Telegram Web Link
ቤተ ክርስቲያን አርባ አራት ጥንዶች ልትሞሽር ነው

| ጃንደረባው ሚድያ | ግንቦት 12 ቀን 2017 ዓ.ም.|

በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ ጃን ቃና ዘገሊላ የቅድመ ጋብቻ ትምህርት ያስተማራቸው 44 ጥንዶችን ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም በቶታል ደብረ ገነት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሊድር እንደሆነ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በማኅበሩ አገልግሎት ላይ ካሉ የውስጥ አባላት መካከል 47 የሚሆኑት በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ጋብቻቸውን የፈጸሙ መሆናቸውን የኢጃት የሰው ኃይል ክፍል ኃላፊው ዲያቆን በረከተ ሥላሴ እሸቱ የገለጹ ሲሆን በጃን ቃና ዘገሊላ ሥር ደግሞ ጥር 28 ቀን 2015 ዓ.ም በታሪክ የመጀመሪያው በሆነው የብዙኃን ጋብቻ መርሐግብር 23 ጥንዶች መዳራቸውን የጃን ቃና ዘገሊላ አስተባባሪ ወ/ት መቅደስ ጌታሁን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ጃን ቃና ዘገሊላ ፕሮጀክት በወርኃ መጋቢት 2017 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ ለአንድ ወር ያህል ለ4ኛ ዙር ያዘጋጀውን የቅድመ ጋብቻ ትምህርት ለ350 ወጣቶች የሰጠ ሲሆን ትምህርቱን ከወሰዱ 44 የሚሆኑት ጥንዶች የብዙኃን ጋብቻ በተሰኘው ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን በኅብረት በምትድርበት ልዩ መርሐግብር ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡

የብዙኃን ጋብቻ የዝግጅት ሂደትንና የጋብቻ ሥርዓቱ ስለሚፈጸምበት ሁኔታ ተብራርቶ የቀረበ ሲሆን በተጨማሪም ይህ የብዙኃን ጋብቻ መርሐግብር አላማ ያደረገው ወጣቶች በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ጋብቻቸውን እንዲፈጽሙ ለማድረግ፣ ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን በኅብረት የምትድርበትን ቀን ለመፍጠርና በሠርግ ምክንያት አድርጎ የሚሰባሰብ ትልቅ ኦርቶዶክሳዊ ቤተሰብና ማኅበረሰብን ለመገንባት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በዚህ መሠረት እንደ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ 44 ጥንዶች ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም በቶታል ደብረ ገነት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ብፁአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በደማቅ ስነ ሥርዓት ጋብቻቸውን የሚፈጽሙ ይሆናል፡፡
በመግለጫው ምዕመናን በዚሁ ቀን በካቴድራሉ ተገኝተው የደስታቸው ተካፋይ እንዲሆኑ ሙሽሮቹንም በጸሎት እንዲያስቡ ጥሪ ቀርቧል፡፡ በቀጣይ ዓመት ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ ጋብቻቸውን የፈጸሙ ምዕመናን ቃል ኪዳነቸውን የሚያድሱበት በጋራ ስጋወ ደሙን የሚቀበሉበት መርሐግብር እንደሚዘጋጅም ወ/ት መቅደስ አሳውቀዋል፡፡

ጃን ቃና ዘገሊላ የብዙኃን ጋብቻ የሚያደርገው በደጋግ ክርስቲያኖች የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ሲሆን አላማው ገብቷቸው የቤተ ክርስቲያንን አደራ ተቀብለው ይህ ታሪካዊ መርሐግብር እንዲሳካ የበኩላቸውን ጥረት ላደረጉ አጋር ተቋማትና ግለሰቦች በመግለጫው ምስጋና ቀርቧል፡፡

የጋዜጣዊ መግለጫውን ሙሉ ይዘት 12:00 ሰዓት ላይ በጃንደረባው ሚዲያ ዩቲዩብ ገጽ የሚለቀቅ ይሆናል፡፡

ጋብቻዬን በሥርዓተ ቤተ ክርሰቲያን እንዳልፈጽም የሚከለክለኝ ምንድን ነው?
የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና ፥ ያውም እናንተ ናችሁ።

1ኛ ቆሮ 3፥17
2025/07/01 21:20:33
Back to Top
HTML Embed Code: