Telegram Web Link
ብዙዎቻችን ስለ መብት እናወራለን። ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ ስለ መብት በቂ ግንዛቤ የለንም።

የመብትን እውነተኛ ትርጉም በአግባቡ ማወቅ የመብት ጥሰትን ያቀላል።

መብት የሚገባው ለማነው? ይህንን በአግባቡ መረዳትም የራሱ ዋጋ አለው።

የማንወዳቸው ሰዎች ፥ ከእኛ የተለየ እምነት ያላቸው ፥ የተለየ ዝንባሌ ባለቤቶች ፥ ወዘተ መብት እንደሚገባቸው ማወቅም የመብት ጥሰትን ያቀላል።

ስለ መብት መከበር ማውራት ጥሩ ነው። ነገር ግን ስለ መብት መረዳት እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው።

መብት አይነጣጠልም ፥ በዘፈቀደ አይሸራረፍም። አንዱን መብት ጥሶ ሌላ መብት ማክበር አይቻልም። ቢቻልም ወንዝ አያሻግርም።

ሃሳብን በነፃነት የማክበር መብትን ደፍጥጦ የንብረት መብት አከብራለሁ ማለት ተራ ቧልት ነው። የመንቀሳቀስ መብትን አግዶ ስለ እምነት መብት ማወራት ስላቅ ነው።

መብት ለሁሉም ይገባል ፥ ለማንወዳቸውም ሰዎች ጭምር። ደግሞም አይነጣጠልም።


@Tfanos
👍74
ጠዋት ስለ ሴት መብት አውርተው ከሰአት በዲጄ ሊ መልክ መቀለድ ከራስ ጋር መላተም ነው። ትላንት ፌሚኒስት ሴቶችን "መልከ-ጥፉ" ያሉ ሰዎችን ወቅሰው፥ ዛሬ በዲጄ ሊ ላይ አፍ ማላቀቅ ከራስ ጋር መላተም ነው።

ስለ መብት ማውራት እና ስለ መብት ማወቅ ይለያያል። ብዙ ሰው ስለመብት ያወራል እንጂ ስለ መብት አያውቅም።

ሰብአዊ ክብር በየትኛውም ሁኔታ ሊገረሰስ የማይገባ ነው። መብት የማይሸራረፍ ፥ ደግሞም ለሁሉም ሰው እኩል የተገባ ነው። የማይገረሰስ ፥ የማይሸራረፍ ፥ ለሁሉም የሚገባ!

አንዳንድ ሰው ድርጊቱ እና ንግግሩ እርስ በእርስ የሚደባደብ ነው። ፉከራ ከማሰማት ፥ አደባባይ ላይ ቃላት ከማሰማመር በፊት መርህ ተከል እንሁን። እናምነዋለን ከምንለው እሴት ፀብ አንግጠም። ከዛ ውጭ ያለው መንገድ ተራ ግብዝነት ነው።


@Tfanos
10
"ህይወት የሚያስከፍል ግድየለሽነት"
(ተስፋኣብ ተሾመ)
* * *

የሰው ስጋ መብላት ተረት እንጂ እውነት አይመስልም። ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች ህይወታቸው ተረት አከል ነው።

መሐመድ ኦጋ ስደተኛ ኢትዮጵያዊ ነው። እነ መሐመድ ከሊቢያ ወደ ጣሊያን ጉዞ ጀምረው ባህር ላይ አቅጣጫ ሳቱ። ጀልባቸው ነዳጅ ጨረሰ። ሁሉም ነገር ፅልመት ለበሰ።

ረጅሙን ታሪክ እናሳጥረው።

በጀልባው የነበሩ ተጓዦች ቁጥር 17 ነበር። የሚበላ የላቸውም። መመለስም ሆነ ወደፊት መጓዝ አይችሉም። የሚጠጣ ውሃም አልነበራቸውም። የባህሩን ውሃ እንዳይጠጡ ውሃው ጨዋማ ስለሆነ አደገኛ ነው። የባህር ውሃ መጠጣት ሞትን ያፋጥናል። ስለዚህ ምን ቢጠማ ባህር ላይ ሆነው ውሃ ያምራቸዋል እንጂ አይቀምሱትም።

እነ መሐመድ ኦጋ በሜድትራንያን ባህር ላይ ያላቸው ቆይታ እየጨመረ ሲሄድ ውሃ ጥሙ በረታ። ይሄኔ አንዳንድ ሰዎች ጨክነው የባህሩን ውሃ ሊጠጡ ቆረጡ። ገዳይ እንደሆነ እያወቁ "በጥም ከምሞት ውሃ ጠጥቼ ልሙት" አሉ። ትራጄዲውን የሚያበረታው ሽንት ብርቅ መሆኑ ነው።

ተጓዦቹ ምግብ እና መጠጥ ስላላገኙ ሽንት ከባህር ውሃ ቀላቅለው መጠጣት ፈለጉ። "እባክህን ሽንትህን ሽናልኝ" እያሉ ጓዶቻቸውን መለማመን ጀመሩ። እንደ ደህና ነገር "ሽንትህን ተባበረኝ" እያሉ ይለምናሉ።

የባህሩ ቆይታ አስራአንድ ቀን የፈጀ ነው። ከተወሰነ ቀን በኋላ ሰዎች መሞት ጀመሩ። የመጀመሪያውን ሟች አስክሬን ወደ ባህሩ ሲጥሉ ሃዘን እየተሰማቸው ነበር። ቀጥሎ ግን ሞትን ተላመዱ። በየጊዜው የሚሞቱ ሰዎችን በድን እንደዋዛ ወደ ውሃው ይወረውራሉ።

ወደ አሰቃቂው ታሪክ እንሸጋገር

የባህሩ ላይ ቆይታ እየጨመረ ስሄድ ረሃብ በረታ። የሚበላም የሚጠጣም የለም። በህይወት ለመቆየት የሚያግዛቸው ምንም ነገር የለም። ሁሉም ነገር ጨልሟል። ረዳት አልባ ናቸው።

በህይወት የተረፉ ሰዎች በተዳከመ ስሜት ውስጥ ሆነው "ምን እናድርግ?" ተባባሉ። አጠገባቸው የሞተ ሰው ገላ ተጋድሟል። እሱን ለመብላት ወሰኑ። አዎን የሰው ስጋ ለመብላት ወሰኑ።

ከሟቹ ታፋ አከባቢ ስጋ ቆረጡ። መሐመድ ኦጋ ከባህሩ ውሃጋ አጣቅሶ የሰው ስጋ ጎረሰ። በሁለት የተለያዩ አጋጣሚዎች ህይወቱን ለማቆየት የሰው ስጋ በላ....

ወደ ዋናው ነጥብ እንምጣ፥

እነ መሐመድ ኦጋ እዛ ሁሉ ምስቅልቅል ውስጥ የገቡት በአንድ ግለሰብ ግድየለሽነት ነው። በጀልባው ላይ ካሉ ሰዎች መካከል አንዱ ጂፒኤስ መያዝ ነበር ሃላፊነቱ። ጂፒኤስ ሲሰጠው አለአግባብ እንዳይነካካው ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ነበር። ነገር ግን ቸልተኛ ሆነ። በግድየለሽነት ነካክቶ አበላሸው። ጂፒኤሱ ሲበላሽ አቅጣጫ ሳቱ። በተሳሳተ አቅጣጫ ሲጓዙ ነዳጅ ጨረሱ። ከዚህ በኋላ በባህሩ ላይ 11 ቀናት ያለ አጋዥ ሲቆዩ ሽንት ጠጡ፥ የሰው ስጋ በሉ። በመጨረሻም ከ17ቱ ተጓዦች መካከል መሐመድ ኦጋ ብቻ ተረፈ። ሌሎቹ ሞቱ።

የዚህ ሁሉ ቀውስ ሰበብ ፥ በግድየለሽነት ጂፒኤስ ነካክቶ አቅጣጫ ያዛባው ሰው ነው።

አንዳንድ ሰው እንዲህ ነው። ሃላፊነት አይሰማውም። በግድየለሽነት የሰው ህይወት ያመሳቅላል። በግድየለሽነት በሚፈፅማቸው ስህተት ሌሎች ሰዎች ህይወት ይከፍላሉ።

ሌላውን ሰው ህይወት የሚያስከፍል ስህተት የሚሰሩ ፥ በግድየለሽነት የሰውን ኑሮ ያናጉ ፥ አቅጣጫ ያዛቡ ፥ ተስፋ የቀሙ ስንት ናቸው?

መሐመድ ኦጋ ከዛ ሁሉ ሰቆቃ በህይወት የተረፈ ብቸኛ ሰው ነው። አትፍረድ በሚል መፅሐፍ ህይወቱ ተተርኳል።

@Tfanos
@Tfanos
6😢2
ህይወት ውድ ናት!
(ተስፋኣብ ተሾመ)
* * *

"የሰው ስጋ በልቶ ህይወቱን ያተረፈው ለምንድነው? ምን የሚያጓጓ ነገር አለ?"

ትላንት ባጋራሁት ታሪክ ላይ የሞራል ጥያቄ ያነሱ ሰዎች ነበሩ። ራስን ለማቆየት ሲባል የሬሳ ስጋ መብላት ትርጉሙ ያልታያቸው አሉ። "በህይወት መቆየት ምን የሚያጓጓ ነገር አለው?" የሚል መሟገቻ አላቸው።

አስራአንድ ቀናት በባህር ላይ በቆየበት ወቅት የሚበላ በማጣት የሰው ስጋ ስለበላው ሰው ፅፌ ነበር። የሞተ ሰው ስጋ በመብላት ህይወቱን ማቆየቱ ለአንዳንድ ሰው አልተዋጠም። "እንዴት እንዲህ ይደረጋል?" የሚሉ አሉ።
የሰው ስጋ በልቶ ህይወቱን ያቆየው ሰው መሐመድ ኦጋ ይባላል። ታሪኩን የተረከበት መፅሐፍ አትፍረድ ይሰኛል። "አትፍረድ" ተራ ቃል ብቻ አይደለም። አንተ በቦታው ብትሆን ምን ትወስናለህ? ለማንኛውም አትፍረድ!

መሐመድ ኦጋ የኦነግ ታጣቂ ነበር። በኤርትራ በረሃ የኦነግ ሰራዊት በነበረበት ወቅት አንድ አሰልጣኝ ገጠመው። አሰልጣኙ ለነመሐመድ ወታደርን ሊገጥም ስለሚችል መከራ አስተምሯል። በችግር ወቅት ምን ማድረግ እንዳለባቸው ነግሯቸዋል።
ከሁሉም በላይ ግን ጠቃሚ ምክር ሰጥቷቸዋል። "ህይወት ውድ ነገር ናት" ይላቸው ነበር። እየደጋገመ የህይወትን ውድነት አስተምሯቸዋል።

"ደማችሁ ያለ ማቋረጥ ቢፈስ የገዛ ደማችሁን ላሱት፥ ቢርባችሁ ማንኛውንም መርዛማ ያልሆነ ነገር ብሉ፥ ፍየሎች የሚበሉትን ቅጠላቅጠል ፥ የኤሊ ስጋ ፥ ሌሎች የተከለከሉ መብሎችን ለመብላት እንዳታመነቱ። ከመሞት በህይወት መቆየት ይሻላል። የትኛውንም ነገር አድርጋችሁ በህይወት ቆዩ። ምናልባት የነገዋ ፀሐይ ሌላ ተስፋ ይዛላችሁ ልትመጣ ስለምትችል አትሙቱ" ይላቸው ነበር።

"ህይወት ውድ ናት" ይላቸዋል እየደጋገመ።

እነ መሐመድ በባህር ላይ ብቻቸውን ሲቀሩ ሁሉም ተስፋ ቆረጡ። መሞታችን ነው አሉ። መሐመድ ግን መሞት የለብኝም ይል ነበር። "ህይወት ውድ ስለሆነች መሞት የለብኝም" ይላል እየደጋገመ። አሰልጣኙ ስለ ህይወት ውድነት የነገረው ነገር ተስፋ እንዳይቆርጥ አደረገው።ውድ ህይወቱን ለማቆየት በፅናት ታገለ።

"የሰው ስጋ በልቶ ህይወቱን ያተረፈው ለምንድነው? ምን የሚያጓጓ ነገር አለ?" ያሉ ጠያቂዎች ነበሩ። መልሱ ህይወት ውድ ስለሆነች የሚል ነው።

የመፅሐፉን ርዕስ ላስታውሳችሁ። "አትፍረድ" ይላል። "አትፍረድ" ጥሩ ርዕስ ነው።

ከመፅሐፉ ጠቃሚ ትምህርት እንምዘዝ። ህይወት ውድ ነገር ናት።

ከትዳር መለየት ፥ ከጓደኛ መቆራረጥ ፥ ከተማ መቀየር ፥ ከቤተሰብ መራቅ.... ከባድ ውሳኔ ነው።ነገር ግን የግድ ይወሰናል። አንዳንዴ ከሁለት መጥፎ አንዱን የመምረጥ ግዴታ ውስጥ እንገኝ ይሆናል። ያኔ ከባዱን ለመወሰን እንጨክናለን። ምክኒያቱም ህይወት ውድ ናት

ህይወት የከበረች ነገር ናት። ደግሞም ውድ ናት። የከበረውን ላለማርከስ ፥ ውዱን ነገር ለመጠበቅ ሲባል መራራ ውሳኔ ይወሰናል።

አንዳንድ ሰው የህይወት ክብር አይገባውም። ከሰዎችጋ ያለው ግኑኝነት የተዛባ ሆኖ ህይወቱን ያስከፍለዋል። አንዳንድ ሰው ስራውን ከህይወቱ በላይ ያከብራል። አንዳንድ ሰው የፍቅር ግኑኝነቱ ከህይወት ይበልጥበታል። ነገር ግን እውነታው ሌላ ነው።

ህይወት ውድ ነገር ናት። ለውድ ነገር ውድ ዋጋ ይከፈላል።

እርግጥ ህይወት ውድ ነገር ናት


@Tfanos
6
ዮናስ ጎርፌ...

አንዳንድ ሰው ደፋር ነው። ከኖረው ልማድ ለመቃረን አይፈራም። ከሰፊው ህዝብ መለየት አያስደነግጠውም። ማፈንገጥን ያጌጥበታል።

በእርግጥ የሚያፈነግጡ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም። ዛሬ ዛሬ ቀላል ቀጥር የሌላቸው ሰዎች ሲያፈነግጡ እንመለከታለን። ነገር ግን ለማፈንገጣቸው በቂ ምክኒያት ማቅረብ የሚችሉ ጥቂት ናቸው።

ቀላል ቁጥር የሌላቸው ሰዎች በኖረው ልማድ እና ገዢ አስተሳሰብ ላይ ያምፃሉ። ማፈንገጣቸው ግን ስሜት የሚጫነው ይሆናል። ጥቂቶች ደግሞ የተለየ ሃሳብ ሲያራምዱ የተደራጀ መከራከሪያ ያቀርባሉ። አቋማቸውን በምክኒያት መሰረት ያኖራሉ። እንዲህ ያሉት ጥልቅ አሳቢ ናቸው።

ዮናስ ጎርፌ የተለዩ ሃሳቦችን ለማራመድ አይፈራም። ለሚያራምደው ሃሳብ በቂ መከራከሪያ ያቀርባል። መሟገቻዎቹን በእውቀት መሰረት ያንፃል።

2007 አ.ም ላይ "ቤት ያጣው ቤተኛ" የሚል መፅሐፍ አሳተመ። መፅሐፉ ዘፈንን ሃጢያት የሚያደርገው አካሄድ ስህተት ስለመሆኑ የሚያትት ነው። ማስረጃ እንዲሆነው መፅሐፍ ቅዱስን አጣቅሷል።

ፕሮቴስታንት ቤት ያደግን ሰዎች እንደምናውቀው ዘፈንን ሃጢያት አይደለም ማለት ድፍረት ይፈልጋል። ድፍረት ሲደመር አፈንጋጭነትን ይጠይቃል። ዮናስ ደፈረ። እውቀታዊ ሙግትን ለሚወዱ ሰዎች አዲስ ስጦታ አበረከተ። አይን ገለጠ።

በዚህ አመት ደግሞ ሌላ መፅሐፍ አሳተመ። "ፕሮቴስታንታዊያን በኢትዮጵያ ፖለቲካ" ይሰኛል መፅሐፉ። ሞጋች መፅሐፍ ነው። ጴንጤቆስጤያዊንን በደፋር ብዕር ይሞግታል። አማኙ ማህበረሰብ በፖሊቲካ ሰፈር ቦታው ምን መሆን እንዳለበት ይጠይቃል። አይን ገላጭ መፅሐፍ ነው።

መፅሐፉ "ኢየሱስ ከሰው በላይ የሚወደው የለም። ይህ ክርስቶሳዊ ፖለቲካ ነው" ይለናል። (ቃል በቃል አይደለም)

ደፋር ሰው እወዳለሁ። ሞጋች ሰው ይመቸኛል። ከሰው ለመለየት ያህል ሳይሆን ፥ አሰላስሎ የተለየ አቋም የሚይዝ ሰው አከብራለሁ።

የፕሮቴስታንት ማህበረሰብ ለዮናስ ጎርፌ ሃሳቦች ዋጋ ቢሰጥ የሚጠቀም ይመስለኛል። በተለይ በሁለተኛ መፅሐፉ ላይ ላነሳቸው ሃሳቦች ክብር መስጠት ፥ በርዕሰ ጉዳዩ ማሰላሰል፥ መወያየት ፥ መተቸት ፥ መከራከር የሚጠቅም ይመስለኛል።

የፅህ ፅሁፌ አላማ የዩቲዩብ ቻናሉን ማስተዋወቅ ነው። የዩቲዩብ ቻናሉን ለማስተዋወቅ ያደረግኹት መንደርደሪያ ረዘመ መሰለኝ...

ዮናስ የዩቲዩብ ቻናል አለው። Yonas Gorfe / ዮናስ ጎርፌ ይሰኛል ቻናሉ። በዩቲዩብ ቻናሉ ላይ በምክኒያት የተፈተኑ ሃሳቦችን ያነሳል። ዝግጅቶቹ አይን ገላጭ ናቸው። እኔ በግሌ ስለ ክርስቲያን ፅዮናዊያን የሰራውን ፕሮግራም ወድጄዋለሁ


@Tfanos
3👍1
"ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር የኑሮ ውድነቱ ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል"

"ኢትዮጵያ አትፈርስም"

"ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር የዜጎች ደህንነት አደጋ ላይ ወድቋል። ለዚህ ችግር መፍትሄ ማፈላለግ ያስፈልጋል"

"ኢትዮጵያ አትፈርስም"

"የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን ላይ ጥያቄ አለን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር"

"ኢትዮጵያ አትፈርስም"

"ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር የአባይ ግድብን በተመለከተ በቂ መረጃ የለንም"

"ኢትዮጵያ አትፈርስም"

"ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱ ልክ አይደለም"

"ኢትዮጵያ አትፈርስም"

"ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ሙስና ክፉኛ ተስፋፍቷል"

"ኢትዮጵያ አትፈርስም"

"ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር 'ኢትዮጵያ አትፈርስም' ማለት መልስ አይሆንም። ለጥያቄዎቻችን ትክክለኛ መልስ ይስጡን"

"ኢትዮጵያ አትፈርስም"


@Tfanos
😢7👍1
"የኮሞሮሱ አውሮፕላን አደጋ"

B-67 ቦይንግ ጄት ንብረትኑ የኢትዮጵያ አየር መንገገድ ነው።

ህዳር 14 ቀን 1989 አ.ም የተለመደ አገልግሎት ለመስጠት ተሰማራ። ወደ ኖይሮቢ በረራ ጀመረ። በአውሮፕላኑ ውስጥ 163 ተሳፋሪ እና 12 የበረራ አስተናጋጆች ይገኛሉ።
አገር አማን ብለው ወደ ኬኒያ ናይሮቢ እየተጓዙ ሳለ ድንጌቴ ነገር ገጠማቸው።

3 ወጣቶች እምር ብለው ተነስተው ማንም ያልገመተውን ነገር አደረጉ። አውሮፕላኑን መጥለፋቸውን አረዱ። ለተሳፋሪዎቹ አስደንጋጭ መልክት ነገሯቸው። 'ቦንብ ይዘናል፥ የምንፈልገው ካልተደረገ አውሮፕላኑን እናጋያለን' አሉ። ተጓዡ በስጋት መቅሰፍት ተመታ፥ ፍርሃት ወረራቸው።

አውሮፕላን አብራሪው ከጠላፊዎቹ የደረሰው ትዕዛዝ ለመተግበር የማይመች ነው። ወደ አውስትራሊያ እንዲያበር ነው ያዘዙት። አብራሪው ይሄን ማድረግ አይችልም፥ ቀድሞ ነገር ኬኒያ መጓዝን እንጂ አውስትራሊያ መብረር አልታቀደም። የአውሮፕላኑ ነዳጅ በቂ አይደለም። ወደ አውስትራሊያ ጉዞ ቢጀምሩ መንገድ ላይ ያልቃል፥ አያደርሳቸውም። ይሄን ለጠላፊዎቹ አስረዳ 'በቂ ነዳጅ የለንም፥ በድፍረት ጉዝ ብንጀምር መንገድ ላይ እንከሰከሳለን' አላቸው። ሊሰሙት አልወደዱም። ''ትዕዛዛችንን ፈፅም፥ ወዳዘዝንህ ቦታ የማትጓዝ ከሆነ አየር ላይ አውሮፕላኑን እናጋየዋለን'' አሉ። ያለ በቂ ነዳጅ መብረር አደጋ እንዳለው ቢነገራቸውም 'በጀ' አላሉም።

አብራሪው ጠላፊዎቹ ግትር መሆናቸውን በማመኑ የጭንቀት መፍትሄ አፈላለገ። ማሳሙኑ አልሆን ቢለው አማራጭ የመሰለውን እርምጃ ወሰደ።
የምስራቅ አፍሪካን ድንበር ይዞ በህንድ ውቂያኖስ ላይ መብረር ጀመረ።
ከጥቂት ጉዞ በኋላ ግን የአውሮፕላኑ አንዱ ሞተር ጠፋ፥ አውሮፕላኑ 29 ሺ ጫማ ከፍታ እየበረረ የነበረ ሲሆን በአንዱ ሞተር መጥፋት የተነሳ ወደ 25 ሺ ጫማ ዝቅ አለ። የትራጄዲው የመጀመሪያ ምዕራፍ ተከፈተ።

"ግድ የላችሁም እመኑኝ፥ ነዳጁ የምትፈልጉት ስፍራ አያደርሰንም። አሁን የአውሮፕላኑ አንዱ ሞተር ጠፍቷል። እንዲህ የሆነው በነዳጅ የነተሳ ነው" አለ አብራሪው። ጠላፊዎቹ ግን በግትርነታቸው ፀኑ። "ልታታልለን እየሞከርክ ነው" አሉት። አብራሪው ሃሳባቸውን ካልተቀበለ እንደሚያጋዩ ዛቱ።

አማራጭ የለም። ጠላፊዎቹን ማሳመን ስላልተቻለ ያለ በቂ ነዳጅ መብረር ቀጠለ።

ከጥቂት በረራ በኋላ ተራፋሪዎች የአውሮፕላን አብራሪውን ድምፅ ሰሙ። አብራሪው ለተሳፋሪው አስደንጋጭ ትዕዛዝ አስተላለፈ። አውሮፕላኑ ከሰማይ ወደመሬት መውደቂያው ስለደረሰ ተጓዡ ለአደጋው ራሱን እንዲያዘጋጅ ፓይለቱ ተናገረ፥ መርዶ አረዳቸው።

"ክቡራን ተሳፋሪዎቻችን ፥ አውሮፕላኑ በአጭር ጊዜ መከስከሱ አይቀርም፥ ስለዚህ ቦታችሁን ያዙ። ወደፊት አጎንብሳችሁ ተቀመጡ፥ በጭንቅላታችሁ ላይ ትራስ ጫኑ"

አውሮፕላኑ መጠለፉ ከተነገረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳፋሪው ተሸበረ። አንዲት የበረራ አስተናጋጅ በጉልበቷ ተንበርክካ እጆቿን ወደላይ ሰቅላ ፀሎት ጀመረች። 'እግዚአብሔር ሆይ አድነን' አለች። ከልጆቹ ጋር የተሳፈረ አባት የሚይዘውን የሚጨብጠውን አጣ። ልጆቹን በጭኑ አስቀምጦ በሃይል አቀፋቸው። ሰውነታቸው በድንጋጤ የሚንቀጠቀጥ ተሳፋሪዎች ወደ ፈጣሪ ልመና ጀመሩ። አንዳንድ ተሳፋሪዎች ጠላፊዎችን ካልገደልን አሉ። ፍርሃት በአውሮፕላኑ ነገሰ።

አውሮፕላኑን ከመክስከስ ለማዳን ብዙዎች እየተረባረቡ ነው። የ'ሞሮኒ አውሮፕላን ማረፊያ' ሰራተኞች ከተጠለፈችው አውሮፕላን ሰራተኞች ጋር ተነጋግረው ስለነበር አውሮፕላኑን ለማደን ፈቃደኛ መሆናቸውን ገለፁ። "ኑ እኛ ዘንድ እረፉ" አሏቸው።ይሄም ቢሆን የሚሳካ አይደለም። የአውሮፕላኑ ነዳጅ እዛ አያደርስም።

የአውሮፕላን አብራሪው ለተጓዡ የመጨረሻ መልክት አስተላለፈ
"ለተፈጠረው ነገር ተጠያቂዎቹ ጠላፊዎች ናቸው። ምናልባት ከኛ መካከል በህይወት የሚተርፍ ሰው ከተገኘ ጠላፊዎችን በሕግ እንጠይቃለን። ስለዚህ በደንብ እዩዋቸው" አለ

ከዚህ በኋላ ግኑኝነት ተቋረጠ፥ ነዳጅ አለቀ። አውሮፕላኑ ድንገት አሽቆለቆለ። አንዳች ትርዒት የሚያሳይ ይመስል ከሰማይ እየተምዘገዘገ ኮሞሮስ ባለ የባህር ዳርቻ ቁልቁል ወረደ። የሚምዘገዘገው በአስፈሪ ፍጥነት ነበር። በሰኣት 200 ማይል ከሰማይ ወደ መሬት ተምዘገዘገ።

ጠላፊዎቹ "አውሮፕላኑን ባህር ላይ ጣለውና ሁላችንም እንሙት። አጥፍተን እንጥፋ" አሉ። አብራሪው ግን ቁልቁል እየወረደች ያለችውን አውሮፕላን ለመቆጣጠር የቻለውን ሁሉ ማድረግ ቀጠለ።

የአውሮፕላኑ አንድ ክንፍ ውሃውን መታና ተገነጠለ፥ አውሮፖላኑ ለሶስት ተከፈለ።
ከኢትዮጵያ ወደ ናይሮቢ በረራ የጀመረው አውሮፕላን በኮሞሮስ ደሴት ተከሰከሰ። የተከሰከሰው 'ኑ እኛ ዘንድ እረፉ' ከተባለው የሞሮኒ አውሮፕላን ማረፊያ 16 ማይል ቅርበት ላይ ነበር። ያቺን አጭር ርቀት ለመሄድ የሚሆን ነዳጅ አልነበረምና ተከሰከሱ

በአውሮፕላኑ 175 ሰዎች ነበሩ። ከነዚህ መካከል በህይወት የተረፉት 52 ብቻ ናቸው። ሌሎች ላይመለሱ አንቀላፉ


@Tfanos
2
መንግሥታችን ምን ይመስላል?

የመንግሥትን እውነተኛ መልክ ለማወቅ ከሚረዱ ነገሮች መካከል አንዱ ልደቱ አያሌው ነው።
መንግሥታችን ልደቱ ላይ የሚከተለው ፖሊሲ አሳፋሪ ከሚለው ቃል በቀር በምንም ሊገለጥ አይችልም።

1፥ መንግስት የነልደቱ አያሌው ፓርቲ የሆነውን ኢዴፓ በሃሳብ በመሞገት ፋንታ አገደው። ኢዴፓ እንዲሰረዝ ተደረገ።

2፥ ልደቱ በታሰረ ወቅት ፍርድ ቤት ነፃ አድርጎት ነበር።ፍርድ ቤት "ወንጀል የለበትም" እያለ ፖሊስ በማን አለብኝ ስሜት በእስር አቆየው። የልብ ህመም እንዳለበት እየታወቀ ፥ ከእስር ቤት ወጥቶ ህክምና ማግኘት እንደሚገባው እየታወቀ ህይወቱ ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ በእስር ቤት ቆየ

3፥ ከሐገር ወጥቶ ህክምና እንዳያገኝ ተስተጓጎለ

4፥ አንድም ቀን ጠመንጃ አንስቶ እንደማያውቅ እየታወቀ ፥ በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሚታገል እየታወቀ በሽ*ብር ተወነጀለ። ተቃውሞ ስላቀረበ "ህገመንግስትን በሀይል ለመናድ ተንቀሳቅሰሃል" ተባለ

5፥ ልደቱ በሽብር*ተኝነት የተወነጀለ ጊዜ "አሸ*ባሪ ካላችሁኝ እና መረጃ አላችሁ ክሰሱኝ፥ በፍርድ ቤት ተከራክሬ ራሴን ነፃ አወጣለሁኝ" አለ። ያኔ በሚዲያ አሸ ባሪ ያለው አካል ክስ ሊመሰርትበት አልፈቀደም።

6፥ ልደቱ በአሜሪካን ሐገር የሚከታተለውን ህክምና ጨርሶ ወደ ሐገሩ ሊመጣ ተሰናዳ። ነገር ግን መንግሥት አትገባም ብሎ ከለከለው። ተደርጎ በማይታወቅ ሁኔታ ዜግነቱን ገፈፈው። በሐገሩ የመኖር መብቱን ነጥቆ ሀገር አልባ አደረገው።

7፥ ንብረቶቹን የመውሰድ እንቅስቃሴ ጀመረ። ከቀናት በፊት በላሊበላ ያለውን ሎጅ ንግድ ባንክ በጨረታ ሊሸጥበት እንቅስቃሴ መጀመሩን ሰምተናል። ዛሬ ደግሞ በቢሾፍቱ የሚገኘውን የልደቱን መኖሪያ የመውረስ እርምጃ ተጀምሯል። "በአስር ቀን ውስጥ በቤት ውስጥ የሚገኙ እቃዎች ይውጡና እወርስብሃለሁ" ተብሏል።

ምን ይባላል? እንዲህ ያለ መንግስታዊ አይናውጣነት በምን ቃል ይገለፃል?

ታሪክ ይመዘግባል።

የዚህን መንግስት እውነተኛ መልክ ለማወቅ ከሚረዱ ነገሮች መካከል አንዱ ፥ መንግስት ልደቱ ላይ የተከተለው ፖሊሲ ነው!


@Tfanos
7
የህዳሴ ግድብ በአሜሪካ ገንዘብ መሰራቱን ዶናልድ ትራምፕ ለ3ኛ ጊዜ ተናግረዋል።

በአንድ ወቅት ጌታቸው ረዳ "ግድቡ ተሸጧል" ብሎ ነበር።

አቢይ ግብፅ ሄዶ "ወላሂ" ብሎ በመማል ለግብፅ ቃል ገብቶ ነበር

መንግስት ለትራምፕ ንግግር ምላሽ መስጠት አልፈለገም።

ደህና አረፈዳችሁ?

@Tfanos
😁71
ሰዶማዊነትን እና ወስባዊ ልቅነትን መግታት ይቻል ይሆን?

ሰዶማዊነት በፍጥነት እየተስፋፋ መጥቷል። አሁን የሚሄድበትን ፍጥነት ከተመለከትን በቀላሉ የሚገታ አይመስልም። ምናልባት ታናናሾቻችን በሰዶም ወጥመድ ውስጥ ይገቡ ይሆናል። የኛ ትውልድ ልጆቹን ከወሲባዊ ልቅነት በቀላሉ ላይታደግ ይችላል።

ከዚህ ቀደም ወጣቶች ከጋብቻ ውጭ ወሲብን ከጀመሩ እንደ ትልቅ ጥፋት ይቆጠር ነበር። ዛሬ ግን ነገሩ ተቀይሯል። መቀየሩ ብቻ ሳይሆን የተቀየረበት ፍጥነት አስደንጋጭ ነው።
ነገ ደግሞ የከፋ የሚሆን ይመስላል።

ወሲብ ልቅ ሆኗል። ትዳር እያላቸው የሚማግጡ ሰዎች አያስደነግጡንም። በእድሜ ለጋ የሆኑቱ ልቅ ወስበኛ ሲሆኑ አንገረምም። ሰዶማዊነት ላይ ለዘብተኞች ሆነናል።

በቀደመው ዘመን ስለ ተመሳሳይ ፆታ ወሲብ ማሰብ እንኳን ከባድ ነበር። ዝንባሌው ያላቸው እንኳ ድርጊታቸውን የሚከውኑት በስውር ብቻ ነበር።
በጊዜ ሂደት ግን ነገሮች መለወጥ ጀመሩ።

በፊልም ፥ በስነፅሁፍ ፥ በማህበራዊ ገፆች የተነሳ ሰዶማዋነት ተለመደ። ስለጉዳዩ መስማት የማያስደነግጥ ሆነ። "እኔን እስካልነኩ ድረስ ምን አገባኝ?" ማለት ተጀመረ። ለወደፊት ደግሞ "እኔን እስካልነኩኝ ምናገባኝ" ብለን ያሳደግናቸው ልጆች ሰዶማዊ ሆነው እናገኛለን። ይህ የማይቀር ሽግግር ነው።

ትላንት ፥ ልጆች ከጋብቻ ውጭ ወሲብ ሲፈፅሙ ወላጅ ይደነግጥ ነበር። ነገ ይህ ይቀራል። የነገው ወላጅ ልጆች ከጋብቻ ውጭ ወሲብ ሲፈፅሙ ደስ ይሰኝ ይሆናል። "ልጄ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ወሲብ መፈፀሙ ደስ ያሰኛል። ሰዶማዊ እንዳልሆነ አረጋግጫለሁ" ይላል። ከነገ ወዲያ ደግሞ...

የወሲብ ልቅነት ዘመን ላይ ነን ያለነው። የጥርስ ሳሙና ማስታወቂያ ለመስራት ወሲብ ቀስቃሽ የሴት ምስል ይታያል። ወሲብ እና የጥርስ ሳሙና ምን አገናኘው? ወሲብ ሸቀጥ ሆኗል!

ሰዶማዊነትን ለመግታት ፥ ወሲባዊ ልቅነትን ለመቆጣጠር ሀይማኖት እና ባህል የራሳቸው ሚና አላቸው። ነገር ግን ሚናቸው እጅግ የተገደበ ነው። ያለነው ግለሰባዊነት የገነነበት፥ ኢአማኚነት የተስፋፋበት ፥ አፈንጋጭነት በነገሰበት ዘመን ነው። በባህል እና በሃይማኖት ተጠቅመን ሰዶማዊነትን እና ወሲባዊ ልቅነትን መግታት አይቻለንም። ስለዚህ ሌላ መፍትሔ መሻት ይኖርብናል።

ሰዶማዊነት እና ወሲባዊ ልቅነት ትክክለኛ ጉዳቱ ምንድነው? በግለሰብ ህይወት ላይ ምን አይነት ችግር ያስከትላል? አእምሯዊ እና ስነልቦናዊ ጣጣው ምን ድረስ ነው? ይሄን ለመሰሉ ጉዳዮች ሳይንሳዊ ማብራሪያ የማምጣት ግዴታ አለብን። ሀይማኖት እና ባህልን ተጠቅሞ ማስቆም ከባድ ነው። ይልቅ ባህልና ሃይማኖት እንደተጠበቁ ሆነው ብርቱ የሆነ ሳይንሳዊ ማብራሪያ እና ትምህርት ያስፈልጋል።

ሌላ ደግሞ

የማህበረሰብ እሴት እና የግለሰብ ነፃነት ሲጋጭ ህግ ለየቱ ያድላ? ሚዛን መጠበቅ ይቻላል? ይህ ወሳኝ ጥያቄ ነው። የፍልስፍና ሰዎች ፥ የሕግ ሰዎች ፥ ፖለቲከኞች ፥ የማህበረሰብ ጥናት ባለሞያዎች በዚህ ጉዳይ ላይ መነጋገር እና አዋጭ መፍትሔ መቀየስ አለባቸው።


Via ተስፋኣብ ተሾመ

@Tfanos
13
በትግራይ ክልል ሌላ ጦርነት ሊደረግ እየተሟሟቀ ይመስላል። የቃላት መተኮስ ፥ መዛዛት ፥ ፉከራ ተጀምሯል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ "ህወሃት የደበቀውን ጦር መሳሪያ ያስረክብ" ብለዋል። ዛቻም አክለዋል።
አሁን እየሆነ ያለው ሁሉ የቀደመውን ይመስላል። ትላንት የሆነውን ጥፋት ለመደግም እየተሯሯጥን ነው።

ከታሪክ የተማርነው ምንድነው? ከታሪክ የተማርነው ከታሪክ አለመማርን ነው።

ያለፉት ሰባት አመታት የእርስ በእርስ ጦርነት አመታት ናቸው።ድህረ 2010 ከአንድ ጦርነት ወደሌላ ጦርነት የገባንባቸው አመታት ናቸው።

በምዕራብ ኦሮሚያ ከኦሮሞ ነፃነት ጦር (በመንግሥት አጠራር ሸኔ) ጋር የተጀመረው ጦርነት እስካአሁን መቋጫ አላገኘም። ህይወት እንደዋዛ እየተቀጠፈ ቢሆንም የህዝብን ትኩረት አላገኘም። የተዘነጋ ውጊያ ነው።

በ2013 በትግራይ ተቀስቅሶ የነበረው ጦርነት ሚሊዮን ነብስ በመቃብር ፥ ሌላ ሚሊዮን ነብስ ደግሞ በመጠለያ አድርጎ በፕሪቶሪያ ስምምነት የተቋጨ መሰለ።

ከትግራዩ ጦርነት ማግስት በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ጦርነት የከበረውን የሰው ልጅ ህይወት እየነጠቀ ፥ ንብረት እያወደመ ፥ ተስፋ እየቀማ ቀጥሏል።

አሁን ደግሞ በትግራይ ክልል ሌላ ጦርነት የሚቀሰቀስ ይመስላል።

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ከታሪኩ የማይማር ሰው ስህተቱን እንደ እንስሳ ይደጋግማል ይላሉ።

ሰው ከእንስሳ ይለያል። የሰው ልጅ ከታሪኩ የመማር እድል አለው። ከታሪክ የሚማር ስህተት አይደጋግምም። እኛ ግን ስህተት እንደጋግማለን። ጠዋት የመታን እንቅፋት ከሰአትም ይነርተናል። ከሰአት የመታን እንቅፋት ማታም ይደግመናል። በአንድ እንቅፋት ደጋግመን የምንመታው ለምንድነው?

ከታሪካችን የተማርነው ከታሪክ አለመማር ነው።


Via ተስፋኣብ ተሾመ

@Tfanos
7😢3👍2
እኔ ጠቅላይ ሚኒስቴር ብሆን....

ሰፊው ህዝብ ሐገር እንድመራ እድል ብሰጠኝ ፥ ህዝብ እንዳገለግል እድሉን ባገኝ ከዚህ በታች የዘረዘርኳቸውን ነገሮች እከውናለሁ።

(ትላንት ኢንጂነር ጌቱ ከበደ ጥያቄ አጋርቶን ነበር "ሐገር ለመምራት የምትወዳደሩ ቢሆን ምን ምን ታደርጋላችሁ?" ብሎ ጠየቀን። ለጌቱ ጥያቄ የኔ ምላሽ እነሆ)

1፥ የሕገመንግስት ማሻሻያ አደርጋለሁ።

የሕገመንግስቱን መግቢያ አሻሽላለሁ። አንቀፅ 39ን እለውጣለሁ። ስለ ጠቅላይ ሚኒስተር ስልጣን የሚያወራውን አንቀፅ 74 አሻሽላለሁ። ጠቅላይ ሚኒስተሩ ስልጣን አለአግባብ ስለተለጠጠ እንዲገደብ አደርጋለሁ። የጠሚ የስልጣን ዘመን ከ10 አመት እንዳይበልጥ አደርጋለሁ

2፥ የክልል አወቃቀር አሻሽላለሁ።

አሁን ያለውን ቋንቋ ተኮር የክልል አወቃቀር አሻሽላለሁ። መለወጥ ሳይሆን ማሻሻል። ቋንቋ (ብሔር) ለክልል አወቃቀር አንዱ መመዘኛ ይሆናል። በተጨማሪም ጂኦግራፉ እና የአስተዳደር አመችነት መመዘኛዎች ይሆናል። ከላይ በተጠቀሱት 3 መስፈርቶች ክልሎች እንዲዋቀሩ የሚደረግ ሲሆን በጠቅላላው እስከ 20 የሚደርሱ ክልሎች የሚኖሩ ይሆናል። እያንዳንዱ ክልል በህዝብ ቁጥር እና በቆዳ ስፋት ከሌላው ክልል ጋር ተመጣጣኝ እንዲሆን ይደረጋል

3፥ አፋን ኦሮሞ ተጨማሪ የሐገሪቱ የስራ ቋንቋ ይደረጋል።
(እዚህ ጉዳይ ላይ ጠንከር ያለ እምነት ነው ያለኝ። ሌላ ጊዜ ምክኒያቴን በሰፊው እፅፋለሁ)

4፥ የመሬት ፖሊሲ ይለወጣል።

መሬት መሸጥ እና መለወጥ የሚችል የግለሰብ ሃብት ይሆናል። መሬት የመንግስት (የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች) የሚለው አሰራር ሙሉ ለሙሉ ይለወጣል።
ገበሬው መሬቱን አስይዞ ከባንክ የሚበደርበት ምቹ አሰራር እንዲቀየስ ጥረት ይደረጋል። መሸጥ የሚፈለግ ደግሞ ያለ ምንም ገደብ መብቱ ይከበራል።

5፥ የታክስ ስርአቱ ላይ ማሻሻያ ይደረጋል።

ደሞዛቸው እስከ አስር ሺ ብር ያሉ ዜጎች ታክስ ነፃ ይሆናሉ። በተጨማሪም የታክስ ጣሪያው ከ15 በመቶ እንዳይበልጥ ይደረጋል።

6፥ መንግሥት መሰረታዊ በሆኑ ስራዎች ላይ ብቻ በማተኮር የግል ዘርፉ በሌሎች ስራዎች ላይ እንዲሰማራ ይደረጋል።

በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስቴር አልሆንም። ነገር ግን እንደው ለወጉ ያህል "ስልጣን ቢኖረኝ ይህን አደርጋለሁ" ለማለት ያህል ነው

ተስፋኣብ ተሾመ

@Tfanos
👏10
የቃለህይወት ልጅ ነኝ።

አንደኛ ክፍል ከመግባቴ በፊት በሻሸመኔ መሐል ከተማ ቃለህይወት ቤተክርስቲያን ትምህርት ቤት ገባሁ፥ ዜሮ ክፍል ተመዘገብኩ። ዜሮ ክፍል ማለት እንደ Kg ያለ መዋለ ህፃናት ነው። መምህራኖቻችን በብዛት የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋይ ጭምር ናቸው። ለወላጆቻችን መፅሐፍ ቅዱስን ያስተምራሉ፥ ለታላላቆቻችን ወንጌል ይሰብካሉ፥ እኛን ፊደል ያስቆጥራሉ።

ከዜሮ ክፍል ቀጥሎ እስከ 3ተኛ ክፍል የተማርኩት ቃለ ህይወት ነው። አብዛኛው ተማሪ የወንጌላውያን አማኝ ቢሆንም በጣም ጥቂቶቹ ከሌላ እምነት የመጡ ናቸው።
ሰንበት ትምህርት የተማርኩትም ቃለ ህይወት ነው። መምህራችን ሙሉዬ ትባላለች።

ሙሉዬን እወዳታለሁ

"ወልድ ያለው ህይወት አለው" ከሚለው ስመ-ገናና የቃለህይወት መፈክር ቀጥሎ የማስታውሰው ሙሉዬን ነው።

ልጆች ሳለን ቃለህይወት ቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት እንማር ነበር። መምህራችን ሙሉ እመቤት ትባላለች። ሙሉዬ ነው የምንላት።
ሙሉዬን የሻሸመኔ መሓል ከተማ ቃለህይወት ቤተክርስቲያን ወጣቶች ሊሸረፍ በማይችል ፍቅር እንወዳታለን። በሁላችንም ላይ በጎ ተፅዕኖ አሳድራለች።

ከእለታት በአንዱ ግጥም ፃፍኩና አነበብኩላት። ያኔ እድሜዬ 11 ቢሆን ነው። ኦርቶዶክስን የሚተች ግጥም ነው ያነበብኩላት።
አንብቤ ስጨርስ አለቀሰች።

የግጥም መፃፊያ ሰበብ ኦርቶዶክሳዊያን ጎረብቶቼ ናቸው። ፀሐይ እና ስንታየሁ የሚባሉ እህትማማቾች "ጴንጤዎች ነደዱ ፥ ነጠላ ቀደዱ" የሚል የብሽሽቅ ዜማ ሲያዜሙ ስለሰማሁ ለነሱ ምላሽ የሚሆን ማብሸቂያ ፅፌ አነብኩላት። ሙልዬ ደስ እንደሚላት እርግጠኛ ነበርኩ። እሷ ግን አለቀሰች።

"እስከዛሬ በከንቱ ነው የደከምኩት ማለት ነው" አለችኝ በእንባ። "ያሰተማርኩት ሁሉ ሜዳ ላይ ቀረ? ለሰው ሁሉ ፍቅር ይኑራችሁ ብዬ አስተምሬ ሰዎችን የሚሰድብ ግጥም ፃፍክ" ብላ አለቀሰች።

ደነገጥኩ።

ሙሉዬ "ኢየሱስ እናንተን ይወዳል ፥ እናንተ ሰዎችን ሁሉ ውደዱ፥ የትኛውንም እምነት ተከታይ እንዳታዋርዱ። በሃይማኖት አትበሻሸቁ። የቱንም ሃይማኖት አትሳደቡ" እያለች ደጋግማ ነግራናለች።
በአንድ አጋጣሚ ተሳስቼ ብታዬኝ ራሷን ጥፋተኛ አደረገች። ያን ቀን ለተሰበሰብነው ልጆች ሁሉ "እናንተ ልብ ውስጥ ጥላቻ ካለ እኔ ራሴን እወቅሳለሁ፥ ማንንም አትጥሉ" አለች።

የቃለ ህይወት ልጅ ነኝ

ከቃለ ህይወት የሸመትኳቸው ዘመን ዘለል ትምህርቶች አሉ። ኢየሱስን መውደድ፥ ታላላቆችኝ ማክበር ፥ የሌላውን ሀይማኖት ማክበር ፥ ፅንፈኛ አለመሆን ፥ ለእውቀት ክብር መስጠት... ወዘተ ገና በልጅነት እድሜዬ ከቃለ ህይወት የተማርኩት ነው።

ቃለ ህይወትን እወዳለሁ።

"ወልድ ያለው ህይወት አለው" የሚለው የቃለ ህይወት መሪ ቃል የተለየ ስሜት ይፈጥርበኛል፥ የቃለህይወትን አርማ ማየት ደስተኛ ያደርገኛል።

ቃለ ህይወትን እወዳለሁ።

የሆነ ዘመን ላይ ቸርች መሄድ ተውኩ። መፅሐፍ ቅዱስ ማንበብ አቆምኩ። ፀሎትን ሸሸሁ። የእግዚአብሔር መኖር ላይ ጥርጣሬ ተፈጠረብኝ። በዚህ ሁሉ መሐል ግን ለቃለ ህይወት ያለኝ ፍቅር አልጎደለም። አርማው ፥ መሪ ቃሉ ፥ ወግ አጥባቂነቱ ፥ ስሙ ጭምር በልቤ ያላቸው ትልቅ ቦታ አልተፋቀም።

ቃለ ህይወትን እወዳለሁ።

የዘመኑ ጴንጤዎች ተብሎ ሲሰደብ "ቃለ ህይወትን ብታውቁ" ማለት ያምረኛል። የሌላውን እምነት የሚተናኮሱ ጴንጤዎችን ስመለከት ድንጋይ ሲወረወርባቸው ፥ ሲሰደቡ ፥ ሲጠቁ ዝም የሚሉትን ፣ ለበዳዮች ምህረትን የሚለምኑትን አባቶቼን አስቤ ጥፍሬ ስር መሸሸግ ያምረኛል።

ቃለ ህይወትን እወዳለሁ።

ቃለህይወት ነው ያደግኩት ስል ከትከሻዬ ቀና ከደረቴ ሰፋ ብዬ ነው።
ከወዳጆቼ ጋር ስነጋገር ቃለ ህይወትን ቃልዬ ነው የምለው።

የቃለህይወት ልጅ ነኝ
ቃለህይወትን እወዳለሁ።
ቃለህይወታዊያን "ወልድ ያለው ህይወት አለው" ይላሉ።

"ወልድ ያለው ህይወት አለው"

Via ተስፋኣብ ተሾመ

@Tfanos
11
ብልግናን የመሸለም ልማድ...
(ተስፋኣብ ተሾመ)
* * *

ዝነኛ እና ተወዳጅ ሰዎች የማህበረሰብን ንቃተ ህሊና ገላጭ ናቸው ብዬ አምናለሁ። ያከበርናቸው ሰዎች ስለ ግላዊ ስብዕናችን የሚናገሩት ብርቱ ሐቅ አለ።

ማንን ትወዳለህ? ማንን ታደንቂያለሽ? ማን ተፅዕኖ ያሳድርባችኋል?

ባለጌን የሚወድ ሰው ልብ ውስጥ ብልግና አለ። ዘረኛን የሚያድንቅ የሰወረው ዘረኝነት ይኖረዋል። በጥላቻ ከተሞላ ሰው በፍቅር የሚወድቅ ሰው ፥ ያው ነው እርሱም።

ነውርን የመግታት ሃላፊነት የማህበረሰብ ጭምር ነው። ማህበረሰብ ነውርን የሚቀጣበት መንገድ ሊኖረው ይገባል።

"አንድ ብር" የሚባለው ግለሰብ ምን እንዳደረገ ሰምተናል። አንዲትን ፍልስጤማዊት እናት ካዋረዳት በኋላ የተናገረው ነገር አስደንጋጭ ነው። "አሜሪካዎች የሚፈፅሙባችሁ ግፍ ትክክል ነው" የሚል ይዘት ያለው ንግግር ተናግሯል።

በአንድ ግለሰብ ላይ የሚፈፀም ኢ-ሰብአዊነት ለሰው ልጅ ሁሉ ስጋት ነው። በአንድ ስፍራ የሚደርስ ኢ-ፍትሃዊነት ለሁሉም አከባቢ አስጊ ነው። ይህን ሃቅ በልባችን መመዝገብ ይኖርብናል።

ከቅርብ ጊዜ በኋላ በማህበራዊ ገፆች ላይ ባለጌ ሰዎች ገናና ስም ይኖራቸዋል። ሚሊዮን መንጋ ያጨበጭብላቸዋል። ብልግናን ተሰብስበን እናነግሳለን።

አስደንጋጩ እና አሳሳቢው ነገር ፥ ብልግና ክፍያ የሚያስገኝ መሆኑ ነው። ተሳድበው ፥ ነውር ፈፅመው ፥ በመሃ* ይም መንገድ ተራምደው ዝና ያገኙ ሰዎች ፈጥነው ባለጠጋ ይሆናሉ። ትልልቅ ድርጅቶች ማስታወቂያ ያሰሯቸዋል። የብራንድ አምባሳደር ያደርጓቸዋል።

ብራንድ አምባሳደር ማለት ምን ማለት ነው?

ድርጅቶች ስለሚወክሏቸው ሰዎች ማንነት ግድ ሊሰጣቸው ይገባል። ተሳዳቢ ሰውን ብራንድ አምባሳደር ማድረግ "ተቋሜን የሚወክለው ስድብ ነው" የማለት ያህል ነው።

ደግሞም ማህበራዊ ሃላፊነት የሚባል ነገር አለ። ተቋማት ምርታቸውን የሚያቀርቡት ለህዝብ እስከሆነ ድረስ ህዝብን ማክበር አለባቸው። ህዝብ ማክበር የህዝብ እሴት በማክበር ይገለጣል።

ተሳድቦ ዝናን ላገኙ ሰዎች ማስታወቂያ አሰርቶ ገንዘብ መክፈል መብት ሊመስል ይችላል። ነገር ግን "ሌሎቻችሁም ተሳደቡና ዝና አግኙ፥ ከዛም ገንዘብ ትሰራላችሁ" የሚል መልእክት ማስተላለፍ ነው።

በአጭር ቃል ለተሳዳቢ እና ጋጠወጥ ሰዎች ማስታወቂያ ማሰራት እና ብራንድ አምባሳደር ማድረግ ፥ ለብልግና ደሞዝ መክፈል ነው።


@Tfanos
12
በቅርብ ቀን በአዲስ ስራ...

"የዙፋን ልፊያ"

ተስፋኣብ ተሾመ
15
ነገረ- ብልፅግና

እኛ ከሌላው አለም አንለይም። ፍፁማዊ የፖለቲካ ስርኣት አንጠብቅም። መንግስት እንከን የለሽ እንዲሆን አንመኝም።

በየትኛውም አለም ያለ የፖለቲካ አደረጃጀት (ገዢም ሆነ ተቃዋሚ) ፍፁማዊ ድጋፍን ከሕዝብ ሊያገኝ አይችልም። ዜጎች በተለያየ ምክኒያት ለመንግስታቸው ጭምር ተቃውሞ ቢኖራቸው የሚጠበቅ ምናልባትም ተፈጥሯዊ ነው።

ግን ደግሞ፥ በኢትዮጵያ ፖለቲካ እጅግ ምቾት የሚነሳ ነገር አለ። ዜጎች መንግሥትን ከመቃወም ማለፍ ጀምረዋል። ከገዢው ፓርቲ ወገን ለሚቀርብ ማንኛውም አይነት ሃሳብ መሳለቅን ምላሻቸው የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። ይኽ እንዲሆን ካደረጉ ነገሮች መካከል አንዱ ደግሞ በመንግሥት ላይ ያለ እምነት መሟጠጡ ነው።

ጥላቻ የተፈጠረባቸው ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለም። የገዛ መንግስታቸውን የሚጠሉ ኢትዮጵያን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው ብንል ደፋር ድምዳሜ አይሆንም።
የማይካድ ሃቅ አለ፤ ጥላቻ ወይም ፍቅር በአመዛኙ ለሁኔታዎች የሚሰጥ አፀፋ ነው። ቀላል ቁጥር የሌላቸው ዜጎች ገዢውን ፓርቲ ወደ መጥላት የተሸጋገሩት ክፉ ስነልቦና ስላላቸው ሳይሆን ከሚያዩት ምቾት የሚነሳ ነገር ተነስተው ነው። ጥላቻቸው መሰረት አለው። (አፀፋ ነው)

ከሁሉም የባሰው ክፉ ነገር ፥ መንግስት እና የገዢው ፓርቲ መሪ ለዜጎች ስሜት የሰጡት ፍፁም የተሳሳተ ትርጉም ነው። ፓርቲው ላይ የሚሰነዘረውን ተቃውሞ፥ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ላይ የሚቀርበውን ትችት፥ መንግስት ላይ የሚመጣውን ሂስ ሁሉ እጅግ በተሳሳተ መንገድ ተርጉመውታል።

በገዢው ፓርቲ እና በመሪው ብይን መሰረት መንግስት ላይ እምነት ያጡ፥ የተቃወሙ፥ በምሬት ወደመጥላት ያደጉ ሁሉ፥ ብሔራዊ ጥቅምን የሚጉዱ፥ ሉኣላዊነትን የሚንዱ፥ ሐገራዊ ክብርን አሳልፈው የሚሰጡ፥ ከብሔራዊ ጠላት ጋር የሚተባበሩ፥ ነገር ያልገባቸው፥ ማልቀስ የሚወዱ፥ ጨለምተኞች ወዘተ ተደርገው ተበይነዋል።
ከሁሉም የሚከፋው ነገር፥ ይኽ መንግስት ለተቺዎቹ የሰጠው የተሳሳተ ትርጉም ነው። እንዲህ ያለ ትርጉም ሲጎለበት ቅጥ ያጣ አምባገነናዊ ስርኣት ያዋልዳል፥ ሲብስ ደግሞ ሐገርን ቅርቃር ውስጥ ይከታል።

መንግስት ሆይ አተረጓጎምህን አርም!

ለነገሮች የሚሰጥ ትርጉም ቀጥሎ የሚመጣውን ይወስናል። ተቃውሞን በተሳሳተ መንገድ የሚተርጉም መንግስት ስህተቱን አያርምም። ለትችት ጆሮ የሚነፍግ ገዢ በጥፋቱ ይቀጥላል። የጥፋት ድግግሞሽ ፥ የስህተት ድርብርብ መጨረሻው ጥፋት ነው። መንግስት የሚከተለው የተሳሳተ አተረጓጎም ጥፋት ማዋለዱ አይቀርም። ዝቅ ሲል መንግስትን ጠልፎ ይጥላል፥ ሲከፋ ደግሞ ሐገርን የማይወጣ ቅርቃር ውስጥ ይከታል።


@Tfanos
👍51
"የደርግ አሽ*ከር ፥ የሻዕቢያ ጆሮ ጠቢ..."
(ተስፋኣብ ተሾመ)
* * *

ሳሚ ይባላል። አባቱ በዘመነ ደርግ የተመሰገነ ወታደር፥ የሐገር ጠባቂ ነው። በመልኩ ጥቁር የሆነው ኢትዮጲያዊ ኮረኔል ከአስመራ ሴት ተፋቅሮ ትዳር መሰረቱ፥ ልጆችንም አገኙ። ሁለቱ ተጣማሪዎች በትዳራቸው ደስተኛ ቢሆኑም ባል በሚስት ዘመዶች አልተወደደም። 'የኤርትራ ናፅነት እንዳይሳካ ሳንካ የሆነ የደርግ ወታደር' በመሆኑ ጠሉት፥ በመልኩም ተሳለቁበት።

የወታደሩ ልጅ ሳሚ እድሜው ደርሶ ወደ ትምህርት ገበታ ሲገባ በተማሪ ቤት ጓደኞቹ ተገለለ፥ እኩዮቹ ናቁት፥ ህፃናቱ ጠሉት። የእድሜ አቻዎቹ 'የባሪያ ልጅ' አሉት። በሰፈር እኩዮቹ ፥ በትምህርት ቤት አቻዎቹ መገለል የገጠመው ሳሚ ግልፍተኛ ሆነ፥ መደባደብንም አመሉ አደረገ።

ዘመን አለፈና አባት ሞተ፥ ዘመኑን ሙሉ ከሻቢያ ሲዋጋ የኖረው ኮረኔል አንቀላፋ። ከዚህ በኋላ የቤተሰብ ኑሮ ተናጋ። 'ከጠላታችን ወታደር ተጋብተሻል' ያሉ ዘመዷች እናትን ችላ አሏት። ልጆች ለመከራ ተዳረጉ። ይህ ያስጨነቃት እናት መላ ዘየደች። አዲስ አበባ ያለችን የባሏ እህት አስጠጊኝ አለች። 'የወንድምሽ ልጆች በችግር እየተጠበሱ ነውና ድርሽላቸው' ብላ ጠየቀች። አስመራን ለቃ ወደ አዲስ አበባ ተዛወራች።

አዲሳባ ሌላ ችግር ተወለደ። 'የሻቢያ ተላላኪ' ተባሉ፥ ሌላ መገለል እና መሰደብ ተከተለ። አስመራ ሳሉ ልጆች በአባታቸው ማንነት የተነሳ ተገፈሩ፥ አዲሳባ ሲገቡ ደግሞ የእናታቸው ማንነት የመገፋታቸው ሰበብ ሆነ። እናት የሻቢያ ሰላይ ተደርጋ ተቆጠረች። "ጆሮ ጠቢ ስለሆነች ተጠንቀቁ" ተባለ።

የእናት እውነተኛ ስም አስመራ ነው። ነገር ግን እናት ስሟን ፈራች። ከአስመራ ወደ አዝመራ ለወጠችው። 'አስመራ' የሚለው ስም ማንነቷን አሳብቆ እንደ ሻቢያ ተላላኪ የሚስቆጥራት ስለመሰላት 'ስሜ አዝመራ ነው' አለች።

ደርግ ዘመን ከዳው፥ ኢህአዲግ በለስ ቀንቶት መንበር ያዘ። የደርግ ሰራዊትም ተበተነ።

አንድ ቀን በብሔራዊ ቴሌቭዥን መለስ ዜናዊ ብቅ አለ። ይህን ሰኣት እነ ሳሚ ከእናታቸው ጋር ቴሌቭዥን እየተመለከቱ ነበር። መለስ ንግግር አደረ። የቀድሞ ወታደሮቹን 'የደርግ አሽከር' አለ። የጦር መኮንኑን 'ከህዝብ የሚሰርቅ ሌባ' ሲል ተናገረ።

እናት ይህን ስትሰማ እምር ብላ ተነሳች። በለቅሶ ስርኣት ደንብ ነጠላዋን ዘቅዝቃ ለበሰች፥ ምርር ብላ አለቀሰች። "አባታችሁ ዛሬ እንደ ተገደለ እመኑ" አለች ለልጆቿ። "ባሌ ዘመኑን ሙሉ በቀበሮ ጉድጓድ መሽጎ ሲዋጋ የከረመው የኢትዮጲያን ሉአላዊነት ሊያስከብር ነበር፥ ዛሬ ግን የደርግ አሽከር ተባለ" ብላ አለቀሰች። እንደ እብድ ሆነች።

ከዚያች ቀን በኋላ አዲስ ሰው ሆነች። በመራራ ሀዘን ውስጥ ገባች፥ ከማህበራዊ ኑሮ ራሷን አገለለች፥ ዝምተኛ ሆነች። ዝም እንዳለች ወደ ማይቀረው ሞት ተጓዘች።

ሳሚ በእናቱ ኤርትራዊ በአባቱ ኢትዮጲያውዊ ነው። እውነተኛ ስሙ ሳምረይ ቢሆንም ሳሚ ተብሎ ይጠራል። በኤርትራ ሳለ በአባቱ ማንነት የተነሳ ተገለለ፥ በኢትዮጲያ ደግሞ በእናቱ ሰበብ ባይተዋር ሆነ። ሐገር እያለው ሐገር አልባ ሆነ።

ለኤርትራዊያን አባቱ የደርግ አሽከር ነው። የናፅነት ጠላታቸው ነው። ለኢትዮጵያውያን ደግሞ እናቱ ጆሮ ጠቢ...

እውነት መስሎ ባይታየንም ፖለቲካ የግለሰቦች ህይወት ላይ ጥላውን ያኖራል፥ የፖለቲከኞች የግል አቋም የግለሰቦች ህይወት ላይ አሻራ ያሳርፋል፥ የፓርቲዎች ፕሮግራም ዜጎችን እስከማወክ ስልጣን ይኖረዋል። እውነት መስሎ ባይታይም ፖለቲካ የግለሰቦችን ህይወት በብርቱ ይዳስሳል።

ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ "ያልተቀበልናቸው" የሚል መፅሐፍ አለው። በመፅሐፉ ከላይ ያነሳነው የሳሚ ቤተሰብ ታሪክ ተካቷል። ታሪኩ እውነተኛ ነው።

እነሳሚ የአስመራ ስደተኛ ፥ የአዲስ አበባ ባይተዋር ናቸው። የእነሱ ቢጤ ስንት ሰው አለ?

@Tfanos
1
2025/10/23 03:09:35
Back to Top
HTML Embed Code: