Telegram Web Link
#30ዎቹ_ባለውለታዎች| እያሉ እናክብር| እንዳንቆጭ
#hawassa| ዘውትር ሐሙስና እሁድ
|ባለውለታዎቻችን_የት_በምንሁኔታ_ውስጥ_ናቸው?|
    አንድ ማሻሻል ያለብን ጉዳይ አለ። ሰው በህይወት እያለ ላበረከተው አስተዋፅኦ ክብር፣ እውቅናና ምስጋና ከማቅረብ ይልቅ፤ ሲለዩን ስለማንነታቸው የመጎሰም ልማድ ነው። ይህ ለተለየን ሰው ምን ፋይዳ አለው?
    ይህ ማህበራዊ ሚዲያ ከተቋቋመ ጀምሮ የሰሩትን ማመስገን፤ የሚሰሩትን ማበረታታት፣ የመሳሰሉ መልካም እሴቶችን ለማዳበር ጥረት ያደርጋል። ሁሉም በፈጣሪና በናንተ ቀናነት ተሳክቶ ብዙዎችን አፍርተናል።
   
     በስራቸው ሃገርን፣ ትውልድን እና ተቋማትን የታደጉ እድሜና ህመም ገድቧቸው በየቤታቸው የከተሙ ባለውለታዎችን በልጅ ወግ ልንጎበኝ፣ ታሪክና ተሞክሯቸውን ልንዘክር፣ ከወዳጆቻቸው ጋር ለማገናኘትና ዋጋቸው ምንኛ ታላቅ እንደሆነ ለማሳየት #30_ዎቹ_ባለውለታዎች በሚል የመጀመሪያ ዙር የምስጋና ፕሮግራም አሰናድተናል።
    አዎን የሰራ ሲከበር፣ ለራስ ደስታን፣ ለቤተሰብ ኩራት ለሚሰራ ትውልድ መነሳሳትን ይፈጥራልና አብራችሁን ስለሆናችሁ ከልብ ለማመስገን እንወዳለን።
    የመጀመሪያዎቹን 30 ባለውለታዎች ከዚህ ቀደም ከናንተ ባገኘነው ጥቆማ መሰረት በማድረግ እኛም ከተለያዩ ምንጮች ባሰባሰብነው መረጃ በህይወት ያሉ አባትና እናቶች ተመርጠዋል። ይሁን እንጅ በከተማችን በርካታ ባለውለታዎች ከተለያየ መስክ በመኖሩ የመጀመሪያው ዙር እንዳበቃ በሁለተኛው ዙር የሚካተቱ ይሆናል።
     እነማን የሚለውን እና ታሪካቸውን ጭምር በቅርብ ቀን (ታህሳስ 7 እሁድ) ወደናንተ የምናቀርብ ይሆናል።
    ለዚህ ዝግጅት በገንዘብ፣ በሐሳብ፣ መረጃ በመስጠት አብረውን ለነበሩ እናመሰግናለን። እንዲሁም በቤታቸው ስንሄድ አላማችንን ተረድተው በክብር ላስተናገዱንና ታሪካቸውን ለትውልድ በማጋራት ለተባበሩን የባለውለታዎቻችን ቤተሰብና ባለውለታዎቻችንን ከልብ እናመሰግናለን።
  ይህን እቅዳችንን ስንነግራቸው በባህር ማዶ ኑሯቸውን ያደረጉት (ፍቅሩና ጓደኞቹ) ቅን የከተማችን ልጆች የዛሬ አመት ነበር አፋጣኝ ምላሽ የሰጡን። እኛም እነዴት መስራት እንዳለብን ከእናንተም ከአዋቂ አባቶችም ባገኘነው መረጃ ብንሰናዳም ወቅቱ አልፈቀደም ነበር። በዚህ መሐልም ጥቂት የማይባሉ በድንገት ተለይተውናል። አሁንም አልረፈደምና ቀኑ ደርሶ የመጀመሪያ ዙር 30 በህይወት ያሉ ባለውለታዎቻችንን ቤት ለቤት በመሔድ አክብሮታችንን በመላ የከተማችን ነዋሪ ስም እናበረክታለን። ታላላቆቻችንን ጠርተን ሳይሆን እኛው በቤታቸው በድንገት እንከሰታለን። 
     ውድ የሐዋሳ ትዝታ ቤተሰቦች ለዚህ ዝግጅት ስምረት በሐሳብ፣ ስጦታዎችን በማቅረብ እንዲሁም ፍቅርና ምስጋናዎቻችንን ለማቅረብ አብራችሁን ትሆኑ ዘንድ በድጋሚ ለማስታወስ እንወዳለን። አዎን ፍቅራችንን ዛሬ እንግለፅ፤ እንዳንቆጭ!
    ለመሳተፍ የምትፈልጉ እንዲሁም አብራችሁን ለመገኘት የምትፈልጉ ቅን ልቦች በኢንቦክስ አናግሩን።
የመጀመሪያው ጉብኝት የፊታችን እሁድ ይጀመራል!
    |በነገራችን ላይ ከዚህ በታች የምትመለከቱት ምስል የማን ይመስላችኋል?|
   የፍቅር የሰላምና የአንድነት አርበኞች!
    
#እንግዳችን| ሼህ መሐመድ ጀማል
#hawassa| ከልብ የተሰጠ አገልግሎት
    በቀን #5 ጊዜ አዛን “አላሁ አክበር” የሚለው ሰው ማን ይመስልዎታል?

የህፃንነታችንን ወራትን አሳልፈን ድምጽ መለየት ከቻልንበት ጊዜ አንስቶ ከለሊት እስከ ምሽት ለመሸምደድ እስኪዳዳን ድረስ የተለማመድነው ድምጽ “አላሁ አክበር” ነው፡፡
ሙስሊም ላልሆንን ሰዎች ትርጉሙን ባንረዳውም እንኳ አንድ ነገር ያስማማናል የትምህርት ቤት ሰዓት መድረሱን  የሚነግረን ከመስኪድ የሚወረወረው ተስረቅራቂ ድምጽ እና የእርሻ ጣቢያ ደወል ነው፡፡ ሰዓት አጠገባችን ባይኖር ግዴለም፡፡ “አላሁ አክበር” አልጮህም አይደል? እንባባላለን፡፡ ትምህርት ቤት ለመሄድ እንደመቀስቀሻ ደውል ተጠቅመንበታል “አላሁ አክበር” የሚሉት ሰው ከሰዓቱ ውልትፍ አይልም፡፡ ግን… ግን… “አላሁ አክበር” የሚሉ ሰው ማናቸው?
       በሀዋሳ ከተማ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢማምነት (በአሰጋጅነት) ሼህ ጄቱ መሐመድ በዜግነት የመናዊ የነበሩ ሲሆን እሳቸው በሞት ሲያልፉ በምትካቸው ሼህ ሺፋ “ሙአዚን” ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከዚያም በሦስተኛነት ደረጃ ሼህ መሐመደ ጀማል በኢማምነት፣ በሙአዚነት እንዲሁም ታዳጊ ልጆችን በማስቀራት ከ45 ዓመታት በላይ እንዳገለገሉ በቅርበት የሚያውቃቸው ሰዎች ይመሰክሩላቸዋል፡፡
        ሼህ መሐመድ በዋናነት ከሚታወቅበት አገልግሎት በሰላት ወቅት ሰዓቱ እንደየወቅቱ ወደኃላ እና ወደፊት መቀያየሩ እንዳለ ሆኖ በ11፡20 ሱብሂ፣ 7፡00 ዝሁር፣ 10፡00 አስር፣ 1፡00 መግሪብ፣ 2፡00 ኢሻህ እነዚህ ሥርዓቶች እያንዳንዱ ትርጉም ያላቸውን ሰላቶችን በተገቢው ተግብረዋል፡፡

     በመስኪዱ ቅጥር ጊቢ ውስጥ ቤት ተሰጥቷቸው አሁንም ድረስ እዚያው አሉ፡፡ ለብዙ ጊዜያት መስኪድ ጊቢ እንደኖሩ ስለሚታወቅ ሰዎች ገንዘብ ሲሰጧቸው ተቀብለው፤ ሰዎች እኔ ጋ መጥተው እህል ሳይቀምሱ እንዳይወጡ፡፡ ምክንያቱም ተርበው ይሆናል፡፡ ምግብ ስታቀርቡላቸው ትበላለህ? አትበሏቸው፡፡ መብላት እየፈለጉ አፍረው በቃኝ ሊሉ ይችላሉ በማለት እንደአቅማቸው ትንሹም ትልቁም የሚመገብበት ቤት ነበር፡፡
      ነገር ግን እኚህ ባለውለታ ግማሽ አካላቸው ፓራላይዝ ሆነው አንደበታቸው ተይዞ መንቀሳቀስ እና እንደልብ መዘዋወር ካቃታቸው 9 ዓመት አለፋቸው፡፡

     ሀጂ መሐመድ ቤት ስንሄድ ያሉበት ሁኔታ እጅግ ልብ የሚነካ ነው፡፡ አባታችን ቀና ማለት የሚችሉት ሰዎች ካገዟቸው ብቻ ነው፡፡ ከዚያም በተጨማሪ ወንድ ልጃቸው የአእምሮ ታማሚ ሆኖባቸዋል፡፡ አጠገባቸው ሆነው የሚንክነባከቧቸው ባለቤታቸው ወ/ሮ ሙሉካ ሲሆኑ የሚተዳደሩት ሀጂ መሐመድ የወር ደሞወዝ እንደሆነ ነግረውን ከዚህ ቀደም የሚያውቋቸው ሰዎች እንደአቅማቸው ገንዘብም እንዲሁም ወተት እንደሚያመጡላቸው ገልፀውልናል፡፡
      በቅርቡ ደግሞ የሚኖሩበትን ክፍል ወጣቶች ቤታቸውን እንዳደሱላቸና እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡ (ቤት ያደሱላቸውን ወጣቶች አመስግኑልን) በአካል ቤታቸው ተገኝተን እንደተመለከትነው ለመንቀሳቀስ አለመቻላቸው ብቻ ሳይሆን ለመንቀሳቀስ በሚሞክሩ ግዜ ከፍተኛ ህመም እንሚሰማቸው ተረድተናል። ባለቤታቸው እሳቸውን ለማንቀሳቀስ #ዊልቸር እንኳ የላቸውም።
       እናንተ የሀዋሳ ውድ ቤተሰቦች በእርግጥ በየቤቱ እንደእነ ሀጂ መሐመድ ያሉ ሰዎች አሉ፡፡ ለሀገርና ለበጎ ስራ ተሰማርተው ነገር ግን የተረሱና ያልታሰቡ አሉ፡፡ እኛ ግን ለምክንያት ፈጣሪ እሳቸው ወደሚኖሩበት ቤት ወስዶናልና የቻልነውን እናድርግ መልዕክታችን ነው፡፡
#እሳቸውን ለማግኘት እንዲሁም የበኩላችንን ድጋፍ ለማድረግ የሚከተለውን ስልክና የባንክ አካውንት አስቀምጠናል።
ስልክ 09 26 16 82 90 ወይም 09 32 6398 80
ንግድ ባንክ 1000 4720 54507
#በሐና በቀለ
የፍቅር የሰላምና የአንድነት አርበኞች!
ታህሳስ 2016
👍
#ጥያቄ| ይመልሱ ይሸለሙ
#hawassa| የሰንበት እንግዳችን ማን ናቸው?
  ፎቶውን ይመልከቱ፣ ይመልሱ! በትክክል የሸለሙ ሁለት ቤተሰቦች የዶ/ር አስፋውን መፅሐፍ ይሸለማሉ። አሸናፊ የሚለየው በእጣ ነው።
የፍቅር የሰላምና የአንድነት አርበኞች!
መልካምነት መልካም እድልን ይዞ ይመጣል!
#ባለውለታ| መላከምህረት ጳውሎስ ቀፀላ /እያያ/
#hawassa| ጋቢ አልብሰናል አመስግነናል

     መላከምህረት ጳውሎስ ቀፀላ /እያያ/ ትውልዳቸው እና እድገታቸው ጎጃም ሀገር ነው። ከተማችን ሐዋሳ በቀድሞ አጠራር (የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት) ከተቆረቆረች ገና የ16 አመት ሙሽራ በነበረችው ሐዋሳ ጥቅምት 1966 ዓ.ም መጡ።
     እንደመጡ የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የምትተዳደረው  ቤተክህነት ትምህርት ቤት በአማርኛ መምህርነት ተቀጥረው ከ19 66 ዓ.ም እስከ 1970 ዓ.ም ድረስ ለአራት አመታት በትጋትና መሰጠት አገልግለዋል። ይህ ብርታትና ትጋታቸው፣ የነቃ የስራ ወዳድነታቸውና እምቅ አቅማቸው ከፍ ላለው ሐላፊነት እንዲታጩ አድርጓቸዋል።
  በዚሁ አመት የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ፣ የሐዋሳው ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ሀገረ ስብከት አስተዳዳሪ በመሆን እስከ 1980 ዓ.ም ድረስ አንኳር ተግባራትን አከናውነዋል። ከሚጠቀሱት አበይት ክንውናቸው መሐከል በወቅቱ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች ለ4 ዓመታት በቤተክርስቲያኒቱ የሚመራ ድርጅች ከአቶ በርሔ ጋር በመሆን ቡርጂ፣ ቦረና፣ ወላይታ፣ ጌዴኦና ሌሎችንም አካባቢዎችን ጨምሮ እርዳታ የማድረስ ስራን በተሳካ አፈፃፀም ተገቢው ድጋፍ ለተገቢው የማህበረሰብ ክፍል እንዲደርስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።

       ሌላው መላከምህረት በተሾሙበት በአስተዳዳሪነታቸው ወቅት ከሞያሌ እስከ ወላይታ ሶዶ ያገለገሉ ብርቱና ፈሪሐ እግዚአብሄር ያላቸው ሆነው ማገልገላቸው ሲሆን በተለይ ዛሬም ድረስ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያለው የሐዋሳ የካህናት ማሰልጠኛ ተቋም (በቤተክርስቲያኒቱ ቅጥር ግቢ የነበረውን በዚህ መልክ መቀጠል አይገባም ሲሉ) ቀድሞ የፖሊስ ማሰልጠኛ የነበረውን ቦታ ወይም ሀይቅ ዳር ከታቦር ተራራ ስር ያለውን ቦታ በእሳቸው ያላሰለሰ ትግል፣ ጥረትና ተጽዕኖ ፈጣሪነት የቤተክርስቲያኒቱ እንዲሆን በማስፈፀም፤
     ከየአውራጃው የሚመጡ ካህናት ማደሪያና የተለያዩ መንፈሳዊ እውቀት እንዲሁም ሌሎች ክህሎቶችን እንዲሰለጥኑ፣ (መጽሐፍ ቅዱስንና ሌሎች መንፈሳዊ ትምህርትን ጨምሮ፣ የሽመና ስራዎችን ሰልጥነው እንዲወጡ) ምግባቸውንም እዚያው በመመገብ በሙሉ ልብ ለተግባሩ ግንባር ቀደም ሚና እንደነበራቸው ይነገራል፡፡
   ዛሬ አይናቸው ታውሮ ልበብርሃንነታቸው ነገ ሊከሰቱ ቸሚችሉ መልካም አጋጣሚና ተግዳሮቶች የሚታያቸው ባለ ብሩህ አእምሮ መሆናቸው የሚመሰከርላቸው አባት ለመጀመሪያም ጊዜ ሰበካ ጉባኤን የማቋቋም ጥረታቸው እና ለስኬት ማብቃታቸው ዛሬ በተዋህዶ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ፍቅርና አክብሮት እንዲሰጣቸው ያስቻለ መሆኑ ይነገራል።

       ቴክኖሎጂ እንደዛሬ ባልዘመነበት፣ ሰው ለመሰብሰብ ጥሩምባ ተነፍቶ በመንደር ተንከራቶ በሆነበት ወቅት መምህር መላከምህረት  የቻይና ሳይክልን በመጠቀም ካህናት ስብሰባዎች ሲኖር ከቃጫ ፋብሪካ ጀምሮ በየቤቱ በመዘዋወር የስብሰባ ቀንና ሰዓትን በመናገር ያወያዩ ነበር፡፡

    መላከምህረትን “እያያ” ይሏቸዋል ልጆቻቸው እንዲሁም የቅርብ ወዳጆቻቸው ታዲያ በማህበራዊ ህይወታቸውም ቢሆን አይታሙም በሳይክላቸው ምዕመኑ ቤት በመዘዋወር በመምከር፣ በመገሰጽ፣ በማስተማር ይታወቃሉ፡፡

       ይሁንና ለ3 ዓመታት ማለትም እስከ 1983 ዓ.ም የሰበካ ጉባኤ አለቃ /ገበዝ/ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተው አይናቸው እየደከመ መምጣት ጀመረ። ወዲያውም አንድ አይናቸው ማየት አቆመ። ይሄኔ የሚወዱትና የተጠሩለት አገልግሎታቸውን ለማቋረጥ የሚያስገድዳቸው ስለመሆኑ ሲያስቡት ተጨንቀዋል። 
      ለህክምና በቤተዘመድና ቤተክርስቲያኒቱ ጥረት እስራኤል ሀገር ሄደው ቢታከሙም አይናቸው ከመታወር አልዳነም፡፡

      በስተመጨረሻ ማስተዳደሩን በገዛ ፈቃዳቸው በመልቀቅ የሰበካ ወንጌልን ማስተማር፣ ወጣቶችን በወንጌል በማብቃት፣ ገፍተውበት ዛሬ ላይ ከ10 በላይ ካህናትን በማብቃት የእሳቸው ተማሪዎች እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
     ከዚያም ባሻገር ሌሎችም በሳቸው የእውቀት ማዕድ የተዋጁ ተማሪዎች በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የሚገኙ አገልግሎትም በመስጠት ላይ ያሉ ብዙዎች ናቸው፡፡
    ይሁን እንጅ መላከ ምህረት ከ60 አመት በላይ በበርካታ ፈተና፣ ፅናትና እልህ አስጨራሽ ትጋት የቃረሙትን እውቀት ለትውልድ ለማጋራት እንዲሁም ተሞክሮና ልምዳቸውን ለማሳየት "መድብለ ሚስጥር"ን ጨምሮ 3 መጽሐፍቶችን አሳትመው ለአንባቢያን ቢያቀርቡም ነገሮች ባልተጠበቀ መልኩ ሁነው ልፊት ብቻ ተርፏቸዋል። ከመጽሐፉ ተጠቃሚ አልነበሩም፡፡ 
        አባታችን እድሜያቸውን ሙሉ መንፈሳዊ ትምህርትን ሲማሩና ሲያስተምሩ አይናቸውን እስከማጣት ደርሰዋል፡፡ ከሁለት አመት በፊት ወደ መኖሪያ ቤታቸው የገቡት መላከምህረት  እድሜያቸው ወደ 100ዎቹ ቢጠጋም አሁንም እሳቸው በፈጣሪ ቸርነት ብርቱ ናቸው፡፡

ከቃጫ ፋብሪካ እስከ ታቦር ተራራ ድረስ በሳይክል የጎበኙ አባት አሁን አቅማቸው ተዳክሟል ግን ሰው ይናፍቃሉ፡፡ መጎብኘትን ይፈልጋሉና በአካል እንኳ ተገኝታችሁ መጠየቅ ባትችሉ ደውላችሁ አግኝዋቸው ማለትን ወደድን፡፡ 
ስልክ መላከምህረት 09 21 45 25 33 እንዲሁም የልጃቸው ክፍለብርሃን 09 16 45 02 74 ነው፡፡
የፍቅር የሰላምና የአንድነት አርበኞች!
#ፈር_ቀዳጅ_ባለውለታ| ጋሽ ልሳነወርቅ ይማም
#hawassa| በልጅ ወግ አንግሰናል
    #ኢትዮጵያ_ትቅደም_ትምህርት_ቤት

እንዲህ ነበር ሲጀመር በ1964 ዓ.ም ዋርካ ስር የሰፈር ልጆችን በመሰብሰብ ፊደል በማስቆጠር የተጀመረው ትምህርት በሰዓቱ እምብዛም ትኩረትን የሳበ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ልጆች ዕለት ዕለት እውቀትን በመቅሰም ማንበብና መፃፍ እንደቻሉ ያዩ ወላጆች በጠዋት ልጆቻቸው “ሀሁ..” እንዲማሩ መላክ ጀመሩ፡፡

ይህንን ያስተዋሉት የፊደል አባት እዚያው ዋርካዋ ስር ትንሽ ቅርጮ በመከለል ከሰፈርና ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡ   ሕፃናትና ታዳጊዎችን በመቀበል በትጋት እና በፍቅር የሚወዱትን የትምህርት ሙያ በእንዲህ መልኩ አስቀጠሉ፡፡

እኚህ መልካም ሰው የትምህርት ቤቱ ባለቤት እና ርዕሰ መምህር ልሳነወርቅ ይማም ይባላሉ፡፡  ተማሪዎቻቸው ጋሽ ልሳኑ ልጆቻቸው ደግሞ አብዬ ይሏቸዋል፡፡

በእንዲህ ሁኔታ የተጀመረው የፊደል ቤት በከተማዋ ጥሩ ትምህርት ቤት ተከፍቷል የሚል መልካም ወሬ አንዱ ለአንዱ እየነገረ ብዙ ህፃናትን ወላጆች ወደ ጋሽ ልሳኑ ማምጣት ጀመሩ፡፡

ከዚያም የቅርጮዋ ትምህርት ቤት እንደማያዛልቃቸው ሲያውቁ ከዳሱ የተሻለ ቤት በማገር እና በቆርቆሮ በመስራትና አግዳሚ ወንበሮችን በአጠና አዘጋጅተው ከ0 እስከ 4ኛ ክፍል በአዲስ መልክ በማስጀመር ተማሪዎችን በእድሜ በመለየት በዋናነት አማርኛ እና እንግሊዝኛ ትምህርቶችን በትኩረት ማስተማርን ቀጠሉ፡፡

አሁን የተማሪዎቹ ብዛት እሳቸው ብቻ አስተምረው እንደማይዘልቁ ሲረዱ ተማሪዎች እንደየክፍላቸው ደረጃ ከ2 ብር እስከ 5 ብር እየከፈሉ እንዲማሩና ከተማሪዎች የሚሰበሰቡ ብሮችን ለአስተማሪዎች ክፍያ፣ ለትምህርቱ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ማሟያ እና ሌሎችን ክፍሎች ለመጨመር አስበው ተግባራዊም አደረጉ፡፡

ከዚያም 12ኛ የጨረሰ መምህር መኮንን ካሳዬን በ95 ብር  በመቀጠልም በ1975 ዓ.ም ማስታወቂያ በማውጣት አወዳድረው ለሁለተኛ ጊዜ መምህርት ወጋየሁ ብርሃኑን በ50 ብር ቀጠሩ፡፡  በሀዋሳ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ የግል ትምህርት ቤት “ኢትዮጵያ ትቅደም” በሚል እሳቸው ስያሜውን በመስጠት ስራው በይፋ ተጀመረ፡፡

በከተማዋ የሚገኙ ወላጆች በጋሽ ልሳኑ ማስተማር አመኔታን ስላገኙ ጋሽ ልሳኑ እና ወላጆች  ይህ ትምህርት ቤት በመንግስት ደረጃ እውቅናን ማግኘት ይገባዋል በሚል ተማከሩ፡፡

ከዚያም ጋሽ ልሳኑ ከተማሪዎች ወላጆች ኮሚቴው ገንዘብ ያዥ፣ ሂሳብ ሹም በመምረጥ ቃለ-ጉባኤ በመያዝ  አቶ ሸምሲያን አሊ፣ መምህር ማስረሻ ተገኝ፣ አቶ ሞገስ በዳሶ፣ አቶ አሰፋ ሰይፉ እና ሌሎችንም በመጨመር ትምህርት ቢሮ እውቅናን እና የተለያዩ ድጋፎች እንዲደረግላቸው በጠየቁት መሰረት መንግስት የተወሰኑ መምህራኖችን መደበ፡፡ ከዚያም ትምህርት ቤቱ ደግሞ የራሱን ተጨማሪ መምህራንን በመቅጠር ሙሉ የትምህርት ካሪኩለሙን እንዲማሩ ፈቃድ አገኙ፡፡

በጊዜው በአንድ ክፍል ከ60 እስከ 70 ተማሪዎችን በመያዝ እውቅናን አግኝቶ ቀጠለ፡፡ በዚያ ሁሉ ግን ጋሽ ልሳኑ ርዕሰ መምህርና መምህር ብቻ ሳይሆኑ ከመምህራንና ተማሪዎች ቀድመው ወደ ትምህርት ቤቱ በመምጣት ጊቢው አፈር ስለነበር ውሃ አርከፍክፈው ያፀዳሉ፣ ክፍሉን ይጠርጋሉ፣ ወንበር ይወለውላሉ፡፡ እሳቸው ሁለገብ ናቸው፡፡

ልጄ ተደባድቦ መጣ፣ ጊቢው ለልጄ ምቹ አይደለም ብለው ስሞታ የሚያመጡ ወላጆችን ተቀብለው በእርጋታ ካነጋገሩ በኋላ ይስተካከላል እናንተ ብትደግፉኝ ደግሞ የጎደለውን አሻሽላለሁ በማለት አረጋግተው በሠላም ይሸኝዋቸዋል፡፡

ተማሪዎቻቸው አማርኛ ሲያነቡ ሳልስና ሳድስ ገድፎ ማለፍ አይታሰብም፡፡ በተለይ ጀማሪዎች ላይ እራሳቸው ማብቃትን ስለሚፈልጉ ዋጋ ከፍለው ያስተምሩ ነበር፡፡ የ1ኛ ክፍል ተማሪዎች አማርኛ በትክክል ያነባሉ፡፡

ይህ ክትትል በተማሪዎች ብቻ አያበቃም፤ መምህራን ሲያስተምሩ ክፍል በመግባት በትኩረት ይመለከቱና ቢሮ ሲመለሱ ጥፋታቸውንና ጥንካሬያቸውን በግልጽ ይናገራሉ፡፡

ለመምህራን የትኩረት አቅጣጫ- ከሀደራ ጋር ያስጠነቅቃሉ፡፡ የእስክሪፕቶ አያያዝ አስተካክሉላቸው፣ ሲጽፉ በቀኝ እንጂ በግራ እንዳይለምዱ፣ ሳልስና ሳድስ እንዳይገድፉ  ይሄ የሁልጊዜ ማስጠንቀቂያቸው ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር ጋሽ ልሳኑ በመጠነኛ ቅጣት ያምናሉ፡፡ ስርዓት ለተላለፈ፣ ስነምግባር የጣሰ የእሳቸውን ቁንጥጫ፣ አለንጋ፣ አንበርክኮ ቅጣት አይቀርለትም። እንደእኔ ረባሽ ለነበረ ተማሪ ደግሞ የህይወት ዘመን ትዝታው ሆኖ ቀርቷል። ያው ቅጣት የአባትነት ወግስ አይደል?

ከሁሉ ከሁሉ ግን ትልቋ መቅረጫቸው የሚዘነጋ አይደለም። አንድ ጊዜ 10 ሳንቲም የከፈለ ተማሪ ዓመቱን ሙሉ እርሳሱ ይቀረጽለታል፡፡ ተማሪው ቢሮ መሄድ አይጠበቅበትም እሳቸው ከትምህርት በፊት አልያም ከትምህርት በኋላ ቀርጸው ይመለሳሉ፡፡ ከልብ የተሰጠ ሙያና ማህበራዊ ሐላፊነትን ያለመታከት በመወጣት የቅቡልነታቸው አንዱ ሚና ነበር።

    እሳቸው ጋ በክረምት እረፍት ተብሎ አይታሰብም፡፡ በጊዜው ለመጀመሪያ ጊዜ የጥናትና የክረምት ትምህርት ባልተለመደበት ወቅት ያስተዋወቁና እሳቸውን ጨምሮ ከሌሎች መምህራን ጋር ክረምቱን ሙሉ በማስተማር ያሳልፉ ነበር፡፡

ጋሽ ልሳኑ የሚታወቁት በእርጋታቸው፣ አባትና መምህር፣ ያሰቡት ሚሳካላቸው፣ መጽሐፍትንና ወንበርን ለተማሪዎቼ ብለው መለመንን የሚያውቁበት፡፡ መምህራኖቻቸውንም ቢሆን ሰውን አክብሩ ሰውን አትናቁ ብለው ሚመክሩ አባት ናቸው፡፡   

ጋሽ ልሳኑ በዚህም ሁሉ ግን የተሻለ ትልቅ ጊቢና ትምህርት ቤት ይታያቸዋል፡፡ ራዕይያቸው ሰፊ ነው፡፡ ይህ ቦታ አይበቃንም ሌላ ቦታ ሊሰጠን ይገባል በማለት 2ኛውን ኢትዮጵያ ትቅደም ትምህርት ቤት እንዲቋቋም እና ትምህርት ቤቱ አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ ብዙ ለፍተውበታል፡፡


የድሮው ኢትዮጵያ ትቅደም ትምህርት ቤት ከ1 እስከ 4 ሲሆን አዲሱ ኢትዮጵያ ትቅደም ደግሞ ከ1 እስከ 8 የማስቀጠል ዕቅዳቸውም ተሳክቶላቸዋል፡፡ እንደጋሽ ልሳኑ ሀሳብ የነበረው የመጀመሪያውንና በሁለተኛነት የተከፈተውን ትምህርት ቤት ተማሪዎቹ የቀረባቸው ቦታ እንዲማሩ ነበር፡፡ ግን አልሆነም ይዞታው የመንግስት ስለሆነ ለነዋሪዎች ይፈለጋል በሚል ከቀድሞ ትምህርት ቤት እንዲለቁና 2ኛው ኢትዮጵያ ትቅደም ትምህር ቤት ተጠቃልሎ እንዲገባ ተደረገ በዚህ የጀመረው ፈተና አንድ ብሎ ቀጠለ፡፡

ከ1983 ዓ.ም ከመንግስት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሀገር ባለውለታ የሆኑት እኚህ ሰው ውለታቸው ተዘንግቶ ተገፉ፡፡ ልጅነታቸውንና እድሜያቸውን መስዋዕት ካደረጉበት የግል ትምህርት ቤታቸው እንዲወጡ ተደረገ፡፡ አንዳንድ ወንጀሎች ፈጽመዋል በሚል የውሸት ክስ እስር ቤት አቆዩዋቸው፡፡ ይህም ሳይበቃቸው ከእስር ሲፈቱ  ደግሞ በልፋታቸው የገነቡትን ትምህርት ቤት እንዳይገቡ በጠራራ ፀሐይ ተከለከሉ፡፡ የርዕሰ መምህርነት ቦታቸውን በሌላ ሰው ተክተው ጠበቃቸው፡፡ “ሀገሬ ሞኝነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” ማለት ይሄ አይደል? 

ጋሽ ልሳኑ እንዲሁ በዋዛ እጃቸውን አጣጥፈው ወደቤታቸው መግባትን አማራጭ አላደረጉም፤ በቻሉት አቅም ሁሉ ተካሰዋል፡፡ ፍትሕ ይሰጡኛል ብለዋ ባመኑበት ቦታ ሁሉ ደጅ ጠንተዋል ግን አልተደመጡም፡፡ ከገዛ የግል ትምህርት ቤታቸው ሲያስወጧቸው የዳረጎት እንኳን አልተሰጣቸውም፤ የምስጋና ወረቀትም አልታሰበላቸውም፡፡ የሀገር ባለውለታ እንደምናምን ተጥለዋል፡፡ “ሲያልቅ አያምር” ነበር ያለው ያገሬ ሰው?
ጋሽ ልሳኑ የሶስት ሴትና የአንድ ወንድ ልጆች አባት ናቸው (የአብራካቸው ክፋይ የሆኑት ምእራፍ ልሳነወርቅ፣ ምስክር ልሳነወርቅ፣ ተዋነይ ልሳነወርቅ፣ ትንሳኤ ልሳነወርቅ ይባላሉ፡፡ )  የብዙዎችም የዕውቀት አባት ናቸው፡፡ ብዙ በስራቸው ታዋቂና አንቱ የተባሉ ልጆችን በሀገር ውስጥና በውጪም አፍርተዋል፡፡ በዚህ ደስተኛ ናቸው፡፡

ይሁን እንጅ በጊዜው በደረሰባቸው በደል እና የሚወዷቸውን የትዳር አጋራቸው የነበሩትን ወ/ሮ ፀሐይ እንደሻውን በሞት በማጣታቸው የልብ ስብራት ደርሶባቸው ወደቤታቸው ገብተው ቀርተዋል፡፡

ነገር ግን እኛ ልናደርግ የቻልነው አንድ ነገር ነው፡፡ ፈጣሪ ብድርዎን ይክፈል፣ እድሜና ጤና ይስጦት፣ ለሀገር የከፈሉትን ዋጋ አንረሳውም፣ ስላስተማሩን እናመሰግናለን ማለትና በልጅ ወግ ፍቅራችንን እና ክብራችንን በቂ ባይሆንም በመላ የከተማችን ነዋሪዎችና ተማሪዎቻቸው ስም ጋቢ ለማልበስ እቤታቸው ተገኘን፡፡

በመጨረሻም ከመጀመሪያው የምታውቃቸው መምህርት ወጋየሁ ብርሐኑን ጋሽ ልሳነወርቅን እንዴት ትገልጪያቸዋለሽ ብዬ ጠየኳት “ንፁህ አባት” ስትል ገልፃቸዋለች፡፡ መልካም ጊዜ ይሁንላችሁ፡፡

በሐና በቀለ
#የ03_ቀበሌ_ትዝታዎች| በተስፋዬ ታደሰ (አቹሜ)
#hawassa| ክፍል - 6
(ይህ ፅሑፍ እውነታን ዘና ባለ መንገድ በትዝታ መዳሰስና ማዝናናት ያለመ ብቻ ነው)

መታነቅ ትንቅንቅእና የመጀመሪያዎቹ

የሞተባቸውን ታዳጊ ህፃን አስክሬን ሳጥን ውስጥ ሳያስገቡት ጓዳ ሸጉጠውት   ባዶውን ሳጥኑን ቀብረው የመጡ ሀዘንተኞች በአፍሪካም...በሌሎችም አህጉራት ሊኖር አይችልም ከ03 ቀበሌ ውጪ...እንደገና ለመቅበር ትንቅንቅ

በቡና ቤት የመጀመሪያው ነበርን

ሀዋሳ ከተማ ውስጥ ያለው ከታረቀኝ ሰፈር አስቀድሞ ከፈለቀች ሆቴል ወረድ ብሎ አንድ አነስተኛ ቡና ቤት ነበረች......"ወርቄ" የምትባል ሴተኛ-አዳሪ ነበረች....
(በሴተኛ አዳሪነቱም ስራ  03 ቀበሌ የመጀመሪያው ሊሆን ይችላል )
ወርቄን ለማየት አይቶም ለማግኘት ትንቅንቅ ነበረ.....ወርቄ ቀይ ናት ቆንጆ ...ረጃጅም የጆሮ ጉትቻዎች አጫጭር የጂንስ ቁምጣ አቤት ሲያምርባት.... እሷን ፍለጋ  ከኦጎባና ከወንዶ-ጢቃ ወታደሮች ....ከገበያ ላብአደሮች....03 ቀበሌ በምትገኘው አነስተኛው ቡና ...ወርቅ ለማፈስ እንጂ ወርቄን ለመጥቀስ አይመስልም ነበረ.....

በአነስተኛው ቡና ከሚሸጠው ካቲካላና  "ሜታ" እኩል ሻሜታ 03 ይታወቃል .....

በህክምናው  የመጀመሪያው ነበርን

የጥርስ ህመም ላጋጠማቸው ፍቱን መፍትሔ የሚሰጡ አባት አሁን በህይወት የሉም....
ፊንሳ ጉጠትና ካቻቢቴ ተጠቅመው እንደ አረም ንቅል ሲያደርጉ ....ቆሮቆንዳ ጉንጭ ውስጥ ይከቱና ግራና ቀኝ ሁለት የቤት ልጆች ጠፍረው እንዲይዙ ይደረጋል ....አንዳንድ ጊዜ ከታመመው ጥርስ ይልቅ ጤናማው ይነቀላል ........
በጀርባ አስተኝተው ደረት አካባቢ በአንድ እግር ረግጠው በሁለት እጃቸው በፊንሳ ሲጎትቱት ትንቅንቁን መቸም አልረሳውም


በጥበቃ

የመጀመሪያዎቹ የ03ቀበሌ ወላጆች አሁን አሁን በእርጅና በሞትና  በበሽታ እየመነመኑ ጥቂቶቹ ነው የቀሩት። ዕድሜ ይስጣቸው። እባካችሁ ጎብኟቸው .....የራሳቸው ዘመድ እንኳን አልጠይቅ ቢሏቸው ይመስለኛል ..."ከስጋ ዘመድ ስጋ ይሻላል"

ጥበቃ ሊቀጠር የሔደው የቀበሌያችን አባወራ እንግሊዝኛ መቻል ግዴታህ ነው ሲባል ....ሌቦቹ ፈረንጅ ናቸው እንዴ ??? ...ብሎ ትንቅንቁን ጥሎ መጥቷል..

03  ቀበሌ  በሲጋራ ምርት  ቀዳሚ ነበረ

በጋዜጣ የተጠቀለለ ሲጋራ ኮሾ ማምረቻው እኛጋ ነበረ....አምራቹ እሸቱ ጠማማ ይባላል...እሼ አንገቱ በተፈጥሮ ዞር ያለ ነው.... የ ኮሾ  ሲጋራን እሱ ሲያጨስ ....አካባቢው በጉም የተሸፈነው ከተማ ይመስላል  ።


03 ቀበሌ ባይኖር እኛ አንኖርም
እኛ ባንኖር ግን  ታሪከኛው  03 ቀበሌ ይኖራል

03 ቀበሌ በኮሞዲኖ  እና  በኮሜዲው ዘርፍ

በቀጣዩ የክፍል -7 ጠብቁን
አመሰግናለሁ 🙏🙏
[email protected]
የፍቅር የሰላምና የአንድነት አርበኞች!
#ጉምቱ_ስፖርተኛ| ጋሽ ከማል አህመድ
#hawassa| ባለውለታ 3ኛ ዙር ከ 30
     አንዳንድ ሰዎች አሉ ያሰቡት ሚሳካላቸው፣ የነኩት ሚባረክላቸው፣ ያየህ ይውደድህ ተብለው የተመረቁ፤ ከእነዚያ መካከል አንዱ ጋሽ ከማል ናቸው ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ ጋሽ ከማል ስፖርቱ መቼ ከደማቸው ጋር እንደተዋሃደ አያውቁትም ብቻ ራሳቸውን ሲያውቁ ከኳስ ጋር ናቸው፡፡

የሁሉ ወዳጅ ናቸው፡፡ ቀልድም ያውቁበታል፡፡ ቁምነገራቸውም በግልጽ ሚታይ ነው፡፡ ከትንሹም ከትልቁም ጋር መግባባትን ያውቁበታል፡፡ የሰውም መውደድ አላቸው፤ እሳቸውም እንዲሁ ተግባቢና ቀለል ያሉ ሰው ናቸው፡፡  እስቲ በስራ ዘመናቸው ምን አከናወኑ እንመልከት፡፡

• በአሰልጣኝነት ደረጃ ኤ ላይሰንስ፣
• ከ1966 – 1970 የአዲስ አበባ ምስራቃዊት ሄዋን ክለብ አሰልጣኝ፣
• ከ1971 – 1980 የእርሻ ጣቢያ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ፣
• ከ1981 – 1988 የአዲስ አበባ የአግሮ ኢንዱስትሪ መንግስት እርሻ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ፣
• ከ1988 – 1993 የሀዋሳ ከነማ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ፣
• በ1994 የወንጂ ስኳር ፋብሪካ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ፣
• በ1995 የደብረ ብርሃን ብርድልብስ ፋብሪካ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ፣
• ከ1996 -2003 የሀዋሳ ከነማ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ፣
• ከ2004 – 2005 የኒያላ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ፣
• በ2006 የወላይታ ዲቻ እግር ኳስ ክለብ አማካሪ፣
• በ2007 የአዲስ አበባ ውሀ ስራዎች እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ፣
• በ1999 ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ፣
• በ2000 የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ፣
• በ2001 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ በሴካፋ ውድድር፣
• ሀዋሳ ከተማ ብቻ ለ13 ዓመታት በማሰልጠን 3 ጊዜ የዋንጫ ባለቤት፣
• በ1996 እና 1999 የኮከብ አሰልጣኝ በመሆን ተሸላሚ፣
• ከ50 ዓመታት በላይ በአሰልጣኝነት ያገለገሉ አንጋፋ አሰልጣኝ ናቸው፡፡
በእሳቸው የአሰልጣኝነት የህይወት ጉዞ በርካታ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን በማፍራት ለዘርፉ አስተዋፅኦ ካበረከቱት በዋናነት ይጠቀሳሉ። ስለ አንጋፋው አሰልጣኝ ጋሽ ከማል ከዚህ ቀደም የሐዋሳ ማዘጋጃ ቤት ካሳተመው መፅሔት መረጃውን አቀረብኩ እንጂ ያልተነገረላቸው ብዙ ስራዎች እንደሰሩ ይታወቅልኝ፡፡
  

ጋሽ ከማል አሁን “ከማል አካዳሚ” ካምፕ በመክፈት ከ260 በላይ ታዳጊዎች በማሰባሰብ እግር ኳስ ማሰልጠኛ ከፍተው እየሰለጠኑ ይገኛሉ፡፡

አሁን እሳቸው ከስራው ጋር በተያያዘ ረዥም ጊዜ ከመቆም ጋር ተያይዞ አንድ እግራቸው ስለሚታመሙ እንደቀድሞው ተሯርጠው መስራት ባይችሉም ከአቶ መለሰ ከበደ ጋር በመሆን ድርጅቱን በመቆጣጠርና በማማከር ስራዎችን በመስራት የሚወዱትን ሙያ በማስቀጠል ላይ ይገኛሉ፡፡

ጋሽ ከማል ባለትዳርና የአንዲት ሴት፣ የሁለት ወንዶች አባት ሲሆኑ 5 የልጅ ልጅ አሏቸው፡፡ ጋሼ በኑሮአቸው ባለፉበት መንገድና አሁን የደረሱበትን መንገድ እያስታወሱ ፈጣሪን ያመሰግናሉ፡፡ ያሰቡትንም እንዳሳኩ ይሰማቸዋል፡፡

ወደመኖሪያ ቤታቸው በሄድንበት ወቅት እጅግ በጣም ደስተኛ ነበሩ፡፡ ይሄ ለእኔ ከገንዘብ በላይ ነው በጣም ደስ ብሎኛሎ በማለት የአባትነታቸውን መርቀውን ተመለስን፡፡ ለአባታችን ረዥም እድሜን ከጤና ጋር ተመኘን፡፡

ጋሽ ከማል አሁን መጽሐፍ ጽፈው አጠናቀዋል፡፡ መጽሐፉ ለሕትመት ዝግጁ ሆኖ ህትመት ብቻ ይቀረዋል፡፡ አባታችን ህልማቸው ተሳክቶላቸው ዳግም ለመገናኘት ያብቃን፡፡
( countdown 3 of 30 round one) ለዚህ በጎ ስራ ለተባበራችሁ ውድ ቤተሰቦች (ፍቅሩና ጓደኞቹ) ከልብ የመነጨ ምስጋናችን ይድረሳችሁ።

@በሐና በቀለ
የፍቅር የሰላምና የአንድነት አርበኞች
(ከላይ የተጠቀሰው ቁጥር ከ30 ሶስተኛ ዙር ላይ መድረሳችንን ብቻ የሚገልፅ ነው)
2025/10/19 19:53:33
Back to Top
HTML Embed Code: