Telegram Web Link
የቃና ሰርግ ቤት ታሪክ ለጊዜው እናቆየውና አንድ ልጅ በአደባባይ በሰዎች ፊት እናቱን በምንም ምክንያት ቢቆጣ እንኳን ከሃይማኖት አንጻር ከሥነ ምግባርም አንጻር የሚደገፍ ሥራ አይደለም፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን ‹እናቱን በቁጣ ተናገራት› የሚለው አስተሳሰብም እንዲሁ ብዙ የሚያመጣው ጣጣ አለ፡፡ ‹‹እናትና አባትህን አክብር›› ‹‹እናቱን የሰደበ ይሙት›› የሚለውን ሕግ የሠራ አምላክ ‹እኔን ምሰሉ› እያለ ለሰው ልጆች አርኣያ ሊሆን በመጣበት በዚህ ዓለም ራሱ እናቱን በአደባባይ በሰው ፊት ያቃልላታል ብሎ ማሰብ እጅግ ከባድና ለብዙ ሰዎች የኃጢአትን በር ወለል አድርጎ ከፍቶ መረን የሚለቅ ነው፡፡ (ዘጸ. ፳፥፲፪ ፣ ፳፩)

እመቤታችንን የጎዱ መስሏቸው ‹ጌታ እናቱን ተቆጣ› ብለው የሚሰብኩ ሰዎችም ሳያውቁት እየተናገሩ ያሉት በእመቤታችን ላይ ሳይሆን በራሱ በጌታችን ላይ ነው፡፡ ጌታችን ‹‹ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚወቅሰኝ ማን ነው?›› ብሎ የተናገረ ንጹሐ ባሕርይ ነው፡፡ (ዮሐ. ፰፥፵፮) ‹የሚጤስን የጧፍ ክር የማያጠፋ ፣ የተቀጠቀጠ ሸንበቆን የማይሰብር› በአነጋገሩ ጭምት ነው፡፡ ስንክሳሩም ‹‹ወንድሜ ምእመን ሆይ ጌታችን ለንጽሕት እናቱ ለድንግል ማርያም ከአንቺ ጋር ምን አለኝ ጊዜዬ ገና አልደረሰም በማለቱ የክብርት እናቱን ቃል እንዳቃለለ አታስብ›› ይላል፡፡ (ስንክ. ጥር ፲፪ ቁ. ፵)

በማስከተልም ‹‹ጌታችን የሰማያዊውና የመለኮታዊ አባቱን ክብር እንደጠበቀ ይታወቅ ዘንድ እንዲሁ ከእርስዋ ፍጹም ሥጋንና ፍጽምት ነፍስን ነሥቶ ከመለኮቱ ጋር ያዋሐደውን የእናቱን ክብር ጠበቀ፡፡ በወንጌል ይታዘዛትና ይላላካት ነበር ተብሎ እንደተጻፈ›› ይላል፡፡ (ስንክ.ጥር ፲፪ ቁ. ፵፪)
በእርግጥም ጌታችን የባሕርይ አባቱን አብን ክብር እንደጠበቀ በራሱ አንደበት ‹‹አባቴን አከብራለሁ›› ሲል ተናግሯል፡፡ (ዮሐ. ፰፥፵፱) ለእመቤታችንና ለአሳዳጊው ዮሴፍም እንዲሁ ‹‹ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፥ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር።›› ተብሎ ተጽፎአል፡፡ (ሉቃ. ፪፥፶፩) እመቤታችን በቃና ዘገሊላ ስለ ወይኑ የነገረችውም የልጅዋን መታዘዝ በልብዋ ትጠብቀው ስለነበር እና እንደሚታዘዛት ታስብ ስለነበር ነው፡፡

እስቲ ነገሩን ሌሎች ከሚያዩበት ማዕዘን ለመመልከት እንሞክር፡፡ እውነት ግን ጌታችን እናቱን ሊቆጣ የሚችልበት ምን ምክንያት ነበረው? ከላይ እንደተመለከትነው የለመነችው ስለ ራስዋ ጥቅም አይደለም፡፡ በዚያ ላይ ልመናዋ ከሚያስፈልግ ነገር ውጪ ይደረግ የተባለ አላስፈላጊ የቅንጦት ልመና አይደለም፡፡ በሰርግ ቤት ሙሽሮችን ለዕድሜ ልክ ውርደት ሊዳርግ የሚችል የወይን ጠጅ እጥረት በተከሰተበት ሰዓት ‹ወይን እኮ የላቸውም› ብሎ ማመልከት እንኳን በሩኅሩኁ አምላክ ፊት ይቅርና በእኛ በጨካኞቹ የሰው ልጆች ፊት እንኳን ሊያስቆጣ የሚችል ነገር አይደለም፡፡

የለመነችው እንደ አይሁድ ምልክት ለማየት ጓጉታ አይደለም፡፡ እንደ ፈሪሳዊያንና ሰዱቃውያን ‹አይተን እንድናምንህ ምን ምልክት ትሠራለህ?› ‹ከሰማይ ምልክት ልናይ እንወዳለን› የሚል የፈተና ጥያቄ አልጠየቀችም፡፡ (ማቴ. ፲፮፥፩ ፤ዮሐ. ፮፥፳) ተአምር የማየት ምኞት አድሮበት እንደጠየቀው እንደ ሄሮድስም በአጋጣሚው ልጠቀምና ተአምር ልይ ብላም አይደለም፡፡ (ሉቃ. ፳፫፥፰) ደግሞስ ያለ ወንድ ዘር በማኅጸንዋ አድሮ በታተመ ድንግልና ሲወለድ ያየች እናት ሌላ ምን ተአምር ሊያስደንቃት ይችላል?
የሰርጋቸው ቀን የኀዘናቸው ቀን ሊሆን ስለተቃረበ ሙሽሮች ተጨንቃ መለመንዋ እንዴት የሚያስቆጣ ሊሆን ይችላል? ያለጊዜው ስለለመነችውና ስለቸኮለች ተቆጣት እንዳንል ልመናዋን ትንሽ ብታዘገየው ኖሮ ነገሩ ይፋ እየሆነ ፣ ሙሽሮቹ መዋረዳቸው ነው፡፡ ስለዚህ የደረሰችው በሰዓቱ ነው፡፡

የጌታችን አሠራር እንዲህ አልነበረም፡፡ የቅዱስ ጴጥሮስ አማት በንዳድ በታመመች ጊዜ እንዲፈውሳት ሲለምኑት እሺ ብሎ ንዳዱን ገሥፆ አላቀቃት፡፡ (ሉቃ.፬፥፴፱) የአንድ መቶ አለቃ ልጅ በታመመ ጊዜ የአይሁድ ሽማግሌዎች ሊያማልዱ በመቶ አለቃው ተልከው መጡ፡፡ ጌታችን ከይሁዳ ነገድ መሆኑን በማሰብም ‹‹ይህን ልታደርግለት ይገባዋል፤ ሕዝባችንን ይወዳልና ምኵራብም ራሱ ሠርቶልናል ብለው አጽንተው ለመኑት። ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ሄደ።›› የመቶ አለቃውንም ልጅ በመጨረሻ ፈወሰው፡፡ (ሉቃ. ፯፥፪-፮) እነዚህ ሰዎች ተአምር እንዲያደርግ ሲጠይቁት እሺ ያለ ጌታ እናቱ ስትለምነው ይቆጣል ብለን እንዴት እንቀበል? የአይሁድን ሽማግሌዎች እንኳን ያልተቆጣውን ጌታ በምን አንደበታችን እናቱን ተቆጣ ልንለው ይቻለናል?

ከሁሉ በላይ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ጸሎቴን ያልከለከለኝ ምሕረቱንም ከእኔ ያላራቀ እግዚአብሔር ይመስገን›› እንዳለው በረከሰ አንደበታችን ፣ በሚወላውል ልባችን ፣ በሚባክን ሃሳባችን ወደ እርሱ የምንጸልየውን የእኛን የኃጢአተኞቹን ጸሎት ለምን ጸለያችሁ ብሎ ያልከለከለ አምላክ ንጽሕት እናቱ በፍጹም ትሕትና ለለመነችው ልመና የቁጣ ምላሽ ሠጠ ማለት እንዴት እንደፍራለን? ዳዊት ‹‹በልቤስ በደልን አይቼ ብሆን ጌታ አይሰማኝም ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ሰማኝ የልመናዬን ድምፅ አደመጠ›› ብሏል፡፡ እርሱ በልቡ በደል ስለሌለ ጌታ ከሰማው በሃሳብዋ ድንግል የሆነች እናቱን እንዴት አልሰማትም እንላለን? (መዝ. ፷፮፥፲፱-፳)

እመቤታችን የጠየቀችው ይህን ያህል የማይጠየቅ ነገር ነው እንዴ? የመንግሥትህን እኩሌታ ፣ የሥልጣንህን ፈንታ ሥጠኝ አላለችውም፡፡ የጠየቀችው ስለ ድሆቹ ሙሽሮች ነው፡፡ እኛ በረባ ባልረባው ስንዘበዝበው የምንውለውና የምናድረው ታጋሽ አምላክ ለእናቱ ለእኛ የሠጠውን ነገር ይነሣል ማለት ፈጽሞ አይታሰብም፡፡ ‹አብን አሳየንና ይበቃናል› ፤ ‹እሳት ከሰማይ ወርዶ ሕዝቡን ያጥፋቸው› ፤ ‹በግራ ቀኝህ አስቀምጠን› የሚሉ ደቀ መዛሙርትን ታግሶ ለሦስት ዓመት ከሦስት ወራት ያስከተለ ጌታ ቅድስት እናቱ ተገቢ ልመና በተገቢ ሰዓት ስትለምነው ሊቆጣ አይችልም፡፡
እንደ ወንጌሉ ብቻ ከሔድን ደግሞ እመቤታችን ከዚህ በፊትና በኋላ ምንም ነገር ስትለምነው አልተጻፈም፡፡ በወንጌል ለተጻፈው ለዚህ ብቸኛ ልመናዋም መልሱ ቁጣ ነው ብለን አምነን መቀመጥ ለእኛ ለኦርቶዶክሳውያን ፈጽሞ የሚዋጥልን ሃሳብ አይደለም፡፡ በልጅነትዋ ወልዳው ለተሰደደችው ፣ በነፍስዋ የኀዘን ሰይፍ ላለፈባት እናቱ አንዴ ብትለምነው ተቆጣ ብለን እንዴት እንናገራለን?

ጌታችን በዚህ ሰርግ ቤት እንኳንስ እንዲህ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የሚተረጉመው ‹ከአንቺ ጋር ምን ጠብ አለኝ› የሚል የአክብሮት ንግግር ተናግሮ ቀርቶ ፤ ለእናቱ የተናገረው በቀጥታና በግልፅ የቁጣ ንግግር ቢሆን ኖሮ እንኳን ጾመን ጸልየን ፣ ወድቀን ተነሥተን ምሥጢራዊ ትርጉሙን እንፈልጋለን እንጂ ሰማይና ምድር ቢነዋወጥ ‹ጌታ እናቱን ተቆጣ› ብለን አናምንም!!!

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ከቃና ዘገሊላ መጽሐፍ የተወሰደ
+ ከቤተ ክርስቲያን ጎን እንቁም +

የቤተ ክርስቲያናችን ወቅታዊ ሁኔታ እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን የትኛዋ ለመሆንዋ ማሳያ ነው፡፡ የትም ዓለም ብንሔድ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ይገፋሉ፡፡ ሶርያ ፣ ግብፅ ሌላው ቀርቶ ኢራቅ እንኳን ኦርቶዶክሳውያን የተለየ መከራ ይደርስባቸዋል ፡፡ ለምን ቢባል ሰይጣን የእውነተኛዋን ቤተ ክርስቲያን አድራሻ ስለማይሳሳት ነው፡፡

‹‹ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደጠላኝ እወቁ›› ከሚለው ቃል ውጪ ምንም መጽናኛ የለንም፡፡ (ዮሐ. ፲፭፥፲፰)

"ነገር ግን እንዳስጨነቁአቸው መጠን እንዲሁ በዙ፥ እጅግም ጸኑ" ተብሎ እንደተጻፈ መከራው ለመብዛትና ለመጽናት ምክንያት ይሁንልን:: (ዘጸ 1:12) በአንድ ሲኖዶስ እየቀደሰችያለችው ቤተ ክርስቲያን የዕረፍት ጊዜ የላትምና አሁንም ፈተናዎችዋ በዝተውባታል::


በዚህ የፈተና ወቅት ከሁሉ የሚበልጠው እና እንደ መፍትሔ ሲነሣ በንቀት የሚሳቅበት የመጀመሪያው መፍትሔ ጾም ጸሎትና የሁላችን የአንድነት ንስሓ ነው፡፡ ጾምና ጸሎት ንስሓ የነነዌን መቅሠፍት ፣ የአስቴርና የሕዝቡን ፍርድ ፣ የዮዲትን ሥቃይና የሆሊፎርኒስን ጭካኔ የገለበጠ መፍትሔ ነው፡፡

እንደ ክርስቲያን መጮኽ ያለብን ወደ እግዚአብሔር ነው፡፡ ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ማቅ ለብሶ በጾምና በጸሎት ቢተጋ ፣ ሚድያ ላይ ከሚጮኸው የበለጠ ቤተ መቅደስ ውስጥ ቢጮኽ ሁሉም ነገር ይለወጣል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ጦር ሠራዊቷ በየገዳማቱ ያሉ አባቶቻችን ፣ ፍጹም ሃይማኖት ያላቸው ምእመናንዋ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለጋራ ንስሓ ፣ ምሕላ ፣ ጾምና ጸሎት አሁኑኑ ነጋሪት ብትጎስም ተራራ የሚያፈልሱ ስምዖኖች በየሥፍራው አሏት፡፡ ሁሉን ፈተና ድል መንሣት ይቻላል፡፡ በዚህ የማያምን ሰው ካለ የማያምንባት ቤተ ክርስቲያን ነገር ምን ያስጨንቀዋል? ‹‹ዓለሙን የሚያሸንፈው እምነታችን ነው›› (1ዮሐ. 5፡4)

ከዚህ ጋር ቤተ ክርስቲያናችንን በዚህ የፈተና ዘመን ልናግዛት የሚገቡን ለእኔ የታዩኝ ጥቂት ነገሮች አሉ፡፡

1 የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማዊ ክብር መጠበቅ

ምሳሌ ልሥጥ:- ባለፈው ዓመት በመገናኛ ብዙኃን የሙስሊም ምክር ቤት ሓላፊዎች ልዩነታቸው እንደተፈታ እና እንደታረቁ ሰምተን ነበር፡፡ በምን ነበር የተጣሉት? በምን ታረቁ? ከሥልጣን የወረዱት ሰዎች ጥፋት ምንድር ነው? እኔ ምንም አላውቅም፡፡ ከጠየቅኳቸው ጥቂት ሰዎችም እንዲህ ነው ሲባል የሰማሁት ነገር የለም፡፡ ተቋማዊ ክብርን መጠበቅ ማለት ይኼ ነው፡፡

የእኛ ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ግን ‹‹አቡነ እገሌ ሲናገሩ አቡነ እገሌ ራሳቸውን በኀዘን ነቀነቁ›› እስከሚለው ድረስ ፀሐይ ላይ ይሠጣል፡፡ ምእመናን ስለ ቤተ ክርስቲያን መረጃ የማግኘት መብት የላቸውም አላልኩም፡፡ ለመረጃም ግን ልክ አለው፡፡ የመሸከም አቅምም የሚባል ነገር አለ፡፡ ከቤተ ክርስቲያን በተቃራኒ የቆሙ ሰዎችም እኩል መረጃውን ያነባሉ፡፡ ቢያንስ ግን መፍትሔው እንኳን የአደባባይ የጦር ምክር መሆን የለበትም፡፡ ካበላሸነው የቆየነውን የቤተ ክርስቲያኒቱን ገጽታ ስለመጠበቅ እያወራሁ አይደለም፡፡

በምሳሌ ላስቀምጥ ፡-

ለምሳሌ አቶ ሀ በቤተክርስቲያን ላይ ክፉ ሴራ ጠነሰሱ እንበል፡፡ በዚህ ዙሪያ ቤተ ክርስቲያን ስብሰባ ተቀመጠች፡፡ አቶ ሀም ከነጓደኞቹ የቤተ ክርስቲያኒቱን ጠንካራና ደካማ ጎን ቁጭ ብሎ ያነባል፡፡ እነማንን ማስፈራራት ፣ እነማንን ማሸማቀቅ ፣ እነማንን ማጥቃት እንዳለበት ሰላይ ሳይልክ ያነባል፡፡ በእኛ መካከል ያለውን ልዩነትና አለመግባባት ተጠቅሞ ለመከፋፈልም እጅግ ይመቸዋል:: እንዲህ የተከፈተ በር ይዘን ነው እንግዲህ ሰው ሌባ የምንለው፡፡

ተኝቶ ከእንቅልፉ ሲነሣ ‹‹ሲኖዶሱኮ ተኝቷል›› ብሎ ሲቀድሱ ላረፈዱ ጳጳሳት ሥምሪት የሚሠጥ ትውልድ ፈጥረን ነገን መቀጠል አንችልም፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ከሲኖዶስ በላይ አሳቢ መስሎ መታየትን ያህል ለቤተ ክርስቲያን አለማሰብ የለም:: አባቶች ሲናገሩ "የት ከርማችሁ ነው?" ዝም ሲሉ "ተኝታችኁዋል" እየተባሉ ቤተ ክርስቲያን በገዛ ልጆችዋም በጠላቶችዋም እየተሸማቀቀች ምንም ሥራ መሥራት አንችልም::
ቤተ ክርስቲያን እኔና አንተ ነን:: አንተ የሠራኸው ጥሩ ሥራ ሁሉ ቤተ ክርስቲያን የሠራችው ነው:: ካልሠራህም እጅዋን ሽባ ያደረግኸው አንተ ነህ::

የአንድ ቀበሌ አመራር የሚከበረውን ያህል ለሲኖዶስ ክብር ሳንሠጥ መንግሥት ሲኖዶስን እንዲያከብር መጠበቅ የለብንም፡፡ መንግሥት የሚያነበው ዛሬ አቡነ እገሌ የሠጡትን መግለጫ ብቻ ሳይሆን እኛ ትናንት ስለ አቡነ እገሌ ያጋለጥነውን መረጃ ጭምር ነው፡፡ አባቶች በመንግሥት ባለ ሥልጣናት ፊት ለቤተ ክርስቲያን ተቆርቁረው ሺህ ጊዜ ተቆጥተው ቢናገሩ እንኳን የመንግሥት አካል የሚሰማቸው በሆዱ ‹‹ሕዝባዊ መሠረት እኮ የላቸውም›› እያለ ነው፡፡ ሰድበን የላክናቸው አባቶች ተሰድበው ቢመለሱ ቤተ ክርስቲያንን ያስናቅናት እኛው ነን፡፡ ይህን በማድረግ ደግሞ ጣት መቀሳሰር ሳያስፈልግ ሁላችንም የየድርሻችንን ጥፋት ወስደናል:: በሚድያ ያቃለልናት አለን ያለሚድያ በየመንገዱ በቤታችን ያቃለልናት አለን::

ሌሎች የእምነት ተቋማት የሚጣሉበት ብዙ የውስጥ ሽኩቻ ሳይኖር ቀርቶ አይደለም:: ለገጽታቸውና ተቋማዊ ቅቡልነታቸው ሲሉ ግን አፍነው ያስቀሩታል::

2. ለጠላት መንገድ የመጠቆምን አካሔድን ማቆም

ድንገት ሌቦች ከቤትህ ገቡ እንበል ፤ ቤት ገብተው አንተን ከነልጆችህ እንዳትንቀሳቀስ አሉህ፡፡ ከፊት ለፊት ያገኙትን ዕቃ መሰብሰብ ጀመሩ፡፡ ይህን ጊዜ ሴት ልጅህ ‹‹ወይኔ በዚህ ዓይነትማ አልጋ ሥር የተደበቀውን ወርቅም ልትወስዱት ነው ማለት ነው?›› ብላ ጮኸች፡፡ ሌቦቹ ስለ ጥቆማው አመስግነው ወርቁን ከአልጋ ሥር ወሰዱት፡፡ ልጅህ ግን አላቆመችም ‹‹ወይኔ ጉዴ በዚህ አያያዝማ መሳቢያው ውስጥ ያለውን አልማዝም ልትወስዱት ነው!›› አለች፡፡ የልጅህን አፍ መያዝ አያምርህም? እንዳትይዝ ግን እጅ ወደላይ ተብለሃል፡፡

የእኛ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ትመስለኛለች፡፡ ‹አሁን ደግሞ እንዲህ ሊያደርጉ ነው› ፣ እንዲህ ሊሠሩ ነው በሚል ንግግር ተበረታትተው የተሠሩባት ብዙ ክፉ ነገሮች አሉ፡፡ ከተወራ አይቀር ተብለው የተደረጉ የአስተዳደራዊ ውሳኔ ስኅተቶች ፣ የጠላት ጥቃቶች አሉ፡፡ ስጋታችንን እንደሰነድ እያቀረብን ለጠላት ፍኖተ ካርታና የመጨረሻ ግብ የምንሠጠው እኛ ነን፡፡ በዚህ ምክንያት ‹የገበያ ፍላጎት ካለ ለምን አንገባበትም?› ብለው የዘመቱብን ሰዎች ብዙዎች ናቸው፡፡

‹‹ሁሉንም የንብ ቀፎዎች በአንድ ጊዜ አትክፈታቸው›› የሚል አባባል አለ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሳናውቅ የምናደራጃቸው ጠላቶችም አሉ፡፡ ‹እገሌና እገሌ እኮ ከጀርባቸው እገሌ ስላለ ነው› ‹እነ እገሌና እገሌ አላማቸው አንድ ነው› ወዘተ በሚሉ ንግግሮች ሳይተዋወቁ ያስተዋወቅናቸው ፣ አብረን ከተሰደብን አይቀር አብረን እንሥራ ብለው ይደራጃሉ ፣ ይደጋገፋሉ፡፡ ይህ አካሔድ በውስጥም ብዙ ጉዳት አስከትሏል፡፡
በነቀፋ ብቻ አይደለም፡፡ አንድ ባለ ሥልጣን ቤተ ክርስቲያንን የሚጠቅም ነገር በሥልጣኔ ላድርግ ቢል እንኳን ‹‹የተዋሕዶ ልጅ እንዲህ አደረገ›› የሚል ታግ ስለሚሠጠውና በአንዴ አጣቂኝ ውስጥ ስለሚገባ ማድረግ ቢሻም አያደርገውም፡፡ (ይኼ የፈጠራ ምሳሌ ሳይሆን እውነተኛ ገጠመኝ ነው) ለቤተ ክርስቲያን መሥራትም አስጊ የሆነበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ትናንት ቤተ ክርስቲያን ባንክ ልትከፍት ነው ዓላማዋን ሳተች ለማለት ብዕሩን ያላነሣ የለም፡፡ አሁን ሌሎች ዐሥር ባንክ ሲከፍቱ ቁጭ ብሎ የሚቆጥረው ኦርቶዶክሳዊው ነው፡፡ በየትኛውም ፕሮጀክት ላይ በቤተ ክርስቲያን የሚፈጠር ማንኛውም ክፍፍል ለቤተ ክርስቲያኒቱ ጠላቶች በጎ ዕድል ነው፡፡ እስኪቃደዷት ድረስ ለጊዜው በጋራ የወጓታል፡፡

3. የመፍትሔ እንጂ የችግሩ አካል አለመሆን

ቤተ ክርስቲያንን ለብዙ ግፍ የዳረጋት ምንድር ነው? በዘረኝነት የታወረ ፖለቲካ? ካልን እኛ ከምንም ዓይነት የዘር ጠብ ለቤተ ክርስቲያን ስንል መውጣት አለብን::
ቅድሚያ ለነፍሳት ድኅነት የምትሠጥ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እስካለን ድረስ በአላስፈላጊ ፖለቲካዊ ውዝግቦችና እልሆች ውስጥ ገብተን ትልቋን ቤተ ክርስቲያን ለእሳት አንዳርጋት:: ስለ ጊዜያዊው ታሪክ ክርክር ስንዋደቅ ዘላለማዊትዋን ቤተ ክርስቲያን አንጣት:: ቤተ ክርስቲያንን ወክለን ቡድን ሠርተን ስንሳደብ ዱላው የሚያርፈው መከረኛይቱ ቤተ ክርስቲያን ላይ መሆኑን ልብ እንበል:: ስለዚህ ጥላቻችንን ወገንተኝነታችንን ጠበል አጥምቀን መንፈሳዊ ለማስመሰል አንሞክር::

የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ከየትኛውም ብሔር ከየትኛውም ቋንቋ ከየትኛውም ባሕል የሚበልጥ ወንጌል በእጃቸው ታቅፈው ከአንዱ ጉያ የሚለጠፉ መሆን የለባቸውም:: ቤተ ክርስቲያን ሁሉን ነገድ ሁሉን ቋንቋ የምታቅፍ አይሁዳዊ ግሪካዊ የማትል ናት:: የእርስዋን አገልግሎትም ከዚህ በጸዳ መንገድ በማስኬድ የማይስማሙ ሁሉ የሚስማሙባት የሀገር ሽማግሌ ልትሆን ትችላለች:: ለዚህም ሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋይ ከችግሩ አካልነት ወደ መፍትሔው አካልነት ራሱን የመቀየር ግዴታ አለበት:: በወደቀው እየዘበተ ላሸነፈው የሚደግፍ ዓይነት አካሔድ እስካለን ድረስ ግን በእኛ ተገለባባጭነት ቤተ ክርስቲያንን ዋጋ እናስከፍላለን:: ከተሾመው ሁሉ ጋር ጋብቻ የምትፈጽም ቤተ ክርስቲያን የተሾመው ሲሻር "ባልዋ የሞተባት" እንዳትባል ሁልጊዜም ቤተክርስቲያን የማይሻረው ሙሽራዋን ክርስቶስን ብቻ አንግሣ በአቅዋምዋ መጽናት ይገባታል::

በቤተ ክርስቲያን ላይ በጠላት ለሚነሡ ሁሉ ምክንያቱን መድኃኔዓለም ክርስቶስ ነግሮናል:: "ይገድሉአችኁዋል :: ይህንን ሁሉ የሚያደርጉት አብንና እኔን ስላላወቁ ነው" ብሎአል: በእርግጥም ሌላውን ሥጋዊ ምክንያት ትተን ራሳችንን ብንወቅስ ትናንት በየሥፍራው በየቋንቋው ያልደረሰው የስብከተ ወንጌል ሥራ ዛሬ መልሶ ዋጋ ማስከፈሉ አልቀረም:: ነቅተን ሰው ተኮር ሥራ ካልሠራን በቤተ ክርስቲያን ሕንፃ መቃጠል በምንንገበገበው ልክ ሰዎች ከሃይማኖት ሲወጡ መንገብገብ ካልቻልን ያላስተማርናቸው ሁሉ አብና ወልድን ያላወቀ የሚያደርገውን ያደርጉብናል::

4. የራሳችንን ሰዎች አለማጥቃት

እርስ በእርስዋ የምትከፋፈል መንግሥት አትጸናም፡፡ ይህ ቃል የተነገረው ለአጋንንት ነበር:: ፍቅር የማያውቁት አጋንንት እንኳን ለዓላማቸው ሲሉ ይስማማሉ:: በዚህ እሳት ዘመን ተከፋፍለን አይሆንም፡፡ ልዩነቶቻችንን ወደ ጎን አድርገን ለምንኖርባትም ለምንሞትላትም ሃይማኖታችን መቆሚያው ጊዜ አሁን ነው፡፡ በዘር ፣ በፖለቲካ አቋም ፣ በአመለካከት የምንለያይ ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን አንድ መሆኛው ጊዜ አሁን ነው፡፡ በመንግሥት ሥልጣንና ሓላፊነት ላይ ላለን ክርስቲያኖች ሙሴ የፈርዖን የልጅ ልጅ መባሉ የእናቱን ጡት ከመጥባት እንዳልከለከለው ማስታወስ ግድ ይለናል፡፡ የቤተ ክርስቲያን መከራ ከጸና ደግሞ የልጅ ልጅ መባልንም ትቶ ከዕፀ ጳጦስ እመቤታችን እግር ሥር መደፋትና ሱባኤ መያዝም ይጠይቃል፡፡

በቤተ ክርስቲያኒቱ ለረዥም ዓመታት ደክመው ፣ ወጥተው ወርደው ያገለገሉ ፣ በዓለምም ቤተ ክርስቲያንዋን ወክለው የሚሠሩ ልጆች አሉአት፡፡ እነዚህ አባቶችና ወንድሞች ያሉበት ለመድረስ ረዥም የምንኩስና ዳገት ፣ ረዥም የትምህርት ሒደት ፣ ረዥም የአገልግሎት አቀበት ወጥተዋል፡፡ ወደድንም ጠላንም የቤተ ክርስቲያኒቱ ማኅተሞች ናቸው፡፡ በግላቸው ብዙ ድክመቶች ሊኖሩባቸው ይችላል፡፡ ሆኖም የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትእምርት ሆነው በምእመናንም በሌሎችም ልቡና ታስበዋል፡፡ እነዚህን ሰዎች በማጥቃት የምናጠቃው የፈረደባትን ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡

ሌሎች በአንድ ጀንበር ተወዳጅ ሰዎችን ፈጥረው : ወጣቱን ለመውሰድ ለምስል ግንባታ ለቢልቦርድ ፣ ለቲቪ ቻናል ፣ ለታላላቅ አዳራሾች ወዘተ በሚሊየኖች ያፈስሳሉ፡፡ በእኛ በኩል ግን Already የታወቁትንም ለማዋረድ እንታገላለን፡፡ ምክንያቱ ምንም ቢሆን በዚህ ሰዓት ለቤተ ክርስቲያን አይጠቅማትም፡፡ አሁን ግን አጥር የማጠሪያ እንጂ አጥር የማፍረሻ ጊዜ አይደለም፡፡

ብንወቃቀስ እንኳን በውስጥ እንጂ በገሃድ አይደለም:: ጊዜውም አሁን አይደለም፡፡ ‹እናቴን ያገባ ሁሉ አባቴ ነው› ብለን በእምነት የሚመስሉንን ከመዋጋት መሰብሰብ አለብን፡፡ የእኛ የሆኑትን በአካሔዳቸው ባይስማሙን እንኳን ሰይጣን ደስ አይበለው ብለን ዝም ማለት ይገባናል::

5. በስልት አባቶቻችንንና ቤተ ክርስቲያናችንን መደገፍ

በእኛ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እጅግ የሚጎድለን ነገር ‹ከዛስ?› የሚለውን ጥያቄ አለመጠየቃችን ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ አንድ ነገር ሲፈጠር በስሜት ሆነን ‹‹ተነሥ ወገኔ›› ልንል እንችላለን፡፡ ‹‹ከዛስ›› የሚለው ጥያቄ ግን ከሁለቴ በላይ መልስ አያገኝም፡፡ መልሱ ሳይገኝም በጥያቄው መጮኽ ረክተን እንተወዋለን፡፡ ላለንበት ዘመንም በቅዱስ ሲኖዶስ መሪነት ምሥጢር ጠባቂነትን ያስቀደመ ፣ በስልት የተነደፈ ፣ ጥቃቶችን ከግምት ያስገባ ፣ ኦርቶዶክሳዊያንን የሚያስተሳስር አካሔድ በቀጣይ ይጠበቃል፡፡ የይህ ስልታዊ ዕቅድ ሁሉምን ‹‹ከዛስ›› የሚሉ ጥያቄዎች የሚመልስ መሆን ይጠበቅበታል፡፡

"እረኛን በማጣት ተበተኑ" የሚለው ቃል ለእኛ ምእመናን የሚሠራ ቃል ሆኖአል:: ትውልዱ ወደ መናፍቃን የሚነዳው በወሳጆቹ ጥንካሬ ሳይሆን በእኛ ድክመት ነው:: ወደ ትውልዱ ነፍስ የሚቀርብ የተባበረ አገልግሎት : ከተዋበውና ከጠለቀው ነገረ ሃይማኖት ጋር ትውልዱን የማገናኘት ሓላፊነታችንን ሳንወጣ "ከእኛ ዘንድ ወጡ" እያልን ልንጽናና አንችልም:: የቤተ ክርስቲያንዋን እውነተኛ ማንነትና ጥልቅ መንፈሳዊነት አጉልተን ማሳየት ብንችል በብዙ ሚልየን በጀትና በስልት ተደክሞበት የተነጠቅናቸውን የዋሃን ነፍሳት በሚገርም ፍጥነት ከነ ነጣቂዎቻቸው መመለስ እንችል ነበር::

በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ላይ የተቀመጡት ሊቃነ ጳጳሳት መንፈሳዊያን መነኮሳት ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ዕድሜያቸውን ሙሉ ሲዘጋጁና ሲማሩ የኖሩት ለቅኔ ፣ ለቅዳሴ ፣ ለድጓ ፣ ለመጻሕፍት ወዘተ መምህርነት ነው እንጂ ለተወሳሰበ የመሪነት ሥራም አልነበረም፡፡ ሀገር የሆነች ቤተ ክርስቲያን ለመምራት የሚችሉበት የአስተዳደር ዘዴ ሲሰለጥኑ አልኖሩም፡፡ ሆኖም በተፈጥሮ ብስለታቸውና መንፈሳዊው ትምህርት በሚሰጠውጥበብና እርጋታ እስካሁን መርተው አስረክበውናል፡፡
ዘመኑ ያመጣውን ትምህርት የተማረ የሚባለው የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጅ ስልት በመንደፍ ፣ አቅጣጫ በመጠቆም ፣ የቤተ ክርስቲያንዋን ገጽታ በመጠበቅ አባቶቹን መደገፍ አለበት፡፡ አህያ በወለደች ታርፋለች የሚለውን ብሒል በወለደች ትሰደባለች አድርገን ከማንቋሸሽ ለቤተክርስቲያን የሚጎድላትን መሥራት ይሻላል::

ከዚህ ውጪ ግን የአስተዳደር ድክመቶችን እያወጣን የእናቱን ዕንባ በአደባባይ የሚዘራ ቢሆን ‹እንዲህ ብዬ ነበር› ከማለት ያለፈ ጥቅም የለውም፡፡ ሁላችንም ‹ተናግሬ ነበር ሰሚ አጣሁ እንጂ › ለማለት ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያን ብንሮጥ ብዙ ለውጥ እናመጣለን፡፡

በማለቃቀስና ሁሌ ሮሮ ማውራት የኦርቶዶክሳዊትን ገጽታ ከማበላሸትና ያልጸኑትን ነፍሳትም እንዲኮበልሉ ከማድረግ ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው አምነን ነገን እንዴት እንቀጥል እንዴት ዘመኑን እንዋጅ የሚለው ላይ ተተግባሪ እቅድና ሥራ ላይ ማተኮር የግድ ነው::

እንደ ነህምያ በአንድ እጅ እየሠሩ በአንድ እጅ መጸለይ የሚገባን ዘመን ላይ ነን፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ከእኛ ከልጆችዋ በላይ ማንም ሊነሣ አይችልምና ከቅዱስ ሲኖዶስ ጎን መቆሚያው ጊዜ አሁን ነው፡፡ በመጪው ዘመን ወደ ሥራ የሚገቡ በርካታ መንፈሳዊ ሚዲያዎቻችንን ይዘን የሃይማኖታችን አጥር የመሆን የአበው አደራ አለብን፡፡ የአባቶቻችንን አክሊል የመቀዳጀት ዕድል ቢገጥመን በሚል ተስፋም የሚመጣውን ሁሉ በንስሓ ተዘጋጅተን መጠበቅ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን በመከራ እሾኽ ውስጥ የምታብብ አበባ ናት:: በሚወረወርባት ድንጋይ ቤተ መቅደስ የምታንጽ ጦር ሲሰካባት እንደ ያሬድ የምታዜም ሙሽራ ናት:: ከቻልን ችግርዋን እንፍታ ካልችልን ችግር መሆናችንን ብቻ እናቁም:: ቢያንስ ንስሓ ገብተን የራሳችንን ልብስ እንጠብ ያን ጊዜ ሁሉም ሰላም ይሆናል::

‹‹በውስጥሽ ሰላም ይሁን አልሁ
ስለ አምላካችን ስለ እግዚአብሔር ቤት
መልካምነትሽን ፈለግሁ››

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ነሐሴ 2012 ዓ ም

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ዘንድ ጸልዩ! ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like እና Share ያድርጉ
FB: https://www.facebook.com/officialHenokhaile/
Telegram: https://www.tg-me.com/deaconhenokhaile
Instagram: https://www.instagram.com/p/CBnMF0nnhcQ/?igshid=549jvl607bv4
Youtube: https://www.youtube.com/channel/UCOaVsWC05aUjeqIEW3fWj7g
+++ ከጵጵስና ሽሽት +++

ረዣዥሞቹ ወንድማማቾች ተብለው የሚጠሩት አውሳብዮስ ፣ አሞንዮስ ፣ ዲዮስቆሮስና አውሳሚዮስ በቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ላይ በብዙ መልኩ ይጠቀሳሉ። "አውሳብዮስ አሞንዮስ ተናግረውታል" የሚል ማስረጃ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትርጓሜ መጻሕፍት ላይ ማግኘት የተለመደ ነው። እነዚህ ቁመታምና መልከ መልካም የነበሩት ወንድማማቾች ሕይወታቸውን ለቤተ ክርስቲያን የሠጡ የዘመኑን ፍልስፍና ተምረው በሃይማኖት እውቀት የመጠቁ ነበሩ። የእስክንድርያ ትምህርት ቤት ቀደምት ሊቃውንትን መጻሕፍትም እጅግ ያነበቡ ፣ ከሊቃውንት ተርታ የሚመደቡ የታሪክና የትርጓሜ መምህራን ነበሩ።

ከእነዚህ ወንድማማቾች መካከል አንዱ አባ አሞንዮስ ነው። ይህ አባት ከእውቀት ጋር ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ ሕይወት የነበረው ነበር። ለዚህም ማሳያ የሚሆነን በዚያን ዘመን የዓለም ማእከል ወደነበረችውን ሮም በሔደበት ወቅት ከቅዱስ ጴጥሮስና ከቅዱስ ጳውሎስ አብያተ ክርስቲያናት ውጪ አንድም ነገር ሳይጎበኝ መመለሱ ነው።

አባ አሞንዮስ በበአቱ ተወስኖ በሚኖርባት ሄርሞፖሊስ የምትባል ከተማ የነበሩ ምእመናን መንፈሳዊ ሕይወቱንና ጥልቅ እውቀቱን ተመልክተው ጳጳስ ሆኖ እንዲሾምላቸው ተመኙ። ስለዚህም ወደ እስክንድርያው ፓትርያርክ ጢሞቴዎስ ሔደው አመለከቱ። ፓትርያርኩ የአባ አሞንን መንፈሳዊነትና እውቀት በመረዳት ጳጳስ አድርጎ ሊሾምላቸው ፈቀደ። ምእመናኑ ተደስተው ወደ አባ አሞንዮስ እየገሰገሱ ደረሱ። ወደ በአቱ ሲገቡ ግን ያጋጠማቸው ነገር እጅግ አስደንጋጭ ነበር።

አባ አሞንዮስ ሕዝቡ ወደ ፓትርያርኩ ሔደው ጳጳስ አድርገው ሊያሾሙት እንደሆነ ሰምቶ ጳጳስ ሆኖ ላለመሾም የቀኝ ጆሮውን ቆርጦት ነበር። ይህንን ያደረገው በሥርዓቱ መሠረት ጳጳስ የሚሆነው ለአገልግሎት የሚከለክል የአካል ጉድለት የሌለበት ሰው እንደሆነ ስለሚያውቅና ምእመናኑም "ጳጳሳቸው ጆሮው ቆራጣ ነውእንዳይባሉ ፈርተው ይተዉኛል" ብሎ አስቦ ነበር።

ይህን ያዩት ምእመናን በሁኔታው ቢደነግጡም ይህን የመሰለ አባት ማጣት ስላልፈለጉ ወደ ፓትርያርኩ ተመለሱ። ነገሩን የሰሙት ፓትርያርክ ጢሞቴዎስ ግን "ይህን ሥርዓት አይሁድ ይጠብቁት እኔ ግን አፍንጫውም ቢቆረጥ እሾመዋለሁ" አሉ።

ምእመናኑ ደስ ብሏቸው ወደ አባ አሞንዮስ ተመለሱ። አባ አሞንዮስ በአቱን ጥሎ ሮጠ። ምእመናኑ ተከታትለው ያዙት። እየተንፈራገጠ እያለቀሰ ወደ ፓትርያርኩ ሊወስዱት ሞከሩ። አባ አሞንዮስ ግን "እባካችሁ ተዉኝ ግድ ብላችሁ ብትወስዱኝና ብታሾሙኝ ምላሴን እቆርጣለሁ" አላቸው። ይህንን ከማድረግ እንደማይመለስ ስለተረዱ ምእመናኑ እያዘኑ ተዉት።

መጽሐፈ መነኮሳት ሹመትና ክብር እንደ ጥላ ነው ይላል። የሚከተሉትን ይሸሻል የሚሸሹትን ይከተላል። በቤተ ክርስቲያን ሓላፊነት እንጂ ሥልጣን ባይኖርም ቤተ ክርስቲያን ግን ከትናንት እስከ ዛሬ መሾምን እንደ ጦር የሚፈሩና በግድ እያለቀሱ የሚሾሙ አባቶች ነበሯት ፣ ዛሬም አሏት። እያለቀሱ የተሾሙትም የቤተ ክርስቲያንን ዕንባ ይጠርጋሉ።

ይህን ታሪክ የጻፍሁት "ዛሬ ምን አባት አለና ..." የሚለውን የተለመደ የስድብ ዶፍ ለመቆስቆስ አይደለም። ይህን ማድረግ ለአሕዛብ መሳለቂያ ከመሆን በቀር ምንም አይጠቅምም። "ለቤተ ክርስቲያን ቅን መሪን የሚሠጥ" እያልን በማለዳ ደጅ የምንጠናው አምላካችን ወደ መንፈሳዊ ማዕረግ ሊመጡ የታሰቡትን የቀደሙትን አበው መንፈስ እንዲያድልልን የምንጸልይበት ብርቱ ጊዜ ግን አሁን ነው።

አንድ ገጣሚ እንዳለው "ቤተ ክርስቲያን እንደ ኦሪቱ ዘመን ምነው በድንኳን በሆነችና ምነው ጠቅልለን ይዘናት በሸሸን" የሚያሰኝ ጊዜ ላይ ነን። ለምናየው ክፉ ነገር የኛን ኃጢአት ምክንያት ብናደርግና ብናነባ የሚሻልበት ጊዜ ነው። ለአንዱ ደግ መሪ ለሙሴ ሕዝቡን አጥፍቼ ሌላ ሕዝብ ልቀይርልህ ያለ ፈጣሪ ሕዝቡ ቅን ሆኖ ቢገኝ ደግሞ መሪ መቀየር የሚሣነው አይምሰለን። መሰዳደቡን ትተን ሃይማኖታቸው የቀና ደገኛ አባቶችን እንዲሾምልን እንጸልይ።
(ይ ዲ "ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተ ክርስቲያን)

"በውስጥሸ ሰላም ይሁን አልሁ ፣ ስለ አምላካችን ስለ እግዚአብሔር ቤት ላንቺ መልካምነትሽን ፈለግሁ። "
(መዝ 122:9)

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
[email protected]
ሰኔ 24 2008 ዓ ም
ከለን ጀርመን
እምነ በሃ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን - ቤተ ክርስቲያን እንደምን አለሽ?

ከማሃ ኀዘን ወተሰዶ ሶበ በኩለሄ ረከቦ
ርእዮ ለይብኪ ዓይነ ልብ ዘቦ::
እንደ እርስዋ ኀዘንና ስደት የደረሰበት ሰው
የልብ ዓይን ያለው አይቶ ያልቅስ::

"የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል?" ኢሳ 53:1

ያልተቀደደችውና ከላይ ጀምሮ ወጥ የሆነችው የክርስቶስ ቀሚስ ከዚህ ዓለም ያልሆነችው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ ለአራት የተከፈለው ደግሞ የምታስተምረው ወንጌል ነው፡፡ ወንጌል ሊከፋፈልና ለዓለም ሁሉ ሊዳረስ ይችላል፡፡ ወንጌል በዘር በቋንቋ በሀገር አይገደብምና የክርስቶስ ወታደሮች የሆኑ ካህናትና መምህራነ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ተከፋፍለው ለዓለም ማከፋፈል አለባቸው፡፡

አብያተ ክርስቲያናት በየሀገራቱ ቢቋቋሙ ፣ አህጉረ ስብከቶች ቢስፋፉ ፣ ሊቃነ ጳጳሳት ፣ ካህናት ፣ ዲያቆናት ፣ ሊቃውንት ፣ ሰባክያን በቁጥር በዝተው ፣ በቦታም ተከፋፍለው ቢያገለግሉ እጅግ መልካም ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በሁሉ ጎዳና … ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል›› እንዳለ የመምህራን መብዛት የወንጌል መስፋፋት እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነው፡፡ (ፊል. ፩፥፲፰)

ቀሚሱ የተባለችን ቤተ ክርስቲያንን ከተቃደዷት ግን አደጋ አለው ፤ ‹የሐዋርያት በሆነች በአንዲት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን› ብለን የምንናገርላት ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ቀሚሱ ናት፡፡ በሰው እጅ ያልተሰፋች ፣ ማንምም ሊሠፋት የማይችል ቀሚስ ናት ፤ ከላይ ጀምሮ ወጥ ሆና በመሠራቷም አትከፋፈልም፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ሊከፋፍሏት የሚፈልጉ ሰዎችን አውግስጢኖስ እንዲህ ሲል ይጠይቃቸዋል ፡- ‹‹ሮማውያን እንኳን ያልቀደዱትን የክርስቶስን ልብስ እናንተ ስለምን ትቀድዱታላችሁ?››

"ከሁሉም በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰቡአት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን"

ከቅዱስ ሲኖዶስ ጎን እንቁም!
+ የአባቶች ድንቅ ጥበብ የተሞሉ መልሶች +

ባለ ብዙ ታሪኩ የወሊሶው ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ያጠምቁና ያስተምሩ በነበረበት ሥፍራ አንድ በትዕቢት መንፈስ የሚሰቃይ ወጣት መጣና መፈክርነት ያዘለ ቃል ተናገረ:: ክብር ይግባትና ንግግሩ የድንግል ማርያምን ዘላለማዊ ድንግልና የሚቃወም ነበር::

ወደ አባ ዲዮስቆሮስ ቀርቦ እንዲህ አላቸው :-
ወጣቱ :- "ድንግል ማርያም እኮ ብዙ ልጆች አሉአት"
አቡኑ :- "ባታውቀው ነው እንጂ ለአንተም እኮ እናትህ ናት!"

✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽

የቦሩ ሜዳው መምህር አካለ ወልድ ከሌሎች ሊቃውንት ጋር ኢየሩሳሌምን ሲሳለሙ ድንገት የሌላ ሀገር መነኮሳት መጥተው በዱላ አጣደፉአቸው:: ነገሩን ሲጠይቁ ለምን በእግዚአብሔር ሦስትነት እንደማያምን ሰባልዮሳዊ
አንድ ጣታችሁን ብቻ ወደላይ ጠቁማችሁ ታማትባላችሁ? ለምን እንደ እኛ ሦስት ጣቶቻችሁን (እንደሚጎርስ ሰው) በአንድ ገጥማችሁአታማትቡም?" አሉና በቁጣ ጮኹ::

መምህር አካለ ወልድ በፈሊጥ እንጂ በፍልጥ የሚሆን ነገር ስለሌለ ቁጭ ብለን እንነጋገር አሉ::

"እኛ በአንድ ጣት ብናማትብም ሦስትነቱን እናምናለን:: አንድዋ ጣትም እኮ ሦስት አንጉዋዎች አሉአት:: አንድ መሆንዋ አንድነቱን ሦስቱ አንጉዋ ሦስትነቱን ያስረዳል::
የታችኛው አንጉዋ መሠረት ነውና የወልድ የመንፈስ ቅዱስ መሠረት ይሆነው የአብ ምሳሌ ነው:: የመካከለኛው በሁለቱ ህልው የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው : የላይኛው ጥፍር የለበሰው ደግሞ ባዕድ ሥጋን የተዋሐደ የወልድ ምሳሌ ነው:: ሀገራችሁ ሔዳችሁ አስተምሩበት" አሉአቸው

(ይህ ትርጓሜ በወንጌል አንድምታ ላይ በእግዚአብሔር ጣት አጋንንትን አወጣለሁ የሚለው በተተረጎመበት ሥፍራ ይገኛል)

✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽

ንቡረ ዕድ ክፍለ ዮሐንስን ደግሞ አንድ ወጣት መጥቶ
"ለእግዚአብሔር የአምልኮ ለቅዱሳን የጸጋ ስግደት እንደሚሰገድ አውቃለሁ:: ግን በቅዱሳን ሥዕል ፊትና በፈጣሪ ፊት ስሰግድ እንዴት ለይቼ የጸጋ የአምልኮ እያልኩ መስገድ እችላለሁ?" አላቸው
ንቡረ ዕድ መለሱ
"አንተ ዝም ብለህ ስገድ እነርሱ የድርሻቸውን ይወስዳሉ!"

✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽

አቡነ ሺኖዳ ከሾፌራቸው ጋር ሲሔዱ ሾፌሩ መኪናውን ከመጠን በላይ አበረረው
ፓትርያርኩ እንዲህ አሉ
"ልጄ ስለምንቸኩል ቀስ በል”

✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽

አንድ ታላቅ የጉባኤ መምህር ተጠየቁ
"ካህናት ዶሮና በግ ወዘተ ማረድ የማይችሉት ለምንድን ነው?"
"የክርስቶስን ሥጋና ደም የሚፈትት ካህን እንደ ኦሪት ካህን የእንስሳ ደም አያፈስስም"
"ካህናቱስ መልካም ሴት ልጅስ ማረድ ለምን ትከለከላለች?"
"ሕይወት የምትሠጥ ሴት ሕይወት አታጠፋም"

✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽

አለቃ ለማ ልጃቸውን ለምን በጣም እንደሚገርፉት ተጠየቁ
"ልጄን እኔ ካልቀጣሁት እግዚአብሔር ይቀጣብኛል
የእግዚአብሔር ቅጣት ደግሞ ሞት ነው"

✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽

አንዱ መጥቶ አንድን የመጽሐፍ መምህር
"ጥምቀት ጋድ አለው ወይ?" አላቸው
እርሳቸውም መለሱ
"አምና ነበረው የዘንድሮን እንጃ"

✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽

አቡነ ዮሐንስ አንድን ሥራ ፈቶ የአብነት ተማሪዎችን
ሲማሩ ከሩቅ የሚያይ ወጣት አዩና
"አንተ አትማርም ወይ?" አሉት
"አይ አባቴ ምን እየበላሁ ልማር ብለው ነው?" አለ እየተቅለሰለሰ
አቡኑ መለሱ
"አሁን ምን እየበላህ ነው የምትደነቁረው?"

✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽

አቡነ ጎርጎርዮስ በዝዋይ ሳሉ አንድ ወጣት ሰርቆ ሲያመልጥ አባርረው ይዘው ሰዎች አመጡላቸው
ዕቃው ከተመለሰ በኁዋላ ሌባውን ለሕግ አሳልፈው ሊሠጡ ሲቸኩሉ አይሆንም አሉአቸው:: ሰዎቹ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ወደ ፖሊስ እንውሰደው አሉአቸው
እርሳቸውም መለሱ
"ኦርቶዶክሶች ተሰራርቀው ተካስሰው መጡ ከሚል ስም ውጪ ምንም አናተርፍም"

✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽

ብፁዕ አቡነ ሰላማን አንዱ ባለ ሥልጣን ጉዳይ ሊያስፈጽሙ በሔዱበት ቢሮው "አንተ" ብሎ በማናገር ሊያቃልላቸው ሞከረ::
እርሳቸው እንዲህ አሉት
"የቤተ ክርስቲያኔን ጉዳይ ፈጽምልኝ እንጂ እንኩዋን አንተ ቀርቶ አንቺም ብለህ ጥራኝ

✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽

የደርግ መንግሥት እንዳሻው ሊዘውራቸው ተስፋ ያደረገባቸው ፓትርያርክ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በመሪው አማካኝነት እንዲህ ሲል ጠየቃቸው
"የቅድስት ሥላሴ ካቴድራልን ወደ ሙዝየምነት የመቀየር ሃሳብ በመንግሥት በኩል ተይዞአል:: ይህንን ለማድረግም የእርስዎን ድጋፍ የግድ ነው"
ፓትርያርኩ መለሱ
"ምን ችግር አለ በቅርቡ የዓመቱ ሥላሴ ክብረ በዓል ስላለ ሕዝቡ ባለበት እናንተም ተገኝታችሁ አብረን ለምን አናወያየውም"
በዚህ ምላሽ ምክንያት እቅዱ ተሠረዘ

✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
+ አቤቱ ቅጣኝ ነገር ግን እንዳታዋርደኝ! +

እግዚአብሔር ፍቅር ነው ፣ መሐሪ ነው ፣ ይቅር ባይ ነው፡፡ ፍቅር ይቆጣል ወይ? ይቅር ባይስ ይቀጣል ወይ? ብዙዎቻችን ስለ ክርስቶስ ሲነገረን መሐሪነቱና ፍቅሩ ብቻ ቢነገረን አንጠላም፡፡ ጨርሶ የማንፈራው እግዚአብሔር እንፈልጋለን፡፡ እንዲህ አታድርግ! የሚለን ሲመጣ ‘አትፍረድ’ እንላለን ፤ ቆይተን ግን የሰማዩን ዳኝም አትፍረድ ማለት ይቃጣናል፡፡ ቅጣት የሌለበት ክርስትና እንሻለን፡፡

ይህ ዓይነቱን ክርስትና ‘ጣፋጭ ክርስትና’ {የስኳር ክርስትና ይሉታል} ምንም ምሬት የሌለበት ሁሌም ማር ማር የሚል ሕይወት አድርገው ክርስትናን የሚሰብኩም ብዙ ናቸው፡፡ ‘አይዞህ ብትታመም ትፈወሳለህ ፣ ቤትህ ይሞላል ፣ ቀዳዳህ ይደፈናል ፣ ብትበድልም አትቀጣም’ ብቻ የሚሉ ስብከቶች የስኳር ክርስትና ስብከቶች ናቸው፡፡ ይህንን ብቻ የሚያጮሁ ሰዎች ክርስቶስ ‘የምድር ጨው ናችሁ’ ያለውን ትተው የምድር ስኳር ለመሆንና ዓለምን ለማስደሰት የሚፈልጉ ናቸው፡፡
በእርግጥ እግዚአብሔር ይቆጣል ወይ? አዎን ይቆጣል! እንዲህ ይላል መጽሐፉ

‘እግዚአብሔር ቀናተኛና ተበቃይ አምላክ ነው እግዚአብሔር ተበቃይና መዓትን የተሞላ ነው እግዚአብሔር ተቃዋሚዎቹን ይበቀላል፥ ለጠላቶቹም ቍጣውን ይጠብቃል። በቍጣው ፊት የሚቆም ማን ነው? የቍጣውንም ትኵሳት ማን ይታገሣል? መዓቱ እንደ እሳት ይፈስሳል፥ ከእርሱም የተነሣ ዓለቶች ተሰነጠቁ’ ናሆ 1፡1፣6
‘‘ከቍጣው የተነሣ ምድር ትንቀጠቀጣለች አሕዛብም መዓቱን አይችሉም’’ ኤር 10፡10
‘‘እኛ በቍጣህ አልቀናልና፥ በመዓትህም ደንግጠናልና’’ መዝ. 90፡7

እግዚአብሔር በተቆጣ ጊዜ የሚመልሰው የለም፡፡ ቅዱሳን የቁጣውን መጠን ስለሚያውቁ በትሕትና ይለምኑታል፡፡

ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ቁጣ ደጋግሞ ቢነግረንም አንድ ሌላ ደስ የሚያሰኝ ነገርም ነግሮናል፡፡ የእግዚአብሔር ቁጣው ለዘላለም አይደለም፡፡ "ምሕረቱ ለዘላለም ነውና" ይላል እንጂ "ቁጣው ለዘላለም ነውና" አይልም:: የእግዚአብሔር ቁጣ ጊዜያዊ ነው፡፡

‘መሐሪ ነኝና ለዘላለም አልቆጣም’ ኤር 3፡12
‘ቁጣው ለጥቂት ጊዜ ሞገሱ ግን ለሕይወት ዘመን ነው’ መዝ 29፡5
‘ጌታ ለዘላለም አይጥልም ቢያሳዝንም እንደ ምሕረቱ ብዛት ይራራል ፤ የሰው ልጆችን ከልቡ አያስጨንቅም አያሳዝንምም’ ሰ.ኤር 3፡31

የፈጣሪን የነነደ የቁጣ እሳት ማጥፋት የሚቻለን በዕንባ ነው፡፡ በደላችንን አምነን ቅጣት ይገባናል ነገር ግን መሐሪ ነህና ማረን ማለት ይገባል፡፡ ንጉሥ ዳዊት ‘አቤቱ በቁጣህ አትቅሠፈኝ በመዓትህም አትገሥፀኝ’ ብሎ የፈጣሪን ቁጣ አበረደ፡፡ /መዝ 38፡1/ ነቢዩ ኤርያስም ‘አቤቱ ቅጣኝ ነገር ግን እንዳታዋርደኝ በመጠን ይሁን እንጂ በቁጣ አይሁን’ ብሎ ተለማመጠ፡፡ ኤር 10፡24

አንድ ሠዓሊ በጣም ብዙ ደክሞ የተጠበበትን ሥዕሉን የፈለገ ቢበሳጭ ለረዥም ጊዜ ያንን ሥዕል ለመሳል የተጠበበትን ጥበብ አስቦ ሥዕሉን ወደ እሳት አይጨምረውም፡፡ አባ ጊዮርጊስ እንዲህ ሲል ይለምናል ‘ሠዓሊ ሥዕሉን ያጠፋል ወይ? [ጌታ ሆይ እኔን ስትፈጥር የተጠበብክበትን] የቀደመ ጥበብህን አስብ እንጂ! አስበህም ማረኝ! [ያጠፋዖኑ ለሥዕሉ ሠዓሊ ፤ ኪነተከ ዘትካት ኀሊ]

ይቅርታውን በንስሓ ለሚለምኑ ሁሉ ምሕረቱ ቅርብ ነው፡፡ በቀኝና በግራው ወንበዴዎች በተሰቀሉበት በዕለተ አርብ የግራው ወንበዴ ሲሰድበው ጌታ መልስ አልሠጠም፡፡ የቀኙ ወንበዴ ማረኝ ሲለው ግን ከአፉ ተቀብሎ በገነት ትሆናለህ አለው፡፡ ቁጣው የራቀ ምሕረቱ የበዛ እርሱ የራበው ሰው ለምግብ የሚቸኩለውን ያህል ይቅር ለማለት ይቸኩላል፡፡ ‘ምሕረትን ይወድዳልና ቁጣውንም ለዘላለም አይጠብቅም ተመልሶ ይምረናል ፤ ክፋታችንንም ይጠቀጥቃል ፤ ኃጢአታችንንንም በባሕሩ ጥልቅ ይጥለዋል’ ሚክ 7፡18

ልጆች ሳለን ጥፋት ስናጠፋ ከወላጆቻችን እንደበቃለን፡፡በተደበቅንበት ሰዓት ውስጣችን በፍርሃት ይርዳል፡፡ ‘ዛሬ ገደለኝ’ ‘ዛሬ መሞቴ ነው’ ብለን እንጨነቃለን፡፡ የሚደርስብንን ቅጣት እጅግ አጋንነን ከመፍራታችን የተነሣ መሬት ተሰንጥቃ ብትውጠን አንጠላም፡፡ በዚያ ሁሉ ጭንቀት ውስጥ ግን ወላጆቻችንም እስኪያገኙን ይጨንነቃሉ፡፡ እግዚአብሔርም እንዲህ ነው፡፡ አጥፍቶ በገነት ዛፎች መካከል የተሸሸገ አዳምን ወዴት ነህ ብሎ የፈለገ እርሱ እኛንም ይፈልገናል፡፡ አዳም ከገነት ሳይባረር ገነት ውስጥ እንደጠፋ ፈጣሪ ሳያባርረን ራሳችንን በኃጢአት ተሸማቅቀን ያባረርን እኛን ይፈልገናል፡፡ እርሱ ስለመጥፋትህ ይጨነቃል አንተ ‘ዛሬስ አይምረኝም’ ትላለህ፡፡

የሚገርመው በጥፋታችን ከተደበቅንበት ወላጆቻችን ካገኙን በኋላ ሁለተኛው ዙር ጭንቀታችን ‘ምን አጥፍተህ ነው የተደበቅከው’ መባል ነው፡፡ ጥፋታችንን ሲያውጣጡን እንንቀጠቀጣለን፡፡ ያጠፋነውን ስለምናውቀው ስንት እንደሚያስገርፈንም እናውቀዋለን፡፡ ‘ብትናገር ይሻላል? ግዴለህም!’ ብለው አግባብተውም አስፈራርተውም ወላጆቻችን ጥፋታችንን ያውጣጡናል፡፡ እየፈራን ያጠፋነውን ጥፋት ስንናዘዝ ግን ወላጆቻችን በጥፋታችን ቅጥል ብለው ‘አልመታህም ተናገር’ ያሉንን ረስተው የዱላ ዝናም ያዘንቡብናል፡፡ እግዚአብሔር ግን ጥፋትህን ስትነግረው ቁጣው የሚገነፍል አባት አይደለም፡፡
’’ኃጢአታችንን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነፃን የታመነና ጻድቅ ነው’ 1ዮሐ 1፡9

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
++ የድንግል ማርያም ተነሥታለች! +++

ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በልጅዋ ፈቃድ ከሞት መነሣት ኦርቶዶክውያን አባቶች ሲያስተምሩ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቅሱት ማስረጃ በመዝ. 131፡8 ላይ ያለውን ‹‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦት›› የሚለውን ቃል ነው፡፡ ይህንን ጥቅስ ከድንግል ማርያም ትንሣኤ ጋር አያይዞ መጥቀስ አሁን የተጀመረ ነገር ሳይሆን ብዙ ክፍለ ዘመናትን ያስቆጠረ ነገር ነው፡፡ ሠላሳ ሦስተኛው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ቅዱስ ቴዎዶስዮስ ከእርሱ ቀድመው የተነሡ አበው ያስተላለፉለትን የእመቤታችንን ዕረፍትና ትንሣኤ ታሪክ የዛሬ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በፊት በጻፈው ድርሳን ላይ ፣ በነገረ ማርያም ሊቃውንት ዘንድ Doctor of Dormition በመባል የሚታወቀው ሊቁ ዮሐንስ ዘደማስቆ ፣ ሐዋርያውያን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በድርሳኖቻቸው ላይ ስለ ድንግል ማርያም ትንሣኤ ባነሡና በዓለ ዕርገትዋን ባከበሩ ቁጥር የሚያነቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ‹‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦት›› የሚለውን የዳዊት መዝሙር ነው፡፡ በእርግጥ ይህንን ቃል ከድንግል ማርያም ጋር ምን ያገናኘዋል? ‹ማርያም ተነሣች› የሚል ነገር አለውን? የሚለውን ጥያቄ በዚህች አጭር ጽሑፍ እንመለከታለን፡፡ ወደዚህ ጉዳይ ከመግባታችን በፊት ግን አንድ ቁምነገርን እናስቀድም፡፡

በሐዲስ ኪዳን ለምናምን ፣ በወንጌል ለምንመራ ክርስቲያኖች የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ምን ያደርጉልናል? የሙሴ ሕግጋት ፣ የነቢያት መጻሕፍት ፣ የዳዊት መዝሙራት ለክርስቲያኖች ምን ይጠቅሙናል? ብለን ከመጠየቅ እንጀምር፡፡ የዚህ ጥያቄ መልሱ ጌታችን ‹‹በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ሊፈጸም ይገባል›› እንዳለው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ በምሥጢር የሚናገሩት ስለ ክርስቶስ ስለሆነ ነው፡፡ (ሉቃ. 24፡44) ‹ከሙሴና ከነቢያት ጀምሮ ስለ እርሱ የተጻፈውን ተረጎመላቸው› ተብሎ የተነገረላቸው የኤማሁስ መንገደኞች ‹በመንገድ ሲናገረን መጻሕፍትን ሲከፍትልን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን?› ብለው እንደተናገሩ ብሉይ ኪዳን በእርግጥ ስለ ክርስቶስ እንደሚናገር በሚገባ ትርጉሙን ከተረዳን ልባችን በጥልቅ ተመሥጦ ይቃጠላል፡፡ ይህንን የአባቶችን ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ መነፅር በዓይናችን ካጠለቅን ብሉይ ኪዳንን እያነበብን በሐዲስ ኪዳን ባሕር ውስጥ መዋኘት እንችላለን፡፡ በኅብረ አምሳል (Typology) አስቀድሞ የተነገረበትን ምክንያት (Primary application) እና ፍጻሜውን (Ultimate fulfillment) ስንረዳ በታሪክና ትንቢት ሁሉ ውስጥ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስን እያገኘነው ስንደነቅ እንኖራለን፡፡

በገነት መካከል ተኝቶ ከጎኑ የሁላችንን እናት ሔዋንን ያስገኘውን አዳም ታሪክ ስናነብ በዕለተ ዓርብ በቀራንዮ በመስቀል ላይ አንቀላፍቶ ከጎኑ በፈሰሰው የጥምቀት ውኃ የሁላችን እናት ቤተ ክርስቲያንን ያስገኘውን ክርስቶስን እናየዋለን፡፡ ወይን ጠጥቶ ሰክሮ ዕርቃኑን የወደቀውንና ካም ሲዘብትበት ፣ ሴምና ያፌት ዕርቃኑን የሸፈኑለትን የኖኅን ታሪክ ስናነብ የሞትን ጽዋ ጠጥቶ በሰው ልጅ ፍቅር ሰክሮ ዕርቃኑን የተሰቀለውንና አይሁድ ሲዘብቱበት ፀሐይና ጨረቃ ዕርቃኑን የሸፈኑለትን ክርስቶስን እናየዋለን፡፡ አብርሃም የሚወደውን ልጁን ይስሐቅን ሊሠዋ መፍቀዱንና በግ የመሠዋቱን ታሪክ ስናነብ አንድያ ልጁን እስኪሠጥ ድረስ ዓለሙን የወደደውን እግዚአብሔር አብንና እስከ ሞት ድረስ የታዘዘ ልጁን ንጹሑን በግ ክርስቶስን እናየዋለን፡፡ ዳዊት ጎልያድን ድል አድርጎ እስራኤልን ነጻ ሲያወጣ ስናይ ክርስቶስ ዲያቢሎስን ድል አድርጎ የሰው ልጅን ነጻ ሲያወጣ ይታየናል፡፡ እስራኤል በበረሃ ተጉዘው በበትር ከተመታው ከዓለት ውኃ ፈልቆላቸው ሲጠጡ ስናይ በዕለተ ዓርብ ጎኑን በጦር ተወግቶ በደሙ ጥማችንን ያረካልን መድኃኔ ዓለም ይታየንና ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ‹ያም ዓለት ክርስቶስ ነበረ› እንላለን፡፡

ወደ መገናኛው ድንኳን ገብተን ደብተራ ኦሪትን ብንጎበኝ እንኳን ክርስትናችን አይለቀንም፡፡ በመሠዊያ ላይ የሚሠዋውን በግ ስናይ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደው የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ ክርስቶስ በሕሊናችን ይመጣብናል፡፡ ወደ ድንኳኑ ዘልቀን በመቅረዙ ላይ መብራት ሲበራ ስናይ እውነተኛው ብርሃን ክርስቶስ ፣ ዕጣን ስናይ የኃጢአት ሽታችንን ያራቀልን ክርስቶስ ፣ በወርቅ የተለበጠ ታቦት ስናይ በመለኮቱ መለወጥ የሌለበትን ክርስቶስ ፣ መናውን ስናይ የሕይወት እንጀራ ክርስቶስ እየታየን እንደ ኤማሁስ መንገደኞች ‹‹ልባችን እየተቃጠለ ለካስ ኦሪትና ነቢያት ሁሉ የሚናገሩት ስለ ክርስቶስ ነበረ?›› እንላለን፡፡

ኦርቶዶክሳውያን ከሆንን ደግሞ ጌታን ባገኘንበት ሥፍራ ሁሉ እመቤታችንን ፍለጋ ማማተራችን አይቀርም፡፡ አዳምን የክርስቶስ ምሳሌ ሆኖ ስናየው አዳምን ያለ አባት ያስገኘችዋ መሬት ያለ ወንድ ዘር የወለደችውን ድንግል ሆና ትታየናለች፡፡ አብርሃም የሠዋውን ከዱር ቀንዱ እንደታሰረ የወጣ በግ ስናይ የድንግልናዋ ማኅተም ሳይፈታ የወለደችው የበጉ እናት ትታየናለች፡፡ ወደ መገናኛው ድንኳን ገብተንም አናርፍም ፣ እርሱ መብራት ሆኖ ሲታየን እርስዋ መቅረዝ ትሆንልናለች፡፡ እርሱ ዕጣን ሲሆን እርስዋ ማዕጠንት ትሆናለች ፣ እርሱ ታቦት ሲሆን እርስዋ ታቦቱ ያለበት ቅድስተ ቅዱሳን ትሆናለች ፣ እርሱ ጽላት ሲሆን እርስዋ የጽላቱ ማደሪያ ታቦት ትሆናለች ፣ እርሱ በጽላት ላይ የተጻፈው ቃል ሲሆን እርስዋ ጽላት ትሆናለች ፣ እርሱ የተሰወረ መና ሲሆን እርስዋ የመናው መሶበ ወርቅ ትሆናለች፡፡ ለሰብአ ሰገል ‹ሕጻኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት› እንደተባለላቸው እኛም በሔድንበት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ የጌታችንን ምሳሌ ባነበብንበት ሥፍራ ሁሉ እናቱንም እናያታለን፡፡

እውነቱን ለመናገር ለመመርመር ትዕግሥት ላለው ሰው ስለ ክርስቶስ በሚናገሩት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ እንኳን ድንግል ማርያምን ቀርቶ ከሐዲው ይሁዳንም ማግኘት ይቻላል፡፡ ዮሴፍ የክርስቶስ ምሳሌ ሲሆን ዮሴፍ በሃያ ብር እንዲሸጥ ሃሳብ ያቀረበው ወንድሙ ይሁዳ የአስቆሮቱ ይሁዳ ምሳሌ አይደለምን? ፍልስጤማውያንን ድል ያደረገው ናዝራዊው ሶምሶን የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ሲሆን ሶምሶንን እየሳመች አሳልፋ የሠጠችው ደሊላ ስሞ የሸጠው የይሁዳ ምሳሌ አይደለችምን? አባቱን ለመግደል ሲያሴር ኖሮ መጨረሻ በዛፍ ላይ ተሰቅሎ የሞተው አቤሴሎምስ ጌታውን አሳልፎ ሠጥቶ ተሰቅሎ የሞተው የይሁዳ ምሳሌ አይደለምን? ‹የታመንሁበት የሰላሜ ሰው እንጀራዬን የበላ ተረከዙን በእኔ ላይ አነሣ› ተብሎ የተነገረው ስለ ይሁዳ አይደለምን? ብሉይ ኪዳን እንኳን አምላክን ስለወለደችው ቅድስት ድንግል ቀርቶ አምላኩን ስለሸጠው ይሁዳም ትንቢት ተናግሯል፡፡

አሁን ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ! ‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦት› ብሎ ዳዊት ስለ ቤተ መቅደስ መሠራትና ታቦቱም ወደ ቤተ መቅደሱ ስለመግባቱ የዘመረው መዝሙር ፣ ልጁ ሰሎሞንም መቅደሱ ተሠርቶ ሲያልቅ ደግሞ የዘመረው ይህ መዝሙር ከድንግል ማርያም ጋር ምን ያገናኘዋል? (2ዜና 6፡41) ኦርቶዶክሳውያን አባቶች ከጥንት ጀምሮ ይህንን ጥቅስ ከድንግል ማርያም ጋር የሚጠቅሱት ዳዊት ስለ መቅደሱ መሠራትና ስለ ታቦቱ መግባት የተናገረ መሆኑ ጠፍቷቸው ነው? ‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦት› የሚለውን የዳዊት መዝሙር
ከድንግል ማርያም ጋር አገናኝተን እንድናስብ ያነሣሣን ምንድር ነው? ወደሚለው እንምጣ፡፡

ዳዊት ስለ ታቦቱ የተናገረውን እኛ ስለ ድንግል ማርያም ሆኖ እንዲሰማን ያደረገው ራሱ ዳዊት ነው፡፡ ዳዊትን የእግዚአብሔር ታቦት ወደ እርሱ ስትመጣ ‹‹የእግዚአብሔር ታቦት እንዴት ወደ እኔ ይመጣል?›› ሲል አልሰማነውምን? (2ሳሙ. 6፡9) ይህን ንግግርስ ኤልሳቤጥ ‹‹የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?›› ብላ ለድንግል ማርያም አልደገመችውምን? (ሉቃ. 1፡43) ዳዊት የፈራው ታቦት ወደ እርሱ ሲቀርብ ከዙፋኑ ተነሥቶ በታቦቱ ፊት እየዘመረ ሚስቱ ሜልኮል እስክትንቀው አልዘለለምን? (2ሳሙ. 6፡16) በኤልሳቤጥ ማኅፀን የነበረው ዮሐንስስ የድንግልን ‹‹የሰላምታዋን ድምፅ በሰማ ጊዜ› እናቱ እስክታደንቀው ‹ፅንሱ በደስታ ዘለለ›› አልተባለምን? (ሉቃ. 1፡44) ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ የድንግል ማርያምና የልጅዋ ክብር ላልገባቸው ሰዎች ‹‹እንደ ዮሐንስ በማኅፀን ውስጥ መዝለል ቢያቅታችሁ ምነው ነፍስ ካወቃችሁ በኋላ እንኳን ለእግዚአብሔር ማደሪያ እንደ ዳዊት በምስጋና ብትዘሉ?›› ያለው ለዚህ ነው፡፡ እኛ ምን እናድርግ የእግዚአብሔር ታቦት በጌት ሰው በአቢዳራ ቤት ሦስት ወር ያህል ቆየች እንደተባለ ‹‹ማርያምም በዘካርያስ ቤት ሦስት ወር ያህል ቆየች›› ተብሎ ተጽፎ አነበብን፡፡ (2ሳሙ. 6፡11 ፤ ሉቃ. 1፡56) ታዲያ የድንግል ማርያም ታሪክ ከእግዚአብሔር ማደሪያ ከታቦቱ ታሪክ ጋር አንድ ሆኖ ስናገኘው ዳዊት ስለ ታቦት የተናገረውን ስለ ድንግል ማርያም እንደምን አንጠቅስ? የነገረ ማርያምን ታሪክ እንጥቀስ ካልንማ ታቦቱ በወርቅ እንደተለበጠ በንጽሕና ያጌጠችውን ፣ ታቦቱ በመቅደስ እንደኖረ በመቅደስ ያደገችውን ፣ ታቦቱን በትሩ አብባ የተገኘች አሮን እንደ ጠበቃት በትሩ ያበበች ዮሴፍ የጠበቃትን፣ ታቦቱን የነካ ዖዛ እንደተቀሠፈ (2ሳሙ. 6፡7) የድንግልን ሥጋ ነክቶ የተቀሠፈውን ታውፋንያ ታሪክ እንጠቅስ ነበር፡፡

‹የመቅደስህ ታቦት› ማለት መቅደስ የተባለው የሰውነትህ ማደሪያ እናት ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ ሰውነቱን ‹ይህን መቅደስ አፍርሱት› አላለምን? ‹በጉ መቅደስዋ ነው› ተብሎ አልተጻፈምን? ስለዚህ ‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት› ማለት ጳውሎስ ወደ ዕረፍቱ ለመግባት እንትጋ እንዳለው ‹‹ጌታ ሆይ ‹ዕረፍትህ› ወደተባለ ወደ ሰማያት አንተ ብቻ ተነሥተህ አትቅር የመቅደስ ሰውነትህ ማደሪያ እናትህንም ይዘህ ተነሥ›› ማለት ነው፡፡

የእመቤታችን ትንሣኤ ብዙዎችን ማከራከሩ እንዴት ያሳዝናል? ክርስቶስ ‹ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ› ብሏል፡፡ እውነት ትንሣኤን ለወለደች እናት መነሣትዋ ትልቅ ነገር ነው? የሕይወት እናት ሕያው ሆነች ቢባል ያስቆጣልን? ሞትን የሞተው በልጅዋ አይደለምን? የሕይወትን እናት ሞት ይዞ አስቀራት ማለት ደስታ የሚሠጠው ለሞት አበጋዞች ነው፡፡ ‹‹አምላክ ያደረባት የምትናገር ታቦት ፈርሳ ቀርታለች ማለት ፣ ታቦተ ጽዮን ድንግል በሞት ፍልስጤም ተማርካ ቀርታለች›› ማለት የሚያስደስተው በማኅፀንዋ ፍሬ የተፈረካከሰው ዲያቢሎስ ነው፡፡ ለእኛ ለኦርቶዶክሳውያን የሚደንቀን መሞትዋ እንጂ መነሣትዋ አይደለም፡፡

ቅዱስ ያሬድ ‹‹የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል›› እንዳለው ሕይወትን ያስገኘች ድንግል ፣ አምላክን የታቀፉ ክንዶች ፣ የእግዚአብሔር ዙፋን የሆኑ ጉልበቶች በሞት መሸነፋቸው ያስደንቀናል፡፡ መነሣትዋ ግን የምንጠብቀው ነው፡፡ አልዓዛርን ‹አልዓዛር አልዓዛር› ብሎ ያስነሣ ጌታ ፣ በዕለተ ዓርብ በሞቱ ብዙ ሙታንን ያስነሣ ጌታ እናቱን አስነሣ ሲባል የሚቆጡ እንዴት ያሉ ናቸው?

ሁለቱ ምስክሮች የተባሉ ሄኖክና ኤልያስ ወደ ምድር መጥተው አስተምረው ከተገደሉ ‹‹ከሦስት ቀን ተኩል በኋላ ከእግዚአብሔር የወጣ የሕይወት መንፈስ ገባባቸው በእግሮቻቸውም ቆሙ… በሰማይም ፡- ወደዚህ ውጡ የሚላቸውን ታላቅ ድምፅ ሰሙ ፤ ጠላቶቻቸውም እየተመለከቱአቸው ወደ ሰማይ ወጡ›› ይላል፡፡ (ራእ. 11፡4-12) ሄኖክና ኤልያስን ከምጽአቱ በፊት ዳግም ላይሞቱ ከሞት አስነሥቷቸው በጠላቶቻቸው ፊት ወደ ሰማይ የሚያሳርጋቸው አምላክ እናቱን በወዳጆችዋ ፊት አስነሥቶ አሳርጓታል ሲባል በቁጣ መቃወም ምን ይባላል?

እንደልጅዋ በራስዋ ዐረገች (Ascension) በማለትና ልጅዋ ወደ ራሱ ነጥቆ ወሰዳት (Assumption) በማለት መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት ከቻልን የእመቤታችን ማረግ ምኑ ያከራክራል? ዝናምን ከከለከለው ኤልያስ ንጹሑን ዝናም ያስገኘችው ድንግል አትበልጥምን ፣ አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር ካደረገው ሄኖክስ ይልቅ ለእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነችው እመ አምላክ አትበልጥምን?

እኛ ግን ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ‹‹በሞትዋ ምድር መራራ ኀዘን ስታዝን በሰማይ ደስታ ሆነ እንዳለ›› እመቤታችን ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም ስትሸጋገርም ሆነ ፣ በልጅዋ ሥልጣን ተነሥታ ስታርግ በሰማይ የሚኖረውን ደስታ በእምነት እናስተውላለን፡፡ ያ ደሃ አልዓዛር እንኳን ሲሞት መላእክት ነፍሱን ወደ አብርሃም አጅበው ወስደውት ነበር ፣ ኤልያስም ሲያርግ መላእክት በእሳት ሰረገላና በእሳት ፈረሶች ነጥቀውት ነበር፡፡ የአምላክን እናት ዕርገት ስናስብ ከዚህ በላይ ዝማሬ ይታየናል ፤ ቅዱስ ቴዎዶስዮስ እንደጻፈው ቅዱስ ያሬድም ‹በመሰንቆሁ እንዘ የሐሊ› እንዳለው አባትዋ ዳዊት ‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት› እያለ እየዘመረ ወላዲተ አምላክ ወደዚያኛው ዓለም ተሸጋግራለች፡፡ ኤልያስ ወደ ሰማይ ሲነጠቅ መጎናጸፊያውን ለበረከት እንዲሆነው ለደቀ መዝሙሩ ኤልሳዕ እንደሠጠው እመቤታችንም በልጅዋ ሥልጣን ወደ ሰማይ ስታርግ መግነዝዋን (መታጠቂያዋን) ለቶማስ በመሥጠትዋ ኦርቶዶክሳዊያን አብያተ ክርስቲያናት አሁንም ድረስ ተከፋፍለው በታላቅ ፍቅር በረከትዋን ይቀበሉበታል፡፡

እኛ ኦርቶዶክሳዊያን ስለ እመቤታችን መነሣት ስናስብ የምንጠይቀው ‹ተነሣች ወይስ አልተነሣችም ፤ ወደ ሰማይ ዐረገች ወይንስ ዐላረገችም› ሳይሆን ‹በሰማይ የተደረገላት አቀባበል ምን ይመስል ይሆን?› ብለን ነው፡፡ ደሃው አልዓዛር በሞተ ጊዜ መላእክት ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት ከተባለ የአምላክን እናት ምን ያህል አጅበዋት ይሆን? ወደ ሰማይ ማረግ ለእርስዋ ቁምነገር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሰማይን በእጆቹ የሚይዘውን አምላክ በእጆችዋ የያዘች ሁለተኛ ሰማይ ናት፡፡ እርስዋ ወደ ሰማይ በማረግዋም ዕድለኛዋ እርስዋ ሳትሆን ሰማዩ ነው፡፡ ሰማይ ዙፋኑ ነው ፣ ምድርም የእግሩ መረገጫ ናት ድንግል ማርያም ግን እናቱ ናት፡፡ ከእናትና ከዙፋን እናት ትበልጣለች፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ እንዳለው ሰማይ አልወለደውም ፣ አላሳደገውም ፣ አላጠባውም ድንግል ግን ይህንን ሁሉ አድርጋለች፡፡ ስለዚህ ወደ ሰማይ ማረግዋ ክብሩ ለሰማዩ እንጂ ለእርስዋ አይደለም፡፡

እመቤታችን ወደ ሰማይ ስታርግ በእርግጥ አቀባበሉ እንዴት ይሆን? እኛ የሰው ልጆች እናታችንን ማክበርም መጦርም የምንችለው በምድር እስካለችና እኛም እስካለን ድረስ ነው፡፡ ‹እናትና አባትህን አክብር› ያለን ፈጣሪ ግን እናቱን ማክበር የሚችለው በምድር ብቻ ሳይሆን በሰማይም ጭምር ነው፡፡ እናቱ ወደ እርሱ ስትመጣ መድኃኔዓለም ክርስቶስ እንዴት ተቀብሏት ይሆን?
ንጉሥ ሰሎሞን እናቱ ቤርሳቤህ ወደ ቤተ መንግሥቱ በመጣች ጊዜ ያደረገውን እናስታውስ፡፡ ‹‹ንጉሡም ሊቀበላት ተነሣ ሳማትም ፤ በዙፋኑም ተቀመጠ ፤ ለእናቱም ወንበር አስመጣላት በቀኙም ተቀመጠች፡፡ እርስዋም ፡- አንዲት ታናሽ ልመና እለምንሃለሁ አታሳፍረኝ አለች፡፡ ንጉሡም ፡- እናቴ ሆይ አላሳፍርሽምና ለምኚ አላት›› ተብሎ ተጽፎአል፡፡ (1ነገሥ. 2፡19-20) ከዳዊት ሆድ ፍሬ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ንጉሥ ሰሎሞን ይልቅ በዳዊትን ዙፋን ለዘለዓለሙ ይነግሣል የተባለለት ክርስቶስ ይበልጣል፡፡ ስለ ክርስቶስ ‹‹ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ›› ተብሎ ተጽፎአል፡፡ (ማቴ. 12፡42) ክርስቶስ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከሆነ የክርስቶስ እናትም ከሰሎሞን እናት ትበልጣለች፡፡ ሰሎሞን ለእናቱ ከሠጣት ክብርም በላይ ክርስቶስ ለእናቱ የሚሠጣት ክብር ይበልጣል፡፡ የሰሎሞን ቤተ መንግሥት በምድር ነው ፤ የክርስቶስ ቤተ መንግሥት ግን በሰማይ ነው፡፡ መድኃኔ ዓለም ወደ ሰማያዊው መንግሥቱ እናቱን በጠራት ጊዜ እንደምን ተቀብሏት ይሆን? እንደ ሰሎሞን እናት ወንበር አስመጣላት እንዳንል በሰማይ መቆም መቀመጥ የለም፡፡ ነገር ግን ‹‹የወርቅ ልብስ ተጎናጽፋ ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች›› ተብሎ ድንግሊቱ ስለተሠጣት ክብር ተጽፎአል፡፡ ወርቅ መልበስዋ አነሳት የሚል ካለ ደግሞ ‹‹አሕዛብን በብረት በር የሚገዛቸውን ወንድ ልጅ የወለደችው›› ድንግል ‹‹ፀሐይን ተጎናጽፋ ፤ ጨረቃም ከእግሮችዋ በታች የሆነላት ፣ ዐሥራ ሁለትም ከዋክብት አክሊል የሆኑላት አንዲት ሴት ነበረች›› ተብሎ ተጽፎላታል፡፡ (መዝ. 44፡9 ፣ ራእ. 12፡1)

ለእኛ ለኦርቶዶክሳዊያን ድንግል ወደማያልፈው ዓለም ስትሸጋገር የነበራትን የክብር አቀባበል በሕሊናችን ከማሰብ በቀር ምን የሚያውከን ነገር የለም፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ድንግልን ምን ብሎ ተቀብሏት ይሆን? እዚህ ‹ጸጋን የተሞላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ› ብሎ ሰላምታ ያቀረበላት ይህ መልአክ ጸጋን የተሞላችው ወደ እርሱ ስትመጣ ምን ብሎ ተቀብሏት ይሆን? ቅድስት ኤልሳቤጥስ አሁንም ‹ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?› ብላት ይሆን? መጥምቁስ ዳግም በሰማይ በደስታ ዘልሎ ይሆን? ነቢያቱ ድንግልን እንዴት ተቀበሏት? ኢሳይያስ ‹ትፀንሳለች› ያላትን ድንግል ሲያያት ምን ይል ይሆን? ሕዝቅኤልስ ‹የተዘጋችዋ ደጅ› ወደ እርሱ ስትመጣ ምን አለ? ጌዴዎን ጸምሩን ፣ ኤልሳዕ ማሰሮውን ፣ አሮን በትሩን ፣ ኖኅ መርከቡን ባየ ጊዜ ምን ብሎ ይሆን? ሙሴስ ያልተቃጠለችው ዛፍ ወደ እርሱ ስትመጣ ዳግም እንደ ሲና ተራራው ጊዜ ጫማውን አውልቆ ይሆን? አዳም የልጅ ልጁን ሲያይ ሔዋንስ ዳግሚት ሔዋንን ስታይ ምን ብላ ይሆን? ሁሉንም በሰማይ ለመረዳት ያብቃን!

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ሚያዝያ 21 2010 ዓ ም ተጻፈ
(ይህችን አመት ተወኝ ) ስነ ግጥም በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ)
የዲ'ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች
ይህችን አመት ተወኝ +
_
(በመ/ር ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ)
+

የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ ጸልዩ! ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like እና Share ያድርጉ
FB: https://www.facebook.com/officialHenokhaile/
Telegram: https://www.tg-me.com/deaconhenokhaile
Instagram: https://www.instagram.com/p/CBnMF0nnhcQ/?igshid=549jvl607bv4
Youtube: https://www.youtube.com/channel/UCOaVsWC05aUjeqIEW3fWj7g
Audio
✝️ተግባራዊ ክርስትና ✝️
መምህር ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ )

ክፍል አንድ<፩>
ቤተ ክርስቲያናችን እንደወትሮው ሁሉ አሁንም መከራ አልተለያትም:: በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ እየተቀበልን ጸንተን መቆም የሚጠበቅብን ሲሆን በሚከተለው መንገድ ደግሞ ቤተ ክርስቲያናችንን እንድናግዛት በአክብሮት እጠይቃለሁ:: (መቼም ጸልዩ ማለት የዲያቆን ሥራ ነው)

የክርስቲያኖች ትልቁ መሣሪያችን እጃችንን ለጸሎት ወደ ሰማይ መዘርጋት ነው:: ዕንባችንም እንደ ራሔል ዕንባ ባሕርን ይከፍላል:: ራሳችንን በንስሓ ካዋረድንና ካለቀስን የማንቀለብሰው ነገር የለም::

የፊታችን ሰኞ የሦስት ቀናቱ ጾም ጾመ ነነዌ ይገባል::

ጾሙ ከመግባቱ አስቀድሞ ኦርቶዶክሳውያን ሁላችን ንስሓ እንግባ:: በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ ይህንን ያያችሁ ወንድሞቼና እኅቶቼ ሁላችሁ ንስሓ አባቶቻችሁን ምስክር አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር ተናዘዙ:: "ጌታ ሆይ ይህ የሆነው በእኔ በደል ነውና ኃጢአቴን ይቅር በለኝ" ብለን አብረን አምላካችንን እንማጸነው::

ከዚህ ንስሓ ጋር የታወጀውን የየነነዌ ጾም ጠዋት በኪዳንና ከሰዓት በቅዳሴ ማታ ደግሞ በጸሎተ ምሕላ በየአጥቢያችን እየተገኘን አምላካችንን እንማጸነው::
የቻልን ሦስቱን ቀናት እስከ ማታ እየጾምንና እየሰገድን የፈጣሪያችንን ምሕረት እንለምን::

በሦስት ቀን ጾም የነነዌን መዓት የመለሰ : በሦስት ቀን ጾም የግብፅን ተራራ ያፈለሰ የነስምዖን አምላክ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ ሊመጣ ያለውን እሳት ሁሉ በቸርነቱ ይመልስልን ዘንድ በልባችን ጉልበት እንስገድ::

ከቤተ ክርስቲያን አንድነት የተለዩትን እንዲመልስልን!
በዚህ ምክንያት የሚጠፉ ነፍሳትን እንዲጠብቅልን!
የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መናወጽ የሚሻውን ሁሉ እንዲያስታግሥልን ወደ ፈጣሪያችን በጋራ እንጩኽ::

በየጊዜው ለችግራችን ስእለት እንደምንሣለው አንድ ጧፍ እንኩዋን ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላም ስእለት አድርገን እንጸልይ:: አርከ መሀይምናን (የምእመናን ወዳጅ) ለቤተ ክርስቲያንም ቅን መሪን የሚሠጥ ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ በፊቱ ስለሚማልሉ የዋሃን ብሎ ሰላማችንን ይመልስልን::

"እግዚአብሔር እንዳይቀየማቸው ከመዓትም ተመልሶ ፍጹም ዕረፍትን ይሠጣቸው ዘንድ ስለ በደሉ አባቶቻችንና ወንድሞቻችን እንማልዳለን" በእንተ ቅድሳት

#ነነዌ_ኢትዮጵያ
#ንስሓ_ግቡ
#ትጉና_ጸልዩ
#አንዲት_ቤተ_ክርስቲያን
#አንድ_ሲኖዶስ
#አንድ_ፓትርያርክ
#eotc_one_holy_synod
#one_church
#one_patriarch
#his_holiness_abune_mathias
#oriental_orthodox
መዝሙረ ዳዊት 45

1. አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፥
ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው።

ከክፉ ነገር የምንዋጋበት ኃይላችን ብንሸሽም የምንጠጋበት ጋሻችን እግዚአብሔር ብቻ ነው:: በመጣብን ታላቅ መከራም ከእርሱ በቀር ረዳት የለንም::

2፤ ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፥
ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም።

እግዚአብሔርን ረዳታችን መጠጊያችን ኃይላችን ብለን አምነናልና ምድር የተባሉ ሰዎች በቁጣ ቢነሡብን እንደተራራ የገዘፉ ሰዎችም ወደ ዙሪያችን ቢመጡ አንፈራም::

አንድም ተራሮች ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም

እንደ ተራራ ያከበርናቸው ሰዎች ክብራቸውን ትተው ባሕር ወደ ተባለች ወደዓለም ውስጥ ጭልጥ ብለው ቢገቡና ራሳቸውን ቢያዋርዱ አንፈራም

እንደ ተራራ የገዘፈ የእምነት ጽናት ያላቸው ሰዎች ቢክዱ በባሕር ክህደት ልብ ቢወሰዱ አምላካችን ኃይላችን መጠጊያችን ነውና አንፈራም::

ተራሮች አባቶች ከእምነት ቢናወጹ
ወደ ባሕር ልብ ውስጥ ሸፍተው ቢሔዱ ቀድሞም መጠጊያችን አምላካችን ነውና አንፈራም::


3፤ ውኆቻቸው ጮኹ ተናወጡም፥
ተራሮችም ከኃይሉ የተነሣ ተናወጡ።

ጉልበተኞች በቁጣ ተነሡ መጡ መጡ ሲባል ሰምተን ነበር:: ኃያላን ሁሉ ከእግዚአብሔር ኃይል የተነሣ ፈራርሰዋል::

በየዘመናቱ ብዙዎች በቁጣ ተነሥተውብን ነበረ:: የሚያምንን ሰው ዓይኑን አያሳየኝ ብለው ጮኹ ተናወጡም:: ሆኖም ልባቸው እንደ ተራራ ያበጠ ሁሉ ኃይላችን መጠጊያችን ረዳታችን በሆነው በእግዚአብሔር ተናወጡ::

4: የወንዝ ፈሳሾች የእግዚአብሔርን ከተማ ደስ ያሰኛሉ፤ ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ።

መከራ እንደወንዝ ቢፈስስባት የእግዚአብሔር ከተማ ቤተ ክርስቲያን አዝና ተከፍታ አታውቅም::
የመከራ ፈሳሾች ቤተ ክርስቲያንን ደስ ያሰኙአታል::

ልጆችዋን የሚያጠነክርላት ወደ ቤቱ የሚመልስላት
በንስሓ የሚያጸዳላት በሰማዕትነት አክሊል የሚያከብርላት ነውና የወንዝ ፈሳሾች የእግዚአብሔርን ከተማ ቤተ ክርስቲያንን ደስ ያሰኛሉ::

እንደ ወንዝ ከሰማይ ወደ ምድር የሚወርዱ መላእክትም ቤተ ክርስቲያን በጥበቃቸው ደስ ያሰኙአታል::

ልዑል እግዚአብሔር ማደሪያው ቤተ ክርስቲያንን ለየ:: በመከራዋ ደስ የምትሰኝ ስለ ቁስልዋ የምትዘምርና ሐሴት የምታደርግ ቤቱን ከዚህ ዓለም ክፋት ሁሉ ለየ::

5፤ እግዚአብሔር በመካከልዋ ነው አትናወጥም፥
እግዚአብሔርም ፈጥኖ ይረዳታል።

የምትናወጽ የምትበጠበጥ ይመስላል እንጂ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር በመካከልዋ ነውና አትናወጥም::

"ጥበቃዬን አንሥቻለሁ" የማይል አምላካችን እግዚአብሔር አምላክዋ ነውና አትናወጥም:: በእሳት ሠረገላ ዙሪያዋን የሚከብባት በማይተኛ አምላክ የምትጠበቅ ናትና አትናወጥም::

6፤ አሕዛብ ተናወጡ መንግሥታትም ተመለሱ፤
እርሱ ቃሉን ሰጠ፥ ምድርም ተንቀጠቀጠች።

ቤተ ክርስቲያንን የናቁ ሁሉ ከክብራቸው ተዋረዱ
በቁጣ የተነሡባት ሁሉ ወደ ኋላቸው ተመልሰዋል::

ዝም ያለ የሚመስለው አምላክ ስለ ቤተ ክርስቲያን እርሱ ቃሉን ሰጠ፥ ምድርም ተንቀጠቀጠች።

7፤ የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር ነው፤
የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው።

በምድር ካሉ ሠራዊት ሁሉ የሚበልጡ መላእክት ጌታቸው እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው::
ብንሸሽም መጠጊያችን እሱ ነው::

8፤ የእግዚአብሔርን ሥራ፥ በምድር ያደረገውንም ተኣምራት እንድታዩ ኑ።

እግዚአብሔር በሰማይ ብቻ ያለ ይመስላችሁ እንደሆነ በምድርም የሚሠራውን ድንቅ ነገር ታዩ ዘንድ ኑ::

9፤ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነት ይሽራል፤
ቀስትን ይሰብራል፥ ጦርንም ይቈርጣል፥
በእሳትም ጋሻን ያቃጥላል።

የምንነደፍበትን ቀስት ሰብሮ የምንወጋበትን ጦር ቆርጦ ከጋሻ ጋር ያቃጥላል:: ጦርነትም ይሻራል:: ኃይላችን እርሱ ነውና ጦር አንሻም:: ጋሻችንም እርሱ ነውና::

10፤ ዕረፉ፥ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ፤
በአሕዛብ ዘንድ ከፍ ከፍ እላለሁ፥ በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ።

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል :- ዕረፉ፥ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ፤
በአሕዛብ ዘንድ ከፍ ከፍ እላለሁ፥
በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ።

11፤ የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር ነው፤
የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው።

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጥር 27 2015 ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
2025/07/13 15:27:05
Back to Top
HTML Embed Code: