ፍቅር በዚያ ወራት

፤፤፤ ሚካኤል.አ ፤፤፤

(ክፍል 1)

ስሜ ንፁህ ይባላል ። የስሜ እዳ አለብኝ። እንኳን ለሰው ልጅ ለመላዕክት እንኳ ያልተገባ መጠሪያ መያዜን ሳስበው እሸማቀቃለሁ።
ከክፍል ጓደኞቼ ጋር እየጨፈርን.. .ሺሻ እያጨስን በምናሳልፋቸው ወቅቶች ስሜን የሚጠራኝ ሰው ባይኖር ስል እመኛለሁ።
ደግሞ ማንም እንደሚያውቀው የትምህርት ቤት ህይወት (ላይፍ ይሉታል ጓደኞቼ በቋንቋቸው) ፈታኝ መሰናክሎች አሉት ።
ጥሩ ፋሽን የማይለብስ ...የማያጨስ ...የማይጨፍር ተማሪ ፋራ ተደርጎ ይቆጠራል። ከማህበራዊ ህይወት ገሸሽ ይደረጋል። ከዚህ ክበብ መውጣት የማይፈልግ ሰው ደግሞ በሰዎች ፍላጎት መሾር ይጀምራል።
ስጨፍር የሰው ነኝ...ከወንዶች ጋር ስላፋ የሰው ነኝ...አጭር ቀሚስ አድርጌ እንደ እሳት የሚጋረፉ ወላፈን ጭኖቼን ሳሳይ የሰው ነኝ።
ስስቅ የሰው ነኝ ። ሁሉ ነገሬ አርቴፊሻል !
ከዚህ ግብግብ ስወጣ ግን ጥያቄ አለብኝ።
የህሊናዬን ጥያቄ ማፈን ስለምፈልግ መጠጥ እጠጣላሁ።
ለምን ትጨፍሪያለሽ?
ለምን ከወንዶች ጋር የውሸት ትስቂያለሽ?
ለምን ትቅሚያለሽ?
ለምን ታጨሻለሽ?
ከዛ መጠጣት.. . መጠጥ ደግሞ ጀንትል ያደርገኛል። ህሊናዬን እናትህን እለዋለሁ ።
እጠጣለሁ.. .እጨፍራለሁ...እቅማለሁ...አምራለሁ ...
እንቅልፍ ይወስደኛል።
ስተኛ ም ዝም አልልም...ተኝቶ ማሰብ ይቻላል ወይ? ለምትሉኝ ሰዎች መልሴ ድብን አድርጎ ማሰብ ይቻላል የሚለው ነው።
የማስበው ዶክተር ዘካርያድን ነው። ምርጥ መምህሬ ... ማኔጅመንት ያስተምረናል...ራሴን ማኔጅ ማድረግ ለተሳነኝ ሴት የድርጅት ማኔጅመንት መማር ግን አያስቅም?
ዛኪ መደበቂያዬ ነው። በሱ ክፍል እኔን ጨምሮ የብዙ ሴት ጓደኞቼ አይን ይስለመለማል ። የሄዋን ዘር ይውደድህ ተብሎ የተመረቀ መምህር ።
አይቅለበለብም...አይቸኩልም...
እርጋታው...እውቀቱ.. .ንፅህናው (ፍንትው ያለ ነጭ ሸሚዝ የሚያደርግ ብቸኛው መምህር እኮ ነው)... ሁሉም ባህሪያቶቹ የሴትን ልጅ ልብ መክፈቺያ ቁልፎች ናቸው።
ቆፍጣና ወንድ !
ከትምህርት በተረፈው ሰዓት ማህበረ ቅዱሳን እንደሚያገለግል ሰምቻለሁ።
እሱ ሰላም ሲለኝ ሀጥያቴ ተሰርዮ የተቀደስኩ ይመስለኛል። ሳቁ.. .ጨዋታ አዋቂነቱ አይምጣብኝ ። በመሀል ጣል የሚያደርጋት ስብከት ለኔ የህይወት ስንቅ መሆኑን ማን በነገረው?
እንደ ሌሎች ቀለብላባ ወንድ መምህራን ለሴት ልጅ ባትና ዳሌ እጅ ስለማይሰጥ የፍቅር ፋኖስ ልቤ ውስጥ ተለኮሰ!
ቡም !
አዲስ ወጋገን...አዲስ ፍኖት ተለኮሰ !
ከእንቅልፌ ስነሳ ትራሴን ጭምድድ አድርጌ አቅፈዋለሁ። ዛኪ ነፍስያዬን ያግላታል። ሰውነቴን ሲተኩሰኝ እሰማዋለሁ። ትንፋሹ ከሱ ጋር ሳይሆን ከኔ ጋር ያድራል።
ከሁለት ሰዓታት በኋላ አይኑን ማየቴን ሳስበው ሀሴትን አደርጋለሁ።
ሆኖም ከደስታዬ ሲለጥቅ አንድ ጥያቄ ገረፍ አድርጎኝ ያልፋል።
ኪሩ ከዚህ ሁሉ አፍቃሪ ሴቶቹ መሀል እኔን እንዴት ሊመርጠኝ ይችላል?
ከኔ በላይ ቆንጆ ሴቶች ደግሞ አሉ። ልቤ ን ግን አያክሉትም...ልቤ ተራራ ነው። ማንንም ማንበርከክ ...ማንም እንዲያሸረግድልኝ የሚያደርግ ቅብዓ ቅዱስ አለኝ።
ሰለዚህ እሱን አማልሎ ወጥመዴ ውስጥ የማስገባበት ብልሀት ወጠንኩኝ...ትምህርት ቤት ስሄድ እሱን እንደምረታው ለራሴ እየነገርኩት ነው።
ንፁህ ታሸንፊያለሽ ! ብሎ የሚፎክር ጀብደኛ ልብ አለኝ።
ዶክተር ኪሩ መጣሁልህ !

(ይቀጥላል...)
ዛሬ ምሽት 12 ሰዓት አዲስ ዋልታ ላይ ይጠብቁን
ሲሄድ በመንገድ
ሲጓዝ ሲረማመድ
ነቅሎ ከጣላቸው
እሾህ እንቅፋቱን
ዘሎ ካለፋቸው
ጉድባ ና መዓቱን
ሠሪ ካልፈለገ ...
ከ'ሱ መዳፍ በቀር
የጀግና ትርጉሙ
ይሄ ነው ሲነገር !
(ሚካኤል አ)
አሁን መጉዳቷ ነው
ልቧ ብላል ውልቅ!
እኔን ልታሳቅቅ...
ካይን የራቀ በሚል
የሰነፎች ብሂል…
'ርቆ ለመዘንጋት
ልፊ ብሎ ፈጥሯት
መሄድ መኮብሏ ...
ጓዟን ማንጠልጠሏ
መራቋ ከቀዬው...
መውጣቷ ከመንደር
ልቤ ቤቷ መሆኑ
ካልገባት በስተቀር
እንዴት ትሄዳለች ?
ሸሽቶ ድል ለመንሳት
ይልቅ ለልቤ ቤት…
ኪራይዋን መክፈሌን
ሰዎች በነገሯት !!
===
(ሚካኤል . አ)
ይናፍቀኝ ነበር
(ገጣሚና ሰአሊ ገብረክርስቶስ ደስታ)
...

ዞሮ ዞሮ ከቤት
ይላል የኛ ተረት ::

አቧራው ፀሃዩ ይናፍቀኝ ነበር፤
አፈሩ ጠጠሩ ይናፍቀኝ ነበር::

የመንደር ጭስ ማታ…….
ይናፍቀኝ ነበር የሳር ቤት ጥቀርሻው
መደቡ ምሰሶው፤
ማገሩ ግድግዳው፤ አጥሩና ጥሻው::

የፈራረሰ ካብ………
ቀጭን ጠባብ መንገድ በመንደር የሚሮጥ፤

ቅጠል የሸፈነው፡
ሳር ያለባበሰው፤
እነዚህ እነዚህ ይናፍቁኝ ነበር፤

የተቆላ ቡና ፤
የሚወቀጥ ቡና፤
የጎረቤት ቡና አቦል ሁለተኛ፤
የተረጨ ቆሎ የሚያርቅ መጋኛ፤
የሚጨሰው ዕጣን………

እንጀራ በመሶብ ወጥ የፈሰሰበት
ያገልግል እንጀራ፤ የሚቧጠጥ ፍትፍት፤
የክክ ወጥ የሽሮ፤
የስጋ የዶሮ፡፡

ይናፍቀኝ ነበር ቅራሪ ጉሽ ጠላ፤
ይናፍቀኝ ነበር ፊልተር ዞማ ኮላ፡፡

ያገራችን ድግስ……..
ከበሮው ጭፈራው፤
ዝላዩ እስክስታው፤ ስካሩ ሁካታው፡፡

ትርክምክሙ ነገር ግፍያው ትንቅንቁ፤
ኳኳታው እርግጫው ዘፈን ድብልቅልቁ፡፡

“አሸወይና ወይና“
“እስቲ እንደ ጎጃሞች“
“አሲዮ ቤሌማ… ኦሆሆ አሀሀ…"
የቄስ ትምህርት ቤት
የህፃናቱ ድምፅ፤

“ሀ...ሁ…ሂ…ሃ…“ ዜማ ነበር የናፈቀኝ
የጽጌ ጭፈራ ነበር የናፈቀኝ፡፡

ከበሮ ፅናፅል፤
ሆሳዕና ጥምቀት፤
ፋሲካ ገና ሁዳዴና ስግደት፤
ቡሄ ሆያ ሆዬ፤
የእስላሞች አረፋ የኦሮሞች ሸጎዬ፤
የቁልቢ ገብርዔል፤
ልደታ፤
ፍልሰታ፡፡

ዕንቁጣጣሽ ነበር መስከረም ሲጠባ፤
አውቆ የበቀለ ወፍ ዘራሽ አበባ፡፡

ለምለም አረንጓዴ…
ያልተጠበቀ መስክ ከብት የሚግጥበት፤
የደመና ግላጭ የሚጫወትበት፡፡

ሌላም ብዙ ነበር…
ሌላም ….ደግሞ ሌላ…..፡፡

ያገሬ ሰው ነበር እኔን የናፈቀኝ፤
ጠይም ቆዳ ነበር እኔን የናፈቀኝ፤
ቀይ ዳማ ነበር ጥቁር ቆዳ ነበር፤
ቁርንጫጭ ከርዳዳ፤ ዞማ ጠጉር ነበር፤

ያገራችን ቋንቋ…
ያገሬ ሙዚቃ ያገራችን ዜማ፤
ጥበብ እጀ ጠባብ ያገራችን ሸማ፤
ነበረ ናፍቆቴ ለሁሉም…
ለሁሉ፡፡

ለሸዋ፤ ለወሎ፤ ለትግሬ፤ በጌ ምድር፤
ለጎጃም ወለጋ፤ አሩሲ ኢሉባቡር፤
ኤርትራ ገሙጎፋ፤
ሲዳሞና ከፋ፡፡
ለሁሉም ለሁሉ ነበረ ናፍቆቴ፤

አለብኝ ትዝታ
ዘመዶቼ ሳሙኝ፤
ጓደኞቼም ጋብዙኝ፤
ሊስትሮ ጨብጠኝ::

ባለጋሪ ንዳ መንደሩን አሳየኝ፤
ያገሬ ልጅ ቆንጆ “ቤት ለእንግዳ በዪኝ“፡፡

አለብኝ ትዝታ…..
አዲስ አበባ ላይ ነበረ ናፍቆቴ
መናገሻ ነበር፤ እንጦጦ ነበረ፤
ኤረር ጋራ ነበር፤ ዝቋላ ነበረ፤
ጃን ሜዳ ነበረ፤ ኮተቤ ነበረ፤
ገፈርሳ ነበረ፤ ጉለሌ ነበረ፤

አዲሱ ከተማ…
“መርካቶ ዲጂኖ ችምችም ያለው መንደር“
ከተማው እንብርት ደጃች ውቤ ሰፈር
የቸርችል ጎዳና፤
የባቡሩ ጣቢያ፤
ቢሾፍቱ ነበረ፤ ናዝሬት፤ ሞጆ አዋሽ::
ድሬዳዋ ነበር፤
ዓለምማያ ነበር::

ሐረርጌ ነበረ የተወለድኩበት
እናትና አባቴን ጥዬ የሄድኩበት::
የሚካዔል ጓሮ…
ሐረርጌ ነበረ፡፡
ዞሮ ዞሮ ከቤት…
አገሬ ነበረ እኔን የናፈቀኝ::
ኢትዮጵያ ነበረች♥️
#ከትናንትና መልስ !
።።።።።
(ሚካኤል አስጨናቂ)

#ይሄ በውብ አፀድ የተዋበ መንገድ
ትናንት ካንቺ ጋራ አብረን የሄድንበት
ለካ በአበቦች ዙሪያው ተሽሞንሙኗል
ትናንት አልታየኝም ለአይኔ ተሰውሯል።
አይገርምም?
ደግሞም ይሄ ጉድጓድ
ትናንት አደናቅፎ እግሬን የለከፈኝ
ህመሙ አይሎ ...
ብቻዬን ስጓዝ ነው ፣ ጣቴን ያነዘረኝ።

መንገዱስ ብትይ?
አውላላው ጎዳና
እድል ስኬታቸው ተስፋቸው ኮስምና
ከራሳቸው ሰብረው ሀዘን ላይ የዋሉ
ምስኪናን እንዳሉ.. .
ትናንት ሳላስተውል ዓይኔ አይቶ ሲዋሸኝ
ዛሬ ስመለስ ነው ፣ ህይወታቸው ከፍቶ ልቤን የሰበረኝ።

ለካ በመንገዱ በዙሪያው ዳርዳርታ
ከአፀዱ ከተክሉ ከአበባው ሽውታ
ባሻገር ስቃኘው ሸጋ የሚመስለኝ
የፈራረሰ ነው፣
ስለ እውነት ገረመኝ!

ይገርመኛል በጣም
ሽኩኔታ ገፊ ጎማ አሽከርካሪ
ዥንጉርጉር መኪና ለእርዳታ ጥሪ
ጥጥ ፈታይ ሴትዮ ፣ የሸማ ደዋሪ
ቆንጆ ፣ ቆንጆ ሴቶች በውበት አስካሪ
ዘራ ማስታወቂያ
ብዙ ብዙ ታክሲ ፣ ብዙ ብዙ ግፊያ
ብዙ ብዙ ጩኸት.. . ሕገ - ወጥ ገበያ
የእየሱስ ሰባኪ…
ቃላቶችን ተንታኝ
ጥቅሶችን ሰካኪ
መጥሀፍ የሚገልጥ ፣ ጯሂ ባደባባይ
ትናንት ይሄን ሁሉ አይኔ ኖሮ ሳያይ…
:
ዛሬ ብትቀሪ ፣ በሄድንበት መንደር
አውቀዋለሁ ባልኩት
በማላውቀው መንገድ ፣ አለፍኩ ስጠራጠር፤
ለካስ ካንቺ ውጭ አይታየኝም ነበር!
ጎዳናው ላይ ...
ስንኩል ሽባነቱን ለሠማይ የሚያሳይ
"እጅ ከሰጠኸኝ ልመና አቆማለሁ" ብሎ እየማለ
አብዝቶ የሚያለቅስ ፥ አንድ ለማኝ አለ።

በዛ ጎዳና ላይ
አመዱን ነስንሶ
እንባ እየረጨ
የጠየቀው ለማኝ
ለበረከት ታጨ።
:
ይኸው የእግዜር ምህረት !
በጥልቅ እንቅልፍ ጥሎ ~ እጅ አበጃጀለት
ላፈሰሰው እንባ ፣ ለጠለየው ጠሎት መልሱ ተላከለት።
:
እርሱ ግን ሲነቃ...
እንዲህ ሲል ቀጠለ...
በልቅሶ በሲቃ ፣
:
"መንገድ ላይ ወድቄ
ተዘከሩኝ እያልሁ ~ በስምህ ስጣራ
ጤነኛ ነው ብለው...
ፈራንካ ለመስጠት ~ ሰው እንዳይኮራ
ይህን አስብበት ~ ጌታ ሆይ አደራ።
.
እጅህ ያለ ገንዘብ
የለውማ ረብ !!”

ሚካኤል አ
#እሷና ወንዝነት
(ትርጉም ፦ Khalil Gibran)
አለ ፍርሀት በወንዝ እውነት
በባህር ውስጥ መቅረት።
እሷም እንደዚህ ናት ...
ከላይ ስትወርድ ፣ ከተራራው ቁልቁል
ከተማ 'ሚያካልል ...
አለ ውቅያኖስ ከመንደሩ ማዶ
የብስም አይሆን ነገር ወደኋላው ሄዶ
አትችልም መሻገር ...
እጆቿን ከፍ አ'ርጋ ፣ ከማመን በስተቀር ፤
ማመን ትልቅነት
አቅምን መገመት
ሰው ሲሆን ተፈጥሮህ
ያድናል ከመስመጥ።
ሆኖም ለወንዝነት
ልብህ ከተሰጠ ለዚህ ትልቅነት
ፍርሀት አይደለም
በዛው ሰርጎ መቅረት
ውረድ.. ፍሰስ.. .ክነፍ
ግባ ከሰፊው አምድ ፣ ሳትሰጋ ተንደርደር
ፍርሀት ሲሞት ነው ...
ባህር ነህ ተብሎ ፣ ላንተ የሚነገር!

(ሚካኤል.አ)
#የመብረር ነፃነት !
(ሚካኤል አስጨናቂ)
.
"አልበር እንዳሞራ
አልበር እንደ ንስር"
በሚሉት ሙዚቃ
በሚሉት ዘፈን ስር
ሰው ሆኖ ተፈጥሮ መብረር የከጀለ
መራመድ ያስጠላው ያንዱ መሻት አለ።
.
"አልበር እንዳሞራ
አልበር እንደንስር"
በሚሉት ሙዚቃ በሚሉት ዘፈን ስር
ብበር እንዳሞራ ብበር እንደንስር
ምድር ላይ ያለውን ከላይ ብመነጥር
ላስከፉኝ አናቶች ድንጋይ ብወረውር
ብለው የሚመኙ ፍትህን የሚሉ
ተበዳይ ስንኞች በቅኔ ውስጥ አሉ።
.
"አልበር እንደንስር
አልበራ እንዳሞራ"
በሚሉት የዘፈን የስንኝ ቅመራ
ፈጣን ተጓዥ ሆኖ በክንፉ በረራ
የእትብቱን ሳይለቅ ዓለሙን ሊያጣራ
ነፃነት ፈልጎ ጮሆ የሚጣራ
ሀገሩን የሚወድ!
አንድ ገጣሚ አለ ከተጓዦች ተራ።
👇
(ፎቶው ግጥሙን የሚገልፅ ሆኖ ስላገኘሁት ከጓድ Ephi Mack የፌስቡክ ገፅ የተወሰደ ነው። )
2024/05/14 23:01:17
Back to Top
HTML Embed Code: