Telegram Web Link
#ጼዴንያ - #መስከረም_10

መስከረም ዐሥር በዚች ቀን ጼዴንያ በምትባል አገር ሥጋ የለበሰች ከምትመስል ሥዕል ከሠሌዳዋ ቅባት እየተንጠፈጠፈ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም ተአምር ተገለጠ።

ይቺንም ሥዕል የሣላት ወንጌላዊ ሉቃስ ነው ይባላል። ወደ ጼዴንያ አገርም የመጣችበት ምክንያት አንዲት ስሟ ማርታ የሚባል መበለት ሴት ነበረችና ቤቷንም ለእንግዳ ማደሪያ ያደረገች ናት። አምላክን የወለደች እምቤታችን ድንግል ማርያምንም እጅግ ትወዳት ነበር። በሚቻላትም ሁሉ ታገለግላታለች።

በአንዲት ቀንም ስሙ ቴዎድሮስ የሚባል መነኩሴ ከእርሷ ዘንድ እንግድነት አደረ በመልካም አቀባበልም ተቀበለችው በማግሥቱም ስተሸኘው አባት ሆይ የምትሔደው ወዴት ነው አለችው። እርሱም በከበሩ ቦታዎች ውስጥ ልሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም እሔዳለሁ አላት እርሷም ከእኔ ገንዘብ ወስደህ የእመቤታችን ማርያምን ሥዕል ግዛልኝና በመመለሻህ ጊዜ አምጣልኝ አለችው። እርሱም በራሴ ገንዘብ ገዝቼ አመጣልሻለሁ አላት።

ከዚህም በኋላ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከቅዱሳት መካናት ተባረከና ሥዕሏን ሳይገዛ ወደ ጎዳናው ተመለሰ። ያን ጊዜም ሥዕል መግዛትን ለምን ረሳህ የሚል የሚያስደነግጥ ቃልን ሰማ ወደ ገቢያም ተመልሶ ላሕይዋና መልኳ ያማረና የተወደደ የሆነ የእመቤታችን ማርያምን ሥዕል አግኝቶ ገዛት በሐርና በንጹሕ ልብስም ጠቀለላት።

በጎዳናውም እየተጓዘ ሳለ ከሚያስፈራ ዱር ውስጥ ወንበዴዎች ተነሡበት ሊሸሽም ወደደ ከዚያቺም ሥዕል መንገድህን ሒድ የሚል ቃል ወጣ የተከተለውም ሳይኖር መንገዱን ተጓዘ። ሁለተኛም ነጥቆ ሊበላው አንበሳ ተነሣበት ያን ጊዜም ከዚያች ሥዕል የሚያሥፈራ ድምፅ ወጥቶ አንበሳውን አባረረው።

አባ ቴዎድሮስም ይህን ሁሉ ድንቅ ተአምር ባየ ጊዜ ያቺን ሥዕል ወደ አገሩ ሊወስዳት ወደደ ግዛልኝ ላለችው መበለት ይሰጣት ዘንድ አልፈለገም።

ከዚህም በኃላ በመርከብ ተሳፍሮ በሌላ አቅጣጫ ሲጓዝ ታላቅ ነፋስ ተነሣበት ወደ ማርታ አገር ወደ ጼዴንያም ወሰደው ከመርከቡም ወርዶ ከብዙ እንግዶች ጋር ወደዚያች መበለት ቤት ሔደ ማንነቱንም አልገለጠላትም እርሷም አላወቀችውም።

በማግሥቱም ተሠውሮ ወጥቶ ወደ አገሩ ሊሔድ በፈለገ ጊዜ የቅጽሩን ደጃፍ አጥቶ ሲያጥመሰምስ ዋለ በመሸ ጊዜም ወደ ማደሪያው ተመለሰ። ያቺም መበለት በአየችው ጊዜ ታደንቃለች እንዲህም ሁኖ እስከ ሦስት ቀን ኖረ በመሸ ጊዜ በሩን ያየዋል ነግቶ መሔድን ሲሻ የበሩ መንገድ ይሠወረዋል። ያቺም መበለት ያዝ አድርጋ አባቴ ሆይ አእምሮህ ተነክቷልን ስትቅበዘበዝ አይሀለሁና ምን ሆነህ ነው አለችው።

ከዚህም በኋላ ከዚያች ሥዕል የሆነውን ሁሉ ነገራት ራሱንም ገለጠላት። ያቺንም ሥዕል ሰጣት ተቀብላም የተጠቀለለችበትን ልብስ ፈታች ወዝ ከሥዕሊቱ ሲንጠፈጠፍ አገኘች። ከደስታዋም ብዛት የተነሣ የዚያን መነኩሴ እጆቹንና እግሮቹን ሳመች።

ከዚህም በኋላ ያቺን ሥዕል ወደ ጸሎት ቤቷ ወስዳ በታላቅ ክብር የምትቀመጥበትን አዘጋጅታ አኖረቻት ማንም እንዳይዳስሳትም የነሐስ መስኮትን ሠራችላት በቀንና በሌሊትም የሚበሩ መቅረዞችን በፊቷ ሰቀለች ከመቅረዞችም ውጭ የሐር መጋረጃን ጋረደች። ከሥዕሊቱ በታችም ከሥዕሊቱ እየተንጠፈጠፈ የሚወርደው የወዝ ቅባት የሚጠራቀምበት ከዕብነ በረድ የተሠራ ወጭት አኖረች ያም መነኩስ እስከሚሞትበት ቀን ድረስ የእመቤታችንን ድንግል ማርያምን ሥዕል እያገለገለ ኖረ።

የሀገሩም ሊቀ ጳጳሳት የዚያችን ሥዕል ዜና በሰማ ጊዜ ከኤጲስቆጶሳትና ከካህናት ከሕዝቡም ሁሉ ጋር መጣ በሠሌዳውም ውስጥ በአዩዋት ጊዜ ሥጋ የለበሰች ሁና አገኙዋት ከዚህ ከአምላካዊ ግብር የተነሣ አደነቁ ከዚህም ቅባት ቀድተው ለበረከት በተካፈሉ ጊዜ ወዲያውኑ በወጭቱ ውስጥ ይመላል።

ወደ ሌላ ቦታም ሊወስዷት በፈለጉ ጊዜ ንውጽውጽታ ሆኖ ብዙዎች በድንጋጤ ወደቁ ሥዕሊቱም እስከ ዛሬ በዚያች አገር ትኖራለች።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእናቱ በእመቤታችን በድንግል ማርያም ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም)
81🙏11🕊5💔2
ስለ ጌጠኛ ልብስ - ፩

ዕርቃናችንን የምንሸፍንበት ልብስ ብቻ ልንለብስ ይገባናል፡፡ ብዙ ወርቅን ብናደርግ ምንድነው ትርጉሙ? ብዙ ወርቅን ማድረግ በተውኔት ቤት ነው፤ ተዋንያን ብዙ ተመልካችን ለማግኘት ያደርጉታልና፡፡ ጌጠኛ ልብስ መልበስ የአመንዝራ ሴቶች ግብር ነው፤ ብዙ ወንዶች ይመለከቱአቸው ዘንድ ይህን ያደርጋሉና፡፡ እነዚህን ማድረግ ልታይ ልታይ ለሚሉ ሰዎች ነው፡፡ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት የምትሻ ሴት ግን ይህን ጌጥ ማድረግ አትፈልግም፡፡ ራስዋን የምታስጌጠው በሌላ መንገድ ነውና፡፡

እናንተም ይህን ጌጥ ማድረግ የምትፈልጉ ከኾነ ማድረግ ትችላላችሁ፡፡ ተውኔት ቤትን የምትሹ ከኾነም ወርቀ ዘቦአችሁን የምታደርጉበት ሌላ ተውኔት ቤት አለላችሁ፡፡ ያ ተውኔት ቤትስ ምንድን ነው? መንግሥተ ሰማያት ነው፡፡ ተመልካቾቹ ቅዱሳን መላእክት ናቸው፡፡ ይህን የምናገረው በገዳም ለሚኖሩት መኖኮሳይያት ብቻ አይደለም፤ በማዕከለ ዓለም ለሚኖሩትም ኹሉ ጭምር ነው እንጂ፡፡ በክርስቶስ ክርስቲያን በወልድ ውሉድ የተባለ ኹሉ የራሱ ተውኔት ቤት አለውና፡፡

ስለዚህ ተመልካቾቻችንን ደስ ለማሰኘት ራሳችንን ደኅና አድርገን እናጊጥ ብዬ እማልዳችኋለሁ፡፡ ለመድረኩ የሚመጥን ልብስን እንልበስ ብዬ እማፀናችኋለሁ፡፡ እስኪ ንገሩኝ! አንዲት ሴሰኛ ሴት ተውኔት ለመሥራት ብላ ብዙ ወርቋን አወላልቃ፣ ቄንጠኛ መጎናጸፍያዋን ጥላ፣ በሳቅ በስላቅ ሳይኾን ቁም ነገርን ይዛ፣ ተርታ ልብስን ለብሳ ወደ መድረኩ ብትወጣና ሃይማኖታዊ ንግግርን ብትናገር፣ ስለ ንጽህና ስለ ቅድስና ብትናገር፣ ሌላ ክፉ ንግግርም ባትጨምር በተውኔት ቤቱ የሞላው ሰው አይነሣምን? ተመልካቹ ኹሉ የሚበተን አይደለምን? ሰይጣን የሰበሰበው ተመልካቹ የማይፈልገውን ነገር ይዛ ስለ መጣች ኹሉም የሚሳለቅባትና እንደ ትልቅ አጀንዳ የሚወራላት አይደለምን? አንተም በብዙ ወርቅ፣ በጌጠኛ ልብስ ተሸላልመህ ወደ መንግሥተ ሰማያት ብትገባ ቅዱሳን መላእክት አስወጥተው ይሰዱሃል፡፡ ምክንያቱም በመንግሥተ ሰማያት የሚያስፈልገው ልብስ እንደዚህ ዓይነት አይደለም፤ ሌላ ነው እንጂ፡፡ “እርሱስ ምን ዓይነት ነው?” ትለኝ እንደኾነም “ነፍስን በትሩፋት ማስጌጥ ነው” ብዬ እመልስልሃለሁ፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት፡- “ልብሷ የወርቅ መጐናጸፍያ ነው” ያለውም ይህንኑ ነው እንጂ በዚህ ምድር የምንለብሰው ልብሳችንን ፀዓዳና አንጸባራቂ ስለ መኾን አይደለምና (መዝ.45፡13)፡፡ ምክንያቱም “ለሐሴቦን ንጉሥ ልጅ ኹሉ ክብሯ ነው” እንዳለ በዚያ (በመንግሥተ ሰማያት) መራሔ ተውኔቷ እርሷ ናት፡፡

ይቀጥላል...

(የክርስቲያን መከራ እና ሌሎች ቅዱስ ዮሐንስ_አፈወርቅ እንደአስተማረው ገጽ 47-55➛ገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተረጎመው)
77🙏18👍2
እናመሰግናለን

ነገ መስከረም 11/2018 በሰሜን ወሎ ወልድያ ማረሚያ ቤት ከሚገኙ ታራሚዎች ጋር  በምናካሂደው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በዕለቱ ለምናስረክበው የመጽሐፍ ቅዱስ ስጦታ ከ27 የቻናላችን ቤተሰቦች ብር 49,550 የተገኘ ሲሆን በዚህም ለመግዛት የሚያስችለውን 40 መጽሐፍ ቅዱስ በነገው እለት የምናስረክብ ሲሆን፤ በዚህ መልካም ተግባር የተሣተፋችሁ፣ ለመሣተፍ አስባችሁ ያልተሳካላችሁ እንዲሁም በጸሎት ያገዛችሁን ኹሉ በኃያሉ በልዑል እግዚአብሔር ስም ምስጋናችን ይድረሳችሁ።

ማሳሰቢያ፦
መጽሐፍ ቅዱስ ለመግዛት ያሰብነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በ900 ብር ሒሳብ የነበረ ቢሆንም በዚህ ወቅት በማኅበሩ ያለው የኅትመት መጠን አናሳ መሆን የተነሳ ከወልድያ መንበረ ንግሥት ኪዳነ ምሕረት የመሠረተ ሕይወት ሰንበት ት/ቤት ልማት ተቋም ከመደበኛ ዋጋው በመቀነስ በብር 1200 ዋጋ 40 መጽሐፍ ቅዱስ የገዛን መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን።
56🙏7😍2
ዛሬ በሰሜን ወሎ ማረሚያ ቤቶች በወልድያ ማረሚያ ቤት የወልድያ ከተማ አስዳደር ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበባት አክሊለ ብርሃን በተገኙበት ከስብከተ ወንጌል አገልሎት በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ስጦታውን ለታራሚዎች ኮሚቴ አስረክበናል።
58🙏12👍3👌1
ስለ ጌጠኛ ልብስ - ፪

....እኅቴ ሆይ! ራስሽን መሸላለም ብትፈልጊ እንዲህ አጊጪ፡፡
ከዚያም ከምረረ ገሃነም ትድኛለሽ፡፡ ባልሽንም ከማዘን ከመቆርቆር ትታደጊዋለሽ፡፡

ባልሽ እጅግ ደስ የሚሰኘው እንዲህ ስታጌጪ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ወንዶች ሚስቶቻቸው “ሥጋችንን እናጊጥ” ሲሉአቸው ደስ አይላቸውም፡፡ እንዲህ በሚያዘወትሩ ሚስቶቻቸውም ያፍራሉ፡፡ ከክብረ ሥጋ ይልቅ ክብረ ነፍስን የምታስቀድሙ ከኾነ ግን ገንዘብ ስጡን ስለማትሉአቸው ሰጠናቸው ብለው ከመታበይ ይድናሉ፡፡ እኔ እበልጥ የሚል ስሜታቸው ይወገዳል፡፡ ምድራዊ ወርቅን እንደማትፈልጊና ለዚያ መግዣ የሚኾን ገንዘብ ሳትጠይቂው ሲመለከት እጅግ ቁጡ ቢኾንም አጊጠሸ ከሚያከብርሽ በላይ ሳታጌጪ ያከብርሻል፡፡ አንቺም የእርሱ ተገዢ አትኾኚም፡፡ የሰው ተገዢ የምንኾነው ከዚያ ሰው ብዙ [ምድራዊ] ነገርን የምንሻ ከኾነ ነውና፡፡ በዚህ ዓለም አላፊና ጠፊ ነገር ግድም እንደሌለን ሲያውቅ ግን ያ ሰው እኛ ላይ የሚሠለጥንበት ምክንያት የለውም፡፡ በመኾኑም እንደዚህ ስትኾኚ ባልሽን የምትታዘዢው ጊዜአዊ ነገር ስለ ሰጠሸ ሳይኾን እግዚአብሔርን ፈርተሸ እንደ ኾነ ይገነዘባል፡፡ ከዚህ በኋላ አንድ ነገር ስላደረገልሽ ብታመሰግኚው እንኳን የሰጠሽው ክብር ስላደረገው ነገር እንዳልኾነ ይረዳል፡፡ አንቺ በምላሹ የሰጠሽው ነገር ትንሽ ቢኾንም ትንሽ ነው ብሎ አይቈጥረዉም፡፡ ወይም አይበሳጭም፡፡

በብዙ ወርቅ መሸላለምና ጌጠኛ ልብስን ለብሶ በአደባባይ ከመዞር በላይ ምን ስንፍና አለ? በአደባባይስ ብዙ ባልደነቀኝ፤ እንዲህ ተሸላልማ ወደ ቤተ ክርስቲያን የምትመጣ ግን እጅግ ሰነፍ ናት፡፡ “በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቁ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸላለሙ” የሚለውን ቃል መስማት ሲገባት እንዲኽ አጊጣና ተሸላልማ የምትመጣው ምን ለማድረግ ነው? (1ኛ ጢሞ.2፥9)፡፡ አንቺ ሴት እስኪ ንገሪኝ! ምን ለማድረግ ነው የመጣሽው? ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ጠብ ክርክር ለመግጠም ነውን? እልፍ ጊዜ እንዲህ አትልበሺ ብሎ ቢነግርሽም ንቀሽው አጥቅተሺው መምጣትሽ ምን ለማድረግ ነው? ወይስ ቅዱስ ጳውሎስን መስለን እንዲህ የምናስተምረው መምህራን ትምህርቱን በከንቱ እንዳስተማርን ዐይተን እንድናፍር ሽተሸ ነው? እኮ ንገሪኝ! አንድ እነዚህን የቅዱስ ጳውሎስ ቃላት የሰማ ኢአማኒ ባል “በወርቅ ወይም በዕንቁ ወይም በከበረ ልብስ አይሸላለሙ” የሚለውን የሐዋርያው ቃል ለመስማት ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመኼድ የምትዘጋጀውን ክርስቲያን ሚስቱ ራስዋን በብዙ እንደምትሸላልም፣ ጌጠኛ ልብስን እንደምታደርግ ቢያያት ምንድን ነው የሚለው? “ባለቤቴ ምን እየሠራች ነው? በመስታወቱ ፊት ይህን ያህል ሰዓት መቆየቷ ስለ ምንድን ነው? ይህን ያህል ወርቅ መልበስዋ ለምንድን ነው? መኼድ ያሰበችው ወዴት ነው? ወደ ቤተ ክርስቲያን ነውን? ምን ለማድረግ? በወርቅ ወይም በዕንቁ ወይም በከበረ ልብስ አይሸላለሙ የሚለውን ቃል ለመስማት ነውን?” እያለ ብዙ አይዘብትምን? ብዙስ አይሳለቅምን? ሃይማኖታችንስ ስላቅና ማታለል እንደ ኾነች አያስብምን?

ይቀጥላል...

(የክርስቲያን መከራ እና ሌሎች ቅዱስ ዮሐንስ_አፈወርቅ እንደአስተማረው ገጽ 47-55➛ገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተረጎመው)
61🙏19😍3👍2
"ለቤተ መቅደስህ ተክል ያደረግኸኝ፡፡ አቤቱ ሆይ የውጭ ተክል አታድርገኝ፡፡ የጽድቅ ተክል አድርገኝ፡፡ የኃጢአት አይደለም፡፡ የዕውነት ተክል አድርገኝ የሐሰት አይደለም የፍቅር ተክል አድርገኝ የጥል አይደለም፡፡

የመጻሕፍት መጀመሪያ የምትሆን ኦሪት ደመና የምትጋርደኝ፡፡ ከቅዱስ ወንጌል ፈሳሽ የምጠጣ ከጎንህ ከፈሰሰው ደም የምረካ ልሁን፡፡ በእናትህ በድንግል ጸሎት የሃይማኖት አበባ ላብብ፡፡ የጽድቅ ፍሬን ላፍራ ከቅዱሳንህ ሐዋርያትም ከቃላቸው ፍሬ የተነሣ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ የተባረከ የወይን ቦታ ልባል የጽድቅን ፍሬ የሚያስቀረውንም የኃጢአት እሾህ ጠምዝዘው ከደጁም አሜከላውን አረሙንም ሙጃውንም ንቀለው፡፡ አቤቱ ከኔም አርቀው ሥርዓትህን የሚሠሩትን ያበባቸውን ፍጻሜ እንዳፈራ አድርገኝ"

ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
96🙏24💯4
በማረሚያ ቤት ውስጥ ለሚገኙ የሕግታራሚዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ስጦታ ተበረከተ።

መስከረም 11/2018 ዓ.ም (ሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሚዲያ)

በሰሜን ወሎ መንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት የወልድያ ከተማ አስተዳደር ቤተክህነት የስብከተ ወንጌል ክፍል 50 መጽሐፍ ቅዱስ ለሰሜን ወሎ ማረሚያ ቤት የሕግ ታራሚዎች በስጦታ አበርክቷል።

በዛሬው ዕለት በከተማ አስተዳደር ቤተክህነቱ የስብከተ ወንጌል ክፍል የ2018 ዓ.ም የመጀመሪያ ልዩ ጉባኤ ከታራሚዎች ጋር ያከናወነ ሲሆን ዋና ሥራ አስኪያጁ መጋቢ ጥበባት አክሊለ ብርሃን ተመስገን ትምህርተ ወንጌል ሰጥተው መጻሕፍቱንም አስረክበዋል።

በከተማ አስተዳደር ቤተክህነቱ የስብከተ ወንጌል ክፍል ኀላፊ መ/ር ቡሩክ ተስፋዬ አስተባባሪነት ከበጎ አድራጊዎች በተሰበሰበ የገንዘብ ድጋፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ስጦታ የተበረከተ ሲሆን በቀጣይም የልዩ ጉባኤያት አገልግሎቱና የመጻሕፍት ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

መጻሕፍቱ ሰሎሞን አያሌው ከቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የቴሌግራም ቻናል ቤተሰቦች፣ ቀሲስ ሠምረ ሞላ ከንስሐ ልጆቻቸውና ከሌሎች በጎ ፈቃደኞች በተሰበሰበ ከ70 ሺህ ብር በላይ ወጪ የተገዙ ናቸው።

የመጻሕፍት ስጦታውን የተረከቡት የማረሚያ ቤቱ አስተባባሪዎችና ታራሚዎች የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው በማረሚያ ቤት ሰፊ ጊዜ ቢኖራቸውም የመጻሕፍት ዋጋ ውድ በመሆኑ ገዝተው ለማንበብ ይቸገሩ እንደነበር ገልጸዋል።

ታራሚዎቹ እንዲህ ያለው ድጋፍ ለወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

#የሰሜን_ወሎ_ሀገረ_ስብከት_የማኅበራዊ_ሚዲያ_አማራጮችን_ይወዳጁ_ለሌሎችም_ያጋሩ
~ቴሌግራም፡ https://www.tg-me.com/NWDnews
~ዩቲዩብ፡ https://youtube.com/c/NorthWolloDioceseMedia
~ድረገጽ፡ https://eotc-nw.org
~ፌስቡክ፡https://www.facebook.com/EOTCNWD?mibextid=ZbWK
~ https://www.tiktok.com/@eotc.north?_t=ZM-8ukkHRXMOYg&_r=1
34😍1
2025/10/21 23:32:00
Back to Top
HTML Embed Code: