Telegram Web Link
44ቱ ሙሽሮች ለታራሚዎች ድጋፍ አደረጉ

ጃንደረባው ሚዲያ | ግንቦት 17 2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ በማኅበራዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጃን ጳውሎስና ሲላስ ከጃን ቃና ዘገሊላ ጋር በመሆን 44ቱን ሙሽሮች በማስተባበር በልደታ ክ/ከተማ በሚገኘው በወንጀል ነክ ነገር ውስጥ ገብተው የተገኙ ሕፃናት ማቆያና ተሐድሶ ተቋም ተገኝተው የአልባሳት፣ የንፅህና መጠበቂያ ቁሶች ድጋፍና የምሳ ግብዣ አድርገዋል፡፡

ይህ መርሐግብር በዋናነት የተዘጋጀው ጃን ጳውሎስ ሲላስ አሜሪካን ሀገር ከሚገኘው የሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን (SPOT church) የተበረከተለትን 10 ሻንጣ ልብስ ለዚህ ተቋም ለማስረከብና ጃን ቃና ዘገሊላ ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም በሚያዘጋጀው 2ኛው ብዙኃን ጋብቻ የሚሞሸሩት 44 ጥንዶች ከሰርጋቸው በፊት የታሰሩትን በመጠየቅ የጽድቅ ሥራ ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ፤ የትዳር ሕይወታቸውንም በተመሳሳይ የበጎ ምግባራት እንዲያሳልፉ ለማነሳሳት ነው ያሉት የጃን ቃና ዘገሊላ ተወካይ ዲያቆን በረከት ወርቁ ናቸው፡፡

ከሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን የተበረከተውን 10 ሻንጣ ልብስ እንዲሁም 44ቱ ሙሽሮች የለገሱትን የንፅሕና መጠበቂያ ቁሶች ለተቋሙ ተጠሪ ኃላፊ አቶ ጭምዴሣ ነገሣ ያስረከቡት የኢጃት ቦርድ አባል ወ/ት ማስረሻ ምትኩ ሲሆኑ ታዳጊዎቹ የእርምት ጊዜያቸውን ጨርሰው ሲወጡ እንደ 44ቱ ሙሽሮች ትምህርታቸውን ጨርሰውና ራሳቸውን ችለው የወጣትነት ጊዜያቸውን በመንፈሳዊ አገልግሎት እንዲያሳልፉ ምክር ሰጥተዋል፡፡

በመርሐግብሩ ታዳጊዎቹ ለ44ቱ ሙሽሮች መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡ ሙሽሮቹም በተግባር ለሕጻናቱ አርአያ በመሆን የሰርጋቸውን ዋዜማ መልካም የሆነ ክርስቲያናዊ ተግባርን በመፈጸም ጀምረዋል፡፡ ጃን ጳውሎስና ሲላስ ለሕግ ታራሚዎች የጥየቃ መርሐ ግብር ፣ መንፈሳዊ የምክር አገልግሎትና የመጻሕፍት ልገሳም ላይ ከዚህ ቀደም ሲሠራ እንደቆየ ይታወሳል::
የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ 2ተኛው የብዙኃን ጋብቻ ግንቦት 21 /2017 ዓ.ም
እውነት እላችኋለሁ ከሁሉ ከሚያንሱ ከነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት...
ማቴ 25፡40
ለነዚህ ፎቶዎች “Caption” ይጻፉ
2025/07/01 07:29:56
Back to Top
HTML Embed Code: