Telegram Web Link
#ምክር_ዘቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ

እስኪ ንገሩኝ! ከእናንተ መካከል ከመዝሙረ ዳዊት ውስጥ አንዲት ምዕራፍ ወይም ከሌላው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ጥቂት [በቃልህ] ድገም ቢባል ይህን ማድረግ የሚችል ማን ነው? አንድ ሰውስ እንኳ አይገኝም፡፡

እጅግ የሚያሳዝነው ነገር ግን ይኼ ብቻ አይደለም፡፡ ከመንፈሳዊ ነገሮች አንጻር እንደዚህ አእምሮ የጎደላችሁ ኾናችሁ ሳለ ዲያብሎሳዊ በኾኑ ነገሮች ላይ ግን እሳት የላሳችሁ ናችሁ፡፡ እንዲህም በመኾናችሁ አንድ ሰው መጥቶ ዲያብሎሳዊ ዘፈኖችንና የዝሙት ሙዚቃዎችን ንገሩኝ ቢላችሁ፥ ከእናንተ መካከል እነዚህን በትክክል የሚያውቁና ደስ ተሰኝተው የሚደግሙአቸው ብዙ ሰዎችን ያገኛል፡፡

ለምንድን ነው እንደዚህ የምትኾኑት? ከእናንተ መካከል “እኔ መነኰሴ አይደለሁም፡፡ ሚስት አለችኝ፡፡ ልጆች አሉኝ፡፡ የቤተሰብ መሪ ነኝ” የሚል ምክንያት የሚያቀርብ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ለምን እንደዚህ ትላላችሁ? ብዙዎችን ያጠፋው “ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ለመነኰሳት ብቻ ነው” የሚለው አመለካከታችሁ ነው፡፡ ከመነኰሳቱ ይልቅ ይበልጥ ማንበብ ያለባችሁ ግን እናንተ ናችሁ፡፡ ይበልጥ መድኃኒት የሚያስፈልጋቸው ሰዎች በዓለም የሚኖሩና ዕለት ዕለትም ቁስል የሚያገኛቸው ሰዎች ናቸውና፡፡ ስለዚህ ካለማንበባችሁም በላይ “የእኛ ማንበብ ትርፍ ነገር ነው” ብላችሁ ማሰባችሁ በራሱ የዲያብሎስ አሳብ ነው፡፡ ወይስ ንዑድ ክቡር የሚኾን ጳውሎስ “ይህም ኹሉ እኛን ሊገሥጸን ተጻፈ” ያለውን አላደመጣችሁምን? (1ኛ ቆሮ.10፡11)፡፡

አንተ ሰው እስኪ ንገረኝ! ወንጌልን በእጅህ ለመያዝ ብትፈልግ አስቀድመህ እጅህን ትታጠባለህ፡፡ ታዲያ በወንጌሉ ውስጥ ያለውን ቃለ እግዚአብሔር ከዚህ በላይ እጅግ አስፈላጊ እንደ ኾነ አታስብምን? ብዙ ነገሮች ምስቅልቅላቸው የወጣው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ጥቅሙ እንደ ምን የበዛ እንደ ኾነ ማወቅ የምትሻ ከኾነ መዝሙረ ዳዊትን ስትሰማና የአጋንንትን ዘፈን ስታደምጥ ምን እንደምትኾን፣ ቤተ ክርስቲያን ስትኾንና ቤተ ተውኔት ስትቀመጥ እንዴት እንደምታስብ ራስህን መርምር፡፡ ያን ጊዜ በነፍስህ ላይ የሚስተዋለው ልዩነት እንደ ምን ታላቅ እንደ ኾነ ትገነዘባለህ፡፡ ነፍስህ አንዲት ብትኾንም ቅሉ እዚያ ስትኾንና እዚህ ስትኾን በአኳኋንዋ እንዴት እንደምትለያይ ታስተውላለህ፡፡ ይኸውም የተወደደ ጳውሎስ፡- “ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” እንዳለው ማለት ነው (1ኛ ቆሮ.15፡33)፡፡ ስለዚህ ዘወትር ከመንፈስ ቅዱስ የኾኑ መዝሙራትን ልንሻ ይገባናል፡፡ ግዕዛን ከሌላቸው ፍጥረታት ያለን ብልጫ ይህ ነውና፡፡
ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE

     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin
ጾም
ጾም መድኃኒት ናት። አወሳሰዷን ለማያውቁ ግን ምንም ጥቅም የላትም፡፡ ይህቺን መድኃኒት የሚወስድ ሰው
በየስንት ሰዓቱ እንደምትወሰድ፣ በምን ያክል መጠን እንደምትዋጥ፣ ለምን ዓይነት በሽታ እንደምትጠቅም፣ በየትኛው ወራትና በየትኛው የአየር ሁናቴ እንደምትወሰድ፣ ከርሷ ጋር የሚሄዱና የማይሄዱ ምግቦችን እንዲሁም ሌሎች ከእርሷ ጋር የማይስማሙ ነገሮችን ለይቶ ማወቅ አለበት። እነዚህን ግምት ውስጥ አስገብተን የማንወስዳት ከሆነ ግን ከጥቅሟ ይልቅ ጓዳቷ ያመዝናል። አንድ በሐኪም የታዘዘንን የደዌ ዘሥጋ መድኃኒት በትክክል ከወሰድነው ከሕመማችን እንፈወሳለን፤ የነፍሳችንን ደዌ ለመፈወስ ብለን በምንወስደው መድኃኒት ደግሞ ከዚህ የበለጠ መጠንቀቅ ይገባናል።
ጾም ሁለመናችንን የምንለውጥባት መሣሪያ ናት። ምክንያቱም የጾም መሥዋዕት ማለት ከምግብ ብቻ መከልከል አይደለምና፤ ከኃጢአት ሁሉ መከልከል እንጂ። ስለዚህ እየጾምኩ ነው እያለ ራሱን ከምግብ ብቻ የሚከለክል ሰው ቢኖር እርሱ ጾምን እያቃለለና እያጥላላ ነው። እየጾማችሁ ነውን? እንዲያውስ መጾማችሁን በተግባር አሳዩኝ። 'እንዴት አድርገን እናሳይህ?'' ትሉኝ ይሆናል። እኔም እንዲህ ብዬ እመልስላችኋለሁ፦ ደሃው እርዳታችሁን ፈልጎ እንደሆነ ቸርነትን አድርጉለት፤ የጠላችሁትን ሰው ካያችሁት ፈጥናችሁ ታረቁ።
ባልንጀራችሁ ተሳክቶለት ስታዩት በእርሱ ላይ ቅናት
አትያዙ። ቆነጃጅቶችን ስታዩ በዝሙት ዓይን አትመኙ። እንዲህ እንዲህ እያደረጋችሁ በትክክል መጾማችሁን አሳዩኝ።
ምንጭ፦ ሰማዕትነት አያምልጣችሁ፣

በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE

     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin
እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታ ፍቺ በዓል በሰላምና በጤና አደረሰን አደረሳቹ።

የእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ምድር የኖረችው ስልሳ አራት ዓመት ነው። እነዚህ አመታት ሲተነተኑ ሦስት አመት በወላጆቿ ሐናና ኢያቄም ቤት፣ አስራ ሁለት አመት በቤተ መቅደስ፣ ሰላሳ ሶስት አመት ከሶስት ወር ከልጇ ከወዳጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አስራ አምት አመት ከሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ጋር ነው።

ያረፈችውም ጥር 21 ቀን በ49 ዓ.ም ነው። ባረፈችም ወቅት ቅዱሳን ሐዋርያት ክቡር ስጋዋን ለማሳረፍ ወደ ጌቴ ሴማኒ ሲሔዱ አይሁድ ቀድሞ ልጇ በሶስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ፣ በአርባኛውም ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ፣ ተመልሶም ይህንን አለም ለማሳለፍ ይመጣል እያሉ በማስተማር ሕዝባችንን ወስደውብናል። አሁን ደግሞ ዝም ብለን ብንተዋት እርሷም እንደ ልጇ ተነሳች እያሉ በማስተማር ሊያውኩን አይደለምን? ኑ! ተሰብስበን በእሳት እናቃጥላት ብለው ክፉ ምክር ተማከሩ።

ከመካከላቸውም ብርቱ ሰው የሆነው ታውፋንያ የተባለ ቅድስት ስጋዋን ከሐዋርያት ነጥቆ ለማስቀረት ክቡር ስጋዋን ያለበትን የአልጋ ሽንኮር ሲይዝ በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እጁ ተቆርጣ ከአልጋው ላይ ተንጠልጥላ ቀረች፣ ከዚህ የጥፋቱ ስራው ተምሮ እመቤታችንን በመለመኑ እመቤታችን የተቆረጠች እጁን መልሳለታለች።

ከዚህም በኋላ መልአከ እግዚአብሔር የእመቤታችን የተቀደሰ ስጋዋን ጌታችን ይወደው የነበረ ተብሎ የተነገረለት ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን ይዞ በገነት በዕፀ ሕይወት ስር አስቀመጠው። ቅዱስ ዮሐንስም የሆነውን ሁሉ ለወንድሞቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ነገራቸው። እነሱም የእመቤታችንን ስጋ በክብር ለማሳረፍ ካላቸው ጉጉት የተነሳ ከነሐሴ 1 ቀን ጀምሮ ሱባኤ ገቡ።

ከሁለት ሱባኤ ቆይታ በኋላ ማለትም በአስራ አራተኛው ቀናቸው ጌታችን የእመቤታችንን ትኩስ ስጋ ሰጣቸው። ሐዋርያትም በዝማሬና በታላቅ ምስጋና በጌታ ሴማኒ ቀበሯት። ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት "አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነስ አንተና የመቅደስህ ታቦት" ተብሎ ትንቢት የተናገረውን ሲተረጉሙት "ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ሆይ ወደ መንግስተ ሰማያት የምታሳርፈው የመቅደስህ ታቦት የሆነችውን ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነስ" ብለው ያመሰጥሩታል። /መዝ.131÷8።

የእመቤታችን ቅድስት ስጋዋን ሐዋርያት ሲቀብሯት በሀገረ ስብከቱ ሕንድ የነበረው ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ሲመለስ እመቤታችን ስታርግ ያገኛታል ለምልክት እንዲሆነው ሰበኗን(የመግነዟን ጨርቅ) ተቀብሏት ይለያያሉ። ለወንድሞቹ ሐዋርያት ያየውን ይነግራቸዋል።

ለበረከት የሰጠችውን ሰበን ያካፍላቸዋል፣ ሐዋርያት "ዕርገቷን እንዴት እሱ ብቻ ተመልክቶ ለምን እኛ ይቀርብናል" ብለው በዓመቱ ማለትም በ50 ዓ/ም ነሐሴ 1 ቀን ሱባኤ ገቡ። ነሐሴ 16 ቀን የልባቸው መሻት ተፈጸመላቸው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቅ(ረዳት) ቄስ፣ ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስን ገባሬ ሰናይ (ዋና ዲያቆን) አድርጎ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው።

በትህትና የያዙት ሱባኤም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ዕርገቷን ለማየት አበቃቸው። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን መሠረት አድርጋ ከነሐሴ 1 እስከ 16 ጾመ ፍልሰታ በማለት ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ አድርገን እንድንጠቀምበት ስርዓት ሰራችልን።

በነቢያት እና በሐዋርያት መሠረት ላይ የታነጽን ኦርቶዶክሳውያን የተዋህዶ ልጆች በየዓመቱ ይህን ጾም ሱባኤ በማሳለፍ ከእመቤታችን ጸጋና በረከት ተሳታፊዎች እንሆናለን፣ ሆነናልም። እግዚአብሔር አምላክ ሀገራችንን ሰላም አድርጎ ከቁጥር ሳያጎል በሰላም በጤና ጠብቆ ለአመቱ ያድርሰን🙏

ከእመቤታችን ረድኤት በረከት ተቋዳሾች ያድርገን። አሜን🙏
ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE

     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin
ድንግል ሆይ !

❝አንቺን የወለደ ማህጸን እንዴት ያለ ብሩክ ነው❞ አንቺን የታቀፉ ክንዶችስ እንዴት ያሉ ድንቅ ናቸው ! አስራ ሁለት ዓመት ወደ ቤተመቅደስ የተመላለሱ እግሮችሽስ እንዴት የከበሩ ናቸው ! የቅዱሱን መልአክ ብሥራት የሰሙ ጆሮዎችሸስ እንዴት ያሉ ንቁ ናቸው ! ❝የቃልን ሰው መሆን ያመነው ልብሽ እንዴት ያለ ንጹሕ ነወ ! ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ጌታን የተሸከመው ማሕፀንሽ እንዴት ያለ ግሩም ነው ! ይህን ታላቅ አምላክ የታቀፉ ክንዶችሽስ እንዴት ያሉ ጽኑ ናቸው ! ጌታዬን ያጠቡት ጡቶሽን እንዴት የለመለሙ ናቸው ! ድንግል ሆይ ክብርሽ ከፍ ያለ ነውና አከብርሻለሁ❞ ሰላሳ ሶስት ዓመት ከሶሶት ወር ከጌታ ጋር ያኖረሽን እምነት እኔ ልጅሽ ለአንድ ሰዓት እንኳ የለኝምና እጅግ ጎስቋላ ነኝ ። አስራ ሁለት ዓመት ከወንጌላዊው ዮሐንስ ቤት ያኖረሽን ልበ ሰፊነት እኔ ደካማው ልጅሽ ለአንድ ሰዓት እንኳ ከምወደው ጋር ለመሆን አልታደልኩምና እጅግ ደካማ ነኝ ! ቅድስት ሆይ የምልጃሽ በረከት የእግዚአብሔርን እገዛ ይላክልኝ ። ፍልሰትሽ መጪውን የምዕመናንን ትንሳኤ ጎልቶ ያሳያል ።  ዕርገትሽ መጪውን የምዕመናን ዕርገት በግልጥ ያስተምራል ። ከሚታስበው በላይ  ቅድስት ፣ ከሚነገረው በላይ ትሁት ፣ ከምሰማው በላይ ቡሩክት ፣ ከጻፉልሽም በላይ ንጽህት ፣ ከተረኩሽም በላይ ልዕልት ነሽና ልቤ ታመሰግንሻለች !


ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE

     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin
የመጀመሪያው ሰው አዳም ገነት ተሰጥታው ሳለ፥ በአንዲት ትእዛዝ መተላለፍ ምክንያት ከክብሩ ተዋርዶ [በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ፣ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነም ተፈርዶበት] ያን ኹሉ መከራና ሥቃይ ካገኘው፥ መንግሥተ ሰማያትን የተቀበልን፣ ተቀዳሚ ተከታይ ከሌለው አንድ ልጁ ጋር አብረን ወራሾች ከኾንን በኋላ ርግቢቱን ሳይኾን እባቡን ተከትለን የምንኼድ እኛ’ማ ሊደረግልን የሚችል ይቅርታ እንደ ምን ያለ ይቅርታ ይኾን?

ከእንግዲህ ወዲህ በእኛ ላይ የሚፈረደው ፍርድ እንደከዚህ በፊቱ “አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህ” የሚል አይኾንምና (ዘፍ.3፡19)፡፡ “ምድርን ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኃይሏን አትሰጥህም” የሚል አይደለምና (ዘፍ.4፡12)፡፡ ይህን የመሰለ ሌላ ፍርድም አይደለምና፡፡ ታዲያ ምንድን ነው? በውጭ ወዳለው ጨለማ መጣል! መቼም ቢኾን መች በማይፈታ እስራት መታሰር! በማያንቀላፋ ትል መበላት! ጥርስ ማፋጨት ባለበት ጽኑ ፍርድ መጣል (ማቴ.25፡30)

ይህም እጅግ ምክንያታዊ ነው፡፡ እንዴት ቢሉ አንድ ክርስቲያን ታላቅ የኾነ ጸጋን (ልጅነትን) ተቀብሎ ሳለ በዚያ በተቀበለው ጸጋ መነሻነት [ወይም ለተቀበለው ጸጋ እንደሚገባ] ብልጫ ያለው ሕይወትን የማያሳይ (የማይኖር) ከኾነ፥ የሚያገኘው መከራም የዚያን ያህል ታላቅ ነው፤ የሚቀበለው ቅጣትም እጅግ ጽኑ ነው፡፡

አንድ ጊዜ ኤልያስ ሰማይን ከፍቶ ዘግቶ ነበር፡፡ ያን ያደረገው ግን ዝናብ እንዲዘንብና እንዳይዘንብ ለማድረግ ነበር፡፡ ለአንተ ግን ሰማይ የተከፈተው ዝናብ እንዲዘንብ ወይም እንዳይዘንብ እንድታደርግበት አይደለም፤ ወደዚያ እንድትወጣበት ነው እንጂ፡፡ ወደዚያ እንድትወጣ ብቻም አይደለም፤ ፈቃደኝነቱ ካለህ ሌሎች ሰዎችንም ወደዚያ እንድትመራበትም ጭምር ነው እንጂ፡፡ አየህ! ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ ገንዘቡ ከኾነው በጸጋ ይህን ያህል ድፍረትና ኃይል ነው የሰጠህ!
#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE

     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin
"እኔ ነኝ" ዩሐ 9፥9

ጌታችን ከቤተመቅደስ አስተምሮ ሲወጣ በመንገድ ሲያልፍ እውር ሆነ የተወለደውን አየ። ይህን ሰው ምራቁን እንትፍ ብሎ ጭቃ አድርጎ ዐይን ሠርቶ ሂዲና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ አለው ያም እውር ሒዶ ታጠበና እያየ ተመለሰ። በመንገድ በሚመጣበት ወቅት ቀድሞ ያውቁት የነበሩት ሠዎች 'ይህ በመንገድ ተቀምጦ ይለምን የነበረው አይደለምን? ' ብለው መጠየቅ ጀመሩ ገሚሶቹም እርሱ ይሆን አለ? ገሚሶቹ 'አይደለም እርሱን ይመስላል እንጂ'  አሉ፤ እርሱ ግን "እኔ ነኝ" አላቸው።
    ልክ እንደዚህ እውር ዛሬም በጨለማ የነበርኩ ሆኜ ሣለሁ ብርሃንህን አይ ዘንድ ውሣጣዊ ዐይኔን ብሩህ አርገህ ከጨለማ ያወጣኸኝ። ከድቅድቅ ጨለማ ወደ ሚደንቅ ብርሃን በፍቅርህና በምህረት የጠራኸኝ። ሥራዬ እጅግ የከፋ በበደሌ በሠው ሁሉ የታወቅኩ በመጨለማ መሆኔ ለሠው ሁሉ የተገለጠ እኔን በፍቅርህ  የሣብከኝ "እኔ ነኝ" መዓዛዬ በኀጢኣት የከረፋ ሆኜ ሣለሁ በነውሬ ብዛት መሽተቴን ሣትጠየፍ ወደእኔ መጥተህ ምዑዝ  የሆነ መዐዛህ የሠጠኸኝ በኃጢያት ባህር በጥልቁ ሠምጬ ሣለሁ የንስሐን ገመድ የምህረትህን እጅ ልከህ ከኀጢያት ያወጣኸኝ እኔ ነኝ።
      ሠዎች በቤትህ ለልጅነት መሾሜን በፍቅር መጠራቴን አይተው ይኸህ በጨለማ ህይወት ይኖር የነበረው አይደለምን ይላሉ። አዎን "እኔ ነኝ" የማይወጡትበት የኃጢያት ረግረግ የተዋጣኩ የማይነጋ በሚመስለው ጨለማ ውስጥ የተቀመጥኩ ብሆንም እርሱ ግን ሳይንቀኝ ወደ እኔ ቀረበ ፍቅሩና ቸርነቱን አበዛልኝ ከረግረጉ ጎትቶ ያወጣኝ ጨለማውን ገላልጦ ብርሃኑን ያበራልኝ "እኔ ነኝ"። የምህረቱና የቸርነቱ መጠን ማሳያ እኔ ነኝ። ሊቁ "ብዙ ኃጢያት ባለችበት የእግዚአብሔር ጸጋ ትበዛለች" ብሎ እንደመሠከረ ከሁሉ የበደልኩ ሆኜ ሣለ ከሁሉ ይልቅ የምህረትህን የችሮታህን ጸጋ ያበዛልኝ እኔ ነኝ።
        አሁንም በፍቅርህና በምህረትህ ጠርተኸኝ ከጨለማው አላቀኸኝ ብርሃንህን አሳይተኸኝ ዐይኔን አብርተህልኝ ወደ ጨለማው የምናፍቅ ከኀጢኣት ጽልመት አርቀህ ወደ ጸአዳነት መልሰኸኝ ማረፊያ አጥቼ ስዋልል የነበርኩትን በቤትህ አሳርፈኸኝ ተርቤ የነበርኩትን ሥጋህናን ደምህን መገበኸኝ ሁሉን ሰጥተኸኝ ሣለ አሁንም ከብርሃን ይልቅ ጨለማውን የምናፍቅ ከጽድቅ ብርሃን ይልቅ ጽልመትን የምመኝ ከዘላለም ማረፊያዬ ይልቅ ስደተኝነትን የምከጅል እንደ ግመል ሽንት ወደኋላ የምል ልጅህ እኔ ነኝ።
         ዛሬም ምህረትህ የሚያስፈልገኝ ጥሪህ የሚናፍቀኝ በቤትህ በቅጥርህ ሆኜ ባስቀመጥከኝ ያልተገኘው የጠፋው ባሪያህ  እኔ ነኝ። በቅዱሱህ ስፍራህ ያለውኝ ቅድስናን ግን ገንዘብ ማድረግ ያቃተኝ በብርሃን ሆኜ መንገዴ የጠፋብኝ። ብዙ የተቀበልኩ ብዙ የሚጠበቅብኝ ሆኜ ሣለው ምንም የሌለኝ  ከጽድቅ የተራቆትኩትኩኝ ባዶ እኔ ነኝ። ልክ እንደ ድሪሙ በቤትህ ሆኜ ዘወትር ከቅጥርህ ሣልጠፋ ነገር ግን ቆሻሻ በሆነ ህይወት በኀጢኣት ውስጥ የጠፋው በብርሃንህ ሥፍራ ብገኝም ኀጢኣቴና በደሌ አይኔን አዉሮኝ ጽድቅህንና ብርሃንህን ማየት የተሣነኝ ልጅህ እኔ ነኝ። አሁንም ምራቅህን ጥቅ ብለህ አንተን ማየት የሚችሉ ዓይንን ፍጠርልኝ። በፊቴ ላይ ቅዱስ ምራቅህን ጥቅ በልብኝ በፍቃዴ ያጠፋውትን ዓይኔንም አብራልኝ።

ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE

     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin
በቤትህ ያለው ዳቦ ለተራበው ሰው የሚውል(ንብረቱ) ነው፥ በልብስ ማስቀመጫህ ውስጥ ያለው የማትጠቀመው ኮት የችግረኛው ገንዘቡ ነው፥ በጫማ ማስቀመጫህ ውስጥ አልፈልገውም ብለህ ሊበላሽብህ የሆነው ጫማ የደሃው ጫማ (ጫማ ለሌለው ገንዘቡ) ነው ፥ ያከማቸኸው ገንዘብ ለድሃው የሚገባው ነው....

ዛፍ በፍሬው ይታወቃል፥ ሰውም በድርጊቱ፡፡ መልካም ስራ መቼም አይጠፋም፡፡ መልካም እርዳታን የሚዘራ፥ ወዳጅነትን ያጭዳል፡፡ ደግነትን የሚተክል ፍቅርን ይሰበስባል፡፡

"ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ብቻ የለብንም፥ ነገር ግን ካነበብነው ተምረን ማደግ አለብን፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ምንም የማይጠቅም ነገር እንዳልተጻፈ ተገንዘብ፡፡

አሁንም ለጥንካሬ፣ ለመታገስ፣ለመዳን፣ለመለወጥ ጊዜ አለህ! ተኝተሃልን? ንቃ! ኃጢአት ሰርተሃልን? እንግዲያውስ  መስራቱን አቁም፡፡

ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ
ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE

     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin
😐😐😐ዝምታ😐😐😐

አንዳንድ ጊዜ ዝምታ ከቃላት ይልቅ ውጤታማ፣ ይበልጥ ተገቢና እጅግ ጠቃሚም ነው። ወይም ደግሞ ቢያንስ - ቢያንስ ተናግሮ ከሚመጣ ጉዳት ይልቅ ሳይናገሩ የሚመጣ ጉዳት ይሻላል። በዝምታ ውስጥ ጥበብና ጥንካሬ ከመኖራቸው በተጨማሪ ክብርና ሞገስም አሉ፡፡

አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ይናገር ዘንድ እኛ ዝም እንላለን፣እኛ ልንናገር ከምንወደው ከማንኛውም ነገር የበለጠ የእግዚአብሔር ቃል እጅግ ኃያል ነውና። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አስመልክቶ የተናገረው ቃል ምንኛ ድንቅ ነው! «እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፤እናንተም ዝም ትላላችሁ. . » ዘጸ 14፥14።

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጲላጦስ ፊት በዝምታ ቆይቷል። በዚያን ጊዜ እርሱ  አፉን አልከፈተም ራሱንም አልተከላከለም። ጌታ ዝምታን በመረጠ ጊዜ ጲላጦስ "ይህን ጻድቅ ሰው የምወነጅልበት ምንም ዓይነት ምክንያት አላገኘሁም" በማለት ተናግሮ ነበር፡፡

ዝምታ ትርፍ አስገኚ ይሁን እንጂ የተወሰነ መመሪያ አይደለም፡፡ ወርቃማው መመሪያ፡- ሰው ሊናገር የሚገባው በትክክለኛው ጊዜ መሆኑና ዝም ማለት የሚገባውም ዝም ማለት በሚገባው ትክክለኛ ጊዜ መሆኑ ነው።

ሰው ዝም ሲል ልቡ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲነጋገር ስለሚፈቅድ በእርሱ ፈንታ ጌታው እንዲናገር ይጠይቃል ማለት ነው፡፡

(አቡነ ሽኖዳ ሣልሳዊ - የሕይወት ልምድ ገጽ 14 - በአያሌው ዘኢየሱስ የተተረጎመ)

ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE

     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin
ወንድሞቼ "እገሌ እኮ እንዲህ እንዲህ ዓይነት ኃጢአት ሠርቷል" ብላችሁ የምታሙትን ወንድማችሁ ከዚያ ኃጢአቱ ነጻ እንዲወጣ ትፈልጋላችሁን? እንግዲያስ ስለ ኃጢአቱ አልቅሱለት፤ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩለት፤ ለብቻ ወስዳችሁም ምከሩት እንጂ አትሙት። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እንዲህ ብሎ ጽፎላቸው ነበር፡- "ነገር ግን ወዳጆች! እናንተን ልናንጻችሁ ሁሉን እንናገራለን። ስመጣ እንደምወደው ሳትሆኑ አገኛችሁ ይሆናል፤ እኔም እንደምትወዱት ሳልሆን ታገኙኝ ይሆናል ብዬ እፈራለሁና፡፡ ምናልባት ክርክር ቅንዓትም ቁጣም አድመኝነትም ሐሜትም ማሾክሾክም ኩራትም ሁከትም ይሆናሉ፡፡ እንደ ገና ስመጣ በእናንተ ዘንድ አምላኬ እንዲያዋርደኝ፥ አስቀድመውም ኃጢአት ከሠሩትና ስላደረጉት ርኵሰትና ዝሙት መዳራትም ንስሐ ካልገቡት ወገን ስለ ብዙዎች ምናልባት አዝናለሁ ብዬ እፈራለሁ" /2ቆሮ.12፥19-21/። ስለዚህ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ በትልቁ ደግሞ እንደ ጌታችን "ኃጢአተኛ ነው" የምትሉትን ወንድማችሁ ውደዱት፡፡ ለብቻው አድርጋችሁ ስትነግሩትም አመጣጣችሁ እርሱን ለመምከርና ለመገሰጽ ደግሞም ከኃጢአቱ እንዲመለስ እንጂ እርሱን ከመጥላታችሁ የተነሣ እንዳልሆነ አስረዱት፡፡ ስለዚህ በትክክል ካለበት ደዌ እርሱን መፈወስ ስትፈልጉ ወደ እርሱ መሄድን አትፍሩ፤ ጥፋቱን ለመንገርም አትፈሩ፡፡

ሐኪሞችን አይታችሁ ከሆነ አንድ አስቸጋሪ ታማሚን ለማከም መጀመርያ ቀስ ብለውና ጊዜ ወስደው ታማሚዉን ያሳምኑታል፤ ከዚያም መራሩን መድኃኒት ይሰጡታል፡፡ ታካሚውም በሽታው የሚድን ከሆነ ይፈወሳል፡፡ ሐኪሙን የሚያመሰግነው ግን ሲድን ነው፡፡ እናንተም እንደዚህ ሐኪም መሆን አለባችሁ፡፡ ከምታሙት ይልቅ የወንድማችሁን ቁስል የበለጠ እንዳይመረቅዝ ፈጥናችሁ ወደ ሐኪም ቤት (ወደ ቤተክርስቲያን) ውሰዱት። ከዚያም ሐኪም (ካህን) እንዲያየው አድርጉ፡፡ እንዲህ ስታደርጉ እናንተም ወንድማችሁም በእጅጉ ትጠቀማላችሁ፡፡ እውነተኛ ጦም ጦማችሁ ማለትም እንዲህና ይህን የመሰለ መልካም ምግባር ስታደርጉ ነው፡፡
#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE

     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin
#ዕጣንና_ጽንሃ_በቤተክርስቲያን

#ዕጣን
ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ዕጣንን የተመላ ሰማያዊ ማዕጠንት በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት እየሰገዱ ለአለም ድህነት የሚለምኑበት ነዉ፡፡ በቤተክርስቲያን ካህናት መንፈቀ ሌሊት ፡ በነገህ ጊዜ በቅዳሴ ጊዜ በየማዕዘኑ ዕጣን ያጥናሉ ቅዳሴውን ጸሎቱንና ልመናዉን ወደ እግዚአብሔር ያሳርጉበታል ፡፡

ስለ እጣን የመፅሀፍ ቅዱስ ማስረጃ

ዘጸ 30፥1 የዕጣን መሰዊያዉን ስራ ከግራር እንጨት አድርገው።

ዘጸ 30፥35 በቀማሚ ብለሀት እንደተሰራ፥ በጨዉም የተቀመመ ንጹህና ቅዱስ እጣን አድርገው፡፡

ዘጸ 30፥34 እግዚአብሄርም ሙሴን አለዉ፦ ጣፋጭ ሽቱ ዉሰድ የሚንጠባጠብ ሙጫ በዛጎል ዉስጥ የሚገኝ ሽቱ፥ የሚሸትትም ሙጫ፥ ጥሩም ዕጣን ዉሰድ የሁሉም
መጠን ትክክል ይሁን፡፡

ዘፀ 40፥5 ለዕጣንም የሚሆነዉን የወርቅ መሠዊያ በምስክሩ ታቦት ታኖራለህ፥ በማደሪያዉም ደጃፍ ፊት መጋረጃዉን ትጋርዳለህ፡፡ ዘጸ 40፥27 የጣፋጩን ሽቱ ዕጣን አጠነበት፡፡

ዘሌ 10፥1 የአሮንም ልጆች ናዳብና አብድዩድ በየራሳቸዉ ጥናዉን ወስደዉ እሳት፥ በላዩም ዕጣን አኖሩበት በእግዚአብሔር ፊት እሱ ያላዘዛቸውን ሌላ እሳት አቀረቡ፡፡

ዘሌ 16፥12 በእግዚአብሔር ፊት ካለዉ መሠዊያ ላይ የእሳት ፍም አምጥቶ ጥናዉን ይሞላል፥ ከተወቀጠውም ከጣፋጭ እጣን እጁን ሙሉን ይወስዳል ወደ መጋረጃውም
ዉስጥ ያመጣዋል፡፡

ዘኁ 16፥7 ነገም በእግዚአብሔር ፊት እሳት አድርጉባቸው፥ ዕጣንም ጨምሩባቸው እንዲህም ይሆናል እግዚአብሔር የሚመርጠው እርሱ ቅዱስ ይሆናል እናንተ የሌዊ ልጆች
ሆይ እጅግ አብዝታችኀል ብሎ ተናገራቸው፡፡

ዘዳ 33፥10 ፍርድህን ለያዕቆብ፥ ህግህንም ለእስራኤል ያስተምራሉ ፤ በፊትህ ዕጣንን፥ በመሰዊያህም የሚቃጠል መስዕዋት ይሠዋሉ፡፡

መዝ 140፥2 ጸሎቴን በፊትህ እንደ እጣን ተቀበልልኝ ፥ እጅ መንሳቴም እንደሰርክ መስዕዋት ትሁን፡፡

ማቴ 2፥11 ወደ ቤትም ገብተው ህጻኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር እዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት ሣጥኖቻቸዉንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤን አቀረቡለት፡፡

ሉቃ 1፥10 በዕጣንም ጊዜ ህዝቡ ሁሉ በዉጭ ቆመውዉ ይጸልዩ ነበር፡፡

ራእ 5፥8 መጽሀፉንም በወሰደ ጊዜ አራቱ እንሰሶችና ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በበጉ ፊት ወደቁ፥ እያንዳዳቸም በገናንና የቅዱሳን ጸሎት የሆነ ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃ ያዙ፡፡

ራእ 8፥3 ሌላም መለአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሰዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለዉ በወርቅ መሰዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ
እጣን ተሰጠዉ

#ጽንሃ

ጽንሃ የእጣን ማሳረጊያ ወይም ማጠኛ ነው። ሦስት ሰንሰለቶች አሉት። ሰንሰለቶቹ ሶስት መሆናቸው የሚስጢረ ሥላሴ ምሳሌ ነው። በሰንሰለቶቹ ላይ ቢያንስ አስራ ሁለት (12) ቢበዛም ሃያ አራት (24) ሻኩራዎች ይኖሩታል።
‘’ሻኩራ’’ ማለት ሶስቱ ሰንሰለቶች ላይ ያሉት ክብ ነገሮች ናቸው። የሻኩራዎቹ ቁጥር አስራ ሁለት (12) መሆኑ የሐዋሪያት ምሳሌ ነው። ሃያ አራት (24) መሆኑ ደግሞ የሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ምሳሌዎች ናቸው ። ከስሩ እጣኑ የሚቀመጥበት ሙዳይ የመሰለ ክፍል የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ሲሆን: መለኮት ከሥጋዋ ሥጋ ነፍሱዋ ነፍስ ነስቶ ሰው መሆኑን ያመለክታል።  ፍሙ የጌታችን የመለኮትነቱ ምሳሌ ሲሆን እጣኑ እንደሚቃጠልና መዓዛው ሁሉን እንደሚያውድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ብዙዎች ኃጢያት ራሱን መስዋዕት በማድረግ አቅርቦ ዓለሙን ሁሉ ማዳኑን ያሳያል።
ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE

     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin
#ጻድቁ_አቡነ_ተክለሃይማኖት - #ነሐሴ_24

ነሐሴ ሃያ አራት በዚህችም ቀን ታላቅ የከበረ ሐዲስ ሐዋርያ የትሩፋትም መምህር የሆነ አባታችን ተክለሃይማኖት አረፈ። የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም ጸጋ ዘአብ የእናቱ ስም እግዚእ ኀረያ ነው እሊህም ቅዱሳን ለኢትዮጵያ የሃይማኖት ብርሃንን ላበሩ ካህናት ከወገኖቻቸው የሆኑ ናቸው። እግዚእ ኀረያም መካን ስለሆነች ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እያዘኑ ሲጸልዩ ኖሩ።

በዚህም ነገር እያሉ የዳሞት ገዥ ሞተለሚን ሰይጣን አነሣሣው የሸዋን አውራጃዎች እስከ ጅማ እስከ ገዛ ድረስ። የሀገር መኳንንቶችም በየተራቸው ሚስቶቻቸውን ይሰጡታል። ከማረከውም ደምግባት ያላቸውን ሴቶች ያገኘ እንደሆነ ቁባቶች ያደርጋቸዋል።

በዚያም ወራት ወደ ጽላልሽ ደርሶ ብዙ ክርስቲያኖችን ገደለ ከእርሳቸውም የሚበዙትን ማረከ ጸጋ ዘአብም ከግድያ ፍርሃት የተነሳ ሸሸ አንድ ወታደርም ተከተለው እርሱም ወደ ባሕር ተወርውሮ ገባ በእግዚአብሔርም ፈቃድ በባሕሩ ውስጥ ተሸሸገ።

ሚስቱን እግዚእ ኀረያንም ወታደሮቹ ማረኳት ወደ ሞተለሚም አደረሷት ባያትም ጊዜ ውበቷንና ላህይዋን አደነቀ በልቡም እጅግ ደስ ብሎት ብዙ ሽልማትን ጌጥን ሰጥቷት በሽልማትና በጌጥ ሁሉ ሸለማት አስጌጣትም የጋብቻ ሥርዓትንም ማዘጋጀት ጀመረ ለሠርጉም እንዲሰበሰቡ ወደመኳንንቶቹ ሁሉ ላከ።

እግዚእ ኀረያም ይህን በሰማች ጊዜ ከአረማዊ ጋር አንድ ከመሆን ያድናት ዘንድ በብዙ ልቅሶ ወደ እግዚአብሔር ጸሎትን አደረገች። ያን ጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በብርሃናዊ ክንፉ ተሸክሞ ከዳሞት አገር ወደ ምድረ ዞራሬ አድርሶ ወዲያውኑ ወደ ቤተ መቅደስ አስገብቶ በሴቶች መቆሚያ አቆማት። ባሏ ጸጋ ዘአብም ከማዕጠንት ጋራ በወጣ ጊዜ እንደተሸለመች ቁማ አያት አድንቆ በልቡ ይቺ ሴት ምንድን ናት ወደዚህስ ማን አመጣት አለ።

የማዕጠንቱንም ሥራ ጨርሶ ወጣ በጠየቃትና በመረመራት ጊዜ እርሷ ሚስቱ እግዙእ ኀረያ እንደሆነች አገኛት እርሷም ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው እግዚአብሔር ያደረገላትን ነገረችው።

ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ በአንዲት ሌሊት ተገለጠላቸው የዜናው መሰማት በዓለሙ ሁሉ የሚደርስ የተባረከ ልጅ ይወልዱ ዘንድ እንዳላቸው ነገራቸው አበሠራቸው።

ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ይህ ቅዱሱ ተፀንሶ በታኀሣሦ ወር በሃያ አራት ተወለደ በጸጋ ዘአብና በእግዚእ ኀረያ ቤታቸው ታላቅ ደስታ ሆነ ከዘመዶቻቸውና ከጐረቤቶቻቸው ጋራ ደስ አላቸው።

ለክርስትና ጥምቀትም በአስገቡት ጊዜ ፍሥሓ ጽዮን ብለው ሰየሙት። ሕፃኑም አደገ ድንቅ ተአምራትንም እያደረገ ዕውቀትንና ኃይልንም ተመልቶ በመነፈስ ቅዱስ ጸና።

ከዚህም በሗላ ዲቁና ይሾመው ዘንድ አባ ጌርሎስ ወደ ተባለ ጳጳስ ወሰዱት በዚያንም ዘመን በዛጔ መንግሥት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ብንያሚን ነበር። ወደ ጳጳሱም በአደረሱት ጊዜ ይህ ልጅ የተመረጠ ዕቃ ይሆናል ብሎ ትንቢት ተናገረለት። የዲቁና ሹመትንም ተቀብሎ ወደ ሀገሩ ተመለሰ።

ጐልማሳ በሆነ ጊዜ አራዊትን ሊያድን ወደ ዱር ሔደ። ቀትር ሲሆንም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልኩ የሚያምር ጐልማሳ አምሳል በቅዱስ ሚካኤል ክነፍ ላይ ተገለጠለትና እንዲህ አለው ወዳጄ አትፍራ እንግዲህ የኃጢአተኞችን ነፍስ ወደ ሕይወት የምታጠምድ ትሆናለህ እንጂ አራዊትን የምታድን አትሆንም ስምህም ተክለ ሃይማኖት ይሁን እንደ ኤርምያስና እንደ አጥማቂው ዮሐንስ እኔ ከእናትህ ማኀፀን መርጬ አከብሬሃለሁና እነሆ በሽተኞችን ትፈውስ ዘንድ ሙታንንም ታሥነሣ ዘንድ ሥልጣንን ሰጠሁህ ርኩሳን አጋንንትንም ከሁሉ ቦታ ታሳድዳቸዋለህ።

ወደ ቤቱም በተመለሰ ጊዜ ገንዘብን ሁሉ ለድኆችና ለምስኪኖች በተነ ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጠፋ ለሰው ምን ይጠቅመዋል እያለ ቤቱን እንደ ተከፈተ ትቶ ምርኩዙን ይዞ በሌሊት ወጣ።

ከዚህም በኋላ ወደ ጳጳስ ሔዶ የቅስና ሹመት ተቀብሎ ለሸዋ አገር ሁሉ ወንጌልን መስበክ ጀመረ። ዐሥራ ሁለት ሽህ ሦስት መቶ ነፍስ ያህል አጠመቀ ለጣፆት የሚሠውበትን ሁሉ ሻረ በውስጡ የሚኖሩ አጋንንት እስከሸሹ ድረስ ዐፀዶቻቸውን ሁሉ ቆረጠ።

ሁለተኛም ወደ ዳሞት ምድር ሔዶ ብዙ ሟርተኞችንና አስማተኞችን ጠንቋዮችን አሳመነ ከሀዲ ሞተለሚም ብዙ ወራት ተቃወመው በጉማሬ ማጥመጃ ውስጥ በመጨመር ብዙ ጊዜ ወደ ገደል ወረወረው እርሱ ግን በደኀና ይመለሳል ደግሞ ሊወጋው ጦር ወረወረ ጦሩም ተመልሶ እጁን ወግቶ ተጠመጠመበት በተሠቃየም ጊዜ አባታችንን ለመነው እርሱም የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አሳምኖ አዳነው የተጠመጠመበትንም ጦር ፈታለት ቀናውን መንገድ የሚያጣምሙ ሟርተኞችንም አጠፋቸው።

ከዚህም በኋላ በክብር ባለቤት ጌታችን ስም ያደረገውን ድንቅ ተአምራቱን አይተው የአገር ሰዎች ሁሉም ከንጉሣቸው ጋራ አመኑ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው ቤተ ክርስቲያንም ሠርቶላቸው የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት አስተማራቸው በቀናች ሃይማኖትም አጸናቸው ከዚህም ሁሉ ጋራ በጾም በጸሎት በስግደት ሁልጊዜ ያለ ማቋረጥ ተጠምዶ ይጋደል ነበር።

ዜናውንም ሰምተው ወደርሱ የሚመጡትን የነፍሳቸውን ድኀነት ያስተምራቸዋል የክብር ባለቤት የሆነ ጌታችን ኢየሱስን በማመን ያጸናቸዋል።

ከዚህ በኋላ በኤልያስ ሠረገላ ተቀምጦ ወደ አምሐራ ሀገር ሔደ በገድል ተጸምዶ ወደሚኖር መነኰስ ወደ አባ በጸሎተ ሚካኤል በአንዲት ቀን ደርሶ በዚያ እንደባሪያ ሲያገለግል ኖረ በአንድነት የሚኖሩ መነኰሳትንም ያገለግላቸው ነበር የሞተውንም እስከማንሳት ድረስ ከደዌያቸው ይፈውሳቸው ነበር።

በዚያም ዐሥራ ሁለት ዓመት ከሆነው በሗላ ሐይቅ በሚባል ቦታ ወደሚኖር ወደ ኢየሱስ ሞዓ የእግዚአብሔር መልአክ እንዳዘዘው ሔዶ ከእርሱም የምንኲስና ልብስ ቀሚስና ቅናትን ተቀበለ። ከዚያም ወደ ደብረ ዳሞ ሔዶ ለአቡነ አረጋዊ አራተኛ ከሆነ ከአባ ዮሐኒ ዘንድ ቆብንና አስኬማን ተቀበለ። ሁለተኛም ወደ ኢየሩሳሌም ሒዶ ከከበሩ ቦታዎችና ከሊቀ ጳጳሳቱ ቡራኬን ተቀበለ።

በዚያም ወደ ሸዋ ምድር ተመልሶ የአባቱ ወንድም ልጅ የሆነ አባ ዜና ማርቆስን አገኘው በወግዳ በረሀም በአንድነት ኖሩ ከዚያም ግራርያ ወደ ሚባል አገር ሒዶ በኮረብታ መካከል ዋሻ አዘጋጅቶ ተቀመጠ በቀንም በሌሊትም ከዚያ አይወጣም ነበረ ከጥቂት ቅጠልም በቀር እህልን አይቀምስም መጠጡም ጥቂት ውኃ ነው።

ብዙ ወንዶችና ሴቶች ወደርሱ መጥተው መነኲሳቶች ሆኑ በአንድ ቤት ውስጥ በአንድ መኝታ ላይ ተኝተው ያድራሉ እርስበርሳቸውም አይተዋወቁም እነርሱም እንደ ሕፃናት ናቸው በጸሎትና በቅዳሴ ጊዜም በአንድነት ይቆማሉ በዘመኑ ሰይጣን ሰለ ታሠረ ወንዱ ሴቷን ሴት እነደሆነች አያውቅም እንዲሁም ሴቷ ወንዱን ወንድ እንደሆነ አታውቅም።

በዚህም በኋላ መጠጊያ ሠርቶ በፊቱ በሗላው በቀኙ በግራው የተሳሉ ፍላጻዎችን ተከለ ይህንም ማድረጉ በመደገፍና በመተኛት እንዳያርፍ ነው በዚያም እግሩ ከቅልጥሙ እስቲሰበር ሰባት ዓመት ቆመ። በዚያም ወራት ምንም የዕንጨት ፍሬ ወይም ቅጠል ሳይቀምስ ውኃም ሳይጠጣ ኖረ።
ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርቶስ ወደርሱ መጣ ከእርሱም ጋራ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ደግሞ የከበሩ ነቢያትና ሐዋርያት ሁሉም ሰማዕታትና ጻድቃን የጳጳሳት አለቆች የመላእክት አለቆችም ከሠራዊቶቻቸው ጋራ አሉ።

መድኃኒታችንም እንዲህ አለው ወዳጄ ሆይ አንተ በመከራዬ መሰልከኝ እኔም በመንግሥቴ ከእኔ ጋራ እንድትመስለኝ አደርግሃለሁ። እነሆ የዚህ ዓለም ድካምህ ተፈጸመልህ በእኔ ዘንድም የምቀበለው ሆነ ከእንግዲህስ መንግሥተ ሰማያትን ትወርስ ዘንድ ና። እነሆ ስምህን ለሚጠራ መታሰቢያህን ለሚያደርግ ገድልህን ለሚጽፍ ለሚያነበውና ለሚሰማውም ቤተ ክርስቲያንህን ለሚሠራ በስምህ መባ ለሚሠጥ ለድኆችም በስምህ ለሚመጸውት በመታሰቢያህም ቀን ለሚቆርብ ስለ አንተ በጎ ሥራ ለሚሠራ ሁሉ እኔ እስከ ዐሥር ትውልድ እምርልሃለሁ።

አባታችንም እጅግ ደስ አለው ለጌታችንም ሰገደ ጌታችንም ከእርሱ ዘንድ በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ። ከዚህም በኋላ አባታችን በንዳድ በሽታ ታመመ ዕድሜውም ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከስምንት ወር ከአንድ ቀን ሆኖት በለመለመ ዕርጅና አረፈ። በመዘመርና በማመስገን አክብረው ገንዘው በዋሻው ውስጥ ቀበሩት።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳ በአባታችን ተክለሃይማኖት ጸሎት ይማረን። በረከቱም ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኅ_ነሐሴ)
ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE

     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin
በየቀኑ እነዚህን አምስት(5) ጸሎቶች ይጸልዩ

እግዚአብሔርን በጸሎት የምንጠይቅባቸው ልዩልዩ ጉዳዮችና ምክንያቶች ቢኖሩም እንዚህን አምስት የጸሎት ክፍሎች ግን አዝወትሮ መጸለይ ይገባል።

1.  የምስጋና ጸሎት:- ስላለፈው ትናንትና፣ ስላለህበት ዛሬ፣ በተስፋና በእምነት ስለምንጠብቃት ነገ ማመስገን ይገባል። “ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ በእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና።” 1ተሰሎንቄ 5:17

2.  አቅጣጫ/ምሪት ለመቀበል:- ተመሳሳይ ሕይወትን ላለመምራት /ሁልጌዜ ያለንሰሐ ከመመላለስ ለመጠበቅ/፣ በየቀኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ በጎ ምሪት/አቅጣጫ ለመቀበል እርሱ ቅዱሳኑን በራሱ መንገድ እንዲመራቸው እኛንም እንዲመራን መጸለይ አስፈላጊ ነው። “አቤቱ መንገድህን ምራኝ በእውነትህም እሄዳለሁ”። መዝ-86:11

3.  ለጤንነትና ለመለኮታዊ ጥበቃ:-በየቀኑ ጤንነታችን እንዲጠበቅ፤ እንዲሁም ከምታዩትና ከማታዩት  የክፉ ፍላጻ እንድንሰወር መጸለይ አስፈላጊ ነው። “ከቀስትህ ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩህ ምልክትል ሰጠሃቸው።” መዝ-60:4

4.  እግዚአብሔር እንዲጠቀምብን:- በየአንዳንዱ የሕይወት አጋጣሚ ውስጥ እግዚአብሔር ቅዱሳንን እንደተጠቀመባቸው እኛንም እንዲጠቀምብን መጸለይ አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም በየአንዳንዱ የምድር ጥያቄ የእግዚአብሔር መልስ ያለው በእኛ ውስጥ ነው።

5.   ጥበብ እንዲሰጠን:- መለኮታዊ ጥበብን ለማግኘት ውስጣችን በንሰሐ ክፍት መሆን አለበት። በዚህ ጥበብ ለመሞላትም ዘውትር መጸለይ አለብን። “ከመካከላችሁ ጥበብ የጎደለው ሰው ቢኖር እግዚአብሔርን በጸሎት ይጠይቅ፤ እግዚአብሔር ለሚጠይቁት ሁሉ ቅር ሳይሰኝ በደስታ የሚሰጥ ቸር አምላክ ስለሆነ።” ያዕቆብ 1:5

ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE

     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin
#ሰውን_የሚጥለው_መመካቱ_ነው

ወንድሜ ሆይ በሥራህ ሁሉ የታመንህ ሁን አገልጋይ ባልንጅሮችህን ውደዳቸው። ንጹሑን አረጋዊ መቼም መች አክብረው።

ወንድሜ ሆይ በታላላቆች መሃል አትቀመጥ። ተቀመጥ እስኪሉህ ድረስ ቁም እንጅ በሽማግሌዎች መካከል አትቀመጥ፤ በዝቀተኛው ማዕርግ ተቀመጥ እንጅ።

ወንድሜ ሆይ ቁጡ ወይም አንጎራጓሪ አትሁን፤ በጸሎት ጊዜ ሐኬተኛ አትሁን፤ በጸሎት ጊዜ ምንም ተግባር ለመፈጸም ወዲያና ወዲህ አትናወጽ። እንዳትዋረድ በሊቅ በአዋቂ መሃል አትናገር።

ልጄ ሆይ በጽድቅህ አትመካ፤ ራስህን አታመስግን፤ ሰይጣን ትምክሕትን እንዳያመጣብህ ራስህን በፈቃድህ አዋርድ እንጅ። በትዕቢትና ትምክሕት ሰዶምና ገሞራ ወደቁ። ከእግዚአብሔር መንገድም ተሰናከሉ። ትምክሕተኛውን መነኩሴ ፈተና ያገኘዋል፤ መንፈስ ቅዱስም ይለየዋል፤ የዲያብሎስ መንፈስም ያድርበታል። በሥራችሁ ሁሉ አትመኩ፤ ሁሉም ሰው እግዚአብሔር የሰጠውን ይሠራል እንጅ ከራሱ የሆነ ምንም የለምና። ነቢይ የተናገረውን አልሰማችሁምን? ፈጽማችሁ አትመኩ ታላላቅ ነገርንም አትናገሩ፤ ክፉ ነገርም ከአንደበታችሁ አይውጣ

ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE

     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin
#ሰውን_የሚጥለው_መመካቱ_ነው

ወንድሜ ሆይ በሥራህ ሁሉ የታመንህ ሁን አገልጋይ ባልንጅሮችህን ውደዳቸው። ንጹሑን አረጋዊ መቼም መች አክብረው።

ወንድሜ ሆይ በታላላቆች መሃል አትቀመጥ። ተቀመጥ እስኪሉህ ድረስ ቁም እንጅ በሽማግሌዎች መካከል አትቀመጥ፤ በዝቀተኛው ማዕርግ ተቀመጥ እንጅ።

ወንድሜ ሆይ ቁጡ ወይም አንጎራጓሪ አትሁን፤ በጸሎት ጊዜ ሐኬተኛ አትሁን፤ በጸሎት ጊዜ ምንም ተግባር ለመፈጸም ወዲያና ወዲህ አትናወጽ። እንዳትዋረድ በሊቅ በአዋቂ መሃል አትናገር።

ልጄ ሆይ በጽድቅህ አትመካ፤ ራስህን አታመስግን፤ ሰይጣን ትምክሕትን እንዳያመጣብህ ራስህን በፈቃድህ አዋርድ እንጅ። በትዕቢትና ትምክሕት ሰዶምና ገሞራ ወደቁ። ከእግዚአብሔር መንገድም ተሰናከሉ። ትምክሕተኛውን መነኩሴ ፈተና ያገኘዋል፤ መንፈስ ቅዱስም ይለየዋል፤ የዲያብሎስ መንፈስም ያድርበታል። በሥራችሁ ሁሉ አትመኩ፤ ሁሉም ሰው እግዚአብሔር የሰጠውን ይሠራል እንጅ ከራሱ የሆነ ምንም የለምና። ነቢይ የተናገረውን አልሰማችሁምን? ፈጽማችሁ አትመኩ ታላላቅ ነገርንም አትናገሩ፤ ክፉ ነገርም ከአንደበታችሁ አይውጣ

ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE

     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin
🌺 አባቶቻችን እንዲህ አሉ 🌺

🍀"በኃጢአት በወደቅህ ጊዜ ተስፋ ቆርጠህ ጸሎትህን እንዳታቆም። ንስሓ እስከምገባ ድረስ ብለህ ጸሎት ካቆምክ መቼም ንስሓ አትገባም። ምክንያቱም ጸሎት ራሱ የእውነተኛ ንስሓ መግቢያ በር ነው" ቅዱስ ቄርሎስ ሳድሳዊ

🌺"ሰዎች አንድ ሰው ተነሥቶ ሌላውን ሲገድል ወንጀለኛ ነህ ይሉታል። አንድ ላይ ተሰባስበው ብዙ ሰዎችን ሲገድሉ ግን ውጊያ ይሉትና መግደላቸውን ጀግንነት ይሉታል" ቅዱስ ቆጵሮሳዊ

🍀"ሰዎች የሚያብዱበትና እንደነሱ ያላበደ ሰው ሲያዩ "እንደኛ ስላልሆንክ አብደሃል" የሚሉበት ዘመን ይመጣል"
ቅዱስ እንጦንዮስ

🌺"መካሪ አያስፈልገኝም የማለትን ያህል ታላቅ ትዕቢት የለም"
ቅዱስ ባስልዮስ

🍀"ይህንን ካስታወስክ በሰው መፍረድ ታቆማለህ:: ይሁዳ ሐዋርያ ነበር:: ከጌታ ቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ ነፍሰ ገዳይ ነበር" ቅዱስ ዮሐንስ ዘሰዋስው

🌺"የክርስቲያኖች መሣሪያ በእጃቸው ሰይፍን መታጠቅ ሳይሆን እጃቸውን ወደላይ ለጸሎት መዘርጋት ነው"
ቅዱስ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያ

🍀"እግዚአብሔር ለአብርሃም "ከሀገርህ ውጣ ከወገኖችህ"ተለይ ብሎት ነበር። በዚህ ጥሪ እግዚአብሔር ሁላችንንም የተወለድንበት ዘር እንድንተው ይጠራናል። ሰማዕቱ ዮስጦስ (100 AD-165 AD)

🌺"ክርስቶስ ጴጥሮስን "ሰይፍህን ወደ ሰገባው አስገባ" ሲለው ትጥቅ ያስፈታው ጴጥሮስን ብቻ ሳይሆን እንደ ጴጥሮስ በእርሱ የሚያምኑትን ሁሉ ነበር" ሊቁ ጠርጡለስ (160 AD - 220 AD)

🍀‹‹ይጸልያል ነገር ግን የሌሎችን ጸሎትም ይሰማል፡፡ ያለቅሳል የሌሎችን ዕንባ ግን ያብሳል፡፡ ሰው ነውና አልዓዛር ወዴት እንደተቀበረ ጠየቀ፡፡ አምላክ ነውና አልዓዛርን ከሞት አስነሣ፡፡ እርሱ በርካሽ ዋጋ ያውም በሠላሳ ብር ብቻ ተሸጠ፡፡ ነገር ግን ዓለምን በውድ ዋጋ በከበረ ደሙ ገዛ፡፡ እንደ በግ ለመታረድ ተነዳ እርሱ ግን የእስራኤል እረኛ የዓለምም ሁሉ ጠባቂ ነበረ፡፡ እንደ በግ ዝም አለ ነገር ግን እርሱ በምድረ በዳ በሚጮኽ ሰው ድምፅ የተሰበከ ቃል ነበር፡፡ እርሱ የተሰቃየና የቆሰለ ነበር ፤ ሁሉንም በሽታና ቁስል ግን ይፈውስ ነበር››
🌺ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ🌺

🍀"ለቤተ መቅደስህ ተክል ያደረግኸኝ፡፡ አቤቱ ሆይ የውጭ ተክል አታድርገኝ፡፡ የጽድቅ ተክል አድርገኝ፡፡ የኃጢአት አይደለም፡፡ የዕውነት ተክል አድርገኝ የሐሰት አይደለም የፍቅር ተክል አድርገኝ የጽል አይደለም፡፡
የመጻሕፍት መጀመሪያ የምትሆን ኦሪት ደመና የምትጋርደኝ፡፡ ከቅዱስ ወንጌል ፈሳሽ የምጠጣ ከጎንህ ከፈሰሰው ደም የምረካ ልሁን፡፡ በናትህ በድንግል ጸሎት የሃይማኖት አበባ ላብብ፡፡ የጽድቅ ፍሬን ላፍራ ከቅዱሳንህ ሐዋርያትም ከቃላቸው ፍሬ የተነሣ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ የተባረከ የወይን ቦታ ልባል የጽድቅን ፍሬ የሚያስቀረውንም የኃጢአት እሾህ ጠምዝዘው ከደጁም አሜከላውን አረሙንም ሙጃውንም ንቀለው፡፡ አቤቱ ከኔም አርቀው ሥርዓትህን የሚሠሩትን ያበባቸውን ፍጻሜ እንዳፈራ አድርገኝ"
🌺ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ🌺

🕊ወስብሐት ለእግዚአብሔር🕊
ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE

     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin
+ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ አለ +

አንድ ሰው እኔ ክርስቲያን ነኝ ሲል በአንድ ቃል ዜግነቱንና ቤተሰቡን ሥራውን ጠቅልሎ ተናገረ ማለት ነው:: የሚያምን ሰው ከሰማያዊት ኢየሩሳሌም በቀር ምድራዊ ከተማ የለውም"

🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯

"እግዚአብሔር የሚጠይቅህ ጥቂት ነው የሚሠጥህ ግን ብዙ ነው

🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯

"የዚህ ዓለም ኑሮ እንደ እንቅልፍ ነው:: በዚህ ሕይወት የሚሆኑት ሁሉ ሕልም ናቸው::
በሕልምህ ባለጸጋ ብትሆን ምን ጥቅም አለው? በእንቅልፍ ልብ ሆኖ በቅዠት የሚናገር ሰው ስለ ንግግሩ አይፈረድበትም:: እኛ ግን በዚህ የእንቅልፍ ዘመን የምንናገረው ሁሉ የዘላለም ሕይወትን ሊያሳጣን ይችላል"

🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯

"በድህነት እና በረሃብ የሚሰቃዩ ሰዎች እንደ ሠለስቱ ደቂቅ ናቸው:: ከድህነት የበለጠ ምን እሳት አለ? ከረሃብስ የሚበልጥ ምን ነበልባል አለ?
ሦስቱ ወጣቶች እሳት ውስጥ ሆነው እንደዘመሩ በመከራ ውስጥ ሆኖ ፈጣሪን የሚያመሰግን ሰው የመከራው እሳት ውኃ ይሆንለታል:: ለድሆች ምጽዋትን የሚሠጥ ሰው ደግሞ ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት የታደገውን የእግዚአብሔር መልአክን ይመስለዋል"

🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯

በትንንሽ ነገሮች ማመስገንን ከለመድህ ትንንሽ ነገሮች ብዙ ስለሆኑ ሕይወትህ ምስጋና ይሆናል"

🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯

በኀዘን ጊዜ የማያጉረመርሙ ከንፈሮች ከቅዱሳን ሰማዕታት እኩል ናቸው

🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯

ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE

     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin
ጳጉሜን

የጳጉሜን ወር ዕለተ ምጽአት የሚታሰብበትም ወር ነው በቅድስት ቤተክርስቲያን ካሉት ሁለት የፈቃድ አጽዋማት መካከል አንዱ በዚህ በጳጉሜ ወር የምንጾመው የፈቃድ ጾም ነው፡፡

ጳጉሜን ማለት ጭማሪ ማለት ነው፡፡ ይህም በዓመቱ መጨረሻ ላይ አምስት ወይም ስድስት ቀን በመሆን የምትመጣ ናት፡፡ በአራት ዓመት አንዴ ማለትም በዘመነ ሉቃስ ጳጉሜን ስድስት ቀን ይሆናል፡፡ በዚህም ሐገራችን ኢትዮጵያ የአስራ ሦስት ወራት ጸጋ / Thirty months of sunshine / በመባ ትታወቃች ትለያለች፡፡ ጳጉሜ በዘመነ ዮሐንስ መግቢያ በዘመነ ሉቃስ ማብቂያ  ስድስት በምትሆንበት ጊዜ ጾመ ነቢያት / የገና ጾም/ ህዳር 15 ቀን ይገባና ታህሳስ 28 ቀን ጾሙ ተፈቶ የልደት በዓል

በቅድስት ቤተክርስቲያን ካሉት ሁለት የፈቃድ አጽዋማት መካከል አንዱ በዚህ በጳጉሜን ወር የምንጾመው የፈቃድ ጾም ነው፡፡ ይህም ጾመ ዮዲት በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ግን እንደ አንደኛው የፈቃድ ጾም /ጽጌ ጾም/ በብዙዋኑ ዘንድ የታወቀ አይደለም፡፡ የዮዲት ጾም የሚባለውም እርሷ ስለ ጾመችው ነው፡፡ እዚህ ላይ ዮዲት ተብላ የተጠቀሰችው በቤተክርስቲያን ታሪክ ትምህርት ላይ በጥፋት ሥራዋ በተደጋጋሚ የምትጠቀሰው ዮዲት ጉዲት እንዳልሆነች ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡ ወደ ታሪኩ ስንመለስ የፋርስ ንጉስ ናቡከደነጾር በሠራዊቱ ተመክቶ ሹም ጠላት አጥፋ ድንበር አስፋ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበልህ ያላመነውን እያሳመንህ ና ብሎ ለጦር አበጋዙ ለሆሎፎርኒስ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ዮዲ 2፥2-7፡፡ እርሱም እንደታዘዘው በኃይላቸው የታመኑ 12ሺህ እግረኞችንና በፈረስ የተቀመጡ 12ሺህ ጦረኞችን እየመራ ዘምቶ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበለ ያላመነውን እያሳመነ ብዙ ሀገሮችን እያጠፋ ሲሔድ ከአይሁድ ከተማ ደረሰ በዚህም ብዙ ጥፋ በመድረሱ የእስራኤል ልጆች አለቀሱ፡፡ ዮዲት ባሏ ሞቶባት ከወንድ ርቃ ንጽሕናዋን ጠብቃ በጾም በቀኖና በሀዘን ተወስና ትኖራለች በተፈጠረው ጥፋት ህዝቡ ላይ ለመጣው መከራ ማቅ ለብሳ በራስዋ ላይ ትብያ ነስንሳ ወደ እግዚአብሔር አለቀሰች፡፡

የፍጥረቱን ጥፋት የማይሻ እግዚአብሔር አምላክም ሕዝቡን የሚያድኑበትን መንገድ ለመጠየቅ ሱባኤ በገባች በሦስተኛው ቀን ገለፀላት፡፡ዮዲ 8፥2 ፡፡ ከዚህ በኋላ ጠላታቸውን በዮዲት ምክንያት እስራኤላውያን እስከ ዮርዳኖስ እየተከተሉ አጥፍተዋቸዋል፡፡ ዮዲት ጠላቷን ለማጥፋት የቻለችው በጾምና በጸሎት ከእግዚአብሔር አምላክ ኃይል አግኝታ ነው፡፡ ስለዚህ ምዕመናን ጥንተ ጠላታችን ሰይጣንን ፈቃደ ሥጋን ለማሸነፍ በጾም ከፈጣሪያችን ኃይልን መጎናጸፍ አለብን ብለው ጳጉሜን በፈቃድ ይጾማሉ፡፡

የጳጉሜን ወር ዕለተ ምጽአት የሚታሰብበትም ወር ነው፡፡ ይህም ጳጉሜ የዓመታት መሸጋገሪያ ጨለማው የክረምት ወቅት ወደ ማብቂያው የምናልፍባት እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ከጊዜያዊው ወደ ዘላለማዊ ከምድራዊ ወደ ሰማያዊ ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው መሸጋገሪያ ነውና ነው፡፡
ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE

     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin09
#ያለፈውን_መርሳት

በህይወታችን ብዙ ውጣ ውረዶችን አይተናል። ብዙ ትዝታዎች አሉን። ብዙ ልምዶችን ገንብተናል። ነገር ግን ትዝታችን ወደ ኋላ እየመለሰ ያስቸግረናል። ወደ ፊት ከመጓዝ ይልቅ በድሮው ተውስታ መኖር እንመርጣለን። ይህ ደግሞ ይጎዳናል። ስለሆነም እንዴት ያለፈውን እንርሳ?

በሰራነው ክፉ ስራ ጥፋተኛ መሆናችንን ማወቅ አለብን ይህ ደግሞ ወደ ፊት እንድንሄድ ሊያደርገን ይገባል። ወደ ፊት እንድንሄድ ማድረግ ካልቻለ በራሱ ሌላ ውድቀትን ሊያመጣ ይችላል። አዋ ኃጢአትን ፈፅሚያለሁ፣ አዋ ስህተትን አድርጊያለሁ፣ አዋ ህይወቴ ፈፅሞ መንገዱን ስቷል

ያም ሆኖ እግዚአብሔር አሁንም ይወደኛል። ፈፅሞ አይተወኝም።   ሊተወኝ አይፈልግም። እኔ ከእርሱ ብርቅም እርሱ ግን ሊርቀኝ አይፈልግም ከእኛ ደኅነት በስተቀር እግዚአብሔር ሌላ የሚፈልገው ነገር የለም።

በክርስቶስ አዲስ ሰው መሆን አለብን።  አሮጌውን ሰው ትተን አዲሱን ሰው ተላብሰን ወደ ፊት መራመድ ይኖርብናል "ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው" የሚለውን ቃል በጥንቃቄ እንየው። ሁሉም እንጂ የተወሰኑት ብቻ አይልም።

በመጀመሪያ በእውቀት መታደስ ያስፈልጋል። ስለ እግዚአብሔር ማወቅ አለብን።  ያን ጊዜ የድክመቶቻችንን ቀናት መርሳት እንችላለን በኃጢአት በሪያ የሆኖንበትን ጊዜ መላቀቅ እንችላለን። የቁጣ፣ የሕመም፣ የኃጢአት፣ የጉስቁልና የድክመት ዘመንን አልፈን ወደፊት መጓዝ ይኖርብናል።

ይህን ደግሞ በክርስቶስ እንችለዋለን። ስለዚህ በኃጢአት ምክንያት በባርነት ውስጥ ሆነን  የቀድሞውን እያሰብንና እያደረግን ረጅም ጊዜ ማሳለፍ የለብንም። ከዚህ ህይወት ወጥተህ ከእኔ ጋር ሆነህ ወደ ፊት ተራመድ ይላልና እግዚአብሔር።

ከእርሱ ጋር ከሆንን ያበረታናል፣  ይመራናል።  ከምድረ በዳ ወጥተን በገነት እንኖራለን፣ ከኃጢአት ወጥተን ወደ  ፅድቅ አንራመዳለን፣ ከሞትና ከጨለማ ወጥተን ወደ ብርሃን አንነጓዛለን።
ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE

     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin
[ጳጉሜን 3 በዓሉ የሚከበርለት የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሩፋኤል ታሪክ]
በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
ቅዱስ ሩፋኤል ቊጥሩ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት ሲኾን፤ ሩፋ ማለት ሐኪም፤ ኤል ማለት እግዚአብሔር ማለት ሲኾን ሩፋኤል ማለት “እግዚአብሔር ሐኪሜ ነው” ማለት ነው፤ ሄኖክም “በሰው ቁስል ላይ የተሾመ ከከበሩ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነው” ይለዋል (መጽሐፈ ሄኖክ 6፥3)::

ይኽ መልአክ በራማ ሰማይ ያሉ ነገደ መናብርትን የሚመራቸው ነው፡፡ ነገደ መናብርት ያላቸው ቅዱስ ሩፋኤል የሚመራቸው በራማ ሰማይ የሚኖሩ ነገደ መላእክት ናቸው፡፡

ቅዱስ ኤጲፋንዮስም በሥነ ፍጥረት መጽሐፉ ላይ “ወለዳግም ጾታ ዐሠርቱ ስሞሙ መናብርት ወሊቆሙ ሩፋኤል እሉ እሙንቱ እለ ይቀልል ሩጸቶሙ እምነፋስ ወእለ ይጸውሩ ወላትወ መብረቅ ወኲናተ እሳት ዘይነድድ ወአንበሮሙ በዳግሚት ሰማይ” ይላል በራማ ሰማይ የሚገኘውን ኹለተኛውን ዐሥሩን ነገድ መናብርት ሲላቸው አለቃቸው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፤ እነዚኽም ረቂቅ የኾነ የመብረቅ ጋሻ የእሳት ጦር ይዘው ከነፋስ ይልቅ የፈጠኑ ሲኾኑ በራማ በኹለተኛው ክፍል ላይ አስፍሯቸዋል፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል ከሚመራው ከዚኽ ነገድ 24ቱ ካህናተ ሰማይ ወጥተዋል፡፡

አባ ጊዮርጊስም በሰዓታቱ ላይ ስለነዚኽ መላእክት ፡-

“ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ጽርሐ አርያም ማኅፈዱ
መካነ ትጉሃን ዐጸዱ ካህናተ ሰማይ ቅዉማን በዐውዱ አክሊላቲሆሙ ያወርዱ ቅድመ መንበሩ እንዘ ይሰግዱ ይርዕዱ ወኢይዝብጦሙ ሶበ ይበርቅ ነዱ”

(ጽርሐ አርያም አዳራሹ፤ የትጉሃን መኖሪያ ቦታው የሚኾን እግዚአብሔር ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ተብሎ በአንድነት በሦስትነት ይመሰገናል፤ ካህናተ ሰማይ በዙሪያው ይቆማሉ፤ በዙፋኑ ፊት እየሰገዱ አክሊሎቻቸውን ያወርዳሉ፤ እሳትነቱ (ባሕርዩ) በሚበርቅ፣ ወገግ በሚል ጊዜ እንዳይመታቸው ይንቀጠቀጣሉ) ይላል

ሊቁ እንደጠቀሰው በዕለተ እሑድ ሥሉስ ቅዱስ ሰባቱን ሰማያት ፈጥረዋል፤ ከዚያም ልዑል እግዚአብሔር በዕለተ እሑድ ሰባቱን ሰማያት ከፈጠረ በኋላ ሊቁ በአክሲማሮስ እንደገለጸው ከቅዱሳን መላእክት መኻከል፡-

“ወእምዝ ነሥአ እግዚአብሔር እምሰራዊተ ሩፋኤል ፳ወ፬ተ ሊቃናተ ወአቀሞሙ ዐውደ መንበሩ፤ ወሰመዮሙ ለእሙንቱ ካህናተ ሰማይ ወወሀቦሙ ማዕጠንታተ ዘእምወርቀ እሳት ወአክሊላተ ብርሃን ዘእምጳዝዮን ወአብትረ ዘከተማሆን መስቀል ወአልበሶሙ አልባሰ ክህነት” እንዲል ከሰራዊተ ሩፋኤል ፳፬ት ሊቃናትን መርጦ በመንበረ ስብሐት በመጋረጃዋ ውስጥ ዙሪያዋን ክንፍ ለክንፍ ገጥሞ አቁሟቸዋል (ሕዝ ፩፥፲፩-፲፪)።

ቊጥራቸውን ኻያ አራት ማድረጉ በኻያ አራቱ ጊዜያት ጸልየው ሌላውንም ራሳቸውንም ጠብቀው ዋጋቸውን ተቀብለው የሚኖሩ በመኾናቸው ሲኾን እነዚኽንም መላእክት “ካህናተ ሰማይ” ሲላቸው የእሳት የወርቅ ጽና ሲያሲዛቸው የብርሃን አክሊል ጳዝዮን የሚባል የብርሃን ዘውድ ደፍቶላቸዋል፤ የብርሃን ዘንግ ማኅተሙ መስቀል የኾነ ሲያሲዛቸው የብርሃን ካባ ላንቃ ሕብሩ መብረቅ የመሰለ አልብሷቸዋል ( ራእ ፬፥፬-፭፤፲-፲፩)።

እነዚኽ ከሰራዊተ ሩፋኤል የወጡ ሰማያውያን ካህናት በአንድ ላይ ባጠኑ ጊዜ ዛሬ በክረምት ጊዜ ጉም ተራራውን እንደሚሸፍነው ከማዕጠንታቸው የሚወጣው ጢስ መልኩ መብረቅ፣ ድምፁ ነጐድጓድ፣ መዐዛው መልካም የኾነና ጽርሐ አርያም፣ መንበረ መንግሥት የተባሉትን የብርሃን ሰማያት የሚሸፍንና የሚጋርድና ከጢሱ ጋር የቅዱሳን ጸሎት ዐብሮ ወደ እግዚአብሔር ፊት ይወጣል።

“ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሠዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሠዊያ ላይ ለቅዱሳን ኹሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ” እንዳለ ዮሐንስ በራእዩ (ራእ ፰፥፫-፭)፡፡

ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በአክሲማሮስ ላይ “ወቦ ኪሩቤል ይቀውሙ በየማን በአምሳለ ቀሳውስት ወሱራፌል ይቀውሙ በአምሳለ ዲያቆናት ወድኅሬሆሙ ካህናተ ሰማይ ወቦ እልፍ አእላፋት ወትእልፊተ አእላፋት መብረቅ ወነጐድጓድ ወሠረገላሆሙኒ ምሉኣነ አዕይንት” እንዳለ
★ ኪሩቤል በቀኝ ሱራፌል በግራ ከፍ ብለው የሩፋኤል ሰራዊት ካህናተ ሰማይ ክንፍ ለክንፍ ገጥመው በስተኋላቸው ሲታዩ በሰማይ ውዱድ ዙሪያ እልፍ አእላፋት መብረቅ፣ ነጐድጓድ፣ ሠረገላ፣ እንደ መስታየት ብሩህ የኾነ ሲኖርበት እነዚኽ ቅዱሳን መላእክትም ሳያቋርጡ “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር” እያሉ ፈጣሪያቸውን በአንድነቱ በሦስትነቱ ያመሰግኑታል (ራእ ፬፥፰)፡፡

ይኽ መልአክ ሩፋኤል ጦቢትን የተራዳ መልአክ ነው፤ ይኽ ጦቢት ዐሥሩ ነገድ በ፯፻፳ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ሲማረኩ ዐብሮ የተማረከ ጻድቅ ሰው ነው፤ ይኽ ሰውን በመርዳት በደግነቱ የታወቀው ጦቢት ከመንገድ ወድቆ የተገኘ በድን ቀብሮ፤ በዚያው ሌሊት ከቅጥሩ አጠገብ ፊቱን ተገልጦ ተኝቶ ሳለ አዕዋፍ ትኩስ ፋንድያ ዐይኑ ላይ ጥለውበት እንደ ብልዝ ያለ ወጥቶበት ዐይኑ ጠፋ፤ ሚስቱም ባለማስተዋል “አይቴ ውእቱ ምጽዋትከ ወጽድቅከ” (በጐነትኽ ምጽዋትኽ ያዳነኽ ወዴት ነው?) በማለት በተናገረችው ጊዜ ዐዝኖ ሞትን ተመኘ (ጦቢ ፪፥፲፬)፡፡

ያን ጊዜ መልአኩ ሩፋኤል ባሎቿ ስለሞቱባት ቤተሰቦቿ ያንቋሽሿት የነበረችውን የራጉኤል ልጅ ሳራን ለማዳን ተልኮ በመምጣት አስቀድሞ በርሷ ላይ ዐድሮ ባሎቿን ይገድልባት የነበረውን ጋኔን አስወጥቶላት የጦቢት ልጅ ጦብያ እንዲያገባት አድርጓል፤ በዚኽም “ፈታሔ ማሕፀን” ተብሏል "ለሰብእ ወለእንስሳ ፈታሔ ማሕፀኖሙ አንተ" እንዲለው፡፡

በኋላም ወደ ጦቢት በመኼድ ረዥም ዘመን የታወረ ዐይኑን አብርቶለት “አነ ውእቱ ሩፋኤል መልአክ አሐዱ እምነ ሰብዐቱ ቅዱሳን መላእክት” (ከሰብዐቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሩፋኤል እኔ ነኝ) ብሏቸው ተሰውሯል (ጦቢ ፲፪፥፲፭)፡፡

በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ ተጻፈ
[የቅዱስ ሩፋኤል በረከት ይደርብን]

ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                      •➢ ሼር // SHARE

     🔸 @dr_zebene_lemma
🔸🔹🔸 @dr_zebene_lemma
     🔸 @dr_zebene_lemma

✍️Comment @Channel_admin
2025/07/06 17:02:59
Back to Top
HTML Embed Code: