"ከመድኃኒትነቱ የተነሳ ከቤቱ መሠረት ሳይናወጥ ከልዑል መንበሩ ወረዶ ጸጋንና ኃይልን አሳየ ። ሆሣዕና በአርያም ሆሣዕና በአርያም ሆሣዕና በአርያም። "
          ቅዳሴ ጎርጎርዮስ

እንኳን ለበዓለ ሆሣዕና በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ። አምላከ ቅዱሳን ለብርሃነ ትንሣኤ በሰላም ያድርሰን!!!
ብሒላተ አበው ወእመት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
Photo
✥✥✥ ዕለት ሰኞ ✥✥✥

- ይህ ዕለት አንጽሖተ ቤተ መቅደስ እና መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለተ ነው፡፡ በቅዱስ ማርቆስ ወንጌል እንደተገለጠልን ጌታችን ከቢታንያ ወጥቶ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ተራበ፡፡ በለስም ከሩቅ ዓየ፣ በለስዋ ግን ከቅጠል ብቻ በቀር ፍሬ ምንም ኣላገኘባትም ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ለዘለዓለም ፍሬ ኣይገኝብሽ ከአንቺ ፍሬ የሚበላ ኦይኑር አላት ያን ጊዜውንም በለሲቱ ደርቃለች (ማር.11፥12-19/ማቴ.21፥19/ሉቃ.19፥45-46)

በለስ የተባለች ኦሪት ናት፡- በለስ አገኘ ማለቱ ኦሪት በዚህ ዓለም ሰፍና አገኛት ሲል ነው፡፡ ወደ እርስዋም ሄደ ማለት ፈጻሜ ሕግ ተባለ (ሥርዓተ ኦሪትን ማለት በ8ኛው ቀን መገዘር በ40 ቀን መሥዋዕት ማቅረብን... እየፈጸመ አደገ) ማለት ነው፣ ፍሬ አላገኘባትም አለ ሕግ ከመባልዋ በቀር ድኅነትን አላደረገባትም፣ ፍሬ አይገኝብሽ አላት ሲል፡- ባንቺ ድኅንነት አይደረግ አላት፡፡ ይህም ቅዱ ዳዊት ‹‹መሥዋዕትን ቁርባንን አልወደድሁም ሥጋህን ኣንጻልኝ፣ የሚቃጠለውንና ስለኃጢኣት የሚቀርበውን መሥዋዕት አልወደድሁም ሲለ የኦሪትን ሕግ (ዐሠርቱ ትዕዛዛትን) አሳለፋቸው ማለት አይደለም፡፡ ቅዱስ ዳዊት እንደነገረን በመሥዋዕተ ኦሪት ፍፁም ድኅንነት ኣለመገኘቱን አውቆ ማሳለፉን እና ፍፁም ድኅንነት የምናገኝበትን ቅዱስ ሥጋውን እና ክቡር ደሙን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረቡን ያሳያል፡፡››

አንድም፦ በለስ ያለው ኃጢኣትን ነው፡፡ የበለስ ቅጠል ሰፊ እንደሆነ ኃጢኣትን በዚህ ዓለም ሰፍና ኣገኛት፡፡ ወደ እርሷ ሄደ ፍሬም አላገኘባትም ማለት በአይሁድ አንደበት በሐሰት ኃጢኣተኛ ተባለ እንጂ (ስለ እኛ መተላለፍ እንደበደለኛ ተቆጠረ እንጂ) ኃጢኣትን አልሠራም ሲል ነው፡፡ ፍሬ አይገኝብሽ ሲል፡- ባንቺ በመጣ ፍዳ የሚያዝ አይኑር አላት ማለት ነው፡፡

ከዚህ በመቀጠል ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፡፡ ቤተ መቅደሱም ቤተ ጸሎት፣ ቤተ መሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተ ምስያጥ (የንግድ ቤት) ሆኖ ቢያገኘው ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኋት ብሎ በዚያ ያሉትን ሁሉ አስወጣቸው፡፡ ይኸም በጠቅላላው ማደሪያው ቤቱ የነበርን የአዳም ለጆች ኃጢኣት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያገኘን ኃጢኣታችንን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው፡፡ (ማቴ.21፥12-17/ማር.11፥15-24/ሉቃ.19፥4)
በሰሙነ ሕማማት የካህናት የጸሎት ማሳረጊያ፦

➦ እንበለ ደዌ ወሕማም፤ እንበለ ፃማ ወድካም፤ ዓመ ከመ ዮም፤ ያብጽሐኒ ያብጽሕክሙ ለብርሃነ ትንሣኤሁ እግዚአብሔር በፍስሐ ወበሰላም አሜን።

ትርጉም:-
➦ ያለ ደዌና ያለ ሕማም ያለ ፃማ (ሥቃይ፣ መከራ) ያለ ድካም እግዚአብሔር ለትንሣኤው ብርሃን በደስታና በሰላም ያድርሰኝ ያድርሳችሁ።
አሜን 🙏
"ሰላም ለኪ ሐመረ ብዕል፡ ሙዳየ ዕፍረት ቢረሌ ጽዱል፡ ምዕራፈ ተድላኪ በብሔር ጥሉል፡ መልክአ ገጽኪ በአርያም ስዑል"

(መልክአ ሕማማት፤ ዘሰዓተ ሠርክ)

* "መልክአ ገጽኪ በአርያም ስዑል" - 'የፊትሽ መልክ በሰማይ የተሳለ' ... ህምምም ... ተመስጦ 😇
* ስብሐት ለከ ኢየሱስ በአፈ ኲሉ ውዱስ፤
+ በኹሉም አፍ የተመሰገንኽ ኢየሱስ ሆይ ምስጋና ላንተ ይገባል

* ስብሐት ለከ ኢየሱስ ቀዳሴ ሥጋ ወነፍስ፤
+ ሥጋንና ነፍስን ያከበርኽ ኢየሱስ ሆይ ምስጋና ላንተ ይገባል

* ስብሐት ለከ ኢየሱስ ለዕሩቃን ልብስ፤
+ [በኃጢአት] ለተራቆቱት [የጸጋ] ልብስ የኾንኽ ኢየሱስ ሆይ ምስጋና ላንተ ይገባል

* ስብሐት ለከ ኢየሱስ ዘኢትሠዐር ንጉሥ፤
+ የማትሻር ንጉሥ ኢየሱስ ሆይ ምስጋና ላንተ ይገባል

* ስብሐት ለከ ኢየሱስ ቃለ አብ ቅዱስ
+ ቅዱስ የአብ አካላዊ ቃል ኢየሱስ ሆይ ምስጋና ላንተ ይገባል።

(መቅድመ ተአምረ ኢየሱስ)
ችንካሮች

“ከልቦቻችን በማይነቀሉ የፍቅሩ ችንካሮች ተቸነከርን። ያዝነው አንለቀውም እርሱም አቀፈን አልተወንም። ወደ እርሱ በሃይማኖት አቀረበን። ከእርሱም ወደ ቀኝ ወደ ግራ አንሸሽም። እንደ ቀለበት በልባችን እንደ ማኅተም በክንዳችን አኖርነው። እንደ ዕንቁ በልባችን ሳጥን አስቀመጥነው። እንደ ወርቅ በሕሊናችን መዝገብ አኖርነው።

እንደ ግምጃ ለበስነው። እንደ ሐር ግምጃ ተጎናጸፍነው። እንደ ወታደር ሰይፍ ታጠቅነው። ለጦር ዕቃ እንደተዘጋጀ የድል ጋሻ ተደገፍነው። ተከዜና ግዮን በኢሎል ወር እንደሚሞሉ ፍቅሩ በልባችን መልቶአል። እንደ መከር ጊዜ የዮርዳኖስ ወንዝ እንደ ክረምት ጊዜም የጤግሮስ ወንዝ ስንዴ ሲያሹት እንደሚሆን እንደ ኤፍራጥስ ወንዝ ልባችንን በወንጌል ፈሳሽነት አረሰረሰው። መርከባችንንም በሃይማኖት ወንዝ አስዋኘው" 

ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ 
መጽሐፈ ምሥጢር 24:20
"በሠላሳ ብር በርካሽ ዋጋ የተሸጠው እርሱ ዓለምን በውድ ዋጋ ገዛ፤ ይኸውም ክቡር ደሙ ነው።"
ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ
".... ዐይኖችን በሚፈጥር ፊት ምራቃቸውን ተፉበት። ዳግመኛም ፊቱን በጥፊ መቱት። ኪሩቤል ፊቱን ከማየት የተነሣ በእሳት አክናፍ የሚሠወሩት ያልበደላቸውን እሱን አይሁድ ፊቱን ጸፉት፤ ፊቱ እንደ መንፈስ ቅዱስ፣ እንደ አባቱ ሲሆን በሥጋው ፊቱን ጸፉት፤ ከፊቱ ግርማ የተነሣ ፍጥረቱ ሁሉ የሚርዱለት፣ የሚንቀጠቀጡለት የፈጣሪያቸውን ፊቱን ጸፉት። መዠመሪያ በመመታቱና የሾኽ አክሊል በመሸዳጀቱ ራሱ የቆሰለ ከመሆኑ በላይ የያዘውን በትር ከእጁ ተቀብለው ራሱን መቱት።
ነገር ግን የሾኽ አክሊልን በመቀዳጀቱ በምድራችን ላይ የበቀሉትን አሜከላና እሾኽ እርግማንን አጠፋልን። ራሱንም በዘንግ በመመታቱ የታላቁን እባብ ሰባቱን እራሶቹን ዐሥሩ ቀንዶቹን አጠፋልን።"

         የኅሙስ ድርሳነ ማኅየዊ
❖ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ❖

"አዳምን የፈጠሩ እጆች በመስቀል ቀኖት ተቸነከሩ ፡ ወዮ ፤ በገነት የተመላለሱ እግሮች በመስቀል ቀኖት ተቸነከሩ ፡ ወዮ ፤ በአዳም ፊት የህይወት መንፈስን እፍ ያለ አፍ ከሃሞት ጋራ የተቀላቀለ የኮመጠጠ መፃፃን ጠጣ ፡ ወዮ ፤ የወልድን መከራውን የሚናገር ምን አፍ ነው? ምን ከንፈር ነው? ምን አንደበት ነው? የፍቅር ጌታ ሕማማት በተነገረ ጊዜ ልብ ይለያል ፡ ህሊናም ይመታል ፡ ነፍስም ትንቀጠቀጣለች ፡ ስጋም ይደክማል፡፡ የማይሞተው ሞተ ፡ ሞትን ይሽረው ዘንድ ሞተ ፡ ሙታንን ያድናቸው ዘንድ ሞተ ፤ የምትወዱት ሰወች ፈፅሞ አልቅሱለት ፤ ወየው ወየው ወየው አማኑኤል አምላካችን፡፡ ወየው ወየው ወየው መድሃኒታችን ኢየሱስ ፤ ወየው ወየው ወየው ንጉሳችን ክርስቶስ ፤ ወየው ወየው ወየው ፃድቃን ከእንጨት አወረዱት ስጋውንም ለመገነዝ ከርቤ የሚባል የጣፈጠ ሽቱንና ንፁህ በፍታን አመጡ፡፡ ሞተም ተቀበረም ፤ ሙስና ሳይኖርበት ከሙታን ተለይቶ ፈፅሞ ተነሳ ፤ ከሃጢአት ቀንበርም ነፃ አደረገን ፤ በዚያች ስጋ በመለኮት ሃይል ወደ ሰማይ ወደ ቀደመ አኗኗሩ አረገ፡፡"
#በመቃብር_አደረ

"ዳግመኛም ይህ ሥጋ ከመለኮቱ ሳይለይ በመቃብር አደረ ነፍሱም ከመለኮት ሳትለይ በገሀነም ተግዘው ለነበሩ ነፍሳት ድኅነትን ታበስር ዘንድ፤ ነፃም ታደርጋቸው ዘንድ ወደ ሲኦል ወረደች።"

ሃይማኖተ አበው ዘአትናቴዎስ
"ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም፤ በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ።"
አባ ሕርያቆስ
እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ልደት አደረሰን 🙏🙏🙏
"ሰይጣንም የአንቺን ምስጋና ወሬ ሲሰማ በብስጭት ጥርሱን ያፏጫል፤ የምስጋናሽ ወሬ በእርሱ ዘንድ መራጃ ነውና እራሱን ይቆርጠዋል፡፡ ከስምሽ አጠራር የተነሣ መብረቅ በኃይል ሲጮህ እንደ ሰማ ሁሉ ይደነግጣል፡፡ አንቺ ከተወለድሽ ጀምሮ ፈጽሞ ዕረፍት አላገኘም፡፡ በአንቺ ታመመ በልጅሽም ተጨነቀ በአንድ ልጅሽ መስቀል ሥቃይ አገኘው፡፡ ከፍጡራን ወገኖች ሁሉ ይልቅ ሰይጣል አንቺን ይጠላል፡፡"

#አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ
2024/05/09 09:33:10
Back to Top
HTML Embed Code: