓለም ጎሳ ጉዳይ በታየበት ችሎት ነው ፍርድ ቤቱ መገናኛ ብዙሃን ችሎቱን እንዳይታደሙ ያገደው፡፡

በዛሬው ችሎት ፖሊስ የመገናኛ ብዙሃን በተለያዩ ጊዜያት “የችሎቱን ውሎ በተደጋጋሚ አዛብተው ዘግበውታል” በሚል የምርመራ ሂደቱ ላይ እክል በመፍጠራቸው በችሎቱ እንዳይታደሙ ጠይቋል፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ በችሎቱ የተጠየቁት የተከሳሽ ጠበቃ በፊናቸው ፖሊስ ያቀረበውን አቤቱታ እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡

ችሎቱም ግራ ቀኙን ካደመጠ በኋላ “መገናኛ ብዙሃን ካሁን በፊት አንድ ጊዜ ተከሳሽ ለፋሲካ በዓል ወጥቶ ኮንሰርት ለማዘጋጀት ጠይቋል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሟች የግል ማህደር (ዳይሪ) በተከሳሽ ጠበቃ እጅ ነው የሚገኘው የሚሉ የተዛቡና ሀሰተኛ ዘገባዎች ማቅረባቸው በችሎቱና በምርመራ ሂደቱ ላይ እክል እንደሚፈጥር በመታመኑ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች (ጋዜጠኞች) ችሎቱን እንዳይታደሙ” በሚል ብይን ሰጥቷል።

በዛሬው ችሎት በዚህ አይነት መልኩ ትክክለኛውን የችሎት ውሎ ከመዘገብ ይልቅ እውነትን አዛብተው የዘገቡ መገናኛ ብዙሃን የትኞቹ ናቸው የሚለው ሳይለይ፤ ችሎቱ ላይ የታደሙ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ለቀው እንዲወጡ በዳኛው በታዘዘው መሰረት የዶይቼ ቬለ ዘጋቢ እና የሌሎችም መገናኛ ብዙሃን ዘጋቢዎች በዚሁ ትዕዛዝ ከችሎቱ ለቀው ወጥተዋል ሲል ዶቼቬሌ ዘግቧል።

ለተጨማሪው:https://www.tg-me.com/EventAddis1
📌የፈረጃ ፊልም ቀረፃ ሚያዝያ 20 ይጀምራል

በህዝብ መዋጮ የሚሰራዉና በኢትዮጵያ የመጀመርያው (Crowdfunding) ፊልም የሆነው ፈረጃ የተሰኘዉ የቦክስ ፊልም ከብዙ ዝግጅትና አድካሚ ጉዞ በኋላ የታሰበዉ በጀት ባይሞላም ቀረፃዉ ሚያዝያ 20 ሊጀመር ነዉ።

አርቲስት ሄኖክ ወንድሙ ሂደቱ ከባድ እንደነበር ተናግሮ የቦክስ ፊልም እንደመሆኑ ለቀረፃዉ ብዙ ሰው እንደሚያስፈልግና በተሳትፎ እንዲያግዙት ወጣቱን ኃይል ጠይቋል።

በገንዘብና በሀሳብ ላገዙት ሰዎች በሙሉ ትልቅ ክብርና ምስጋናዉንም አቅርቧል።

ለተጨማሪው:https://www.tg-me.com/EventAddis1
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
"ሕይወት አጭር ናት" ያለው ሰለሞን ተካልኝ አረፈ

ከሳምንታት በፊት "ሕይወት አጭር" ሲል የተናገረው ሰለሞን ተካልኝ ዛሬ ማረፉ ተሰማ።

አነጋጋሪ እና አወዛጋቢ የፖለቲካ ዘፈኖችን በመስራት የሚታወቅው ሰለሞን ተካልኝ ከሳምንታት በፊት በፍሎረዳ ግዛት ክሊር ዋተር በተባለ ቢች ላይ ሆኖ በራሱ የቲክቶክ ገፅ ላይ ይሄን ቪዲዮ ለተከታዮቹ አጋርቶ ነበር በቪዲዮው ላይ "ሕይወት አጭር ናት" ሲል የተናገረው ሰለሞን ዛሬ ማረፉ ተሰምቷል።

ለተጨማሪው:https://www.tg-me.com/EventAddis1
📌ዛጎል የመጻሕፍት ባንክ ለዲላ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የመጻሕፍት ድጋፍ አደረገ

ዛጎል የመጻሕፍት ባንክ ለዲላ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አጠቃላይ ሆስፒታል  200 የሚደርሱ ልዩ ልዩ የህክምና መጻሕፍት ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉን የተረከቡት የዲላ ዩኒቨርሲቲ  ቤተ መጻሕፍትና ኢንፎርሜሽን ዳይሬክተር አስናቀ ሙልዬ(ዶ/ር)፣ በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት፤ ከዛጎል የመጻሕፍት ባንክ  ለዩኒቨርሲቲው የተበረከቱት መጻሕፍት በቁጥር  200 የሚደርሱ የህክምናና ልዩ ልዩ መጻሕፍት እንደሆኑ ገልጸው፤  እነዚህ መጻሕፍት በተለይ በዚህ ወቅት ተማሪውን ወደ ንባብ ለመመለስም ይሁን ላይብረሪውን በተሟላ ሁኔታ  ለማደራጀት አስተዋጽኦቸው  የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዶ/ር አስናቀ አያይዘውም፤ ይህ በመጻሕፍት ባንኩ የተደረገው ድጋፍ ለአሁኑ እንደ ጅምር ይታይ እንጂ በቀጣይ ከዛጎልም ይሁን ከሌሎች ተቋማት ጋር ግንኙነቶችን በማጠናከር ሌሎች ላይብረሪዎችንም የማደራጀቱ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ዛጎል የመጻሕፍት ባንክን ወክለው መጻሕፍቱን ያስረከቡት ወ/ሪት ፍፁም ማሩ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት ፤ ዛጎል የመጻሕፍት ባንክ ከ2013 ጀምሮ መጻሕፍትና አንባቢ ለማገናኘት የተቋቋመ የበጎ አድራጎት ድርጅት እንደሆነ አውስተው፣ድርጅቱ ይህን አላማውን ለማሳካት ከየግለሰቦችና ተቋማት መጻሕፍትን እያሰባሰበ እስካሁን ወደ 40 ሺህ የሚደርሱ መጻሕፍትን እንዳሰራጨ በመግለጽ  ለዲላ ዩኒቨርሲቲ 200 ልዩ ልዩ መጻሕፍትን እንዳስረከበ ተናግረዋል።

ወ/ሪት ፍፁም  አክለውም፥ በቀጣይም ይህንኑ ድጋፍ በሌሎች መስኮች ላይም አጠናክሮ ለማስቀጥል ከዩኒቨርሲቲው ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ ገልጸው ፤  በዩኒቨርሲቲው ለተደረገላቸው መልካም አቀባባል ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ለተጨማሪው:https://www.tg-me.com/EventAddis1
📌 "ደሸቆ" የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ በቃ

በደራሲ እመቤት ተሾመ ከበደ የተጻፈውና "ደሸቆ" የተሰኘ ርዕስ የተሰጠው አዲስ መጽሐፍ ዛሬ ሚያዝያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ለንባብ በቅቷል።

መጽሐፉ በ310 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን በ500 ብር የጀርባ ዋጋ ለአንባቢያን ቀርቧል።

"ደሸቆ" የካፊኛ ቃል ሲሆን የጭድ ጥጃ እንደማለት እንደሆነም ተገልጿል።

የመጽሐፉ ዋና አከፋፋይ ጃፋር የመጽሐፍ መደብር ነው።

ደራሲ እመቤት ተሾመ ከዚህ ቀደም "ምንሽሮ" በግሏ ከሌሎች ደራሲያን ጋር ደግሞ "የነፍስ እኩያሞች" የተሰኙ መጻሕፍትን ለንባብ አብቅታለች።

ለተጨማሪው:https://www.tg-me.com/EventAddis1
📌ስታር ዋይድ ሽልማት

"ምስጋናን ባህላችን እናድርግ" በሚል መሪ ቃል ለ2ኛው ዙር የተዘጋጀው ስታር ዋይድ ሽልማት የፊታችን ግንቦት ወር ላይ ይካሄዳል ተብሏል።

ሽልማቱ በተለያዩ የስራ መስኮች በግልም ይሁን በተቋም ደረጃ ለሀገር መልካም ሰርተው ያለፉትን ለማስታወስ፣እየሰሩ ያሉትን ለማበረታታት ዓላማው ያደረገ ነው።

ዘንድሮም በንግድ፣ በስራ ፈጠራ፣ በጠቅላላ ኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በኮንስትራክሽን፣ በባንክ፣ በትምህርት፣ በህዝብ አገልጋይነት፣ በሆቴልና ቱሪዝም ፣ ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ በመጠቀም፣ በእድሜ ዘመንና በሌሎችም በርካታ ዘርፎች ከአገር መሪዎች እስከ ትልልቅ ኩባንያዎች እውቅና ይሰጣችኋል።

ተሸላሚዎችን ለመምረጥ ከልዩ ልዩ መስኮች ዳኞች እንደተዘጋጁም አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።

በከለር ፉል ኤቨንት ኦርጋናይዘር የተዘጋጀው ሽልማቱ ዘንድሮ 19 ዘርፎች ያሉት ሲሆን ሁሉም ተሸላሚዎች በግንቦት ወር በሚካሄደው የሽልማት ሥነሥርዓት ላይ ይታወቃሉ ተብሏል።

ለተጨማሪው:https://www.tg-me.com/EventAddis1
📌ዛሬ ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቀን ነው!

የዓለም መጽሐፍ ቀን በየዓመቱ ሚያዝያ 15 ይከበራል

ሚያዝያ 15 ለዓለምአቀፍ የመጽሐፍ ቀንነት የተመረጠበት ምክንያት የዊልያም ሼክስፒር እና ስፔናዊው የታሪክ ጸሐፊ ኢንካ ጋርሲላሶ ዴ ላ ቬጋ የሞቱበት ቀን በመሆኑ እንደመታሰቢያ እንዲሆን ነው።

በእዚህ ቀን በዓለምአቀፍ ደረጃ በተለይ ወላጆች ለልጆቻቸው መጻሕፍትን በስጦታ መልክ በመስጠት ያከብሩታል።

የቀኑም ትልቁ ዓላማ የንባብ በዓል ማዳበረ ነው።

#Worldbookday!

ለተጨማሪው:https://www.tg-me.com/EventAddis1
📌 የሪፖርተር ጋዜጠኛ ታሰረ

የሪፖርተር ጋዜጣ ዘጋቢ ጋዜጠኛ አበበ ፍቅር ታሰረ፡፡ ጋዜጠኛ አበበ የታሰረው ትናንት ሚያዚያ 15 ቀን 2017 ዓ.ም. ምሽት አካባቢ ነው፡፡

ጋዜጠኛው ለእስር የተዳረገው ከልደታ ክፍለ ከተማ ኃላፊዎች መረጃ በማሰባሰብ ላይ እያለ ሲሆን፣ የታሰረበት ምክንያት እስካሁን ግልጽ አልሆነም፡፡ ጋዜጠኛ አበበ በዕለቱ በፖሊሶች ተይዞ ከመወሰዱ በስተቀር በወቅቱ ወዴት እንደተወሰደና እንደታሰረ ባለመታወቁ፣ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሪፖርት በማድረግ የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ባደረገው ትብብር ጋዜጠኛው በልደታ ክፍል ከተማ ፖሊስ መምሪያ ጌጃ ሰፈር አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ መታሰሩ ታውቋል፡፡

ጋዜጠኛው ለእስር የተዳረገው እየሠራው ለነበረው ዘገባ ሚዛኑን ለመጠበቅ፣ የክፍለ ከተማውን ኃላፊዎች ለማነጋገር በሥፍራው በተገኘበት ወቅት ነበር፡፡

ዘገባው የሪፖርተር ጋዜጣ ነው።

ለተጨማሪው:https://www.tg-me.com/EventAddis1
📌"ነገረ መጻሕፍት" ውይይት ነገ ይካሄዳል

የነገረ መጻሕፍት አዘጋጆችና ታደሚያን ቅዳሜ "ቀይ ባህር ሲቀላ " በተሰኘ መጽሐፍ ላይ ይወያያሉ።በዛጎል የመጻህፍት ባንክ የሚዘጋጀው "ነገረ መጻሕፍት" የመጻህፍት ውይይት ነገ ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ጀምሮ ምኒልክ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኘው "FSS" አዳራሽ ውስጥ ይካሄዳል።በዚህ ሳምንት የተመረጠው መጽሐፍ "ቀይ ባህር ሲቀላ " የተሰኘ መጽሐፍ ሲሆን በክብር እንግዳነት የመጸሐፉ ፀሐፊ ዶ/ር ፍርድአወቀ ማሞ ይገኛሉ ተብሏል። የፕሮግራሙ አዘጋጅና አቅራቢ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ነው።

ለተጨማሪው:https://www.tg-me.com/EventAddis1
📌"ህልም እልም" የሥዕል አውደርዕይ ሰኞ ይከፈታል

የሠዓሊ ስዩም አያሌው የሥዕል ስራዎች የሚቀረቡበት "ህልም እልም " የሥዕል አውደርዕይ የፊታችን ሰኞ ሚያዝያ 20 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሐያት ሪጀንሲ ውስጥ በሚገኘው ፈንድቃ የባህል ማዕከል ውስጥ ለእይታ ይበቃል። ይህ የሥዕል አወድርዕይ እስከ ግንቦት 4  2017 ዓ.ም ድረስ ይቆያል ተብሏል።

ለተጨማሪው:https://www.tg-me.com/EventAddis1
📌አድማስ የሙዚቃ ባንድ ከአርባ አንድ ዓመት በኋላ ወደ መድረክ ላይ ሊወጣ እንደሆነ ተገለፀ

የፊታችን ሚያዚያ 25 እና 26 2017 ዓ.ም በሚከበረው የኢትዮጵያ የጃዝ ፌስቲቫል ላይ ከ41 ዓመታት በኋላ አበጋዝ ክብረወርቅን፣ ሔኖክ ተመስገን፣ ቴድሮስ አክሊሉን እና ግሩም መዝሙርን ያቀፈው አድማስ ባንድ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራዎቹን ያቀርባል፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፣ አ.አ ባህል ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ እና ሳይ ሪኮርድስ በጋራ የሚያዘጋጁት ሁለተኛው የዓለም የሥነጥበብ ቀን እና የኢትዮጵያ ጃዝ ፌስቲቫል ከሚያዚያ 21 2017 ጀምሮ ከአለ ሥነጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት የተሰባሰቡ የቆዩ ሥዕሎችና ከሠዓሊያን ማኅበር የተገኙ የዘመኑ ስዕሎች ተዋኅደው የሚታዩበት አውደርዕይ የሚከፈት ሲሆን የፊታችን ቅዳሜና እሁድ ሚያዚያ 25 እና 26 ከ7፡00 ጀምሮ ደግሞ የሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገር የሚመጡ የጃዝ ሙዚቀኞች ሥራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ አዘጋጆቹ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ለሁለተኛ ጊዜ በሚዘጋጀው ታላቅ ዝግጅት ላይ ከአድማስ ባንድ በተጨማሪ ነጋሪት ባንድ፣ አስሊ ባንድ፣ መሐሪ ብራዘርስ ባንድ፣ ሳሙኤል ይርጋ እና ሌሎች ከሀገር ውስጥ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን ዘሯ ከኢትዮጵያ የሚመዘዘው ትውልደ እስራኤላዊት ሔዋን መሸሻ እና ዚምባቡዌያዊቷ ናሲቦ ሙቲዚ (ናንሲ) መድረኩን ያስውቡታል፡፡

ከሚያዚያ 21 2017 ጀምሮ ለሳምንታት ለዕይታ የሚቀርበውን የሥዕል ትርኢት በሥራ ሰዓት እና ቅዳሜ ለሁሉም ሰው ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን ታዳጊ ህጻናት ራሳቸውን ከሥነጥበብ ጋር የሚያቆራኙበት መርሐግብርም የፌስቲቫሉ አካል እንደሆነ ተገልጿል፡፡
 
በዝግጅ ላይ ለመታደም ትኬቱ ቴሌ ብር ላይ የሚገኝ በርካታ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ይታደሙበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ለተጨማሪው:https://www.tg-me.com/EventAddis1
📌የአርብ ምሽቱ አርትስ ስፔሻል በትኩሱ ደርሷል !!

በዚህ ሳምንት እነዚህን ጉዳዮች ታገኛላችሁ

የአርትስ ስፔሻል መረጃዎች ዋና ዋና ጉዳዮች:

1.ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) በእስራኤል የነፃነት ቀን በቴሌቪብ የሙዚቃ ኮንሰርቱን እንደሚያቀርብ ይፋ ካደረገ በኃላ ተቃዋሞ እና ድጋፍ ገጠመው።

2.የአዲስ አበባው የጣይቱ የባህልና ትምህርት ማዕከል ነገ በድማቅ ሥነሥርዓት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ሊጀምር ነው።

3.የዝነኛዋ ፎቶግራፍ አይደ ሙሉነህ የፎቶግራፍ አውደርዕይ በይፋ ተከፈተ።

4."በይው ተቀየረ እንጂ ትሪው አልተነሳም" የተሰኘ የሥዕል አውደርዕይ ነገ ይከፈታል።

እነዚህንና ሌሎችንም የአርትስ ስፔሻል የኪነት እና ኩነት መረጃዎች እናቀርብላችኋለን።

"አርትስ ስፔሻል"ዝግጅታችንን ይመለከቱ:
https://youtu.be/wLacEyqFBHY?si=J5xScqMLoLe-9xnF

📌መልካም ምሽት

ለተጨማሪው: https://www.tg-me.com/EventAddis1
📌የ50 ሚሊዮን ብር ሎተሪ በአዲስ አበባ ኮንሰርቶች

የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት በሀገሪቱ ውስጥ የመዝናኛ እና የዕድል ፍላጎትን ለማጣጣም በሚያስችል አዲስ እና ትኩረት የሚስብ አካሄድ ከታምኮን ሶፍትዌር ሶሉሽን ጋር በመተባበር በነገው እለት በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄዱ ሶስት ታዋቂ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን ተከትሎ  የፊታችን ግንቦት ወር የሚወጣውን 50 ሚሊዮን ሎተሪ እንደሚያስተዋውቅ ገለጸ።

በሙዚቃ ኮንሰርት ታዳሚዎች  በመዝናናታቸው ጎን ለጎን የ50 ሚሊዮን ብር ግዙፍ ሎተሪ የመቁረጥ ዕድል ይኖራቸዋል ተብሏል።

ዛሬ በሚደረጉ ሶስቱም ኮንሰርቶች ላይ ለሚሳተፋ በነፃ ለሚመዘገቡ ባለዕድለኞች የ50,000 (የሃምሳ ሺህ ብር) ሽልማትም ቀርቧል።

ይህ ልዩ ዕድል ሽልማት ዛሬ በሚካሄዱት በሚሊኒየም አዳራሽ ሽርጉድ ኮንሰርት ፣ በግዮን ሆቴል  ልዑል ኮንሰርት እና በማርዮት ሆቴል በሚካሄደው  ኤሌጋንስ ኮንሰርቶች ላይ የሚሳተፉትን ተሳታፊዎች ሎተሪ በመቁረጥ በEthiolottery.et ድረ ገጽ ላይ በመመዝገብ በቀላሉ እድለኛ እንዲሆኑ የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት አሳውቋል።

ለተጨማሪው: https://www.tg-me.com/EventAddis1
📌"በይው ተቀየረ እንጂ ትሪው አልተነሳም"

የሠዓሊ አሸናፊ መስቲካ የሥዕል ስራዎች የቀረቡበት "በይው ተቀየረ እንጂ ትሪው አልተነሳም" የተሰኘ የሥዕል አውደርዕይ ባሳፍነው ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም ቦሌ ብራስ አካባቢ በሚገኘው አርታዊ የሥዕል ማሳያ ውስጥ ለእይታ በቅቷል።

ይህ የሥዕል አውደርዕይ እስከ ግንቦት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ድርስ እንደሚቆይ አዘጋጆቹ ተናግረዋል።

ለተጨማሪው: https://www.tg-me.com/EventAddis1
📌የአይዳ ሙሉነህ የፎቶግራፍ ዓውደርዕይ

በአይዳ ሙሉነህ ተዘጋጅቶ በ ዘ-ኢንድ ፈንድ አዘጋጅነት እና በሪቺንግ ዘ-ላስት ማይል ድጋፍ ለህዝብ የቀረበው ሪፍሬሚንግ ኔግሌክት የተሰኘ የፎቶ ዓውደ-ርዕይ ተከፈተ፡፡

በዓውደ-ርዕዩ አይዳ ሙሉነህን ጨምሮ የሰባት አፍሪካዊ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ስራ ስብስብ የቀረበ ሲሆን በዋነኝነትም ደሀ ከሚባሉ አገራት ውስጥ ከሚከሰቱ በሽታዎች ያላቸውን ማህበራዊ እና ኢኮሚያዊ ጫና ለተመልካች ለማቅረብና የአፍሪካዊያንን ድምፅ ለአለም ለማሰማት የተዘጋጀ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በስራዎቻቸው ጠንካራ ታሪክን በፎቶ የማስቀረት እና ማህረሰቡ የሚያልፍበትን እውነታ የማንፀባረቅ ድንቅ ችሎታ ያላቸው የስድስት አፍሪካዊ ባለሙያዎች 54 የስነጥበብ ስራዎችና ዘጋቢ‐ፎቶዎች የተካተተበት ዓውደ-ርዕይ ስነ-ጥበብ ምን ያህል ወሳኝ ጉዳዮችን የማጉላት ትልቅ አቅም እንዳለው ያሳያሉ ተብሏል፡፡

እ.ኤ.አ በ2022 ተጀምሮ በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ እና በአፍሪካ 2.8 ሚሊዮን ሰዎችን ተደራሽ ያደረገው ይሄው ዓውደ-ርዕይ በታላቅ ክብረበአል ሚያዚያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 12 ሰአት ጀምሮ እስከ ግንቦት 19 2017ዓ.ም በገብረክርስቶስ ደስታ ማዕከል ለተመልካች ክፍት ይሆናል፡፡

ለተጨማሪው: https://www.tg-me.com/EventAddis1
📌ቴዲ አፍሮ በስምንት ሙዚቃዎች ላይ በግጥምና ዜማ የተሳተፈበት የአንጋፋዋ ድምጻዊት ኩኩ ሰብስቤ "ደጃዝማች" የተሰኘ የሙዚቃ አልበም የፊታችን አርብ ይለቀቃል

ይህ የአንጋፋዋ ድምፃዊት ኩኩ ሰብስቤ "ደጃዝማች" የተሰኘ ስምንተኛ አዲስ የሙዚቃ አልበም ላይ አስራ ሶስት ሙዚቃዎችን ይዟል።

ከእነዚህ አስራ ሶስት ሙዚቃዎች ውስጥ የስምንቱ ሙዚቃዎች ግጥምና ዜማ የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ / ሲሆን ሌሎቹን ሙዚቃዎች ደግሞ በግጥም ገጣሚ ይልማ ገብረአብ፣ገጣሚ መሰለ አስማማው፣ ገጣሚ ናትናኤል ግርማቸው የሰሩ ሲሆኑ ሞገስ ተካ እና ምስክር አወል ግጥምና ዜማ በመስራት በአልበሙ ላይ ተሳትፈዋል።

ከተቀሩት ስራዎች ውስጥ "ወለላዬ" የተሰኘው ሙዚቃ ደግሞ የኩኩ የድሮ ሙዚቃ ሲሆን ቴዲ ማክ እንደገና ሪአሬንጅ /Re Arrange/ አድርጎ የሰራው ሙዚቃ ነው።

የድምፃዊት ኩኩ ሰብስቤ " ደጃዝማች" በተሰኘው አዲስ አልበም ላይ ስመጥር የሆነ የሙዚቃ ባለሞያዎች የተሳተፉበት ሲሆን የሙዚቃ አቀናባሪው አቤል ጳውሎስ ዘጠኙን ሙዚቃዎች በማቀናበር እንዲሁም አስራ አንዱን ሙዚቃዎች ሚክስ በማድረግ ተሳትፏል።

ሁለቱን ሙዚቃዎች አሬንጅ ያደረገው ማሩ ዓለማየሁ ሲሆን ሙዚቀኛ ያሬድ ተፈራ፣ ሙዚቀኛ አክሊሉ ወ/ዩሐንስ (ጆኒ ሳክስ) እና ሙዚቀኛ ዘሪሁን በለጠ በሳክስፎን፣ግሩም መዝሙር እና ሳሙኤል አሰፋ በጊታር ተሳትፈዋል።

"ደጃዝማች"ን ሙሉውን አልበም ማስተር ሳውንዱን /Sound Mastering/የሰራው ኪሩቤል ተስፋዬ ነው።

"ደጃዝማች" የተሰኘ ስምንተኛ አልበም የፊታችን አርብ ሚያዚያ 24 ቀን 2017 ዓ.ም በራሷ ዩቲዩብ ቻናል ይለቀቃል።

ለተጨማሪው: https://www.tg-me.com/EventAddis1
📌ድምጻዊ ልዑል ሲሳይ በፕሪስቴጅ አዲስ ዝግጅት ላይ እንግዳ በመሆን ይቀርባል

(መግቢያው በነፃ ነው)

የተለያዩ የጥበብ ባለሞያዎችን እየጋበዝ ልምዶቻቸውን እንዲያጋሩ እያደረገ ያለው ፕሪስቴጅ አዲስ መርሐግብር ልዑል ሲሳይን ጋብዟል::

የፕሪስቴጅ አዲስ አዘጋጆች"ከልዑል ጋር በሚኖረን ቆይታ የሥራ፣ የህይወት ልምድ እና ተሞክሮውን የሚያካፍለን ሲሆን ከእናንተ ከወዳጅ እና አድናቂዎቹ የሚቀርቡለትን ጥያቄዎች ደግሞ የፊታችን  ማክሰኞ ሚያዚያ 28, 2017 ዓ.ም መልስ ለመስጠት ቀጠሮ ይዘናል" ሲሉ ለኤቨንት አዲስ ሚዲያ ገለጸዋል።

በዕለቱ ከድምጻዊ ልዑል ሲሳይ ጋር የፎቶግራፍ መነሳትና አውቶግራፍ የማስፈረም መርሃግብር ይኖራል ተብሏል::

ፕሪስቴጅ አዲስ ከልዑል ሲሳይ ጋር  የሚያደረገው አዝናኝ እና አስተማሪ ቆይታ  ማክሰኞ ሚያዝያ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ጀምሮ አሜሪካን ኢምባሲ ቅጥር ግቢ ውስጥ ( ከስድስት ኪሎ ወደ ሽሮሜዳ መሄጃ ) ይካሄዳል።በዝግጅቱ ላይ ለመታደም ከታች ያለውን ሊንክ በመንካት ይመዝገቡ:

📎 በ ዝግጅቱ ላይ ለመታደም ከታች ያለውን ሊንክ በመንካት ይመዝገቡ ፡፡👇🖱

 https://jazzio.land/register

መታወቂያ መያዝ እንዳይረሳ፣ማርፈድ ወደ ውስጥ እንዳትገቡ ያደርጋል ፕሮግራሙ ከመጀመሩ ቀደም ብላችሁ ለመገኘት ሞክሩም ተብላችኋል።

ለተጨማሪው:https://www.tg-me.com/EventAddis1
2025/07/07 15:24:07
Back to Top
HTML Embed Code: