Telegram Web Link
ደርስ
~
•  ኪታቡ፦ ዶላሉ ጀማዐቲል አሕባሽ
•  ደርሱ የሚሰጥበት ቦታ:- አሸዋ ሜዳ፣ ጉቱ ሪል እስቴት መስጂድ
•  ጊዜ፦ ከመግሪብ እስከ ዒሻእ
•  የኪታቡን pdf ፋይል በዚህ ማግኘት ይቻላል:-
https://www.tg-me.com/IbnuMunewor/8025
• የዛሬ ደርስ መነሻ፦ ገፅ፡ 23
• ደርሱ በዚህ የቴሌግራም ቻናል ይተላለፋል፣ ኢንሻአላህ፦
https://www.tg-me.com/IbnuMunewor
Live stream finished (53 minutes)
ለዱዓት!
~
ዘመኑ በደዕዋ ስራ ላይ ርብርብ የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው። ለማስተማር፣ ወገኑን ለመጥቀም የሚያስችል አቅም ያለው ሁሉ የበኩሉን አስተዋፅኦ ሊያበረክት ይገባል። ስለዚህ በያላችሁበት በአካል በአካባቢያችሁ፣ እንዲሁም በማህበራዊ መገናኛዎች ላይ የደዕዋ ድርሻ ይኑራችሁ። ደዕዋ ላይ ተሳታፊው ሲበዛ ሐቅ ጥንካሬ ይኖረዋል። ባጢል ጉልበቱ ይሳሳል። የኸይር ስርጭት አድማሱ ይሰፋል።

ደግሞም የደዕዋ ስራ ለሌሎች ብቻ ሳይሆን ለራስም ብዙ ፋይዳዎች አሉት። ራስን መግራት አለበት። ራስን ማስተማር አለበት። ከደዕዋ የራቀ ሰው በሂደት ከእውቀትም ነው የሚርቀው። በልፋቱ የሚያገኘው ምንዳና ደረጃም ከፍ ያለ ነው። አላህ እንዲህ ይላል :-
{ وَمَنۡ أَحۡسَنُ قَوۡلࣰا مِّمَّن دَعَاۤ إِلَى ٱللَّهِ وَعَمِلَ صَـٰلِحࣰا وَقَالَ إِنَّنِی مِنَ ٱلۡمُسۡلِمِینَ }
"ወደ አላህ ከጠራና መልካምንም ከሠራ፣ 'እኔ ከሙስሊሞች ነኝ' ካለም ሰው ይበልጥ ቃሉ ያማረ ማን ነው?" [አልፉሲለት: 33]
* በሰማይ በምድር ያለው ሁሉ ኢስቲግፋር ያደርግልህ ዘንድ አስተምር።
* ከሞትህ በኋላ እንኳ የማይቋረጥ ምንዳ ይኖርህ ዘንድ አስተምር።
* ከዱንያ ውድ ንብረቶች ሁሉ የበለጠ ምንዳ ይኖርህ ዘንድ ለሰዎች ሂዳያ ሰበብ ሁን።
* ወገንህ ዛሬ ካለበት መልከ ብዙ ኋላ ቀርነት ይወጣ ዘንድ አላህ በሰጠህ እውቀት ሰዎችን ጥቀም።

ባጭሩ የደዕዋ ጥቅሙ ተቆጥሮ የሚዘለቅ አይደለም። ስለሆነም እባካችሁ፣ እባካችሁ አላህ ባገራልን መልኩ በደዕዋ፣ በተድሪስ ላይ እንረባረብ። አቅም እያላቸው የተቀመጡትንም እንቀስቅሳቸው።
=
የቴሌግራም ቻናል :-
https://www.tg-me.com/IbnuMunewor
https://www.tg-me.com/IbnuMunewor
Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)
Photo
የሚያጓጓው ሰላም
~
አሰላሙ ዐለይኩም ወረሕመቱላሂ ወበረካቱሁ።

ሰላም ሰላሙን ለተከተሉ ሁሉ ይሁን፡፡ እኛ ሙስሊሞች ሰላማዊ ነን፣ ከሰላሙ ጌታ ሰላምን የምንሻ፡፡ ስማችንም ሀይማኖታችንም ከሰላም ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ እርስ በርስ ስንገናኝ ከማንኛውም የቃላት ልውውጥ በፊት ከየትኛውም ህዝብ በተለየ በቋንቋ የማይግባቡ ህዝቦችን የሚያግባባ ውብ፣ ድንቅ፣ አጭር አለማቀፋዊ ቋንቋ አለን- “አሰላሙ ዐለይኩም” (ሰላም በናንተ ላይ ይሁን)፣ “ወዐለይኩም አሰላም” (ሰላም በናንተም ላይ ይሁን)፡፡ እኛ እንደነ ጀምስ “ሀይ” እንደነ እንትና “ታዲያስ” … ብለን በጥያቄ፣ በነገር፣ በፉገራ፣ በመአት … አንጀምርም፡፡ ይልቁንስ በዱዓ ነው የምንጀምረው፣ በመልካም ምኞት! ፊትን ፈታ አድርጎ፣ እዝነትና ትህትና በተላበሰ መልኩ “አሰላሙ ዐለይኩም!”

ኢስላም፣ ኢስቲስላም፣ ሙስሊም፣ ሰላም፣ …!! ከጌታችን ስሞች አንዱ አሰላም ነው፡፡ ከአምስቱ እለታዊ ግዴታዎቻችን ከሶላቶቻችን በኋላ ከአሰላሙ ከጌታችን ሰላምን እንለምናለን፣ “አላሁመ አንተ ሰላም፣ ወሚንከ ሰላም፣ ተባረክተ ያዘልጀላሊ ወልኢክራም” በማለት። “ጌታችን ሆይ! አንተ ነህ ሰላሙ፤ ሰላምም ካንተ ነው፤ በስምህ የሚገኘው በረከት ሰፋ፤ አንተ የልቅናና የቸርነት ባለቤት ሆይ”፡፡

ብንገናኝ፣ ብንለያይ፣ ብንፀልይ፣ ብንወያይ፣… በሰላም ነው፣ ለሰላም፣ ስለሰላም! ጌታችን አሰላም፣ የምንመኘው አገር ዳሩ ሰላም– የሰላሙ ሀገር - (ጀናህ)! የሰላሙ አገር ሰላምታም ሰላም ነው፣
( وَتَحِيَّتُهُمْ فِيهَا سَلَامٌ)
"በእርሷ ውስጥ መከባበሪያቸውም ሰላም መባባል ነው።"
ከአንድየው ከአሰላሙ የሚመጣውም ብስራትም ሰላም ነው፣
(سَلَامٌ قَوْلًا مِنْ رَبٍّ رَحِيمٍ)
"(ለነርሱም) አዛኝ ከሆነው ጌታ በቃል ሰላምታ አላቸው።" [ያሲን: 58]
በሰላሙ ሀገር በጀናህ የሚሰማውም ወሬ ረብ- የለሽና እንቶ ፈንቶ ሳይሆን ሰላም ነው፣
(إِلَّا قِيلًا سَلَامًا سَلَامًا)
"ግን ሰላም መባባልን (ይሰማሉ)፡፡" [አልዋቂዐ: 26]

ሱብሐነላህ! አሁን እንደ ኢስላም ለሰላም ትልቁም ዋጋ የሰጠ አለወይ?! ሙስሊም መሆን ምንኛ መታደል ነው? ውስጣዊ ሰላምን የሚያጎናፅፍ ልዩ ተድላ! ሙስሊም ነዎት?! አላሁ አክበር!! የታላቅ ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል! ያሸነፉት ሎተሪ አይደለም! በጭራሽ! ያሸነፉት ለሰው-በላ ጭራ ^ቆች፣ ለፀረ-ሰላም ሀይሎች፣ ለነ ሻሮን ወንድሞች ጭምር የሚሰጠውን የነ ጀምስን የኖቤል የሰላም ሽልማት አይደለም፡፡ ሽልማትዎ አይን ያላየው፣ ጆሮ ያልሰማው፣ በሰው ልቦና ውስጥ ፍፁም ውል ብሎ የማይውቅ እጅግ ውድና አጓጊ ነገር ነው! ሽልማትዎ ይሄውና! ከባለ ሰላሙ ጌታ ከአሰላሙ በኢማን ለታጀበው የሰላም ትጋትዎ ዳሩ ሰላም! ጀናህ!
فَمَنْ زُحْزِحَ عَنِ النَّارِ وَأُدْخِلَ الْجَنَّةَ فَقَدْ فَازَ
"ከእሳትም የተራቀና ጀነትን የተገባ ሰው በእርግጥ ምኞቱን አገኘ፡፡" [ኣሊ ዒምራን: 185]
ከዚህ የሚበልጥ ምን ሽልማት አለ? አያሽቀዳድምም?
(وَسَارِعُوا إِلَىٰ مَغْفِرَةٍ مِنْ رَبِّكُمْ وَجَنَّةٍ عَرْضُهَا السَّمَاوَاتُ وَالْأَرْضُ أُعِدَّتْ لِلْمُتَّقِينَ)
ከጌታችሁ ወደ ሆነች ምሕረትና ስፋቷ እንደ ሰማያትና ምድር ወደ ሆነች ጀነት አላህን ለሚፈሩ የተዘጋጀች ስትሆን ተቻኮሉ፡፡" [ኣሊ ዒምራን: 133]

ሙስሊም ሙስሊማት ዒባዱ ሰላም! የአዛኙ የአሰላም ባሪያዎች በምድር ላይ ሲጓዙ በሰኪና ነው፣ በትህትና፣ በሰላማዊ ሁኔታ፡፡ ቂሎች፣ ከቂል የሚጠበቁ ቃላትን ቢወረውሩባቸው፣ በቂልኛ ቢያናግሯቸው፣ ፀረ-ሰላም ሚሳኢል ቢያስወነጭፉባቸው፤ ኢላማውን በማይስተው የሰላም ሚሳኢል ያከሽፉታል፣ አቅጣጫ ያስቀይሩታል፡፡ “ሰላም” በማለት፣ ሰላም በመመለስ፣ በሰላምኛ በማናገር፡፡
وَعِبَادُ الرَّحْمَٰنِ الَّذِينَ يَمْشُونَ عَلَى الْأَرْضِ هَوْنًا وَإِذَا خَاطَبَهُمُ الْجَاهِلُونَ قَالُوا سَلَامًا
"የአረሕማንም ባሮች እነዚያ በምድር ላይ በዝግታ የሚሄዱት፣ ባለጌዎችም (በክፉ) ባነጋገሩዋቸው ጊዜ ሰላም የሚሉት ናቸው፡፡" [አልፉርቃን: 63]

የኢማን፣ የኢስላም፣ የሰላም አርአያዎቻችን ከአሰላሙ ጌታችን ለተቀበሉት የሰላም አደራ - ለኢስላም ሲሉ የደሙት፣ የቆሰሉት፣ የተሰቃዩት፣ የሞቱት ነቢዮቻችን ናቸው፡፡ እነዚያ በአስፈሪው የቂያማ ጭንቅ ጊዜ እንኳን ስለ ሰላም ዱዓ የሚያደርጉት “አላሁመ ሰሊም ሰሊም” በማለት፡፡ ሰላም በነሱ ላይ ይሁን፡፡
ውድ የኢስላም አጋሮቼ! እንቁ የኢስላም ወገኖቼ! በኢስላም ከአሰላም ዳሩ ሰላምን እንፈልግ፡፡ በኢስላማዊ ሰላምታችን ደግሞ ሰላማዊ ህይወት ለመጎናፀፍ የሚያግዘንን “አጅር” እንሰብስብ፡፡ ሰላምታን እናብዛ፡፡ የሰላም ሀዋሪያው ሰላም ወዳዱ ዐብዱላህ ብኑ ሰላም ረዲየላሁ ዐንሁ ከሰላሙ አርበኛ ከውዱ ነቢያችን ሙሐመድ ብኑ ዐብዲላህ ዐለይሂ ሶላቱ ሰላም እንዲህ የሚል የሰላም መልእክት አስተላልፈዋል፡-
يَا أيُّهَا النَّاسُ، أفْشُوا السَّلاَمَ، وَأطْعِمُوا الطَّعَامَ، وَصِلُوا الأرْحَامَ، وَصَلُّوا والنَّاسُ نِيَامٌ، تَدْخُلُوا الجَنَّةَ بِسَلاَم
“እናንተ ሰዎች ሆይ! ሰላምታን አብዙ፣ የተራበን አብሉ፣ ዝምድናን ቀጥሉ፣ ሰዎች ሲተኙ ስገዱ፣ ጀነትን በሰላም ትገባላችሁ፡፡”

ሱብሓነላህ! እስኪ ይህንን ውብ አነጋገር እናጣጥመው! ቃላቱ፣ ስኬቱ፣ መልእክቱ፣ ሰአቱ፣ ሂደቱ፣ ውጤቱ፣ ሁሉ ሰላም!! የነኚህን ቃላት ዐረብኛ ወዝ ላጣጣመ ደግሞ ሌላ እርካታ፣ ሌላ ጣዕም፣ ሌላ ሰላም!
ውድ ሙስሊሞች የሰላም ሀይሎች የዳሩ ሰላም ናፋቂዎች! ከአሰላም የተጣለብንን ሀላፊነት እንወጣ፣ ሰላማችንን እንዳናጣ፡፡ ስለ ሰላም ዱዓእ እናድርግ። “አሰላሙ ዐለይኩም” እንባባል፡፡ የተሻለውን ጥለን የወራረዱ አንለቃቅም፡፡ ሰላምታችን ኮተት የለውም አያሳፍርም፡፡ ሰላምታችን ቦምብ አይደለም አያስፈራም፡፡ ሰላም እንዴት ያስፈራል?! ያ ሰላሙ! ሰላማችንን መልስልን።
ወሰላሙ ዐለይኩም ወረሕመቱላህ፡፡

(ኢብኑ ሙነወር፣ 2001 ላይ የተፃፈ)
የቴሌግራም ቻናል:-
https://www.tg-me.com/IbnuMunewor
ደርስ
~
• ኪታቡ፦ ዶላሉ ጀማዐቲል አሕባሽ
• ደርሱ የሚሰጥበት ቦታ:- አሸዋ ሜዳ፣ ጉቱ ሪል እስቴት መስጂድ
• ጊዜ፦ ከመግሪብ እስከ ዒሻእ
• የኪታቡን pdf ፋይል በዚህ ማግኘት ይቻላል:-
https://www.tg-me.com/IbnuMunewor/8025
• የዛሬ ደርስ መነሻ፦ ገፅ፡ 27
• ደርሱ በዚህ የቴሌግራም ቻናል ይተላለፋል፣ ኢንሻአላህ፦
https://www.tg-me.com/IbnuMunewor
Live stream finished (53 minutes)
የልባችን ድርቀት አንዱ መንስኤ ይሄውና!
~
በዚህ ዘመን ከገጠሙን ከባባድ ፈተናዎች ውስጥ አንዱ የልብ ድርቀት ነው። የልብ ድርቀት ከልብ ድካም የከፋ በሽታ ነው። በዚህ በሽታ በፅኑ ከመጠቃታችን የተነሳ ዒባዳችን ጣዕም አጥቷል። ሶላታችን ኹሹዕ የሌለው በድን እንቅስቃሴ ሆኗል። ዚክራችን ወዝ የለውም። ሲጀመር ዚክር እናደርጋለን ወይ? ልባችን በመድረቁ የተነሳ በወንጀል የማንደነግጥ ደንታ ቢሶች ሆነናል።

ለዚህ ሁኔታችን ብዙ ምክንያቶች አሉት። በማህበራዊ ሚዲያ የምንከታተላቸው ነገሮች ለዚህ የልባችን ጉዳት የራሳቸው ድርሻ አላቸው። ማንነታችንን በመግራት ላይ አስተዋፅዖ ካላቸው ትምህርቶች ይልቅ አስቂኝ ነገሮችን ማሳደድ ላይ ተጠምደናል። ለዱንያም ይሁን ለዲን ከሚጠቅሙ ቁም ነገር ትምህርቶች ይልቅ ሰዎችን ለማሳቅ የተዘጋጁ ቪዲዮዎች፣ ፅሑፎች የበለጠ ገበያ እንዳላቸው ለማንም የሚታይ ነው። እነዚህን ነገሮች መመልከት ሲበዛ ደግሞ ልባችን እየደነዘዘ፣ ከተቅዋ ያለን ርቀት እየጨመረ ይሄዳል። ይሄ አላህ የጠበቀው ሲቀር ሁላችንም የተለከፍንበት በሽታ ነው። የአላህ መልእክተኛ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦ "ሳቅ አታብዙ። የሳቅ መብዛት ልብ ያደርቃል።" አልባኒይ ሶሒሕ ብለውታል።
=
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://www.tg-me.com/IbnuMunewor
https://www.tg-me.com/IbnuMunewor
በዚህ ዘረኝነት በተንሰራፋበት ዘመን የፖለቲከኞችን የጥላቻ ስብከት ረጋግጦ ከየትኛውም ብሄር ቢሆን ወንድሞቹን መውደድ የቻለ ሰው ምንኛ የታደለ ነው?!
=
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://www.tg-me.com/IbnuMunewor
https://www.tg-me.com/IbnuMunewor
Forwarded from MuhammedSirage M.Noor (Ms MN)
ስለፎቻችን ከቁርአን እና ከዚክር ለአንዲትም ቀን ቢሆን የማይታለፍ ዕለታዊ ልምድ ነበራቸው ። ቀኑ በነሱ ላይ ነግቶ አይመሽም የልምዳቸውን ያህል ቁርአንን ያነበቡና አሏህን ያወሱ ቢሆን እንጂ ! በ3 ቀን .... በሳምንት .... በ10 ቀን ..... ቁርአንን ያኸትሙ ነበር ።

ዛሬ ... በመካከላችን ረመዷን ሲገባ እንጂ ቁርአንን የማያስታውስ አለ ! ጁሙዓ ሲመጣ እንጂ ግማሽ ጁዝእ እንኳን ቁርአን ሳይቀራ የሚከርም አለ !

ኧረ አሏህን እንፍራ !

የማይታለፍ እለታዊ የቁርአን መቅራት ልምድ ይኑረን - የዚክርም እንደዚሁ ።

https://www.tg-me.com/msirage4
Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)
Photo
ከአገር መፍረስ ባሻገር
~
አገር እንድትፈርስ የሚመኙ፣ አገር ለማፍረስ በተግባር የሚጥሩ፣ ለአገር አፍራሾች ድጋፍ የሚሰጡ ብዙ አካላት አሉ። ወንድሜ ሆይ! እውነት በሃገር መፍረስ የምታተርፍ መስሎህ ነው? ለመሆኑ አገር ሲፈርስ ምን ምን ሊከሰት እንደሚችል አሻግረህ ተመልክተሃል? ወይስ በሆኑ አካላት ላይ ያለህ ጥላቻና ቁጭት በሩቅ እንዳትመለከት ሸፍኖብሃል? ወንድሜ አገር ዳቦ አይደለም፤ እንደዋዛ ቆራርሰህ በመካፈል አትገላገልም።

* ሃገር ሲፈርስ እልፍ አእላፍ ይፈናቀላሉ። እንኳን አገር ፈርሶ በብሄር ግጭትና ጥቃት ብቻ የሚሊዮኖች ህይወት ተመሰቃቅሏል። ምናልባት አንተ ከሚፈናቀሉት ባትሆን እንኳ ራስህን በነሱ ጫማ ላይ አድርገህ ተመልከት።
* ሃገር ሲፈርስ እልፍ አእላፍ ትዳር ይፈርሳል። ከሌላ ብሄር ጋር የተጋቡ ወገኖቻችን እጅግ ብዙ ናቸው። ይሄ ዘር እየለየ የሚገድል ትውልድ የሚተዋቸው እንዳይመስልህ። ስንት ቤተሰብ እንደሚበተን ተመልከት።
* ሃገር ሲፈርስ እልፍ አእላፍ ንብረት ይወረሳል። እንኳን አገር ፈርሶ ሰላም በመጥፋቱ ብቻ የስንቱ ምስኪን ንብረት በተለያዩ ክልሎች በጉልበተኛ ተነጥቋል!

* ሃገር ሲፈርስ እዚህም እዚያም መቋጫ የሌለው የድንበር ግጭት ይነሳል። በአንድ መንግስት ስር ሆነን ነው በሶማሊና በኦሮሞ የድንበር ግጭት ከሚሊየን በላይ ህዝብ የተፈናቀለው። በአንድ መንግስት ስር ሆነን ነው አፋርና ዒሳ በየጊዜው የሚጋደለው። በአንድ መንግስት ስር ሆነን ነው ዘጠኝ መቶ ሺ አካባቢ የጌዲዎ ህዝብ የተፈናቀለው። በአንድ መንግስት ስር ሆነን ነው የወሎ ኦሮሞና የሸዋ አማራ የሚጋጨው። በአንድ መንግስት ስር ሆነን ነው በደቡብ ክልል የተለያዩ ህዝቦች መካከል ግጭት የሚቀሰቀሰው። በአንድ መንግስት ስር ሆነን ነው "ወሎ ኦሮሞ ነው"፣ "ወልቃይት፣ ደራ፣ በረራ፣ መተከል አማራ ነው" የሚል ጩኸት የምንሰማው፡፡ ሃገር ከፈረሰ እነዚህ ጩኸቶች ዛሬ ከምናየው በላይ ሚሊዮኖችን የሚበላ እሳት ይቀሰቅሳሉ።

* ሃገር ሲፈርስ እልፍ አእላፍ ነፍስ ይጠፋል። ከላይ የተጠቀሱት በሙሉ መጨረሻቸው እልቂት ነው።
* ምናልባት መልኩ ይቀየር ካልሆነ በስተቀር በሃገር መፍረስ ጭቆና የሚቀር፣ ለድሃ ቀን የሚወጣ እንዳይመስልህ። ወላሂ! ዘር እየለየ፣ ሃይማኖት እየመረጠ በሚገድል ቡድን፣ ከርሱን በሚያስቀድም ፖለቲከኛ መቼም ፍትህና ነፃነት አታገኝም።

የሚሻለው በጋራ ለሰላምና ለፍትህ መጣር ነው። መፍትሄው እንደ ህዝብ ከገጠመን የስነ ምግባር ዝቅጠት ለመውጣት ተባብሮ መሥራት ነው። ችግራችን ስር የሰደደ ነው። ችግራችን በማህበረሰብ ደረጃ የተንሰራፋ ነው። ስለ መንግስት ችግር ጧት ማታ ማውራቱን እንደ ንቃት ቆጥረን እራሳችንን እየሸወድን እንጂ ከመንግስት አልፎ እንደ ህዝብ መተዛዘናችን ሳስቶ መጨካከን ነግሶብናልኮ።

~ በየገበያው የሚያጭበረብረው፣ በየተቋሙ ህዝብ የሚያጉላላው፣ ... ሁሉ ምንም ስቅ ሳይለው ስለ ፍትህ እየወሸከተ ነው።
~ ለብዙዎች ከትምህርት ገበታ መራቅ ሰበብ የሚሆነው፣ ዘርና ሃይማኖት እየለየ ተማሪዎቹን የሚያከላፍተው አስተማሪ ምንም ሳያፍር ስለ ፍትህና ርትእ እየጮኸ ነው።
~ ታካሚዎቹን ፊቱን አጨፍግጎ የሚያስተናግደው፣ በግዴለሽነት የሰው ነፍስ ላይ የሚቀልደው፣ ለርካሽ ጥቅም ሲል የማይገናኝ ምርመራ እያዘዘ ደካማ ወገኑ ላይ ጭካኔ የሚፈፅመው ሃኪም እኮ ነው ስለ ፍትህ የሚጮኸው!
~ የተበላሸ ምግብ፣ ጊዜው ያለፈበት መድሃኒት፣ ፎርጂድ እቃ፣ የተጭበረበረ ምርት፣ ... የሚሸጠው ነጋዴ እኮ ነው "መስራት አቃተን" እያለ የሚያለቅሰው። አዎ አቅቶታል። ግን እሱስ መቼ ከግፍ እጁን ሰበሰበ?
~ ፍትህ በገንዘብ የሚሸጠው፣ ከሌባ ጋር ተቀናጅቶ የሚሰራው፣ እምነትና ብሄር እየመረጠ ፍትህ የሚቀብረው ዳኛና ፖሊስ እኮ ነው ስለ ፍትህ የሚዘፍነው።

~ ሚሊዮኖች የወጡበትን መሬት ሶስት አራት ካርታ ሰርቶ የሚቸበችበው ሰራተኛ፣ የሚሊዮኖችን ውሃና መብራት እየቆረጠ ሺ ጊዜ ብር እየተቀበለ የሚቀጥለው ሌ ^ባ እኮ ነው ስለ ፍትህና ስለ ነፃነት የሚለፍፈው።
~ መንገዶችንና ህዝባዊ ተቋማትን ከደረጃ በታች እየሰራ በሀገር በወገኑ ላይ የሚቆምረው እኮ ነው ለሀገር ለወገኑ ተቆርቋሪ መስሎ የሚፈተፍተው።
~ መኪናና ሞተር ሳይክል አዘጋጅቶ፣ አንድ ላምስት ተደራጅቶ የሚዘርፈው፣ ህፃናት እያፈነ የሚወስደውኮ ነው እኩል ስለ ፍትህ የሚያወራው!
~ የሁለት ቀን ጨቅላ፣ የ70 አመት አዛውንት፣ አቅመ ደካማ ሴቶችን ሳይቀር የሚገድለው እኮ ነው የነፃነት ታጋይ የሚባለው።

እስኪ በየትኛው ዘርፍ ነው የሚነሳ ጥሩ ነገር ያለን? ፖለቲከኞቹ የኛው ነፀብራቆች ናቸው። እኛኑ ነው የሚመስሉት። ከኛው የወጡ እንጂ ከሌላ ፕላኔት የመጡ አይደሉም። ክፋታቸው ክፍታችን፣ ንቅዘታቸው ንቅዘታችን ነው።

እንደ ህዝብ በዚህ ደረጃ መልካሞች የመነመኑ ከሆኑ እንዴት ነው ፍትህና እፎይታ የምናገኘው? በቅድሚያ በራሳችን ላይ ሰፊ ስራ መስራት ይጠበቅብናል። ወደተነሳሁበት ስመለስ፣ ስግብግብ ስሜታችን እየጋረደን፣ ቁንፅል አመልካከታችን እየሸወደን እንጂ በርግጠኝነት በሃገር መፍረስ እንደ ህዝብ ከሳሪዎች እንጂ አትራፊዎች አይደለንም። ስለዚህ ደግመን ደጋግመን ልንመለከት፣ ሰላምን ከሚያደፈርስ ድርጊቶች ልንርቅ፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለአገር አፍራሾች ድጋፍ ከመሆን ልንጠነቀቅ ይገባል። ጥፋትን ማስቆም ባንችል እንኳ ቢያንስ ተጋሪ ባለመሆን የራሳችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባል።

(ኢብኑ ሙነወር፣ ሐምሌ 11/2014)
=
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://www.tg-me.com/IbnuMunewor
https://www.tg-me.com/IbnuMunewor
Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)
Photo
ሰው ውሎውን ይመስላል
~
ሰው ወደሚያዘወትረው ነገር ልቡ ያዘነብላል። ሙዚቃ የሚያዘወትር ወደ ሙዚቃ፣ ፊልምና ድራማ ላይ የሚጣድ ወደ ፊልምና ድራማ፣ ዜና የሚያሳድድ ወደ ዜና፣ ፖለቲካ የሚያነፈንፍ ወደ ፖለቲካ፣ ሚምና ፕራንክ ባየ ቁጥር የሚቆም ወደዚያው፣ ቁም ነገር ላይ የሚያተኩርም እንዲሁ ወደ ቁምነገር ይሳባል። ይሄ የሰው ልጅ ልቦና ስሪት ነው። ለዚያም ነው የማህበራዊ ሚዲያ ፕላትፎርሞች አልጎሪዝም አጠቃቀማችንን የሚያነፈንፈው። ደጋግመን የምናየውን ወይም ትክ ብለን የምንቆይበትን ይዘት እያጤነ ተመሳሳይ ይዘቶችን ያቀርብልናል።

ይህንን እንያዝና እራሳችንን እንታዘብ። ቁርኣን መቅራትና ማዳመጥ ላይ እንዴት ነን? ንባብ ላይስ? ደዕዋዎችን፣ ዱሩሶችን፣ ጠቃሚ ፕሮግራሞችን ለመከታተል ሶብር አለን ወይ? እነዚህን ወሳኝ ነጥቦች ስናስብ ብዙዎቻችን በጣም እንደተዘናጋን የምንግባባ ይመስለኛል። መፍትሄው አጭር ነው። ባይሆን ቁርጠኝነት ይጠይቃል። ዛሬ ነገ ሳንል ወደ መስመር መግባት። ቁርኣን እንቅራ፣ እናዳምጥ፣ ቋሚ የደርስ ፕሮግራም ይኑረን፣ ቁም ነገር የያዙ ኪታቦችንና መፅሀፎችን እናንብብ። ወደ መስመር ለመግባት ትንሽ ጊዜ ነው የሚጠይቀን። ስንቆይበት ጣእሙን እናገኘዋለን። ያኔ ስላለፈው ጊዜ እንቆጫለን። የልብ እርካታ፣ የአእምሮ ሰላም ይመጣል።

ሌሎችም ኸይር ስራዎች ላይ እንዲሁ ነው። ገንዘቡ እያላቸው ከሶደቃ፣ ከዘካ የራቁ ሰዎች ወደ መስመር የመግባት እድላቸው እየራቀ ነው የሚሄደው። መስጠትን ሲዳፈሩ፣ በመስጠት ውስጥ ያለውን ደስታ ሲያዩት እየለመዱት ይሄዳሉ። አመት ጠብቀው ዘካቸውን አስበው ለመስጠት ተራራ አይሆንባቸውም። ኸይር ስራዎችም ላይ አይታጡም።

ሸሩም ላይ እንዲሁ ነው። ዝሙቱ፣ ስርቆቱ፣ ነፍስ ማጥፋቱ፣ ዘረኝነቱ፣ ማጭበርበሩ፣ ወዘተ. የሚጨንቀው መጀመሪያ አካባቢ ነው። አንዴ ከተለመደ ሁሉም ኖርማል ይሆናል። እንዲያውም ጀብድ ይሆናል። ጨዋነት ፋራ መሆን ይመስለዋል። ጥንቡ ዘረኝነት ለሱ ልዩ መአዛ አለው። መቼስ ከዚያ በኋላ ዘረኝነት ብሎ አይገልፀውም። የራስ ምን አይገማም ይባላል። ስለዚህ? እያሸሞነሞነ ይገልፀዋል። ከወሮ በላ ጋር ተሰልፎ መዝረፍ፣ ማገትና ነፍስ ማጥፋት ዘመኑን የቀደመ ንቃት ይሆንና ይህንን መፀየፍ ደግሞ ማንቀላፋት፣ ወደ ኋላ መቅረት ተደርጎ ይያዛል። ሰው አንዴ ጥፋትን ከተላመደ መነፅሩ ይንሸዋረራል፣ መለኪያው ይዛባል። ተሳስተሃል ብትለው የስድብ ያህል ነው የሚቆጥረው።

ባጭሩ የኸይር ስራ አንዱ ሽልማቱ ወደ ኸይር ማሻገሩ ሲሆን የጥፋት አንዱ ቅጣቱ ይበልጥ ወደሚያስቀጣ የከፋ ጥፋት ማሻገሩ ነው። የኑሮ ዘይቤያችንን፣ የጊዜ አጠቃቀማችንን ወደተሻለ መቀየር ከፈለግን ቅድሚያ ከልባችን፣ ከራሳችን ጋር እንስማማ። ወደዚያም ወደዚህም የምትጎትተን ነፍሲያችን ላይ እናምፅ። እምቢ በቃሽ እንበላት። ለውጥ ከውስጥ ነው የሚጀምረው። ውስጣችን ካላመነ ለውጥ በምኞት አይመጣም።
=
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://www.tg-me.com/IbnuMunewor
https://www.tg-me.com/IbnuMunewor
Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)
Photo
ኡስታዝ ሆይ! ከምትጠበቁበት ተገኙ
~
ኡስታዝ ሆይ! አደራህን በየትኛውም መልኩ እጅህ ላይ የደረሰን አማና አትብላ! ከሙናፊق ምልክቶች ውስጥ አንዱ ሲታመኑ መክዳት እንደሆነ የምታውቀው ነው። የሰዎችን አማና መክዳት፣ በደዕዋ ስም ሰብስቦ ለግል ጥቅም ማዋል አንዳንድ ኡስታዞች የሚከሰሱበት ወንጀል ነው። ፅሁፌ በዚህ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው።

በዚህ ዘመን አላህን ከመፍራት የራቁ፣ ያለ አንድ መረጃ እንዲሁ ቡድናዊ ጥላቻ የወለዳቸው የስም ማጥፋት ውንጀላዎች በስፋት እንዳሉ ይታወቃል። ይሄ ቡድንተኝነት ያመጣብን ልክፍት ነው። ይሁን እንጂ ይሄ ማለት የተረጋገጡ ጥፋቶች የሉም ማለት አይደለም። በተለያየ መልኩ እጃቸው የገባን አማና የካዱ፣ በተደጋጋሚ በደዕዋ ስም ገንዘብ እየሰበሰቡ ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ፣ ወዘተ. አካላት አሉ። እነዚህ ጥፋቶች ሲደጋገሙ፡

* የሌሎችንም ዱዓት ስም የሚያጠፉ፣ ተአማኒነትን የሚያሳጡ ስለሚሆኑ አጠቃላይ ደዕዋው ላይ የሚኖራቸው ጠባሳ ከባድ ነው የሚሆነው።
* በዱዓት መካከል መራራቅን ስለሚያስከትሉ እና የትብብር መንፈስን ስለሚጎዱ በዚህም በኩል ደዕዋው ላይ ትልቅ ጉዳት ይኖራቸዋል።
* ከዚህም ባለፈ እንዲህ አይነት አመሎች ሌሎችም ዱዓት ተመሳሳይ ጥፋት ላይ እንዲወድቁ በር ሊከፍቱ ይችላሉ።

ስለዚህ በየትኛውም ባልተፈቀደ መልኩ የሰዎችን ሐቅ ወደራስ ኪስ ማድረግ እና ዲን በማስተማር ያገኘነውን መልካም ስም ላልተገባ ነገር ማዋል አላህን ልንፈራበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ስንቶች አሉ በኡስታዞች አማናቸውን ተክደው "አሁን ብናገርስ ማን ያምነኛል?" ብለው እያለቀሱ ዝም ያሉ። እንዲህ አይነት ነገር ሁሌ ተሸፍኖ አይቀርም። በሂደት ውርደትን ያከናንባል፣ መንናቅንም ያመጣል።

እዚህ ላይ ልጅ እያለሁ የገጠመኝ አንድ የማይረሳኝ ክስተት ላንሳ። አንድ ከወረዳችን አልፎ በጣም ብዙ የወሎ አካባቢዎች ዘንድ ስሙ የገነነ፣ የተናገረው መሬት ጠብ አይልም ተብሎ በወልይነት የሚታምንበት ሸይኽ ነው ባለ ታሪኩ። ስሙን ብጠቅስ ብዙዎች ያውቁታል። በዙሪያው የነበሩ ሰዎች እንዴት እንደሚሽቆጠቆጡለት ልነግራችሁ አልችልም። በአቅራቢያ ፍርድ ቤት ስለሌለ ለቀበሌ ሸንጎ ሁለት ሰዎችን በመሬት ጉዳይ ከሶ ነው የቀረበው። ተከሳሾች አንዲት ሴት እና አንድ ወንድ ናቸው።

ሴቷ ፡ "ጭራሽ ወልይ ነኝ እያለ እያስፈራራ ንብረታችንን ሊነጥቀን ነው የተነሳው! ይሄ ወንበዴ ነው!" እያለች ታዳሚው ለመስማት እስከሚሳቀቅ ድረስ እየጮኸች ትናገራለች። ወላጅ አባቴ ተሸማቆ ጥግ ሲይዝ አየሁት።
ወንዱ ተከሳሽ በጣም የተረጋጋ ነው። ለሽህየው ያለው ፍራቻና አክብሮት አሁንም እንዳለ ያስታውቃል። ድምፁን ዝቅ አድርጎ፡ ''ወላሂ አሕመድ! በ1980 (?) የመስኖ መሬቴን ወስደውብኝ ፈርቻቸው ዝም ብያለሁ። አሁን ደግሞ የእርሻ መሬቴ ላይ ነው የመጡብኝ" አለው ለአባቴ።

ችሎቱን የሚያዩት የቀበሌ ሰዎች ለነዚያ ሁለት ሰዎች ፈርደዋል። የሽሁን ክስ አልተቀበሉም። እንዲያውም በሽሁ ተደጋጋሚ ክስ እንደተሰላቹና ከዚህ በኋላ ይህንን የመሬቱን ጉዳይ ደግመው እንደማያዩ ተናገሩ። ሸህየው "እና እናንተ የሰማዩን ጉዳይ ነው የምታዩት?" ብሎ ሲሳለቅ አጃቢዎቹ ሳቁ። ከዚህም ውጭ ደስ የማይሉ ንግግሮች ከሸሁ ይወጡ ነበር። ብዙው ታዳሚ ፍርሃት ባረበበበት ዝምታ ቢያሳልፍም ያንገሸገሻቸው ሰዎችም ነበሩ። "መከበር በከንፈር" ነው ነገሩ።

የፈለገ የማይደፈር የሚመስል ስም ቢኖርህ እንኳ በክፉ ግብርህ ክብርህን ታጣለህ ልልህ ነው ምሳሌውን ያመጣሁት። መቼስ የሱፍያ ወልዮች ህዝብ ዘንድ ያላቸው አይነት ቦታ እንደማይኖርህ አታጣውም። ልብ በል! ጥፋትህ ሲደጋገም የሚያምንህ እየቀነሰ፣ የሚንቅህ እየበዛ ነው የሚሄደው። ይሄ ስለ ዱንያው ስናወራ ነው። ነገ በቂያማ ቀን በፍጥረታት ሁሉ መሀል ከመዋረድ አላህ ይጠብቀን።

ፅሁፌን በአንድ ነጥብ ልቋጭ! የሰዎችን አማና ለግል ጥቅም በማዋል ስማችሁ በተደጋጋሚ የተነሳባችሁ ኡስታዞች! ለመስጂድ፣ ለመድረሳ፣ ለደዕዋ #በስማችሁ ገንዘብ ለመሰብሰብ አትሞክሩ። ይቅርባችሁ። ክብራችሁንም ጠብቁ፣ ሰውንም አታስወንጅሉ። አስፈላጊ ሆኖ ካገኛችሁት ስራውን ሌሎች ይስሩት። እናንተ ስማችሁን አርቃችሁ እንዲሁ በቅስቀሳ ብቻ አግዙ። አንዳንዴ ሰው ይሳሳታል። ጥፋትን መታወቂያ ልማድ ማድረግ ግን ያስንቃል። እወቁበት። ወላሁ አዕለም።

ማሳሰቢያ፦

* ህዝብ ዘንድ የምትታመኑ እና አማናችሁን የምትወጡትን እየነካሁ አይደለም። እናንተ መታመናችሁን ለበለጠ ኸይር ስራ ልትጠቀሙበት ነው የሚገባው። ውለታችሁም ለብዙ ሰው ነው። አንዳንዴ በአጥፊዎች ላይ የሚሰነዘረው ወቀሳ ጤነኞችን እንዳያሸማቅቅና እንዳያስበረግግ ያስፈራል።
=
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://www.tg-me.com/IbnuMunewor
https://www.tg-me.com/IbnuMunewor
የገዝዛ ጉዳይ
~
የገዝዛ ጉዳይ ለጊዜውም ቢሆን ትልቅ ደስታ ይሰጣል። ከሰሞኑ ጦርነቱ ቆሞ ገዝዛውያን አንፃራዊ ሰላም ማግኘታቸው ከዚህም በተጨማሪ እርዳታ መግባቱ ትልቅ ነገር ነው። ስምምነቱ አሁንም ስጋት ያጠላበት ነው። ለዚህም ዋናው ምክንያት ይሄ በትራምፕ የቀረበው ስምምነት አንዳንድ አንቀፆቹና እና አፈፃፀማቸው ግልፅነት የሚጎድላቸው መሆናቸው ነው። ያንን ተከትሎም በተለይ ሶስት ነጥቦች መግባባት ላይ የሚደረስባቸው ይሆናሉ ወይ የሚለው አሁንም አጠራጣሪ ነው።

1ኛ፦ ጊዜያዊ ስምምነቱን ተከትሎ ኢ $ ራኤል ከያዘቻቸው የገዝዛ አካባቢዎች ቢጫ ወደተቀለመው አፈግፈጋለች። ነገር ግን ይሄ በቢጫ የተቀለመው ክፍል ከጠቅላላው የገዝዛ ስፋት 58% የሚሸፍን ነው። ከስምምነቱ ፍፃሜ ላይ የእውነት ይህንን ክፍል ለቃ ትወጣለች ወይ? ሃገሪቱ ከበፊት ጀምሮ የሚከሰቱ ጦርነቶችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ግዛቷን እያሰፋች ነው የመጣችው።

2ኛ፦ በስምምነቱ ሃማS ሙሉ ትጥቁን እንዲፈታ ይጠበቃል። የእውነት ይሄ ጉዳይ ይፈፀማል ወይ? አጠያያቂ ነው። አሁንም ቡድኑ በዚህ ነጥብ ላይ ፈቃደኛ እንዳልሆነ እየገለፀ ነው።
3ኛ፦ በስምምነቱ ፍፃሜ ላይ ገዝዛን በሚያስተዳድረው አካል ውስጥ ሐማS ምንም ቦታ እንደማይኖረው ተገልጿል። ይልቁንም ተዋጊዎቹ ወይ ጠቅልሎ ወደ ውጭ መውጣት፣ አለያ ደግሞ ምህረት ተደርጎላቸው በሰላም መኖር ብቻ ነው የቀረበላቸው አማራጭ። ይህ ራሱ ለቀረበው ስምምነት ሌላ ማነቆ የሚሆን ይመስላል።

እነዚህ ሶስት ነጥቦች ላይ አለመግባባት ችግሩን ወደነበረበት እንዳይመልሰው ያሰጋል። ለጊዜው የኢ $ ራኤል ድብደባ ቆማል። የእርዳታ እህሎችና ቁሳቁሶች እየገቡ ናቸው። ከፊል ተፈናቃዮች ወደ ወደሙ መኖሪያ ሰፈሮቻቸው እየተመለሱ ነው። ከፊሎቹ አካባቢዎቻቸው አሁንም በኢ $ራኤል የተያዙ በመሆናቸው መመለስ አልቻሉም።

=
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://www.tg-me.com/IbnuMunewor
https://www.tg-me.com/IbnuMunewor
2025/10/27 15:09:57
Back to Top
HTML Embed Code: