Telegram Web Link
ቃና ዘገሊላ

በቃና ዘገሊላ ወይም በገሊላዋ ቃና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፈጸመውን ተአምር በማሰብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በዓል ታከብራለች፡፡ ይህም በጥምቀት በዓል ማግስት በጥር ፲፪ ነው፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገሊላ ክፍል በምትሆን በቃና በተደረገ ሰርግ ላይ ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር ተገኝቶ ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በወንጌሉ ‹‹የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ እናት ድንግል ማርያምም በዚያ ነበረች›› እንዳለ እመቤታችን ለሠርገኞቹ ዘመድ ነበረችና ከልጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ በሠርጉ ላይ ተገኝታ ነበር፡፡ በተጨማሪ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ከጌታ ጋር በሠርጉ ተገኝተው ነበር፡፡ ሆኖም ግን የሠርጉ ሥነ ሥርዓት እየተከናወነ ባለበት ጊዜ ድንገት የወይን ጠጅ አለቀ፡፡ አሳላፊዎቹም በጭንቀት ግራ በገባቸው ጊዜ የጭንቅ አማላጅ አዛኝ እናታችን ድንግል ማርያም ጭንቀታቸውን ተረድታ ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወር ብላ ‹‹የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም›› አለችው፡፡
እርሱም መልሶ ‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› ‹‹ጊዜዬ ገና አልደረሰም›› አላት፡፡ እመቤታችንም ለአሳላፊዎቹ ‹‹የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ›› አለቻቸው፡፡ ጌታም በቦታው የነበሩ ስድስት የድንጋይ ጋኖች ውኃ ሞልተው እንዲያመጡ አዘዛቸው፡፡ ሲያመጡለትም ውኃውንም ወደ ወይን ለውጦ ለአሳዳሪው እንዲሠጡት አዘዘ፡፡ አሳዳሪውም ወደ ወይን የተለወጠውን ውኃ በቀመሰ ጊዜ አደነቀ፡፡ ከወዴት እንደመጣ ስላላወቀ ሙሽራውን ‹‹ሰው ሁሉ መልካሙን የወይን ጠጅ አስቀድሞ ያመጣል፤ ከጠገቡ በኋላም ተርታውን ያመጣል፤ አንተ ግን መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆየህ›› አለው፡፡ (ዮሐ.፪፥፩-፲፩)
ይህንን ድንቅ ተአምርም በማሰብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን አስተምህሮ በጥምቀት በዓል ማግስት ቀን የቃና ዘገሊላ በዓል ይከበራል፡፡ የቃና ዘገሊላ ጥንተ ነገሩ የተፈጸመው የካቲት ፳፫ ቀን ነው፡፡ ነገር ግን አባቶቻችን የውኃን በዓል ከውኃ በዓል ጋር ለማክበር ብለው የካቲቱን በዓል ወደ ጥር ፲፪ አምጥተውታል፡፡ ይህም ውኃ ወደ ወይን የተለወጠበትን በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ለማከናወን ነው፡፡
ከበዓሉ ረድኤት ያሳትፈን፤ አሜን!
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
#በጥምቀት_ዙሪያ_የሚነሱ_ጥያቄዎች_እና_መልሶቻቸው
#ጌታችን_ለምን_ተጠመቀ?
1. ምሥጢርን ለመግለጥ፡-
ጌታችን በፈለገ ዮርዳኖስ ሲጠመቅ ምስጢረ ሥላሴ ግልፅ ሆኗል፡፡ አብ በደመና “የምወደው የምወልደው ልጄ ይህ ነው” በማለቱ አብ የወልድ አባት መሆኑ ታወቀ፡፡ መንፈስ ቅዱስም የባሕርይ ሕይወቱ መሆኑን ሲያስረዳ በአምሳለ ርግብ በራሱ ላይ ተቀመጠ ወልድም በተለየ አካሉ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ ታየ፡፡ ስለዚህ ምሥጢርን ለመግለጥ ስንል የአንድነት የሦስትነት ምስጢር በጐላ ሁኔታ እንዲታወቅ ተጠመቀ ማለት ነው፡፡ /ማቴ. 3፥16/

2. ትንቢቱን ለመፈፀም፡-
በመዝሙር 46/47/፥16 ላይ “አቤቱ ውሆች አዩህ፣ ውሆችም አይተውህ ፈሩ ጥልቆች ተነዋወጡ ውሆችም ጮኹ፡፡” ተብሎ በቅዱስ ዳዊት የተነገረውን ትንቢት ለመፈፀም ተጠመቀ፡፡

3. አርአያ ሊሆነን፡-
ተጠምቆ እንድንጠመቅ አደረገን ሥርዓትን ሠራልን ቀድሞ በአርአያውና በአምሳሉ እንደፈጠረን አሁንም አርአያ ምሳሌ ሆነን፡፡ ለዚህም ነው ምሳሌን ከእኔ ተማሩ ያለን፡፡ /ማቴ 11፥29/ ለትምህርት ለአርአያ /ዮሐ. 13፥1-17/

4. የዕዳ ደብዳቤያችንን ለመደምሰስ፡-
አዳምና ሔዋን ፍዳው በፀናባቸው መከራው በበዛባቸው ጊዜ የሚያቃልልላቸው መስሏቸው ዲያብሎሰ ስመ
ግብርናችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ ባላቸው ጊዜ አዳም ገብሩ ለዲያቢሎስ (አዳም የዲያብሎስ የወንድ አገልጋይ) ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ (ሔዋን የዲያብሎስ ሴት አገልጋይ) ብለው ጽፈው ሰጡት፡፡ ዲያብሎስም ይህንን ደብዳቤ አንዱን በሲኦል አንዱን በዮርዳኖስ አስቀመጠው፡፡ በዮርዳኖስ ያስቀመጠውን ጌታችን ሲጠመቅ እንደሰውነቱ ረግጦ ደምስሶታል፡፡ ይህንን ጽሕፈት ለመደምሰስ ነው ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀው፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተፃፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፡፡” ያለው ቆላ 2፥14

#ጌታችን_መች_ተጠመቀ?

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው በ5531 ዓመተ ዓለም ዘመነ ሉቃስ ማክሰኞ ጥር 11 ቀን ከሌሊቱ በ10ኛው ሰዓት ነበር፡፡ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 19 በተጠመቀም ጊዜ ዕድሜው 30 ዓመት ከ13 ቀን ነበር፡፡ /ሉቃ. 3፥23/

#ጌታችን_ስለምን_በ30_ዓመት_ተጠመቀ?
በብሉይ ኪዳን ሥርዓትና ልማድ ካህናት ለቤተ እግዚአብሔር ተልእኮ እና መንፈሳውያን አገልግሎቶች ከ30 ዓመት ዕድሜ በፊት አደባባይ አይወጡም ነበር፡፡ እጅግ አስፈላጊ እንኳ ቢሆን ከ20 እና 25 ዓመት አስቀድሞ ለአገልግሎት መሰየም ልማድ አልነበረም፡፡ የቤተ እግዚአብሔር አገልጋዮች በዕድሜና በዕውቀት የበሰሉ፣ በጠባይና በሥራ ልምድ የተፈተኑ ተልዕኳቸውን በብቃት ለመወጣት በተገልጋዩ ሕዝብ ዘንድ የተመሰከረላቸው መሆን ነበረባቸው፡፡ /ዘፀ. 4፥3፤1ዜና መዋ. 23፥24፤ 1ጢሞ.  3፥6-10/ ያንን ሥርዓት ለመፈጸም ጌታችን የተጠመቀውና ለትምህርተ ወንጌል የተገለጠው በ30 ዓመቱ ነበር፡፡

ዮሐንስ መጥምቅም የጌታን መምጣት ለማወጅ በዮርዳኖስ ይሁዳ ምድረ በዳዎች ወጥቶ የታየው ከ30 ዓመት ዕድሜው በኋላ ነው፡፡ ሌላው ዐቢይ ምክንያት የሰው ሁሉ መጀመሪያ አዳም የ30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ተፈጥሮ በ40ኛ ቀን ተሰጥቶት ኋላም በኃጢአት ምክንያት ያስወሰደውን ልጅነት ለማስመለስ ነው፡፡

ክርስቶስ የተጠመቀው ክብር ሽቶ ሳይሆን የአብ የባሕርይ ልጅነቱን (የባሕርይ አምላክነቱን) ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ለማስመስከር፣ ውኃውን ለመቀደስ፣ የአዳምን ልጆች የእዳ ደብዳቤ ለመደምሰስና በስህተት የጠፋውን የልጅነት ክብር ለመመለስ ነው፡፡ ጌታ ተጠምቆ ከውኃው ከወጣ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ በማረፍ አብ በደመና ‹‹ይህ ልጄ ነው›› ብሎ ሲመሰክርለት ምሥጢረ ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በጉልህ ተረጋግጧል፡፡ /ማቴ. 3፥16/

#ጌታችን_በዮሐንስ_እጅ_ለምን_ተጠመቀ?

ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ሲሆን በአገልጋዩ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ በፍጹም ትሕትና ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ ይህንንም ያደረገልን አብነት ሊሆነን ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታችን ቅዱስ ዮሐንስን ‹‹መጥተህ አጥምቀኝ ›› ብሎት ቢሆን ኖሮ ነገ ነገሥታቱና መኳንንቱ ካህናቱን መጥታችሁ አጥምቁን ባሉ ነበር ስለዚህ እንዲህ እንዳይሆን ነው፡፡ ጌታችን ‹‹ጌታ ስሆን በባርያዬ እጅ እንደተጠመቅሁ እናንተም ወደ ቤተክርስቲያን ሄዳችሁ በካህናት እጅ ተጠመቁ›› ሲል ነው፡፡

ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀው ልጅነትን የምታሰጥ ጥምቀትን ባርኮ ቀድሶ ሊሰጠን እንጂ ክብር እንዲሆነው አይደለም፡፡ ምክንያቱም፡- እርሱ እከብር አይል ክቡር እጸድቅ አይል ጻድቅ ነውና፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ_ጌታችንን_በማን_ስም_አጠመቀው?

ጌታችን ዮሐንስን አጥምቀኝ ባለው ጊዜ "ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለሁ አንተን በማን ስም ላጥምቅህ? በአብ ስም እንዳላጠምቅህ አብ አባትህ ባንተ ሕልው ነው በወልድ ስም እንዳላጠምቅህ ወልድ አንተ ነህ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዳላጠምቅህ መንፈስ ቅዱስ ሕይወትህ ባንተ ሕልው ነው ታዲያ በማን ስም ላጥምቅህ?" ብሎ ቢጠይቀው ጌታም ‹‹እንደ መልከጼዴቅ ሥርዓት አንተ የዓለም ካህን ብርሃንን የምትገልጥ የአብ የባሕርይ ልጅ ሆይ ይቅር በለኝ›› ብለህ አጥምቀኝ አለው፡፡

#ዮሐንስ_ጌታን_ሲያጠምቀው_እጁን_ለምን_አልጫነበትም?
- ዮሐንስ በጥምቀት አከበረው /ልዕልና ሰጠው/ እንዳይባል፡፡
- መለኮትን በእጅ መንካት ስለማይቻል

#ጌታችን_ጥምቀቱን_ለምን_በዮርዳኖስ_አደረገው?
በኢየሩሳሌም አካባቢ ብዙ ወንዞች ኩሬዎችና ሐይቆች መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ ጌታ ጥምቀቱን በዮርዳኖስ ያደረገው ስለዚሁ አስቀድሞ የተነገረውን ትንቢት መፈጸሙን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ‹‹ባሕር አይታ ሸሸች ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ›› /መዝ.113፥3/ ከዚህም ጋር ከላይ ምንጩ አንድ የሆነው ዮርዳኖስ ዝቅ ብሎ በደሴት ተከፍሎ እንደገና እንደሚገናኝ በግዝረት በቁልፈት (በመገዘርና ባለመገዘር) ተለያይተው የነበሩ ሕዝብና አሕዛብ መላው የአዳም ልጆች በጌታችን ጥምቀት አንድ መሆናቸውን የሚገልጽ ትርጉም አለው፡፡ እስራኤል ዮርዳኖስን ተሻግረው ምደረ ርስት ገብተዋል፡፡ ያመኑ የተጠመቁ ምዕመናንም በጥምቀት ገነት መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉ፡፡ ሌላው በዮርዳኖስ ተጥሎ የነበረውን የዕዳ ደብዳቤ ይደመስስልን ዘንድ /ቈላ. 2፥14/

#ጌታችን_ለምን_በውሃ_ተጠመቀ?
እግዚአብሔር አምላክ በዘመነ ኦሪት ሰብዐ ትካትን በንፍር ውሃ ፈርኦንና ሰራዊቱን በኤርትራ ባሕር ካጠፋ በኋላ ሰዎች ውሃ ለመዓት እንጂ ለምሕረት አልተፈጠረም ይሉ ነበርና ለምሕረት እንደተፈጠረ ለማጠየቅ በውሃ ተጠመቀ ( ዘፍ 7÷17፤ ዘጸ 14÷1-29)

አንድም ውሃ እሳትን ያጠፋል እናንተም በውሃ ብትጠመቁ ከገሃነመ እሳት ትድናላችሁ ሲል ነው፡፡

አንድም ውሃ መልክን ያሳያል እናንተም በውሃ ብትጠመቁ መልክዓ ሥላሴን የአምላክን ቸርነት ርህራሔ ታያላችሁ ሲል ነው፡፡

አንድም በማር በወተት ቢጠመቅ ኖሮ እነዚህ ለባለጸጎች እንጂ ለድሆች አይገኝም ውሃ ግን በሁሉ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ጥምቀት የታዘዘ ለሁሉ ነው ሲል ነው፡፡

አንድም ማርና ወተት ቢታጠብበት ያቆሽሻል እንጂ አያነጣም ውሃ ግን እድፍን ያስለቅቃል እናንተም በማየ ገቦ ብትጠመቁ ከኃጢአት ትጠራላችሁ ሲል ነው፡፡
አንድም ማርና ወተት ቢታጠብበት ያቆሽሻል እንጂ አያነጣም ውሃ ግን እድፍን ያስለቅቃል እናንተም በማየ ገቦ ብትጠመቁ ከኃጢአት ትጠራላችሁ ሲል ነው፡፡
አንድም ማርና ወተት ተክል ላይ ቢያፈሱት ያደርቃሉ እንጂ አያለመልሙም ውሃ ግን ያለመልማል እናንተም በውሃ ብትጠመቁ ልምላሜ ሥጋ ወነፍስ ታገኛላችሁ ሲል ነው፡፡ (ዮሐ 19÷35)
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
​​ኑፋቄ ምንድን ነው?

ኑፋቄ ማለት እግዚአብሔር የገለጠውን ሃይማኖት እንደ ምእመናን ሙሉ በሙሉ ሳይቀበሉ፣ እንደ ኢአማንያንም ሙሉ በሙሉ ሳይክዱ የተወሰነውን ተቀብሎ ሌላውን ደግሞ አለመቀበል ወይም መጠራጠር ነው፡፡ እንዲህ የሚያደርጉት ሰዎች ደግሞ መናፍቃን (ተጠራጣሪዎች) ይባላሉ፡፡ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ መናፍቃንን እንዲህ ገልጸዋቸዋል፡-

የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ሳይሆኑ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች መስለው ወይም ከቤተ ክርስቲያን እምነትና ትምህርት ግማሹን ይዘው ግማሹን ያልያዙ ጎደሎዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች እንክርዳድ ስንዴ መስሎ እንዲያድግ በክርስቶስ ዐጸደ ወይን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የበቀሉ አሳሳቾች ናቸው, ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጠላቶች ናቸው'' (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ፣ ገጽ 30)

መናፍቃን የሚባሉት እግዚአብሔር እንድንበት ዘንድ የሰጠውን መንገድ (የክርስትናን ሃይማኖት ተቀብለናል፣ እናምናለን ካሉ በኋላ ያን ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠውን የመዳን መንገድ ለእነርሱ የመሰላቸውን ያህል ቆንጽለውና ክፍለው እንጂ እንዳለ ሙሉ በሙሉ የማይቀበሉ ናቸው፡፡ ኢአማንያን የሚባሉት ከመጀመሪያውም የክርስትና ሃይማኖትን ያልቀተበሉ ሲሆኑ መናፍቃን የሚባሉት ግን ክርስቲያኖች ነን እያሉ ነገር ግን ከክርስትና አስተምህሮ ውስጥ ለራሳቸው አስተሳሰብና ምኞት የሚመቻውን ብቻ ተቀብለው ሌላውን የማይቀበሉና የሚጠራጠሩ፣ በእውነተኛው ትምህርት ፋንታም የራሳቸውን የፈጠራ ትምህርት የሚያስተምሩ ናቸው፡፡

እንደዚህ ያሉት ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ አገላለጾች ተገልጸዋል፡፡ ለምሳሌም "በመልካሙ እርሻ ጠላት የዘራው እንክርዳድ” (ማቴ. 13፡25-26): “የክፉው ልጆች" (ማቴ. 13፡39)፡ “ሐሰተኞች ወንድሞች": ክፉዎች ሠራተኞች", "ውሾች" (ፊል. 3፡2)፣ “መናፍቃን' (2 ጴጥ. 2፡1 ፣ የሐዋ. 24: 5) በሚል መጠሪያ ተጠርተዋል፡፡ ይህም ስድብ ሳይሆን የግብራቸው መገለጫ ነው፡፡

ለምሳሌ የሚሰርቅ ሰው "ሌባ" መባሉ የግብሩ መገለጫ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ሰው የአንድን ነገር ግብሩን ወድዶ ስሙን ብቻ ቢጠላ ትርጉም አይኖረውም፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም በሃይማኖት ላይ የሚጨምር 'ደፋር: የሚቀንስ ደግሞ 'ሌባ' ነው" ሲል ይገልጻል፡፡

ቅዱስ መጽሐፍ የኑፋቄን ከባድ ኃጢአትነትና አጥፊነት አበክሮ ይገልጻል፡፡ “ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ፣ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፣ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ"፡፡ 2 ጴጥ. 2፡1 ኑፋቄ የእግዚአብሔርን መንግሥት የማያስወርስ ነው፤ “መለያየት፡ መናፍቅነት፡… እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።" ገላ. 5:21

ክርስቲያኖች መስለው የክርስቶስን ስም እየጠሩ፣ ነገር ግን የስህተት ትምህርት የሚያስተምሩ መናፍቃን እንደሚነሡ ጌታችን አስቀድሞ እንዲህ ሲል አስጠንቅቆናል- “በዚያን ጊዜ ማንም እነሆ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፣ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ። እነሆ አስቀድሜ ነገርኋችሁ። እንግዲህ እነሆ በበረሀ ነው ቢሏችሁ አትውጡ፤ እነሆ በእልፍኝ ነው ቢሏችሁ አትመኑ ማቴ 24፡23-26 ጌታችን ካስተማረውና ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከጌታ ከተቀበለችው የድኅነት አስተምህሮ የተለየ ትምህርት የሚያስተምር መናፍቅ የተረገመ መሆኑንና ልንቀበለውም የማይገባ መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።

አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፤ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን” ሲል በጽኑ አስጠንቅቋል፡፡ ገላ. 1:8-9እንዲህ ካለ መናፍቅ መለየት እንደሚገባም “ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ፡ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት'' ሲል ቅዱስ መጽሐፍ ያስጠነቅቀናል፡፡ 2 ዮሐ. 10

ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊም እንዲህ ብሏል፡-

ከመጀመሪያው ጀምሮ ከባለቤቱ ከጌታችን የተሰጣት የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ትውፊት፡ ትምህርትና እምነት በሐዋርያት የተሰበከ እና በአባቶች የተጠበቀ ነው። ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በዚህ ላይ ነው፤ ከዚህ የሚያፈነግጥ ማንም ቢሆን ክርስቲያን አይደለም፣ ክርስቲያን ተብሎ ሊጠራም አይገባውም፡፡ (ለጳጳስ ሴራፒዮን ዘትሙይስ የተላኩ አራት መልእክታት-21)

ኑፋቄ ታላቅ ኃጢአት ነው፡፡ ኃጢአት ብቻም ሳይሆን በሰውነት ድክመት በምግባር ፍኖት ከሚፈጸሙ ኃጢአቶች ሁሉ በላይ የመጨረሻ ከባድ ኃጢአት ነው፡፡ ምክንያቱም በሃይማኖት ውስጥ ያለ ሰው የሚሠራው ኃጢአት ንስሐ ከገባ ሥርየትንና ምሕረትን ሊያገኝ ይችላል፣ ኑፋቄ ግን ሥርየትና ምሕረት በሚገኝበት በራሱ በሃይማኖት ላይ የሚፈጸም ኃጢአት በመሆኑ ነው፡፡

ለምሳሌ አንድ ሰው ቢታመም በመድኃኒት አማካይነት ሊፈወስ ይችል ይሆናል፡፡ ሆኖም ያ በሽተኛ በመድኃኒቱ ላይ የሚያምጽና የሚቀልድ ከሆነ ግን የመዳን ተስፋ እንኳ የለውም፣ ምክንያቱም በመድኃኒቱ ላይ አምጿልና፡፡ ለሰው ልጅ የተሰጠው ታላቁ ሀብትና ጸጋ እምነት ነው፡፡ ኑፋቄ ደግሞ ይህን ታላቅ ጸጋ የሚያሳጣ ስለሆነ እጅግ ከባዱ ኃጢአት እርሱ ነው፡፡

ሰዎች ወደ ኑፋቄ የሚገቡባቸው ከተለያዩ ምክንያቶች መካከል እውነተኛውን የክርስትና ትምህርት አለማወቅና በተሳሳቱ ሰዎች ትምህርት መለከፍ፣ በራስ አስተሳሰብና ስሜት ብቻ መመራት፣ እኔ አውቃለሁ ማለት፡ ከትዕቢት የተነሣ ስህተትን ሲነገሩ አለመቀበልና በራስ መንገድ ብቻ መጓዝ፣ አንድ ጥቅስ ወይም በጣም ጥቂት ጥቅሶች ላይ ብቻ መንጠልጠል፣ እምነትን ለቁሳዊ ጥቅም ማግኛ መንገድ ማድረግ፣ በዘመኑ ያሉ ኃይላትን ለማስደሰትና ሹመትና ሥልጣንን ለማግኘት ማሰብ ይገኙባቸዋል፡፡

ቅዱሳን አባቶቻችን የኑፋቄ መሥራቾችና ተከታዮች የሆኑ መናፍቃንን ከሁሉም ይልቅ ክፉዎች መሆናቸውን ይናገሩ ነበር፡፡ ለአብነትም ቅዱስ ፖሊካርፐስ መርቅያን የተባለውን መናፍቅ የዲያብሎስ የበኩር ልጅ ይለው ነበር፡፡ ቅዱስ አግናጥዮስ ደግሞ መናፍቃን መርዝን የተመሉ ናቸው ይላቸው ነበር፣ እንዲሁም በሰው መልክ ያሉ አራዊት ናቸው ይላቸው ነበር፡፡ ሰማዕቱ ቅዱስ ዮስጢኖስ ደግሞ መናፍቃንን ዲያብሎስ ያነቃውን ስህተት የሚከተሉ ይላቸው ነበር፡፡ አባ ሄሮኒመስ ደግሞ መናፍቃንን የሰይጣን ምኩራቦች ይላቸው ነበር፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
​​ሽማግሌው አባታችሁ ደህና ነው? +

ዮሴፍ በግፍ የሸጡት ወንድሞቹን ለሁለተኛ ጊዜ ሲያገኛቸው እንዲህ ሲል ጠየቃቸው ‘የነገራችሁኝ ሽማግሌው አባታችሁ ደህና ነው? ገና በሕይወት አለን?’ እነርሱ መለሱ ፦ አባታችን ደህና ነው ገና በሕይወት አለ አሉት፡፡ (ዘፍ 43:27)

ዮሴፍ የጠየቀው የአረጋዊውን አባቱን የያዕቆብን ደህንነት ነበር፡፡ እነርሀሱ ወንድማቸው መሆኑን ገና ስላላወቁ ‘አባቴ ደህና ነው?’ በማለት ፈንታ  ‘ሽማግሌው አባታችሁ’ አለው፡፡ እርግጥም ያዕቆብ መቶ ሠላሳ ዓመቱ ነበር፡፡ ዮሴፍ እንደፈራው አልሞተም፡፡ ገና በሕይወት ነበረ፡፡

ይህንን ዮሴፍ ለወንድሞቹ የጠየቀውን ጥያቄ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ጻድቁን አቡነ አረጋዊን ለመጠየቅ በሔደ ጊዜ ዳግም ተናግሮታል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ወደ ደብረ ሃሌሉያ ዳሞ ተራራ በደረሰ ጊዜ ከተራራው ግርጌ ዮሴፍና ማትያስ የተባሉ ሁለት የአቡነ አረጋዊ ደቀ መዛሙርትን አገኘ፡፡

‘ዳኅንኑ ዝስኩ አረጋዊ አቡክሙ’ ሽማግሌው አባታችሁ ደህና ነውን ብሎም ጠየቃቸው፡፡ ይህ ንግግሩ መልስ አግኝቶ ሳያበቃ ምስጋና ሆኖ በአቡነ አረጋዊ ማሕሌት ይዜማል፡፡ ሽማግሌው አባታችሁ አረጋዊ አቡክሙ የተባለለት ጻድቁ አቡነ ዘሚካኤል አረጋዊ ተብሎ ለመጠራት እንደ ያዕቆብ 130 ዓመታት መቆየት አላስፈለገውም፡፡ ገና በዐሥራ አራት ዓመቱ መንኖ ለብዙዎች መመነን ምክንያት የሆነ በዕድሜው ሳይሆን በቅድስናው አረጋዊ ለመባል የደረሰ ጻድቅ ነበር፡፡

ዛሬም ላይ ሆነን የዮሴፍንና የቅዱስ ያሬድን ጥያቄ ደግመን እንመልስ፡፡  ‘’ሽማግሌው አባታችሁ ደህና ነው? ገና በሕይወት አለን?’’ ለሚለን ሁሉ መልሳችን ‘አረጋዊው አባታችን አቡነ አረጋዊ ደህና ነው፡፡ አሁንም ድረስ በሕይወት አለ ፤ እግዚአብሔር ሰወረው እንጂ አልሞተም፡፡ የሚል ነው፡፡

ጻድቁ አባታችን አረጋዊ ሆይ ዮሴፍ ስለ አባቱ ደህንነት እንደጠየቀ እኛ ስለ አንተ ደህንነት አንጠይቅም፡፡ እግዚአብሔር ያከበረህ ሆይ ባይሆን እኛ ልጆችህ ግን ደህና አይደለንም፡፡ ነፍሳችን ዛሬ በፊትህ የከበረች ትሁንና ልጆችህን በምልጃህ አስበን፡፡ ዮሴፍ ሽማግሌ አባቱን በፈርኦን ፊት እንዳቀረበ እኛም አረጋዊ አባታችንን በእግዚአብሔር ፊት ትማለድልን ዘንድ በጸሎታችን እናቀርብሃለን፡፡

ከዳሞ ተራራ ላይ ሆነህ ከችግር መውጫ ቸግሮአት ሰማይ ሰማዩን ለምታይ ሀገራችን የምልጃህን ገመድ ወርውርላት፡፡ ሊተናኮሏት የተጠመጠሙባትን ዘንዶዎችም ወደ መልካም ዘመን መወጣጫ መሰላሎችዋ አድርግላት፡፡ ካለችበት ውድቀት ወደ ከፍታ መወጣጫ ወደ መልካም መሸጋገሪያ ገመድ ትፈልጋለችና የጸሎት ገመድህን ላክላት። ያን ጊዜ እንዲህ ትላለች ፦
ገመድ ባማረ ስፍራ ወደቀችልኝ ርስቴም ተዋበችልኝ’ መዝ 16፡6

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
“አንኳኩቼ አላገኘሁም” አትበል፡፡ ብቻ የለመንከው፣ ደጅ የጠናኸው አንተ የምትወደው ሳይሆን እግዚአብሔር የሚወድልህ ይሁን፡፡ ወደ እግዚአብሔር የተዘረጋ እጅ ፈጽሞ ባዶውን አይመለስም፡፡ ስለዚህ ራስህን፣ ልመናህን ምን ዓይነት እንደሆነ ፈትሽ እንጂ አንኳኩቼ አላገኘሁም አትበል፡፡ እንኳንስ ንጹሐ ባሕርይ የሆነው እግዚአብሔር ክፋት የሚስማማው ምድራዊ አባትም ለልጁ ጀሮውን አይደፍንም፡፡

አስቀድሞ ሕያዊት ነፍስን “እፍ” ብሎ እንዲሁ የሰጠን ጌታ፣ ኋላም ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አንድ ልጁን ሳይራራ ከሰጠን እንደምን በዚህ ይታማል? እንደምንስ አይሰጠንም እንላለን? /ሮሜ.8፥32/፡፡ ልጁን የሰጠው እኮ ጭራሽ “ስጠን” ብለው ላልለመኑ አሕዛብም ጭምር ነው፡፡ ታድያ እንዲህ የምንለምን እኛማ እንዴት አብልጦ አይሰጠንም? የሚበልጠውን ሰጥቶን ሳለስ እንደምን ትንሹን አይሰጠንም እንላለን? ስለዚህ ከእኛ የሚጠበቀውን ሳናደርግ “እግዚአብሔር ጸሎቴን አይሰማም” የሚል የሰነፎች አባባል የምንናገር አንሁን፡፡ ጀሮን የፈጠረ ይሰማል!”
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
#እግዚአብሔርን_መፍራት

ከፍርሃታችን የሚመጡትን ጥቅሞች ታያላችሁ? ፍርሃት ባይጠቅም ኖሮ አባቶች ለልጆቻቸው ሞግዚቶችን አይቀጥሩም፤ ሕግ አውጪዎችም በከተሞች ላይ ዳኞችን አይሾሙም ነበር። ከገሃነም የበለጠ የሚያስፈራስ ምን አለ? እናም ገሃነምን ከመፍራት የበለጠ የሚጠቅም ነገር የለም:: ገሃነምን መፍራት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ይመራናልና፡፡ ይህ ፍርሃት ባለበት ምቀኝነት ቦታ የለውም፤ ይህ ፍርሃት ባለበት የገንዘብ ፍቅር ቦታ የለውም፤ ቁጣ ይጠፋል፣ ክፉ ምኞቶች ይወገዳሉ፡፡

አንድ ዘብ ሁልጊዜ ነቅቶ በሚጠብቅበት ቤት ውስጥ ሌባ፣ ዘራፊ ወይም ክፉ አድራጊ ሊመጣ እንደማይችል ኹሉ ፍርሃት አዕምሯችንን ሲይዝ፣ ልቅ ምኞቶች በቀላሉ አያጠቁንም፡፡ ይልቁንም ሸሽተው በየአቅጣጫው፣ በፍርሀት ምክንያት ይባረራሉ፡፡

ነገር ግን ፍርሃት ማባረር ብቻ አይደለም ጥቅሙ፤ ክፉ ፍላጎቶቻችንን ማስወገድ ብቻ ሳይሆን፣ እያንዳንዱን በጎነት ወደ ነፍሳችን ለማምጣትም ይጠቅማል፡፡ ፍርሃት ባለበት ለጋስ መሆን አለ፤ የጸሎት ብርታት፣ ትኩስ የሚደጋገም እንባ እና ለንስሃ የነቃች ነፍስ አለች። ኃጢአትን የሚሸፍን በጎነትን የሚያብበው በማያቋርጥ የፍርሃት ሁኔታ ውስጥ ስንሆን ነው:: ስለዚህ በፍርሃት የማይኖር ሰው ልቡ ደንድኖ የሰይጣን ባርያ እንደሚሆን ኹሉ፣ በፍርሃት የሚኖር ሰው በማያውቀው ጎዳና እንደማይጓዝ ኹሉ፣ እግዚአብሔርን መፍራት በትክክለኛው የጥበብ መንገድ ይወስደናል፡፡
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
​​​​✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን፡፡ ✞

ቅዱስ ጊዮርጊስ ልዳዊ

መጽሐፈ ገድሉ እንደሚለው የሰማዕታት አለቃቸው: አንድም ሞገሳቸው ታላቅና ክቡር ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ7 ዓመታት ስቃይ በኋላ ተሰይፏል:: ይህስ ጥንተ ነገሩ እንደምን ነው ቢሉ:-

ቅዱሱ የተወለደው ከአባቱ ዘረንቶስ (አንስጣስዮስ) እና ከእናቱ ቴዎብስታ የድሮው ፋርስ ግዛት ፍልስጥኤም (ልዳ) ውስጥ ነው:: የተባረኩ ወላጆቹ ክርስትናን ጠንቅቀው አስተምረውት አባቱ ይሞታል::

ቅዱስ ጊዮርጊስ 20 ዓመት ሲሞላው የአባቱን ስልጣን እጅ ለማድረግ ሲሔድ የቢሩት (የአሁኗ ቤይሩት-ሊባኖስ) ሰዎች ዘንዶ/ደራጎን ሲያመልኩ አገኛቸው:: እርሱ ግን የከተማውን ሕዝብ አስተምሮ: አሳምኖ: ደራጎኑንም በፈጣሪው ኃይል ገድሎ መንገዱን ቀጥሏል::

ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ዱድያኖስና 70 ነገሥታት ዘንድ ሲደርስ ክርስቶስ ተክዶ ለጣዖት ይሠገድ ነበር:: በዚያች ሰዓት ድንግል እመቤታችን ወደ ሰማዕቱ መጥታ መከራውንና ክብሩን ነገረችው:: እርሱም በክርስቶስ ስም መሞት ምርጫው ነበርና ከእመቤታችን ተባርኮ ወደ ምስክርነት አደባባይ (ዐውደ ስምዕ) ደረሰ::

ከዚያም ለተከታታይ 7 ዓመታት ብዙ ጸዋትወ መከራዎችን ተቀበለ:: 3 ጊዜ ሙቶ ተነሳ:: ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ትዕግስት በላይ የሆነ ስቃይን ስለ ቀናች ሃይማኖት ሲል በመቀበሉ የሰማዕታት አለቃቸው: ፀሐይና የንጋት ኮከብ በሚል ይጠራል:: "ተውላጠ ጻማሁ ወሕማሙ: ዘተለዐለ ሞገሰ ስሙ" እንዲል መጽሐፍ::

ከ7 ዓመታት መከራ በኋላም ከብዙ ተዓምራት ጋር ተሰይፎ ደም: ውሃና ወተት ከአንገቱ ፈሷል:: 7 አክሊላትም ወርደውለታል::

"ዝርወተ ዓጽሙ"

ይህቺ ዕለት ለሰማዕቱ 'ዝርወተ አጽሙ' ትባላለች:: በቁሙ 'አጥንቱ የተበተነበት' እንደ ማለት ነው:: ቅዱስ ጊዮርጊስን ለዘመናት በብዙ ስቃያት ሲያስጨንቁት ኖረው በጽናቱ አሸነፋቸው:: 70 ነገሥታትን ከነ ሠራዊታቸው ከማሳፈሩ ባሻገርም በርካታ (በመቶ ሺ የሚቆጠሩ) አሕዛብን ማርኮ ለሰማዕትነት አበቃ::

በዚህ የተበሳጨ ዱድያኖስም ኮከበ ፋርስ ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲቆራርጡት አዘዘ:: ወታደሮቹም ቅዱሱን ቆራርጠው በብረት ምጣድ ላይ ጠበሱት:: ያለ ርሕራሔም አካሉን አሳረሩት:: ቀጥለውም ፈጭተው አመድ አደረጉት::

በአካባቢው ወደ ነበረው ትልቅ ተራራ ጫፍ (ደብረ ይድራስ) ወጥተውም በነፋስ በተኑት:: "ሐረድዎ ወገመድዎ: ወዘረዉ ሥጋሁ ከመ ዓመድ" እንዲል:: (ምቅናይ)

እነርሱ ይህንን ፈጽመው ዘወር ሲሉ ግን የቅዱሱ ዓጽም ባረፈባቸው ዛፎች: ቅጠሎችና ድንጋዮች ሁሉ "ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት" የሚል ጽሑፍ ተገኘ:: ስለዚህም ይህቺ ዕለት ቅዱሱ አለቅነትን የተሾመባት ናት ማለት ነው::

ወዲያው ግን ኃያል ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተበተነበት ተነስቶ ወታደሮችን አገኛቸውና "በክርስቶስ እመኑ" ብሎ: አስደንቆ ወደ ሕይወት መራቸው:: 70ው ነገሥታት ግን አፈሩ::

ዝክረ ቅዱሳን
ወስብሐት ለእግዚአብሄር
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
መልካም መልዕክት፦

አባት ልጁ ከቤት ወጥቶ መኪና እንዳይገጭበት፣ ወድቆ እንዳይሰበርበት፣ ድንገት በአከባቢው የሚያልፉ ከብቶች ገፍተው እንዳይጥሉበት መውጫው በሩን ይዘጋበታል፡፡ ይኼኔ ልጁ በሩ ለምን እንደተዘጋበት አያውቅም፤ ልጅ ነውና፡፡ አባቱ የጠላው መስሎትም ምርር ብሎ ሊያለቅስ ይችላል፡፡ ማልቀስ ብቻ አይደለም፤ ቂምም ሊይዝበት ይችላል፡፡ አባቱ ግን በሩን የዘጋበት ምክንያት ያውቃል፤ ጠልቶት ሳይሆን ይጐዳበታልና ልጁ ቢያለቅስም አይከፍትለትም፡፡

እውነተኛው አባታችን እግዚአብሔርም አንዳንድ ጊዜ የማይጠቅሙን ይልቁንም ክፉኛ ሊጎዱን የሚችሉ በሮችን ይዘጋብናል፡፡ ከእውቀት ከፍለን የምናውቅ ልጆቹ ነንና አባታችን ለምን እንደዘጋብን ለጊዜው አይታወቀንም፤ ብቻ የከለከለን ይመስለናል፡፡ በመሆኑም ቂም ልንይዝበት ልናማርረውም እንችላለን፡፡ እርሱ ግን ይታገሠናል፤ ለእኛ የሚያስባት መልካሚቱን በር እርሱ ያውቃታልና ይከፍትልናል፤ በእኛ እይታ መልካም የምትመስለንን ነገር ግን ክፉይቱን በር ይዘጋብናል፡፡

ቅዱስ አባት ሆይ ስለ ከፈትክልን ብቻ ሳይሆን ስለ ዘጋህብንም በር እናመሰግንሃለን፡፡ አሜን!
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
​​የቀራንዮ በግ

ከዓመት እስከ ዓመት ግርግር በማያጣትና ሁሌም በሰውና በገበያተኛ በተጨናነቀችው ኢየሩሳሌም ውስጥ እየተጓዝን ነው:: ጥንታዊትዋ የኢየሩሳሌም ከተማ በአሁኑ ሰዓት በአራት ሩቦች ተካፍላ ትተዳደራለች:: የክርስቲያን እርቦ ፣ የሙስሊሞች እርቦ ፣ የአርመኖች እርቦ እና የአይሁድ እርቦ ይባላሉ::

ለሦስቱ አብርሃማውያን እምነቶች (Abrahamic religions) ለአይሁዳዊነት ለክርስትናና ለእስልምና ትልቅ ፋይዳ ባላት ኢየሩሳሌም "አርብ አርብ" ብቻ ሳይሆን ሁሌም ሽብርና ግርግር አለ::  በሁሉም ሩቦች ተሳላሚዎች ፣ ጎብኚዎች ፣ ሻጮች ፣ ገዢዎሽ እስከ እኩለ ሌሊት ይርመሰመሳሉ:: 

ዘንድሮ እግር ጥሎኝ ከአንድ ወዳጄ ጋር በአይሁድ እርቦ (Jewish quarter) በኩል ሳልፍ አንድ ልብ የሚነካ ሥዕል ዓይኔ ውስጥ ገባ:: ሥዕሉን ሳይ ዕንባ በዓይኔ ሞላ:: የኢሳይያስ 53ቱን የሕማም ሰው ፣ የማይናገረውን በግ በአንገቱ የእሾህ አክሊል ጌጥ አድርገውለት እንዲህ ሆኖ ሳየው ችዬ የማላነበውን ኢሳይያስ 53 በሥዕል ሲያመጣብኝ ከማልቀስ ውጪ ምንም አቅም አልነበረኝም::

ነቢዩ ኢሳይያስ ሳይናገር በፊት የሚቀበለው እንደሌለ አውቆ "የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል?" ብሎ የተጨነቀበትን ይህን አስጨናቂ ራእይ እንዴት እንረሳዋለን? ከኢትዮጵያዊው ጃንደረባስ በቀር ኢሳይያስ 53 ን አንብቦ "ማን አምኖአል?" (ሐዋ. 8:26) የእግዚአብሔር ክንዱ የተባለ ክርስቶስስ ለማን ተገልጦአል?

በግርፋቱ ብዛት ፊቱ በደም ተለውሶ "ባየነው ጊዜ እንወደው ዘንድ ደም ግባት የለውም" የተባለበትን ውበቱ ስለ እኛ የጠፋው የሕማም ሰው እንዴት ከሕሊናችን ተሰወረ?

"እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።ተጨነቀ ተሠቃየም በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም" የሚለው ቃል ምንኛ ያስጨንቃል? ቆስሎ የሚፈውስ ታምሞ የሚያድን ታስሮ ነፃ የሚያወጣውን የእግዚአብሔር በግ ለመግለፅ ቃላት አቅም ቢያጥራቸው እንዲህ በብሩሽ ኃይል ተሥለው ሳያቸው ሁሉን ነገር ዘነጋሁት::

አንድ ልብሱ በቀለም ያደፈ ሰው በሥዕል ጋለሪው ደጃፍ ቁጭ ብሎ ይፈርማል:: እንደ መታደል ሆኖ ሰውዬው የሥዕሉ ባለቤት UDI MERIOZ ነበረ:: ቀርቤ ስለ ሥዕሉ የተሰማኝን ስነግረው እሱም ስሜቱ ተነካ:: "ይሄንን ሥዕል እኔ ብሥለውም የእኔ ፈጠራ አይደለም:: ሸራውን ወጥሬ በቀለም ላይ የሠራሁት እኔ ነኝ:: ነገር ግን ከመሣሌ በፊት በተደጋጋሚ በሕልሜ አየው ነበር:: የሣልሁትም ያየሁትን ነው" አለኝ:: ሥዕሉንም ፈርሞ ለእኔና ለወዳጄ ሠጠን::

ቅዱስ ኤፍሬም "ጌታ ሆይ ረዥሙን ሥቃይህን ማን ሊገልጸው ይችላል?" እንዳለው የጌታን መከራ የሚገልፅ አንደበት የሚሥለው ብሩሽ ባይኖርም ለአፍታ ግን እንዲህ በየሰዉ ላይ ባሳረፈው ጸጋ ሕማሙን ያስታውሰናል::

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
​​ጥር ፳፩ የእመቤታችን በዓለ ዕረፍት (አስተርእዮ ማርያም)

”አስተርእዮ ማርያም“

አስተርእዮ ማለት መታየት፣ መገለጥ ማለት ነው። ቃሉ አስተርአየ ታየ፣ ተገለጠ ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ነው። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት በሥጋ የተገለጠበት(የታየበት) ፣ አንድነት ሦስትነቱም የተገለጠበት ወቅት በመሆኑ ከልደት በዓል እስከ ጥር መጨረሻ በሙሉ ዘመነ አስተርእዮ በመባል ይታወቃል። የእመቤታችን በዓለ ዕረፍት በዘመነ አስተርእዮ ውስጥ ስለሚከበር “አስተርእዮ ማርያም” ተብሏል።

ልቡናዋ በይኩነኒ የጸና ንጽሐ ሥጋ ፣ ንጽሐ ነፍስ፣ ንጽሐ ልቡና አስተባብራ የያዘች ወላዲተ አምላክ ምንም እንኳን የአምላክ እናት ብትሆንም ሞተ ሥጋ ለሁሉም ዕጣ ፈንታ በመሆኑ በቃል መነገሩ በልብ መታሰቡ ከፍ ከፍ ይበልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ተንሥኢ ወንዒ”  የነፍሴ ደስታ የኾንሽ ውድ እናቴ ሆይ ተነሥተሽ ወደ እኔ ነዪ (መኃ ፪፥፲) ብሏታል።

ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኲሉ

ቅዱስ ዳዊት “ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር “ መዝ.፹፮፥፫ እግዚአብሔር ማህጸንሽን ከተማ አድርጎ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን የኖረብሽ ሆይ ስለ አንቺ የተነገረው የተደረገው ነገር ዕጹብ ድንቅ ነው እንዳለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት ሆና ማረፏ ይደንቃል። ታላቁ የቤተክርስቲያናችን አባት ቅዱስ ያሬድ ሞቷ የሚያስደንቅ መሆኑን «ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኲሉ፤ ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል» በማለት ገልጾታል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
"...ክርስቲያኖች ግን ክርስቲያኖች ለመኾናቸው መታወቅ የሚገባቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው ምሥጢራትን ሲቀበሉ ብቻ ሳይኾን የትም ቦታ በሚኖሩት የቅድስና ሕይወት ነው፡፡ በአፍአ የከበሩ ሰዎች በአፍአ ከሚያሳዩት ምልክት እንደሚታወቁ ኹሉ፥ እኛም ልንታወቅ የሚገባን በነፍሳችን ክብር ነው፡፡ በሌላ አገላለጥ አንድ ክርስቲያን መታወቅ ያለበት በተሰጠው ልጅነት ብቻ ሳይኾን ለልጅነቱ እንደሚገባ በሚያሳየው አዲስ ሕይወትም ጭምር ሊኾን ይገባል፡፡ ይህ ክርስቲያን ለዓለም ብርሃንና ጨው ሊኾን ይገባዋል፡፡ ለዓለም ብርሃን መኾንህስ ይቅርና ለራስህ እንኳን ብርሃን መኾን ካልተቻለህ፣ የሚሰፋ ቁስልህን በዘይት ማሰርም ካቃተህ፥ ክርስቲያን መኾንህን የምናውቀው እንዴት ነው? ወደ ተቀደሰው ውኃ ገብተህ በመጠመቅህ ነውን? በዚህስ አይደለም ! ይህስ እንዲያውም ዕዳ ፍዳ ይኾንብሃል [እንጂ ክርስቲያን መኾንህን እንድናውቅህ አያደርገንም]፡፡ ይህ ሀብት (ልጅነት) ታላቅ ነውና ለዚህ ሀብት እንደሚገባ ለማይኖሩት ሰዎች ዕዳ ፍዳ መጨመሪያ ነው፡፡ አዎን፥ ክርስቲያን ለዓለም ብርሃኑን ማብራት ያለበት ከእግዚአብሔር በተቀበለው ጸጋ ብቻ ሳይኾን እርሱ ራሱም ድርሻውን በመወጣት ነውና፡፡ ክርስቲያን ካልኾኑት ይልቅ በኹለንተናው በአረማመዱ፣ በአተያዩ፣ በአለባበሱ፣ በአነጋገሩ ብልጫ ሲኖረው ነውና፡፡ ይህንም የምለው ልጅነትን የተቀበሉ ክርስቲያኖች ልጅነትን ተቀበሉ በመባል ብቻ ሳይኾን የሌሎች ሰዎች ረብ ጥቅም ይኾን ዘንድ ለተቀበሉት ልጅነት የሚገባና ሥርዓት ያለው ሕይወት እንዲኖሩ ስለምሻ ነው፡፡

አሁን ግን ከሌሎች ከማያምኑት ብልጫ ኖሮህ እንዳየው በምፈልገው ሕይወት፥ በኹሉም ረገድ ተቃራኒ ኾነህ አይሃለሁ፡፡ ለምሳሌ ከቦታ አንጻር፥ ቀኑን ኹሉ የፈረስ እሽቅድምድምንና ተውኔትን፣ ነውርን የተሞሉ ትርኢቶችንና የክፉዎችን ማኅበር፣ ርኵሰትንም የተሞሉ ሰዎችን ስትመለከት እንደምትውል አይሃለሁ፡፡ ከፊትህ አንጻር፥ ዘወትር ያለ ልክና እንደ አመንዝራ ሴት ስትስቅ እመለከትሃለሁ፡፡ ከአለባበስህ አንጻር፥ ከተዋንያንና ጠቢባን ነን ከሚሉ ሰዎች ምንም እንደማትለይ አስተውልሃለሁ፡፡ ከሚከተሉህ ሰዎች አንጻር፥ ብዙ ውዳሴ ከንቱንና ሽንገላን እንደምትሻ አይሃለሁ፡፡ ከንግግርህ አንጻር፥ ምንም ደኅና ነገር፣ በቁዔት ያለው ቃል፣ ለሕይወታችን የሚረባ ንግግር እንደሌለብህ አደምጣለሁ፡፡ ከማዕድህ አንጻርም ከዚያ ጽኑዕ የኾነ ወቀሳ የሚያመጣብህ እንደ ኾነ አያለሁ፡፡

ታዲያ እስኪ ንገረኝ ! ክርስቲያንን ክርስቲያን ከሚያስብሉት ነገሮች እጅግ የራቅህ ኾነህ እያለ፥ ክርስቲያን መኾንህን መለየት የምችለው በምንድን ነው? ክርስቲያን መባልህስ ይቅርና፥ ሰው ብዬ ልጠራህ የምችለውስ እንዴት ነው? እንደ አህያ ትራገጣለህና፤ እንደ ኮርማ ትሴስናለህና፤ እንደ ፈረስ ከሴቶች ኋላ ኾነህ ታሽካካለህና፤ እንደ ድብ ሆዳም ነህና ፤ ሥጋህን እንደ በቅሎ ሥጋ ትሰገስጋለህና፤ እንደ ግመል ቂም ትይዛለህና፤ እንደ ተኵላ ትነጥቃለህና፤ እንደ እባብ ትቈጣለህና፤ እንደ ጊንጥ ትናደፋለህና፤ እንደ ቀበሮ ተንኰለኛ ነህና፤ እንደ እባብ ወይም እንደ እፉኝት በጕረሮህ መርዝ አለና፤ እንደ ክፉ ጋኔን ከወንድምህ ጋር ትጣላለህና፡፡ ታዲያ ክርስቲያን የሚለውስ ይቅርና፥ በምንህ ሰው ብዬ ልጥራህ? ሰው የሚያስብል ምልክት ሳይኖርህ እንዴት ብዬ ከሰው ዘንድ ልቊጠርህ? የንኡሰ ክርስቲያኖችና የክርስቲያኖች ልዩነት ባሰብሁ ጊዜ ልዩነቱ የሰውና የአርዌ ገዳም ያህል ይኾንብኛል፡፡ ታዲያ ምን ብዬ ልጥራህ? አርዌ ገዳም ብዬ ልጥራህን? እንዲህስ አልልህም፤ ጭካኔህ ከአራዊተ ገዳም በላይ ነውና፤ (በሌላ መልኩ ደግሞ እነርሱ እንደዚያ የኾኑት ከተፈጥሮአቸው የተነሣ እንጂ እንደ አንተ ወደውና ፈቅደው አይደለምና፡፡ )ታዲያ ምን ብዬ ልጥራህ? ጋኔን ልበልህን? እንዲህስ አልልህም፤ ጋኔን የሆድ ባሪያ አይደለምና፤ ፍቅረ ንዋይም የለበትምና፡፡ ታዲያ ከአራዊተ ገዳምም ከአጋንንትም የሚብስ ክፉ ግብር ከያዝህ፥ ንገረኝ - ሰው ብዬ እጠራህ ዘንድ ይገባኛልን? ሰው ለመባል እንኳን የሚበቃ ምግባር ከሌለህስ፥ ክርስቲያን ብለን ልንጠራህ የምንችለው እንዴት ነው?"
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
"እስኪ ከእኔ ጋር ሆናችሁ ቅዱስ ዳዊት ምን ያህል እግዚአብሔርን ከልቡ ይወደው እንደነበር እናስተውል። ቀን ቀን ያስባቸው ዘንድ ግድ የሚሉት የመሪዎች፣ የአዛዦች፣ የመንግሥታቱ፣ የሕዝቡ፣ የሠራዊቱና ስለ ጦርነት ውሎዎቹ፣ ስለ ሰላም፣ ስለ ፖለቲካውና በቤቱ ውስጥ ወይም ከቤቱ ውጪ ወይም በጎረቤቶቹ ዘንድ ስላለው ችግር ማውጣት ማውረዱ ልቡን ከፍለው ይወስዱበታል።

በዕረፍት ጊዜው እያንዳንዱ ሰው ለመኝታው የሚጠቀምበትን ሰዓት እርሱ ደግሞ ለንስሐ ለጸሎትና ዕንባውን ለማፍሰስ ይጠቀምበታል፡፡ እንዲህ ያለ ተግባሩን የሚፈጽመው ዛሬን አድርጎ ነገን ሳያደርግ አይደለም። ወይም ደግሞ ሁለት ወይም ሦስት ሌሊት በማለፍ አይደለም፤ በእያንዳንዷ ሌሊት እንጂ፡፡ «ሌሊቱን ሁሉ አልጋዬን አጥባለሁ፣ መኝታዬንም በዕንባዬ አርሳለሁ።» የሚለው ቃል የዕንባውን ብዛትና ዕንባው አለማቋረጡን ይገልጽልናል፡፡

እያንዳንዱ ፀጥ ባለ ዕረፍት ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ እርሱ ግን እግዚአብሔርን ብቻውን አግኝቶ ለዕንቅልፍ ባልተከደኑ ዓይኖቹ ያለቀስና ያዘነ የግል ኃጢአቶቹን ይነግረዋል፡፡ አንተም ብትሆን እንዲህ ዓይነቱን አልጋ ለራስህ ታበጅ ዘንድ ይገባሃል። በወርቅና ብር ተከበህ መተኛት ከሰዎች ቅናትን ከአርያም ደግሞ ቁጣን ይቀሰቅስብሃል፡፡ እንደ ዳዊት ያለ ዕንባ ግን የሲዖልን እሳት ያጠፋል፡፡

ሌላ አልጋ ደግሞ ላሳይህን? ይህ አልጋ የያዕቆብ ነው። ለስውነቱ ባዶ መሬትን ለትራሱ ደግሞ ድንጋይን የተጠቀመበት አልጋ! ይህ በመሆኑም ያን መንፈሳዊ ድንጋይና ያቺን መላእክት ሲወጡባትና ሲወርዱባት የነበረችውን መሰላል ሊመለከት ችሏል፡፡ (ዘፍ 28፣ ከ1ኛ ቆሮ 10፥4 ጋር አዛምድ፡፡) በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ድንጋዮች ለክርስቶስ ምሳሌ ሆነው ተጠቅሰዋል፡፡ እኛም እንዲህ ያሉ ሕልሞች እናይ ዘንድ ሕሊናችንን እንደዚህ ባሉት አልጋዎች ላይ እናሳርፍ፡፡ ነገር ግን ከብር በተሠሩ አልጋዎች ላይ ብንተኛ ደስታን ብቻ ሳይሆን የምናጣው ችግርንም እንጋፈጣለን፡፡

እጅግ በጣም ቀዝቃዛ በሆነ እኩለ ሌሊት አንተ በአልጋህ ውስጥ ተኝተህ ሳለህ ድሀው ሰው ግን በጭድ ክምር ላይ በደጅህ ወድቆ በብርድ እየተንቀጠቀጠና በረሀብ እየተገረፈ ተዘርግቷል:: አንተ ከስዎች ሁሉ ልበ ደንዳና ብትሆን እንኳ ለዚህ ለድሀ የሚገባውን ሳታደርግለት ለራስህ አላስፈላጊ ምቾቶችን መፍቀድህ እርግጠኛ ነኝ ራስህን እንድትረግም ያደርግሃል። «የሚዘምተው ሁሉ ለጦር ያስከተተውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ትዳር በሚገኝበት ንግድ ራሱን አያቆላልፍም።» (2ኛ ጢሞ. 2፥4) ተብሎ ተጽፏልና፡፡

አንተም መንፈሳዊ ወታደር ነህ፡፡ እንዲህ ያለ ወታደር ደግሞ በመሬት ላይ ይተኛል እንጂ ከዝሆን ጥርስ በተሠራ አልጋ ላይ አይተኛም፤ እጅግ ያማረ ሽቶም ኣይቀባም፡፡ እንዲህ ያለው ተግባር በመድረክ ላይ እየተወኑ በግድ የለሽነት ከሚኖሩና ከጋለሞታ ሴቶች ጋር ጊዜያቸውን በማባከን የሚኖሩ የምግባረ ብልሹ ሰዎች ተግባር ነው፡፡ የእኛ ጥሩ መዓዛ ግን ሽቱ ሳይሆን መልካም ሥራ ሊሆን ይገባል፡፡ በሽቱ መዓዛ ከሚመጣው ጠንቅ የበለጠ ነፍስን የሚያቆሽሽ ነገር አይኖርም፡፡ በአብዛኛው አፍአዊ (ውጪያዊ) መልካም መዓዛ የሰው ውስጣዊ ማንነት ማደፍና መቆሸሽ ምልክት ነው፡፡

ዲያብሎስ ነፍስን በራስ ወዳድነት ተዋግቶ ሲያሸንፋትና በታላቅ ከንቱነት ሲሞላት አስቀድሞ አቆሽሾት ወይም አጉድፎት ወይም አበልዞት የነበረውን ሰውነት በሽቶ ያጸዳዋል:: ልክ በጉንፋን እንደተያዙና ያለማቋረጥ በአፍንጫቸው የሚወጣውን ፈሳሽ ለማጽዳት ልብሳቸውን፣ እጆቻቸውንና ፊታቸውን እንደሚያጎድፉ ሁሉ እንዲህ ያለው የክፉ ስው ነፍስም ሰይጣን በሰውነቱ ላይ ያፈሰሰበትን ኃጢአት ለማጽዳት ይሞክራል፡፡ ሽቶ ሽቶ ከሚያውድ፣ ከጋለሞታ ጋር ወዳጅነት ከመሠረተ፣ የዳንኪረኛነት ሕይወትን ከሚመራ ሰው ማን ጨዋና መልካም ነገርን መጠበቅ ይችላል? እስቲ ነፍስህ መንፈሳዊ መዓዛን ትተንፍስና ለአንተም ሆነ ለወዳጆችህ ታላቅ በረከትን ታድላቸው፡፡"

ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
ተወዳጆች ሆይ! ሌላ ሰው አደረሰብኝ የምትሉት ጉዳት ምንድነው? ተቆጥቶ ሰደበኝ፤ ያለ ስሜም የሆነ ስም ሰጠኝ የሚል ነውን? ታዲያ ይኼ ምን ጉዳት አለው? በፍጹም ጉዳት የለውም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች ጉዳቶች ሳይሆኑ ትዕግሥተኞች ከሆናችሁ ጥቅማቸው የበዛ ነውና፡፡ ሲጀምር በእናንተ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚፈልገው ሰው የሚያደርገውን አያውቅም፡፡ የሚያደርገው ሁሉ ወዶና ፈቅዶ አይደለም፡፡ ምንም እንኳን እናንተን የጐዳ ቢመስለውም ራሱን እየጐዳ ነው፡፡ የብዙዎቻችን ችግር ጐጂውና ተጐጂው ማን መሆኑን ለይተን አለማወቃችን ነው፡፡ ምክንያቱም ይኼንን ለይተን ብናውቅ ኖሮ ራሳችንን ለመጉዳት ባልተነሣሳን ነበር፤ ሌሎች ክፉ ይደርስባቸው ዘንድ ባልጸለይን ነበር፤ ማንንም መጕዳት እንደማንችል በገባን ነበር፡፡ ትልቁ በደል ደግሞ ክፉን መቀበል ሳይሆን በሌሎች ላይ ክፉትን መፈጸም ነው፡፡

ስለዚህ ከዛሬ ጀምራችሁ ሌላ ሰውን በድላችሁ ከሆነ ራሳችሁን ውቀሱ፤ ሌላው ክፉ አድርጐባችሁ እንደሆነ ግን ለእናንተ ያደረገው ነገር መልካም ነውና ጸልዩለት፡፡ ምንም እንኳን ሰውዬው እናንተን ለመጥቀም ብሎ ያደረገው ባይሆንም በመታገሣችሁ ግን ትልቅ ጥቅምን ታገኛላችሁ፡፡ ክፉ አደረገብኝ የምትሉት ሰውዬ ድርጊቱ ክፉ እንደሆነ ሰዎችም የእግዚአብሔር ቃልም ይፈርዱበታል፤ እናንተ ግን እንዲህ ስትታገሡ ለጊዜው ምንም የተጐዳችሁ ቢመስላችሁም ጌታ እንደተናገረ ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነው።

ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
​​ጥንተ አብሶ የውርስ ኃጢያት

ጥንተ አብሶ ቃሉ የግእዝ ቃል ሲሆን የጥንት ወይም የበደል መጀመሪያ ማለት ሲሆን፤ ጥንተ አብሶ መባሉም የመጀመሪያዎቹ ሰዎች በአዳምና በሔዋን የተፈፀመ እነርሱ የሰሩት ኃጢያት ስለሆነ ነው፡፡ በዚህ በደላቸውም ልጅነታቸው ተገፎ ከጸጋቸው ተራቁተው ዕርቃናቸውን በመቅረት ከክብር ባዶ ሆነዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በሞተ ስጋ ላይ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ሲኦል ተፈርዶባቸው፤ የመርገመ ስጋ እና የመግረመ ነፍስ ቀንበር ወድቆባቸው ከእግዚአብሔር አንድነት ሲለዩ በነርሱ በደል ምክንያት ሰዎች ከእግዚአብሔር አንድነት ሲለዩ በኃጢያት በበደል ላይ በደል በመጨመር ለ5500 ዘመናት ያህል ሲኖሩ ይህ የወደቁበት ኃጢያት ጥንተ አብሶ (ምልእተ ኃጢያት) ይባላል፡፤ ሮሜ 5÷14

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥንተ አብሶ/የውርስኃጢያት አንደሌለባት

ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ የነገረ ድኅነት ትምህርት ተገልፆለት ያለፈውን ያለውን እና የሚመጣውን አገናዝቦ ሲናገር የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንን ገሞራንም በመሰልን ነበር ብሏል ኢሳ 1÷9 ይህም ለፍፃሜው በእመቤታችን የተነገረ ትንቢት ነው፡፡ ከዚህም በበለጠ ሁኔታ ትርጓሜ የሚያሻው ደረቅ ትንቢት ሲናገርም ስለዚህ ጌታ እራሱ ምልክት ይሰጣችኋል እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች (ብላ ትጠራዋለች)፡፡ ብሏል ኢሳ 7÷14 እነ ነቢዩ ኢሳይያስ በጥንተ አብሶ ምክንያት ሁላችን እንደ እርኩስ ሰው ሆነናል ጽድቃችን ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፡፡ ኢሳ 46 ቢልም እግዚአብሔርባወቀ ጥንተ አብሶ ፈጽሞ ባልደረሰባት በእመቤታችን ይመኩ ተስፋም ያደርጉ ነበርለዚህም ነው ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ ... ያሉት እመቤታችን ከጥንተ አብሶ ገና ከጠዋቱ ንጽሕት ሆና የተዘጋጀች ጥንተ መድኃኒት ናትና ነው፡፡

አንዳንድ ሰዎች እመቤታችን ንጽሕት ናት ከተባለውና ኃይለ አርያማዊት ነች ያሰኛታል በማለት ጭፍን ያለ የተሳሳተ ሐሳብ ሲሰጡ ይደመጣሉ ሆኖም ግን ኃይለ አርያማዊነት ኃጢያት ካለመስራት ጋር ምንም አያያይዘውም ለምሳሌ የሰው ልጆች መገኛ ንጽሐ ጠባይ ሳያድፍባቸው ምንም መርገም ሳይኖርባቸው በገነት በእግዚአብሔር ህግጋት ጠብቀው 7 ዓመት እንደኖሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይጽፋል ታዲያ አዳምና ሔዋን 7 ዓመት ንጽሐ ጠባይ ስላለደፈባቸው ኃይለ አርያማውያን ናቸው ልንላቸው ነውን አይደለም አንላቸውም ስለዚህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ኃጢያት እንደጉም በከበበው በዚህ ዓለም ሳለች ከኃጢያት ርቃ ንጽሐ ጠባይ ሳያድፍባት ምልእተ ጸጋ ሆና መገኘቷ በእጅጉ አስደናቂ ነውና ሊቃውንትም ይህንን ይዘው ”እግዝእትነ ትነጽሕ እመላእክት” እመቤታችን ማርያም ከመላእክት ይልቅ ንጽሕት ናት በማለት የንጽሕናዋን ነገር በስፋት አስተምረውበታል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
"ስለ ሰርግ ቀን" የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ምክር

ወጣቶች ትዳራቸው፥ ኦርቶዶክሳዊ ትዳር እንዲኾንላቸው ከፈለጉ ከኹሉም አስቀድመው ሊያደርጉት የሚገባቸው ልክ እንደ ቃና ዘገሊላው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰርጋቸው ዕለት እንዲገኝ ማድረግ ነው፡፡ ይኸውም ሰርጋቸውን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን ማከናወን ማለት ነው፡፡

ሊቁም ይህን አስመልከቶ ሲናገር እንደዚህ ይላል፡- “ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ በመገኘትና ጸጋውን በመስጠት ሰርግን ቀድሷል፡፡ ሌሎች ይረባል ይጠቅማል ብለው ካመጡት ስጦታ ይልቅ ከፍ ያለ ስጦታ ይዞ በመምጣት ይኸውም ውኃውን ወደ ወይን በመለወጥ ሰርግን አክብሯል፡፡ … ስለዚህ የዲያብሎስ ትርኢትን በማምጣት ጌታችን ያከበረውን ሰርግ አናቃልል፡፡ ወደ ትዳር የሚገቡ ሰዎችም በቃና ዘገሊላ በተደረገው መልኩ ያግቡ፡፡ በመካከላቸው ክርስቶስ እንዲገኝ ያድርጉ፡፡ ‘ይህንንስ እንዴት ሊያደርጉ ይችላሉ? ጌታችን ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ በአካል እንደ ተገኘ ዛሬም መገኘት ይችላልን?’ ብሎ የሚጠይቅ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ አዎ! ካህናትን ይጥሩ፡፡ ጌታችን ‘እናንተን የተቀበለ እኔን ይቀበላል’ በማለት ተናግሯልና (ማቴ 10፥40)፡፡

እንደዚህ በማድረግ ዲያብሎስን ያርቁት፦
  ➛ ጸያፍ ዘፈኖችን፣
  ➛ ርኵሳን ሙዚቃዎችን፣
  ➛ ሥርዐት የለሽ ውዝዋዜዎችን፣
  ➛ አሳፋሪ ንግግሮችን፣
  ➛ ዲያብሎሳዊ ትርኢቶችን፣
  ➛ ወሰን የለሽ ሁካታዎችንና ሳቆችን፣
እንደዚሁም እነዚህን የመሰሉ ሌሎች ነውርን የተሞሉ ድርጊቶችን ያርቁ፡፡ ከእነዚህ ይልቅ የክርስቶስ አገልጋዮችን ይጥሩ፡፡ ያን ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት ያለ ሐሰት ከእናቱና ከወንድሞቹ ጋር በሰርጋቸው ይገኛል፤ ይታደማልም፡፡”

ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
​​ቃል ኪዳን

እግዚአብሔር ለቅዱሳን ፍጹም የሆነ ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ “ከመረጥኋቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ” መዝ 88፤3 በማለት እንደተናገረ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ያደረጋቸው ቃልኪዳኖች ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህንም ቃል ኪዳናት እስከመጨረሻው ይጠብቅላቸዋል፡፡

“አቤቱ የሰማይ አምላክ ሆይ ለሚወዱህና ትዕዛዝህን ለሚያደርጉ ቃል ኪዳንህንና ምህረትህን የምትጠብቅ ታላቅና የተፈራህ አምላክ ሆይ” ነህ 1፤5 እንዲሁም በዘዳግም ላይ “አንተም አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደሆነ አምላክ እንደሆነ ለሚወዱትም ትእዛዙንም ለሚጠብቁ ቃልኪዳኑንና ምህረቱን እስከ ሺ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ የታመነ አምላክእንደሆነ እወቅ” ዘዳ 7፤9 በተጨማሪም በመጽሐፈ ነገስት ላይ ያለውን ተመልከት 1ነገ 8፤23 እነዚህ ጥቅሶች የሚያስረዱት ይህንን ነው፡፡

ለምሳሌ ከጥፋት ውሃ በኋላ እግዚአብሔር ኖህን “ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት” ዘፍ9፤1 አለው፡፡ ኖህ ግን “ብንበዛ ምን ዋጋ አለው ሰው ከማጥፋት ላያርፍ አንተም ከመቅጣት ላታርፍ ” ሲል መለሰ፡፡ በዚህ ጊዜ ነው እግዚአብሔር “እነሆ ቃል ኪዳኔን ከእናንተ በኋላ ከሚመጣው ዘራችሁ ጋር አቆማለሁ ከእናንት ጋርም ላሉትም ሕያው ነፍስ ላላቸው ሁሉ፡፡

ከእናንተ ከመርከብ ጋር ከመርከብ ለወጡት ለወፎች ለእንስሳትም ለምድር አራዊትም ሁሉ ይሆናል” ያለው በዚህ ለኖህ አምላክ በሰጠው የሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን እንስሳትም አራዊትም አዕዋፍም ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ከዚህም የምንረዳው እግዚአብሔር በቅዱሳን ቃል ኪዳን እንደሚጠብቀን ነው፡፡

ኢየሩሳሌም በአሶር ንጉስ በሰናክሬም ሠራዊት በተከበበች ጊዜ እግዚአብሔር ለቅዱስ ዳዊት የገባውን ቃል ኪዳን አስቦ “እግዚአብሔር ስለ እኔም ስለባሪያዬም ስለ ዳዊት ይህችን ከተማ አድናት ዘንድ እጋርዳታለሁ” ያለው በዚህም “የእግዚአብሔር መልአክ ወጣ ከአሶርም ሰፈር መቶ ሰማኒያ አምስት ሺህ ገደለ ማለዳም በተነሱ ጊዜ እነሆ ሁሉ በድኖች ነበሩ” ኢሳ 37፤33-36 ንጉስ ዳዊትም በዘመኑ ስለተሰጠው ቃል ኪዳን ሲገልጽ “የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ… ከእኔም ጋር በሁሉ ነገር ቅንና ጽኑ የሆነውን የዘለአለም ቃል ኪዳን አድርጎአል፡፡” ብሏል፡፡

2 ሳሙ 23፤1-5 የዘላለም በማለትም በቅዱሳን ቃል ኪዳን እረፍተ ዘመን (የዘመን ግድግዳ) የማይገታው ዘለዓለማዊ መሆኑን የተናገረው ስለዚህም ነው “መታሰቢያችሁን የሚያደርገውን ቤተክርስቲያን የሚያንጸውን በስማችሁ እንዲሁ ለተራቆተ የሚያለብሰውን የታመመ የሚጎበኘውን የተራበ የሚያበላውን የተጠማ የሚያጠጣውን ያዘነ የሚያረጋጋውን መመስገኛችሁን የፃፈውን ያፃፈውን ያነበበውን የስማውን ልጆቹን በስማችሁ የሰየመውን በበዓለ ንግሳችሁ ዝማሬ ያቀረበውን እምርላችኋለሁ፡፡ ”እንዳለ በየጊዜው የተነሱትን ቅዱሳን ቃል የሚገባላቸው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
የምክር ቃል

ቅዱስ፣ ጥንቁቅ፣ ግልጽና ብልህ ሁን፡፡ እርጋታን የተላበሰ ሰብእና ይኑርህ፡፡ ደስተኛ ሁን፤ ሰላምታህ በፈገግታ የታጀበ ንጹሕ ይሁን፡፡ ንግግርህ የታረመ አጭርና በጨው እንደ ተቀመመ ጣፋጭ ይሁን፡፡ቃላቶችህ የተመጠኑና ጤናማዎች ሁሉም የሚረዳቸው ይሁኑ፡፡ የጓደኛህን ምስጢር አትግለጥ፤ ለሚወዱህ ሁሉ የታመንክ ሁን፡፡ ወደ ጭቅጭቅና ንትርክ ከመግባት ራስህን ጠብቅ፡፡ የሚሰሙህ ሁሉ እንዳይጠሉህ ወደ ጠብ አትግባ፡፡

የበደሉንን ይቅር ማለት መሸነፍ ሳይሆን ፍቅርን ማስተማር ነው። ከሰይጣን በቀር ምንም ጠላት አይኑርህ፡፡ የሰዎችን ስህተት አትመራመር፤ የባልንጀራህን ኃጢአት አትግለጥ፡፡ የባልጀራህን ውድቀት ደጋግመህ አታውራ፡፡ በራስህ ኃጢአት ላይ ፍረድ እንጂ በሌሎች ላይ አትፍረድ ገዢያቸው አይደለህምና፡፡

ኃጢአትን በፈጸመ ሰው ላይ ወቀሳ አታብዛ አንተም ትበድላለህና፡፡ ነገር ግን ከኃጢአቱ ይመለስ ዘንድ ረዳትና መካሪ ሁነው፡፡ ከወደቀበትም የስህተት ሥራ እንዲወጣ አበርታው፡፡ ተስፋውን በእግዚአብሔር ላይ ቢያደርግ ኃጢአቱ ልክ በእሳት ፊት እንደ ወደቀ ገለባ ፈጥኖ እንደሚወገድለት ንገረው፡፡

ተፈጥሮ እንደ መጽሐፍ ፍጥረታት እንደ ጽላት ይሁኑህ፡፡ ከእነሱ ሕግጋትን ተማር፤ በተመስጦ ሆነህ በመጽሐፍ ያልሰፈሩትን ምስጢራት ተረዳ፡፡

እግዚአብሔርን ከሚፈራ በቀር ባለጸጋ የሆነ ሰው ማነው?  የእውነት እውቀት ከጎደለው ሰው በላይ ፍጹም ደሃ  የሆነ ማን ነው? ሁል ጊዜም እውነተኛ ፍቅራችን ጸንቶ ይቀጥል ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ፡፡ እርሱን ለምነው፡፡ ስለ ቸርነቱ ምስጋና አቅርብ፤ ምክሬን ፈጽሞ ቸል አትበል፡፡
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
​​ጾመ ሰብአ ነነዌ

ጾመ ነነዌ ከሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት አንዷ ስትኾን የምትጾመውም ለሦስት ቀናት ነው፡፡ ይህቺ ጾም የምትጀመርበት ዕለትም ልክ እንደ ዐቢይ ጾም ሰኞን አይለቅም፡፡ ጾሟ የምትጀመርበት ቀን ሲወርድ ወይም ወደ ኋላ ሲመጣ እስከ ጥር ፲፯ ቀን ድረስ ነው፡፡

ቀኑ ሲወጣ ወይም ወደ ፊት ሲገፋ ደግሞ እስከ የካቲት ፳፩ ቀን ይረዝማል፡፡ ጾመ ነነዌ በእነዚህ ፴፭ ቀናት ውስጥ ስትመላለስ (ከፍ እና ዝቅ ስትል) ትኖራለች፤ ከተጠቀሱት ዕለታት አትወርድም፤ አትወጣም፡፡ በዚህ ዓመትም የካቲት ፫ ቀን ትጀመራለች፡፡

‹‹ጾመ ሰብአ ነነዌ፤ የነነዌ ሰዎች ጾም›› የሚለው የጽሑፋችን ርእስ እንደሚያስረዳው ይህቺን የሦስት ቀን ጾም የጾሟት በነነዌ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ከተማዋም (ነነዌ) በጤግሮስ ወንዝ ዳርቻ የምትገኝ ስትኾን መሥራቿም ናምሩድ ነው  ዘፍ.፲፥፲፩-፲፪/ ፡፡ ጥንታዊቷ የነነዌ ከተማ ለአሦር መነሻ የኾነች፤ እጅግ ሰፊና ያማረች፤ የቅጥሯ ርዝመትም ፲፪ ኪሎ ሜትር የሚሸፈን ነበር። በከተማዋ ንጉሡ ሰናክሬም ብዙ ሕንጻዎችን ገንብቶባት ነበር /ዮናስ ፬፥፲፩/፡፡

በዚያ ዘመን የነበሩ የነነዌ ሰዎች ኀጢአታቸው በዝቶ እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ሲል ቸርነትና ምሕረቱ የማያልቅበት እግዚአብሔር መክሮ፣ ዘክሮ እንዲመልሳቸውና ንስሐ እንዲገቡ ነቢዩ ዮናስን ወደ ነነዌ ሕዝብ ላከው /ሉቃ.፲፩፥፴/፡፡

ዮናስ የስሙ ትርጕም ‹ርግብ› ማለት ነው፡፡ በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት የነበረ ነቢይ ነው፡፡ ይህ ነቢይ መኖሪያው በገሊላ በጋትሔፌር ድንበር ከተማ ነበረ፡፡ አባቱም አማቴ ይባላል፡፡ ኢዮርብዓም ሶርያውያንን አባሮ የእስራኤልን ድንበር እንዲመልስ ነቢዩ ዮናስ ትንቢትን ተናግሯል /፪ኛነገ.፲፬፥፳፭፤ ዮናስ ፩፥፩/፡፡

ነቢዩ ኤልያስ ያስነሣው የሰራጵታዋ መበለት ሕፃን ነቢዩ ዮናስ እንደ ኾነ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል /፩ኛ ነገ.፲፯፥፲፱/፡፡ መድኀኔታችን ክርስቶስም የዮናስን ከዓሣ ኾድ መውጣት የራሱ ትንሣኤ ምሳሌ አድርጎ ነግሮናል /ማቴ.፲፪፥፲፱-፵፪፤ ሉቃ.፲፩፥፴-፴፪/፡፡

እግዚአብሔር ‹‹ሔደህ በነነዌ ላይ ስበክ›› ባለው ጊዜ ነቢዩ ዮናስ ‹‹አንተ መሐሪ ነህ ፤ ልትጠፉ ነው ብዬ ተናግሬ ብትምራቸው ሐሰተኛ ነቢይ እባላለሁ›› ብሎ ላለመታዘዝ እስራኤልን ለቆ በመርከብ ወደ ተርሴስ ሸሸ፡፡

እግዚአብሔርም ታላቅ ነፋስን አስነሥቶ መርከቧ በማዕበል እንድትመታ አደረገ፡፡ ከዮናስ ጋር በመርከቧ ተሳፍረው የነበሩ ነጋድያንም ያላቸውን ሀብት ወደ ባሕሩ መጣል ሲጀምሩ ነቢዩ ዮናስ ጥፋቱን ተገንዝቦ ‹‹ማዕበሉ በእኔ ምክንያት የመጣ ስለ ኾነ ንብረታችሁን ሳይኾን እኔን  ወደ ባሕር ጣሉኝ›› ብሎ ተማጸናቸው፡፡

እነርሱም ‹‹ስለዚህ ሰው ነፍስ እንዳንጠፋ፣ ንጹሕም ደም በእኛ ላይ እንዳይደረግብን አይኾንም›› አሉ፡፡

ወደ ባሕሩ ለመጣል ዕጣ በተጣጣሉ ጊዜም ዕጣው በዮናስ ላይ ስለ ወጣ ነጋድያኑ ዮናስን ወደ ባሕሩ ጣሉት፡፡ ወዲያውኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ታላቅ ዓሣ አንበሪ ዮናስን በአፉ ተቀብሎ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት አሳድሮ ወደ ነነዌ አደረሰው፡፡

እግዚአብሔር የቅል ተክልን ምሳሌ በማድረግ ቅጠሉ በመድረቁ ዮናስ ባዘነ ጊዜ ‹‹አንተ ላልደከምክበት እና በአንድ ቀን በቅሎ ላደገ ቅል ስታዝን እነሆ በታላቂቱ ነነዌ ከተማ ያሉ ከአንድ መቶ ሃያ ሺሕ በላይ ሕዝብና እንስሳቱ የእጄ ፍጥረቶች ስለ ኾኑ ያሳዝኑኛል›› በማለት ነቢዩ ዮናስም ውሸታም ላለመባል መኮብለሉ ስሕተት መኾኑን አስረድቶታል፡፡

ዮናስም ነነዌ መሬት ላይ መድረሱን ባወቀ ጊዜ ከእግዚአብሔር መሸሽ አለመቻሉን ተረዳ፤ የነነዌ ሰዎችንም ‹‹ንስሐ ግቡ›› እያለ መስበክ ጀመረ፡፡ የነነዌ ሰዎችም ንስሐ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር ይቅር ብሎ ከጥፋት አድኗቸዋል። ሐሰት እንዳይባልም እሳቱ እንደ ደመና ኾኖ ከላይ ታይቶአል፡፡

የታላላቁ ዛፍ ቅጠል እስኪጠወልግ ድረስ አድርቆ ለሕዝቡ አሳይቷቸዋል፡፡ ንስሐቸው በከንቱ እንዳልቀረ አስረድቷቸዋል /ትንቢተ ዮናስን በሙሉ ይመልከቱ/። ታኅሣሥ ፭ ቀን የሚነበበው የመጽሐፈ ስንክሳር ክፍል ‹‹ወበልዐ አሐደ ኀምለ›› በማለት ንስሐ ያልገቡ አንድ አገር ያህል ሰዎች በእሳቱ እንደ ጠፉ ይነግረናል፡፡

ጾመ ነነዌ የሦስት ቀን ሱባኤ ናት፤ በሦስት ቀናት ጾምና ጸሎት ንስሐ የገቡ የነነዌ ሰዎች ከጥፋት እንደ ዳኑ ዅሉ፣ በብሉይ ኪዳን አስቴር ሦስት ቀን ጾማ፣ ጸልያ በእስራኤል ላይ የመጣውን መቅሠፍት እንዲመለስ አድርጋለች /አስ.፬፥፲፭-፲፮/፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ከበዓል ስትመለስ ሕፃኑ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ ላይ ጠፍቶአት ከሦስት ቀን ፍለጋ በኋላ በቤተ መቅደስ አግኝታዋለች /ሉቃ.፪፥፵፮/፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለሄሮድስ በሰጠው ምላሽ መልስ ሦስት ቀን የሱባኤ ፍጻሜ መኾኑን ገልጿል /ሉቃ.፲፫፥፴፪/፡፡

ጾመ ነነዌ የእግዚአብሔርን ቸርነትና መሐሪነት የምናስታውስበት ጾም ነው። ይኸውም እኛ ፍጡራኑ በበደልን ጊዜ ፈጽሞ ከማጥፋት ይልቅ ምክንያት ፈልጎ እንድንድን ያደርገናል፡፡ ዮናስ ለስብከት ፈቃደኛ ባይኾን እንኳን እግዚአብሔር በተለየ ጥበቡ እንዲሔድ አድርጎታል፡፡

በእርግጥ እግዚአብሔር ሌላ የሚልከው ነቢይ አጥቶም አይደለም፤ እርሱንም ጭምር ሊያስተምረው ስለ ፈለገ እንጂ። የነነዌ ሰዎች የተነሳ ሕያን ምሳሌ ናቸው፡፡ ይህም ማለት ሰው ጥፋቱን አምኖ ንስሐ ከገባ እግዚአብሔር ይቅር ማለቱን አይተውም፡፡ ለዚህም ነው ዮናስን ‹‹አንተ ላልደከምክበት እና በአንድ  ቀን በቅሎ  ላደገ ቅል  ስታዝን እነሆ በታላቂቱ  ነነዌ ከተማ ያሉ ከአንድ መቶ ሃያ ሺሕ በላይ ሕዝብና እንስሳቱ የእጄ ፍጥረቶች ስለ ኾኑ ያሳዝኑኛል›› ያለው፡፡

ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶቻችን ይህን እና ሌሎች አጽዋማትን እንድንጾም የወሰኑልን ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ሕጉ የተዘጋጀልን እንደ ነነዌ ሰዎች እኛም ጾመን፣ ጸልየን ከኀጢአታችን እንነጻ ዘንድ ነው፡፡ ዛሬ ዓለማችን በኀጢአት ማዕበል እየተናወጠች ባለችበት ወቅት እኛም እንደ ነነዌ ሰዎች ከበደላችን ብንመለስ እና ንስሐ ብንገባ ቸሩ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ይቅርታና ምሕረት የባሕርይ ገንዘቡ ስለ ኾነ ‹‹ወደ እኔ  ተመለሱ፤ እኔም ይቅር  እላችኋለሁ፤›› ይለናል፡፡

ስለኾነም በነቢዩ ዮናስ ላይ የተደረጉ ተአምራትንና ካለመታዘዝ የሚመጣ ቅጣት ቀላል አለመኾኑን በማስተዋል፣ ለነነዌ ሰዎች የወረደውን ምሕረት በመገንዘብ ለእግዚአብሔርም ኾነ ለሃይማኖት አባቶች እና ለወላጆቻችን መታዘዝ ይገባናል፡፡

ስንጾምም እግዚአብሔር አምላካችን መዓቱን በምሕረት፣ ቍጣውን በትዕግሥት መልሶ በኀጢአት ለጠፋው ዓለም ይቅርታውን ይልካል፡፡ በመጾማችን ራሳችን ከመዓትና ከመቅሠፍት ከመዳናችን ባሻገር በእኛ በደል ምክንያት አገራችን፣ ዕፀዋቱና እንስሳቱም ሳይቀር ከድርቅና ከቸነፈር ይተርፋሉና፡፡

✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
‹‹ትንቢተ ዮናስ››
በህዝብዋ መካከል ዓመጽ ስለ ፀና
በጣም ተቆጥቼ አዝኛለሁና
ይህን ለነነዌ ንገራት በአዋጅ
አለና ለዮናስ ለአሚታይ ልጅ
እግዚአብሔር አዘዘው እንዲሄድ በቶሎ
ዮናስ እምቢተኛው አሰበ ኮብልሎ
ከአምላክ ተደብቆ አምልጦ ሊጠፋ
ወደ ተርሴ ሊጓዝ ፤ ሄደ ወደ ያፋ
ዋጋ ከፈለና በመርከብ ተሳፍሮ
አያጉረመረመ ባህሩን ተሻግሮ
ዮናስ ተደብቆ ሊሄድ በግስገሳ
ከእግዚአብሄር ተልኮ ማዕበል ተነሳ
ታላቅ ሞገድ ሆኖ ባህሩ ተቆጣ
መርከበኞች ፈሩ ትልቅ ሽብር መጣ
መርከቡ እንዲቀለው እናድርግ እያሉ
አንስተው ብዙ እቃ ወደ መርከብ ጣሉ
ባህሩም ባሰበት በጣም ተናወጠ
መርከከቡ መሰለ የተገለበጠ
ሰው ሁሉ ተነሳ ጸሎት ለማድረስ
ይህ ሁሉ ሲሆን ተኝቷል ዮናስ
ወደ ዮናስ ሄዶ የመርከቡ አለቃ
ቀሰቀሰው እና ከእንቅልፉ ሲነቃ
እግዜር እንዲድነን ከዚህ ክፉ ጥፋት
ተነስ ፀልይ አለው ይብቃህ ማንቀላፋት
በመርከብ ውስጥ ያሉ ሰዎች ተሰብስበው
ተመካከሩ እና በነገሩ አስበው
አለ ሀጥያት ሰርቶ ከእኛ ጋር የመጣ
ለይተን ለማወቅ እንጣጣል እጣ
አለዚያ አንድንም ስለተባባሉ
ተሰበሰቡ እና እጣ ሲጣጣሉ
እውነትም እንዳሉት አጥፊው ሰው ታወቀ
በእንቢተኛው ነብይ በዮናስ ወደቀ
ዮናስ ተረዳና እጁ እንደተያዘ
ያጠፋውን ጥፋት ገልፆ ተናዘዘ
ምነው ባትመጣ ተጣልተህ ከጌታ
እየው መርከባችን እንደሚንገላታ
ቁጣው እንዲታገስ ለማግኝት ጸጥታ
በል አንተው ፍረደን ምን ይበጃል ቢሉ
ዮናስ መለሰና እዚህ ያለህ ሁሉ
ስለምን ይጠፋል በኔ የተነሳ
ወደ ባህር ጣሉኝ አለብኝ አበሳ
ተመልከቱ እነሆ ስራውን አወቀ
ጥፋቱን ገለጠ ይህው መች ደበቀ
እሱ ከፈረደ መልሶ በራሱ
ምን እናድግ ብለው ሊጥሉት ተነሱ
ከደሙ አንፃን ሲሉ ለእግዜር አመልክተው
ወደ ባህር ጣሉት ዮናስን አንስተው
በዮናስ ላይ ኖሮ የመጣው ይህ መዓት
ባሕሩ ፀጥ አለ ልክ በዚያው ሰዓት
ምዕራፍ 2
ዮናስን እንዲውጥ ሕይወቱን ሳይጎዳ
አንድ ትልቅ አሳ እግዜር አሰናዳ
ዮናስም ተውጦ በእግዚአብሔር ፍቃድ
ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት ሲያድር በአሳ ሆድ
ተቀይመህ ኖሮ ከላይ ብተቆጣ
ይህን ያህል መዓት በራሴ ላይ መጣ
የባህሩ ሞገድ እኔን አዋከበኝ
ውሀና ጨለማ ሲኦልም ከበበኝ
አያለ በአሳ ሆድ ዮናስ ሲቀመጥ
አምላኩን ለመነው በመለማመጥ
የታዛዥነትም ጠባይ እያሳየ
አዝኖ ተጸጽቶ ከልቡ ጸለየ
ምን ጊዜመ ቢቆጣ ነው እና መሓሪ
ፊቱን መልሶለት ታረቀው ፈጣሪ
አሳውም ዮናስን ውጦ ሳያስቀረው
ከባህር ተፋና መሬት ወረወረው
ምዕራፍ 3
ይህንን የእኔን ቃል ስማና በቶሎ
ሄደ ለነነዌ እንድትነግራ ብሎ
ደገመና እግዚአብሄር ዮናስን አዘዘ
ነነዌ ሊገባ ዮናስ ተጓዘ
ድምጹን ከፍ አድርጎ ነብዩ ዮናስ
‹‹ ከዛሬ ጀምሮ አርባ ቀን ድረስ
ነነዌ ጠፊ ነች ከሥር ተገልብጣ ››
አለና ለፈፈ የእግዚአብሔርን ቁጣ
ሳያንገራግሩ ሁሉም ስላመኑ
የነነዌ ሰዎች ተጨነቀው አዘኑ
ከትልቅ ጀምሮ ህጻኑ ድረስ
ሕይወቱ የቆመች በስጋ በነፍስ
ሰውም ሆነ እንስሳ ይቀበል ንስሓ
ፍጡር ሁሉ ይጹም ይለይ ከእህል ውኃ
ሁሉም ከልብ አዝኖ ማቅ እየለበሰ
ከክፉ ወደ ደግ እየተመለሰ
መቼም ወሰን የለው እግዚአብሔር ምሕረቱ
ይጸልይ አለና ይለምን በብርቱ
ንጉሡ አሳወጀ ከነመኳንንቱ
የነነዌ ሰዎች በውነት ከልቦና
መጸጸታቸውን እግዚአብሔር አየና
ፍጡር ቢለምነው እንባ እያፈሰሰ
ምህረቱን አውርዶ መዓቱን መለሰ
ምዕራፍ 4
የተናገረው ቃል ስላልተፈጸመ
ዮናስ ተቆጥቶ እያጉረመረመ
እኔን መጀመሪያ ነነዌ ለመላክ
አስበህ ብታዘኝ ይህንኑ ዐውቄ
ወደ ተርሴስ ልሄድ ጠፋሁ ተደብቄ
ምህረትህ የበዛ መሐሪና ታጋሽ
በደል የምትረሳ ከቁጣ ተመላሽ
የቁጣህን ያህል ምሕረትህ የጠና
መሆንህን ጥንቱንም እኔ አውቄአለሁና
እኔን ግን ግደለኝ ልሙት ልቀበር
ሀሰት ተናግሬ የማይሆን ነገር
አልፈልግምና ቆሜ ለመኖር
ከከተማ ወጥቶ በምስራቅ በኩል
ከወደ ዳር ሆኖ ነነዌን ሊያስተውል
ምን እንደሚያገኛት ለማየት ዮናስ
ተሰርቶ ተቀመጠ አንዲት ትንሽ ዳስ
እግዜር በጥበቡ አንድ ቅል አብቅሎ
ቅሉም አደገና ከፍ ከፍ ብሎ
የዮናስ ራሱ እንዲያገኝ ጥላ
ከጸሀዩ ንዳድ ሆለት ከለላ
በዚህ በቅል ነገር ዮናስ ደስ አለው
እንዲህ ቶሎ ደርሶ ስላገለገለው
እግዜር በማግስቱ ጧት በማለዳ
ቅል የሚበላ ትል ፈጠረ አሰናዳ
ትሉ ቅሉን በልቶ በፍጥነት  ደረቀ
ፀሀይ ወጣችና ጊዜው በጣም ሞቀ
እግዜር አዘነና ትኩስ ንፋስ መጣ
የሚከለልበት መጠጊያ ስላጣ
ቅሉ ደረቀና ንዳድ ቢያቃጥለው
ዮናስ ተበሳጭቶ ለአምላክ እንዲህ አለው
እንደዚህ ሆኜ ቆሜ ከመኖር
እባክህ ግደለኝ ልሙት ልቀበር
ደረቀብኝ ብለህ ይህን ቅል በማጣት
እውን ይገባል ሆይ ያንተ እንዲህ መቆጣት?
ብሎ እግዜር ቢጠይቅ መለሰ ዮናስ
በንዴት ብዛት እስክሞት ድረስ
አዎን ይገባኛል መናደድ መጤስ
እግዜርም መለሰ ለምን ጠፋ ስትል
ይህ ያለፋህበት ያልደከምክበት ቅል
አንተ ስትናደድ ፈጥሬያት እኔማ
ሳጠፋት ሳፈርሳት ነነዌን ከተማ
መቶ ሀያ ሺህ ነው የህዝቧ ብዛት
ለምን ትቆጣለህ እኔ ባዝንላት
ብሎ በምሳሌ ሲያስተምር ይቅርታ
ለዮናስ ነገረው የምህረቱ ጌታ
ለእግዚአብሔር ቸርነት ምስጋና ይድረስ
በዚህ ተፈፀመ ትንቢተ ዮናስ

መልካም ጾም
ለተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
2025/07/04 18:02:09
Back to Top
HTML Embed Code: