ታላቁ ዕርቅ
በመጋቢ ተስፋዬ ጋቢሶ

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት መታሰቢያ ፕሮግራም በሀዋሳ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን ሚያዝያ 25/2016 በጸሎት፣ በዝማሬ፣ የእግዚአብሔርን ቃል በመካፈል፣ እንዲሁም የጌታን መታሰቢያ እራት በጋራ በመውሰድ በአንድ መንፈስ፣ በጋራ አምልኮ ተከብሯል።

በሀዋሳ ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን ከሚያዝያ 21/2016 የጀመረው የጾምና የጸሎት ፕሮግራም ዛሬ በስቅለት ቀን ፍጻሜውን ያገኘ ሲሆን በምስጋና በንስሃ፣ በልመናና በምስጋና ርዕሶች ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር በማሰብ በእንባ ወደ እግዚአብሔር ጸልየዋል።

ከሰኞ እስከ ሐሙስ ባሉት ምሽቶች መጋቢ ታሪኩ ቃባቶ ሰኞ እና ማክሰኞ ምሽት ዮሐንስ ወንጌል 3:14-18 እና ሮሜ 5:1-11 ያለውን ቃል መነሻ በማድረግ "በክርስቶስ የተገለጠው የእግዚአብሔር ፍቅር" በሚል ርዕ፤ እንዲሁም ወንጌላዊ አዳነ አየለ ረቡዕ እና ሐሙስ ምሽት ማቴዎስ 27:1-66፣ማቴዎስ 27:46 የሚገኘውን ቃል መነሻ በማድረግ "ክህደት ፊት የተገለጠ ፍጹም ንጽህና" እና የመተ'ው ስቃይ - የተወን ሲመስለን አልተወንም አይተወንምም!!! በሚሉ ርዕሶች የእግዚአብሔርን ቃል አስተምረዋል።

በፕሮግራሙ መጨረሻ በዛሬው የስቅለት ፕሮግራም ላይ የቤተክርስቲያኒቱ አባላት በአንድነት የጌታን እራት ወስደዋል። የጌታ እራት መታሰቢያውን ፕሮግራም የመሩት መጋቢ ተሾመ ወርቁ ሲሆኑ ከመጽሀፍ ቅዱስ ሉቃ 22:14-20፣ 1ኛ ቆሮ 5:7 እና 1ኛ ቆሮ 11: 23-24 ያሉትን ክፍሎች በማንበብና በመጸለይ ፕሮግራሙን አካሂደዋል።

በዛሬው የስቅለት መታሰቢያ የአምልኮ ፕሮግራም ላይ መጋቢ ተስፋዬ ጋቢሶ ሮሜ 5:1-10 ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መነሻ በማድረግ "ታላቁ እርቅ" በሚል ርዕስ የእግዚአብሔርን ቃል አካፍለዋል።

"ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤" (ሮሜ 5 ፡10)

በዚህ የፋሲካ በዓል ወቅት ልናሰላስላቸው ከሚገቡ አሳቦች አንዱ መታረቅ ነው። በዋናነት ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ። አቻ የማይገኝለት ታላቁ ዕርቅ። በኃጢአት በወደቀና ከእግዚብሔር ጋር በተጣላ ዓለም ውስጥ የምንኖር ነን። ከመታረቃችን በፊት እኛም የጥሉ ተሳታፊዎች ነበርን። የመታረቅ ጉዳይ አንገብጋቢና ለነገ የማይባል ነው፤ መታረቃችን መዳናችን ስለሆነ። መታረቃችንና መዳናችን ተያይዘው ተገልጸዋል። "ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን።"

የታረቅነው በእግዚአብሔር ልጅ በክርስቶስ ሞት ነው። ሞቱም የመስቀል ሞት ነው። ጭንቁና ስቃዩ እጅግ ከባድ የሆነበት የውርደት ሞት። ሞቱ የምትክነት፣ ስለሁላችን ኃጢአት የተፈጸመ ሆኖ፣ አስቀድሞ የታሰበበትና ዓላማ ያለው ነው። (ኢሳ 53) ዓላማው ግንኙነትን የማደስ (የማስታረቅ)፣ እኛን ከኃጢአታችንና ከሞት የማዳንም ነው።

ቀድሞ የነበርንበት አጠቃላይ ሁኔታችን የተገለጠባቸው ቃላት አሉ፦

ደካሞች - ራሳችንን መርዳት ወይም ማዳን የማንችል (5:6)
ኃጢአተኞች - በቅዱሱ አምላክ ፊት ለመቅረብ የሚያበቃ ተቀባይነት -
ጽድቅም ቅድስናም - ያልነበረን (5:8)
ጠላቶች - አመጸኞች፣ የእግዚአብሔር ተቃዋሚዎች፣ (5:10)
መታረቅ በእጅጉ የሚያስፈልገን ነበርን።

ስለ መታረቃችን ሦስት ነገሮች:-
1. መታረቃችን ያስፈለገው ጥል ስላለ ነው። ጥሉ በቀዳሚነት የገባው በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ነው። ጥሉ በበደላችን፣ በኅጢአታችን፣ በአልታዘዝ ባይነታችን፣ በአመጸኝነታችን ምክንያት የገባ ነው። ጥልና ጠላትነት ክፉ ነው። የፍቅርና የሕብረት ተቃራኒ ነው። ጥል ግድግዳ ሆኖ በሰላም መተያየትን ይከለክላል። የሚጥለው ጠባሳና የሚያደርሰው ጥፋትም እጅግ ከባድ ነው። የሰላም እጦት፣ ጭንቀት፣ መንፈሳዊ ስብራትና ሞት፣ የጥል ውጤቶች ናቸው። መፍትሔው መታረቅ ብቻ ነው።

2. መታረቃችን፣ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መመለሳችን፣ ደኅንነታችን ነው። መዳናችን፣ እንደ ቀላል የምናየው አይደለም፤ እጅግ ታላቅ ነው። ታላቅ መዳን የተባለ። (ዕብ 2፡3)
ከታላቁ የእግዚአብሔር ቁጣ፣ ከታላቁ የእግዚአብሔር ፍርድ፣ ከታላቁ ሞት ታላቅ ዋጋ ተከፍሎልን ስላመለጥን፣ መዳናችን በእርግጥም ታላቅ ነው። ያገኘነው መታረቅ ወደ መዳን፣ ለዘላለም በሕይወት ወደ መኖር አድርሶናል።

3. መታረቃችን፣ ከላይ እንዳየነው፣ ዋጋ ተከፍሎበት የተገኘ ነው። አሁን ሰላም ወርዷል። ይህ የሆነው በመስቀል ላይ በተፈጸመው በልጁ የምትክነት ሞት፣ በክርስቶስ የመሥዋዕትነቱ ደም አማካይነት ነው። መሥዋዕቱ ከመሥዋዕቶች ሁሉ፣ ደሙም ከሌላው ደም ሁሉ፣ የላቀና የሚሻል ነው። ይህን አውቀን በስሙ ስናምን ከታላቁ የእግዚአብሔር ቁጣ፣ ከሞት ፍርድ ድነናል።

በዚህ ምክንያት፣ የመስቀሉ ሥራ ትኩረታችን፣ በክርስቶስ በኩል የተገለጠልን የእግዚአብሔር ፍቅርና ምሕረት፣ ያገኘነው መታረቅ፣ ማዕከላዊ መልዕክታችን ሆኗል። "እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ።እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን።" (2 ቆሮ 5፡ 19-20)

ታላቁ ዕርቅ፣ መልካሙ የምሥራች፣ የደስታችን መግለጫና ምስክርነታችን ነው። ጌታ እስኪመጣ ድረስ የመስቀሉን መልዕክት፣ ሞቱንና ትንሣኤውን የመናገር ኃላፊነት ተሰጥቶናል። መጽሐፍ እንደሚል እያልን። (1ቆሮ 15፡3) ይህን ስናደርግ መዘንጋት የማይገባን አንድ ሌላ ጉዳይም አለ። ስለተሰቀለልን ክርስቶስ ስናወራ፣ እኛም ራሳችንን በመካድ፣ መስቀላችንን ተሸክመን፣ መከራችንን እየታገስን፣ ጌታን መከተል ይኖርብናል። መስቀል መሸከም መልዕክት አለው። የተሸካሚውን መሰቀል። ራሱን የካደ መስቀል ተሸካሚ፣ እንደ ጳውሎስ "ከክርስቶስ ጋ ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም፤ ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤..." ይላል። (ገላ 2:20) መስካሪ ስለተሰቀለው ክርስቶስ ተናጋሪ ብቻ ሳይሆን፣ በሕይወቱ መስቀል ተሸካሚም ነው።

በዓለማችን ላይ ወደ ሞት የሚያመራ ከባድ ጥል አለ። ጥሉ የገባው በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ነው። ጥሉ የተዘራው በሰውና በእግዚአብሔር መካከል በገባው በቀደመው በተንኮለኛው ዕባብ፣ በሰይጣን ነው። የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ 3ኛ ምዕራፍ የሚነግረን ይህንን ነው። መታረቅ አንገብጋቢ ጉዳያችን ነው።

እግዚአብሔር አምላክ መታረቃችንን አቅዶ ፈጽሞልናል። ለዕርቅ የሚሆን ሙሉ ዋጋም ከፍሎልናል። ዋጋው የክርስቶስ ክቡር ደም ነው። በእምነት ይህን የተቀበልን በንስሐ የተመለስን ታርቀናል። ዕርቃችን በእርግጥ ታላቅ ነው። የታረቅነው ከእግዚአብሔር ጋር ነው።

ዕርቁ ወደ ባልንጀራችንም የሚዘልቅ ነው። በክርክቶስ ደም በእውነት የታረቀ የሰላም ሰው ይሆናል። ከሰውም ጋር ይታረቃል፤ ያስታርቃል። የማስታረቅን ቃል፣ ወንጌሉን ይሸከማል። እኛም፣ በክርስቶስ በኩል፣ የማስታረቅና፣ የማዳኑ ጥበብና ኃይል የተገለጠበትን የመስቀሉን ቃል፣ እስከ ፍጻሜው ድረስ እንሰብካለን።

ክብር ለታረደልን፣ ከኃጢአታችን በደሙ ላጠበን፣ ላስታረቀን፣ ለቀደሰን፣ ላጸደቀን፣ በመስቀል ሞቱ ላዳነን፣ ለዋጀን፣ ገንዘቡም ላደረገን፣ ለእግዚአብሔር በግ፣ ለክርስቶስ ይሁንለት።

YouTubeFacebookInstagramTelegram

የሀዋሳ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን ስነፅሁፍና ስነዳ አገልግሎት
ሚያዝያ  25/2016 ዓ.ም
ለጌታችንና ፣ ለመድኃኒታችን ፣ ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ መታሰቢያ በዓል
እንኳን በሰላም አደረሳችሁ!


የሀዋሳ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን
Follow Us
YouTube (https://is.gd/FGBCHawassaYoutube)
Facebook (https://facebook.com/FGBCHawassa)
Instagram (https://ig.me/FGBCHawassa)
Telegram (https://www.tg-me.com/hawassafullgospelch)
የክርስቶስ የትንሣኤ ውጤት
በመጋቢ ሰለሞን ጃቢር

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ መታሰቢያ ፕሮግራም በሀዋሳ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን ሚያዝያ 27/2016 በጸሎት፣ በዝማሬ፣ የእግዚአብሔርን ቃል በመካፈል፣ ትንሳኤውን በማሰብ በታላቅ ደስታና አምልኮ ተከብሯል።

በዛሬው የትንሣኤ መታሰቢያ የአምልኮ ፕሮግራም ላይ መጋቢ ሰለሞን ጃቢር 1ኛ ቆሮ. 15 ፡ 20-22 , 55-57 ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መነሻ በማድረግ "የክርስቶስ የትንሣኤ ውጤት" በሚል ርዕስ የእግዚአብሔርን ቃል አካፍለዋል።

መግቢያ
በሰው ልጆች የሕይወት ታሪክ ውስጥ ከሞት በላይ ጠላት የለባቸውም፡፡ ሞት በኃጢአት ምክንያት የመጣ የሰው ልጆች ጠላት ነው፡፡(ሮሜ 6፡23)፤ የሰው ልጆች ሊቆጣጠሩት ያልቻሉት እና የማይችሉት ጠላታቸው ሞት ነው፡፡ ሞትን ቴክኖሎጂ ፣ እውቀት ፣ ገንዘብ ፣መድሐኒት ሊይዘውና ሊያቆመው አልቻለም ደግሞም አይችልም፡፡ ሞት እያንዳንዳችንን በተለያዩ መንገዶች እያደነን የሚጠቃን ነው፡፡

በዚህ ጊዜ በጣም ደስ የሚለውና ሐሴት ልናደርግበት የሚገባን ጠላታችን የሆነውን ሞትን ክርስቶስ ኢየሱስ በትንሳኤው አሸንፎታል፡፡ ጠላታችን ሞት በክርስቶስ ኢየሱስ የተሸነፈ እና የተማረከ ነው፡፡(ሐዋ.2፡24) የመጀመሪያው ሰው ከሞተበት ጊዜ አንስቶ የተዘጋውን የሞት በር በትንሳኤ ኃይል ሰብሮ የከፈተው ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ክርስቶስ ኢየሱስ ሞትን ያሸነፈው ለራሱ ብቻ አይደለም፡፡ ለእኛም ጭምር ነው(1ኛቆሮ.15፡20 –22)፡፡

የክርስቶስ ኢየሱስ ትንሳኤ የእኛም ዋስትና ነው፡፡ ሞት አያስፈራንም፡፡ በክርስቶስ የተሸፈ ነው፡፡ (1ኛቆሮ.15፡55–57) ጠላታችን ሞት አንድ ጊዜ ለሁሉም ተሸንፏል፡፡ በእውነተኛው መጽሐፍ ቅዱሳዊው የክርስትና እምነት ውስጥ የክርስቶስ ኢየሱስ ትንሳኤ ትልቅ ሥፍራና ብዙ ጠቀሜታ አለው።

ክርስቶስ ኢየሱስ ከሙታን በመነሳቱ ምክንያት ያገኘነው እና የምናገኘው ብዙ ጠቃሚ ነገሮች አሉ፡፡
በዚህ ቀን ጥቂቱን እንመለከታለን ፡-

1. የክርስቶስ ኢየሱስ ትንሳኤ ዳግመኛ ለመወለዳችን ና የእግዚአብሔር ልጆች ለመሆናችን ማረጋገጫ ነው (1ኛ ጴጥ. 1፡3-5)፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል 1ኛ ጴጥ. 1፡3-5 ፡፡ በዚህ ቦታ ላይ እንደምንመለከተው “ሁለተኛ የወለደን” የሚለው ሀሳብ የሚያሳየን የእግዚአብሔር ልጅነትን ነው፡፡ እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ትንሳኤ እንደወለደን እና የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችን ነው፡፡ ይህ ልጅነታችን የተያያዘው ከክርስቶስ ኢየሱስ ትንሳኤ ጋር ነው፡፡


የክርስቶስ ኢየሱስ ትንሳኤ መጀመሪያ - ክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ መሆኑን የተረጋገጠበት ነው (ዮሐ.3፡16)፡፡ አይሁዶች ያልተቀበሉትና ክርስቶስ ኢየሱስ በተያዘበትና በተሰቀለበት ጊዜ የተዘባበቱበት እና የቀለዱበት በእግዚአብሔር ልጅነቱ ነበር(ማቲ. 27፡ 40, 43)፡፡ እግዚአብሔር ግን አንድያ ልጁ እንደሆን በትንሳኤ ኃይል አረጋገጠ (ሐዋ.13፡32- 33 ፣ሮሜ.1፡4)፡፡

ሁለተኛ - እኛ የእግዚአብሔር ልጆች የሆንበት ነው ፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው እኛ ዳግመኛ (ሁለተኛ) በመወለድ የእግዚአብሔር ልጆች የሆንበት ነው፡፡ ዮሐ. 15 ፡13 -15 ላይ ክርስቶስ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ለደቀመዛሙርቱ “…ወዳጆቼ..” ብሉ ይጠራቸው ነበር፡፡ ዮሐ. 20፡ 16- 17 ላይ ከትንሳኤ በኋላ ግን እነዚህኑ ደቀመዛሙርት “ ወንድሞቼ” አላቸው፡፡ ለምን ? በሞቱና በትንሳኤው በማመናቸው ዳግመኛ ስለተወለዱ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን የልጅነት መብት ስላገኙ ነው፡፡

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዮሐ. 12፡24 ላይ እንዲህ አለ፡- “ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች” አለ። በዚሁ መሰረት ክርስቶስ ኢየሱሰ ሞተ፤ በትንሳኤው ብዙ ፍሬ አፈራ፡፡ ለእግዚአብሔር ብዙ ወንድ ልጆች እና ሴት ልጆች አፈራ፡፡ ለእርሱ ደግሞ ብዙ ወንድሞችንና እህቶችን አፈራ፡፡ ኢሳ.53፡10 ላይ እንዲህ የሚል ቃል አለ “..ዘሩን ያያል፥ …”ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሳኤው ዘሩን እያየ ነው፡፡ ብዙ እህቶችንና ወንድሞችን አግኝቷል፡፡ ወደፊትም ያገኛል፡፡ እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ትንሳኤ፡- ክርስቶስን ኢየሱስ አንድያ ልጁ መሆኑን አረጋገጠ ፣ እኛን ደግሞ የእርሱ ብዙ ልጆቹ መሆናችንን አረጋገጠ ፣ ለክርስቶስ ብዙ ወንድሞቹ እና ብዙ እህቶቹ አደረገን(ሮሜ.8፡ 28-29)።

በክርስቶስ ኢየሱስ ከሙታን በመነሳቱ ዳግመኛ በመወለድ የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናል(ዮሐ.1 ፡12 -13 ) ክርስቶስ ኢየሱስ ከሙታን ባይነሳ ማን ይቀበለዋል ? ሦስተኛው - እኛ አዲስ ማንነትን ያገኘንበት ነው፡፡ እኛ በክርስቶስ ኢየሱስ ትንሳኤ ዳግመኛ ተወልደን የእግዚአብሔር ልጆች በመሆን አዲስ ማንነት አግኝተናል፡፡ ይህ አዲስ ማንነት ከእግዚአብሔር ጋር ህብረት ማድረግና እግዚአብሔርን መታዘዝ የሚችል ማንነት ነው፡፡

እኔና እናንተ በክርስቶስ ኢየሱስ ትንሳኤ ከእግዚአብሔር ጋር ህብረት የሚያደርግ እና እግዚአብሔርን የሚታዘዝ የሰውነት አካልና መንፈስ አግኝተናል፡፡ በዚህ አካላችንና መንፈሳችን ከእግዚአብሔር ጋር ህብረት ማድረግና እርሱን መታዘዝ እንድንችል ተደርገናል፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ህብረት የሚያደርግና እርሱን የሚታዘዝ ሁለንተና አግኝተናል፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ በትንሳኤው ልክ እንደ እርሱ ያለ ህይወት እንዲኖረን አድርጎልናል፡፡ ክርስቶስን ያስነሳው የእግዚአብሔር ኃይል በእኛም ይሰራል፡፡

2. የክርስቶስ ኢየሱስ ትንሳኤ ለሰው ልጆች ኃጢአት የተከፈለው ምስዋዕት መጠናቀቁና በእግዚአብሔር ፊት መጽደቃችንን ማረጋገጫ ነው(ሮሜ 4፡25)፡፡

የክርስቶስ ትንሳኤ ለሰው ልጆች ኃጢአት የተከፈለው ምስዋዕት መጠናቀቁን መግለጫ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል ሮሜ.4፡24 -25 ፡፡ የክርስቶስ ትንሳኤ ክርስቶስ ኢየሱስ ደሙን ወደ እግዚአብሔር ዙፋን ያቀረበበት ነው (ዕብ.9፡22 )፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ ሞቶ ደሙን ስለ ኃጢአት በቀራኒዮ መስቀል አፍስሷል፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ ለዓለም ሁሉ ኃጢአት ዋጋ ወይም እዳ ከፍሏል(1ኛ ዮሐ. 2፡2)፡፡ ክርስቶስ በትንሳኤው ደሙን ወደ ቅዱሰ ቅዱሳን ይዞ በመግባት አንድ ጊዜ ለሁሉም በእግዚአብሔር ፊት አቅርቧል፡፡ ክርስቶስ በእንስሳ ደም አይደለም የገባው፡፡ በራሱ ቅዱስ ደም ነው የገባው(ዕብ.9፡12)፡፡

የኃጢአታችሁ እዳ ወይም ዋጋ ተከፍሏል ብሎ በትንሳኤው አረጋገጠልን፡፡እግዚአብሔር የክርስቶስ ኢየሱስን ምስዋዕት እንደተቀበለ አረጋግጦልናል(ሮሜ.6፡4-5)፡፡
የክርስቶስ ትንሳኤ በእግዚአብሔር ፊት መጽደቃችንን ማረጋገጫ ነው ፡፡ ሮሜ 4፡25“… እኛን ስለ ማጽደቅም የተነሣውን ጌታንችንን ኢየሱስን ከሙታን ባስነሣው ለምናምን ለእኛ ይቈጠርልን ዘንድ አለው።” በእግዚአብሔር ፊት የጸደቅነው ወይም ተቀባይነት ያገኘነው በክርስቶስ ኢየሱስ ትንሳኤ ነው፡፡ የጽድቃችን መሰረት እና ምክንያት የሆነው የክርስቶስ ትንሳኤ፡፡ በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ እግዚአብሔር ተቀብሎናል (ሮሜ.6፡23)፡፡
የክርስቶስ ኢየሱስ ትንሳኤ በእግዚአብሔር ፊት እዳችን ሙሉ ለሙሉ መከፈሉንና መጽደቃችንን ያረጋግጥልናል፡፡ ኃጢአት የሌለብን ጻድቃን መሆናችንን እና ተቀባይነት እንዳገኘን ያሳየናል፡፡ እግዚአብሔር እንደተቀበለን ያረጋግጥልናል፡፡ የክርስቶስ ትንሳኤ የሚያሳየን እግዚአብሔር በክርስቶስ ሞት መርካቱንና መደሰቱን ያመለክታል፡፡ ስለ ኃጢአታችን የተከፈለውን ዋጋ ሙሉ ለሙሉ እንደተቀበለውና እዳችንን እንደሰረዘው ያሳየናል፡፡
የክርስቶስን መስዋዕትነት ተቀብሎ እኛ ከእርሱ ጋር ግንኙነት ማድረግ እንደምንችል የሚያረጋግጥልን ነው፡፡ ክእግዚአብሔር ጋር ህብረት እንዳለንና መገናኘት እንደምንችል ያሳየናል፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር መቆማችንን የተረጋገጠበት ነው፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ ከሙታን ሲነሳ እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ የተሰራውን የደህንነት ሥራ መፈጸሙን አረጋግጧል፡፡ የደህንነት ስራው መጠናቀቁን አውጇል፡፡ እንዴት ? ፊል.2፡8 -10 “ … እስከ ሞት የታዘዘ ሆነ - በሞት ዋጋ ከፈለ እንዲሁም ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው - በትንሳኤው ነው

3. የክርስቶስ ኢየሱስ ትንሳኤ እኛም እንደምንነሳ እና እንደተነሳን ማረጋገጫ ነው ( 1ኛ ቆሮ. 15፡20-22 ፣ቆላ.3፡1 )

የክርስቶስ ኢየሱስ ትንሳኤ እኛም በትንሳኤ አካል እንደምንነሳ ማረጋገጫ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል 1ኛ ቆሮ. 15፡20-22 ፡፡ የክርስቶስ ኢየሱስ ትንሳኤ ወደ ፊት እኛም እንደምንነሳ ዋስትናና ማረጋገጫ ነው፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ያመንን እኛም እንደ እርሱ እንደምንነሳ ማስረጃችን ነው፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ በክብር እንደተነሳ በክብር እንነሳለን፡፡ የክርስቶስ ኢየሱስ ትንሳኤ የእርሱ ብቻ አይደለም፡፡ የእኛም ጭምር ነው፡፡ የአንተም ጭምር ነው ፡፡ የአንቺም ጭምር ነው፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ የሞተው ፣የተቀበረው እና የተነሳው ለእኛ ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱሳችን የሚነግረን የእኛ ትንሳኤ የተያያዘው ከክርስቶስ ኢየሱስ ትንሳኤ ጋር ነው 1ኛቆሮ. 6፡14 ፣2ኛቆሮ. 4፡14 ፣1ኛቆሮ.15 ፡20 ላይ “ … አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል።” ይላል፡፡“ በኩር” ይላል በኩር ካለ ተከታይ አለ ማለት ነው፡፡ በዚህ ምድራዊ አካል የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩም በሚመጣው የትንሳኤ አካል ግን አይኖሩም (ፊል.3፡21 ፣ 1ኛ ዮሐ.3፡2 ፣1ኛ ቆሮ.15፡51-57)፡፡ እኔንና እናንተ በክርስቶስ ኢየሱስ ስለሆንን እግዚአብሔር የገባልንን ተሰፋ ይፈጽመዋል፡፡ የክርስቶስ ኢየሱስ ትንሳኤ በእርሱ እንደ እርሱ እንደምንነሳ ያረጋግጥልናል፡፡

የክርስቶስ ኢየሱስ ትንሳኤ እኛም እንደተነሳን ማረጋገጫ ነው (ቆላ.3፡1 )፡፡ ትንሳኤ ወደፊት ብቻ አይደለም፡፡ እኛ አማኞች ተነስተናል ፡፡ እውነት ነው በክርስቶስ ኢየሱስ አምነን ክርስቲያኖች ስንሆን በዚህ ሰውነታችን ሁሉንም የትንሳኤ ሕይወት አላገኘንም፡፡ እሰከ አሁን ድካምና ጉድለት አለብን ፡፡ ህመምና ሞት አለብን ፡፡ ሆኖም ግን በመንፈሳችን ሕያው ሆነኗል፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ትንሳኤ አምነን መንፈሳችን የትንሳኤ ኃይልን አግኝቷል፡፡ እኛ በክርስቶስ ኢየሱስ ያመንን አማኞች መንፈሳዊ ትንሳኤ ተነስተናል፡፡ ለእግዚአብሔር ነገር ሙት የነበረው እውቀታችን ፣ ስሜታችንና ፈቃዳችን ትንሳኤ አግኝቶ ህያው ሆኗል፡፡ ስለዚህ እውቀታችንን ለእግዚአብሔር እውነት እያስገዛን ነው፡፡ ስሜታችንን /ፍላጎታችንን ለእግዚአብሔር ፍቅር እያስገዛን ነው፡፡ ፈቃዳችንን ለእግዚአብሔር ስልጣን ለማስገዛት እየጣርን ነው (ቆላ.2፡12-13፣ ቆላ.3፡1-2 ፣ ገላ. 3፡ 27 ፣ኤፌ. 2፡ 5) ፡፡

ማጠቃለያ
በክርስቶስ ኢየሱስ ትንሳኤ እኛ ዳግመኛ ተወልደን የእግዚአብሔር ልጆች በመሆን አዲስ ማንነት ካገኘን ፣ የኃጢአታችን እዳ ተከፍሎ በእግዚአብሔር ፊት ከጸደቅን ወይም ተቀባይነት ካገኘን ፣ አሁን መንፈሳዊ ትንሳኤ ስለ ተነሳንና ወደፊት በከበረ አካል ስለምንነሳ እንዴት መኖር አለብን ? እውነተኛው መጽሀፍ ቅዱሳችን እንደሚለን መኖር አለብን ፡፡
1. ምድራዊውን ሳይሆን ሰማያዊውን ወይም በላይ ያለውን በማሰብና በመሻት ወይም መፈለግ መኖር (ቆላ. 3፡1 -2)፡፡
2. ክርስቶስ ኢየሱን በመምሰል መኖር (ሮሜ.8፡ 28-29)፡፡
3. በእግዚአብሔር ኃይል ተስፋ በማድረግ መኖር (ሮሜ.6፡14 ፣ሐዋ. 1፡8 )

መልካም የትንሳኤ መታሰቢያ በዓል ይሁንላችሁ !!
Follow Us
🎬 YouTube (https://is.gd/FGBCHawassaYoutube)
📱 Facebook (https://facebook.com/FGBCHawassa)
📷 Instagram (https://ig.me/FGBCHawassa)
✈️ Telegram (https://www.tg-me.com/hawassafullgospelch)

የሀዋሳ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን ስነፅሁፍና ስነዳ አገልግሎት
ሚያዝያ 27/2016 ዓ.ም
Please open Telegram to view this post
VIEW IN TELEGRAM
የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ እናድርግ
በዶክተር አዳሙ አሰፋ

በሀዋሳ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን ግንቦት 4 /2016 ዓ.ም የተካሄደው የእሁድ የጉባኤ የዝማሬ፣ የፀሎት ፣ የአምልኮ እና የቃል ጊዜ

በዕለቱ በነበረው የቃል አገልግሎት ዶክተር አዳሙ አሰፋ  ሰቆቃው ኤርምያስ 3: 26 እና ምዕራፍ 1-5 የሚገኘውን   የእግዚአብሔር ቃል መሰረት በማድረግ " የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ እናድርግ" በሚል ርዕስ ቀጥለው በቀረቡት  ነጥቦች ላይ የእግዚአብሔርን ቃል አስተምረዋል።

በአንድ ወቅት ስለሃገራችን ኢትዮጵያ ከረጅም ዘመናት ጀምሮ እስሳሁን ስላለው ጦርነት፣ የኢኮኖሚ ማሻቀብ፣ የተለያዩ በሽታዎች አጠቃላይ ስለምድሪቱ ጉስቁልና እያሰብኩ ከጓደኞቼም ጋር እየተጫወትን ባለንበት ወቅት  የእግዚአብሔር ቃል ወደ ውስጤ መጣ።

ከጓደኞቼ ጋር ብዙ አውርተን፣ አዝነን፣ ተስፋ ቆርጠን፣ ተማረን እያለ ከመሃከላችን አንዱ ወንድም “ሰው ዝም ብሎ “ በማለት መናገር ሲጀምር ገና ሳይጨርስ ከአፉ ላይ ነጥቄው “ሰው ዝም ብሎ የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው” አልኩኝ። ከዛም ይህ በውስጤ የመጣው ቃል እግዚአብሔር የሰጠኝ መልዕክት ነው ብዬ ወሰድኩት።

ከመፅሐፍ ቅዱስ ሰቆቃው ኤርምያስ ላይ ያለውን እግዚአብሔር የሰጠኝን መልዕክት ዛሬ ይዤላችሁ ቀርብያለሁ።

የሰቆቃው ኤርምያስ መፅሐፍ የሀዘን እንጉርጉሮ ነው። የእስራኤል ህዝብ አይሁዳውያን ወደምርኮ በተወሰዱ ጊዜ ጠላት ያደረሰባቸውን ሁኔታ ኢየሩሳሌም እንዴት እንደፈረሰች፣ ህዝቡ እንዴት እንደተጋዘ፣ በምን አይነት አሰቃቂ ሁኔታ ላይ እንደነበሩ፣ ህዝቡ ወደ ረሃብ፣ ወደ እጦት እንዴት እንደሄዱ የሚያወራ የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው።

ህዝቡ በባቢሎን መንግስት ሲማረከ  በወቅት ነገስታቱ፣ ነቢያቱ፣ ካህናቱ የተሰቃዩበት፣ የተገደሉበት ዘመን መሆኑን እናያለን። በህዝቡ ላይ እርዛት፣ ረሃብ፣ ውርደት የደረሰበት እጅግ አስከፊ ዘመን ነበር። እግዚአብሔር አብሯቸው ስለነበር ብዙዎች የሚፈሯቸው እስራኤላውያን፣ አይሁዶች ያ መፈራታቸው ቀርቶ በታላቅ መከራና ውርደት ውስጥ የገቡበት የአምልኳቸው ስርዓት፣ የበዓላት መከበር የቀረበት እጅግ አስከፊ ዘመን ነበር።

የዚህ መፅሐፍ ፀኃፊ ህዝቡን ወክሎ በተለያዩ አፃፃፍ ዘዴዎች ስለወቅቱ መከራ፣ ስቃይና ችግር ሲናገር እግዚአብሔር ራሱ ጠላት ሆነብን ይላል። ወደ መቅደስ እንዳይገቡ የተከለከሉ ሰዎች ወደ ቤተመቅደሱ ገቡ። ቤተመቅደሱ ፈርሶ ካህናት ብቻ መግባት በሚገባቸው ስፍራ አህዛብ ገቡ። ባቢሎናውያን ገቡ፤ ተዋረድን። ገዢዎቻችን ተሰደዱ። በጎረቤቶቻችን፣ በጠላቶቻችን ተናቅን እያለ ብዙ ሮሮ ያሰማል።

እነዚህ ሰዎች ወደዚህ ሰቆቃ፣ ችግር ለምን ገቡ? እግዚአብሔር እነዚህ ሰዎች እንደዚህ ለመከራ አሳልፎ የሰጣቸው ዝም ብሎ ነው ወይ? ይህ የእግዚአብሔር ቅጣት ነው። እግዚአብሔር ሲቆጣ ነው እንዲህ የሚሆነው?

በዚሁ በሰቆቃው ኤርምያስ መፅሐፍ ውስጥ መልሱን ፀሐፊው ይናገራል።

1. ኢየሩሳሌም ኃጢአት በመስራትዋ ይህ ችግር ደርሶባታል (ሰቆ ኤር 1:15፤ 1:14 ወዘተ)።

በዚሁ መፅሐፍ  ሰቆኤር 1:14 ላይ “ኃጢአቶቼ ቀንበር ሆኑ፤ በእጆቹ ላይ ተገመዱ፤ በአጥቴን ላይ ተጭነዋል፤ ሀይሌን አደከመ። ጌታ በፊታቸው እቆም ዘንድ በማልችላቸው እጅ አሳልፎ ሰጠኝ።  ተብሎ ተፅፏል።
በመቀጠል ይህ መፅሐፍ ከሀገራችን ኢትዮጵያ ጋር በተወሰነ መልኩ የሚያመሳስለው ነገር አለው። ሀገራችን ለረጅም ዘመናት በችግር ውስጥ አለች።  ይህን ሳስብ ሁለት መሠረታዊ ነገሮች በልቤ አሉ።  የመጀመሪያው ህዝባችን ለምን ሁል ጊዜ በችግር በመከራ ውስጥ ይኖራሉ የሚል ጥያቄ በልቤ አለ። “ለዘመናት የማይፈታ እንቆቅልሽ ውስጥ ለምን ገባን” የሚለውን እንጠይቃለን። ለዚህም በእግዚአብሔር ፊት ስለጥፋታችን ዝም ብለን ማልቀስ አለብን።

2. እስራኤላውያን ኃጢአት በመስራታቸው ስለ ኃጢአታቸው ወደ እግዚአብሔር ይፀልዩ ነበር።

እስራኤላውያን  በዚህ ችግር ውስጥ ሲያልፉ ዝም አላሉም። ኃጢአት መስራታቸውን ተረድተው  ስለ ኃጢአታቸው ወደ እግዚአብሔር ይፀልዩ ነበር። እኛም እንደ ሀገር፣ እንደ ህዝብ በእግዚአብሔር ፊት ማልቀስ መጮህ አለብን።
ፀሐፊው ስለ ነበሩበት ሁኔታ በእግዚአብሔር ፊት ይፀልያል። ያሉበትን ችግር መከራ ህዝቡን ወክሎ ይፀልያል።( 3:55-59፤ 1:11፤ 1:20 2:18-20)። እንደመፍትሄ አድርጎ ያስቀመጠው ፀሎትን ነው። ብርቱ ፀሎት እንደደሚያስፈልግ ይነግራቸዋል።

ይህንን አስበን ስለ ሀገራችን ስናስብ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንደ ህዝብ ምን ኃጢአት ሰርታለች? እግዚአብሔር ሁሉን ኃጢአት ይጠላል። በጣም የሚፀየፈው ኃጢአት ደግሞ ከርሱ ውጪ ለሌላ አምላክ የሚቀርብ አምልኮ እና ስግደትን ነው። ለሰይጣን የሚደረጉ አምልኮዎች፣ ፀሎቶች በሀገራችን የሉም ወይ? ይህ እግዚአብሔርን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያስቆጣው ኃጢአት ነው።
ለሰይጣን አስራት የሚሰጡ፣ ራሳቸውንም፣ ልጆቻቸውንም ለሰይጣን አሳልፈው የሚሰጡ አሉ። ይህን ታላቅ ኃጢአትን እግዚአብሔር እንዴት አይጠላውም? እንዴት አይፀየፈውም? ይህ እያለ ታድያ ሀገራችን እንዴት ትባረካለች?

3. የእግዚአብሔር ባህርይ መለስ ብለው እንዲያስታውሱ አደረጋቸው። (3:22-33)

በዚህ ስፍራ የምንማረው ሦስተኛው የእግዚአብሔር ባህርይ መለስ ብለው እንዲያስታውሱ አድርጓቸዋል። ይህን ነገር  ሳስብ ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምህረት የተነሳ ነው። "ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና።  ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህ ብዙ ነው" ሰቆቃው ኤርምያስ 3 : 22-33

ይህን ስናስብ ድርሻችን /እድል ፈንታችን/ እግዚአብሔር መሆኑን አሰብን። እግዚአብሔር ለሚፈልጉት መልካም አምላክ ነው። ጌታ ለዘላለም የሚጥል አምላክ አይደለም። በመከራ፣ በችግር ውስጥ ስናልፍ  ያዝናል፣ ይራራል።
ስለዚህ የእግዚአብሔርን ባህርይ ማለዳ ሁል ጊዜ አዲስ መሆኑን እናስብ።
እግዚአብሔር ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ የሚራራ፣ የሚያስብ፣ የሚያዝን፣ የሚምር፣ የሚራራ አምላክ ነው።

4.  በንስሃ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰዋል።

በመጨረሻ ይህ ሰው በምዕራፍ አምስት ላይ ወደ ንስሃ ድምዳሜ ይገባል (5:19_21)። በጣም ከፍተኛ ችግር ውስጥ ስንገባ ለምን ተውከኝ? ብላችሁ ወደ እግዚአብሔር እንጩህ። ወደ እግዚአብሔር እንፀልይ። አቤቱ ወደ አንተ መልሰን፣ ዘመናችንን እንደቀድሞ አድስ ብለን ወደ እግዚአብሔር እንጩህ።

Follow Us
• YouTube (https://is.gd/FGBCHawassaYoutube)
• Facebook (https://facebook.com/FGBCHawassa)
• Instagram (https://ig.me/FGBCHawassa)
• Telegram (https://www.tg-me.com/hawassafullgospelch)

የሀዋሳ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን ስነፅሁፍና ስነዳ አገልግሎት
ግንቦት  4/2016 ዓ.ም
2024/05/14 05:42:56
Back to Top
HTML Embed Code: