Telegram Web Link
«ተውኔተ ጵጵስና ☞ የጵጵስና ጨዋታ»
✥ °°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°° ✥

የኩላዊት ቤተክርስቲያናችንን ትውፊት [παραδοσις] ትምህርት [διδασκαλια] እና እምነት [πιστις] ከመነሻው ስንመለከት በክርስቶስ የተሠጠ በሐዋርያት የተሰበከና በአበው የተጠበቀ መንገድ ነው። በዚህም ቤተክርስቲያን ተመሠረተች!【ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ】

በቀደመው ዘመንማ የገሃዱ ሢመት ቀርቶ የሕጻናቱ ተውኔት እንኳ ደርዝ ነበረው!

በክርስትና ማኅተም ያልከበርክ
እንዴት ለጵጵስና ተመረጥክ? 【አባ ጊዮርጊስ】

ዛሬ ግንቦት ፯ ቀን በሃይማኖት የተዋቀረ ፦ የማይናወጥ መሠረት፣ የማይፈርስ ግድግዳ ፣ የማያዘነብል ምሰሶ የተባለ ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ፳ኛው የኢትዮጵያና የግብፅ ፓትርያርክ በ፬፻፸፬ ዓ.ም. ከሥጋ ድካም ያረፈበትን ቀን ቤተክርስቲያናችን ትዘክራለች። ይህ የምሥጢር ምንጭ የጉባኤ ኒቅያ አፈ ጉባኤ ደገኛው መምህር ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ለ፵፯ ዓመት በፕትርክና ሲቆይ ሢሦውን 【፲፭ ዓመት】በስደት ነበር ያሳለፈው።

ለኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የመጀመሪያውን ጳጳስ ቅዱስ ፍሬምናጦስን【አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃንን】የሾመልን ባለውለታችንና በመንበረ ማርቆስ የተቀመጠ ፳ኛው ፓትርያርካችን ነው። («ወማርቆስ ወንጌላዊ ‘ወኮነ ሰባኬ ወመጥምቀ ወሠያሜ ካህናት’ በእስክንድርያ ወግብፅ ወኖባ ወምድረ ኢትዮጵያ እስከ ጽንፋ» እንዲል መጽሐፈ ግጽው ምዕራፍ ፩ ቁጥር ፲፩ )

ቅዱስ አትናቴዎስ ወደ ክርስትናው የመጣበትና ለጵጵስና የበቃበት መንገድ እጅጉን የሚደንቅና አስተማሪ ነው። ስንክሳራችን በቀደመ ሕይወቱ ከአረማውያን ቤተሰብ የተገኘ አረማዊ እንደነበርና ለመጠራቱ ምክንያት ስለሆነች «የጵጵስና ጨዋታ» እንዲህ እያለ ይነግረናል

ውእቱ ይነብር ምስለ ሕፃናት እለ ይትሜህሩ ኀበ መምህር ርእዮሙ ለእሙንቱ ውሉደ ክርስቲያን እንዘ ይገብሩ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ወይትዋነዩ በበይናቲሆሙ ወይረስዩ እምኔሆሙ ዲያቆናተ ወኤጲስ ቆጶሳተ አደሞ ተላህዮቶሙ። ሰአሎሙ ዝንቱ አብ ለውሉደ ክርስቲያን ከመ ይሳተፍ ምስሌሆሙ በተላህዮቶሙ። ወከልእዎ ወይቤልዎ እስመ አንተ አረማዊ ኢንዴመር ምስሌከ ወይቤሎሙ ውእቱ አነ እከውን ክርስቲያናዌ ወተፈሥሑ ቦቱ።

【 እርሱም ከመምህር ከሚማሩ ሕፃናት ጋራ እያለ እርስ በርሳቸው በመጫወት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እየሠሩ ከእነርሱ ውስጥ ዲያቆናትን ኤጲስ ቆጶሳትንም ሲያደርጉ እሊያን የክርስቲ ያንን ልጆች አይቶ ጨዋታቸው ደስ ስለአለው ከእሳቸው ጋራ በጨዋታቸው አንድ ይሆን ዘንድ የክርስቲያንን ልጆች ለመናቸው። እነርሱም አንተ አረማዊ ነህና ከእኛ ጋራ አትደመርም ብለው ከለከሉት እርሱም ክርስቲያን እሆናለሁ አላቸው እነርሱም ደስ ተሰኙበት።】

ወነሥእዎ አሜሃ ወረሰይዎ አምሳለ ሊቀ ጳጳሳት ወመትሕቲሁ አምሳለ መንበር። ወእኀዙ ይስግዱ ሎቱ ወበውእቱ ጊዜ ኀለፈ አባ እለእስክንድሮስ ሊቀ ጳጳሳት። ወሶበ ርእዮሙ ለውሉደ ክርስቲያን እንዘ ይትዋነዩ ይቤሎሙ ለእለ ሀለዉ ምስሌሁ ወለዎ ለዝንቱ ሕፃን ይሠየም ሢመተ ክብርተ ወልዕልተ።
【ያን ጊዜም ወስደው በሊቀ ጳጳሳት አምሳል አደረጉት ከበታቹም ወንበር አድርገው ይሰግዱለት ጀመር። በዚያን ጊዜም ሊቀ ጳጳሳት አባ እለእስክንድሮስ በዚያ አለፈ የክርስቲያን ልጆች ሲጫወቱ በአያቸው ጊዜ አብረውት ላሉ ይህ ሕፃን ከፍ ከፍ ያለችና የከበረች ሹመትን ይሾም ዘንድ አለው አላቸው።】

ወንድማለም እንግዲህ ስማ መሾም ስለምትፈልግ ብቻ አትሾምም! እንኳን ሢመቱ ጭውውቱም ቢሆን ሥርዓት አለው። እንዳየኸው ጥንቱን የገሃዱ ሢመት ቀርቶ የሕጻናቱ ተውኔት እንኳ ደርዝ ነበረው! መጽሐፉም ቢሆን እንኳን ራስህን በቦታው ልታስቀምጥ በቦታው ተቀመጥ እንኳ ቢሉህ እምቢኝ በል ነው የሚል።
【"ኢመፍትው ለመኑሂ እምሰብእ ይምሥጥ ሢመተ ክህነት ለርእሱ አላ ለእመ ተውህበ እምእግዚአብሔር ☞ #የክህነትን_ሹመት ከእግዚአብሔር ካልተሠጠው በቀር ከሰው ወገን ማንም ለራሱ ይገባኛል ብሎ ቀምቶ እጅ አያድርጋት" መጽሐፈ ኪዳን ካልዕ ፩፥፷፩】

ዛሬ የሕጻናቱን ያኽል ድፍረት አጥተን መሰል እምነት የሌለው ኢጥሙቅ ልብሰ ጵጵስና ለብሶ ሲተውን አይተን ዝም ከማለት አለፍንና በበር ያልገቡ «መስኮተኞች» አይደለም ጵጵስናው ፕትርክናውም ሳይቀር ይገባናል ሲሉ እየሰማን «ሃይ–ባይ» አለመገኘቱ በእጅጉ ያሳዝናል። «ኧረ ተዉ» የሚል መገስጽ ብቅ ሲል ተቆጪውን መቆጣት ከመንገድ ማጥፋት ሥራችን ሆኖ አረፍነው።

ኧረ ጉድ የዚያ ዘመን የእስክንድርያ ሕጻናት እንዴት አድርገው እንደሚበልጡን እዩልኝማ

«ሰአሎሙ ዝንቱ አብ ለውሉደ ክርስቲያን ከመ ይሳተፍ ምስሌሆሙ በተላህዮቶሙ። ወከልእዎ ወይቤልዎ እስመ አንተ አረማዊ ኢንዴመር ምስሌከ ☞ #እሊያን_የክርስቲያን ልጆች አይቶ ጨዋታቸው ደስ ስለአለው ከእነርሱ ጋራ በጨዋታቸው አንድ ይሆን ዘንድ የክርስቲያንን ልጆች ለመናቸው። እነርሱም አንተ አረማዊ ነህና ከእኛ ጋራ አትደመርም ብለው ከለከሉት »

እንዲህ ያለውን ጨዋታ ወዳጅ ፡ አልፎ ሂያጅ «ና ግባና ጰጵስ» ለሚሉ ድንበር አፍራሾች እንዲህ ባለው የሌባ መንገድ እንዳልመጣ የምናውቀው ራሱ ቅዱስ አትናቴዎስ በድርሳኑ "ንሕነሰ ኢንኌልቆ ምስለ ክርስቲያን አላ ምስለ አረሚ ወዐላውያን ☞ እኛ ግን እንዲህ ያለውን ከማያምኑና ከሚያምጹት እንጂ ከክርስቲያን ወገን እንኳ አንቆጥረውም!” እያለ ይዘልፋል 【ሃይ አበው ፳፱፥፲፭】

አባ ጊዮርጊስ የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታና የእግዚአብሔር ምርጫ የሆነውን ሹመት በራሱ ጳጳስ ነኝ ይገባኛል ለሚል ንሥጥሮሳዊ በላከው ተግሳጽ ይህን ይላል ፦

እፎ ተኀረይከ ለጵጵስና ?
ዘኢተቀደስከ በማኅተመ ክርስትና
እፎ ተኀረይከ ለተክህኖ ?
ዘኢተሠርጎከ በተአምኖ
【በክርስትና ማኅተም ያልከበርህ ለጵጵስና እንዴት ተመረጥህ፡ በመታመን ያልተሸለምህ ሆይ እንደ ምን ለክህነት አገልግሎት ተመረጥህ ?】
【መጽሐፈ ምሥጢር ምዕራፍ ፬ ቁጥር ፲፮】

«ወአንተሰ ተመሰልከ ተክለ ዘእንበለ ፍሬ: ወዖመ ዘእንበለ ቈጽል: ፈለገ ዘእንበለ ውሒዝ : ወዐዘቅተ ዘእንበለ ማይ፡ ንጉሠ ዘእንበለ ጌራ መንግሥት : ሐራዌ ዘእንበለ ንዋየ ሐቅል : ደመና ዘእንበለ ዝናም : ወሰዊተ ዘእንበለ መስበልት : አበ ዘእንበለ ሀብተ ሲሳይ : ወእመ ዘእንበለ አጥባት : ንድቀ ዘእንበለ ተድባብ : ወኆኅተ ዘእንበለ ማዕፆ : መርዓዌ ዘእንበለ አክሊል : ወመርዓተ ዘእንበለ ባዝግና : ካህነ ዘእንበለ ኤፉድ : ምሥዋዐ ዘእንበለ ቊርባን : ኖትያዌ ዘእንበለ ሥርዐተ ሐመር : ወምሥያጣዌ ዘእንበለ ንዋይ : ሠረገላዌ ዘእንበለ ድርዐ ሐጺን : ወፈረሳዌ ዘእንበለ ኲያንው! እፎ ተኀረይከ ለጵጵስና ? ዘኢተቀደስከ በማኅተመ ክርስትና ፣ እፎ ተኀረይከ ለተክህኖ ? ዘኢተሠርጎከ በተአምኖ »
☞ አንተ ግን ፍሬ በሌለው ተክል ፣ ቅጠል በሌለውም ዛፍ ፣ ፈሳሽ በሌለው ወንዝ ፣ ውኃ በሌለው ጉድጓድ ፣ የመንግሥት ዘውድ በሌለው ንጉሥ ፣ የጦር መሣሪያ በሌለው ወታደር ፣ ዝናም በሌለው ደመና ፣ ፍሬ በሌለው እሸት ፣ ለምግብ የሚሆን ሀብት በሌለው አባት ፣ ጡቶች በሌላት እናት ፣ ጣሪያ በሌለው ሕንፃ፡ መዝጊያ በሌለው ደጃፍ፡ አክሊል ባልደፋ ሙሽራ ፣ ጌጥ በሌላት ሙሽሪት፣ ልብሰ ተክህኖ በሌለው ካህን ፣ ቁርባን በሌለው መሠዊያ ፣ የመርከብ ሥርዓት በማያውቅ ዋናተኛ ፣ ገንዘብ በሌለው ገበያተኛ ፣ የብረት ጥሩር በሌለው ባለሠረገላ፣ ጦሮች በሌሉት ፈረሰኛ ትመሰላለህ ! በክርስትና ማኅተም ያልከበርህ ለጵጵስና እንዴት ተመረጥህ? በመታመን ያልተሸለምህ ሆይ እንደ ምን ለክህነት አገልግሎት ተመረጥህ?

Let us look from the beginning at that very tradition, teaching, and faith of the «Orthodox Church» which the Lord gave (εδωκεν), the apostles preached (εκηρυςαν) and the Fathers preserved (εφυλαςαν). Upon this the Church is founded. 【Athanasius of Alexandria (First Letter to Serapion, 28)】

በቃን ማለት አልቻልንበትምና ሥሉስ ቅዱስ ራሱ በቃችሁ ይበለን!

ከቴዎድሮስ በለጠ ☞ ግንቦት ፯ ቀን ፳፻፲፭ ዓ ም 📍ከሀረር መካነ ሥላሴ ካቴድራል
መምህራችን ክቡር ቀሲስ ኅብረት የሺጥላ (Hibret Yeshitila Hibret) ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ያጋሩን ጽሑፍ ነው! በየዓመቱ እንደ አዲስ የሚነበብና ባለብዙኅ ምሥጢር ትምህርት በመሆኑ ተደጋግሞ እንዲነበብ አጋርቻለሁ!
በጎ ጾም መልካም ንባብ ያድርግልን!

✮༒✮ #ጾመ_ሐዋርያት ✮༒✮

(በቀሲስ ኅብረት የሺጥላ)

በየዓመቱ በዕለተ ሰኑይ ብቻ (ሰኞ ቀን ብቻ) የሚጀምሩ ሦስት አጽዋማት አሉ፡፡ እነርሱም ዓቢይ ጾም፣ ጾመ ነነዌ እና ጾመ ሐዋርያት ናቸው፡፡
እነዚህ አጽዋማት ምን ጊዜም ቅበላቸውእሁድ ሲሆን የሚገቡት ደግሞሰኞ ቀን ነው፡፡

በየትኛውም ዓመት ይህን ዕለት አይለቁም፡፡ ስለዚህ የ2004 ጾም ሐዋርያት ግንቦት 27 ሰኞ ዛሬ ተጅምሯል ፡፡ (ጽሑፉ የተለጠፈበትን ዓመት ያመለክታል ለዘንድሮው ሰኔ 1 ዛሬ ሰኞ) ቤተ ክርስቲያናችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በየግላችንም ያጋጠሙንን መንፈሳዊና ሥጋዊ ውጊያዎች በማሰብ ድል የምናደርግበትን ኃይል ፈጣሪያችን ይሰጠን ጾሙን ከወትሮው በበለጠ ጥንቃቄ ልንጾመው ይገባናል፡፡

የጾሙን ታላቅነት ተረድተን እንድንጾመው የትመጣውን፣ ትንቢቱን፣ ምሳሌውንና ምሥጢሩን መረዳት አጋዥ ስለሚሆነን አስቀድመን ስለጾሙ እንማር ዘንድ በአጭሩ አቅርቤዋለሁ! የምችለውን ያህል እጽፍ ዘንድብርታቱንና ጥበቡን የሰጠኝ አምላከ ቅዱሳን ሐዋርያት ክብር ምስጋና ይድረሰው! አሜን!

ጾመ ሐዋርያት በራሳቸው በሐዋርያት የተጀመረ ጾም እንደመሆኑ መጠን በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም ከዛሬ አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ ሲጾም የኖረ ጾም ነው፡፡ ለዚህም የመጽሐፍ ቅዱስ፣ የአዋልድ መጻሕፍትና የታሪክ በርካታ ምስክሮች አሉ ስለዚህ ጾሙን እንደ እንግዳ ነገር መቁጠርና ዘመን አመጣሽ አድርጎ ማየት የራስን አላዋቂነት ያሳያል፡፡ ይህን ማለት ያስፈለገው ጥቂቶች ጾሙን ድሮ ያልነበረና ዘመን አመጣሽአድርገው ስለሚናገሩ ነው፡፡
ጾመ ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ዕድሜያቸው ለጾም የደረሱ ምእመናን በሙሉ እንዲጾሙአቸው ካወጀቻቸው ሰባት የአዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጌታችንና በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ አንደበት ቀን የተቀጠረለት፣ ትንቢት የተነገረለትና ምሳሌ የተመሰለለት ጾም መሆኑ ከአጽዋማት ሁሉ ለየት ያደርገዋል፡፡

ጌታችን ስለዚህ ጾም ትንቢተ በመናገር፣ ምሳሌ በመመሰል ሰፊትምህርት የሰጠው ፈሪሳውያን ወደ እርሱ ቀርበው ‹‹ደቀ መዛሙርትህ የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው?›› ብለው በጠየቁት ጊዜ ነው፡፡ እርሱም ሲመልስ እንዲህ አላቸው፡- ‹‹ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግንሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፤ በዚያ ጊዜም ይጦማሉ፡፡ በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፤ መቀደዱም የባሰ ይሆናል፡፡ በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አቁማዳው ይፈነዳል፤ የወይን ጠጁም ይፈሳል፡፡ አቁማዳውም ይጠፋል፡፡ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል ሁለቱም ይጠባበቃሉ፡፡›› (ማቴ9.14-17)

በመቀጠል እስከ መጨረሻ የምንመለከተው ከላይ የሰፈረውን የማቴዎስ ወንጌል አጭር ገጸ ንባብ ሐሳብ በመሆኑ መለስ እያሉ
ታሪኩን ማንበብ ወይም በልብ ከመዘገቡ በኋላ ቀጣዩን ክፍል ማንበብ ምሥጢሩን ለመረዳት ያግዛል፡፡
በዚህ የጌታችን መልስ ውስጥ ‹‹ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል በዚያ ጊዜም ይጦማሉ፡፡›› የሚል ስለጾመ ሐዋርያት የተነገረ የትንቢት ቃል እናገኛለን፡፡ ይህ አምላካዊ ቃል ጾሙ ስለሚጀመርበት ወራት ቀጠሮ ይሰጣል፡፡ ያም ጊዜ ሙሽራው ከእነርሱ ከተወሰደ በኋላ ያለው ጊዜ ነው፡፡ ‹‹ሙሽራው ከተወሰደ›› በኋላ ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ማለት ሲሆን በቤተ ክርስቲያን ጾመ ሐዋርያት ከዕርገት በኋላ የሚጀምረው በዚህ ቃል ምክንያት ነው፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያን ምን ያህል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያላት መሆኗን ያሳያል፡፡
ጾመ ሐዋርያት ከዕርገት በኋላ ለዐሥር ቀናት ያህል ዘግይቶ እንጂወዲያው አይጀምርም ምክንያቱም የሐዋርያት ሰውነት በአዲስ ሁኔታ ጌታችን ላዘጋጀው የአዲስ ኪዳን ጾም ተመቻችቶ ያልተገኘ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ የሐዋርያት ሰውነት ለጾሙ መዘጋጀት ነበረበት፡፡ ከዚያ በኋላ ሐዋርያት መጾም ጀምረዋል ይህም በጌታችንን የመልስ ቃል ውስጥ የተካተተ እንጂ የፈጠራ ድርሰት አይደለም፡፡ ‹‹በአረጀ ልብስ ላይ››እና ‹‹በአረጀ አቁማዳ›› የሚሉት ሁለት ተከታታይ ምሳሌያዊ ማብራሪያዎች ሐዋርያት ሰውነታቸው በመንፈስ ቅዱስ ከመታደሱ በፊት ጾም መጾም እንደማይጀምሩ ወይም እንደሌለባቸው የሚያስረዱ ምሳሌዎች ነበሩ፡፡ ስለዚህ ሐዋርያት የተዘጋጀላቸውን ጾም መጾም የጀመሩት ከኢየሱስክርስቶስ ዕርገት በኋላ በዐሥረኛው ቀን በወረደ ጸጋ መንፈስቅዱስ የሕይወት ሕድሳት አግኝተው ነው፡፡

ከላይ በተጠቀሰው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ውስጥ ስለጾመ ሐዋርያት የቀረቡ ሦስት ዓይነት ምሳሌዎችን እናገኛለን፡፡ ምሳሌዎቹ በምሥጢር የተሞሉ በርካታ መንፈሳዊ መልእክቶችን ያዘሉ ናቸውና ተራ በተራ እንመለከታቸዋለን፡፡

①ኛ...‹‹ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን?›› የሚለው ዐረፍተ ነገር በገጸ ንባቡ ውስጥ ስለ ሐዋርያት ጾም የተመሰለው የመጀመሪያው ምሳሌ ነው፡፡ ሚዜዎች የተባሉት እንደ መጥምቁ ዮሐንስ መንገድ የሚጠርጉ፣ የሚያስተምሩና ምእመናንን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያቀረቡ ሁሉ ናቸው፡፡ ሙሽሪትን ወደ ሙሽራው መውሰድ የሚዜዎች ሥራ መሆኑ በአይሁድና በኢትዮጵያውያን ባህል ሲሠራበት የኖረ ነው፡፡ ስለዚህ ዋነኞቹ ሚዜዎች ሐዋርያት ናቸው ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽራ ሲሆን ቤተክርስቲያን (ምእመናን) ደግሞመርዓት (ሴት ሙሽራ) ትባላለች፡፡ (2ቆሮ11.2፤ዮሐ3.29)
‹‹ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን?›› ሲልሚዜዎች ሙሽራውን ለማስደሰት ሲሉ ምንም የሚያሳዝን ነገር ቢያጋጥማቸውም እንኳን ጨክነው በመቻል ያሳልፉታል እንጂ በሙሽራው ፊት እንደማያዝኑ፤ እንደዚሁም መጾም ተገቢ ነገር ቢሆንም ሐዋርያትኢየሱስ ክርስቶስ ከእነርሱ ጋር ሳለ መጾም እንደማይገባቸው ነገር ግን ከእነርሱ ተለይቶ ሲያርግ መጾም እንደሚጀምሩ ያስረዳል፡፡

በዚህ ምሳሌያዊ ንባብ ውስጥ ጾም በኀዘን ተመስሏል፡፡ መጾም ተድላነቱ ለነፍስ እንጂ ለሥጋ አይደለምና፡፡ ሥጋ ጾምን እስኪለምድ ድረስ ቅጣት ይሆንበታል፡፡ ስለዚህ በጾም ነፍስ ስትደሰት ሥጋ ግን ያዝናል፡፡ በዚህ ምክንያት ጾም በኀዘን ተመስሏል፡፡ በዚህም ምክንያት ጾም በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከኀዘን፣ ከዕንባ፣ከጸጸትና ከንስሐ ጋር ተያይዞ ቀርቧል፡፡ (ኢዩ2.12)

②ኛ...‹‹በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፤ መቀደዱም የባሰ ይሆናል፡፡›› ይህ ዐረፍተ ነገር ደግሞ ሁለተኛው ምሳሌ ነው፡፡ እራፊ ማለት ቅዳጅ ወይም መጣፊያ ጨርቅ ማለት ነው፡፡ የስፌት ባለሙያ ባረጀ ልብስ ላይ አዲስ ጨርቅ አይጥፍም (አይሰፋም) ወይም አይለጥፍም፡፡ ይህም አንደኛ ግንጥል ጌጥ እንዳይሆን፤ ሁለተኛ ላሮጌ ልብስ ሲባል አዲሱን ማበላሸት እንዳይመጣና አዲሱ ካሮጌው ስለሚበረታ የባሰ እንዳይቦጭቀው በማሰብ ነው፡፡
በምሳሌው መሠረት በጣፊ ወይም በልብስ ሰፊ የተመሰለው ኢየሱስክርስቶስ ነው፡፡ በአዲስ እራፊ ጨርቅ ምሳሌነት የተወከለው ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ በአዲስ ኪዳን እንድንጾመው የሠራልን ጾም ነው፡፡ የተቀደደውና መጣፊያ የሚያስፈልገው ልብስ ደግሞ የሐዋርያት ሕይወት ምሳሌ ነው፡፡
እንደ ምሳሌው ሁሉ ሰዎች የክርስቶስ ልብሶች ይባላሉ፡፡

‹‹አልባሲሁሰ ለክርስቶስ መሃይምናን እሙንቱ›› እንዲል፡፡ ይህም ‹‹የክርስቶስ ልብሶቹ ምእመናን ናቸው፡፡›› ማለት ነው፡፡ክርስቶስም ለሰዎች ልብሳቸው ነው፡፡ሐዋርያው ‹‹እናንተ የተጠመቃችሁ ክርስቶስን ለብሳችኋል›› ብሏልና፡፡(ገላ3.27) ምእመናን የክርስቶስ ልብሶች ናቸው ማለት የክብሩ መገለጫዎች ናቸው ማለት ነው፡፡ ልብስ የክብር መገለጫ ይሆናልና፡፡ እርሱ ደግሞ ለምእመናን ልብስ ነው ማለት ጌጣቸው፣ ነውራቸውንየሚሸፍንላቸውና ክብራቸውም እርሱ ነው ማለት ነው፡፡

ጾም ‹‹እራፊ›› መባሏ ምሥጢር አለው፡፡ ይኸውም እራፊ የተለያየውን እንደሚያቀራርብና አንድ እንደሚያደርግ ጾምም የተለያዩ ፈቃዳት ያሏቸውን ነፍስና ሥጋ አንድ ታደርጋለች፡፡ ከዚህም በላይ ከእግዚአብሔር የተለየውን ሰውም አስታርቃ አንድታደርገዋለች፤ ከመንጋውም እንዲቀላቀል ትረዳዋለች፡፡

‹‹በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፤ መቀደዱም የባሰ ይሆናል፡፡›› ማለት አንድ የስፌት ባለሙያ ባረጀ ልብስ ላይ አዲስ እራፊ እንደማይጥፍ ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስም የሐዋርያት ሰውነት በኃጢአት ያረጀ ሆኖ ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ሳያድስላቸው አዲስ የሠራውን የአዲስ ኪዳን ጾም ጹሙ ብሎ ሐዋርያትን አያዛቸውም ማለት ነው፡፡

ሰውነታቸው ሲታደስ ያን ጊዜ ግን ይጾማሉ፡፡
ይህ አገላለጥ እግዚአብሔር መንጋዎቹን ያለ አቅማቸው እንዲሸከሙ የማያደርግ አዛኝ ጌታ መሆኑን ያሳያል፡፡
እንዴት ቢባል ሐዋርያትን ሊፈጽሙት በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ እያሉ እንዲጾሙ አላዘዛቸውምና፡፡ ፈጣሪ ለሕዝቡ መቼ ሕግ መስጠት እንዳለበት በሚገባ ያውቃል፡፡ ለእስራኤላውያን በባርነት ሳሉ ዐሥርቱ ትእዛዛትን ያልሰጣቸው ስለዚህነው፡፡ ቢሰጣቸውም ሊጠብቁት አይችሉም ነበርና፡፡ በባርነት ያለ ሰው የራሱ ነጻነት እስከሌለው ድረስ የፈቀደውን ማድረግአይችልም፡፡

በታላላቅ ተአምራት ከባርነት ካወጣቸው በኋላ ግን ሕጉን ሰጣቸው፡፡ ስለዚህ ከክርስቲያን ወገን ማንም ቢሆን ከአቅሙ በላይ የሆነ ነገርፈጣሪ እንዳዘዘው አያስብ፡፡ የታዘዝነው ሁሉ በዐቅማችን ልክ እንደሆነ እንመን፡፡

③ኛ... ‹‹በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግንአቁማዳው ይፈነዳል: የወይን ጠጁም ይፈሳል፡፡ አቁማዳውም ይጠፋል፡፡›› ይህ ስለ ጾመ ሐዋርያት የተመሰለው ሦስተኛውና የመጨረሻው ምሳሌ ነው፡፡
በአረጀ አቁማዳ የተመሰለው ሐዋርያት በጸጋ መንፈስ ቅዱስ ሳይታደሱ በፊት የነበራቸው ሕይወት ሲሆን፤ በአዲስ ወይን የተመሰለው ደግሞ ጌታችን በወንጌል የመሠረተልን ጾም ነው፡፡ የጾም ሕግን የሰጠን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ደግሞ በጠጅ ጣዩ (በጠማቂው) ተመስሎ ቀርቧል፡፡ አዲስ ጠጅ ባረጀ አቁማዳ እንደማይጣል አምላካችንም ባልታደሰ ሕይወታቸው ሐዋርያትን እንዲጾሙ አላዘዛቸውም፡፡

ቀደም ሲል ጾም ሥጋን ለጊዜው ደስ ባለማሰኘቱ በኀዘን እንደሚመሰል ተመልክተን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በዚህ ምሳሌ ጾም ነፍስን ደስ የሚያሰኝ በመሆኑ በወይንተመስሎ አገኘነው፡፡ ‹‹ወይን የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል›› እንዲል፡፡ (መዝ103.15) ጠጅ ጣዮች ሲጥሉ (ሲጠምቁ) ተመልክታችሁ ታውቃላችሁ? አስቀድመው ቦታ ያዘጋጁለታል፡፡ እግር እንዳይበዛበትም ጥላ እንዳይወድቅበትም ይጠነቀቃሉ፡፡ እንዳይነፍስበትም ቀን ከሌሊት ይተጉለታል፡፡ በመጨረሻ ሥራው አልቆ ሳለ ጠጁ ከደረቀ (ከጠነከረ) ይላላ ብለውማር ያልሱታል (ይበርዙታል)፡፡ ከላላ ደግሞ ይድረቅ ብለው ጊዜ ይሰጡታል፡፡

በጠጅ ለተመሰለ ለጾምም በዓይነቱ ተመሳሳይ ከጥቅሙ አኳያ ደግሞ የበለጠ ጥንቃቄ ሊደረግለት ያስፈልጋል፡፡ ለጠጅ ቦታ እንደሚዘጋጅለት ለጾምም ሰውነትን ማዘጋጀትና ጊዜና ዕለት ወስኖ መመደብ በአጠቃላይ ጾምን ማወጅ ይገባል፡፡ ስንዱ እመቤት ቤተክርስቲያናችን የአጽዋማት ዐዋጅ ስላላት እኛ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች የዚህ ችግር የለብንም፡፡ ለጠጅ እግር እንዳይበዛበትና ጥላ እንዳይድቅበት እንደሚጠነቀቁለት ጾማችንም በከንቱ ውዳሴ አጋንንት እንዳይገቡበትና ያለ መልካም ሥራ በጾም ብቻ ቀርተን ዋጋው እንዳያንስብን እየተጠነቀቅን መጾም ይገባናል፡፡ ጠጅ ደረቀ ይላላ፤ ላላ ይድረቅ እንደሚባል ጾማችን በሕግ ከተሠራልን በላይ ሠዓቱ እንዳይበዛና ከዓቅማችን በላይ አልፎ ሰውነታችን እንዳይጎዳ፤ እንደዚሁም የአጽዋማትን ሰዓት ሳንጠብቅ ቀርተንም መንፈሳዊ ሕይወታችን እንዳይላላ ማዕከላዊውን ስፍራ ይዘን በሕገ ቤተክርስቲያን መሠረት በጥንቃቄ መጾም እንደሚገባን ይህ ሦስተኛው ምሳሌ ያስረዳናል፡፡

ይህን ትምህርት ጌታችን መድኃኒታች ኢየሱስ ክርስቶስ የሚቋጨው ‹‹አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል ሁለቱም ይጠባበቃሉ፡፡›› በሚለው ኃይለ ቃል ነው፡፡ ዐረፍተ ነገሩ አዲስ የወይን ጠጅ መጣል ያለበት በአዲስ አቁማዳ መሆኑን ይናገራል፡፡ ስለዚህ ሐዋርያት ሕይወታቸው በጸጋ መንፈስ ቅዱስ ከታደሰ በኋላ በአዲሱ አቁማዳቸው አዲሱን ወይን ጣሉ፡፡ ማለትም በአዲስ ሕይወት የአዲስ ኪዳንን ጾም (ጾመ ሐዋርያትን) መጾም ጀመሩ፡፡

አዲስ የወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ ሲጣል ያፈነዳዋል፡፡ በአዲስ አቁማዳ ሲጣል ግን ያለፋዋል እንጂ ሊያፈነዳው አይችልም፡፡ ስለዚህ ወይኑም አቁማዳውም አዲስ የሆኑ እንደሆነ አቁማዳው ወይኑን ያፈላዋል፡፡ ወይኑ ደግሞ አቁማዳውን ያለፋዋል፡፡ በዚህ ጊዜ‹‹ሁለቱም ይጠባበቃሉ›› የሚለው ቃል ይፈጸማል፡፡ ጾምና ሰውነት እንደ ወይንና አቁማዳ ናቸው፡፡ ወይንና አቁማዳ እንደሚጠባበቁ (እንደሚጠቃቀሙ) ጾምና ሰውነትም እንዲሁ ናቸው፡፡ ሰው የጾም ሕግን ቢጠብቅ ሕግም እርሱን ትጠብቀዋለች፡፡ ‹‹ይጠባበቃሉ›› የተባለው ለዚህ ነው፡፡ ይህን የሚያስረዳ ‹‹አኮ ንሕነ ዘነዓቅቦሙ ለሕገጋት አላ እማንቱ ሕገጋት የዓቅቡነ ለዓቂብ ወለተፀውኖ›› የሚል ቃል ይገኛል፡፡ ይህም ‹‹ሕጎችን እኛ አንጠብቃቸውም፡፡ እነርሱ መጠበቅን ይጠብቁናል፤ መጠጊያም ይሆኑናል እንጂ፡፡›› እንደማለት ነው፡፡
ወይኑ ቆዳውን ማልፋቱ መልካም ነገር ነው፡፡ የለፋ ቆዳ ብዙ አገልግሎት ስላለው ይፈለጋልና፡፡ ለቀበቶ፣ ለቦርሳ፣ ለጫማና ለልብስ የሚሆነው የለፋ ቆዳ ነው፡፡ የጾምም ጥቅም እዚህ ላይ ነው፡፡ ለልዩ ልዩ አገልግሎትና ጥቅም የሚውል መንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖረን ከፈለግን በጾም የለፋ (የደከመ) ሰውነት ያስፈልገናል፡፡ ቆዳን ማልፋት ማዘጋጀት እንጂ ከጥቅም ውጭ ማድረግ አይደለም፡፡ ሰውነትን በጾም ማድከምም ለመንፈሳዊ ሥራ ማዘጋጀት እንጂእንዳይሠራ ማድረግ እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የታረሰ መሬት ለዘር እንደሚመች በጾም የደከመ ሰውነትም ለመንፈሳዊጉዞ ይመቻል፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ጉልበቶቼ በጾም ደከሙ›› ያለው ለዚህ ነው፡፡ (መዝ108.24)

ይህን የመሰለ ምሥጢር ያለውን ጾም ‹‹የሽማግሌዎች ጾም፣ ከጥንት ያልነበረ›› እያሉ በመጽሐፍ እና በቀኖና የሌላ ስም በመስጠት ምእመናን እንዳይጾሙት ማድረግ የዲያብሎስ ትጥቅ የማስፈታት ዘዴ እንጂ ሌላምን ሊሆን ይችላል?
ላለመጾም ምክንያት ከመፍጠር ምክንያት ፈጥሮ መጾም በእጅጉ ይጠቅማል፡፡ ደሀው ድኅነት ራሱ ጾም ነው ካለ፤ ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ራሱጾም ነው ካለ ለመጾም ክርስቲያን መሆን ሳይሆን ሀገር ወይም ዜግነትመቀየር ሊያስፈልግ ነው ማለት ነው? ምእመናን ‹‹ይህ የሽማግሌዎች ጾም ነው›› ካሉ ስለ ጾም ማስተማርና ጾመው ማሳየት የሚጠበቅባቸው ‹‹ሰባክያን›› ደግሞ ‹‹ቃለ እግዚአብሔር ይመትር ነደ እሳት›› እያሉ ጾምን ሽሮ ለመብላት ጥቅስ ከጠቀሱ ጾምን በጽሑፍ እንጂ በሥራ ላናውቃትነው ማለት ነው፡፡

ሐዋርያት እንደታዘዙት ዓለምን ሁሉ ለማስተማር ከመሰማራታቸው በፊት መጀመሪያ ያደረጉት ጾምን ነው፡፡ ሐዋርያት አልጾሙም ማለት ከላይ የተብራራው የኢየሱስ ክርስቶስ ትንቢትና ምሳሌ ሐሰት ሆነ ማለት ነው፡፡ ሎቱ ስብሐት! ቃሉም ተፈጽሟል ሐዋርያትም ጾመዋል፡፡ እኛም ጾሙን ጾመን የምናስበውና የምንሠራው በጎ ሥራ ሁሉ ይከናወንልን ዘንድፈጣሪ በረድኤት አይለየን!

ይቆየን! ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

www.tg-me.com/An_Apocalypse
እግዚአብሔር በወዴት ይገኛል ቢሉ፡-

በደዌ ደኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዘዉ በሚማቅቁ፣ አስታማሚና ጠያቂ አጥተዉ ዕለተ ሞታቸዉን በሚናፍቁ ምስኪን ህሙማን መካከል እግዚአብሔር ይገኛል፡፡

በባዶዉ አስፋልት ላይ ካርቶን አንጥፈዉ በሚተኙ ዝናቡ፣ ቁሩ፣ ዋዕዩ በሚፈራረቅባቸዉ፣ ቆሻሻ ገንዳ ላይ ተንጠላጥለዉ የበሰበሰ ፍራፍሬን ቀለባቸዉ ባደረጉ፣ ችጋር ጠንቶባቸዉ መማሪያ ክፍል ዉስጥ እንዳሉ በረሀብ በሚያሸልቡ የድሃ ድሃ ልጆች መካከል እግዚአብሔር ይገኛል፡፡

በግፈኞች ፍትህ ተንጋዶባቸዉ ባልዋሉበት እንደዋሉ፣ ባልሰሩት እንደሰሩ ተደርገዉ በጨለማ እስር ቤት በተወረወሩ፣ብረት በተቆለፈባቸዉ የህሊና ታሳሪዎችና የህዝብ ጠበቆች መካከል እግዚአብሔር ይገኛል፡፡

በእኩይ ባሎቻቸዉ አካላዊም ሆነ ስነ ልቦናዊም ጥቃት በደረሰባቸዉ፣ እጅግ የከበደዉን መከራ መቋቋም ተስኗቸዉ ቀኑ በጨለመባቸዉ እንዲሁም ቢጮሁ ቢጮሁ ሰሚ አጥተዉ ሌት ተቀን በሰቆቃ በሚባዝኑ አንስቶች መካከል እግዚአብሔር ይገኛል፡፡

ለዚህች ሀገር የሚችሉትን ሁሉ አበርክተዉ አቅማቸዉ ሲደክም ጉልበታቸዉ ሲከዳ ጧሪ ቀባሪ ጧሪ ቀባሪ በማጣት ቤታቸዉ በፈረሰባቸዉ እንዲሁም ለልመና እጅ በሰጡ አዛዉንት አባቶችና አሮጊት እናቶች መካከል እግዚአብሔር ይገኛል፡፡

ታዲያ እነዚህን አካላት ሲራቡ በማብላት፣ ሲጠሙ በማጠጣት፣ ሲታሰሩ በመጠየቅ፣ ሲታረዙ በማልበስ፣ ሲያዝኑ በማጽናናት ሲታመሙ በመንከባከብ በመርዳት ከጎናቸዉ ሆነን ችግራቸዉን ከተካፈልን ከእግዚአብሔር ጋር እንገናኛለን ምክንያቱም የእርሱ ቦታዉ እዚህ ነዉና ሁሌም በፍቅሩ ይጎበኘናል እኛ አናየው ይሆናል እንጂ እርሱ ሁሌም በፍቅር ይመለከተናል መሻታችንን ሁሉ ይፈጽምልናል የሚበልጠዉንም ያደርግልናል፡፡


https://www.tg-me.com/joinchat-AAAAAEILHwyFiBuqHNVyRw
ምንት አሥሐቃ ለሳራ ?
   ሣራ ለምን ሳቀች ?
    【ዘፍ. ፲፰፥፲፱】
▦▦ 〣𓆩⪩♱⪨𓆪〣 ▦▦
        የሰው ልጅ ከሌላው ፍጥረት በተለየ በፊት ገጽታው ፣ በአካላዊ ኹኔታው ፣ በቁመናው ፣ በዓይን እንቅስቃሴው ከዚያም ባሻገር በመንካትና በአካል ርሕቀት ጭምር የሚገልጣቸው ሐሳቦች አሉት፤  ታዲያ እኒህ መንገዶች አንዳንዴ ከቃል ንግግር ባልተናነሰ ሳይሆን በተሻለ መንገድ እውነተኛ ስሜትን የመግለጥ ጉልበት ይኖራቸዋል።  የነገረ ሰብእ አጥኚዎች (anthropologist)  ይኽን በአካላዊ እንቅስቃሴና በፊት ገጽታ መልእክት የማስተላለፍ መንገድ ኪኔሲክስ [Kinesics] ብለውታል።

      አንድ መረጃ  ቀጥታ በቃል ሳይነገር  በተዘዋዋሪ መንገድ የስሜት ተረፈ ምርት (emotion residue) በሆነ አካላዊና የገጽታ ኩነት ሲገለጽ  ሐሳቡ እንዴት መተርጎም እንዳለበት ልማዳዊ የጋራ ስምምነቶች ከቦታ ቦታ የሚለያዩ ቢሆንም  በዲበ ተግባቦት (Meta-communication)  ግን የጋራ ትርጉም እንዲሠጣቸው ታሶቦ «እንዲህ የሚኮነው በዚህ ምክንያት ነው» የሚል አስማሚ ትርጉም ይቀመጥላቸዋል።

      ሳቅ ከእነዚህ ውሥጥ አንዱ ነው። በሥሉስ ቅዱስ በኩል ሐይመተ አብርሃም ውሥጥ ለሳራ የቀረበ ጥያቄ አለ ፦  «ምንት አሥሐቃ ለሳራ ☞ ሣራ ለምን ሳቀች?»  በእርግጥ ጥያቄው ሳራ የሳቀችው በምን ምክንያት እንደሆነ ለማወቅ ተፈልጎ የተነገረ ሳይሆን «እንዲህ ተደንቃ የምትስቀው ፣ እጅጉን ተገርማ የምትፈገው ስለምነው? »   ለማለት እንጂ ። “እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፦ ካረጀሁ በኋላ በውኑ እወልዳለሁን? ስትል ሣራ ለምን ሳቀች?”  እርሷ ግን ቅሉ ከሐሳብ አስቀድሞ ሁሉን የሚመረምረውን ፣ ከሕሊና አስቀድሞ ሁሉን የሚያውቀውን ልብአውቃ የሆነ ማእምረ ኵሉ  አምላክን ፈርታ ብትክደውም  “ሣራም ስለ ፈራች፦ አልሳቅሁም ስትል ካደች። እርሱም፦ አይደለም፥ ሳቅሽ እንጂ አላት።” (ቁ፲፭)

      ከዚህ ምዕራፍ ቀድሞ በተገለጠው የዘፍጥረት ታሪክ ውሥጥ ራሱን «ኤልሻዳይ» ብሎ ለአብርሃም የገለጠ ልዑል እግዚአብሔር ለይስሐቅ ይስቃል በሚል መጠሪያ መሰየም መነሻው ከነሚስቱ ሸምግሎ በእርግና ሳለ ትወልዳለህ ሲባል የአብርሃም ተገርሞ መሳቅ እንደነበር እናያለን፦
“አብርሃምም በግምባሩ ወደቀ፥ ሳቀም፥ …  እግዚአብሔርም አለ፦ በእውነት ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ይስሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ ”  【ዘፍ ፲፯፥፲፯(፲፱)】

         አብርሃምና ሳራን ምን አሳቃቸው?  ደስታ ነዋ! 
⊚⃝⊚ ሰው ሲደሰት ይስቃል (ከውሥጥ ወደ ውጪ)
☞ ያዘነ ሰው ፊቱ ጠቁሮ የተደሰተ ሰው ፊቱ በርቶ መታየቱ ለዚያ ነው  «እምከመ ይቴክዝ ልብ ይዴምን ገጽ እምከመ ይትፌሣሕ ልብ ይበርህ ገጽ» እንዲል
⊚⃝⊚  በሌላ መንገድ ሰው ሲስቅም ይደሰታል (ከውጭ ወደ ውሥጥ)
☞ የተከዙ ሰዎች ወደሳቅ የሚቀርቡት ያዘኑ ሰዎች መዝናናት የሚመርጡት ለዚያ ነው   "ሳቅ የደስታ ምንጭ ነው" እንዲል

ኢያሱ ወልደ አልዓዛር (ወልደ ሲራክ) በመጽሐፉ "እስመ እምራእዩ ይትዐወቅ ሰብእ፣ ወእምገጹ ይትዐወቅ ጠቢብ ⇨ ሰው በመልኩ ይታወቃልና ፣ ጠቢብም በገጹ ይታወቃል"

የተረጋጋ፣ ተስፋ የቆረጠ፣  የታመመ፣ የደከመ ሰው ከቸኮለ(ከሚጣደፍ) ፣ ከበረታ ፣ ከሚጓጓ…  ሰው  የሚለየው በአካሐዱ ነው ፤   
           ያዘነ ከሚደሰት ፣ ወደመኝታ የሚሔድ ወደሥራ ከሚሔ ፣ ወደቤተክርስቲያን የሚሔድ ከማይሔድ…  በአለባበሱ እንደሚታወቅ። ሳቅም ከአካሔድና ከለባበስ በበለጠ የአንድን ሰው አሁናዊ ሁኔታ በተሻለ መልክ ያስረዳል፤ በ‘ኢሞጂ’ ውሥጥ የፈገግታ ገጽ / የሳቅ ፊት (smiley face) አንዱ የደስታ ስሜን ወኪል ሥዕላዊ ምልክት (ideogram)  ተቀምጧል።  

«ወእምልብሰቱ ለሰብእ ወእምሑረቱ ወእምሠሐቁ ይትዐወቅ ግዕዙ  ⇨ ካለባበሱና ካካሄዱ ከአሳሣቁም የተነሣ የሰው ጠባዩ ይታወቃል» 【ሲራ ፲፱፥፳፯(፴)】

እንዲያውም  አንዳንዴ ሳቅ ከቁጥጥር ውጪ ‘እየገነፈለ’ የደስታን ስሜት የውሥጥን ሐሴት በሌላው ፊት ያሳብቃል፤ እንደ ሳራ! ታዲያ  ፎቶ አንሺ ፣ ቪዲዮ ቀራጭ ፣ ሠዓሊ… መታወሻ  ምስልን ለማስቀረት ሲሻ "እስኪ ፈገግ በሉ" ማለቱ ቅሉ ለዚህ ነው "ፍሡሓ ገጽ" ሆኖ መታየት የደስተኝነት መገለጫ ነውና።

          አቡነ ኤርምያስንስ ምን አሳቃቸው?
አቡነ ኤርምያስን በሐዘን ፊት ፣ በተቋጠረ ገጽ ፣ በዝቶ በሚፈሰው እንባ ፣ በተከዘ ልብ የማያውቃቸው የለም! «ጦርነት» በተባለው እርስበእርስ ፍጅት ከህዝበ ክርስቲያኑ ጋር የመከራውን ጽዋዕ ቀምሰዋል እንደቀደመው ኤርምያስ
ቅዱስ ቀሌምንጦስ ዘሮም  " ካህኑ ኤርምያስ ከሕዝበ እሥራኤል ጋር አብሮ የተሠደደው እስራኤሎችን ቃለእግዚአብሔር እንዲያስታውሳቸው ነው።" ብሏል! 

         እና ዛሬ ምን ተገኝቶ እንዲህ ይስቃሉ? 
“የእግዚአብሔርም ደስታ ኃይላችሁ ነውና አትዘኑ” 【ነህ ፰፥፲】
እንደሳራ ትውልዱ ላይ ተስፋ ፈንጥቆ የበረከት ዘር ሲተካላቸው  በመካን ማሕጸን ፍሬ ቢታያቸው ገጻቸው በርቶ ፊታቸው ፈክቶ ታይቷል!  በሀገሬ ቲቪ የቀረበው የዶንኪ ቲዩብ ድንቅ ልጆች መሰናዶ በዚህ ሳምንት በደስታ የሚስቁ በሐሤት የሚፍለቀለቁ አቡነ ኤርምያስን ደጋግሞ አሳይቶናል። ዐይናቸው ውሥጥ አንድ ሕፃን ሶልያና ተፈራ ብቻ ሳትሆን  የብዙ ተተኪ አዳጊ ዜጎች ተስፋ ይታያል!  [https://youtu.be/jnt9FJgcj2w]

     ፈለገ አእምሮ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በአቡነ ኤርምያስ ራእይ የታነጸው    “ታላላቅ ካቴድራሎችን ገንብተን በውስጡ አገልጋይ ከሚጠፋ አብነት ት/ቤቶችን ገንብተን እንደጥንቱ በድንኳን ብንገለገል ይሻለናል” በሚል ኃይለ ቃል እንዲህ ያለውን ፍሬ ለማየት ነበር።  ዛሬ ግን የባሰ ሌላ ችግር በሀገረ ስብከቱ ተጋርጧል፤

     ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ (ዶ/ር ) የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የበላይ ጠባቂ በሀገራችን «በወንድማማቾች መኻል ተከስቶ በነበረው እርስ በእርስ ግጭት» የደረሰውን ውድመት ተከትሎ እሑድ ሰኔ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚሌኒየም አደራሽ ከቀኑ 6፡oo ጀምሮ የወደቀችዋን ድንኳን ለማንሳት ፣ የተናደውን ቅጥር ለመጠገን ፣ የፈረሰውን ለማደስና እንደቀድሞው ዘመን ለመሥራት ማንም የማይቀርበት ታላቅ መንፈሳዊ ጥሪ እንዲህ ሲሉ ለቤተክርስቲያን ልጆች አስተላልፈዋል፦
‹‹የክርስትናው ሀዲድ ተሰብሮ የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ እንዳይቋረጥ ሃይማኖታዊ ግዴታችሁን ትወጡ ዘንድ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም አሳስባለሁ፡፡››

«ንሕነኒ ውስተ ሐይላ ንደይ ልበነ ንዴግና ወንበላ በሐ  ወትረ ንሳለማ ለቅድስት ቤተክርስቲያን ☞ እኛም በቤተክርስቲያን  ኃይል ልቡናችንን እንጨምር እንከተላት ሰላምም እንበላት» 【መጽሐፈ ቀሌምንጦስ ፲፩፥፶】

✞ ቴዎድሮስ በለጠ ✞ ሰኔ ፳፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. ከፍራንክፈርት
❀ ተጣሉብኝ ❀
༺♱༻
"ደቂቀ እምየ ተበአሱ በእንቲአየ ⇨ የእናቴ ልጆች ስለእኔ እርስበእርሳቸው ተጣሉብኝ" (መኃ ፩፥፮)

በዛሬው ዕለት የምናገናቸው የከበሩ የቤተክርስቲያን መብራቶች ቅዱሳን ሰማዕታት ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ጴጥሮስ በአንድ ወቅት ስለ እናት ቤተክርስቲያን ክብር ተጣልተው እንደነበር! አንድነቷን ለመጠበቅ «ጽና ፣ አትዛል ፣ ፣ ከጥፋት ተመለስ…» ለመባባል በዛ መንድ ሳይሆን በዚህ መንገድ ጥቀማት እያሉ ተጣሉ!

ዛሬስ ለቤተክርስቲያን ሳይሆን በቤተክርስቲያን ላይ የተነሱ አንድነቷን ለማጽናት ሳይሆን ለመክፈል እንቅልፍ የሚያጡ “በዚህ መንገድ ቢሆን ነው ልክ” በሚል ቅንነት ያለው መበላለጥ ሳይሆን «ትክክል አንተ ነህ እኔ አጥፍቻለሁ» የሚል እንኳ ሲገኝ ይቅርታን በማይቀበል ጥመት ጨፍነው «ዘላቂ ጥቅም እንጂ ቋሚ ጠላት የለኝም» የሚለው ፖለቲከኛው እንኳን የሚበልጣቸው «ሃይማኖተኛ» መሳዮች!

ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው ሆኖ እየታመምን እናስታምማለን እንጂ ቁስላችን ሲያመረቅዙና ሕመማችን ሲያብሱማ ተዉ እንላለን! መንጋውን ለመጠበቅ ያልበቁ በመንጋው መጠበቅ የሚገባቸው ስማቸው እረኛ ከሚለው ወርዶ ተረኛ፣ ዘረኛ … በሚል እየተተካካ ቤተክርስቲያንን የሚያቆስሏት የሚያሳምሟት ከማያምን ይልቅ የከፉ እንዲህ ያሉ ገባርያነ እኪት ጸላዕያነ ሠናያት ለጥፋት ሲሮጡ ሔደው ሲለምኗቸው እምቢኝ ካሉ ተለይተው አለመወገዛቸው ፣ ተጠርተው አለመከልከላቸው ነገ የበለጠ ዋጋ ያስከፍለናል!

“ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፥ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።” 【1ኛ ጢሞቴዎስ 5፥8】

☞ የቀደሙቱ ጳውሎስና ጴጥሮስ ፣ አፈወርቅና ኤጲፋንዮስ ፣ ተክለሃይማኖትና ኤዎስጣቴዎስ… ስለእኔ እርስ በእርሳቸው ተጣሉብኝ ብላ የምታዝንላቸው ቤተክርስቲያን ነበረችን። ዛሬ ግን ስለእርሷ ሳይሆን በእርሷ ላይ ነውና ታዝንብናለች!

በሁሉ መንገድ ሴራው ቢበቃ፣ ሸፍጥ ቢቆም፣ «እበልጥ አልበለጥ» መባባሉ ብናስቀር ፣ መበሻሸቁን ብናርቅ … «በእነ እገሌ ምክንያት ይኽ ሆነ» ባዮች ወጣ ገባውን አይተን ለአንድነት እንቁም መለያየቱን እናስቁም፤ እድሉ ስላለን «በእኛ ምክንያት ነው ይህ ሁሉ የመጣው» ብለን የምንችለውን ብናደርግ። ባትሹት ግን ሁሉን የሚያስችለው እርሱ ሁሉን ይችላል!

ጌታችን ቅዱስ ዮሐንስ ፍቁረ እግዚእን ከሊቀ ሐዋርያቱ ቅዱስ ጴጥሮስ ጋር ወደ አንጾክያ እንዲያስተምሩ ቢልካቸው በዚያ አሕዛብ መከራ አጸኑባቸው ኋላ ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ከቅዱስ ዮሐንስ ቢሰማ በአካሔድ መሳታቸውን ፣ ዘይቤ ማጣታቸውን አይቶ ተለያቸው … የአሕዛብን ልብስ ለብሶ ወደሸንጓቸው ገብቶ በፈሊጥ መከረና ከቅዱስ ጴጥሮስ ደርሶ በፊታቸው በጥፊ መታው ፦ ቅዱስ ጴጥሮስ " ተመይጠኑ ጳውሊ ሃበ ቀዳሚ ግብሩ" ብሎ ደነገጠ "እስኪ ሙት ካስነሳ እንመንበት?" ብሎ መክሮ ከሞተ ፫ ወር (መንፈቅ) ያለፈው የንጉሥ ልጅ እንዲያስነሳ ጠየቀላቸው! ሊቀ ሐዋርያት ሲጸልይ ቅዱስ ጳውሎስ ከውጭ፦ በእነርሱ ልብስ፣ ከውስጥ፦ በንጹሕ መንፈስ "ላንተ ብሎ እንጂ እሾም እሸለምበት ብሎ አይደለምና እባክህ ስማው አስነሳለት" እያለ በጥፊ ለመታው ወንድሙ ለመነ ያም ሙት ተነስቶ ያስነሳኝስ ያ ነው ብሎ ቅዱስ ጳውሎስን ጠቁሞላቸዋል በዚህ ነው "የእናቴ ልጆች ስለእኔ እርስበእርሳቸው ተጣሉብኝ" ያለው የተገለጠው!

የዛሬው የጠሉ የተጠሉና የተጣሉ ጥለኞች ለቤተክርስቲያን ምን እንደሚጠቅሟት እንጃ!

በእግራቸው ገስግሰው በእጃቸው ደም አፍሰው የተመለሱትን አጨብጭቦ ይቅር አልኩ ፣ ረሳሁ ፣ ታረቅሁ… ሲለን ያየነው አካል የገዛ አባቶቹን "ይቅርታቸውን አንቀበልም" ብሎ ልብንም በርንም ዘግቶ መጥፋትቱ የይቅርታን ትርጉም በምን እንደተረዳው እንጃ በራሱ መበቀል እግዚአብሔርን መጣል ነውና የበለጠ ቁጣ ይጠራል!

በዜና አበው እንዲህ የሚል ታሪክ አለ፦

አንድ ወንድም ወደ አባ ስልዋኖስ ሄደና "በጣም ክፉ ነገር እያደረሰብኝ ያለና ሊያጣፋኝ የሚፈልገኝ ጠላት አለብኝ:: እንዲገድሉኝም ለመሰርያን(ክፉ አድራጊዋች) ነግሯቸዋልና እንዲያሳርፍልኝና እንዲገስጸው ልነግር ወደ ባለስልጣኑ መሄድ እሻለሁ" አለው ::እርሱም "እ...የመሰለህን አድርግ አለው...." :: ያም ወንድም "እንግዲያውስ ጸልይልኝ" አለውና አብረው ጸሎት ሲያደርሱ "በደላችንን ይቅር በለን እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል" ከሚለው ስፍራ ላይ ሳሉ አባ ስልዋኖስ "በደላችንን ይቅር አትበለን:: እኛም የበደሉንን ይቅር ስለማንል::" አለ:: ያም ወንድም "አባ... ተው እንጂ እንዲህማ አትበል!" ቢለው "ይበቀልልህ ዘንድ ወደ መኮንኑ የምትሄድ ከሆነ ስልዋኖስ ከዚህ ሌላ አይጸልይም" አለው:: ያም እኁ(ወንድም) ይህን ሰምቶ ወደልቡ ቢመለስ ከእግሩ ሥር ተደፍቶ የበደለውን ይቅር አለ::

❀ ሮሜ. 12:19 "ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና።"

❀❀ ማቴ. 5:44-45 "እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና።"

❀❀❀ ማቴ.6:15 "ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፥ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፥ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና"

በዚህ አያያዝ ክርስትናችን ምኑ ላይ ነው? እንግዲህ እኛም እንደዚህ እያልን ልንጸልይ ነው "በደላችንን ይቅር አትበለን:: እኛም የበደሉንን ይቅር ስለማንል::"
አቤቱ ማረን ፈሪሃ ኃጢዓትን ፣
ፍቅረ መለኮትን ፣
ተዘክሮ ሞትን … ከእኛ አታርቅብን 🙏

☞ ሐምሌ አቦ ፳፻፲፭ ዓ.ም. በቴዎድሮስ በለጠ የተጻፈ።
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ አምስትና በሕገ ቤተክርስቲያን አንቀጽ 19 ቁጥር 3 አስቸኳይ ጉዳይ ሲያጋጥም ምልዓተ ጉባኤ እንደሚያደርግ በተደነገገው መሠረት ሐምሌ 26ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ምልዓተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በተፈጠረው ወቅታዊ የዶግማ፣ የቀኖናና የአስተዳደራዊ ጥሰቶችን አስመልክቶ ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡

ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊትና ዓለም አቀፋዊት የሆነች ቅድስት ቤተክርስቲያን ሕዝብና አሕዛብን፣ ሰውና መላእክትን፣ ፍጡራን እና ፈጣሪን አንድ አድርጋ የሰው ልጆች ሁሉ በቋንቋ፣ በቀለምና በጐሣ ሳይከፋፈሉ ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና አግኝተው ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማህፀነ ዮርዳኖስ የተወለዱ በማየ ገቦ ተጠምቀው የቤተ ክርስቲያን ልጆች በመሆን ልዩነት የሌለባትን ዘለዓለማዊት መንግሥተ እግዚአብሔር እንዲወርሱ በደመ ክርስቶስ የተመሠረተች ስትሆን በየዘመናቱ የተነሣባትን ፈተና ሁሉ አልፋ ከእኛ ዘመን ደርሳለች፤

ምንም እንኳ ከኦርቶዶክስ ትምህርተ ሃይማኖት ፈጽሞ በተለየ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያንን በጐሣና በቋንቋ የመለየት ሂደት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንግዳ ክስተት ቢሆንም ቤተ ክርስቲያን ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ጠባይዋ በተለየ፣ ታሪኳንና ሥርዓቷን በማይመጥን፣ ከሕግ መንፈሳዊ፣ ከሕግ ጠባይአዊ እና ከሕገ አእምሮ በወጣ መልኩ የደረሰባት የዶግማ፣ የቀኖናና የአስተዳደር ጥሰት ቅዱስ ሲኖዶስን እጅግ አሳዝኖታል፤

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሀገር አንድነት፣ ለፍትሕ፣ ለጥበብ፣ ለሕዝብ ትስስር፣ ለማኅበራዊ ዕድገት፣ ለጤና፣ ለሥነ-ምግባር መሠረትና ዐምድ፤ ሆና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈራች፣ የተከበረችና የተወደደች፤ ዕሴቷ እና ዕምቅ የዕውቀት ሀብቷ በምሁራን የታወቀ፣ በትምህርተ ዓለም ሳይቀር የተቀረጸ፤ በእውነተኛ ሊቃውንት የተመሠከረ፣ ቅርሶቿ የተመዘገቡላት ስትሆን፤ ከፍተኛውን ሐዋርያዊ ተልእኮ እንዲወጡ አደራ በተሰጣቸው ሊቃነ ጳጳሳት በማኅበረሰብ ዕድገትና አስተዳደር ውስጥ ከሕዝብ ጋር በቆመች፣ ከፖለቲካ በጸዳች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ መንፈሳዊና ሕዝባዊት ተቋምነቷን በመካድ ከፍተኛ የሆነ ሕገ ወጥ ድርጊትና ተቋምን የመናድ እንደሁም መዋቅሯን የማፍረስ ተግባር ተከናውኗል፡-

በዚሁ መሠረት፡-
ሐምሌ 16 እና 23 ቀን 2015 ዓ/ም በክልል ትግራይ በማእከላዊ ዞን አክሱም ሀገረ ስብከት በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ማርያም ገዳም ውስጥ የተፈጸመውን ሕገወጥ የሆነ አስነዋሪ፤ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት አስመልከቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ሐምሌ 26 ቀን 2015 ዓ/ም አስቸኳይ ምልዐተ ጉባዔ አድርጓል፤

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በደመ ክርስቶስ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ያለፈተና የኖረችበት ጊዜ እንደሌለ ቅዱሳት መጻሕፍትና የታሪክ መዛግብት ሲመሰክሩ በዘመነ ሐዋርያት ቢጽ ሐሳውያን፣ በዘመነ ሊቃውንት የተለያዩ መናፍቃን፣… በየጊዜው እየተነሡ ሲፈታተኗት ኑረዋል፡፡ አሁንም በግልጽ እንደሚታየው ከውጭም ከውስጥም በተደራጁ ምንደኞች በመፈተን ላይ ትገኛለች፡፡ ይህንኑ በመረዳትም ቅዱስ ሲኖዶስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባዔ፣ የሊቃውንት ጉባኤ፤ የሕግ አገልግሎት መምሪያና የህግ ባለሙያዎች አቢይ ኮሚቴ፤ የውጪ ግንኙነት መምሪያ፣ ካቀረቡት ዶግማዊ፣ ቀኖናዊ፣ ታሪካዊና ትውፊታዊ ሰነዶች በመነሣት የቤተ ክርስቲያንን ልዕልና ለማስከበር ያስችል ዘንድ ጥልቅ ውይይት አድርጓል፡፡

በዚህም መሠረት ሐምሌ 16 እና 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በክልል ትግራይ በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ገዳም ውስጥ በትግራይ ክልል በሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳት፡-
1. አባ ኢሳይያስ
2 አባ መቃርዮስ
3. አባ መርሐ ክርስቶስ
4 አባ ጴጥሮስ መሪነት እጅግ አሳዛኝ ኢ-ሲኖዶሳዊ የሆነ አስነዋሪ፣ ሕገ-ወጥ፣ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት በመፈጸም 10 መነኮሳትን በእጩነት በመምረጥና ለዘጠኙ ህገወጥ ሲመት በመፈጸም፣ ሥርወ ትውፊት ዘሐዋርያት የሆነውን የኢትዮጽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ መንበር በመካድ "መንበረ ሰላማ" የሚባል ህገወጥ መንበር በመሠየምና በህገወጥ መንገድ የሾሟቸውን ግለሰቦች ሊቃነ ጳጳሳት በሚመሯቸው በሀገር ውስጥና በውጪ በሚገኙ አህጉረ ስብከት በሕገ ወጥ መንገድ በመመደብ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት አልፎ አንዲት ኩላዊትና ዓለም አቀፋዊት የሆነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን የሚከፋፍል፤ የሀገር አንድነትን የሚሸረሽር እና የሚያፈርስ፣ ምእመናንን ከምእመናን፣ ካህናትን ከካህናት፣ ሊቃውንትን ከሊቃውንት ወጣትን ከወጣት የሚያጋጭ ሰላም የሚያናጋ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ተገንዝቧል። በመሆኑም፤

- የቤተ ክርስቲያን መንበር ሐዋርያዊ ነው፡፡ ሐዋርያዊ መንበር ጌታችን አስተምሮ ከሾማቸው ከዐሥራ ሁለቱ ከሐዋርያት የወጣ አይደለም፤ ሥልጣነ ክህነት የሚተላለፍበት፣ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ትምህርተ ሃይማኖት እና ቀኖና ምንጩ ወይም ሥሩ የሚነገርበት፣ የሐዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን አማናዊና ሐዋርያዊ ታሪክ፣ ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ትውፊት የሚጀመርበት መነሻ ነው፡፡

- ቤተ ክርስቲያን የምትመራው በሐዋርያት ሥልጣነ ክህነት ነው፤ ይኽንን ሥልጣን ማንም እንደፈለገው ሊከፋፍለው አይችልም፤ በየትም ቦታ ያሉ ጳጳሳት ከቅዱስ ሲኖዶስ እና ከቅዱስ ፓትርያርክ ዕውቅና ውጭ እንደፈለጉ በቡድኑ እየሆኑ መንበር አቋቁመናል ሊሉ አይችሉም፤ ይህ ከቤተ ክርስቲያን ትውፊትና ታሪካዊ ቅብብል ውጭ የሆነ መናፍቅነት ነው፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ ሕግ እና ሥርዓት ውጭ መውጣት ሕገ ወጥነት፣ ቀኖናን መሻር፣ ኃይማኖትን ማፍረስ ነው፡፡ የገቡትን ቃል መጣስ ነው፤ ከጥንት ጀምሮ መንበር ያለ ፓትርያርክና ከሀገሪቱ ርእሰ ከተማ ውጭ የማይሰየም መሆኑ እየታወቀ መንበር አቋቁመናል ማለት የፓትርያርክን እና የሲኖዶስን ሥልጣን መቃወም፤ ከሃይማኖትም፣ ከቀኖናዊ ትውፊትም፣ ከአስተዳደራዊ መዋቅርም መውጣትና ራሳቸውን ከቤተ ክርስቲያን መንበር የለዩ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ድርጊቱን አውግዟል፡፡

ይህን ህገወጥ ተግባር ለመፈጸም በሀገራችን ተከስቶ የነበረው ጦርነት እንደ ምክንያት የተጠቀሰ ቢሆንም ቤተክርስቲያን ከጦርነቱ በፊት ጦርነት እንዳይከሰት ያደረገችውን ጥረት በጦርነቱ ወቅት ለተደረጉ ድጋፎችና ከጦርነቱ በኋላ ለተደረጉ የእንወያይ ጥረቶች እንዲሁም በቤተክርስቲያን በኩል የተዘረጋውን የሰላምና የእርቅ በር ይልቁንም ለሰላም ሲባል በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ የተጠየቀውን ይፋዊ ይቅርታ በመግፋት የተደረገ ኢ-ክርስቲያናዊ ተግባር ነው።

በመሆኑም
• በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 16 ንዑስ ቁጥር 30 የአጲስ ቀጶሳት መሾም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፣ በቤተ ክርስቲያን ቀኖና መሠረት እንዲመረጡና እንዲሾሙ የመወሰን ሥልጣን የቅዱስ ሲኖዶስ መሆን የሚደነግገውን ክፍል በግልጽ የጣሰ በመሆኑ
• በሕገ ቤተክርስቲያን አንቀጽ 31 ንዑስ ቁ 1 እና 3 የቅዱስ ፓትርያርኩን የመዓርግ ስምና መንበር በተመለከተ የተደነገገውን ድንጋጌ የሚያፋልስ ህገወጥ ተግባር የተፈጸመ በመሆኑ
• በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 37 ንዑስ ቁ.1 የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ የሚፈጸመው ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ አስፈላጊ መሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሲታመንበትና ሲወሰን ብቻ እንደሚፈጸምና መደንገጉ፤
• በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 18 ንዑስ ቁጥር 5 የቤተ ክርስቲያንን ሃይማኖታዊ ሕግጋትንና ቀኖናን የሚያፋልስ ሊቀ ጳጳስ /ኤጲስ ቆጶስ/ ከአባልነት እንደሚሰረዝ በመደንገጉ፤
• በአጠቃላይ የተፈጸመው ሕገ ወጥ ተግባር በሕገ ሰብእም ሆነ በሕገ እግዚአብሔር ሚዛን የተወገዘ ከመሠረተ እምነት የተለየ፣ በአበው ቀኖና፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን እና በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ተቀባይት የሌለው ነው፡፡ ስለዚህ

1ኛ. በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ንኡስ አንቀጽ 138 መሠረት ሐምሌ 16 እና ሐምሌ 23 ቀን 2015 ዓ.ም በክልል ትግራይ በማዕከላዊ ዞን አክሱም ሀገረ ስብከት በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን ውስጥ
1. ብፁዕ አቡነ ኢሳይያስ የመቀሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የእንቅስቃሴው ሰብሳቢ
2. ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ በክልል ትግራይ የማዕከላዊ ዞን አክሱም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
3. ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ የአዲግራት ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
4. ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የሽሬ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና በመጣስ ባልተሰጣቸው ስልጣን 9 ኤጴስ ቆጰሳትን ሾመናል፤ ሲኖዶስ አቋቁመናል በማለት በተለያዩ ሚዲያዎች በሰጡት መግለጫና በክልሉ መንግሥት ሚዲያ በተላለፈው የቀጥታ ስርጭት የተረጋገጠ በመሆኑ በዚሁ ድርጊታቸው በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም የሚኖረውን ሕዝበ ክርስቲያንን በማታለል የክህደት እና የኑፋቄ ተግባር በመፈጸማቸው በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ፤ ከቤተ ክርስቲያን የተሰጣቸውን ከዲቁና ጀምሮ ያለው ሙሉ ሥልጣነ ክህነት በመሻር አውግዞ ለይቷቸዋል፡፡

በመሆኑም፡-
ሀ. ሥልጣነ ክህነታቸውና የማዕረግ ስማቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ውሳኔ የተነሣ ስለሆነ ከዛሬ ሐምሌ 26 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በቀድሞ ዓለማዊ ስማቸው እንዲጠሩ፤
ለ. በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አገልግሎት ዙርያም በሕይወትም ሆነ በሞት ማናቸውንም መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳያገኙ ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን ለይቷቸዋል፡፡
• ይሁን እንጅ ከላይ በስም ተጠቅሰው የተወገዙት ግለሰቦች በሠሩት የቀኖና ጥሰት ተጸጽው ይቅርታን ቢጠይቁ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምህረት ደጆች ሁል ጊዜ ክፈት መሆናቸውና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የምንቀበላቸው መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳውቃል፤
2ኛ. የቅዱስ ሲኖዶሱንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ልዕልና በመዳፈር እና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ በተነሳሱ ግለሰቦች አማካኝነት የኤጲስ ቆጶስነት ሹመት አግኝተናል፤ ተሹመናል እያሉ የሚገኙ 9 መነኮሳት

፩. አባ ዘሥላሴ ማርቆስ
፪. አባ ኃይለ ሚካኤል አረጋይ
፫. አባ እስጢፋኖስ ገብረ ጊዮርጊስ
፬. አባ መሓሪ ሀብቶ
፭. አባ ኤልያስ ታደሰ ገብረ ኪዳን
፮. አባ ጽጌ ገነት ኪዳነ ወልድ
፯. አባ ዘርአ ዳዊት ብርሃነ
፰. አባ ዮሐንስ ከበደ
፱. አባ የማነ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል

በሕገ ወጥ መንገድ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንንን ጥሰው የተገኙ በመሆኑ አስቀድሞ ከቤተ ክርስቲያን የተሰጣቸው ከዲቁና ጀምሮ ያለው ሙሉ ሥልጣነ ክህነት ተሽሮ ከዛሬ ሐምሌ 26 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አገልግሎት ዙርያ በሕይወትም ሆነ በሞት ማናቸውንም መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳያገኙ ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን ለይቷቸዋል፡፡

3ኛ. ይህ ህገወጥ ሢመት እንዲፈጸም ከመጀመሪያው ጽንሰ ሀሳብ ጀምሮ መሪ ተዋናይና ቀስቃሽ በመሆን ኢትዮጵያን ኤልዛቤል በማለትና ስሟን የሚጠራ የተረገመ ይሁን በማለት እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጋር የዶግማ ልዩነት አለን በማለት የኑፋቄ ትምህርት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተናገሩትና በህገወጥ ሢመቱ ላይም በእጩነት ተመርጠው በሂደት ላይ ያሉት አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤልና ሂደቱን በዋና አስፈጻሚነት በመምራትና መግለጫ በመስጠት ላይ ያሉት መ/ር ተስፋዬ ሐደራ ከዛሬ ሐምሌ 26 ቀን 2015 ዓ/ም ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተወግዘው ከቤተክርስቲያን ተለይተዋል።

ከላይ በስም ተጠቅሰው የተወገዙት ግለሰቦች በሠሩት የቀኖና ጥሰት ተጸጽው ይቅርታን ቢጠይቁ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምህረት ደጆች ሁል ጊዜ ክፈት መሆናቸውና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የምንቀበላቸው መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳውቃል።

4ኛ. “መንበረ ሰላማ” የሚለው ሕገወጥ ሥያሜን በተመለከተ በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ትውፊትም ሆነ በቀደምት አብያተ ክርስቲያናት ትውፊት የማይታወቅ፣ ሃይማኖታዊ መሠረት የሌለው፣ ከቀኖና የወጣ፣ አስተዳደራዊ መዋቅርን የሚያዛባ በመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አትቀበለውም፤ በተጨማሪም ከአንዲት፣ ቅድስት፣ ሐዋርያዊትና ዓለም አቀፋዊትየሆነች የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ መንበር መሠረተ እምነት፣ ታሪክና ቀኖና፣ ከአስተዳደር እና ሕግ ባፈነገጠ ሁኔታ ትውፊትን በመዳፈር ጎሣን መሠረት አድርጎ የተፈጠረ ሕገ ወጥ አደረጃጀት በመሆኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አውግዞታል፡፡ ይሕንንም የክርስትናን ትውፊት እና ሐዋርያዊ መሠረት የሚዛባና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የማይወክል መሆኑ ታውቆ በመላው ዓለም ለሚመለከተው ሁሉ በደብዳቤ እንዲገለጽ እንዲደረግ፤

6. በየደረጃው የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ኃላፊዎች፤ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ መነኮሳት፤ አገልጋይ ካህናት፤ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፤ ልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ማህበራት እና ምእመናን እና ምእመናት ይህን ሕገ ወጥ አድራጎት ከመከላከል እና የቤተ ክርስቲያናችሁን ደህንነት ከመጠበቅ በተጨማሪ ለዚህ ሕገ ወጥ አድራጎት ልዩ ልዩ ድጋፍ የሚያደረግ ተቋማት እና ግለሰቦችን አስፈላጊውን ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ የመከላከል ሥራችሁን እንድትወጡ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

8. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስምን ከፊትም ሆነ ከኃላ በመጨመር እና በመቀነስ በከፊልም ሆነ በሙሉ መጠቀም፤ ዓርማዋን፤ አድራሻዋን፤የአምልኮ እና የሥርዓት መፈጸሚያ የሆኑ ንዋያ ቅዱሳትንና አልባሳት እንዲሁም መጻሕፍት መገልገል የማይችሉ መሆኑ ታውቆ ይህንን ጉዳይ በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊ አካላት እና የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ኃላፊዎች ተከታትለው እንዲያስፈጽሙ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነ ሲሆን በተጨማሪም ይህን ውሳኔ ተላልፈው በሚገኙ ማናቸውም ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ ተገቢውን ሕግ አግባብ ተከትሎ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ዓለማት የሚያስፈጽም ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች በመመደብ ተገቢውን ሁሉ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በኩል እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
9. በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚገኙ መንግስታዊም ሆነ መነግስታዊ ያልሆነ ተቋማት፤ አኃት አቢያተ ክርስቲያናት፤ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት፤ የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት፤ የዓለም አቢያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት፤ የመላው አፍሪካ አብያት ክርስቲያናት ጉባዔ እና ሌሎች የአብያተ ክርስቲያናት እና የሃይማኖት ጉባኤዎች በሙሉ እነዚህ የተወገዙት ግለሰቦች የኢትዮጵያ ኦርቶደክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የማይወክሉ እና ምንም አይነት የሥራ ግንኙነት የሌላቸው መሆኑ ታውቆ ማናቸውም ግንኙነት በቤተ ክርስቲያኑቱ ስም እንዳያደርጉ በጽሑፍ አንዲገለጽ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

11. እነዚህ ግለሰቦች የፈጸሙት ተግባር ሃይማኖቱን የሚወድ፣ አባቶቹን የሚያከብር እና አስተዋይ የሆነውን የትግራይ ሕዝብ የማይወክል፣ የራሳቸውን የሥልጣን ጥማት ለማርካት ያደረጉት ሕገወጥ የቀኖና ጥሰት መሆኑ እንዲታወቅ፤ በተጨማሪም ለሚያሠራጩት የሐሰት አሉባልታ ወደፊት ተገቢው መልስ እንዲሰጥበት ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል።

12. ይኽ ሕገወጥ አደረጃጀት ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የታሰበበት፤ በየጊዜው የነበሩ የፖለቲካ እና የመንግሥት ኃላፊዎች በመታገዝ ሥር የሰደደ ድብቅ አጀንዳ በሚያስፈጽሙ ግለሰቦች የተቀናበረ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ተገንዝቦ ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዞታል፡፡ በመሆኑም ሕገ ወጥ አደረጃጀትን ማምከን እና ቤተ ክርሰቲያንን ነፃ ማድረግ የሚቻለው ጠንካራ ውስጣዊ አደረጃጀት እና ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ሲደረግ በመሆኑ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጀምሮ ሊቃውንት፣ መላው ውሉደ ክህነት፣ ወጣቶች ሰንበት ትምሀርት ቤት አባላት፣ መንፈሳውያን ማኅበራት፣ ምእመናን እና የቤተ ክርስቲያን ወዳጆች በሙሉ በመጾም፣ በመጸለይ፣ የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮና መዋቅር በጠበቀ መልኩ በመደራጀት አፍራሽ እና የጥፋት መረጃዎችን፣ በመሰብሰብ፣ በመተንተን፣ ለውሳኔ በማቅረብ የቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ደኅንነት እስኪረጋገጥ ድረስ ያለማቋረጥ በመንፈሳዊ ተጋድሎ መበርታትና የመጣብንን ፈተና በጽናት መታገል እንደሚገባ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡

13. በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በተለያዩ ክፍሎች እየተከሠተ ያለውን የሰላም መደፍረስ እና የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት የሰው ሕይወትና የንብረት ውድመት የተፈጠረ አለመግባባት ካለፈው ስህተታችን በመማር ችግሩን ተቀራርቦ በውይይትና በእርቅ እንዲፈታ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም አካላት የሰላም ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡

14. እንደ ሀገር የገጠመንን የሰላም መደፍረስ በተመለከተ ዘላቂ መፍትሔ በማፈላለግ እንደ ቤተ ክርስቲያን ስለ ሰላም ጉዳይ የሚሠሩ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ምሁራን ያካተተ ዐቢይ ኮሚቴ በቋሚ ሲኖዶስ በኩል ተቋቁሞ ሥራው እንዲሠራ ወስኗል፡፡

በመጨረሻም እስከ አሁን ድረስ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጎን በመሆን አጋርነታችሁን ያሳያችሁ፣ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት እና ሉዐላዊነት መከበር የበኩላችሁን በመወጣት መግለጫ የሰጣችሁ ሁሉ በልዑል እግዚአብሔር ስም እያመሰገንን ለወደፊቱም በጸሎታችሁ እና በመልካም አጋርነታችሁ ከጎናችን እንድትሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
ሐምሌ 26 ቀን 2015 ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
#የጽዮን_መቀነት
🌈✿ ✥ ✦━

መጪው ጾመ ፍልሰታ ሰሙነ ሱባኤ ነው። በዚህ ወቅት መቸውንም የማይዘነጋውን የቅዱሳን ሐዋርያትን ሐዘን ሐዋርያዊቷ ቤተክርስቲያን በላቀ ትኩረት ታስባለች !

ከክርስቶስ መከራ መስቀል በታች የፍጥረት ሁሉ ጸወን (ምሽግ) የሆነች ጽዮን ማርያምን ማጣት ፣ የሕይወት መሠረት የምትሆን ወላዲተ አምላክን በሞት መነጠቅ እና የትንሣኤ እናት አዛኝቷ ድንግልን ቀብሮ መመለስ… ይኽን የመሰለ ሐዘን በሐዋርያቱ ዘንድ ደርሶ ያውቅ ይሆን? እንጃ!

ይህን ጥልቅ ሐዘን ያስወገደው ሞትን ያሸነፈ ሕይወት ፡ መቃብርን የረታ ትንሳኤ ፡ ርደትን ድል የነሳ ዕርገት በጽዮን መቀነት በሰበነ ማርያም ለሐዋርያቱ የተበሠረው የምሥራች ነው። አብሣሪው ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ ዘሕንደኬ ነው።

ሐተታው እንዲህ ይተረካል

«ጌታችን ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር ቆይቶ ሙስና መቃብር (የመቃብር ጥፋት) ሳያገኘው፣ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በሥልጣኑ እሑድ በመንፈቀ ሌሊት እንደተነሣ ሁሉ እርሷም በተቀበረች በሦስተኛው ቀን ማኅደረ መለኮት ናትና ሙስና መቃብር ሳያገኛት መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳትል የልጅዋ ሥልጣን ኃይል ሆኗት በመነሣቷ ትንሣኤዋ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጅዋ ትንሣኤ” ነው ተብሎ ይመሰከራል! »

የድንግል መካነ ዕረፍት በጌቴሴማኒ ነው፤ ሥርዓተ ቀብሯ በተፈጸመ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ቶማስ ዘሕንደኬ አልነበረምና ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን በተቀበረች በ«ሦስተኛው» ቀን እንደ ልጅዋ ትንሣኤ ተነሥታ ስታርግ ያገኛታል፡፡ ትንሣኤዋን ሌሎቹ ሐዋርያት አይተው ለእርሱ የቀረበት መስሎት ተበሳጭቶ “በመጀመሪያ የልጅሽን ትንሣኤ አሁን ደግሞ የአንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ” ብሎ ከማዘኑ የተነሣ ከደመናው ተወርውሮ ሊወድቅ ቃጣው፡፡ እመቤታችንም ከእርሱ በቀር ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሳኤዋን እንዳላዩ ነግራው አጽናንታዋለች፤ የተጽናናው ቅዱስ ቶማስ ያዘኑትን ወንድሞቹን እንዲያጽናና የሆነውን ሁሉ እንዲነግራቸው አዝዛው #ምልክት_ይሆነው_ዘንድ_ሰበኗን_ሰጠችው በዚያ ገንዘዋት ነበርና።

ቅዱስ ቶማስም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ሐዋርያት በሐዘን እመቤታችንን‘ኮ ቀበርናት ብለው ነገሩት እርሱም የበለጠ ይደነቁ ብሎ “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንዴት ይሆናል?” አላቸው፡፡ “አንተ እንጂ ቀድሞ የጌታን ትንሣኤ ተጠራጠርክ አሁንም አታምንምን?” ብለው በቅዱስ ጴጥሮስ መሪነት ወደ እመቤታችን መካነ መቃብር ይዘውት ሔዱ በዚያም መቃብሯን ቢከፍቱ እንኳን ለእርሱ የሚያሳዩት ለራሳቸውም ያዩት ነገር አልነበረም፤ ሥጋዋን በማጣታቸው ደግመው በሐዘን ተዋጡ እጅጉንም ደነገጡ። ያኔ ሐዋርያው ቶማስ “አታምኑኝም ብዬ እንጂ እመቤታችን ተነሥታ ዐርጋለች” ብሎ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው፡፡ የምሥራቹ ብሥራት ማረጋገጫ ምልክት እንዲሆን ጽዮን ድንግል ማርያም የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው፡፡

☞ ይኽ ሰበኗ መቀነቷ ነው ፣ መታጠቂያዋ ነው ፣ መግነዟም ነው! በገዛ እጇ ከግመል ጠጉር ያሰናዳችው ስለመሆኑ የትውፊት ምስክርነት አለ።

ያንን መቀነት ለበረከት ቆራርጠው ከተከፋፈሉ በኋላ ብዙኅ ገቢረ ተአምራት ፡ ታላላቅ ኅብረ መንክራት እያደረጉበት ወደ የአህጉረ ስብከታቸው በደስታ ሄደዋል፡፡ ምስክርነቱን ለማጽናት ዛሬም ሠራዒ ዲያቆኑ በቅዳሴ ጊዜ በሚይዘው መስቀል ላይ የሚደረገው ጨርቅ የእመቤችን ሰበን ምሳሌ ሆኖ ሐዘናችን በተስፋ ሊታበስበት ይታያል።

ለእኛም የትኛው ቶማስ ይሆን የማርያምን መቀነት አምጥቶ ከሐዘን የሚያረጋጋን?

ለዛሬው ይህን ምሥጢራዊ ሰበን ከሁለት ወቅታዊ ፈተናዎች ጋር አያይዘን ብንመካከርበትስ አልኩ!
አንዱ እሳተ ሰዶምን ያዘነበ ግብረ ገሞራ (እሳተ ገሞራን ያዘነበ ግብረ ሰዶም ቢል አንድ ነው ቃለ ጸሐፊ ነው… )
ሁለተኛው በመንበር ሰበብ ያየነው መከፋፈል

የማርያም ሰበን እና ግብረ ሰዶማዊነት
✥ °°°🌈°°°°°°°🌈°°°°°°°° ✥

ኪዳነ ምሕረትን ትእምርተ ኪዳኑ ለኖኅ ይሏታል። በዚህ መነሻ የማርያም መቀነት የኖኅ ቃልኪዳን ምልክት የሆነው የቀስተ ደመና ሌላ ስሙ ሆኖ ሲጠራበት እንሰማለን። ያንን በኖኅ በኩል ፍጥረቱን ከጥፋት ለማዳን ለምሕረቱ ማሳያ በምልክትነት ከሰማይ ቀስተ ደመናውን እያሳየ ምልክት እንደሠጠ ፡ ይኽን በቶማስ በኩል የሐዋርያት ሐዘን እንዲርቅ ሰበኗን ለምልክት ሠጥታቸዋለች። ዛሬም ለእኛ ከጥፋት ማምለጫ ከሞት መውጫ እንዲሆን የተገባላትን ቃልኪዳን በቀስተ ደመና ቀስተደመናውን በማርያም ሰበን ወክለን «የጽዮን መቀነት ያድነን ከጥፋት» እያልን ወደላይ አንጋጠን ደጅ እንጠናበታለን። በዓለምም ላይ የበጎ ትግል መገለጫ አድርገው አንዳንዶች ተጠቅመውበታል፤ ለምሳሌ በ1994 ዴዝሞን ቱቱና ኔልሰን ማንዴላ የድኅረ አፓርታይድ ዴሞክራሲያዊ ሀገር ዜጎች መጠርያ ይሁን ብለው ነበር። በዚህም የቀስተደመና ሕዝብ በሚል መጠሪያ ዜጎች ታውቀዋል። በሀገሪቱ ሰንደቅ ያለውን የ6 ቀለማት ውክልና እንደሥጦታ አይተው ቀስተደመናዊ [Rainbowism] እንቅስቃሴ የጸረ ዘረኝነትን መገለጫ ሆኗቸው ለነጻነት እንደውክልና አገልግሏል።

ይሁንና አንዳንዶች መቀጣጫ ቀስቱ የተመለሰ ባለኅብር ደጋን [multicoloured circular arc] የመሰለውን ምልክት ዛሬ ላይ በማይገባ መንገድ ለማይገባ ዓላማ መገለጫችን ነው እያሉ ከዓላማው በተጻረረ መንገድ ፡ ቅዱስ ዳዊት "ወረሰዩ ትእምርቶሙ ትእምርተ ዘኢያእመሩ ⇨ የማያውቁትንም ምልክት ምልክታቸው አደረጉ” እንዳለው ቀስተደመናን ያላወቁት ባላወቁት መንገድ እንጠቀምበት ብለው ይኽን የሚያረጋጋውን ምልክት ሁከት የሚፈጥር ፤ ይኽን ሰላም ሠጪውን ዐርማ መንፈስ የሚያስጨንቅ … እናድርገውታል【መዝ ፸፫፥፬】

እንደጊዜአዊ አቋም ስለእነዚህ "ስም አይጠሬ” ነውረኞች አብዝቶ ማውራት፣ ትኩረት መስጠት መረጃ ማዛመትና ዓላማቸውን ማሳካት እንደሆነ ስለማምን ለግንዛቤ ጥቂት ካልን በተከታዩ የቅዱስ መጽሐፍ ቃለ ተማጽኖ እንለፈው።
☞ “ምልክትንም ለመልካም ከእኛ ጋር አድርግ”【መዝ ፷፮ ፥ ፲፯】

የማርያም ሰበን እና የመንበር መከፈል!
✥ °°°🌈°°°°°°°🌈°°°°°°°° ✥

በአንዲቷ ኅብረ ክርስትና የጸኑ ሐዋርያት ሰበኗን ተከፋፈሉና ዓለምን ዞረው አስተማሩ እንጂ እርስ በእርስ ተከፋፈሉ የሚል ከምንም አናገኝም። ከሰሙኑ የታቦተ ጽዮን ማደርያ የቅዱሳኑ ገዳማት መኖርያ የሰሜን ክፍል መንበረ ሰላማ ይባል የሚል የቤት-ሥራ ሰጥተው የሚከፋፍሉን ጥርስ ያወጡ ጉዶች እያየን ነው። በተመሳሳይ ፈተና የወደቀችውን የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለዚህ ጉዳት ክብደት ማሳያ አድርገን በምሳሌነት እናንሳ።

ጥንቱን አንድ የነበረችው የሕንድ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ዛሬ ለሦስት ተከፋፍላለች
① ማርቶማ (በተሐድሶ ኑፋቄ የተከፈለ)
② የጃኮባይት ኦርቶዶክስ ሲሪያን ቤተ ክርስቲያን (አስተዳደርን መነሻ አድርጎ በመንበር ሰበብ የተከፈለ)
③ የማላንካራ ቤተክርስቲያን በሐዋርያዊ እምነቷ ጸንታ የቀረች
ቀደም ብሎ በቅኝ ግዛትና በእርዳታ ሰበብ ወደ ቅዱስ ቶማስ ልጆች ያቀኑ ሚሲዮናውያን በይበልጥ ካቶሊካውያንና ፕሮቴስታንቱ እንዲሁም በ፲፱ኛው መ/ክ/ዘ በውሥጥ ተሰግስገው ቤተክርስቲያኒቷን በተሐድሶ ከፈልናት ያሉ ማርቶማዎች እየተፈራረቁ ዘምተው በሀገረ ሕንድ ካሉና ቅዱስ ቶማስ ከሠራቸው ሰባት ተኩል አብያተ ክርስቲናት ውሥጥ (ስምንተኛውን ሳይጨርስ በሰማዕትነት በማረፉ) ከሦስቱ በቀር ሌሎቹን አብያተ መቅደሶችና ከርትዕት ቤተክርስቲያን ልጆች አያሌዎቹን አስክደው ነጥቀዋል።

ይህ ሳይበቃ ሁለተኛው ወገን ጥያቄው የመንበር በማስመሰል አስተዳደርን ወደ ወደ ቀደመው የሶርያ መንበር እንመልስ የሚል ጥያቄ በማንሳትና የእርስ በእርስ መከፋፈል መርዝ በመትከል ለብዙ ቅርስና ለሚሊዮን የቤተክርስቲያኒቷ ልጆች መነጠቅ ምክንያት ሆኖ እየፈተናት ይገኛል።

የመንበር ጉዳይ በሕንድ ቤተክርስቲያን ?
✥ °°°°°🌈°°°°°°°🌈°°°°°°°° ✥

ከ፪ ዓመታት ቀድሞ ወንድማችን መኮንን ሀብተሚካኤል Mekonnen Habtemichael እጅግ ቁጭት በተመላ የበረሃ ምንጮች (ማላንካራውያን) በሚል እጅግ አስተማሪ መጽሐፉ ይህን እያነሳ የእኛም በዘርና በጎሳ መከፋፈል ወደ መንበር ጥያቄ ማደጉ እንደማይቀር እንደ ቃለ ትንቢት ሥጋቱን ገልጦ እንነበር እናያለን።

የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የየዘመናቱ ተግዳሮትና ለብዙ ችግሮች ምንጭ እንደሆነ በጥልቅ ምክክር የታመነበት የመንበር ጥያቄ ቤተክርስቲያኗ ራሳን ችላ የሕንድ ማላንካራ ቤተክርስቲያን በሚል ከሲርያ መንበር እንድትለይ ሆኖ ነበር ። (የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከግብፅ ቤተክርስቲያን የተለየችውም በተመሳሳይ ርምጃ መሆኑን ልብ ይሏል) ከ1653 ጀምሮ የላቲኑን ቀንበር ጥላ በኦርቶዶክሳዊ ፍኖት ትጓዝ የነበረችው የማላንካራ ሜትሮፖሊታን በ1912 ዓ.ም. በማላንካራ ቤተክርስቲያን በተከሰተው ነውጥ (Turmoil) ስትፈተን የአንጾክያ ቤተክርስቲያን ጣልቃ በመግባት እግድ አስተላልፋባት ነበር። ያኔ ነበር ቤተክርስቲያኗ ራሷን ከአንጾክያ (ሲሪያ) መንበር ነጻ አውጥታ የመጀመርያው የምሥራቅ ማላንካራ ካቶሊኮስ እንዲሆኑ ቅዱስነታቸውን ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ጳውሎስ 【His Holiness Baselios Paulos The First Catholicos ofthe East in Malankara (1912-1913)】በፕትርክና ማዕረግ የሾመችው።

በቅርቡ ግን በሐዋርያት ወራሴ መንበርነት የምትታወቀዋን መንበረ ቶማስ ትተው የንጾክያ መንበር መሥራች የሆኑ በሚል ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ጳውሎስን አንስተውና በሮማው የቅዱስ ጴጥሮስ ላዕለ ኵሉ ርእሰ መንበርነት ሐሳብ ተጠልፈው ከ2002 ዓም ጀምሮ ራሳቸውን ከፍለዋል [The Jacobite Syrian Orthodox Church of India accepted the Petrine primacy and supremacy of Patriarchs akin to the Church of Rome.]

በመንበር ሰበብ አንድ ሚሊየን ሕዝብ ይዘው በአሜሪካ ካናዳ እንግሊዝ ምዕራብ አውሮፓ አውስትራሊያና ሌሎች ሀገራት ሀገረ ስብከት በመክፈት የሕንድ ቤተክርስቲያንን አዳክመዋል።

የማርያም መቀነትና የሕንድ አዲሱ መንበር
✥ °°°°°°°🌈°°°°°°°🌈°°°°°°°° ✥

በቅዱስ ቶማስ በኩል የተላከውን የእመቤታችን ሰበን (የጽዮን መቀነት) ሐዋርያቱ ለበረከት ቆራርጠው ከተከፋፈሉ በኋላ ብዙኅ ገቢረ ተአምራት ፡ ታላላቅ ኅብረ መንክራት እያደረጉበት ወደ የአህጉረ ስብከታቸው በደስታ እንደሄዱ ከላይ ዐይተናል።

ርቱዓን ሐዋርያቱ የተከፋፈሉበት ሳይሆን የተከፋፈሉት ይህን መቀነት The Girdle of Thomas, Virgin's Girdle, Holy Belt, Sacra Cintola , the Cincture of the Theotokos … በሚል መጠርያ በዓለማችን በታላቁ የምሥራቃውያን መካነ ምናኔ ማውንት አቶስን (Vatopedi Monastery on Mount Athos) ጨምሮ በብዙ ቦታ በክብር ተቀምጦ ይጎበኛል።

በሕንድ የቀረው የጽዮን መቀነት የቅዱስ ቶማስ በረከት ግን በመንበር ጥያቄ ሰበብ በተከፈለው ቤተክርስቲያን Manarcad Church (The Holy Girdle of the Virgin Mary ) ሥር መውደቁ የእናት ቤተክርስቲያን የሁል ጊዜ ሐዘንና የማይሽር የመከፋፈል ጠባሳ ሆኖ ያለመፍትሔ ቀርቷል!

የእኛውስ በመንበር ሰበብ መከፋፈል ጥያቄ ወዴት እያመራ ይሆን?
አክሱም ጽዮን ሳስባት የሕንዱ የማርያም ሰበን ቤተ መቅደስ ዕጣ ፈንታ የተጋረጠባት ይመስለኛል! የቃልኪዳኑ ምልክት ታቦተ ጽዮንን እጅ መንሳት የባዕዳንን ደጅ እጅ እንደመንሳት ኅሊናችን እንዲቆጥር አስጨናቂዎች ዕረፍት በማጣት የዋሃንን ሲያስቱ እያየን ነው።

ደብረ ዳሞን ፣ ደብረ በንኮልን ፣ ደብረ ሃሌሉያን ፣ እንዳ ገሪማን ፣ አባ ጰንጠሌን ፣ መርዓዊ ክርስቶስን፣ አቡነ ኢዮስያን፣ ገርአልታን ፣ ጉንዳ ጉንዶን፣ አቡነ ቶማስን ፣ አቡነ ይምዓታን ፣ አብርሃ ወአጽብሃን … ፻፲፭ቱ ጥንታውያን ገዳማት … ስንቱን ዘርዝሮ መጨረስ ይቻላል? ብቻ ብዙ የብዙ ብዙ የሆኑ ሀብቶቻችንን ማንም ምእመን የእኔ የሚላቸው የቤተክርስቲያናችን ቅርሶች ዛሬን መንበረ ሰላማ በሚል ሩጫ መከፋፈሉ ተጀምሮ ነገ ላይ የሌላ እንዳይባሉ አርቆ በማሰብ መሥጋትና መጨነቅ ይገባል።

በእኛውም ቢሆን የአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ዘመነ ጵጵስና በግብፅ መንበር ጥላ ሥር የነበረ እንጂ መንበረ ሰላማ የሚል ያልነበረም የሌለም የማይኖርም እንደሆነ ታሪክና ቅንነት በአስረጂነት ይቀርባል።

በሰሙንኛው ችግር ዙርያ መወጋገዝን እንደጊዜአዊ እሳት ማጥፊያ እንጂ እንደዘላቂ መፍትኼ ማየት ተገቢ አይመስለኝም። ይህን ያልተረዱና ዐርቀው ያላዩ ግን ለመቁረጥና ለመቆራረጥ እንቅልፍ ሲያጡ ማየት በእጅጉ ያሳምማል።

የከሰመውን ተሐድሶ ለመመለስ ከሚውተረተረው ፍኖተ ድድቅ ሩጫ (ድድቅ ያልታሰበ አደጋ ማለት ነው፤ ጽድቅ ብሎ መጥራት ስለማይገባ «ፍኖተ ጽድቅ« ነን ባዮችን ነው ፍኖተ ድድቅ ያልኩት) እና የመንበር ጥያቄ ሰበብ ሊከፋፍለን እንቅልፍ ከሚያጣ የጊዜው ከፋፋይ አጀንዳ ቤተክርስቲያንን ለመታደግ ዘመን መቅደም ዓለሙን መረዳት ቢቻል መልካም በመሆኑ የሕንድን የጭንቅ ዘመን መፍትሔ መመሪያና መማሪያ ብናደርገው።

የሕንድ ቤተክርስቲያን የወሰደችው ርምጃ ምን ነበር?
✥ °°°°°°°°°°🌈°°°°°°°°°°🌈°°°°°°°°°°° ✥

የሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ፺፩ኛ ወራሴ መንበር የሆኑት ቅዱስነታቸው አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ዲዲሞስ ቀዳማዊ በእርጅና እና ዘመን የዋጀ አገልግሎት በሚፈለገው መጠን በሚጠበቀው ደረጃ እንዲሠጥ በሚሉ አሳማኝ ምክንያቶች በፈቃዳቸው ሥልጣን ሲለቁ (abdication) ገና በ፴፮ ዓመታቸው ለጵጵስና ተመርጠው የነበሩትና ቀድሞውኑ ተተኪ ካቶሊኮስ የነበሩት ረዳት ፓትርያርክ ከ2010 ጀምሮ ቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማር ቶማ ጳውሎስ ካልዕ ተብለው በካቶሊኮስነት ተሹመው ቤተክርስቲያኗን ወደቀደመ ልዕልናዋ ለመመለስ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው በብዙ ደክመዋል ። ቅዱስነታቸው ከመንፈሳዊ ትምህርት ብቃት ጋር በሶሺዮሎጂና ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የሁለተኛ ድግሪ ባለቤት መሆናቸው ዓለሙን ለማወቅ ዘመን ለመቅደም ረድቷቸው እንደ 92ኛ የቶማስ መንበር ወራሽ ፣ 8ኛው የማላንካራ ቤተክርስቲያን ካቶሊኮስና 21ኛው የማላንካራ ሜትሮፖሊታን የነበሩት ታላቁ አርቆ አሳቢ ባስልዮስ ማርቶማ
ጳውሎስ በሳንባ ካንሰር ተጠቂነታቸው የሕክምና ክትትል ሲደረግላቸው ቆይቶ ለኮሮና ወረርሽኝ ተጋልጠው በህክምና ሲረዱ ቆይተው 12 July 2021 ማረፋቸው ይታወቃል። በረከታቸው ትደርብን! እግረ መንገድ ከታች የተያያዘውን የወንድማችን መምህር ታደሰ ወርቁን Tadesse Worku + የመንበረ ቅዱስ ቶማስ ትሩፋት + እንድታነቡ እጋብዛለሁ።

በዘር ኮታ በሚሠጥ ሹመት የሰማይ ሀገር ዜጎችን መጠበቅ እንዴት ይቻል ይሆን? የዘር ውክልና ያለው ዘረኛ እረኛስ ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ ዋጅቶ ለመንግሥቱ የመረጣቸውን ምእመናን መምራትና ማሰማራት እንዴት ይችል? አልተግባብቶም!

“አሁንም በምድር ሁሉ ላይ የሚጸናውን የጥፋት ትእዛዝ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰምቻለሁና እስራት እንዳይጸናባችሁ አታፊዙ።”【ኢሳ ፳፰፥፳፪】

ጊዜውን መቅደም ያልቻሉ ምናለ እንደ አረጋዊው ባስልዮስ ማርቶማ ዲዲሞስ በቃኝ ቢሉ …

እኔም አበቃሁ!

(በሱባዔው የደስታ ምልክቷን ጽዮን መቀነቷን ድንቅል ማርያም ሰበኗን ለሁላችን ትላክልን! )

☞ ሐምሌ ፳፱ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. ከቴዎድሮስ በለጠ ስቶኮልም ስዊዲን የተጻፈ 【ሀ-ግእዝ የገዳማት ቀን ጉባኤ】
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
እንተ በኅሊና እግዚአብሔር ተገብረት (2)
መንፈሳዊት ይእቲ ማርያም
በእግዚአብሔር ሐሳብ የተሠራች (2)
እመቤታችን መንፈሳዊት ( አዝ)

ምክንተ ድኅነት አንቺ በመሆንሽ
የሲኦል ደጆችን ታንቀጠቅጪያለሽ
በአንቺ የተደረገው ይህ ታላቅ ምሥጢፈር
አድርጎታልና ሰይጣንን እንዲያፍር

ስለሰዎች ፍቅር ልቦናሽ ያሰባል
ዐለምን ለማዳን አጅሽ ይዘረጋል
በሲኦል አንድ ሰው እንዳይቀር በስቃይ
ለምሕረት ይዘርጋ እጅሽ ወደሰማይ

የሲኦል እሳቱን ስቃዩን አያየሽ
ለፍጥረታት ሁሉ ድንግል ሆይ ታዝኛለሽ
በዓይነ ምሕረቱ እንዲያየን ክርስቶስ
ለምኝልን ማርያም ፍጥረት እንዲቀደስ

እንደሚነገረው በአበው አንደበት
እኛም እንደምናይ ስንኖር በህይወት
ወላዲተ አምላክ ሩህሩህ  ፍጥረት ናት
ምሕረት የምትለምን ዘወትር ሳትታክት
በአግዚአብሔር ሐሳብ የተሠራች (2)
እመቤታችን መንፈሳዊት

እንተ በኅሊና እግዚአብሔር ተገብረት (2)
መንፈሳዊት ይእቲ ማርያም
በእግዚአብሔር ሐሳብ የተሰራች (2)
እመቤታችን መንፈሳዊት

ሊቀ መዘምራን ይልማ ኃይሉ
Forwarded from ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - ‌🇴‌🇷‌🇹‌🇭‌🇴‌🇩‌🇴‌🇽 ‌🇹‌🇪‌🇼‌🇦‌🇭‌🇩‌🇴 (ተεพ๑δr๑ร (አግናጥዮስ) Ignatius Theophoros (Ἰγνάτιος Θεοφόρος))
2025/07/04 21:22:54
Back to Top
HTML Embed Code: