Telegram Web Link
#ዝግጅት_አንድ| ቃል በተግባር
#hawassa| የገና ስጦታ 1

    ውድ ቤተሰቦች እንኳን አደረሳችሁ! ከሰሞኑ እንዳስተዋወቅናችሁ የመጀመሪያውን የስጦታ መርሐ ግብር  አከናውነናል።  ዝግጅቱም በተሳካና በእናት አባቶች ምርቃት ደምቆ ተከናውኗል። ለስጦታ የተዘጋጀው የቅርጫ፣ የዘይት፣ የሽንኩርትና የዳቦ ዱቄት ሲሆን በአለማየሁ፣ ቾምቤና ቤተሰቦቹ ስፓንሰርነት በሐዋሳ ትዝታ ማህበራዊ ሚዲያ አስተባባሪነት የቀረበ ዝግጅት ነው።
    አቶ ከለማየሁና ቤተሰቦቹ ለመልካም ነገር የተሰጡ፣ እውቀት፣ ገንዘብና ጊዜያቸውን ሳይሰስቱ በየአመቱ እስከ መቶ ሺህ ብር የሚጠጋ በጀት መድበው ለምስኪኖች ድጋፍ በማድረግ ይታወቃሉ። በተጨማሪም በቋሚነት የሚደግፏቸው ወገኖችም አሉ።
     መሐል ክ/ከተማ ቤተልሔም አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ግቢ በእለተ ቅዳሜ (ዋዜማ) በአቅማቸው ድጋፍ የሚፈልጉ፣ በእድሜ የገፉና ጧሪ የሌላቸው 24 ወገኖች የስጦታው ተጠቃሚ ሆነዋል። ወገኖቹ የተመረጡት ከከተማዋ ከተለያየ ሰፈር እና በተለያየ ሰዎች ጥቆማ ሲሆን ስጦታውን በማግኘታቸው በአባትና እናት ወግ መርቀዋል አመስግነዋልም።
    በስጦታው ወቅት ከተገኙት እንግዶች መሐከል መ/ር መሐሪ አንዱ ሲሆኑ ይህን በጎ ስራ የሰሩትን ቤተሰቦች ከማመስገን ባለፈ ለዝግጅቱ ስኬት አብረውን ውድ ጊዜና ጉልበታቸውን ሰውተው በመተባበራቸው ከፍተኛ ምስጋናችንን ለማቅረብ እንወዳለን።
   መልካምነት ይከፍላል።
የፍቅር የሰላምና የአንድነት አርበኞች!
ታህሳስ 27/2016
#አንጋፋዋ_ሾፌር| ወ/ሮ ወይኒቱ ከበደ
#hawassa| በልጅ ወግ አክብረናል

በቢሮ ደረጃ የሴት ሾፌር ብርቅ በነበረበት ዘመን እሳቸው ግን ኧረ እናንተ እድሉን ስጡኝ እንጂ ምን ገዶኝ በሚገባ ኃላፊነቴን እወጣለሁ በማለት ከ30 ዓመታት በላይ በሹፍርና አገልግለዋል፡፡

ወ/ሮ ወይኒቱ ከበደ ባሌ ክ/ሀገር የተወለዱ ሲሆን የ10 ዓመት ልጅ እያሉ ነው ወደሀዋሳ አክስታቸው ቤት የመጡት፡፡ በ19 ዓመታቸው የተዳሩት ወ/ሮ ወይኒቱ ቦረና ከዚያም ያቤሎ ከባለቤታቸው ጋር እየኖሩ ባሉበት ወቅት በጊዜው በነበረው ጦርነት 2 ልጆቻቸውን ይዘው ወደሀዋሳ ከተማ ተመለሱ፡፡

በ1970 ዓ.ም የአሁኑ ግብርና ኮሌጅ በፊት አዋሳ እርሻ ኮሌጅ በሚባልበት ወቅት በ21 ዓመታቸው ኮሌጁ እንጀራ ጋጋሪ ማስታወቂያ አውጥቶ ስለነበር ተወዳድረው ገቡ፡፡ ነገር ግን ብዙም በስራው አልዘለቁበትም፤ ሁለት ወር ከሰሩ በኋላ ይህቺ ወጣት ልጅ በአግባቡ እንጀራ እየጋገረች አይደለም ብለው የተማሪ ምገባ ክፍል በመስተንግዶነት እንዲሰሩ ተደረገ፡፡

ከዚያም የሴቶች ጥበቃ ተፈልጐ ስለነበር ወደዚያ በመዛወር ለ3 ወራት ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር  ወታደራዊ ትምህርት በመውሰድ መሣሪያ መፍታት፣ መግጠም ተምረው ሲመለሱ ጥበቃና ፍታሽ ሆነው አገልግለዋል፡፡ 

በኋላ ግን ይላሉ ወ/ሮ ወይኒቱ 1986 ዓ.ም እኔ እና 15 ወንዶች ሹፍርና እንድንሰለጥን መስሪያ ቤቱ ባመቻቸልን ዕድል ስልጠናውን ጨርሰን ላይሰንስ ይዘን ተመለስን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ 3ኛ መንጃ ፈቃድ ድረስም መስሪያ ቤቱ አስተምሮኛል፡፡ ከዚያም የኮሌጁ ትራንስፖርትና ገራዥ ክፍል ከጥበቃ ተዛወርኩ፡፡ በጊዜው የነበሩ ፕሮፌሰር ዝናቡ ገ/ማሪያም እና ፕሮፌሰር አድማሱ ፀጋዬ ሌሎችም ጥሩ ዶክተሮችና ሰራተኞች ነበሩ እኔ እንድማርና እዚህ ደረጃ እንድደርስ ትልቅ  አጽተዋፅኦ አድርገውልኛል ይላሉ፡፡

ከስልጠናው በኋላ ነገሮች አልጋ በአልጋ አልሆኑልኝም፡፡ በቢሮ ደረጃ የሴት ሾፌር ተቀጥራም ሰርታም ስለማታውቅ ከወንዶቹ እኩል ሰልጥኜ ብመጣም መኪና ሊሰጡኝና ወደስራ ሊያሰማሩኝ ፈቃደኛ ስላልነበሩ ያለስራ 10 ዓመታትን ተቀመጥኩ፡፡

ከዚያ ግን በስምሪት ክፍሉ የነበሩ ሀላፊ መኪና ይሰጣትና ሻሸመኔ ደርሳ ትመለስ ብለው አዘዙና አንድ ታዛቢ ሹፌር ተመደበልኝ፡፡ ትንሽዋን ቴዮታ ሰጡኝና ሻሸመኔ፣ አርሲ ኔጌሌ፣ ቱላ፣ ይርጋዓለም ደርሼ ስመለስ ይርጋዓለም ከሄደች በንሳ ደርሳ ትመለስ ተባልኩ፡፡

በሹፍርና የመስራት ፍላጎቱም ስለነበረኝ ከዚያ በተጨማሪ ተከልክዬ የተቀመጥኩበት እልሁም ተጨምሮበት ስራዬን በጥንቃቄና በትጋት እሰራ ነበር፡፡

ኋላ ብቃቴን ስለተመለከቱ የምርምር ስራን የሚሰሩ ባለሙያዎችን፣ አስተማሪዎችንና ዶክተሮችን ይዤ ወላይታ ሶዶ እና አርባምንጭ አድርሻቸው መለስኳቸው፡፡    

አሁን የእኔ ጊዜ መጣ ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ ከዚያም ፒካፕ መኪና ሰጡኝ፤ ቀጠሉና ላንድክሩዘር ብቻ እንዲህ እንዲያ እያልኩ የተገኘነው መኪያ እየቀያየርኩ ሀገራችንን ከጫፍ እስከ ጫፍ ማዳረስ ጀመርኩ፡፡ በሹፍርና ህይወቴ ብዙ የኢትዮጵያ ሃገራትን አይቻለሁ፡፡ በዚያ ደግሞ ትልቅ ኩራት ይሰማኛል፡፡

ወ/ሮ ወይኒቱ ሲናገሩ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በጣም ታላላቅ ሰዎች ብዙ ምሁራን ያሉበት ቤት ነው ያንን ቤት በጣም እወደዋለሁ፡፡ ብዙ ያየሁበት ጊቢ ነው፡፡ ልጅነቴን ያስታውሰኛል፡፡

ከለሊሉ 9 ሰዓት ከወንዶች እኩል በመነሳት የተማሪዎችን ምግብ የሚያበስሉ ሰራተኞችን ከየቤታቸው በመሰብሰብ 12 ሰዓት ወደቤት እመለስ ነበር፡፡ ከዚያም  ቀን እንዲሁ መምህራኖችን በማመላለስ ሰርቻለሁ፡፡

ነገር ግን ስራው እየተደራረበ ድካም ሲበዛብኝ የቅርብ የስራ ኃላፊ የሆነውን ግለሰብ የለሊቱ ስራ እንዳልተመቸኝ ባሳውቅም በወቅቱ ድካሜን ተረድቶ ቅሬታዬን ስላልተቀበለ አንድም ቀን በዚህ መልኩ ስራዬን እለቃለሁ ብዬ ባላሰብኩት ሰዓት 5 ዓመት ለጡረታ ሲቀረኝ የምወደውን ሞያና ዩኒቨርስቲ ለመልቀቅ ተገደዱ፡፡

እኛ ወ/ሮ ወይኒቱ እቤት በሄድንበት ወቅት ጋቢ ስናለብሳቸውና ለሴቶች ተምሳሌት ኖት ስላገለገሉን እናመሰግናለን ስንል በጉንጫቸው የሚወርደውን እምባ እየጠራረጉ ለካስ መስራቴን ለሕዝብ መድከሜን የሚያውቅልኝ ትውል አለ አመሰግናለሁ ነበር ያሉን፡፡

ሆኖም ግን የጡረታ መብታቸውን ካስከበሩ በኋላ መሪ ለቆ ወደቤት መግባት ለእኔ ከባድ ነበር የሚሉት ታታሪዋ ሾፌር ኦዲት ቢሮ ለ11 ወራት እንዲሁም አሁን የመድሐኒት አቅራቢ አገልግሎት ሀዋሳ ቅርንጫ በሾፌርነት 9 ዓመት ያገለገሉ ሲሆን አሁንም በስራ ላይ ናቸው፡፡

በመጨረሻም የመድሐኒት አቅራቢ አገልግሎት ሀዋሳ ቅርንጫፍ ኃላፊ ለሆኑት አቶ ዘመን ለገሰን የከበረ ምስጋና አቅርቢልኝ እሱ መልካምና የልጅ አዋቂ ነው ብለዋል፡፡ እንዲሁም መስሪያ ቤቱ ላሉ ሰራተኞች ስለሁሉም ነገር አመሰግናለሁ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

አሁን ወ/ሮ ወይኒቱ 68 ዓመት ሆኗቸዋል፤ ባለትዳር እና የ2 ሴቶችና የ4 ወንዶች በአጠቃላይ የ6 ልጆች እንዲሁም 10 የልጅ ልጆችን አይተዋል፡፡
 
እኛም ታታሪዋን ሾፌር ለብዙ ሴቶች እህቶቻችን ተምሳሌት ነዎትና በድጋሚ  እያመሰገንን ቀሪ ዘመንዎን አምላክ ይባርክልዎት ማለት ወደድን፡፡

በሐና በቀለ
የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ!
የፍቅር የሰላምና የአንድነት አርበኞች!
#awassa
#አንድ_አበባ_ለአንድ_ባለውለታ| እንድትሳተፉ ተጋብዛችኋል
#hawassa| 30ዎቹ ባለውለታዎች
     ፍቅርን በአበባ ክብርን በጋቢ ማልበስና ታሪክ በመሰነድ እናመሰግናቸዋለን። መሰል ትውልድ እንዲፈጠር አክብሮታችንን በልጅ ወግ ቤታቸው በመገኘት መግለፅ አለብን።
ሰላም ውድ ቤተሰቦች።
  ከተማችን በርካታ ባለውለታዎች እንዳሏት ይታወቃል። በተለያየ የሙያ ዘርፍ ለከተማችን ብሎም ለማህበረሰባችን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ አባትና እናቶችን ሳናመሰግን፣ ሳናከብርና ፍቅራችንን ሳንገልፅ ብዙዎች አልፈውብናል። እኛም ከዚህ አለም መለየታቸውን #በህልፈት መርሐግብራችን ስንገልፅ "መልካም እንደነበሩ፣ ስለሰሩት ጀብዱና ስለተወጡት ማህበራዊ ሐላፊነት...ወዘተ ምስክርነት ሲሰጥ ተመልክተናል። ነገር ግን ሰው ህይወቱ ካለፈ በኋላ መሆን የለበትም።
   ይህንን ልምድ መቀየር ስለሚገባ ባለውለታዎቻችን #በህይወት_እያሉ ታሪካቸውን መሰነድ፣ ማክበር፣ ማመስገንና እውቅና መስጠት መለመድ አለበት። በዚህ መሰረት የጀመርነው በህይወት ላሉ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች አስተዋፅኦ ያበረከቱ #ባለውለታዎችን #በልጅ_ወግ ፍቅራችንን #በአበባ ክብራችንን #ጋቢ በማልበስና ታሪካቸውን በመሰነድ ማቅረብ ጀምረናል። የመጀመሪያ ዙር #30ዎቹ_ባለውለታዎች ዘውትር እሁድ እየቀረበ ይገኛል።
    ሐሳባችንን ስንገልፅላቸው ደግፈው የምናለብሰውን ጋቢ (30 ጋቢዎች) መግዣ ያበረከቱልን በባህር ማዶ የሚኖሩት ፍቅሩና ጓደኞቹ ከፍ ያለ አክብሮት አለን። ለዝግጅታችን መሳካት የናንተ የሐሳብም ሆነ የገንዘብ ድጋፍና ማበረታቻ፣ የኛም የኒዜ፣ እውቀትና የገንዘብ አስተዋፅኦ ድምር ውጤት ነውና እጅግ እናመሰግናለን።
    በዚህ መርሐ ግብር  ክብራችንን በጋቢ፣ ፍቅራችንን በአበባ የምንገልፅ ሲሆን ጋቢ ተገዝቶ ተሰናድቷል አበባውን ግን በየሳምንቱ 300 ብር እኛው እየገዛን ወደ ሰባት የሚጠጉ ባለውለታዎች ጋር ደርሰናል። የቀሩ ወደ 23 ባለውለታዎች ይዘን የምንቀርበውን #የአበባ_ወጭ በመሸፈን ግለሰቦች አልያም ድርጅቶች ከጎናችን ትሆኑ ዘንድ በፍቅር እንጠይቃለን።
      #አንድ_አበባ_ለ_አንድ_ባለውለታ ዋጋው 300 ብር ብቻ!
ማስታወሻ:- የምናቀርባቸው ባለውለታዎች በቅደም ተከተል አይደለም። በአንደኛ ዙር ሲመለመሉ ባላቸው የአስተዋፅኦ መጠን ሳይሆን ከያንዳንዱ ዘርፍ random ነው።
      አበባ ለመግዛት 1000175666137 CBE መጠቀም አልያም በኢንቦክስ ያናግሩን።
የፍቅር የሰላምና የአንድነት አርበኞች!
#ሁለገብ_አገልግሎት| መምህር ጌታቸው ተክሉ
#hawassa| ፍቅራችንንም ክብራችንንም እነሆ
    የሐዋሳ ትዝታ ተመስርቶ የመጀመሪያውን ጉብኝት በመ/ር ድጋፌ (ነብስ ይማር) ካደረግንበት ቀን ጀምሮ በሐሳብም በምክር ከኛጋር የነበሩ፣ በተለየ የማስታወስ ችሎታቸው የመረጃ ቋታችንም የክብር አባላችንም መሆናቸውን በቅድሚያ መግለፅ እንወዳለን!
   መምህር ጌታቸው ተክሉ
መምህር ጌታቸው ተክሉ ባሳለፉት የስራ ዘመን ለሀገራቸው በብዙ የስራ ኃላፊነት አገልግለዋል፡፡ እንዲያው እኔ በጽሁፍ ለመግለጽ እንዲያመቸኝ መምህር እንዲሁም በመሃል ደግሞ እንደልጅነቴ ጋሼ እያልኩ ጽሁፉን ባስነብባችሁ እሳቸውና አንባቢያኖቻችን ቅር እንደማትሰኙ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ወደ 5፡00 ሰዓት ገደማ በመኖሪያ ቤታቸው ደረስን፡፡ በብዙ ፈገግታ ተቀበሉን፡፡ በጠዋት ከቤት ወጣ ብለው እንደተመለሱ ነገሩን፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ የጤና ምርመራ አድርገው አንድ እግራቸውን ከሚያስነክሳቸው በስተቀር ጥሩ ጤንነት ላይ እንዳሉ ሀኪማቸው እንደነገሯቸው አጫወቱን፡፡ እኛም ቀበል አድርገን እግዚአብሔር ከጤና ጋር እድሜን እንዲሰጣቸው ተመኘን፡፡

የመጀመሪያ ጥያቄዬ የነበረው በሚያስተምሩበት ወቅት በጣም ተቆጪ እንደነበሩ ተማሪዎችዎ ነግረውኝ ነበር እርሶ ምን ይላሉ አልኳቸው፡፡ አዎ እቆጣ ነበር ጥፋት ስመለከትና ሳስተምር ሲረብሹኝ አይቼ ማለፍ አልችልም ልክ ናቸው እቆጣ ነበር አሉኝ፡፡ በግል ሕይወትዎና በቤትዎስ ይሄ ባህሪዎ ይንፀባረጋል? አዎ አጠገቤ ያሉ ሰዎች ያውቃሉ ጥፋት ሳይ ፊትለፊት ከመናገር ወደኋላ አልልም፤ ይሄ በቃ ባህሪዬ ነው ምንም ማድረግ እችላለሁ፡፡ አሁንስ ይሄ ባህሪዎ እንዳለ ነው? አይ አሁንማ አረጀሁ ብለው ፈገግ አስባሉን፡፡

መምህር ጌታቸው በ1937 ዓ.ም ጉራጌ ዞን በቡኢ ወረዳ (ከቡኢ 16 ኪ.ሜ ወደ ምድረ ከብድ አቦ በሚወስደው መንገድ) ጨላ በተባለው ቦታ ተወለዱ። የቄስ ትምህርት ቤት ፊደል ከቆጠሩ በኋላ ዳዊት ደግመዋል፣ አስር ዓመት ሲሞላቸው አዲስ አበባ በሚገኘው ልዑል መኮንን ት/ቤት (ያሁኑ አዲስ ከተማ ት/ቤት መርካቶ አወቶብስ ተራ ከ3ኛ ክፍል ጀምሮ በ1952 ዓ.ም) ተምረው በ1961 ዓ.ም የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ። 

  በ1963 ዓ.ም መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ገብተው አንድ ዓመት ደብረዘይት ተናኜ ወርቅ ሃይስኩል የማስተማር  ብሔራዊ አገልግሎት (National Service)፣ በ1965 ዓ.ም ሐምሌ ወር ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እጅ ዲፕሎማቸውን ወስደዋል።

ሲዳሞ ክ/ሀገር ነጌሌ ቦረና ሃይስኩል በእንግሊዝኛ መምህርነት ተመደቡ፡፡ ሁለት ዓመት ካስማሩ በኋላ ቦረና አውራጃ ዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ሲቋቋም ከትምህርት ሚኒስተር በውሰት ተወስደው የቦረና አውራጃ እርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ቅ/ጽ/ቤት የዕለት ደራሽ ኃላፊ ሆነው ለሁለት ዓመታት ሰርተዋል፣ በ1971 ዓ.ም ወደ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የማስተማር ሥራቸውን ተመልሰው እዚያው ቦረና አውራጃ ነጌሌ ሃይሰኩል አስተምረዋል።

#በ1972 ዓ.ም ወደ ሀዋሣ ታቦር ሃይስኩል ተዛወሩ፡፡ በሀዋሣ ታቦር ሃይስልኩል ወስጥ እሰከ 1977 ዓ.ም ካስተማሩ በኋላ መደበኛ ሥራቸውን እየሠሩ ሀዋሣ ማዘጋጃ ቤት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ተመደቡ፣ በ1978 ዓ.ም የሀዋሣ ከተማ ምክትል ሹም ከዚያም ዋና ሹም ሆነው እስከ 1981 ዓ ም ሚያዚያ ወር ድረስ አገለገሉ።

ከ1977 ዓ.ም ጀምሮ ከማዘጋጃ ቤቱ ሥራ ጎን ለጎን የክፍለሀገሩ የቁጥጥር ኮሚቴ አባል ሆነው አገልግለዋል። የሀዋሣ ወረዳ መምህራን ማህበር ተመራጭ ሆነው በገንዘብ ያዥነት  ሠርተዋል።

ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ ሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ቢሮ፣ የቦረና አስተዳደር አካባቢ ፀሐፊ (ሸንጎ ፀሐፊ) ሆነው ተሹመዋል። ቦረና አሰተዳደር አካባቢ እስከ 1983 ዓ.ም ከቆዩ በኋላ በ1984 ዓ.ም ወደ ታቦር ሃይሰኩል ተመልሰው ጡረታ እስከወጡበት እስከ 1994 ዓ.ም ድረስ አስተምረዋል።

ጋሽ ጌታቸው የጡረታ መብታቸውን ካስከበሩ በኋላ:-
1ኛ/አፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ ሀዋሣ ቅርንጫፍ፣ በአስተዳደርና  በተማሪዎች ጉዳይ ኃላፊነት ለሁለት ዓመት፣
  2ኛ/ በደቡብ ኢትዮጵያ የግል ኮሌጅ በዲንነት፣ በአስተዳዳሪነት፣ በውስጥና በውጭ ግንኙነት፣ የኃላፊነት ቦታዎች ለ16 ዓመታት  ሠርተዋል፣
3ኛ/የደቡብኢትዮጵያ ክልል የግል ኮሌጆች ማሕበር ጸሐፊ ሆነው ሠርተዋል።
  እኝህ ሁለገብ የብቃት ማሳያ የሆኑት ብርቱ አባታችን ባሳዩት የስራ ትጋት በተለያዩ ጊዜያት ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል ከሽልማቶቹም መሐከል፡-
   1ኛ/በትምህርት ቤት ደረጃ የምስጉን መምህርነት የምስክር ወረቀት በ1976 ዓ.ም
    2ኛ/በሲዳማ አውራጃ ት/ቤቶች ጸ/ቤት ደረጃ ካሉ መምህራንና ሠራተኞች መካከል ተመርጠው የምስጉን መምህርነት የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል (1975 ዓ.ም)
  3ኛ/በሲዳሞ ክ/ሀገር ት/ቤቶች ደረጃ ካሉ መምህራንና ሠራተኞች መካከል ተመርጠው የምስጉን መምህርነት የምስክር ወረቀትና የገንዘብ ሽልማት አግኝተዋል።
መጥቀስ ይቻላል።

  የትምህርትደረጃቸው፡-
1. ዲፕሎማ በእንግሊዝኛ ቋንቋ
2.በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነጽሁፍ (አማርኛ) ቢ ኤ ዲግሪ (1976 ዓም)
3. Higher Diploma Licence a Certified Professional Teacher Educator (DiLLA UNIVERSITY) January 2007

ጋሽ ጌታቸው አሁን የ79 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ናቸው፡፡ ባለትዳር እና የ6 ልጆች አባት ሲሆኑ 10 የልጅ ልጆቸን አይተዋል፡፡ ባሳለፉ የስራ ዘመናቸው ሀገርንና ህዝብን በታማኝነትና በቅንን እንዳገለገሉ ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ደስተኛ ነኝ የቀረኝን ዕድሜ ፈጣሪን እያመሰገንኩ እኖራለሁ ብለውናል፡፡   

እኛም ህዝባችንን ያገለገሉ ባለውለታዎችን ለመሸለም 30 ሰዎችን ስንመርጥ ከላይ የተጠቀሱትን ስራዎች ባሻገር “የሐዋሳ ትዝታ” ፔጅ እንዲቀጠል በመምክር፤ በማበረታታት፣ ልክ ያልሆኑ ጽሁፎችን ሲመለከቱ በዚህ ቢስተካከል በማለትና በመገሰጽ እሳቸው ካሉበት ዕውቀት ጋር አነፃፀረው ሳይንቁ ትችላላችሁ ጎበዞች በማለት በሀሳብ በመደገፍ እስከአሁኗ ጊዜ ድረስ አብረውን ስላሉ ምስጋናችንን ብቻ ሳይሆን ክብራችንንም ለመግለፅ እንወዳለን።

ጋሼ ክብረት ይስጥልን፡፡ በድጋሚ ረዥም ዕድሜን ከጤና ጋር ተመኘንልዎት፡፡ 

በሐና በቀለ
የፍቅር የሰላምና የአንድነት አርበኞች!
2025/10/19 14:25:08
Back to Top
HTML Embed Code: