Telegram Web Link
Hule Addis Media ( ሁሌ አዲስ ሚዲያ)
Photo
“አደባባይ የወጣሁት ሕዝቤ እንዲደርስልኝ ነው”:- አትሌት ገለቴ ቡርቃ
******

በኢቲቪ ኦፋን ኦሮሞ ቴሌቪዥን ከሚቀርበው "ገመዳ ሾው" ጋር ቆይታ ያደረገችው አትሌት ገለቴ ቡርቃ "አደባባይ የወጣሁት ሕዝቤ ያለሁበትን አስቸጋሪ ሁኔታ አውቆ እንዲደርስልኝ ነው" ብላለች፡፡

ከ800 እስከ ማራቶን ኢትዮጵያን ወክላ በተለያዩ መድረኮች የተወዳደረችው አትሌት ገለቴ ሳላውቅ ትዳሬ እየፈረሰ ነውም ብላለች፡፡

"በሩጫ ባገኘሁት ገንዘብ ወደ ኢንቨስትመንት ልገባ ስል ችግር አጋጥሞኛል" የምትለው አትሌቷ.፣ ባለቤቷ በ2009 ዓ.ም ከቤት ጠፍቶ ስምንት ወር ከቆየ በኋላ ፍርድ ቤት እንዳቀረባት እና እስካሁን ክርክር ላይ እንዳሉ ተናግራለች፡፡

ዘጠኝ ዓመታት አብራ የቆየችው ባለቤቷ በ2009 ዓ.ም ለውድድር ከሀገር ውጭ ስትሄድ ከሸኛት በኋላ ውድድሯን ጨርሳ ስትመለስ ባዶ ቤት እንዳገኘች ገልጻለች፡፡

ፍለጋውን ጀምራ ለፖሊስ ስታስታውቅ "ደውሎ ለምን ስሜን ታጠፊያለሽ? አርፈሽ የማትቀመጪ ከሆነ እገድልሻለሁ" እንዳላት የተናገረችው ገለቴ በ2010 ዓ.ም በእርሱ በኩል የክስ መጥሪያ እንደደረሳት ጠቅሳለች፡፡

ፍርድ ቤት ስትቀርብም ባለቤቷ ጋብቻቸው እንዲፈርስ እንደጠየቀ እሷ ደግሞ የተጋቡት በእምነት ተቋም እንደሆነ እና እምነት ደግሞ ጋብቻ እንዲፈርስ እንደማይፈቅድ ጠቅሳ አላፈርስም እንዳለች ነገር ግን በጫና ጋብቻው እንደፈረሰ ትናገራለች፡፡

"ከዚያ ቀደም የወሰደውን ውክልና ተጠቅሞ ያለውን ንብረቴን ሸጦ ስለነበረ ጋብቻው ከፈረሰ በኋላ ንብረቴን ለማሳገድ ብንቀሳቀስም ከአንድ ቤት በስተቀር ሁሉም ስማቸው ዞሮ ነበር ያገኘሁት" ብላለች አትሌት ገለቴ፡፡

አንዷ የቀረችው ቤትም በ2008 ዓ.ም ውክልናው የተነሳባት ቤት እንደሆነ የጠቀሰችው አትሌቷ፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አሥር ቤቶች፣ አራት መኪና እና ሌሎች በርካት ንብረቶችን ተሸጠውባት ባዶ እጇን መቅረቷን ተናግራለች፡፡

"እናቱ እንዲኖሩበት የሰጠሁትን መንግሥት የሰጠኝን ቤት እንኳን ለእናቱ ሸጧል" የምትለው ገለቴ፣ "ከጋብቻ በፊት ያፈራሁት ንብረቴም ሳይመለስ፣ ከጋብቻ በኋላ ያፈራነውንም ሳልካፈል አንዷን የቀረችውን ቤት ለመካፈል ፍርድ ቤት ወስኖብኛል" ስትል ተናግራለች፡፡

እሱ ቀድሞ ሁሉንም አቅዶበት ስለሄደበት ያላትን አቅም ሁሉ ተጠቅማ ፍርድ ቤት ብትከራከርም ውሳኔው ግን ከሷ በተቃራኒ እንደሆነ ተናግራለች፡፡

ከዚህ አልፎም እንደሚያስፋራራት ለፖሊስ ማልከቷን ጠቅሳ፣ ንብረቱም እንዳይገኝ አንድም ገንዘቡን በሱ ስም እንደማያስቀምጥ እንዲሁም ተሸጡ የተባሉ ንብረቶችም ከዋጋቸው እጅግ ባነሰ የተሸጡ መሆናቸው ጉዳዩን ውስብስብ እንዳደረገው ተናግራለች፡፡

ይህን ጉዳይ የማያውቀው የመንግሥት አካል እንደሌለ የጠቀሰችው አትሌት ገለቴ፣ "እስካሁን መፍትሄ ካለማግኘቴም በላይ ወደ ጎዳና ለመውጣት ከዚያም አልፎ ለሕይወቴ አስጊ ሁኔታ ላይ ስለምገኝ የሚመለከተው አካል ይድረስልኝ" ትላለች፡፡

"አደባባይ የወጣሁት ሕዝቤ እንዲደርስልኝ ነው" ያለችው ገለቴ፣ "ወጥቼ የምወደውን ስፖርት እንኳን እንዳልሠራ ማስፋራራት እየደረሰብኝ ቤት ውስጥ ተዘግቼ ተቀምጫለሁ፤ የአቅሜን ያበረከትኩላት ሀገሬ እና ሕዝብ ያለሁበትን ሁኔታ ይወቅልኝ" ብላለች፡፡

በለሚ ታደሰ ( EBC)
“አሜሪካ ብትሳተፍም ባትሳተፍም፣ እስራኤል የኢራንን የኒውክሌር ተቋማት በሙሉ የማጥፋት አቅም አላት”

- ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ እንደተናገሩት፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቢሳተፉም ባይሳተፉም፣ እስራኤል የኢራንን የኒውክሌር ተቋማት በሙሉ የማጥፋት አቅም አላት።

ኔታንያሁ ይህንን የተናገሩት ዋይት ሃውስ ትራምፕ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ጣልቃ መግባት አለመግባታቸውን ይወስናሉ ከማለቱ በፊት ነው።

የወታደራዊ ጉዳይ ተንታኞች፣ እስራኤል የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ዋነኛ ክፍል የሆነውን ፎርዶው የነዳጅ ማበልጸጊያ ፋብሪካን ለማጥፋት የአሜሪካ እገዛ ሊያስፈልጋት ይችላል ብለው ያምናሉ።

"በሁሉም ኢላማዎቻችንን፣ ሁሉንም የኒውክሌር ተቋሞቻቸውን የማስወገድ አቅም አለን ያሉት ኔታንያሁ፤ ነገር ግን ፕሬዚዳንቱ ለመቀላቀል ይፈልጉ እንደሆነ ወይም እንደማይፈልጉ የሚወስኑት እርሳቸው ናቸው ብለዋል።"

ኔታንያሁ አክለውም እርሱ (ትራምፕ) ለአሜሪካ የሚበጀውን ያደርጋል፣ እኔም ለእስራኤል መንግስት የሚበጀውን አደርጋለሁ ሲሉ ተደምጠዋል።
የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ከዛሬ ጀምሮ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ሆነ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሀገሪቱን የባንክ ዘርፍ ለውጭ ተሳትፎ ክፍት የሚያደርግ አዲስ መመሪያን ዛሬ ይፋ አድርጓል። ይህ እርምጃ የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ለማድረግ ሲደረግ የቆየው ጥረት የመጨረሻው ምዕራፍ ተደርጎ እንደሚወሰዱ ተገልጿል።

መመሪያ ቁጥር SBB/94/2025 ባለፉት አንድ ዓመት በተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተደረጉ ሰፊ ውይይቶች እና ምክክሮች ግብዓት ተደርጎበት የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል።

ይህ መመሪያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፀደቀው የባንክ ሥራ አዋጅ መሰረት የወጣ ሲሆን፣ የሚያስፈልገውን የሕግ ማዕቀፍ ማሟላቱ ተገልጿል።

ይህ አዲሱ የፈቃድ አሰጣጥ መመሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ የውጭ ባለሀብቶች፣ ባንኮችን እና ሌሎች ስትራቴጂካዊ ባለሀብቶችን ጨምሮ፣ በኢትዮጵያ የባንክ ሥርዓት ውስጥ እንዲሳተፉ ያስችላል ተብሏል።

ብሔራዊ ባንክ ዛሬ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣዉ መግለጫ መመሪያው የውጭ ተዋናዮች የባንክ ዘርፉን እንዲቀላቀሉባቸው በርካታ መንገዶችን ያቀርባል፤ ከእነዚህም መካከል ቅርንጫፍ ባንኮችን፣ የውጭ ባንክ ቅርንጫፎችን ወይም የወኪል ቢሮዎችን ማቋቋም ይገኙበታል።

ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሀገሪቱን የባንክ ዘርፍ ለውጭ ተሳትፎ ክፍት መሆኑን የገለፀ ሲሆን የውጭ ባንኮች እና ባለሀብቶችም ማመልከቻዎቻቸውን ከዛሬ ጀምሮ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ እንደሚችሉ አስታውቋል።

Via Capital Newspaper
በቀጣይ አመት ማስተማር የማይችሉ ት/ቤቶች

በ2018 የትምህርት ዘመን ማስተማር የማይችሉ የትምህርት ተቋማትን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ይፋ አድርጓል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን በ2018 የትምህርት ዘመን ማስተማር የማይችሉና እውቅናቸው የተሰረዘ ትምህርት ቤቶችን አሳውቋል።

በ2016 ዓ.ም ማጠቃለያ ላይ በተደረገው የእድሳት ፍቃድ ምዘና ለ2017 የትምህርት ዘመን ካሳዩት ዝቅተኛ ውጤት መሻሻል እንዲያሳዩ እስከ 2017 ዓ.ም ታህሳስ ድረስ ዝግጅት እንዲያደርጉ ፤ በ2017 የትምህርት ዘመን ላይ በማስጠንቀቂያ እንዲያስተምሩ ጊዜ ቢሰጣቸውም በታህሳስ 2017 በተደረገ የእድሳት ፍቃድ ምዘና ውጤታቸው መሻሻል ባለማሳየቱና ዝቅተኛና ከደረጃ በታች በመሆኑ ምክንያት በ2018 የት/ት ዘመን ማስተማር የማይችሉ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን አሳውቋል።

በመሆኑም የትምህርት ማህበረሰቡ እና ወላጆች ይህን በማወቅ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እንድታከናውኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር አሳውቋል።
በታጣቂዎች ጥቃት 16 አሽከርካሪዎች መገደላቸው ተነገረ

"ተሳፋሪዎችና አሽከርካሪዎች ታፍነው ተወስደዋል"

በአማራ ክልል በጎንደር መተማ መንገድ ላይ "መቃ" በተባለች ሥፍራ ታጣቂዎች ሰኞ'ለት በፈጸሙት ጥቃት 16 አሽከርካሪዎች ተገድለው፣ በርካቶች መቁሰላቸውን ዋዜማ ምንጮችን ጠቅሳ ዘግባለች፡፡

በታጣቂዎቹ ከተገደሉት ሾፌሮች በተጨማሪ ተሳፋሪዎችና በርካታ አሽከርካሪዎች ታፍነው መወሰዳቸውን ምንጮች ተናግረዋል።

አብዛኞቹ አሽከርካሪዎች የተገደሉት፣ ከጥቃቱ ለማምለጥ ጥረት በማድረግ ላይ ሳሉ በእሩምታ ተኩስ እንደኾነ ዘገባው አመልክቷል፡፡

ዋዜማ የጥቃቱን ፈጻሚ ታጣቂዎች ማንነት ለጊዜው ባታረጋግጥም፣ የፋኖ ታጣቂዎች ሰሞኑን በመተማ ወረዳ ከቅማንት ብሄረሰብ ታጣቂዎች ጋር የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውን ግን ምንጮች መናገራቸውን ጠቁማለች፡፡
አሜሪካ በኢራን ላይ የፈጸመችው ጥቃት የኒውክሌር ማብላያ ይዞታዎችን እንዳላወደመ የአሜሪካ መከላከያ ማዕከል (ፔንታጎን) የደህንነት ግምገማ አሳየ።

ቅድመ ግምገማው፤ ጥቃቱ የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር ምናልባትም በወራት ወደ ኋላ ሊመልሰው እንደሚችል ነው ያሳየው።

ኢራን ያበለጸገችው የዩራኒየም ክምችት አሜሪካ ቅዳሜ፣ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም በፈጸመችው ጥቃት አለመውደሙን የአገሪቱ የመከላከያ ደህንነት ኤጀንሲ ግምገማን የሚያውቁ ምንጮች ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ተናግረዋል።

ዋይት ሃውስ በበኩሉ፤ "ይህ ፍጹም የተሳሳተ ግምገማ" በማይረባ የደህንንት ማህበረሰብ ሾልኮ የወጣ ነው" ሲል ውድቅ አድርጎታል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው፤ የኢራን የኒውክሌር ይዞታዎች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል በማለት በድጋሚ አጽንኦት ሰጥተው፤ "በታሪክ ውስጥ ስኬታማ ከሆኑ ወታደራዊ ጥቃቶች መካከል አንዱ የሆነውን ለማዋረድ", በሚዲያዎች የሚደረግ ሙከራ ሲሉ ከሰዋል።

ነገር ግን የፔንታጎን የደህንነት ግምገማን የሚያውቁ ምንጮች በበኩላቸው፤ የኢራን ማብላያዎች በአብዛኛው እንዳልተነኩና የጥቃቱ ተጽእኖ ከመሬት በላይ ባለው ብቻ የተወሰነ ነው ይላሉ።

የሁለቱ ኒውክሌር ይዞታዎች መግቢያዎች ተዘግተው እንደነበር የጠቀሰው ግምገማው፣ አንዳንድ መሰረተ ልማቶች ቢወድሙም ወይም ቢጎዱም፤ ከመሬት ስር ያሉት አብዛኛዎቹ ይዞታዎች ግን ከፍንዳታው ቃጠሎ አምልጠዋል ብሏል።

እኚህ ማንነታቸው ያልተገለጹ ምንጮች ለአሜሪካ ሚዲያ እንደተናገሩት፤ ጥቃቱ የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር በወራት ወደ ኋላ ሊመልሰው እንደሚችል መገመቱን ገልጸዋል።

የኢራን የመንግሥታዊ ሚዲያ ምክትል የፖለቲካ ዳይሬክተር ሃሰን አብደኒ በበኩላቸው፤ አሜሪካ ጥቃት ያደረሰችባቸው ሶስቱ የኒውክሌር ይዞታዎች፣ ከጥቃቱ ቀድሞ ክምችታቸው እንዲዛወር መደረጉን ተናግረዋል።

(ቢቢሲ)
በእስራኤል ጥቃት ተገደሉ የተባሉ 3 የጦር መሪዎች የኢራን የድል በዓል ላይ ተገኙ

በእስራኤል ጥቃት ተገደሉ የተባሉ 3 የኢራን ጦር መሪዎች የኢራን የድል በዓልን ከሕዝብ ጋር ሲያከብሩ መታየታቸውን አናዶሉ እና የኢራን የሀገር ውስጥ ብዙኃን መገናኛዎች ዘግበዋል።

እስራኤል ከሰኔ 13 ጀምሮ የኢራን የጦር ጀኔራሎችን መግደሏን ያስታወቀች ሲሆን፤ ሦስቱ የኢራን የጦር መሪዎች በትናንትናው ዕለት ኢራን የድል በዓሏን ስታከብር ከህዝቡ ጋር በመገኘት አክብረዋል ብለዋል ምንጮቹ።

ከዚህ ውስጥ አንዱ የሆኑት የእስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ኮርፕስ ቁድስ ኃይል አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ኢስማኢል ቃኣኒ በዓሉን ከሕብ ጋር ማክበራቸውን የኢራቅ የሀገር ውስጥ ብዙኃን መገናኛዎች ዘግበዋል።

በኢራን ታስኒም የዜና አገልግሎት የተለጠፈ ቪዲዮ ቃአኒ በዝግጅቱ ላይ ከተሰበሰቡት መካከል አሳይቷል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ቃአኒ በእስራኤል ጥቃት ከተገደሉት የኢራን ጦር መሪዎች መካከል አንዱ እንደሆኑ ዘግቦ እንደነበር የሚታወስ ነው።

በተመሳሳይ የወቅቱ የመከላከያ ሚኒስትር እና የአየር ኃይል አዛዥ የነበሩ ብርጋዴር ጄኔራል አዚዝ ናስርዛዴህ በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ በመከላከያ ሚኒስቴር ላይ በተፈፀመ የአየር ጥቃት ተገድለዋል ተብለው የነበረ ቢሆንም በሕይወት እንዳሉ እና አሁንም በስልጣን ላይ እንደሚገኙ ተስኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።

የአያቶላህ አሊ ኻሚኒ ከፍተኛ አማካሪ እና የደህንነት ዋና አማካሪ አድሚራል አሊ ሻምካኒ እ.ኤ.አ ሰኔ 13 ቀን 2025 በእስራኤል የአየር ጥቃት መሞታቸው ከተነገሩት አንዱ የነበሩ ናቸው። አድሚራል አሊ ሻምካኒ በድል በዓሉ ላይ በመገኘት የድል በዓሉን አክብረዋል ሲሉ የኢራን የዜና ወኪሎች ዘግበዋል።
ኢራን ጦርነቱን እንድታቆም ከአሜሪካ የ30 ቢሊየን ዶላር ጉርሻ ቀርቦላታል ተባለ

ኢራን ጦርነቱን እንድታቆም እና ወደ ድርድር እንድትመጣ አሜሪካ የ30 ቢሊዮን ዶላር ጉርሻ እና ማዕቀብ እንዲነሳላት ማድረጓን ሲኤን ኤን ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።

ዘገባው እንደሚለው አሜሪካ ቴህራንን ወደ ድርድር ጠረጴዛው ለመመለስ የተጠናከረ ሙከራ አድርጋለች።

ላለፉት ሁለት ሳምንታት በኢራን እና በእስራኤል ወታደራዊ ጥቃቶች እየተበራከቱ ባለበት ወቅት እንኳን ከመጋረጃው ጀርባ ከኢራናውያን ጋር መነጋገራቸውን ምንጮች ነግረውኛል ሲል ሲ.ኤን.ኤን ዘግቧል።

የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ እነዚያ ውይይቶች በዚህ ሳምንት ቀጥለዋል ብለዋል።

ኢራን ወደ ድርድር ብትመለስም ዩራኒየም ማበልፀግ ላይ የማይወላውል አቋም አሳይታለች ብሏል ዘገባው።

ለኢራን የቀረበው የ30 ቢሊዮን ዶላር ጉርሻ ለሲቪል የኒውክሌር መርሃ ግብር አገልግሎት የሚውል መሆኑን የትራምፕ አስተዳደር ባለስልጣናት እና ሃሳቡን የሚያውቁ ምንጮች ለሲ.ኤን.ኤን ተናግረዋል ብሏል።
Hule Addis Media ( ሁሌ አዲስ ሚዲያ)
Photo
አንጋፋው  ጋዜጠኛ ደረጀ ኃይሌ የጃምቦ ሪል እስቴት ብራንድ አምባሳደር በመሆን ለሦስት ዓመት በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ትላንት  ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል ከድርጅቱ ጋር ተፈራርሟል፡፡

የጃምቦ ሪል ስቴት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ደበበ ሰይፉ በፊርማ ስነስርአቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ጋዜጠኛ ደረጀ ኃይሌ በቅርቡ በሰሜን አሜሪካ በሚካሄደው ዓመታዊ የኢትዮጵያውያን የስፖርት ፌስቲቫል ላይ ጃምቦ ሪል ስቴትን  ወክሎ በመሳተፍ  የመጀመሪያውን የስራ እንቅስቃሴው እንደሚጀምር  ገልጸዋል፡፡

ጃምቦ ሪል አስቴት በቅርቡ በተከበረው የጋዜጠኛው  የ60ኛ ዓመት ልደት በዓል ላይ፣  ባለ ሦስት መኝታ ክፍል  የመኖሪያ ቤት ስጦታ እንዳበረከተለት ይታወሳል፡፡ አንጋፋው ጋዜጠኛ በዕለቱ ከመኖሪያ ቤት በተጨማሪ የመኪና ስጦታ ከታሜሶል እንዲሁም መጠኑ ያልተገለጸ ገንዘብ ከወዳጆቹ እንደተበረከተለት ይታወቃል፡፡

በግራንድ ሃይሌ ሆቴል በተካሄደው የልደት በዓል ላይ ጋዜጠኛው ለጃምቦ ሪል ስቴት  በብራንድ አምባሳደርነት መመረጡ  መጠቀሱን ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ የትላንትናው ሥነስርዓት ያስፈለገው ስምምነቱን ለህዝብ ይፋ ለማድረግና ለመፈራረም መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ጃምቦ ለምን ጋዜጠኛ ደረጄን  በአምባሳደርነት እንደመረጠው ሲያብራሩም፤ "የመረጥነው በብዙ መስፈርቶች ነው፤ ጃምቦ ካለው ዓላማና እንቅስቃሴ ጋር ተመሳሳይና ትክክለኛ ዓላማ ያለው በመሆኑ ነው፤ ደሞም  ምርጫችን ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጠናል" ብለዋል።

"ደረጀ ለሥራው ያለው ፍቅር፣ ቁርጠኝነትና ሙያዊ ታማኝነት የድርጅታችን አምባሳደር እንዲሆን ለመምረጥ አስችሎናል" ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ጋዜጠኛ ደረጀ ኃይሌ ያለው  ሰፊ ልምድ፣ እውቅናና  ተቀባይነት ለጃምቦ ሪል ስቴት ብራንድ ግንባታና ለድርጅቱን ዕድገት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት እምነታቸውን ገልጸዋል።

እስከዛሬ ለጋዜጠኝነት ሙያና ለባለሙያዎቹ ትኩረት ሳይሰጣቸው መቆየቱን ያነሱት አቶ ደበበ ሰይፉ፤ "ለመጀመሪያ ጊዜ ጋዜጠኛና የጋዜጠኝነት ሙያ  ክብርና ዕውቅና በማግኘታቸው ትልቅ  ኩራትና ደስታ ይሰማናል" ብለዋል፡፡፡

ጋዜጠኛ ደረጄ  ኃይሌ በበኩሉ፣ በህይወት ዘመኑ ከጋዜጠኝነት  ውጭ ሌላ ሥራ ሞክሮ እንደማያውቅና እንደማይችል ተናግሯል፡፡

"የምችለው ጋዜጠኝነትን ብቻ ነው። ጋዜጠኝነት አልከፈለኝም ብዬ አማርሬ ግን አላውቅም"  ያለው ጋዜጠኛ ደረጄ ፤ ለተደረገለት ነገር ሁሉ ጃምቦ ሪል እስቴትን አመስግኗል።

ይህ በዚህ እንዳለ፣ ጋዜጠኛ ደረጀ  ኃይሌ በልደቱ ዕለት ቃል የተገባለትን BYD E2  መኪና  በዛሬው ዕለት ከታሜሶል ኮሙኒኬሽንስ ተረክቧል፡፡  የመኪና ስጦታው  3.4  ሚሊዮን  ብር እንደሚያወጣ  ታውቋል፡፡

ጃምቦ ሪል ስቴት ግሩፕ ከ29 ዓመታት በፊት በወንድማማቾቹ አቶ ደበበ ሰይፉና አቶ ወንድይራድ ሰይፉ አማካኝነት "ጃምቦ ኮንስትራክሽን" በሚል ስያሜ እንደተቋቋመ ይታወቃል። ድርጅቱ ከዚያ ጊዜ አንስቶ በግንባታ ዘርፍ ከፍተኛ ልምድ በማካበትና በርካታ  ፕሮጀክቶችን በማከናወን በኢትዮጵያ የሪል ስቴት ገበያ ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ ሆኖ ዘልቋል፡፡
ከኢትዮጵያ ወደ ታንዛኒያ 50 ሜጋ ዋት ኃይል የማስተላለፍ የሙከራ ሂደት በስኬት መከናወኑ ተገለፀ

የኬንያ ኤሌክትሪክ ኩባንያ ሱስዋ-ኢሲንያ ማስተላለፊያ መስመር ከ225 ሜጋ ዋት እስከ 262 ሜጋ ዋት ማስተላለፉን የተቋሙ ሥራ አስፈፃሚ ጆን ማትቪዮ ተናግረዋል፡፡

የማስተላለፊያ መሠረተ ልማት ግንባታው በኬንያ ግምጃ ቤት፣ በዓለም ባንክ፣ በአፍሪካ ልማት ባንክ፣ በፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ እና በአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎለታል።

ከኢትዮጵያ ወደ ታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተላለፍ የሚያስችል የሶስትዮሽ ስምምነት ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ታንዛኒያ ባለፈው ጥር ወር መፈራረማቸው ይታወሳል።
በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የትምህርት ቤት ፈተና ሲወስዱ የነበሩ 29 ህጻናት በአካባቢው በደረሰ ፍንዳታ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

የአከባቢው ሆስፒታል ዳይሬክተር ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ፍንዳታው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማጠናቀቂያ ፈተና እየወሰዱ በሚገኙ ተማሪዎች ላይ የደረሰው በኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር ላይ በገጠመው አዳጋ ነው።

የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ፋውስቲን-አርቸንስ ቱዋዴራ በአደጋው ህይወታቸውን ያጡ ተማሪዎችን ለማስታወስ ብሄራዊ የሐዘን ቀን ያወጁ ሲሆን፤ በአደጋው ​​የቆሰሉት ከ280 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች በሆስፒታል ነፃ ህክምና እንዲያገኙ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

አደጋው የደረሰው ከዋና ከተማው ከሚገኙ አምስት የተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች የባካሎሬት የ2ኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ ፈተና ለመውሰድ በተሰበሰቡበት አካባቢ መሆኑ ተገልጿል።

የሀገሪቱ የትምህርት ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፤ ፍንዳታው የተፈጠረው በዋናው ህንጻ ወለል ላይ በሚገኘው የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር ላይ ጥገና ሲደረግለት የነበረው ኃይል ወደ ቀድሞ ሁኔታው ​​እንዲመለስ በመደረጉ ነው ብሏል።

የትምህርት ሚንስትሩ ኦሬሊን ሲምፕሊስ ኮንግቤሌት ዚምጋስ፤ በአደጋው ልጆቻቸውን ላጡ ወላጆች ሀዘናቸውን ገልፀው ተጨማሪ ፈተናዎች መቋረጣቸውን አስታውቋል።
Forwarded from Capitalethiopia
#CapitalNews ኢትዮጵያ የኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝ ኤክስፖርት ፕሮጀክት ሰረዘች

👉 በምትኩ የማዕድን ሚኒስትር የተፈጥሮ ጋዝን ለአገር ዉስጥ ፍጆታ ለመጠቀም የሚያስችል አዲስ ፕሮጀክት እያጠና ነዉ

ኢትዮጵያ በኦጋዴን ክልል የሚገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ውጭ የመላክ ፕሮጀክት የገንዘብ እጥረትና የትግበራ መዘግየትን ዋቢ በማድረግ እንደሰረዘች አስታውቃለች። በምትኩ፣ የማዕድን ሚኒስቴር የተፈጥሮ ጋዝን ለአገር ውስጥ ፍጆታ፣ በተለይም ማዳበሪያ ለማምረትና ኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል አዲስ ፕሮጀክት እያጠና መሆኑን ገልጿል።

የማዕድን ሚኒስቴር እንደገለጸው፣ ኢትዮጵያ በተለይም በኦጋዴን ተፋሰስ፣ በካሉብና ሂላላ አካባቢዎች ከፍተኛ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ያላት ሲሆን፣ ይህም ከ50 ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ ማዳበሪያ ለማምረት፣ ኃይል ለማመንጨትና ለተለያዩ የነዳጅ ምርቶች ለማገልገል የሚያስችል እንደሆነ ቢገመትም፣ እስካሁን በጥልቀት አልተጠናም።

የጅቡቲ የቧንቧ መስመር ፕሮጀክት መሰረዝ
በ2022፣ ከኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝ አውጥቶ በ767 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባለው የቧንቧ መስመር ወደ ጅቡቲ በመላክ በፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ውጭ ለመላክ ታቅዶ የነበረው ፕሮጀክት መሰረዙ ተገልጿል።

ተጨማሪ ያንብቡ
በጃማይካ የአእምሮ ህመምተኛ የሆኑ ግለሰብ ያለ አግባብ ከ40 አመት በላይ በመታሰራቸው  100 ሚሊዮን ብር ገደማ እንዲከፈላቸው ፍርድ ቤት አዘዘ

ለ50 ዓመታት በእስር ቤት የቆዩት የአእምሮ ህመምተኛ የሆኑት ጆርጅ ዊሊያምስ የፍርድ ቤት ውሳኔን በመጠባበቅ ላይ የነበሩ ሲሆን፣ አሁን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከ100ሚሊዮን ዶላር በላይ ካሳ መንግስት እንዲከፍሏቸው አዟል።

ለፍርድ ቤት ለመቅረብ ብቁ እንዳልሆኑ የተቆጠሩት ዊሊያምስ፣ በፈረንጆቹ ሰኔ 2020 ከተለቀቁ በኋላ ለመንግሥት ካሳ ጠይቀው ነበር።

ጉዳዩን የያዙት  ዳኛ ሶንያ ዊንት ብሌየር ለዊሊያምስ 78.6 ሚሊዮን ዶላር የማካካሻ ካሳ እና 42 ሚሊዮን ዶላር የቅጣት ካሳ እንዲከፈላቸው ወስነዋል።

መንግሥት ለቤተሰቡ 6 ሚሊዮን ዶላር ካሳ አቅርቦ ነበር።

ዳኛ ዊንት ብሌየር በውሳኔያቸው እንዳብራሩት፣ የ42 ሚሊዮን ዶላር የቅጣት ካሳ የተሰጠው “አስፈጻሚው አካል ተገቢውን ህጋዊ መስፈርቶች ባለማሟላቱ፣ ማለትም ተከሳሹ በእስር ላይ በነበረበት ጊዜ የአእምሮ ጤንነቱ እና ደህንነቱ ታሳቢ ሳይደረግ ለ42 ዓመታት ያህል ደህንነቱ የተጠበቀ ጥበቃ እና እንክብካቤ ባለማግኘቱ ነው” በማለት ነው።

ዊሊያምስ፣ ራስታፋሪያን የሆኑ ግለሰብ ሲሆኑ፣ በሀምሌ 1970 በሴንት ካተሪን በሚገኘው ማውንት ዲያብሎ ማኅበረሰብ ውስጥ በመኪና ሲጓዝ በነበረ ቤተሰብ ላይ ቢላዋ በመውጋት ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በዚያው ዓመት ታህሳስ ወር ላይ፣ በዚያ ክስተት ወቅት በቢላ ተወግቶ የሞተውን ያን ላውሪን በመግደል ተከሰሱ።

በየካቲት  1971 ተመርምረው ስኪዞፈሪንያ እንዳለባቸው ተረጋግጧል፤ ነገር ግን በከፊል የማገገም ደረጃ ላይ ነበሩ።

ዊሊያምስ በመጋቢት 1971 ለፍርድ ቤት ለመቅረብ ብቁ እንዳልሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በመንግስት እስር እንዲቆዩ ታዘዋል። ጉዳያቸው በየጊዜው ሳይገመገም ለ42 ዓመታት በእስር ላይ ቆይተዋል ሲሉ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በህወሓት እና ሻዕቢያ መካከል የተፈጠረው ጥምረትና ግንኙነት በፌደራል መንግሥቱ መቋረጥ አለበት ሲሉ የቀድሞ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ!

በቅርቡ ህወሓትና ሻዕቢያ ጥመረት እየፈጠረ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህ የሁለቱ አካላት ጥምረት በመንግሥት ጣልቃ ገብነት ሊቋረጥ ይገባል ሲሉ የቀድሞ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች አሳስበዋል፡፡የቀድሞዋ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም፤ "ይህንን ለጦርነት የተደረገ ጥምረት መንግሥት ሊያቋርጠው ይገባል" ሲሉ ገልጸዋል።

ሌላው የቀድሞ የድርጅቱ አባልና ከፍተኛ አመራር እንዲሁም የዲሞክራሲ ስምረት ትግራይ ፖርቲ መስራች ውስጥ አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት በበኩላቸው፤ "የሁለቱ አካላት ጥምረት ዓላማ ግልፅ አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።በምርጫ ቦርድ የተሰረዘው ህወሐትና የኤርትራ መንግሥት ጥምረት መፍጠር ለጦርነት ዓላማ የተደረገ መሆኑ እየተገለጸ ይገኛል።

በተጨማሪም በትግርኛ "ፅምዶ" ወይንም "ጥምረት ለሀቀኛ ሰላም ለትግራይ እና ኤርትራ" በሚል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እየተደረገ መሆኑንም መመልከት ተችሏል።ይህንን ጥምረት በሚመለከት ሀሳባቸውን የሰጡት የቀድሞ የህወሓት ከፍተኛ አመራር ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም "በግልፅ ለጦርነት የተደረገ ጥምረት ነው" ብለዋል።

"ሕዝብን ከተደቀነበት ጦርነት ማዳን ላይ መስራት አለብን" ያሉ ሲሆን፤ ጦርነቱ የማይቀር እንኳን ቢሆን ዱላው ሕዝብ ላይ እንዳያርፍ መስራት አለብን" ሲሉም ገልጸዋል።"አሁን ላይ በግልፅም ይሁን በድብቅ ጥምረቱ ይታያል" ያሉት ወይዘሮ ኬሪያ፤ "ይህንን ማስቆምና መቁረጥ ያለበት የትግራይ ሊሂቃንና ፌደራል መንግሥት ነው በማለት ሀሳባቸውን" ሰጥተዋል።

ሌላው ሀሳባቸውን ለአሐዱ የሰጡት የቀድሞ የህወሕት አባልና ከፍተኛ አመራር ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት፤ "በአንድ ሉዓላዊት ሀገር ውስጥ ከሌላ ሀገር ጋር ማን ግንኙነት መፍጠር እንዳለበት ይታወቃል" ብለዋል፡፡"ሕገ-ወጥ ግነኙነት ሲኖር ደግሞ ማስቆም ያለበት ማን እንደሆነም ግልፅ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።"ይሁን እንጂ ከኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነት ያልጠራ ነው፤ ነገር ግን ግንኙነቱ በመርህ ላይ ካልተመሰረተ ትክክል አይለም" ሲሉም ለአሐዱ ገልጸዋል።

በዚህ ጥምረት ዙሪያ የፌደራል መንግሥት በግልፅ ያስታወቀው ነገር ባይኖርም፤ ባለፈው ሳምንት አርብ በትግራይ ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ የሚጠይቅ ወይይት ተካሂዶ ነበር።የፌደራል መንግሥት የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከልን በመወከል የተገኙት አቶ መለሰ አለሙ፤ "የፌደራል መንግሥት ኃላፊነት እንዳለ ሆኖ የትግራይ ፖለቲከኞችም ለሰላም ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል" ሲሉ ተደምጠዋል።"የድንበር ጉዳይን በተመለከተ መንግሥት ሉዓላዊነቱን በፍፁም አሳልፎ አይሰጥም" ያሉም ሲሆን፤ የውስጥ ችግሮች ከተፈቱ ሌላውን ማስተካከል እንደሚቻል ተናግረዋል።

Via Ahadu
ባንኮች ላይ የተጣለው አስገዳጅ የቦንድ ግዥ እንዲነሳ ተወሰነ!

ሦስተኛ ስብሰባውን ዛሬ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም ያካሄደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ በሁሉም ንግድ ባንኮች ላይ የተጣለው አስገዳጅ የቦንድ ግዥ እንዲነሳ ወሰነ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው ዛሬ ባደረገው ውይይት የተለያዩ ውስኔዎችን አሳልፏል። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ሁሉም ንግድ ባንኮች የረጅም ጊዜ የግምጃ ቤት ቦንድ (Treasury Bond) እንዲገዙ የሚያስገድደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ (MFAD/TRBO/001/2022) እንዲነሳ ያሳለፈው ወሳኔ ተጠቃሽ ነው።

"አሁን ላይ የመንግሥት ገቢ የማሰባሰብ አቅም በእጅጉ በመሻሻሉ፣ እንዲሁም መንግሥት የበጀት ጉድለቱን ለሟሟላት የውጭና ገበያ መር የሆኑ የሀገር ውስጥ የመበደሪያ አማራጮችን እየተጠቀመ በመሆኑ በባንኮች ላይ ተጥሎ የቆየውን ይህ አስገዳጅ መመሪያ አሁን ላይ ማንሣቱ ተገቢ መሆኑን ኮሚቴው አምኖበታል" ሲል መግለጫው ጠቅሷል።

ኮሚቴው ያመነበት ይህ የገንዘብ ፖሊሲ ምክረ ሐሳብ ሌሎች ለብሔራዊ ባንክ ቦርድ ቀርቦ መጽደቁንም መግለጫው አመልክቷል።ሁሉም ንግድ ባንኮች የረጅም ጊዜ የግምጃ ቤት ቦንድ እንዲገዙ በሚያስገድደው የብሔራዊ ባንክ መመሪያ መሠረት ባንኮች መመሪያው ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት እ.ኤ.አ. ከጃንዋሪ 2022 ጀምሮ ከአጠቃላይ ዓመታዊ ብድራቸው አምስት በመቶ የሚሆነውን ለዚህ የቦንድ ግዥ ሲያውሉ ቆይተዋል። በዚህ መመሪያ መሠረት የገዙት ቦንድ የሚመለሰው (ለቦንድ ግዢ ያዋሉት ገንዘብ ተመላሽ የሚደረግላቸው) ከአምስት ዓመት ቆይታ በኋላ ሲሆን ፣ ባንኮቹ መመሪያው ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ወር አንስቶ እ.ኤ.አ. እስከ ጁን 30 ቀን 2024 ድረስ የገዙት የቦንድ መጠን 94 ቢሊዮን ብር መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር የመንግሥት ዕዳ መግለጫ ያመለክታል።

በገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው ያሳለፈው ሌላኛው ውሳኔ በባንኮች ላይ የተጣለውን የብድር ዕቀባ የተመለከተ ሲሆን ፣ በአሁኑ ወቅት በባንኮች ዓመታዊ የብድር ዕድገት ላይ የተቀመጠው የ18 በመቶ ጣሪያ እስከ መጪው መስከረም 2018 ዓ.ም. ድረስ እንዲቀጠል ኮሚቴው ወስኗል።ለዚህም የሰጠው ምክንያት አሁን ላይ የዋጋ ግሽበት የመርገብ አዝማሚያ እየተስተዋለ ቢሆንም ይህንን ማስቀጠል አስፈላጊ በመሆኑ በባንኮች ላይ የተጣለው የብድር ዕድገት ጣሪያ ባለበት እንዲቆይ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ የሚገልጽ ነው።

Via Reporter
"በሚቀጥሉት 40 ወራት ውስጥ አፍሪካ በማዳበሪያ እራሷን ትችላለች"- አሊኮ ዳንጎቴ

ናይጄሪያዊው የአፍሪካ ቁጥር አንድ ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ አፍሪካ በመጪዎቹ 40 ወራት ውስጥ በማዳበሪያ ምርት እራሷን ትችላለች አሉ።

ዳንጎቴ የማዳበሪያ ፋብሪካው ላይ የ2.5 ቢሊየን ዶላር ማስፋፊያ ለማድረግ ያቀደ ሲሆን ይህም አፍሪካ ከውጪ የምታስገባውን ምርት በእጅጉ ይቀንሳል ተብሏል።

ቢሊየነሩ" አፍሪካ ከ40 ወራት በኋላ ከየትኛውም ቦታ ማዳበሪያ አታስገባም፤ 40 ወራት ብቻ ስጡኝ፥ ዳንጎቴ ከኳታር የበለጠ የዩራያ አምራች እንዲሆን እናደርገዋለን" ብለዋል።

አፍሪካ በአሁኑ ጊዜ ከ6 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ በላይ በአመት ከሌላው አለም እያስገባች ሲሆን አሁን ያለው የዳንጎቴ ፋብሪካ በአመት 3 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ዩሪያ የማምረት አቅም ገንብቷል።

የዳንጎቴ ፋብሪካ የድርጅቱን 37 በመቶ ምርት ለአሜሪካ ገበያ እያቀረበ መሆኑን ጠቅሶ ከማስፋፊያው በኋላ ምርቱን በእጥፍ በመጨመር የአፍሪካን ፍላጎት ያሟላል ተብሎ ይጠበቃል።

እንደ ግዙፉ የአፍሪካ ኤግዚም ባንክ ሪፖርት አፍሪካ በ2021 ከማዳበሪያ ሽያጭ 8.9 ቢሊየን ዶላር ገቢ ስታገኝ ትልቁን ድርሻ የሰሜን አፍሪካ ሃገራት ይይዛሉ ተብሏል።

ሞሮኮ እና ግብፅ 70 በመቶ የአፍሪካን የማዳበሪያ ሽያጭ ሲይዙ በድምሩ 6.23 ቢሊየን ዶላር አግኝተዋል።

ምንም እንኳን የተወሰኑ ሃገራት በማዳበሪያ እራሳቸውን የቻሉ ቢሆንም አብዛኞቹ አሁንም ከውጪ በሚገባ ምርት ላይ ጥገኛ ናቸው።

የዳንጎቴ የማዳበሪያ ፋብሪካ በሚቀጥሉት ሁለት አመታትም በቀን 7 ሚሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ማቀዱን ቢሊየነሩ ገልፀዋል።

በ2022 ስራውን የጀመረው የሌጎሱ የዳንጎቴ የማዳበሪያ ፋብሪካ በናይጄሪያ የምግብ እጥረትን ለመቀነስ በዝቅተኛ ዋጋ እየሸጠ ሲሆን የናይጄሪያን የ1.5 ሚሊየን ቶን አመታዊ የማዳበሪያ ፍጆታም ለመሸፈን እየሰራ ነው።

በአመት ከ400 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ የሚያስመጣው የማዳበሪያ ፋብሪካው የናይጄሪያን የውጪ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው።

የአፍሪካ የማዳበሪያ ዋጋ ከ15 ቢሊየን ዶላር የተሻገረ ሲሆን ይህ ቁጥር በ2030 ወደ 20 ቢሊየን እንደሚያድግ ይገመታል።

በምግብ እጥረት እና በውጪ ምንዛሬ ለምትፈተነው አፍሪካ የዳንጎቴ ፋብሪካ ሁነኛ መፍትሄ እንደሚሆን ሲጠቆም ቢሊየነሩ ዳንጎቴ የአህጉሪቱ መሪዎች የአህጉሪቱን ሃብትና ኢንቨስትመንት ባማከለ መልኩ አፍሪካን ተቀዳሚ አድርገው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

ቢሊየነሩ አሊኮ ዳንጎቴ በኢትዮጵያ የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት መስማማታቸው በቅርቡ ይፋ መደረጉም ይታወሳል።

Source: Reuters, Africa Fertilizer Watch
2025/07/01 00:57:06
Back to Top
HTML Embed Code: