Telegram Web Link
- የሚሮጥ ዲያቆን -

የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ገደማ ነው:: አቧራማውን የጋዛ ምድረ በዳ በፈጣን ሩጫ እያቦነነ የሚከንፍ አንድ ወጣት ታየ:: ሩጫው የነፍስ አድን ሠራተኞች ዓይነት ፍጥነት ያለው ነበረ:: አንዲትን ነፍስ ሳታመልጠው ለማትረፍ እየከነፈ ነው:: የሚሮጠው ደግሞ በፍጥነት በሚጋልቡ ፈረሶች የሚጎተት የቤተ መንግሥት ሠረገላ ላይ ነው:: በሰው አቅም ፈረስ ላይ ሮጦ መድረስ ባይቻልም ይህ ወጣት ግን ፈረሶቹ የሚያስነሡትን የጋዛን አቧራ በአፉ እየቃመ በአፍንጫው እየታጠነ እንደምንም ደረሰ::
በሠረገላው ውስጥ አንድ ጸጉረ ልውጥ የሩቅ ሀገር ሰው ተቀምጦ በእርጋታ መጽሐፍ እያነበበ ነው::

እግሩን እንደ ክንፍ ያቀለለው ሯጩ ዲያቆን ፊልጶስ ይባል ነበር:: በዚያ ምድረ በዳ ብቻውን ሲሮጥ የሚያጨበጭብለት ሰው የሚሸልመው ደጋፊ አልነበረም:: እንዲያውም ልብ የሚሰብ ኀዘን ላይ ነበረ:: እስጢፋኖስ የሚባል አብሮት ዲቁና የተሾመ የቅርብ ጓደኛውን በድንጋይ ወግረው በአሰቃቂ ሁኔታ ከገደሉበት ገና አርባ ቀን አልሆነም:: "ቤተክርስቲያን ስደት ላይ ሆና ምን ስብከት ያስፈልጋል?" በሚል ቀቢጸ ተስፋ እጁን አጥፎ ያልተቀመጠው ፊልጶስ ግን የወንድሜን ኀዘን ልወጣ ሳይል የምሥራች ለማብሠር በበረሃ ሮጠ::

ቀርቦ ያናገረው ጃንደረባ ደግሞ "የሚመራኝ ሳይኖር እንዴት ይቻለኛል?" የሚል ኦሪትን ይዞ ትርጓሜ ፍለጋ የሚቃትት ፣ ጥላው ይዞ አካሉን ፍለጋ የሚጨነቅ ትምህርት የተጠማ ኢትዮጵያዊ ነበረ:: ስለዚህ ይህ ዲያቆን መዳን የምትሻውን የጃንደረባውን ነፍስ በመዳን እውቀት አረስርሶ አሁኑኑ ካልተጠመቅሁ አሰኛት:: ብቻውን የሮጠውና አንድ ሰው ያስተማረው ዲያቆን ፊልጶስ ሮጦ ያዳነው አንድ ሰውን ብቻ አልነበረም:: በአፍሪቃ ቀንድ ለምትገኘው ሀገር ኢትዮጵያና ሕዝቦችዋ የመዳን ቀንድ የሆነ ክርስቶስን አሳያቸው:: አንድ ኢትዮጵያዊ አጥምዶ በእርሱ ብዙዎችን ከማጥመድ በላይ ምን ሙያ አለ? ጴጥሮስን በጀልባው ላይ ከዓሣ አጥማጅነት ወደ ሰው አጥማጅነት የቀየረ አምላክ ገንዘብ ያዡን ባኮስ ነፍሳት ያዥ አድርጎ ሸኘው:: "የህንደኬ ሹም ባኮስ ሆይ ከአሁን ወዲህ በህንደኬ ገንዘብ ላይ ብቻ አትሠለጥንም ፤ የእግዚአብሔር ገንዘቦች የነፍሳት ግምጃ ቤት ላይ የሠለጠንህ የመንግሥተ ሰማያት በጅሮንድ አደርግሃለሁ" ብሎ ሾመው::

ይህ ከሆነ ሁለት ሺህ ዓመት አለፈ:: የጃንደረባው የልጅ ልጅ የኢትዮጵያ ሕዝብም ከሠረገላ አልፎ በፍጥነት በሚሔድ ብዙ ዓይነት መጓጓዣ ሊሳፈር ተሰለፈ:: ትዕግሥት አጥቶ በገንዘብ ላይ ከመሠልጠን ይልቅ ገንዘብ ሠልጥኖበት በፍጥነት ከነፈ:: አንዱ ፊልጶስ ብቻ ሮጦ የማይደርስበት እልፍ ሕዝብ ዛሬ ሠረገላውን አጨናንቆታል:: እንደ ጃንደረባው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሳይሆን ስልኩ ላይ ያቀረቀረ ፣ ስለ ትንቢት ትርጉም ሳይሆን ስለ ኑሮ ብልሃት የተመራመረ ትውልድ ተነሥቶአል:: የኢሳይያስ ትንቢት ስለማን ቢነግር የማይገደው የሕይወት ውጣ ውረድ ፍቺ የሚሻ ትንቢት የሆነበት ፣ በመንፈስ ጭንቀት የታወከ ምስኪን ትውልድ ተነሥቶአል:: በእርግጥ ይህ ትውልድ ከዚህ ጭንቀት ለመውጣት የሚመራው ሳይኖር እንዴት ይቻለዋል? ለዚህ ሁሉ ሕዝብ የሚሆን ፊልጶስ ከወዴት ይምጣ?

ኸረ የዲያቆን ያለህ? ነፍስ አድን ፊልጶሳዊ ዲያቆን ሆይ ከወዴት ነህ? ነፍሳትን ለማዳን የሚያሳድድ እንጂ የሥጋ ምኞቱን የሚያሳድድ ዴማሳዊ ዲያቆን አልጠፋም:: እንደ እስጢፋኖስ በድንጋይ የሚወገር ዲያቆን እንጂ ድንጋይ አንሥቶ የሚማታ ዲያቆን አልጠፋም:: ሰረገላ ላይ ሆነው ግራ የተጋቡ ባኮሶች ብዙ ናቸው የፊልጶስ ግን እጥረት አለ:: ችግራቸውን ፈትቶ ጥያቄያቸውን መልሶ የሚሰወር ከሠረገላ አልወርድም ብሎ የማያስቸግር ፊልጶስ ግን እጥረት አለ:: ከእናንተ ቀድመን በተሾምን ዲያቆናት አንገትዋን የደፋች ቤተ ክርስቲያን በእናንተ ቀና እንድትል እንመኛለን:: የሚሮጥ ዲያቆን ያድርጋችሁ:: ምእመናን እሱን ፍለጋ የሚሮጡለት ዲያቆን ሳይሆን ነፍሳትን ፈልጎ የሚሮጥ ዲያቆን ያድርጋችሁ:: ከመቅደሱ ጠፍቶ የሚፈለግ ሳይሆን ፈረስ የማያመልጠው ዲያቆን ያድርጋችሁ::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ዲበ ሠረገላ ሰማይ በፍኖተ ዋሻ-አንግተን-ደስየ
ለኢጃት ዲያቆናት ሲመት
ግንቦት 6 2016 ዓ.ም.


#share

▫️@diyakonhenokhaile
https://www.tg-me.com/diyakonhenokhaile
እኔና ጓደኛዬ

(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለ ጓደኛው ባስልዮስ)

አንድ ዓይነት ፍላጎት ነበረን:: በተወለድንበት ሀገር ታላቅነት አንዳችን በሌላችን ላይ አንመካም:: ወደ ምንኩስናና ወደ እውነተኛው የሕይወት ፍልስፍና ጉዳይ ስንመጣ ግን ተለያየን:: እሱ ወደላይ ከፍ ሲል እኔ ደግሞ በዓለማዊ ምኞት መውረድ ጀመርሁ:: በወጣትነት ከንቱ ምኞት ክብደት ወደ ታች እስበው ጀመር:: ጓደኝነታችን ቢኖርም ቅርርባችን ግን ተሰበረ:: ምክንያቱም ፍላጎቶቻችን ተለያይተዋልና ውሎአችንን ማውራት አልቻልንም::

ቀስ ብዬ ወደ መንፈሳዊነት ስመጣ ግን ታግሦ በተዘረጋ እጅ ተቀበለኝ:: ከሌሎች ጋር ያለውን ጓደኝነት ትቶ ከእኔ ጋር ለማሳለፍ ፈቀደ:: ሆኖም ልዩነቶቻችንን ማጥበብ አልተቻለም:: በሕግ ችሎት ውስጥ ሁልጊዜ የሚውልና የዚያን መድረክ ደስታ የለመደ ሰው ሁሌም መጻሕፍትን ብቻ ከሚያይና ገበያ እንኳን ወጥቶ ከማያውቅ ሰው ጋር እንዴት አንድ መሆን ይችላሉ?

[ክህነት ሊሠጠን እንደሆነ] ዜናውን ያልሰማሁ መስሎት ሊነግረኝ መጣ:: 'ክህነት እንቀበል ወይስ አንቀበል?' በሚለው ላይ እሱ የእኔን ውሳኔ ሊከተል ወስኖአል:: እኔ ደግሞ [ለክህነት ብቁ ባልሆንም] የእርሱን ዓይነት ብቁ ሰው ወደ ኋላ ልጎትት አልችልም:: ስለዚህ እሺ አልሁ:: ክህነት የሚሠጥ ቀን ግን ተደብቄ አመለጥኩ:: እርሱ ግን ያለሁ መስሎት ተቀበለ:: ሳገኘው እጁን ስቤ በግድ ተባረክሁ:: አውቄ እንዳደረግሁት ሲያውቅ ተጎዳ:: ክህነትን ብቀበል አልጠላም ነበር:: በግ መሆን ያልቻለ ሰው ግን እንዴት እረኛ ሊሆን ይቻለዋል?

[St. John Chrysostom: On Priesthood] (Photo ትርጉም ባለው ቀን የተነሣ)

ጴጥሮሳዊ ቅጽበት

አርብ ዕለት ጌታ ከሰማቸው ስድቦች ሁሉ በፊት ጌታን የሚያቆስል አንድ ቃል ነበረ::
የሚወደው ደቀ መዝሙሩ ጴጥሮስ "አላውቀውም" እያለ ሲምል ሲገዘት ጌታ ሲሰማው ምንኛ ይሰማው ይሆን? እየሰማህ ስትታማ እንኩዋን ይከብዳል:: እየሰማህ አላውቀውም መባል ደግሞ የባሰ ነው::

ጴጥሮስ ያደረገው ታውቆት መራራ ለቅሶ አለቀሰ:: የእኔና የአንተ የአንቺ ጴጥሮሳዊ ቅጽበት መቼ ይሆን?

#share

▫️@diyakonhenokhaile
https://www.tg-me.com/diyakonhenokhaile
ጰራቅሊጦስ የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን ነው:: በትንሣኤው ተፀንሳ እስከ ዕርገቱ ድረስ ለዐርባ ቀናት ተሥዕሎተ መልክእ (Organ formation) የተፈጸመላት ቤተ ክርስቲያን ዛሬ የተወለደችበት ቀን ነው:: እግዚአብሔር በባቢሎን ሜዳ የበተነውን ቋንቋ የሰበሰበበትና እንዱ የሌላውን እንዳይሰማው እንደባልቀው ያሉ ሥሉስ ቅዱስ አንዱ የሌላውን እንዲሰማ ያደረጉበት ዕለት ዛሬ ነው:: ሰው ወደ ፈጣሪ ግንብ ሰርቶ በትዕቢት ለመውጣት ሲሞክር የወረደው መቅሠፍት ዛሬ በትሕትና ፈጣሪን ሲጠባበቁ ለነበሩ ሐዋርያት ፈጣሪ ራሱ ያለ ግንብ ወርዶ ራሱን የገለጠበት ዕለት ነው::

ዛሬ እስራኤል ከግብፅ በወጡ በሃምሳኛው ቀን በሲናን ተራራ የወረደው እሳትና በጽላት ላይ የተጻፈው ሕግ የተሠጠበት ቀን ነው:: ፋሲካችን ክርስቶስ በታረደ በሃምሳኛው ቀን በሐዲስ ኪዳንዋ ደብረ ሲና በጽርሐ ጽዮን በእሳት አምሳል መንፈስ ቅዱስ ወርዶ በሐዋርያት በልባቸው ጽላት ቃሉን የጻፈበት ቀን ነው:: በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ በርግብ አምሳል በትሕትና የወረደው መንፈስ ቅዱስ ዛሬ በእሳትና በነፋስ አምሳል ወደ ሐዋርያቱ የወረደው ዛሬ ነው:: ርግብ ሆኖ የወረደው ሊመሰክርለት እንጂ ኃይል ሊሠጠው ስላልነበረ ነው:: ዛሬ ግን ለሐዋርያቱ ኃይል ሊሠጣቸው ፈልጎ በእሳትና በነፋስ ኃይሉን ገለጠ::

መንፈስ ቅዱስ ሲወርድ በዚያ መገኘት ከፈለጋችሁ በቅዳሴው መካከል ተገኙ:: ካህኑን "ይህች ቀን ምን የምታስፈራ ናት? ይህች ቀን ምን የምታስጨንቅ ናት? መንፈስ ቅዱስ ከመልዕልተ ሰማያት የሚወርድባት?" ሲል ታገኙታላችሁ:: ኢሳይያስ ያየውን ራእይ ማየት ከፈለጋችሁ ወደ ቅዳሴ ገስግሱ:: ሱራፊ በጉጠት ፍሕም ይዞ ኃጢአታችሁን የሚተኩስበትን ደሙን ለመቀበል ከፈለጋችሁ ወደ ቅዳሴው ገስግሱ:: "ፈኑ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ላዕሌነ" እያላችሁ የምታዜሙበት ዕለታዊው ጰራቅሊጦስ ቅዳሴው ላይ ተገኙ:: በአዲስ ቋንቋ ትናገራላችሁ:: የእናንተ ቋንቋ ሳይቀየር የሁሉም ቋንቋ ተናጋሪ ሰምቶ ይረዳችሁዋል::

ለሐዋርያት የተሠጠኸውን ሠጥተኸን ከሐዋርያት ያገኘኸውን ያላገኘህብን ሆይ ቅዱስ መንፈስህ ከእኛ አትውሰድብን:: የማዳንህን ደስታ ሥጠን:: በእሺታም መንፈስ ደግፈን::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ሰኔ 16 2016 ዓ.ም.

#share

▫️@diyakonhenokhaile
https://www.tg-me.com/diyakonhenokhaile
የማይደክመው መምህር ክርስቶስ በምድር ላይ ለ33 ዓመታት ተመላልሶ በአፍም በኑሮም አስተማረ:: ከዚያም ነፍሱ ከሥጋው ስትለይ ወደ ሲኦል ወርዶ ለ33 ሰዓታት በወኅኒ ላሉ ሰላምን ሰበከላቸው:: ከትንሣኤው በኋላ ደግሞ ለአርባ ቀናት እየታየ የመንግሥቱን ነገር (ኪዳንን) አስተማረ:: ከዕርገቱ እስከ ጰራቅሊጦስ ደግሞ ለመላእክት ሥጋዌውን ገለጠ::

የክርስቶስ በአራቱ እንስሳ በሰው በላም በአንበሳና በንስር በተመሰሉ ወንጌላውያን የተጻፈው ታሪኩ በዕርገት ተጠናቀቀ:: ክርስቶስ እንደ ሰው ተወለደ ፤ እንደ ላህም ተሠዋ ፤ እንደ አንበሳ ከሙታን ተነሣ ፤ እንደ ንስር ዐረገ:: ሐዋርያት እያዩት ደመና ሠውራ ተቀበለችው::

በእርግጥ ደመና ሠውራ ስትቀበለው የመጀመርያ አልነበረም:: በተወለደ ጊዜም እውነተኛዋ ፈጣን ደመና በማሕፀንዋ ሠውራ ተቀብላው ነበር:: አሁን ደግሞ ደመና ሠውራ ተቀበለችው:: ሐዋርያት በዕርገቱ ተስፋ ነግሮአቸዋልና ደስ እያላቸው ተመለሱ::

በሃምሳኛው ቀን የነገራቸውን አጽናኝ ላከው:: በዮርዳኖስ ሲወርድ ለምስክርነት ነውና በርግብ አምሳል ነበረ:: አሁን ግን ኃይል ሊሆናቸው በነፋስና በእሳት አምሳል ወረደ::

በዓለ ሃምሳ እስራኤል ከግብፅ ከወጡ ሃምሳኛው ቀን ነበረ:: ይህ ዕለት ሙሴ ጽላት ይዞ የወረደበት ቢሆንም ሕዝቡ ደግሞ መታገሥ አቅቶት ጣዖት ሲያመልክ ተገኘ:: በዚህ ምክንያት በዚያች ዕለት ሌዋውያ ካህናት ስለዚህ ባዕድ አምልኮ ቅጣት 3ዐዐዐ ሰዎች ገደሉ:: (ዘጸ. 32:28) በሐዲስ ኪዳኑ በዓለ ሃምሳ ግን ሐዋርያት በልባቸው ፅላት ወንጌል ተጻፈ:: "የሞት አገልግሎት" እንደተባለችው ኦሪት 3000 ሰው አልገደሉም:: በጴጥሮስ ስብከት 3000 ሰው አዳኑ እንጂ::

የጰራቅሊጦስ ዕለት ክርስቶስ በደሙ የዘራውን ያጨደበት የመከር ቀን ነው:: የመከሩ ባለቤት ሠራተኞችን የላከበት ቀን ይህ ነው:: ጰራቅሊጦስ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን ሠራ::

ኤልያስ በእሳት ሠረገላ ተጭኖ ሲያርግ መጎናጸፊያውን ለኤልሳዕ ወረወረለት:: የእኛ መምህር ክርስቶስ ግን ከኤልያስ ይበልጣል:: ኤሎሄ ኤሎሄ ብሎ ሲጮኽ አይሁድ ባልሰማ ጆሮአቸው "ኤልያስን ይጣራል መጥቶ ያድነው" ብለው እንደዘበቱት አይደለም:: የእኛ መምህር ክርስቶስ ወደ ሰማይ ለማረግ ሠረገላ አይፈልግም:: በእርግጥ የመለኮትን እሳት መሸከም የሚችል ሠረገላ ከየት ይመጣል? እያዩት ከፍ ከፍ አለ:: ልብሱን አልወረወረም:: የእኛ መምህር ክርስቶስ ለሁላችን ልብሱን ሳይሆ ሥጋውና ደሙን ሠጥቶን ሔዶአል:: :: በዐሥረኛው ቀን ደግሞ መንፈሱን ደግሞ በበዓለ ሃምሳ አደለን:: እኛ ክርስቶስ ሲያርግ እያየን አንሮጥም:: ወደ ሥጋ ወደሙ እየቀረብን እርሱ በእኛ እኛም በእርሱ ይኖራል::

ጌታ በትንሣኤው ከኃጢአት ሞት በንስሓ እንድንነሣ አስተማረን:: "አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስ ያበራልሃል" ብሎ ከበደል በንስሓ ትንሣኤ እንድንነሣ ጠራን:: ትንሣኤውን አይተን በንስሓ ከተነሣን የሚቀረን ዕርገት ነው:: ከትንሣኤው በኋላ እያዩት ከምድር ከፍ ከፍ ያለው ጌታ ከንስሓ ማግሥት በጽድቅ ሥራ ከፍ ከፍ እያልን ከምድራዊነት እንድናርግ ይፈልጋል:: ዐርገን በቀኙ መቀመጥ ባንችል በጽድቅ ቀኙ እንዲያቆመን መንገዱ ይኸው ነው::

ጌታ ሆይ ይህን ቅዱስ ቃልህን ባትሠጠን ምን እንሆን ነበር?

ምስለ መዘክር :- ተፍጻሜተ ጉባኤ በሀገረ ቴክሳስ

#share

▫️@diyakonhenokhaile
https://www.tg-me.com/diyakonhenokhaile
2025/07/04 07:11:18
Back to Top
HTML Embed Code: