Telegram Web Link
አዲስ አበባ ማእከል ጠቅላላ ጉባኤ እያከናወነ እንደሚገኝ ገለጸ


ሐምሌ ፳፮/፳፻፲፯ ዓ.ም


የማኅበረ ቅዱሳን አዲስ አበባ ማእከል ጠቅላላ ጉባኤው  ዛሬ ሐምሌ 26 ቀን 2017 ዓ.ም እያከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የማእከሉ ሰብሳቢ ዲያቆን ኀይለማርያም መድኅን መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን  በመልእክታቸውም የማኅበረ ቅዱሳን አዲስ አበባ ማእከል በዘርፈ ብዙ የሥራ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

የአዲስ አበባ ሀገረ  ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምህረት  ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን
በበኩላቸው "አብረን እንሥራ" የሚል አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የዋናዉ ማእከል ተወካይ አጠቃላይ የማኅበረ ቅዱሳን ሪፖርት ምን እንደሚመስል ያቀረቡ ሲሆን የአዲስ አበባ ማእከል ዋና ሰብሳቢ ዲያቆን ኅይለማርያም መድኅን የ፳፻፲፯ ዓ.ም የአዲስ አበባ ማእከል ያከናወናቸዉን ተግባራት አብራርተዋል ።


ለማእከሉ ጠቅላላ ጉባኤ በተዘጋጀው  ዕቅድ ክንውን ላይ የቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ አስተዳደር ፣ የአሠራር ሥርዓትና አስተሳሰብ፣ በቴክኖሎጂ እና በልዩ ልዩ መንገዶች በመደገፍ ዘመኑን የዋጀ ጠንካራ አገልግሎት ማብቃትን ዓላማው ባደረገው በዚሁ ዕቅድ ክንውን ላይ፣ የዋና ዋና ተግባራት ከመፈጸም አኳያ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን የማኅበረ ቅዱሳን አዲስ አበባ ማእከል ሰብሳቢ ዲያቆን ኀይለ ማርያም መድኅን አስረድተዋል።

የቤተክርስቲያን የአስተዳደርና የአሠራር ለውጥ (ዘመኑን የዋጀ ዕቅድ እና ተጠያቂነት ያለበት የሰው ሀብት፣ የፋይናንስ፣ የዕቅድ ግምገማ የቴክኖሎጂና መረጃ አስተዳደር እና የሥጋት አስተዳደር ሥርዓት ) ፍኖተ ካርታን ለማስፈጸም ስልትና ፕሮግራም ማዘጋጀት፤ ከጠቅላይ ቤተክህነት እስከ አጥቢያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተግባራዊ እንዲሆን የማስቻል ሥራዎች መከናወናቸውንም አብራርተዋል።
35👍4🙏3
የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ ለውጥ ፍኖተ ካርታ ሊያስፈጽሙ የሚችሉ የድጋፍ ሥርዓት መዘርጋት እንዲሁም ተጽእኖ ፈጣሪነት ተግባራዊ የሚያደርጉ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናን የሚጠይቅ መሆኑን ሰብሳቢው ጠቁመዋል።

በተደራጀ እና ተደራሹን ማእከል ባደረገ መንገድ ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮን ዘርፈ ብዙ በሆኑ መንገዶች በመላው ዓለም ማስፋፋት ዓላማው ባደረገው በዚህ እንቅስቃሴ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮን አደረጃጀት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ድረስ በማጠናከር፤ ዘመኑን በዋጀ ቴክኖሎጂ፣ በሚዲያና በሌሎች ልዩ ልዩ መንገዶች በተለያዩ ቋንቋዎች ተደራሽ የሚሆንበትን አሠራር ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ሰፋፊ ሥራዎች መሠራታቸውን ሰብሳቢው አስገንዝበዋል።

የቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ አደረጃጀትና አወቃቀር አካባቢያዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ ማጥናት እና የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የአቅም ግንባታ መርሐ ግብር መሪዎችን ማፍሪያ ማዕቀፍ በማዘጋጀትና በመተግበር ረገድም ሥራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

የአገልጋይ ተገልጋዮችን ምጥጥን መሠረት በማድረግ ሰብከተ ወንጌልን በተለያዩ ቋንቋዎች የሚያገለግሉና ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ቀዳሚ ሚና የሚወጡ 8200 መምህራን ማፍራት እና ማሠማራት ተችሏል ሲሉ ገልጸዋል።

በደረጃ አንድ እና በደረጃ ሁለት የሰባኪያነ ወንጌል ሥልጠናን በመስጠት መምህራንን ማፍራት ተችሏል ብለዋል።


ጉባኤው እስከ ነገ ሐምሌ 27 ቀን 2017 ዓ.ም የሚቀጥል ይሆናል።
50🙏4👍3
አሰላ ማእከል  ፳፰ኛ ጠቅላላ ጉባኤዉን እያካሄደ እንደሚገኝ አስታወቀ

ሐምሌ ፳፮/፳፻፲፯ ዓ.ም

ማኅበረ ቅዱሳን አሰላ ማእከል  ፳፰ኛ ጠቅላላ ጉባኤዉን እያካሄደ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡


መርሐ ግብሩ የአርሲ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ታምራት ወልዴ ፣ የሀገረ ስብከቱ የክፍል ኃላፊዎች፣ የወረዳ ቤተ ክህነት ሊቃነ ካኅናት ፣ የአሰላ ከተማ አድባራት አስተዳዳሪዎች በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል፡፡


በዋናዉ ማእከል ልዑክ በአቶ አበበ በዳዳ የማኅበረ ቅዱሳን ግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ኃላፊ የማኅበረ ቅዱሳን መልእክት የቀረበ ሲሆን በአቶ ዉቤ ተሰማ የማእከሉ የጽ/ቤት ኃላፊ የ2017 ዓ.ም የማእከሉን የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

ጉባኤዉ ከትላንት ሐምሌ 25   የጀመረ ሲሆን እስከ እሑድ ሐምሌ 27  እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡
39👍8🙏2
27ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አሜሪካ ማእከል አስታወቀ

አሜሪካ ማእከል 27ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በፖርትላንድ ግ/ጣቢያ አስተባባሪነት ከትናንት ምሽት ሐምሌ 25 ቀን መክፈቻውን በፖርትላንድ ደብረ መንክራት ቅድስት ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን በጸሎተ ወንጌል ያደረገው የማእከሉ ጠቅላላ ጉባኤ በዛሬው እለት ሐምሌ 26 ቀን 2017 ዓ.ም. በፖርትላንድ ምስካዬ ኃዙናን መድኃኒ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በኪዳን ጸሎት የተጀመረ ሲሆን በጉባኤው መክፈቻ የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉት የማእከሉ ሰብሳቢ ዶ/ር አይዳ ግርማ  ማእከሉ በዓመቱ ውስጥ በሀገር ቤት እና በአሜሪካ ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

የጉባኤው መረ ቃል በሆነው “ከበጎ ሥራ ወገን ምን ላድርግ?” የሚለውን ቃለ እግዚአብሔር መነሻ በማድረግ ትምህርተ ወንጌል በአባ ፍቅረ ማርያም መኩሪያ ከኢትዮጵያ ተሠጥቷል፡፡በማስቀጠልም የማእከሉ የ2017 ዓ/ም አፈጻጸም ዘገባ፤ የሒሳብና የኦዲት ረፖርት እንዲሁም ዋና ማእከሉም በዓመቱ ውስጥ ያከናወናቸውን አጠቃላይ ሪፖርት በአቶ ታደሰ አሰፋ ቀርቧል፡፡ የቀረቡትንም ረፖርቶች ተከትሎ በጉባኤው የታደሙት የዋሽንግተን ኦሪገን አይዳሆና አካባቢው  ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ባስተላለፉት መልእክት ቤተክርስቲያንን የሚያሻግር ተተኪ ትውልድ ለማፍራት ማኅበረ ቅዱሳን የሚያደርገው ጥረት እጅግ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው አባላቱ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ እያለፋችሁ ለምታከናውኑት አገልግሎት ድጋፋችንን አጠንክረን እንቀጥላለን ብለዋል:: ብፁዕነታቸው ሥራህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ ሀሳብህም ይጸናልሃል የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በማንሳት ማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎቱን ለእግዚአብሔር አደራ ሰጥቶ እንዲሰራም የማትሰሩ መስላችሁ ሥራችሁን ስሩ በማለት አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል ::

ጉባኤው በተቋማዊ ለውጥ አተገባብርና አባላት ተሳትፎ፤ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮችና የ2018 ዓ/ም እቅዱና ሌሎች አጀንዳዎች መክሮ ውሳኔ የሚያሳልፍ ይሆናል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤው ከአባላት በተጨማሪ ለሕጻናትና አዳጊዎች የተለያዩ አስተማሪ ዝግጅቶች  በተጓደኝ እየተከናዎኑ ናቸው፡፡በማእከሉ ተግባራዊ የተደረገውን መዋቅራዊ ለውጥ ተከትሎ 3ቱ ማስተባበሪያዎች በአካል የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ባለፉት ሳምንታት ሲያካሂዱ ሰንብተዋል ::  የማእከሉ ጠቅላላ ጉባኤ ማስተባባሪያዎቹ በአካል ጠቅላላ ጉባኤ በሚያደርጉበት ዓመት የማእከሉ ጠቅላላ ጉባኤ በዙም እንዲካሄድ በተወሰነው ውሳኔ መሰረት ነው ዘንድሮ በዙም እየተካሄደ ይገኛል:: ዘገባው የአሜሪካ ማእከል ሚዲያ ክፍል ነው::
39🙏3👏2
2025/09/15 20:01:14
Back to Top
HTML Embed Code: