Telegram Web Link
የምርምር ስራዎች ችግር ፈቺ ፣ ከማህበረሰቡ የልማት ፍላጎትና ከሃገራችን የትኩረት አቅጣጫ ጋር የተጣጣሙ መሆን እንዳለባቸው ተገለጸ
******************************************************************************************-
(መስከረም 6/2014ዓ.ም) የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከጅማ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ከመስከረም 6-7/2014ዓ.ም የምርምር ስትራቴጂ እና የትኩረት መስክ ረቂቅ ሰነድ ላይ ምሁራንና ባለ ድርሻ አካላት በጅማ ዩኒቨርስቲ የትሮፒካልና ተላላፊ በሽታዎች ምርምር ማእከል ውይይት እያካሄደ ይገኛል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕ/ር አፈወርቅ ካሱ እንደገለፁት በኢትዮጵያ የምርምር ታሪክ የእድሜዉን ያህል ዉጤት ያላስመዘገበ በመሆኑ ሃገራዊ የምርምር ስትራቴጂ በአዲስ እይታ ሊቃኝና የምርምር የትኩረት መስኮችን በልዩ ትኩረት ሊቀረጹ እንዲሁም በተለያየ ተቋማት ተወስደዉ በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡
በሳይንስና ከፍተኛ ትምህር ሚኒስቴር ለወራት የሃገራችን ምሁራን ከበርካታ ተቋማት ተመርጠው አንድ ላይ ሃሳባአቸዉን አደራጅተዉ ሰነድ እንዲያዘጋጁና በሰነዱ ዉስጥ በተመላከቱ ተግባራት ስለ ምርምር ፣ ስለስትራቴጂ እና በተለያዩ የትኩረት መስኮች ላይ እንዲወያዩ እንዲከራከሩ በማድረግ ጅምር ስራዎች መሰራታቸዉን ገልጸዉ እነዚህ ጅምር ስራዎች በዉስጣቸዉ ብዙ ሃሳቦችንና ስልቶችን የያዙ መሆናቸዉን ፕሮፈሰሩ አብራርተዋል፡፡
“እነዚህ ሃሳቦችና ስልቶች ወደ ስርዓት ተቀይረዉ ተቋማዊ ተደርገዉ፣ ሰፊ የሰዉ ሃይል ተፈጥሮላቸዉ፣ በቅንጂት ተሰርተዉ ዉጤት እንዲያመጡ ይፈለጋልበኢትዮጵያ በግብርና፣ በእንስሳት ሳይንስ ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በጤናና በሌሎችም ረጅም አመት ያስቆጠሩ የምርምር ማእከሎች አሉ እነዚህም የኢትዮጵያን አስተዋጽኦ ለአለም ያሳዩ ናቸዉ ” ብለዋል ፕሮፌሰሩ ፡፡
ነገር ግን ከኢትዮጵያ ልማትና እድገት አንጻር ሲታይ በሚፈለገዉ ልክ አይደለም ስለዚህ በዚህ ዘመን ያለን ኢትዮጵያዊን የስራ ሃላፊዎች፣ ምሁራን ይህ ሊያሳስበን ይገባል ሁሉም ተሳታፊዎችና ምርምር የሚመለካታችሁ ሁሉ በቅንጅት አብሮ መጓዝና መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሙሉ ነጋ በበኩላቸዉ በአስተላለፋት ቁልፍ መልእክት በከፍተኛ ደረጃ የተማረ የሰው ሃይል እና እዉቀት ማመንጨትና ማሻሻል ለእድገት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዉ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለይ የሰዉ ሃይል በማፍራት እዉቀት በማመንጨትና በማሰራጨት ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡
ጎን ለጎንም በትምህርትና ስልጠና፣ ምርምር እና ኢኖቬሽን ሚዛናቸዉን በጠበቀ መልኩ መሰራት አለባቸዉ ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታዉ፡፡
በውይይቱ የሚሰሩ የምርምር ስራዎች ችግር ፈቺ ፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ከማህበረሰቡ የልማት ፍላጎትና ከሃገራችን የትኩረት አቅጣጫ ጋር የተጣጣሙ መሆን እንዳለበት ተገልጿል ፡፡
በተለይም በቀጣይ 10 አመታት ግብርና፡ ማንፋክቸሪንግ፡ ማእድን፡ ቱሪዝም፡ ዲጅታል ቴክኖሎጂ፡ ትምህርት፡ ጤና እና አስተዳደር፣ ደህንነትና ቀጠናዊ ትስስር በአገር ደረጃ የተለያዩ የትኩረት መስኮች ሲሆኑ በእነዚህ የትኩረት መስኮች ላይ የመነሻ ፁሁፍ ቀርበው ውይይት ተካሂዷል፡፡
የወርክ ሾፑ አላማ በኢትዮጵያ የምርምር ስትራቴጂ እና የምርምር ትኩረት መስክ ረቂቅ ሰነድ በምሁራንና በባለድርሻ አካላት ማስተቸትና ግብአት ማሰባሰብ፣ ሃብትና እዉቀትን በማቀናጀት ጥራታቸዉ የተጠበቀና ችግር ፈቺ ምርምሮች እንዲካሄዱና የማህበረሰቡን ኑሮ የሚለዉጡ እንዲሆኑ ማድረግ፣ የሚሰሩ ምርምሮች የሃገሪቱን የልማት አቅጣጫ ትኩረት ያደረገ እንዲሆኑ ማድረግ እና በዉይይቱ የተገኙ ግብአቶችን በማካተት ሰነዱን አጠናክሮ ወደ ስራ ማስገባት ነው ተብሏል፡፡
በወርሾፑ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንትና የምርምር ምክትል ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም በትኩረት መስክ ከተለዩ የምርምር ተቋማት ምሁራን እየተሳተፉ ይገኛል፡፡
በዛሬዉ ዉሎ ከዉይይቱ በተጨማሪ የጅማ ዩኒቨርስቲ የትሮፒካልና ተላላፊ በሽታዎች ምርምር ማእከል እና አውደ-ርእይ የተጎበኘ ሲሆን ፕሮግራሙ ቀሪ ጉዳዮችን በመዳሰስ እና ቀጣይ የስራ አቅጣጫ በመስቀመጥ በነጌዉ እለት ይጠናቀቃል፡፡
2025/07/10 16:48:08
Back to Top
HTML Embed Code: