Telegram Web Link
Forwarded from ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - ‌🇴‌🇷‌🇹‌🇭‌🇴‌🇩‌🇴‌🇽 ‌🇹‌🇪‌🇼‌🇦‌🇭‌🇩‌🇴 (ተεพ๑δr๑ร (አግናጥዮስ) Ignatius Theophoros (Ἰγνάτιος Θεοφόρος))
#ከሰማይም_ከወረደ_በቀር_ወደ_ሰማይ_የወጣ_ማንም_የለም (ዮሐ. ፫፥፲፫)
·:···:···:···:···:···:···:···:···:···:···:···:··

ዕለቱ ሞት ለተፈረደበት የሰው ዘር ሕይወትን፣ ወደ መቃብር ለተጋዘው ዓለም ትንሣኤን የወለደች፤ የሕይወት እናቱ የትንሣኤም ወላዲቱ ፦ ድንግል ማርያም ሕንፃ ሕይወቷ የታደሰበት በትንሣኤ የከበረ ሥጋዋ ወደ ልጇ የፈለሰበት ቀን ነውና የትንሣኤ እና የዕርገቷ የፍልሰቷ ተዝካር ተሰኝቷል።

በዚህ ወቅት ለውሉደ ጥምቀት ምስማክ (መጠጊያ) ፣ በፍኖተ ጽድቅ ምሥጋር (መሻገሪያ) ፣ የመንግሥተ ሰማያቷ ታዕካ (ሰፊ አዳራሽ) እመቤታችን ቅድስት ድንግል ወላዲተ አምላክ ማርያም በፍልሰቷ መታሰቢያ በክርስቶስ አምሳል መነሣቷ፤ ብሎም ኀያልና ከኃሊ ማእምርና ጽኑዕ ወደ ሆነ ልጇ ቀኝ ማረጓን ሐዋርያዊት ቅድስት ቤተክርስቲያናችን አምና ልጆችዋን ታስተምራለች።

በየአዝማናቱ ከሚነሱ ሕጹጸ–ፍኖት፣ ዕልዋነ–ሃይማኖት ውስጥ የእመቤታችን መነሳት ብሎም ማረግ የማይዋጥላቸው መናፍቃን አሉ። እንዲያውም ሲሻቸው ርቱዕ የሆነውን ለመርታት ፣ ራትዓን የሆኑትን ለማምታታት ከቅዱስ መጽሐፍ ሳይቀር አስረጂ ይሆነናል የሚሉትን ስበው ያለአገባቡ ሳይገባቸው ጭምር ይጠቅሱታል፤ በተለይማ ጊዜው «አእምሯቸው የላላ፣ ምላሳቸው የሰላ» የገነኑበት የባለጊዜዎች ነውና የቃሉ ምስክር ሥራው ላልሆነ ነፍሰ ዐንካሳ ከመቼውም ይልቅ ብዙኀኑን ያለ–ተው–ባይ ለመንዳት ያመቸ ሆኗል።

በሥነ አመክንዮ (logic) ለመግባባት እንኳ እንደ ባለ አእምሮ ለሚያስብ የነገሮችን አለመኖር ለማስረዳት «አለ» የሚል መታጣቱ ሳይሆን «የለም» የሚለው ከአስረጂው ታማኝ ምንጭ መገኘቱ የሚያሳምን ይሆናል ፤ እንደዚሁ ሁሉ የነገሩ አናዎር (መኖር) ለማሳወቅ አለመኖሩን የሚያስረዳ መታጣቱ ሳይሆን ህሉናውን ገላጭ መገኘቱ በቂ ይሆናል፤ ነገር ግን መሸናነፍ እንጂ መተማመን እንደ ነውር በተቆጠረበት ትውልድ መኻል፤ ኹሉም ኹሉን አውቃለሁ ባይ ነውና የመጻሕፍትን መነሻ በአስረጂነት (Scriptural Root Evidence) አልያም ቀለል ባሉ ምስለታዊ እሰጣገባ (Simple Analogical Arguments) መናበብን አሻፈረኝ መግባባትንም እምቢኝ የሚል በመብዛቱ ጠያቂን ማስረዳት ቀርቶ ተጠያቂንም መርዳት ከብዷል፤

እግዚኦ! በአብዛኛው ዘንድ ርቱዕ ትምህርቷ እንደ ፈጠራ ወሬ (Hoax) ፣ ነገረ ምዕዳንዋ እንደ ዕለት ዜና (Newscast) መምህራኖቿም እንደ እንቶፈንቶ ጋዜጠኛ (Junket journalist) ለተቆጠሩባት እናት ቤተክርስቲያን "መጥኔ" ይስጥልን (ረዳኤ ወዐቃቤ ወመጽንዔ አምላኳ እርሱ ይሁናት)

ወደተነሳንበት እናምራ፤ ለርእሰ ጉዳያችን የበለጠ አስረጂ አድርገን የባህሪ ክብር ባለቤት ጌታችን ለኒቆዲሞሰ የነገረውን ሕያው ቃል በጥቂቱ በማብራራት እንጀምር፦

" ወአልቦ ዘዓርገ ውስተ ሰማይ ዘእንበለ ዘወረደ እምሰማይ ወልደ እጓለ እመሕያው ዘውእቱ ይነብር ውስተ ሰማይ … ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።” (ዮሐ ፫፥፲፫)

ይኼንን መልእክት ራሳቸውን የሚያመጻድቁ ፣ የቅዱሳንን ጸጋ የሚንቁ ፣ ክብራቸው ኀሳር ፣ ፍፃሜአቸው ሕርትምና የሆኑ መናፍቃን ለሰሙኑ የቤተክርስቲያን በዓል (የድንግል ተዝካረ ትንሣኤ እና ውስተ ሰማይ ዐራጊት መሆንዋን) ለማስተሐቀር ሲዋሱት ይደመጣል፤ "ሌባ ለአመሉ ዳቦ ይልሳል ፣ መናፍቅም ለወጉ ጥቅስ ይጠቅሳል" ሆኖ እንጂ የመጽሐፉስ ቃል የበለጠ የድንግል እናቱን ክብር ልጇ ያስተማረበት ነው!

ይኽ በዮሐንስ ወንጌል ሦስተኛው ምዕራፍ ላይ ለኒቆዲሞስ የተሰጠው ትምህርት አውዱ ስለ ሰው ልጆች ዳግም ልደት የሚያስረዳ መሆኑን እንገነዘባለን፤ ዳግም በጥምቀት የሚገኘውን የውልድና ሀብት ሲሰማ "እንዴት ሊሆን ይችላል?" በሚል ላቀረበው ጥያቄ ነበር ክርስቶስ “ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?” በሚል መነሻ «ምድራዊው ሰው ከሰማይ አባት በጸጋ ልጅነት ይከብራል ያልኩትን ሊረዳ ላልተቻለው፣ ሰማያዊው መለኮት በቅድስት ድንግል ሥጋ መገለጡ እንዴት ይገባዋል? » ያለው! ይኽን አስከትሎ "ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው" በሚል ነገሩን ያስረግጥለታል!

————————————————————

ከዚኽ መነሻ ሦስት ነገሮች እንጠይቃለን

፩) ትምህርቱ የተሰጠበት ጊዜ ጌታችን ገና ሳይሰቀል፣ ሳይሞትና ሳይነሳ ብሎም ወደ ሰማየ ሰማያት ከማረጉ በፊት ሆኖ ሳለ ድርጊቱ ቀድሞ የተፈፀመ እንደሆነ በሚመስል «ወደሰማይ የወጣ (ዘዓርገ) ማንም የለም» በሚል መገለጡ ስለምን ነው?

፪) "ወደሰማይ የወጣ ማንም የለም" የሚለው "ወደ ሰማይ የሚወጣ ማንም የለም" ከሚለው ሐሳብ ጋር ያለው ልዩነት ምንድር ነው?

፫) የእርሷን (የእናቱን) ትንሣኤ እና ዕርገት ከትንሣኤ ዘጉባኤ አስቀድሞ ስለምን አደረገው?

————————————————————

⇨ እኒኽን መነሻ በማድረግ የዕርገቷን ምሥጢር ሊቃውንቱ በመጻሕፍት የሚያስረዱንን እናወሳለን፤
እነሆ ለለባውያንና ለንቁሃን በቅድሚያ ፦ ጌታችን ለምን ተነሳ ለምንስ ዐረገ?

የጌታችን ትንሣኤና ዕርገቱስ ከሞት በኋላ ሕይወት ከመቃብር በኋላ ትንሳኤ ሊኖራቸው በፍኖተ መከራው ለሚሳተፉ ውሉደ ጥምቀት ልጆቹ ያላቸውን ተስፋ የሚቀበሉትን ክብር የሚያሳይ ነው! “ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለ” ይላልና (ሮሜ ፮፥፭)
መጽሐፈ ቅዳሴ እና መጽሐፈ ግንዘትም "ዐርገ ከመ ያለቡ ዕርገተ ጻድቃን… የጻድቃኑን ዕርገት ያስረዳን ዘንድ ዐረገ" ይለናል፤ ስለዚኽ ነው መጽሐፉ "የሚነሳና የሚያርግ የለም" አይልም አላለምም የምንለው! ሐዋርያቱ ሳይቀር በፍፃሜው "በደመና እንነጠቃለን ፤ ሁል ጊዜ ከጌታችን ጋር እንሆናለን" ብለው ሲመሰክሩ ስለዕርገታቸው ሰምተናል (፩ተሰ. ፬፥፲፯)

⇨ ስለዚኽ ቃሉ ለምሥጢራዊው መውጣቱ ፣ በተዋሕዶ ለተገኘ የሥጋ ምልዓቱ፣ «ዕርገቱ» በጽንሰት ለተከናወነለት ትስብእቱ አስረጂ ሆኖ የተነገረ መሆኑን ልብ ይሏል!

ስለተገለጠው ረቂቅ ምሥጢር ለመረዳት አስቀድሞ ስለጥምቀት (ስለ «ምድራዊት» ልደት) ሊገባን ይገባል፤ ይኽ ምድራዊው ሳይሠርፀን የሰማዩን መመርመር እንደምን ይቻለናል? ለዚህ ነው ከዚሁ ቀድሞ ባለቤቱ ክርስቶስ እንዲህ ያለው

☞ “ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?” (ዮሐ ፫፥፲፪)

በቅድሚያ ጥምቀትንስ ለምን «ምድራዊት» ይላታል የሚል ደግሞ ካለ፤

ሊቁ እንዲህ ይላል "እስመ ዘይቤ በእንቲአሃ ምድራዊት ይእቲ እስመ ተፈጸመት እምድር ወእፎመ እንከ የዓቢ ወይፈደፍድ ከመ ትእመኑኒ እም ከሰትኩ ለክሙ መንግሥትየ ወልደትየ እም አብ እምቅድመ ኩሉ ዓለም … ስለእርስዋም (ስለጥምቀት) ምድራዊት ናት ማለቱ ከምድር (በምድር እያሉ) ትፈጸማለችና፤ እንግዲህ ከእርሷ መንግሥቴንና ከኹሉ አስቀድሞ ቅድመ ዓለም ከአባቴ መወለዴ እንደምን እጅጉን አይበልጥ"

በዚኽ ልዩ ተዋሕዶ መለኮት በዚኽ ዓለም በደኃራዊ ሥጋ ከድንግል እንደተወለደ ፣ ሥጋም ጥንታዊ ቀዳማዊ ለመሰኘት በመለኮት ከአብ ተወለዶ ወልደ አብ ወልደ ማርያም አልፋ ወኦሜጋ መባልን ገንዘብ አደረገ።

ታላቁም ተርጓሚ (ወመተርጎምሰ ዘየአቢ) እንዲህ ሲል ያስረዳል የ
Forwarded from ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - ‌🇴‌🇷‌🇹‌🇭‌🇴‌🇩‌🇴‌🇽 ‌🇹‌🇪‌🇼‌🇦‌🇭‌🇩‌🇴 (ተεพ๑δr๑ร (አግናጥዮስ) Ignatius Theophoros (Ἰγνάτιος Θεοφόρος))
ቃል መጨመር የአምላክ በሥጋ ማደር በፍጹም ተዋሕዶ እንጂ ቱስሕት እና ኅድረት አይደለምና መለኮትም ከአባቱ ሳይለይ በማኅጸን አድሯል፤ "ወአኮ በፈሊስ እምውስተ መካን…ከቦታ ወደ ቦታ በመሻገር አይደለም" ወደዓለም ሲመጣ ከሰማይ ዙፋኑ ሳይታጣ፣ ከመለኮታዊ ክብሩ ሳይወጣ ነውና ከድንግል እናቱ የነሳውን የተዋሐደውን ሥጋ ፍጹም አምላክና በሰማይ መንግሥትም ያለ ያደረገው በእርሷው ማኅጸን እያለ ነው! ስለዚኽ ያረገው ሲጸነስ ነው ያሰኛል!

በቁሳዊው እሳቤስ አንድን አካል "ወርዷል ግን ከወረደበት ሥፍራም አለ" የሚለውን መረዳት እንደምን ይቻላል? [It is not possible by the laws of bodies for the same object to remain and to descend.]

ለዚኽም ነው በሰማያት ያለውን "የሰው ልጅ"ም እያለ የጠራው። አፈወርቅ የተሰኘው ታላቁ መምህር ቅዱስ ዮሐንስ «Son of Man Stands for the Whole Person» የሰው ልጅ የሚለውን በጠቅላላው ለመለኮትና ትስብእት ተናገረው በሚል አውድ እንዲህ ያስረዳል፦

☞ "And in this place he does not refer only to the flesh as “Son of man” but now names, so to speak, his entire self from the inferior substance. Indeed, he often likes to do this, referring to his whole person from either his divinity or his humanity ⇝ በዚኽ ሥፍራ ከሰማይ የወረደ ቃልነቱም ከምድራዊ ሰውነቱ ጋር እንጂ ሥጋን ብቻ የሰው ልጅ ብሎ አልጠራውም ! ስለዚኽም በእውነት ይኽን አብዝቶ ማስገንዘብ ሲሻ ከመለኮትነቱ አልያም ከትስብእትነቱ ለይቶ «ሥግው ቃልነቱን» የሰው ልጅ ሲል ይገልጣል" (Chrysostom: Homilies on the Gospel of John 27.1.4, NPNF 1 14:94)

ስለዚኽ ክርስቶስማ ምን በክበበ ትስብእት ቢወሰን በሁሉ ግን አለ [Christ Is Everywhere] የምእመናን አባት የቁስጠንጥንያው ሊቀ ጳጳሳት ሊቁ አፈወርቅ መልሶ እንዲህ ይላል፤

☞ "See how even what appears very exalted is utterly unworthy of his greatness? For he is not in heaven only but everywhere, and he fills all things. But here he still speaks according to the infirmity of his hearer in the hope that he can lead him up little by little ⇝ እስኪ ይኽን ተመልከት ታላቅ ክብሩ ምን እና እንዴት እንደሆነ የቱንም ያኽል በቃል ቢነገር ፣ ለማብራራት እጅጉን የሚያዳግር "ኢይትነገር አላ ይትነከር" የሚሰኝ መሆኑን፤ «በተለየ አካሉ ከሰማይ ወረደ ወደዚህ ዓለም መጣ» ያለውን መልሶ በሁሉ ያለ እና ሁሉን የመላ ነው ይለዋል፤ ታዲያ በዚህ ስፍራ ግን የሰማኢውን (የኒቆዲሞስን) የመረዳት አቅም ድኩም እና ጽኑስ መሆን ተመልክቶ ጥቂት በጥቂቱ ያጎለብተው ዘንድ እንዲህ ተናገረ" [Homilies on the Gospel of John 27.1 NPNF 1 14:94]

በዚኽ መነሻ ከልዕልና ዙፋኑ ወደ ዐለም ለወረደው ቃል ልዕልት ላዕለ ኩሉ ተሰኝታ የከበረ ዙፋን የሆነችውን ከሳሽ ዲያቢሎስን ከሰው የምታርቅ ሰውን ከመሓሪ አምላኩ የምታስታርቅ የአዛኝቷን ድንግል ማሕጸን ሰማይ እንለዋለንና።

ሰማይስ መባል እንደምን ተገባት? የሚል ቢኖር እርሷ ሰማይን ብትበልጥ እንጂ ሰማይ መባሏስ ምን ያስገርማል፤ ሊቃውንትማ የሚደነቁት "ሰማይ ወምድር ዘኢያገምሮ እፎ እንጋ ማኅፀነ ድንግል ፆሮ?" እያሉ ነው (ሰማይና ምድር የማይወስኑትን የድንግሊቱ ማኅፀን እንደምን ቻለው?) እርስዋማ የሕይወት ፍሬን ያስገኘች በምድር የተተከለች ቅርንጫፎቿ እስከ ሰማይ የደረሱ የወይን ሐረግ "እንተ በምድር ሥረዊሃ ወበሰማይ እዕፁቂሃ" ናት፤ በላይዋ ተቀምጦ ንጉሡ የተገለጠባት መላእክቱ ለተልእኮ የሚፋጠኑባት ከምድር እስከ ሰማይ ደርሳ የተተከለች መሠላል "ሰዋስው እምድር ዘይበጽእ እስከ ሰማይ" ናት፤ ከሰማይ ሲወርድ ዙፋን ከምድር ሲያርግ መሠላል ያደረጋት ሰዎችን ሲያይ መስታወቱ ሰዎች እርሱን ሲያዩት ድልድይ የምትሰኝ "ተንከተም ለዕርገት ውስተ ሰማይ" እመቤታችን ናት!

ከምን ተነስተን ሰማይ እንዳልናት እዩ፦

✧ ሰማይኑ ንብለኪ ፀሐየ ጽድቅ ወልድኪ ሐዋርያቲሁ ከዋክብትኪ ወመዋርስቲሁ ለበኵርኪ ⇝ ሰማይን እንበልሽ? የእውነት ፀሐይ ነውና ልጅሽ የበኩርሽ ወራሾች የሆኑት ከዋክብቶችሽ ናቸው ሐዋርያት!

​✧ ትመስሊ ሰማየ ወትወልዲ ፀሐየ ወታገምሪ አዶናየ
⇝ ሰማይን ትመስያለሽ ፀሐይን ትወልጃለሽ አዶናይን ትወስኛለሽ(ትችያለሽ) !

✧ አባ ጊዮርጊስም በሌሊቱ ሰዓታት " ገነይነ ለኪ ኦ ወለተ ዳዊት ክብረ ኩሉ ዓለም ዳግሚት አርያም እንዘ ድንግል ወእም … ገነይነ ለኪ ኦ ወለተ ዳዊት ዳግሚት ሰማይ ሙጻኣ ፀሐይ ወላዲቱ ለአዶናይ"

✧ ወኵሉ ዘተጽሕፈ ለተግሣጸ ዚአነ ትጽሕፈ መፍትውኪ እንከ አኃውየ ንንግር ወንዜኑ በእንተ ማርያም ድንግልኒ ሰማይኒ ይእቲ ምዕናም ግሩም ዘበእንቲሃ ተአንመ በሥጋ ዕፁብ፤

✧ አመ በከዩ ብካየ ረከቡ ወለተ ዘታሥተሰሪ ጌጋየ ለወንጌላውያን ኵልነ ዘኮነተነ ምጕያየ ኢያቄም ወሐና ወለዱ ሰማየ ሰማዮሙኒ አሥረቀት ፀሐየ ምሥራቀ ምሥራቃት ሙፃአ ፀሐይ እግዝእትየ ዘመና ሙዳይ ተወልደት ዮም ዳግሚት ሰማይ ፤

✧ ከጸሎተ ኪዳኑም መቅድም ላይ የዘወትር ሰላም እንዲህ ይላል ፦ "ይትፌሣሕ ልብኪ ኦ ድንግል ወይትሌዓል ቀርንኪ በክብር ሰማይ ዳግማት ብኪ ድኅነ ዓለም ወበወልድኪ ኮነ ሰላም ⇝ በአንቺ ዓለሙ የዳነ በልጅሽ ሰላም የሆነ ሁለተኛዋ ሰማይ ድንግል ሆይ ልብሽ ደስ ይበለው ቀንድሽም በክብር ከፍ ከፍ ይበል"

✧ ሊቁ የማሕሌት ምንጭ ቅዱስ ያሬድ የመዳን ቅጥር የምስጋና በር የሆነች የእግዚአብሔር ወልድ እናትን ባመሰገነበት አንቀጸ ብርሃን እንዲህ አላት " አንቲ ውእቱ ህየንተ አርያም ዘበሰማያት ዘኮንኪ አርያመ በዲበ ምድር ⇝ በምድር ላይ ከፍተኛ አርያምን የሆንሽ ከሰማያት በላይ ያለ የአርያም የልዑል ሥፍራ ምትክ አንቺ ነሽ"

⇨ ስለዚኽ እርሷን ሰማይ ካላት ከሰማይ ወርዶ ወደ ሰማይ–ዳግሚት ወደ አርያም–ካልኢት ወደ እርሷ ከወጣው ልጇ በቀር በእርሷ ያደረ ሌላ ማንም የለምና "ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም" ይላታል! በዚኽም እርሷ እርሱን ብቻ በድንግልና ወልዳ የእርሱ ብቻ እናት ተሰኝታ በዘለዓለማዊ ድንግልና ጸንታ መኖርዋን እንረዳል፤

ለአንክሮ ፦ ልጇ እንበለ ዘርእ ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና ቢወለድ ፣ እናቱ እንበለ ተፈትሖ ጸንታ ታትማ ኖራለች!

ለፍጽምናም ፦ ልጇ አምላክ ወሰብእ ለመባሉ ድንበር እንደሌለው እናቱም ድንግል ወእም ለመባሏ ወሰን የላትም!

ታዲያ «በውስጥ የብፅዓት ልጅ መሆኗ እንደመላእክት ላለ ኑሮ ፣ በአፍኣ ለጠባቂ መታጨቷ ለመንፈሳዊ ተፍኅሮ» ነው!

✧ በዘር በሩካቤ መጽነስ ፣ በእደ ብእሲ መዳሰስ ፈጽሞ የሌለባት ናት ደገኛዋ እናት በትንቢት በታጠረ ፣ በብፅዓት በተቀጠረ ዐውደ ማሕፀኗ ዕሩቅ ብእሲ አያድርም፤

✧ ሠዓሌ ሕፃናት በተሣለበት ሰሌዳዋ ዘርዓ ብእሲ ቀለም ሆኖ ሊሳልበት አይቃጣም፤

✧ የሰውን ልጅ በቅዱሳን እጆቹ የቀረፀው ልዑል ፈጣሪ በተቀረፀበት ሰፋድል ፍጡሩ ያን የከበረ የሥጋ ክርታስ በቅቶ ሊቀረጽበት አይቻለውም!

እስኪ ልብ አድርጉ
Forwarded from ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - ‌🇴‌🇷‌🇹‌🇭‌🇴‌🇩‌🇴‌🇽 ‌🇹‌🇪‌🇼‌🇦‌🇭‌🇩‌🇴 (ተεพ๑δr๑ร (አግናጥዮስ) Ignatius Theophoros (Ἰγνάτιος Θεοφόρος))
እንኳን በአምላክ መጾር «በጳጳስ መንበር ቄስ ፣ በንጉሥ ዙፋን ራስ» ደፍሮ እንደማይቀመጥበት የእርሱንም ምዕራፈ ክብር ማንም አይጋራውም።

"ወይከውን ዘዚአሁ ምዕራፈ ክብር … ማረፊያውም የተከበረ ይሆናል።” [ኢሳ ፲፩፥፲]

የተመረጠው ፃድቅ ዮሴፍ ተከታይ ሞግዚቷ መንፈሳዊ አባቷ እየሆነ ፦ አማናዊት መቅደስ እናቱን ፣ ቅድስተ ቅዱሳን ትስብእቱን ሐዲስ ካህን ሆኖ ያገለገለ አረጋዊ ነው! እርሱ ምንም እንኳ በመጀመርያዋ መጽሐፍ (ብእሲቱ) በኩል ልጆች ማንበብ የሚያውቅ ቢሆንም የታተመችውን መጽሐፍ (እመ አምላክ ድንግልን) ግን በግብር አልደረሰባትምና ከመጠበቅ ውጪ እርሷን ማንበብ አይቻለኝም አለ!

“ ማንበብንም ለሚያውቅ፦ ይህን አንብብ ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ፦ ታትሞአልና አልችልም ይላቸዋል፤” [ኢሳ ፳፱፥፲፩]

ወደዓለም የመጣውን በኩር በሥጋ ያሳየች የበኩር እናት ተሰኘች እርሱም የበኩር ልጇ ተብሎ ተከታይ እንዳይኖረው ወልዳ ዘበኩር ተብሎ ተጠርቷል!

ይኽን ካልን ወደ ማሕፀኗ መውጣቱን ፣ በሥጋ እናቱ በምትሆን አርያም ዙፋን ማደሩን በተዋሕዶ አንድነት ምሥጢራዊ ዕርገት ይዘን ወደሰማይ ማረግ ካልነው ኋላ በአርባኛው ቀን በመርቀቅ ሳይሆን በመራቅ ከቅዱሳን ሐዋርያቱ ተለይቶ ወደላይ ሲወጣ ተመለከትንና ይኽንን (በረቀቀው ጽንሰት ስለተከወነ ዕርገት) በትህትና ያንን (በክብር ማረግ በተዋህዶ አካል ወደ ላይ መውጣቱን ) በልዕልና አልነው።
ሐዋርያው ያን በልዕልና የተፈፀመ ከትህትናው ሲለይ "ወአርገ በስብሐት ⇝ በክብር ያረገ ” (፩ኛ ጢሞ ፫፥፲፮) ሲለው ፤ ዳዊት ሁለቱን ሰማይ አካቶ ይኽን ሰማይ ያንን ከሰማያት በላይ ያለ ሰማይ ብሎ "ዘዓርገ ውስተ ሰማየ ሰማይ ዘመንገለ ጽባሕ " በማለት ገለጠው፤
↳ “በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ለወጣ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ” (መዝ. ፷፰፥፴፫)

በቅዱስ ኤጲፋንዮስ ቅዳሴ "በይእቲ ሥጋ ምስለ ኃይለ መለኮት ውስተ ሰማያት ዐርገ ኀበ ዘትካት ህላዌሁ ⇝ ከእናቱ በነሳው በዚኽ ሥጋ ከመለኮቱ ኃይል ጋር ወደ ቀደመ መኖርያው ወደ ሰማይ ዐረገ" እንዲል፤

————————————————————
ታቦተ መንፈስ ቅዱስ እመቤታችንን ስለምን ቀድሞ አስነሳት? ————————————————————

በፍለሰታው ሱባዕያት በሊቃውንቱ ቅዳሴ ማርያም ሲተረጎምልን እንደምንሰማው "ትምክሕቶሙ ለወራዙት ወደናግል ወመነኮሳት እለ ይተግሁ ውስተ አናቅጺሃ መዓልተ ወሌሊተ … በእርስዋ ደጃፍ (በራፍ) ሌሊትና ቀን ደጅ ለሚጠኑ ወጣቶች ደናግላንና መነኮሳት ትምክሕት ናት" ይላል ሊቁ አባ ሕርያቆስ።

በደጃፎችዋ በሚለው በሕዋሳቶቿ ለሚማጸኑ ትምክሕት ናት ይላል፤ ሕዋሳቶችዋን በሚያነሳ የሰውነት አባላቶቿን በሚያወሳ የመልክ ሰላምታ ለሚያወድሳት ትምክሕት ናት! ለምን? ለእርሱ ማደርያነት የተገቡ ናቸውና ለዘልዓለም ከብረው የሚኖሩ፤ ከፍጥረት ኹሉ ቀድመው ፈጣሪን በከዊን ያወቁና ፈጣሪን በግዘፍ ለፍጥረት ያሳወቁ ደጆች ፦ የተሸከመውን ማሕፀን፣ የጠባውን አጥባት፣ ያዘለውን ዘባን፣ ያቀፈውን እራኅ፣ በፈጣሪ የተሳመ መልታሕት… ከሌሎች ፍጡራን የአካል አባላት እና የሰውነት ሕዋሳት አብልጦ ይወዳቸዋል።

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት መዓዛ መለኮቱ የማይለያትን የሽቱ ሙዳይ “ያበድሮን እግዚአብሔር ለአናቅጸ ጽዮን ⇝ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች አብልጦ ይወድዳቸዋል።” እንዳለ [መዝ ፹፮ (፹፯)፥፪] አብልጦ ይወዳቸዋልና እንደፍጡሩ ለመፍረስ ለመበስበስ አሳልፎ አልሰጠውም!

በእንዚናዙኑ ሊቅ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ቅዳሴ ላይ "ለብሰ ሥጋ ዘይማስን ወረሰዮ ዘኢይማስን" እንደተባለ፤ ከሚፈርሰው ከእኛ ሰውነት የማይፈርሰውን ሕያው አምላክ ለማስገኘት የተመረጠችው የአብ መርዓት፣ የወልድ ወላዲት የመንፈስ ቅዱስ ታቦት የደጆችዋ መቆለፊያ በመቃብር መጥፋት በእሳትም መቃጠል ሳያገኛቸው ጸንተው ኖረዋል፤

“ጽዮንም ሆይ፥ ለአምላክሽ እልል በዪ፤ የደጆችሽን መወርወሪያ አጽንቶአልና " እንዲል [መዝ ፻፵፯፥፲፫]

ፀሐይን ያሠረቀች ዳግሚት ሰማይ፣ እግዚአብሔርን የወለደች እመ አዶናይ ፣ በሥጋና በኅሊና ዘልዓለም ድንግል የሆነች እግዝእትነ ማርያም፦
† በእነታውፋንያ ቁጣ የመጡ አይሁድ ሥጋዋን ለማቃጠል ያሰቡበት ምክር ስለምን ፈረሰ?
† በእሳት ያልጠፋውን ሥጋ "ወኢይገድፍ ምዕቅብናየ ⇝ አደራዬንማ አልተዋትም" ሲል ቅዱስ ዮሐንስ በንጽሕና በእጸ ሕይወት ሥር ሲያገለግላት መቆየቱ ለምነው?
ቀድሞ እሳት ያላቃጠለው ፣ ኋላም አፈር ያልበላውማ ስለሥጋዋ ክብር ነው እንጂ! ተረድተነውማ ቢሆን «ተቀብራ አልተነሳችም» ማለት "ወኢአማሰነ በልደቱ" እንዲል በልደቱ ያልለወጠውን የማደርያውን ክብር በሞት መፍረስና በመቃብር መበስበስ አግኝቶታል፤ አፈር ለውጦ አጥፍቶታል ወደማለት ያደርሳል! ላቲ ይደሉ ክብር ወስብሀት ወለወልዳ አምልኮ ወስግደት።

"ወይከውን ዘዚአሁ ምዕራፈ ክብር … ማረፊያውም የተከበረ ይሆናል።” [ኢሳ ፲፩፥፲]

————————————————————
☞ በቴዎድሮስ በለጠ ◆ ከአርባምንጭ ዚጊቲ አቦ ("#ዝግሕት_ይእቲ") ⇨ [ ነሐሴ ኪዳነ ምሕረት ፳፻፲፩ ዓ.ም ]
————————————————————
Forwarded from ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - ‌🇴‌🇷‌🇹‌🇭‌🇴‌🇩‌🇴‌🇽 ‌🇹‌🇪‌🇼‌🇦‌🇭‌🇩‌🇴 (ተεพ๑δr๑ร (አግናጥዮስ) Ignatius Theophoros (Ἰγνάτιος Θεοφόρος))
‹‹አዲስ ዓመት መልካሙን የምንሰራበት ይሁንልን!››


:
☞ዘመናትን የሚያቀያይርና አዲስ ዓመትን የሚሰጠን እርሱ
ፈጣሪ ነው።
:
ይህንን የፈጣሪን ምህረትና ቸርነት የምናስብ ስንቶቻችን
ነን?
:
ሰው ደግሞ ተጨማሪ አዲስ ዓመትና እድሜ ካልተሰጠው
ምንም ማድረግ አይችልም፡፡
:
ፈጣሪ እንድንኖር ካልፈቀደልን አዲሱን ዓመት ካልሰጠን
ምንም ነገር ማድረግ አንችልም፡፡
:
# ሌላው ቀርቶ፦

➊.ወጥተን→የምንገባው፣
:
➋.ተቀምጠን→የምንነሣው፣
:
➌.ተምረን ለውጤት→የምንበቃው፣
:
➍.ሠርተን→የምናገኘው፣
:
➎.ነግደን→የምናተርፈው፣
:
➏.ወልደን→የምንስመው፣
:
➐.ለመጪው ዓመት ብለን እቅድ→የምናቅደው ፈጣሪ እንደ
ቸርነቱ ወደ አዲሱ ዓመት እንድንሸጋገር ሲፈቅድልን ነው፡፡
:
√ብዙ ሰዎች ግን የፈጣሪን ቸርነት ረስተዋል፡፡
:
√አዲስ ዘመን ሲሰጠን ዋጋ የሚከፈልበት ቢሆን ኖሮ ዋጋውን
ማን ይችለው ነበር?
:
√ግን ፈጣሪ አዲስ ዓመት የሰጠን ያለዋጋ በነፃ ነው።

√ለምንኖርበት ዕድሜ ለሰጠን ተጨማሪ ዓመት የጠየቀን ዋጋ
የለም፡፡
:
√ታዲያ ጊዜ የሰጠን ፈጣሪ ደግሞ ጊዜ እንድንሰጠው
እንድናመሰግነው ይፈልጋል።
:
❀︵♡︵♔︵♡︵♔︵♡︵♔︵♡︵❀
:
# አዎን ወዳጆቼ፥

☞አንዳንድ ሰዎች እንዲኖሩ፣ እንዲወጡና እንዲወርዱ አዲስ
ዓመትና ጊዜ ፈጣሪ ሰጥቷቸው ሳለ አዲስ ዓመት ለሰጣቸው
ለፈጣሪ ግን ጊዜ መስጠትና ማመስገን ተስኗቸው
ይስተዋላሉ፡፡
:
♡ይህቺን ቀን አስበው እዚህች ቀን ላይ፣ ለዚህች ዓዲስ
ዓመት ያልደረሱ ብዙ ሰዎች አሉ።

♡አንተ እኔ ሁላችንም ግን ደርሰናልና እንደ ቸርነቱና ምህረቱ
ለዚህ ላደረሰን አምላካችን እንዲህ እያልን እንፀልይ፦

➊.አምላካችን ሆይ፥ አዲሱን ዓመት ስለሰጠኸን
እናመሰግናሀለን።
:
➋.አምላካችን ሆይ፥ ከዚህ በኋላ የሚኖረን ቀሪ እድሜ
በፊትህ ያማረ ይሁንልን፡፡
:
➌.አምላካችን ሆይ፥ እድሜና ዘመናችን በቤትህ ይለቅ፡፡
:
ማለዳ ማለዳ በአዲስ ምስጋና፣
:
በአዲስ ዝማሬ፣
:
በአዲስ ሽብሸባ፣
:
በአዲስ ቅኔ፣
:
በአዲስ እልልታ ይህ በረከት የሆነው እድሜና ዘመናችን
በቤትህ ይለቅ፡፡

➍.አምላካችን ሆይ፥ ሳናመሰግንህ ላለፉት የምህረት
አመታት ሁሉ ዛሬ ይቅር በለን፡፡
:
➎.አምላካችን ሆይ፥ የሚከፋፍለን የሚያለያዬንን የጥል፤
የክርክር፤ የዘረኝነት ግድግዳ አንተ አፍርስልን።
:
➏.አምላካችን ሆይ፥ በአዲሱ ዓመት ፍቅርና አንድነትን
ስጠን።
:
➐.አምላካችን ሆይ፥ ሐገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ባርክ።
:
➑.አምላካችን ሆይ፥ በሰጠኸንም እንደ ቸርነትህ
በጨመርክልን አዲስ ዓመት መልካሙን እንድንሰራበት አንተ
ይርዳን! # ለዘላለሙ አሜን!
:
♡እስኪ ተመስገን በሉት። ተመስገንንንንንንንንንንንንንንንን
:
❀︵♡︵♔︵♡︵♔︵♡︵♔︵♡︵❀
:
# መጪው አዲስ ዓመት፦

➊.ሀጥያትን→በጽድቅ፣

➋.አለመጸለይን→በመጸለይ፣

➌.ስጋዊነትን→በመንፈሳዊነት፣

➍.አለማገልገልን→በማገልገል፣

➎.ድህነትን→በመስራት፣
:
➏.አለማንበብን→በማንበብ፣
:
➐.አለማወቅን→በመማር፣
:
➑.ጥላቻን→በፍቅር፣
:
➒.ክፉን→በመልካም፣
:
➓.ንፉግነትን→ በመስጠት፣ የምንከርመበትና ፍቅር የበዛበት
ብሩህ ዘመን ይሁንልን!
:
[☞መልካም አዲስ ዓመት☜]
:
«ሼር በማድረግ ለወዳጆ ያካፍሉ»
:
"ሰላማችሁ ይብዛ"
:
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
ባሕረ ሐሳብ በበኲረ ፍሥሐ ቀሲስ ዶ/ር ኃይለ ኢየሱስ አስናቀ

ቀሲስ ዶ/ር ኃይለ ኢየሱስ በአኹኑ ወቅት በሀገረ አሜሪካ በሚገኘው ሲንክሌር ብሮድካስት ግሩፕ ( Sinclair Broadcast Group )
የኮምፒውተር ሶፍትዌር ኢንጂነር ሲሆኑ፤ ቀደም ብሎም በዝነኛው ዲዝኒ ( Disney ) የተንቀሳቃሽ ስልኮች አፕሊኬሽን መርማሪ፣ በሌላው ግዙፍ የኮምፒውተር ተቋም ማይክሮሶፍት ( Microsoft)
የሶፍትዌር ምርምር ክፍል ባልደረባ እና በ ADSWE ዲዛይን ኢንጂነር በመሆን የሰሩ በዓለማዊውም በመንፈሳዊውም በኹለት በኩል የተሳሉ ሰይፍ ናቸው።

በሀገር ቤት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሩቁ ቀሲስ ዶ/ር ኃይለ ኢየሱስ ከኮምፒውተር መሃንዲስነታቸው በተጨማሪ በሲያትል በሚገኙ አድባራት በቅዳሴ፣ በስብከተ ወንጌል፣ በመጻሕፍት ትርጓሜና በሰንበት ትምሕርት ቤቶች መምህርነት በማገልገል ላይ የሚገኙ ካህን ናቸው።

የአገልግሎት ዘመናቸውን ያርዝምልን

©ዲያቆን ጴጥሮስ አሸናፊ ከበደ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - ‌🇴‌🇷‌🇹‌🇭‌🇴‌🇩‌🇴‌🇽 ‌🇹‌🇪‌🇼‌🇦‌🇭‌🇩‌🇴
Photo
+ በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ +

ይድረስ ለተከፋኸው ወንድሜ
መኖር ለደከመህ ፣ ሕይወት ለታከተህ ፣ የሚሰማህ ላጣኸው ፣ የሚረዳህ ሰው ላላገኘኸው መከረኛው ወዳጄ!

ከሞት ውጪ ሌላ መፍትሔ አልታይ ካለህ የአንተ ቢጤ መከረኞቹ ጳውሎስና ሲላስ እስር ቤት ውስጥ ሆነው እንዲህ ይሉሃል::

"በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ" ሐዋ. 16:28

አውቃለሁ ዙሪያው ገደል ሆኖብሃል:: ምነው ባልተፈጠርሁ እስክትል ድረስ ተጨንቀሃል::
ግን ይህ ስሜት በአንተ አልተጀመረም:: ሰው ሆኖ ተፈጥሮ ኑሮ ያልመረረው ማን አለ? መሞት ያልተመኘስ ማን አለ?

ሞት ያማረህ አንተን ብቻ መሰለህ?

" ስለ ምን ከማኅፀን አወጣኸኝ? ዓይን ሳያየኝ ምነው በሞትሁ" ያለውን ጻድቅ ኢዮብ አልሰማህም? (ኢዮ. 10:18)

"ከአባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ" ብሎ እንዲሞት የለመነውን ኤልያስን አላየኸውም? 1ነገሥ. 19:4

ዮናስንስ "አሁንም፥ አቤቱ፥ ከሕይወት ሞት ይሻለኛልና እባክህ፥ ነፍሴን ከእኔ ውሰድ፡ አለው" ሲል አልሰማኸውም? (ዮናስ 4:3)

ወንድሜ እመነኝ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን መኖር ያላስጠላው ሰው በታሪክ ፈልገህ አታገኝም::

ሞት ሞት የሸተተው ልቡ የተሰበረ ብዙ ነው:: አንተ ላይ ብቻ የደረሰ ልዩ ፈተና የለም:: "ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል" ይላል መጽሐፍ:: 1ኛ ቆሮ. 10:13

ምናልባት የልብህን መሰበር የኀዘንህን ጥልቀት አይቶ ምቹ ጊዜ አገኘሁ ብሎ ራስህን እንድትጎዳ ሰይጣን ሊገፋፋህ ይችላል:: እንዴት እንዲህ ዓይነት ሃሳብ በልቤ ሊመጣ ቻለ ብለህ አትረበሽ:: ሰይጣን ይህንን ክፉ ሃሳብ ላንተ ብቻ ሳይሆን ለክርስቶስም አቅርቦለታል::

"የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር" ብሎ ክርስቶስን እንኳን [ማንነቱን ሳያውቅ] ራሱን እንዲወረውር ሊገፋፋው የሞከረ ደፋር ነው:: የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ሰው ግን ራሱን አይጎዳም:: "ጌታ አምላክህን አትፈታተነው" "ሒድ አንተ ሰይጣን" ብለህ ሰይጣንን ገሠፀው::

ሰይጣን ክርስቶስን "ከሕንፃ ጫፍ በመወርወር የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን አሳይ" ሲለው ክርስቶስ ሰይጣንን ሒድልኝ ብሎ በመገሠጹ በክብር ወደ ሰማይ ዐርጎ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ::
ወንድሜ ሆይ አንተም ሰይጣንን አትስማው ሃሳቡ ራስህን ጎድተህ ከፈጣሪህ እንድትጣላ ሊያደርግህ ነው:: ሰይጣንን ከገሠጽከው በእግዚአብሔር ቀኝ ከበጎቹ ጋር ትቆማለህ::

አሁን ያለህበት ችግር ያልፋል:: የሚሰማህ ክፉ ስሜት መቼም የማይለወጥ አይምሰልህ:: ኀዘኑም ፣ ብቸኝነቱም ፣ ተስፋ ቢስነቱም ያልፋል:: ጨለማው ይነጋል:: የተዘጋው በር ይከፈታል:: ችግሩ ሲፈታ አንተ ከሌለህ ግን ትርጉም የለውም::

ስለዚህ ለሚፈታ ችግር የማይቀለበስ ውሳኔ አትወስን:: ራስን ማጥፋት ከጊዜያዊ ችግር ለመሸሽ ሲሉ ዘላቂ ችግር ውስጥ መግባት ነው:: ጊዜያዊ ሕመምን ለማስታገስ የዘላለም ሕመምን ለምን ትመርጣለህ? "የሞተ ተገላገለ" ሲሉ ሰምተህ እንዳትታለል ሞት ዕረፍት የሚሆነው ራሱ እግዚአብሔር ሲጠራህ ብቻ ነው::
"እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ" ያለው ጌታ ሳይጠራህ ራስን ማጥፋት የዘላለም ስቃይ ያመጣል::

ወዳጄ "በራስህ አንዳች ክፉ አታድርግ"

የሕይወትህን ዋጋ ታውቅ ይሆን? አንተ እኮ የእግዚአብሔር ልጅ ለአንተ ሲል የሞተልህ ነህ:: ሊፈውስህ የቆሰለ ፣ ሊያከብርህ የተዋረደ ፣ ሊያረካህ የተጠማ ፣ ሊያለብስህ የተራቆተ ለአንተ እኮ ነው::
ክርስቶስ ስለ አንተ ሞቶአል:: አንተን ግን የጠየቀህ እንድትሞትለት ሳይሆን እንድትኖርለት ነው::
ለሞተልህ አምላክ እንዴት መኖር ያቅትሃል?

ወዳጄ ሆይ ሰውነትህ በአምላክ ደም የተገዛ ክቡር ሰውነት ነው:: አካልህ "አንተ" እንጂ "ያንተ" አይደለም:: "በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ" ይላል

ስለዚህ በከበረ የእግዚአብሔር ልጅ ደም የተገዛ ሰውነትህን ለሰይጣን በርካሽ አትሽጠው:: አትግደል የሚለው ሕግ ራስህንም ይጨምራል:: ቤተ መቅደስ የሆነ ሰውነትህን ለማፍረስ አታስብ::
"ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ" 1ኛ ቆሮ. 3:17

ሰዎች አስቀይመውህ ይሆን?

"አሳያቸዋለሁ ፤ ስሞት የእኔን ነገር ይገባቸዋል" ብለህ በሰዎች ተቀይመህ ራስህን አትጉዳ:: እመነኝ ብትሞት ሰዎች ከሳምንት በላይ አያስታውሱህም:: ለሕይወትህ ዋጋ ያልሠጡ ሰዎች ለሞትህ ዋጋ አይሠጡም:: ፈጥነውም ይረሱሃል:: ለሚረሱህ ሰዎች ብለህ የማይረሳህን አምላክ አታሳዝን:: ሰው ስለ አንተ ግድ የለውም እግዚአብሔር ግን የራስህን ቁጥር ሳይቀር በቁጥር ያውቀዋል :: እንኳንስ ራስህን ልትጎዳ አንዲት ጸጉር እንኳን ከአንተ እንድትወድቅ አይፈልግም::

እግዚአብሔርን በኃጢአት ብታሳዝነው እንኳን ኖረህ ንስሓ እንድትገባ እንጂ እንድትሞት አይፈልግም:: አባትህ ነውና ከእርሱ ጋር ባትሆንም እንድትኖር ይፈልጋል:: በምሳሌ ልንገርህ :-

ሁለት ሴቶች አንድን ሕፃን "የኔ ልጄ ነው" ብለው እየተከራከሩ ጠቢቡ ሰሎሞን ፊት ቀረቡ:: ጠቢቡ ሰሎሞን ሰይፍ አመጣና "ልጁን ቆርጬ ለሁለት ላካፍላችሁ" አላቸው:: አንደኛዋ ሴት "እሺ እንካፈል" ስትል እውነተኛዋ እናት ግን "ልጄ ከሚሞት እርስዋ ትውሰደው" አለች:: እናት መሆንዋም በዚህ ታወቀ::

ወዳጄ ያንተም ኑሮህ ከእግዚአብሔር ጋር ላይሆን ይችላል:: ዓለም የራስዋ አድርጋህም ይሆናል:: በሱስ ውስጥ ትዘፍቀህ ፣ እንደ ሶምሶን በደሊላ እቅፍ ፣ እንደ ዴማስ በተሰሎንቄ ውበት ተማርከህ ይሆናል:: እግዚአብሔር ግን አባትህ ነውና ሞትህን አይፈልግም::

"ልጄ ከሚሞት እርስዋ ትውሰደው" እንዳለችው እናት ፈጣሪህ ከነኃጢአትህም ቢሆን እንድትሞት አይፈልግም:: ከእርሱ ጋር ባትኖርም መኖርህን ይፈልጋል:: "የሟቹን ሞት አልፈቅድምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ" ሕዝ. 18:32

የይሁዳ ኃጢአቱ ጌታውን መሸጡ አልነበረም:: ራሱን መግደሉ ነው:: እግዚአብሔር የሚያዝነው ከበደልህ በላይ በእርሱ ተስፋ ቆርጠህ ራስህን ስትጎዳ ነው::

ወዳጄ የአንተን መኖር የሚፈልጉ ብዙ ናቸው:: ፈጣሪ ወደዚህች ዓለም ያለ ምክንያት አላመጣህም:: በአንተ አለመኖርም የሚጎድል ነገር አለ:: አንተን የሚመስል ሌላ ሰው አልፈጠረምና ለዚህ ዓለም አንተን የሚተካ የለም:: በክብር ወደዚህ ዓለም ያመጣህ አምላክ በክብር ወደራሱ እስኪወስድህ ድረስ "በራስህ ላይ ክፉ ነገር አታድርግ"

"የወኅኒውም ጠባቂ ከእንቅልፉ ነቅቶ የወኅኒው ደጆች ተከፍተው ባየ ጊዜ፥ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ይገድል ዘንድ አስቦ ሰይፉን መዘዘ።
ጳውሎስ ግን በታላቅ ድምፅ፦ ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ፡ ብሎ ጮኸ" ሐዋ. 16:27-28

ይህ ሰው እስረኛ ያመለጠ መስሎት ራሱን ሊያጠፋ ሲል ጳውሎስ "ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ" አለው::

ወዳጄ አንተስ ተስፋ የቆረጥኸው ምን ያመለጠ መስሎህ ነው?
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - ‌🇴‌🇷‌🇹‌🇭‌🇴‌🇩‌🇴‌🇽 ‌🇹‌🇪‌🇼‌🇦‌🇭‌🇩‌🇴
Photo
የትምህርት ዕድል ያመለጠህ መስሎህ ነው? ገና ሺህ የትምህርት ዕድሎች አሉህ:: ዕድሜህ ያመለጠህ መስሎህ ነው? ነገ የሚጠብቁህ ብሩሕ ዘመናት እኮ ቁጭ ብለው አሉ? የሚረዳኝ ሰው የሚያስብልኝ ሰው አጥቼያለሁ? ብለህ ከሆነም ካልሰሙህ ጥቂቶች በላይ ልንሰማህ የምንሻ "ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ"

መከራ ጸናብኝ ኑሮ ጨለመብኝ የሀገሪቱ ሁኔታ ተስፋ አሳጣኝ ብለህ ይሆን? እኛስ አብረንህ አይደልንም? አብረን ከገባንበት ችግር አብረን ብንወጣ አይሻልም? ከአንተ በባሰ ሁኔታ የታሰርንና የተገረፍን ጳውሎሶችና ሲላሶች "ሁላችን በዚህ አለንና በራስህ ክፉ አታድርግ" ስንልህ ስማን::

ይልቅ አንተም እንደ ወኅኒው ጠባቂ "እድን ዘንድ ምን ላድርግ ብለህ?"ነፍስህን የምታድንበትን መንገድ ወደ መቅደሱ ቀርበህ ጠይቅ::

ወዳጄ ይህንን ጽሑፍ ያነበብኸውም በሕይወት ስላለህ ነው:: የአንተን ዓይን የሚጠብቁ ብዙ ጽሑፎች ፣ የአንተን ጆሮ የሚፈልጉ ብዙ ድምፆች ፣ የአንተን መሐረብ የሚፈልጉ ብዙ ዕንባዎች ፣ የአንተን ሳቅ የሚፈልጉ ብዙ ቀልዶች ... ገና ብዙ ብዙ አሉ::

ስለዚህ ሰይጣንን አሳፍረው:: እንዲህ በለው :-

"ጠላቴ ሆይ፥ ብወድቅ እነሣለሁና፥ በጨለማም ብቀመጥ እግዚአብሔር ብርሃን ይሆንልኛልና በእኔ ላይ ደስ አይበልሽ" ሚክ. 7:8

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጥቅምት 2016 ዓ.ም.
ሜልበርን አውስትራሊያ

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን አጥብቃችሁ ስለ እኔ ጸልዩልኝ!
በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ [ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ ሌላ] ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - ‌🇴‌🇷‌🇹‌🇭‌🇴‌🇩‌🇴‌🇽 ‌🇹‌🇪‌🇼‌🇦‌🇭‌🇩‌🇴
Photo
ለማኅበራዊ ሚዲያ ማድመቂያ በማኅሌቱ የሚታየው የሥርዓተ ቤተክርስቲያ ጥሰት ሊቆም ይገባል ሲሉ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ለኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ተናገሩ አቡነ ኤርሚያስ እንዳሉት ከበሮ ይዞ የሚሽከረከሩ፣ ጭፈራ የሚመስል በፍፁም ከኃይማኖታዊ የማይመስሉ ድርጊቶች በቤተክርስቲያን ላይ እየታዩ ነው ይህን ድርጊት ለማስቆም ሊቃውት መናገር ፈርቷል አሁን ደፍረን መናገር አለብን ይህ ድርጊት መቆም አለበት ብሏል። አሁን አላዋቂዎች እና ደጋፊዎቻቸው እየበዙ አዋቂዎች እያነሱ መጥቷል፣ እነዚህ ከእምነቱ ውጪ የሆኑ ድርጊቶች ሲከናወኑ ማህሌቱ ደመቀ ይባል መሆን የለበትም ሊቃውት ይህን ማስቆም አለባቸው ብለዋል።
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - ‌🇴‌🇷‌🇹‌🇭‌🇴‌🇩‌🇴‌🇽 ‌🇹‌🇪‌🇼‌🇦‌🇭‌🇩‌🇴
Photo
[ስምኽ የጣፈጠ መድኃኔ ዓለም]
በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ ጥቅምት 27 የቀረበ ምስጋና
✍️ በአራቱ ወንጌላት ላይ የዳዊት ልጅ፣ የአብርሃም ልጅ፣ ኢየሱስ፣ ክርስቶስ፣ ዐማኑኤል፣ ተወዳጅ ልጅ፣ የእግዚአብሔር ልጅ፣ የሰው ልጅ፣ የአይሁድ ንጉሥ፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ፣ ደንጊያና የመአዝን ራስ፣ የእስራኤል ንጉሥ፣ የልዑል ልጅ፣ የመዳን ቀንድ፣ ከላይ የመጣ ብርሃን፣ አቤቱ፣ የተመረጠ ልጅ፣ ሕያው፣ ቃል፣ አንድ ልጁ፣ ረቢ (መምህር)፣ መሲሕ፣ ልጁ፣ የእግዚአብሔር በግ፣ እግዚአብሔር፣ ሰማያዊ ሙሽራ፣ የዓለም መድኀኒት፣ የእግዚአብሔር እንጀራ፣ የሰማይ እንጀራ፣ የሕይወት እንጀራ፣ የዓለም ብርሃን፣ መልካም እረኛ፣ ትንሣኤና ሕይወት፣ መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት፣ በር፣ እውነተኛ የወይን ግንድ የተባልኽ ቸሩ መድኃኔ ዓለም ሆይ አመልክኻለኹ።

✍️ በሐዋርያት ሥራና በመልእክታት ላይ ቅዱስና ጻድቅ፣ የሕያዋንና የሙታን ፈራጅ፣ ጌታ፣ መድኀኒት፣ የእግዚአብሔር ኀይልና የእግዚአብሔር ጥበብ፣ በግዐ ፋሲካ፣ ኋለኛው አዳም፣ የቤተ ክርስቲያን ራስ፣ ሕያው አምላክ፣ በኲር፣ ታላቅ ሊቀ ካህናት፣ የእምነታችን ራስና ፈጻሚ፣ የነፍስ እረኛና ጠባቂ፣ የእረኞች አለቃ፣ የሕይወት ቃል፣ የአብ ልጅ፣ የእግዚአብሔር አንድ ልጅ የተባልኽ መድኃኔ ዓለም ሆይ እወድኻለኹ።

✍️ መጻኢውን በሚናገረው በዮሐንስ ራእይ ላይ በኲረ ሙታን፣ የምድር ነገሥታት ገዢ፣ የታመነው ምስክር፣ የይሁዳ አንበሳ፣ የታረደው በግ፣ የታመነና እውነተኛ፣ የእግዚአብሔር ቃል፣ ፊተኛውና ኋለኛው፣ አልፋና ዖሜጋ፣ የነገሥታት ንጉሥ፣ የጌቶች ጌታ፣ መዠመሪያውና መጨረሻው፣ የዳዊት ሥርና ዘር፣ የሚያበራ የንጋት ኮከብ የተባልኽ መድኃኔ ዓለም ሆይ ምስጋናን ለአንተ አቀርባለኹ።
(ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ፤ ነገረ ክርስቶስ ከሚለው መጽሐፌ የተወሰደ)
[ውዶች ሆይ በአስተያየት መስጫው ላይ መድኃኔ ዓለምን ብቻ አመስግኑት።]
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - ‌🇴‌🇷‌🇹‌🇭‌🇴‌🇩‌🇴‌🇽 ‌🇹‌🇪‌🇼‌🇦‌🇭‌🇩‌🇴
Photo
እሾኹ ተነቅሏል፡፡

አዳም "እሾኽና አሜከላ ይብቀልብህ" ተብሎ ተረግሞ ነበር፡፡

በዚኽም ምክንያት ይህ እሾኽ የአዳምን እግሮች ሲወጋ ኖረ፡፡ ዛሬ ግን እሾኹ እግር እንዲወጋ ኾኖ አልተሠራም፤
አክሊል ኾኖ በመድኃኔዓለም ራስ ላይ ተደፋ እንጂ፡፡ በእሾኽ ምክንያት መቁሰል ከአዳም እግሮች ጀመረ፤ በመድኅን ክርስቶስ ራስ ላይ ተፈመ፡፡
አዳምን "ይብቀልብህ" ያለውን እሾኽ በራሱ ላይ 'እንዲበቅል' አደረገ፡፡

በዚህ እሾኽ አምሳል፥ ፍዳ መርገም፣ ኀጢኣት…ተነቅሏል:: ከኀሳር ወደክብር ተሸጋግረናል፡፡ መርገሙ ተሽሯል፡፡
በሰላም ወደየቤቶቻችሁ ተመለሱ!

በ፲፫ቱ ቅዳሴ ማብቂያ ላይ ዲያቆኑ "#እትዉ_በሰላም " ሲል በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቅዳሴ ደግሞ ካህኑ በ‘በአንብሮ እድ’ እንዲህ ሲል ያሰናብተናል

🕊 "ሠናይ ለክሙ ሠናይ ለክሙ ሠናይ ለክሙ ኦ አባግዐ መርዔቱ ለክርስቶስ ። በላዕክሙ ወጸገብክሙ ሰተይክሙ ወረወይክሙ #በሰላም_እትዉ_ውስተ_አብያቲክሙ እግዚአብሔር የሀሉ ምስለ ኵልክሙ ⇨ መልካም ይሁንላችሁ (በደህና ሁኑ) የክርስቶስ የመንጋው በጎች በልታችሁ የጠገባችሁ፣ ጠጥታችሁ የረካችሁ #በሰላም_ወደእየቤታችሁ_ግቡ (ተመለሱ) እግዚአብሔር ከሁላችሁ ጋር ይሁን"

እንግዲህ ልብ እናድርግ የቅዳሴው ፍጻሜ በቤተክርስቲያን በአታቸው ለተማጸኑ ምዕመናን በሰላም ሂዱ ሳይሆን በሰላም ግቡ ነው የሚለው! ይኽ "በሰላም እትዉ ውስተ አብያቲክሙ ⇨ በሰላም ወደየቤቶቻችሁ ግቡ" የሚል የልዑካኑ የፍጻሜ ትዕዛዝ "ፃኡ" ሳይሆን "#እትዉ " ነውና ምን መልእክት አለው ይሆን?
"አተወ" የሚለው ግስ ለ"እትዉ" መነሻ ነው በትርጉሙ ገባ ፣ ተመለሰ፣ “መጣ” ማለት ነው። ከዚህ መነሻ መልእክቱ "በሰላም ግቡ፣ በሰላም ተመለሱ፣ በሰላም ኑ… " የሚል መሆኑን ልብ ይሏል። በዚኽም ላይ

↣ "እስመ ውእቱ ሰላምነ ⇨ እርሱ ሰላማችን ነውና" (ኤፌ ፪፥፲፬) በተባለ መስተሳልም (ሰላም አድራጊ) አምላክ በክርስቶስ አምናችሁ፣ እርሱ ባለቤቱ "ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም።" (ዮሐ ፲፬፥፳፯) እንዳለን የሚሰጠውን ፍጹም ሰላም ደጅ ጠንተን፣

↣ "ሰላመ ሰጣዊት፡ ወንርዓይ ብኪ ሰላመ ⇨ ሰላምን የምትሰጪ በአንቺ ሰላምን የምናይብሽ" የምንላትነ የሰላም እናት ቅድስት ድንግል ወላዲተ አምላክ ማርያም ከስደት መመለሷን በምናስብበት በዚኽ #ሰሙነ_ሚጠት በታመነ ምልጃዋ ከእንግልት ፣ ከስደትና ከሞት ተመልሰን በጥላዋ ተጠልለን በልጇ ርስት በሰላም ቤቱ ለማረፍ እንድንበቃ ትርዳን 🙏

https://youtu.be/mYATwMHT28k?si=9FXkwkNZHNRHyuEV
“ነቢይ ዘከመ እሳት ⇨ እሳታዊ ነቢይ”
✥ °°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°° ✥

"ወተንስአ ኤልያስ ነቢይ ዘከመ እሳት ወቃሉኒ ከመ ነድ ያውኢ ⇨ እሳታዊው ነቢይ ኤልያስ ተነሣ ቃሉም እንደ እሳት ያቃጥል ነበር" 【ሲራ. ፵፰፥፩】

መነሻችን የሚሆነው ጥያቄ ነው?
☞ [መኑ ውእቱ] ዘዐርገ በነደ እሳት በሰረገላት ወበአፍራስ ዘእሳት ?
በእሳት ሰረገላና በእሳት ፈረስ ወደሰማይ የወጣ ማነው?
ይህን ጥያቄ የሚያነሳው ሲራክ ብለን የምንጠራው ኢያሱ ወልደ ሲራክ ወይም ኢያሱ ወልደ አልዓዛር በመጽሐፉ ፵፰ኛ ምዕራፍ ቁጥር ፱ ላይ ነው።

በመጽሐፈ ሲራክ መቅድም ሊቃውንቱ ይኽን ነግረውናል
ሲራክ፦ ፀሐፊ ማለት ነው፤ ፀሐፊው ኢያሱ ወልደ አልዓዛር ወልደ ሲራክ ይባላል።
፶፩ ምዕራፎች ፦ በአቀራረቡ ከሰሎሞን መጽሐፈ ምሳሌ ጋር ተመሳሳይነት አለው።
ይዘት ፦ ለመንፈሳዊና ሥጋዊ ሕይወታችን ጥበብና ምክር የሚሰጥ ነው።

ሲራክ ስለእሳታዊ ነቢይ ይጠይቃል፤
ማነው? በእሳት ተጠቅልሎ የተወለደ ፣ በእግዚአብሔር ቃል ሦስት ጊዜ ከሰማይ እሳት ያወረደ ፣ በእሳት ሠረገላና በእሳት ፈረስ ተጭኖ ወደሰማይ የነጎደ ማነው?
በዘይቤ መንፈሳዊ ትምህርትነትና ምክር በስፋት የያዘው ይኽ መጽሐፈ ሲራክ የእሳትን አስተማሪ ምሳሌነ አጉልቶ በብዙ መንገድ ይነግረናል ለአብነት
☞ ወርቅን ወርቅ ለመሆኑ የሚፈትኑት በእሳት እንደሆነው ሁሉ ጻድቅም ችግር በሚያመጣ መከራ ተፈትኖ የሚያልፍ ነው 【፪፥፭】
☞ የሚነድ’ እሳት የሚጠፋው በውኃ እንደሆነው ኃጢዓት የሚሰረየው በምጽዋት ነው 【፫፥፳፰】
☞ ከተናጋሪ ሰው ጋር መከራከር በእሳት ላይ እንጨት እንደመከመር ነው 【፰፥፫】
☞ መልከ መልካምና ደምግባት ያላት ሴት ፍቅር የሚነድ’ እሳት ነው 【፱፥፰】
☞ በነጻ ፈቃድ እንዲመርጥ ለሰው እግዚአብሔር ያቀረበው የጽድቅና የኃጢዓት መንገድ እንደ እሳትና ውኃ ነው 【፲፭፥፲፮】
☞ ሰው በልቡ ሐሳብ መፈተኑ ሸክላ በእሳት እንደሚፈተነው ነው 【፳፯፥፭】
☞ የእግዚአብሔር ፍርድና ቁጣው እሳት ነው 【፳፰፥፳፪】…

እሳት በጠባዩ ይቡስ (ደረቅ) ፣ ውዑይ (የሚያቃጥል) እና ብሩህ (የሚበራ) ነው። በፍጥረትነቱም ከዐራቱ አሥራው ፍጥረታትና ባሕርያት አንዱ ሆኖ በሁሉ የሚገኝ በይብስቱ ከነፋስ በውዕየቱ ከመሬት በብርሃኑ ከውሃ የሚስማማ ፍጥረት ነው።

ሲራክ ምዕራፉን የሚጀምረው የነቢዩን ማንነት እንዲህ ሲል ነግሮን ነው! "ወተንስአ ኤልያስ ነቢይ ዘከመ እሳት ወቃሉኒ ከመ ነድ ያውኢ ⇨ እሳታዊው ነቢይ ኤልያስ ተነሣ ቃሉም እንደ እሳት ያቃጥል ነበር" 【ሲራ. ፵፰፥፩】

አልያስ ማለት ቀናዒ
መደንግጸ አብዳን፡ ሕገ መነኮሳት ሠራዒ
ኤልያስ ማለት ድንግል
ብእሴ ሰላም ፡ መምህረ እስራኤል
ኤልያስ ማለት ቅብዓ ፍሥሐ
ለቤተክርስቲያን ፡ አንቀጸ ጽርሐ
ኤልያስ ማለት ካህነ ኦሪት
ምዑዘ ምግባር ፡ መዝገበ ሃይማኖት
ኤልያስ ማለት ጸዋሚ
ለእግዚአብሔር ቊልኤሁ ፡ ዝጉሐዊ ተሐራሚ

ኤልያስ ማለት…

ኤልያስ ቴስብያዊ ፣ ኤልያስ ቀርሜሎሳዊ ፣ ኤልያስ ታቦራዊ ፣ ኤልያስ ዘሰራጵታ፣ ኤልያስ ነቢየ ፋፃ … በኩረ ሐዋርያት ፣ ቢጸ ነቢያት ፣ ነቢየ ክርስቶስ ፣ ነቢየ ልዑል ባለብዙ ግብር ባለብዙ ስም …

የዚኽ እሳታዊ ነቢይ ስሙ እንዲህ የበዛው ሥራው ስለበዛ ነው "በአምጣነ ዕፁ ለእሳት የዐቢ ነዱ ⇨ በእንጨቱ ብዛት የእሳቱ ነዲዱ ይበዛል" እንዲል【ሲራ. ፳፰፥፲】

ወሬዛ በኃይሉ አረጋዊ በመዋዕሉ ተብሎ የተገለጠ ጸሐፌ ትዕዛዝ ቅዱስ ኤልያስ ጥር ፮ በእሳት ሠረገላና በእሳት ፈረስ ተጭኖ ወደሰማይ ያረገበት ቀን ፣ ታኅሳስ ፩ በአክአብ ፊት በኃይል ለዘለፋ የተገለጠበት(የናቡቴ ዕረፍት) ፣ «ነሐሴ ፳፪ ቀን ደግሞ ልደቱ» ነው፤ በእነዚኽ ቀናት ልንዘክረውና ልናከብረው ይገባል!

እንኳን እሳት ያወረደውን ቀርቶ የወረደውን እሳት ማክበር ተገቢ ነው ፤ አበው እንዴት መያዝ እንደሚገባው ሲነግሩን «እሳትን በገል ውሃን በቅል» ብለዋል።
ሙሴ አንደበቱ ትብ የሆነው እሳት በልቶ ፣ መጻጉዕ እጁ የተኮማተረው እሳት ጸፍቶ መሆኑን እናውቃለን።

ሊቁ እንዲህ ተቀኝቷል
"መጻጉዕ ሕፃን ኢያእማሬ ነፍስ ዓዲ
አኮኑ ፈነወ እዴሁ መንገለ እሳት ነዳዲ

【 መጻጉዕ ሕጻን ነው ነፍስ ማወቅ መች ጀመረ ?
ቢበስልማ ኖሮ ወደሚነደው እሳት እጁን ባልጨመረ 】

ኤልያስ ማለት በእብራይስጡ (ኤል אֵל) እና (ያስ/ ያህ יָהּ)ከሚሉ ሁለት የፈጣሪያችን ስሞች የተገኘ ጥምረት ሆኖ "እግዚአብሔር ጌታዬ ነው" የሚለውን ፍቺ ይሠጣል። በቅዱሱ መጽሐፍም ከታላቁ ነቢይ ውጪ ሌሎች ሁለት እስራኤላውያን በዚህ የከበረ ታላቅ ስም ተጠርተዋል።

በግሪኩ ደግሞ ኤሊያ ἐλαία (አላህያህ) ማለት ወይራ ማለት ነው። ይህን ያዞ ጌታችን የወይራ ዛፍ በበዛበት ተራራ በደብረ ዘይት ሲጸልይበት የነበረውን ዋሻ የኤልዮን ዋሻ እያለ ይጠራዋል

“ወመዐልትሰ ይሜህር በምኵራብ ወሌሊተ ይወፅእ ወይበይት ውስተ ደብር ዘስሙ ኤሌዎን ⇛ዕለት ዕለትም በመቅደስ (በምኩራብ) ያስተምር ነበር፥ ሌሊት ግን [ኤሌዎን በሚባል] ደብረ ዘይት ተራራ ወጥቶ ያድር ነበር ” 【ሉቃስ ፳፩፥፴፯】

መጽሐፍም ኤልያስ ማለት ወይራ ማለት ነው የሚለውን ልሳነ ጽርእ ይዞ የወይራን ተክል ፍሬና ዘይትን ኤልያስ እያለ ይገልጣል (The tree , the fruit or the oil ☞ ዕፀ ዘይት ፣ ፍሬ ዘይት ፣ ቅብዐ ዘይት)

【ኩፋ ፲፯፥፲】 "ወነሥአቶ እሙ ወሐራዊ ወገደፈቶ ታሕተ አሐቲ ኤልያስ ወሖረት ወነበረት አንጻሮ መጠነ አሐቲ ምንጻፍ እስመ ትቤ ኢይርአይ ሞት ለሕጻንየ ወነቢራ በከየት ⇨እናቱ አነሳችውና ሔዳ በአንዲት የወይራ/ዘይት እንጨት ሥር አኖረችው የልጁን ሞት አላይም ብላለችና በዚያ ተቀምጣ አለቀሰች" (13፥31)

【ሔኖ ፫፥፳፬】 "ወአሕቲ መስፈርተ ኤልያስ ትገብር ዐሠርተ ምክያደ ዘይት ⇨አንዲቱም መስፈሪያ ዘይት አስር የዘይት አውድማንበትመላለች "

የእኛ ሊቃውንት ስሙን በዘይቤና በምሥጢር እያራቀቁ «ዕፀ ዘይት ማኅቶት በቅድመ እግዚአብሔር ፣ ሥዩም ላዕለ ምድር ወሥሉጥ ላዕለ ሰማይ ወላዕለ ማይ » በማለት ገልጠውልናል። በ«መልኩ» መነሻ ላይም
ሰላም ለትርጓሜ ስምከ ዘተብህለ ዘይተ
… በጸውኦ ስምከ ኤልሳዕ ዮርዳኖስ አዕተተ" ይላል

የቅዱስ ዮሐንስ ራእይ ቃልም ለእርሱ መነገሩን በምሥጢር አስማምተው ይተረጉማሉ።

"ዕፀ ዘይት ወመኃትው በቅድመ እግዚአብሔር "【ራዕ ፲፩፥፬】
አቡቀለምሲስ በዚህ የራእዩ ክፍል በአምላካቸው ፊት ወይራና መቅረዝ እያለ አክብሮ የጠራው ሔኖክና ኤልያስን ነው።
✧ ወክልኤ ዕፀ ዘይት እለ ቅድመ እግዚአብሔር
(በእግዚአብሔር ፊት ያሉ የእግዚአብሔር ባለሟሎች የሚሆኑ ሁለቱ የወይራ ዛፎች) መባላቸው
☞ ሄኖክ ማለት ተሐድሶ(አዲስ መሆን) ማለት ነው።
ተሐድሶ በዘይት ነውና
☞ ኤልያስም ማለት ከላይ እንዳየነው ዘይት ማለት ነው።

✧ ወክልኤ መኃትው እለ ቅድመ እግዚአብሔር
(በእግዚአብሔር ፊት ያሉ የእግዚአብሔር ባለሟሎች የሚሆኑ ሁለቱ መብራቶች) መባላቸው
☞ በትምህርታቸው የሰውን ልቡና ብሩህ ያደርጋሉና
ነገረ ዘይት/ ወይራ ዛፍ (About Olive Tree)

ከዕለተ ሠሉስ ዕፀው መካከል ዕፀ ዘይት (የወይራ ዛፍ) አንዱ ነው! ቅባት የሚሰጥ ለመብልነት ለመብራትም የሚውል የወይራ ወገን ነው::
 
* በሕገ ልቡና በሰብአ ትካት ለጥፋት ውኃ መወገድ በሰላም አብሣሪዋ ርግብ የመጣ ምልክት ይኼ ወይራ ነው!  "ርግብም በማታ ጊዜ ወደ እርሱ ተመለሰች በአፍዋም እነሆ የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ ነበር። ኖኅም ከምድር ላይ ውኃ እንደ ቀለለ አወቀ።" 【ዘፍ ፰፥፲፩】
 
* በሕገ ኦሪት ከምድረ ርስት ከነአን ገጸ በረከት አንዱ ይኼ ወይራ ነው! "ስንዴ ገብስም ወይንም በለስም ሮማንም ወይራም ማርም ወደ ሞሉባት ምድር፥..." 【ዘዳ. ፰፥፰ በቤተ መቅደሱ ያሉ ሁለቱ ኪሩቤል የተቀረጸው : የመቅደሱ መግቢያ መቃን  እና የቅድስተ ቅዱሳኑ ደጃፍ አምድ የተሰራው ከዚሁ  ከወይራ ነው! 【፩ ነገሥ. ፮፥፳፫-፴፬】
 
* በሕገ ወንጌል በመዋዕለ ሥጋዌው ሌሊት ሌሊቱን ጌታችን የመረጣት የጸሎት ሥፍራ ምጽአቱን ያስተማረባትና ዕርገቱን የፈጸመባት ደብር የወይራ ዛፍ የበዛባትን ሥፍራ "ደብረ ዘይትን" ነው! 【ሉቃ. ፳፩፥፴፯】 ዕለት ዕለትም በመቅደስ ያስተምር ነበር፥ ሌሊት ግን ደብረ ዘይት ወደምትባል ተራራ ወጥቶ ያድር ነበር።
 
በነገረ ሃይማኖት ምሥጢራዊ ምሳሌነቱ

የወይራ ዛፍ የቤተ እግዚአብሔር መብራት ምንጭ ነው! የፈጣሪን ገጸ ምህረት ተወካፌ ጸሎትነት ያሳያል "አንተም መብራቱን ሁል ጊዜ ያበሩት ዘንድ ለመብራት ተወቅጦ የተጠለለ ጥሩ የወይራ ዘይት እንዲያመጡልህ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው።" 【ዘጸ· ፳፯፥፳】
  የወይራ ዛፍ ክር የሚነድበት ዘይት መገኛ ነው! ለእግራችን መብራት ለመንገዳችን ብርሃን የሆነ ህጉን ለሚያስተምሩ ምግባር ለሚያሰሩ አበው ምሳሌ ነው!  "ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው።"  【መዝ. ፻፲፰፥፻፭】
የወይራ ዛፍ በቤተ እግዚአብሔር ያማረ የተወደደ እንደሆነ እንዲሁ በሥላሴ ፊት ባለሟልነት በምዕመናን ዘንድ መወደድ በአጋንንት ዘንድ መፈራት ያላቸውን አበውን የመስላል!  "ለእስራኤልም እንደ ጠል እሆነዋለሁ... ውበቱም እንደ ወይራ ይሆናል" 【ሆሴ. ፻፬፥፮】
የወይራ ዛፍ ብዙ ፍሬ እንዲያፈራ ባለ ብዙ ጸጋና ክብር የሆኑትን አበውን ይመስላል! " ልጆችህ በማዕድህ ዙሪያ እንደ ወይራ ቡቃያ ናቸው።"  【መዝ. ፻፳፯፥፫】
የወይራ ዛፍ ቀን ከአእዋፍ ሌሊት ከአራዊት በአጥር በቅጥር ተጠብቆ  እንዲኖር በረድኤቱ በቤቱ ጥላ ተጠብቀው የሚኖሩ አበውን ይመስላል! "እኔስ በእግዚአብሔር ቤት እንደ ለመለመ እንደ ወይራ ዛፍ ነኝ፤" 【መዝ· ፶፩፥፰】

ለዚህ ነው የኢያሴንዩና የቶና ልጅ ኤልያስን ባለራእዩ ቅዱስ ዮሐንስ በመጽሐፈ ቀለምሲስ  «ዕፀ ዘይት ወመኃትው በቅድመ እግዚአብሔር » እያለ የሚጠራው። እነዚህ በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙ ሁለቱ ወይራዎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው። ማንምም ሊጐዳቸው ቢወድ እሳት ከአፋቸው ይወጣል ጠላቶቻቸውንም ይበላል፤ ማንም ሊጐዳቸው ቢወድም እንዲሁ ሊገደል ይገባዋል። እነዚህ ትንቢት በሚናገሩበት ወራት ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ሊዘጉ ሥልጣን አላቸው፥ ውኃዎችንም ወደ ደም ሊለውጡ በሚፈልጉበትም ጊዜ ሁሉ በመቅሠፍት ሁሉ ምድርን ሊመቱ ሥልጣን አላቸው። በረከታቸው በሁላችን ይደር !

🍁 [ኦ ኤልያስ] ; ብፁዓን ፡ እለ ፡ የአምሩከ ፤ ወእለ ፡ ስርግዋን ፡ በፍቅርከ ፤ ወንሕነሂ ፡ ሕይወተ ፡ ነሐዩ ፡ (በእንቲአከ) ።

🍁 [ኤልያስ ሆይ] ; የሚያውቁህና በፍቅርህ ያጌጡ ሰዎች ብፁዓን ናቸው፣ እኛም ስለአንተ በሕይወት እንኖራለን።

🍁 [Oh Elijah] ; Blessed are they that saw thee, and slept in love; for we shall surely live.
【ሲራ ፵፰፥፲፩, Sirach 48:11】

መጽሐፍ እጅግ ማግነናችንን ከአምላክ ማስተካከላችን እንዳልሆነ ሲነግረን እንዲህ ይላል  ⇨ አኮ ዘናስተአርዮ ምስለ ፈጣሪሁ አላ ናስተማስሎ በኵሉ ግብር ምስለ አምላኩ።  ⇨  ከፈጣሪው ጋር የምናስተካክለው አይደለም በሥራዎቹ ሁሉ ከአምላኩ ጋር እናመሳስለዋለን እንጂ ⇨ We do not equate Him with the Creator, but we view him as an example of God in all his works.
አልያስ ፍጥረቱ እንደኛው መሆኑን  “ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበረ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፥ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም፤ ሁለተኛም ጸለየ፥” 【ያዕ፭፥፲፯】 ነገር ግን ከመጠን ይልቅ ማክበራችን ታዘንና ተለምነን መሆኑን ልብ ይሏል  “ወንድሞች ሆይ፥ በመካከላችሁ የሚደክሙትን በጌታም የሚገዙአችሁን የሚገሥጹአችሁንም ታውቁ ዘንድ፥ ስለ ሥራቸውም በፍቅር ከመጠን ይልቅ ታከብሩአቸው ዘንድ እንለምናችኋለን። ”【፩ኛ ተሰ ፭፥፲፪】

አንድ #ማስተካከያ በማመልከት መልእክታችንን እንቋጫለን።

ኤልያስ የተወለደው በምን ቀን ነው? 
መጽሐፈ ስንክሳራችን ታኅሳስ ፩ ቀን "የተገለጠበት ቀን” የሚለውን ይዘው ናቡቴ ባረፈበት ቀን ተወልዷል የሚሉ መምህራንና አድባራት ጭምር ይታያሉ፤ መገለጡ በጾመ ነቢያት  በነቢይነቱ በ’ነ አክአብ ፊት ፣ በሐሳውያን ነቢያትና በካህናተ ጣኦት ዘንድ፣ በእስራኤላውያን መካከል… መሆኑን ለመግለጥ እንጂ መወለዱን የሚገልጥ እንዳልሆነ መጽሐፍ ያብራራል።
ታዲያ ልደቱ መቼ ነው ያሉ እንደሆነ «መልኩ» በዚሕ መልክ አስቀምጦታል

"…ኤልያስ እምከ ካልዕተ ሣራ ጠባብ
ልደትከ አመ እሥራ ወአመ ሰኑዩ ለአብ
እንዘ ኩለንታከ በእሳት ግልቡብ …"

ከዚህ ውሥጥ «ልደትከ አመ እሥራ ወአመ ሰኑዩ ለአብ»
አብ የተባለው ወርኅ የቱ ነው ብለን የአይሁድን ዜና መዝገብ ብንፈትሽ ታሪክ ጸሐፊው ዮሴፍ (Flavius Josephus ⇝Yoseph Ben Mattithyahu) እንዲህ በማለት የወሩን ቁጥር ጭምር ያመለክትልናል
"ወርኃ ኃምስ ወውእቱ ወርኅ ወርኃ አብ ⇨ አምስተኛው ወር እርሱም አብ የሚባለው ወር ነው"【መጽሐፈ ዮሴፍ ኮርዮን ፶፫፥፭】

ይህ በዕብራውያኑ አብ የተባለው ለሚያዝያ ፭ኛው ወር በእኛ ደግሞ ወርኃ ነሐሴ ነው፤ ስለዚህ የኤልያስ ልደቱ "አመ እሥራ ወአመ ሰኑዩ ለአብ" ባለው መነሻ ነሐሴ ፳፪ ይውላል ማለት ነው።

“እነሆ፥ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ።”【ሚል ፬፥፭ 】

የቅዱስ ኤልያስ በረከቱን አምላካችን ለሁላችን ይላክልን 🙏

✍️ ከቴዎድሮስ በለጠ ታኅሳስ ፩/፳፻፲፮  ዓ.ም. ( Edited & Яερ๑šтεd ƒr๑๓ ጥር ግዝረት ፳፻፲፭  ከእንጦጦ ርእሰ አድባራት ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል አልያስ ወኤልሳዕ)
2025/07/05 07:18:59
Back to Top
HTML Embed Code: