Telegram Web Link
እግዚአብሔርን መውደድ የእ’ሱ የሆነውን ሁሉ በመውደድ ይገለጣል! ይልቁንም የእርሱ ከሆነው ሁሉ  እርሱ የወደደውንና የሞተለትን ክቡር የሰው ልጅ መውደድ እርሱን ወደ መውደድ ያደርሳል!

ሰውን መግፋት እግዚአብሔርን መርሳት ነው። አበው «ተዘክሮተ እግዚአብሔር እና ተዛውኦተ አኃው ካለው ሰው በላይ እግዚአብሔርን ከቶ ማን ይመስለዋል?»  ይላሉ!

ለዐቢይ ጾም ዐቢይ ትዕዛዝ የሚያስተምር ዐበይት ሕግጋቱን የሚናገር ዝማሬ እነሆ "የሕግ ፍጻሜ"

ዲያቆን ዘለዓለም ታከለ (ዘጎላ)  ዝማሬ መላእክት ያሰማልን 🙏

#ሕግጋተ_ወንጌል

ከፍቅረ ቢጽ ጋራ ፍቅረ እግዚአብሔር አጽና
ኦሪትና ወንጌል በሁለቱ ትዕዛዛት ተሰቅለዋልና

በባልንጀራህ ላይ በከንቱ አትቆጣ
የእግዚአብሔር ሰላም ከቤትህ እንዳይወጣ
አድመኝነት ቁጣ ጠብና ክርክር
ፀሐይዋ ሳትገባ ትተህ በፍቅር ኑር

አዝ (ከፍቅረ ቢጽ ጋራ)

ወደሴቲቱ አይቶ ልቡ ‘ሚያመነዝር
ምኞቱ ኃጢዓት ወልዳ ከሞት ጋር የሚኖር
ያለዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ
ከሰማዩ መንግሥት የለው እድል ፈንታ

አዝ (ከፍቅረ ቢጽ ጋራ)

እውነት ከሆነ  አዎን ፡  ካልሆነ አይደለም በል
በሰማይም በምድር  ፡ ፈጽሞ አትማል
ክፉውን በክፉ ፡  ተቃውመህ አትመልስ
መልካም የሆነውን በሰው ሁሉ ፊት ያዝ

አዝ (ከፍቅረ ቢጽ ጋራ)

እግዚአብሔርን መምሰል ራስህን አስለምድ
ላሳዳጆች ጸልይ ጠላትህን ውደድ
የሚረግሙህንም መርቅ እንጂ አትርገም
ይህ ነው ሕገ ወንጌል  ፡ ልዝብ ቀሊል ሸክም

አዝ (ከፍቅረ ቢጽ ጋራ)


https://youtu.be/ERbbNT-RkOE?si=6GS0X04qOY15ikcO
«ወኢትምጻእ ቅድመ እግዚአብሔር አምላክከ ዕራቀከ»
በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ራቁትህን አትምጣ
【ዘዳ ፲፮፥፲፮】

በዚህ መጻሕፍት ይተባበሩበታል
✧ "ወኢታስተርኢ ቅድሜየ ዕራቀከ ☞ በፊቴም አንድ ሰው ባዶ እጁን አይታይ" 【ዘጸ ፴፬፥፳】
✧ "ወኢትትረአይ በቅድሜየ ዕራቀከ ☞ በፊቴም ባዶ እጃችሁን አትታዩ። 【ዘጸ ፳፫ ፥፲፭ / ፳፬፥፲፩】
✧ ሲራክም "ኢትባእ ቅድመ እግዚአብሔር ዕራቀከ ☞ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያ ባዶህን አትግባ" 【ሲራ ፴፪፥፮】

በቅድሜየ ወይም በፊቴ ማለቱ ለእግዚአብሔርስ ሁሉ ቅድሙ ወይም ፊቱ ነው፤ በሁሉ ያለና ከፊቱ የሚሸሸግ የሌለ ሆኖ ሳለ መገለጫ መክበሪያውን ሲያይ ፊቴ ይላል።
☞ በዘመነ ብሉይ በደብተራ ኦሪትና በቤተ መቅደስ በረድኤት ያድር ነበርና
☞ ዛሬም በዘመነ ሐዲስ በሥጋውና ደሙ በቤተክርስቲያን ይገለጽባታልና ከሁሉ አብልጦ ማደርያ ቤቱን ቅድሜየ አላት።

ይህን ራሱ ሙሴ ሲገልጠው «ቅድመ እግዚአብሔር ፥ ውስተ መካን ዘኀርየ እግዚአብሔር አምላክከ ☞ በእግዚአብሔር ፊት ፥ እርሱ አምላክህ በመረጠው ስፍራ» ሲል አስረድቷል፤

ለሰው አካሉን ገልጦና ሰውነቱን አራቁቶ ለመታየት የታወቀ (በቂ) ምክንያት ያስፈልጋል፤ ሠለስቱ ምዕት ለመታከም «የሚተኮስ» «የሚታገም» አካል ቢኖር አልያም ከጸበል ሊነከሩና ሊታጠቡ እንጂ በሌላውስ መንገድ በማንም ፊት እርቃን መታየት ክልክል ነው ብለዋል።

"ወዓዲ ተዐቀብ ከመ ኢትትዐረቅ እምልብስከ ቅድመ መኑሂ ዘእንበለ ዳዕሙ ሶበ ይረክበከ ምክንያት ለተዐርቆ። ☞ ዳግመኛም በማንም ፊት ከልብስህ ራቁትህን እንዳትሆን ተጠበቅ፤ የምትራቆትበት ምክንያት ቢያገኝህ ነው እንጂ" 【ሃይ አበው ፳፥፲፪】

ራቁትነት በውጭ ያለ (አፍኣዊ) ገላን መክደኛ ነውርን መሸፈኛ ከሆነው ጨርቅ ከመራቆት በላይ በሦስት መንገድ ውሳጣዊ እርቃንን የሚያስረዱ ሦስት መንገዶችን እናስቀምጥ

፩ኛ] ራቁት የሚለው #በኃጢዓት_መመላለስ በበደል መጽናትን ነው። ያንን በንሰሐ ሳያጠሩ በእግዚአብሔር ፊት መቆም የሚገባ አይደለምና።

በኃጢዓት ከመውደቃቸው አስቀድሞ የማይተፋፈሩ የነበሩ አዳምና ሴቲቱ ከሕግ ሲወጡ ራቁትነትን አወቁ፤

“የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ፥ እነርሱም ዕራቁታቸውን እንደ ሆኑ አወቁ፤ የበለስንም ቅጠሎች ሰፍተው ለእነርሱ ለራሳቸው ግልድም አደረጉ።” 【ዘፍ ፫፥፯】

ቅዱስ ዳዊት ይህን ድርጊት «እንሰሳትን መምሰል» ብሎታል
【መዝ ፵፰፥፲፪/፳】

አባ ጊዮርጊስም በመጽሐፈ ምሥጢር እርቃን ከመቅረት በላይ እንሰሳትን መምሰል ወዴት አለ? ብሏል
“ምንት ውእቱ ተመስሎ እንስሳ ዘእንበለ ተከሥቶ ዕርቃኑ ማእከለ ዕፀዊሃ ለገነት ሶበ ነፍጸ አጽፈ ብርሃን ዘላዕሌሁ ኀደጎ አጽፈ ብርሃን ⇨ በገነት ዛፎች መካከል ዕርቃኑን ሆኖ ከመተየት በስተቀር እንስሳን መምሰል ምንድ ነው? የብርሃን ልብስ ከበላዩ ላይ በተገፈፈ ጊዜ የብርሃን መጐናጸፊየው ተለየው”

ክዶ ከአምላኩ ተለይቶ የነበረው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታው በፊቱ በቆመ ሠዓት ለጊዜ እርቃኑን በልብስ ደብቆ ከባህር ጠልቆ መታየቱ ነውን በንሰሐ አርቆ ሥጋን በቅጣት አስጨንቆ ድኅነት እንደሚገኝ ማሳያ ነው።
“ኢየሱስ ይወደው የነበረውም ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን፦ ጌታ እኮ ነው አለው። ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ጌታ መሆኑን በሰማ ጊዜ ዕራቁቱን ነበረና ልብሱን ታጥቆ ወደ ባሕር ራሱን ጣለ።” 【ዮሐ ፳፩፥፯】

እንደ ወርቅ የተፈተነ ቃሉን በመያዝ ፣ እንደ ነጭ ልብስ የከበረውን ጸጋ ልጅነት ለማጽናት… ከፊቱ ቀርቦ በንሰሐ መመላለስ ይገባል
“ባለ ጠጋ እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ፥ ተጐናጽፈህም የራቁትነትህ ኃፍረት እንዳይገለጥ ነጭ ልብስን፥ እንድታይም ዓይኖችህን የምትኳለውን ኵል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ።” 【ራእ ፫፥፲፰】

፪ኛ) ራቁት ማለት ራስን መግለጥ #ተርእዮን_መሻት እግዚአብሔርን መርሳት አምላከ ቅዱሳንን ማስረሳት ማለት ነው። ራስን ለመስበክና ስለራስ ለማውራት እግዚአብሔር ፊት መቆም ተገቢ አይደለም።
በሰማይ ያሉ አገልጋዮቹ ከመንበሩ ፊት የቆሙ መላእክቱ ፊት እግራቸውን መሸፈናቸው ለዚህ መማርያ ይሆነናል
“ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር፥ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፤ በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር።” 【ኢሳ ፮፥፪】

ራሱን ሲሰብክ ለዋለው
"ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን ብለው ለመኑት” (ዮሐ 12፥2) የሚል መልእክት ልከው
ኋላ ተመልሶ ራሱን ሰውሮ ክብረ ክርስቶስን ቢሰብክላቸው
“ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው።” (ዮሐ20፥20) ብለው አመስግነውታል።

፫ኛ) ራቁት ማለት ባዶ እጅ #ምንም_ሳይዙ_መምጣት ማለት ነው፤ መባዕ፣ ስእለት ፣ ምጽዋት ፣ ዐሥራት፣ በኩራት፣ ቀዳምያት እና መስዋእት ሳይይዙ ወደመቅደሱ መምጣት የሚገባ አይደለምና።

“ስጡ ይሰጣችሁማል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና፥ የተጨቈነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል።” 【ሉቃ ፮፥፴፰】

የእግዚአብሔር መልስ
መስፈርተ ሠናየ ☞ Good measure
ንሕኑሕ ☞ pressed down/deeper
ምሉዕ ☞ shaken together
ዝሕዙኅ ☞ Running over

በስብከት መልእክቱን በተከታዩ አስፈንጣሪ ያድምጡ

https://youtu.be/cTghI5q7d20?si=KbkRNZ2IdRq366aI
Forwarded from mikiyas danail
✝️ኑ! ቸርነትን እናድርግ ✝️
መጋቢት 15 ቀን 2016 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ፣
+++
ገቢው በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ባጋጠመው ማኅበራዊ ቀውስና ድርቅ የተጎዱ ወገኖቻችንን፣ ገዳማትና አብነት ት/ቤቶች ለመደገፍ የሚውል።
የመግቢያ ትኬቱን፡-
1. በማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ 4ኛ ወለል (ቤተ አብርሃም)
2. በወረዳ ማእከላት ጽ/ቤቶች
3. በማኅበረ ቅዱሳን ንዋያተ ቅድሳት መሸጫ ሱቆች
4. በማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ የዕለት ገንዘብ መሰብሰቢያዎች
5. በአሐዱ ባንክ ሁሉም ቅርንጫፎች
6. በሰ/ት/ቤት ጽ/ቤቶች
ለበለጠ መረጃ
• 09 44 71 82 82
• 09 42 40 76 60

ማኅበረ ቅዱሳን
Forwarded from mikiyas danail
Forwarded from mikiyas danail
መድኃኒታችን

የምኞታችን ማረፊያ፣ መድኃኔዓለም መድኃኒት
ምግብ ልብስና ቤታችን፣ የኑሯችንም መሠረት
⇌⇋♧ ⇌⇋♧ ⇌⇋♧ ⇌⇋♧ ⇌⇋

ትጉህ ኖላዊ  ነው ፤  ነቅቶ የሚጠብቅ
ከተራራው ወርዶ፣ 
ከበለስ ለበላች – ላንዷ የሚጨነቅ
ከአውሬ እየታደገ ፤ እንዳንመስል ዓለሙን
በመስቀል መንበር ላይ፣ 
አዘጋችቶ ሰጠን – ሥጋውና ደሙን 

መድኃኒታችን መድኃኔዓለም
  የማያልቀው ምግብ ለተራበው ዓለም 

⇌⇋♧ ⇌⇋♧ ⇌⇋♧ ⇌⇋♧ ⇌⇋

ጸጋችን ተገ’ፎ ፣ ተራቁተን ብንርቅ
በቁም ሞትን ለብሰን ፣
በለስ አገልድመን –በኃጢዓት ብንደርቅ
በልጅነት ሥልጣን ከክብር ሊመልሰን
ከሸማኔ ጎድጓድ ፣
ከድንግል ተገኝቶ – ራሱን አለበሰን

መድኃኒታችን መድኃኔዓለም
የማያረጀው ልብስ ለታረዘው ዓለም
 
⇌⇋♧ ⇌⇋♧ ⇌⇋♧ ⇌⇋♧ ⇌⇋

ከንቱ ቃል በመስማት ፣ ማረፊያ ስናጣ 
ከገነት ተሰ’ደን ፣ 
ከሰማዩ መንግሥት–ወደ ምድር  ብንመጣ
ተድላና ርስት ሆኖ የምንወርሰው ሀገር
መንግስተ ሰማያት፣
ወንጌልና ተስፋ –እርሱ ነው እግዚአብሔር።

መድኃኒታችን መድኃኔዓለም
የማይፈርስ ጽኑ  ቤት  ለፈላሲው ዓለም 

⇌⇋♧ ⇌⇋♧ ⇌⇋♧ ⇌⇋♧ ⇌⇋
https://youtube.com/watch?v=uHyymObqHQ0&si=VkH5pu91GUt0g8ki
⇌⇋♧ ⇌⇋♧ ⇌⇋♧ ⇌⇋♧ ⇌⇋
Forwarded from Amanuel Ayalew
የመልአከ ፀሐይ ቀሲስ መኮንን ደስታ ሥርዓተ ቀብርን በማስመልከት የተሰጠ መግለጫ

መልአከ ፀሐይ ቀሲስ መኮንን ደስታ ባጋጠማቸው ህመም ምክንያት የህክምና ክትትል ሲደረግላቸው ቆይቶ ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።

የመልአከ ፀሐይ ቀሲስ መኮንን ደስታ ክቡር አስከሬንም ከሀገረ አሜሪካ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ገብቶ ስርዓተ ቀብራቸው እሁድ መጋቢት 15/2016 ዓ.ም በፈረንሳይ ለጋሲዮን በሚገኘው ገነተ ኢየሱ ቤ/ክ ከ4- 6 ሰዓት ይፈፀማል::

ይህንንም በማስመልከት ለመልዐከ ፀሐይ ቀሲስ መኮንን ደስታ መታሰቢያ ለማስቀመጥ ጊዜያዊ ኮሚቴ ተቃቁሞ እንቅስቃሴ ተጀምራል::
በዚህም መሰረት ይህንን የተቀደሰ አላማ ለመደገፍ የምትፈልጉ ከዚህ በታች በተጠቀሱት አካውንቶች ገቢ እንድታደርጉ እንጠይቃለን::


1000614508497 ንግድ ባንክ
179465639 አቢሲኒያ ባንክ
መልአከብርሃንሙላት ክበቤ
መልአከብርሃን ቄሰ ገበዝ ተቋመ ማህቶት
መምህር በላይ ወርቁ

የመልዐከ ጸሐይ ቀሲስ መኮንን ደስታ የቀብር አስፈጻሚ አብይ ኮሚቴ
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
🌾 አንተን ማሳዘኔ በደሌ ቢበዛ
ባታገኝም ከእኔ የጽድቅ መዓዛ

🌾 በምሕረትህ ብዛት አንተ ይቅር በለኝ
ሥራዬን አትይ እኔ ደካማ ነኝ።

🌾 ዘወትር አለቅሳለሁ ድካሜን አውቄ
መኖሬ ሲሰማኝ ከቃልህ ርቄ

🌾 በመንገድህ ምራኝ ፊትህን እንዳይ
ስለ እናት ብለህ ከኔ አትለይ

በዘማሪት ፋሲካ ድንቁ
« ይህን ዝማሬ በነፍሳችን እናኑረው »
°°°°°•°°°°°°•°°°°°°°°°°°°°°°°°
"ወዘያስተጋብዖ ለዝንቱ ዝማሬ ውስተ ነፍሱ ናሁ ረከበ ጸጋሁ ለእግዚብሔር ልዑል ዘይጸንዕ እምኵሉ ምግባራት እንተ ትረክቦ ☞ ይህን ዝማሬ በነፍሱ ያኖረ (በልቡ የያዘ) ሰው እነሆ ከተሰጠው ጸጋ ሁሉ የሚበልጥ ጸጋን ከክቡር እግዚአብሔር ዘንድ አገኘ"
ከመጽሐፈ መነኮሳት ክፍል ማር ይስሐቅ በ፳፱ኛው አንቀጽ ላይ ስለ አእምሮ መንፈሳዊ የተነገረ መልእክት ነው።

☞ ናስተጋብእ ለዝንቱ ዝማሬ በውስተ ነፍሰነ

የበገና መዝሙር በመምህር አቤል ተስፋዬ
Abel Begena አቤል በገና
#ላንዴ_እስከወዲያኛው

#ያንን_ሰው_ባረገኝ#ያቺንም_ሴት_በሆንኩ [፩]

🍁 ላንዴ እስከወዲያኛው
ያንን ሰው ባ’ረገኝ ፣ ያቺንም ሴት በሆንኩ
ላልወጣ ገብቼ ፡ ላልመለስ በሔድኩ
~~~

ምነው እሱን በሆንኩ
ያን የቀኝ ወንበዴ
ብመስለው ላ’ንድቀን : ባየው መንገዴ

ለመስረቅ አይደለም ንብረት ለመቀማት
አልያም ለመዝረፍ ሕይወትን ለማጥፋት

በዚያ መንገድማ

ከሱስ ብበልጥ እንጂ መች ከእርሱ አንስና
እኔን ታውቀኝ የለ …
የወንበዴ አለቃ ያ’ጢኣተኞች ዋና

ያ … ጸጸት ያዘለ
በዚያች የጭንቅ ሠዓት «አስበኝ» እያለ
ከመስቀልህ ጥላ ከሥር ስለዋለ
ካ’ዳም ቀድሞ ገባ ምሕረት ተቀበለ

እኔም እንደ ጥጦስ : ማታዬ እንዲያምር
ብትለኝ ምን አለ? …
«ከገነት ተጠለል: ዛሬን ከእኔ እደር»

🍁 ላንዴ እስከወዲያኛው
ያንን ሰው ባ’ረገኝ ፣ ያቺንም ሴት በሆንኩ
ላልወጣ ገብቼ ፡ ላልመለስ በሔድኩ
~~~

ደ’ሞ ይህን ተመኘሁ
ለንጊኖስን በሆንኩ
ያቺን ዕለተ ዓርብ : ቀራንዮ በዋልኩ

ለአመጽ አይደለም : ከከአይሁድ ለማበር
አልያም ለመውጋት : ያንተን ጎን በጦር

በዚያ መንገድማ

አንተን ለማሳመም: ማን እኔን መሰለ
ስንቴ እንዳቆሰልኩህ …
ስንቴ እንደወጋሁህ : እኔን ታወቀኝ የለ!

ያ …የጲላጦስ ጭፍራ
በመስቀል ላይ ሳለህ በሞት በመከራ
በጦሩ ቢወጋህ ሳያዝን ሳይራራ
ከቀኝ ጎን አፍስሰህ ውኃው ከደም ጋራ
በፍቅርህ ስታስረው ዐይኑን ስታበራ

ትዕግስትህን ጎትቶት ባንተ እንደ ተጠራ
ምናለ እንደው ’ኔንም …
ላንተ ብቻ እንዲያድር : ልቤን ብታበራ

🍁 ላንዴ እስከወዲያኛው
ያንን ሰው ባ’ረገኝ ፣ ያቺንም ሴት በሆንኩ
ላልወጣ ገብቼ ፡ ላልመለስ በሔድኩ
~~~

ላንዴ እስከወዲያኛዉ
https://youtu.be/GjZf3fPaeDs
╔​✞═•┉✽✥✥✽┉•═✞╗
❀.  #የማያሳፍር_ራቁትነት .
╚✞═•┉✽✥✥✽┉•═✞╝     

    ትናንት ሚያዝያ ፬ የመፈጠራቸው ነገ ሚያዝያ ፮ ደግሞ የዕረፍታቸውን መታሰቢያ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን የምትዘክርላቸው አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን በረከታቸው ይደርብን።

★ "ሀለዉ አዳም ወብእሲቱ (ሔዋን) እራቃኒሆሙ ወኢይትኃፈሩ ☞ አዳምና ሚስቱ ሁለቱም ዕራቁታቸውን ነበሩ፥ አይተፋፈሩም ነበር።"  【ዘፍ ፪ ፥ ፳፭】

ሁለት ዐይነት እርቃን አለ  የሚያሳፍር እና የማያሳፍር  የማያሳፍረው ራቁትነት ደግሞ የተፈቀደ እና ያለተፈቀደ ሊሆን ይችላል

ዛሬ ላይ ትውልዱ ባልተፈቀደ መንገድ መራቆቱን ሳያፍርበት እንደፋሽንም እንደ ክብርም ይቆጥረዋል በቀደመው ታሪክ የቃየል ልጆች ባልተፈቀደ መራቆት አምላካቸውን ሲያሳዝኑ እንደታዩ ቅዱስ ቀሌምንጦስ ገልጧል

"ርእዩ አዋልዲሁ ለቃየል በዘይሴኒ ሥነ ራእይ እንዘ የሐውራ ዕራቆን ዘእንበለ ሐፍረት  ☞ የቃየን ሴቶች ልጆች ተውበው እርቃናቸውን በመሆን ሳያፍሩ ሲንቀሳቀሱ እዩዋቸው" 【ቀሌ. ፫፥፵፱】

ታዲያ እንዲህ ባለው መንገድ ነውርን እንደ ክብር መራቆትንም  እንደ መሰልጠን ገላ መግለጥ  እንደፋሽን እያዩ የሚኖሩ መጨረሻቸው ኩነኔ እንደሆነ መጽሐፋችን ይመሰክራል 

“መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው።” 【ፊል ፫፥፲፱ 】

       ለሰው ልጅ አካሉን ገልጦና ሰውነቱን አራቁቶ ለመታየት የታወቀ (በቂ) ምክንያት ያስፈልጋል፤ ሠለስቱ ምዕት ለመታከም «የሚተኮስ» «የሚታገም» አካል ቢኖር አልያም ከጸበል ሊነከሩና ሊታጠቡ እንጂ በሌላውስ መንገድ በማንም ፊት እርቃን መታየት ክልክል ነው ብለዋል።

"ወዓዲ ተዐቀብ ከመ ኢትትዐረቅ እምልብስከ ቅድመ መኑሂ ዘእንበለ ዳዕሙ ሶበ ይረክበከ ምክንያት ለተዐርቆ።  ☞ ዳግመኛም በማንም ፊት ከልብስህ ራቁትህን እንዳትሆን ተጠበቅ፤ የምትራቆትበት ምክንያት ቢያገኝህ ነው እንጂ" 【 ሃይ አበው ፳፥፲፪ 】

መራቆት አለመዘጋጀት እፍረት ማሳየት የመዘናጋት በበጎ ምግባር ሳይተጉ የመኖር መገለጫ ነው።   “እነሆ፥ እንደ ሌባ ሆኜ እመጣለሁ፤ ራቁቱን እንዳይሄድ እፍረቱንም እንዳያዩ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።” 【ራእ  ፲፮፥፲፭】

        አካልን ራቁቶ  መታየት ቀርቶ  የተራቆተ አካልም ማየት ራሱ   ሲያስነቅፍ ፣ ሲያስቀጣና ሲያስረግም እናያለን
በዘፍጥረት መጽሐፍ ምዕራፍ ፱ እንደተገለጸው  በኖኅ ልጅ በካም  ላይ የደረሰው የዚህ ማሳያ ነው
" ኖኅም ገበሬ መሆን ጀመረ፥ ወይንም ተከለ። ከወይን ጠጁም ጠጣና ሰከረ፤ በድንኳኑም ውስጥ ዕራቁቱን ሆነ። የከነዓን አባት ካምም የአባቱን ዕራቁትነት አየ፥ ወደ ውጭም ወጥቶ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው። ሴምና ያፌትም ሸማ ወስደው በጫንቃቸው ላይ አደረጉ፥ የኋሊትም ሄደው የአባታቸውን ዕራቁትነት አለበሱ፤ ፊታቸውም ወደ ኋላ ነበረ፥ የአባታቸውንም ዕራቁትነት አላዩም። ኖኅም ከወይን ጠጁ ስካር ነቃ፥ ታናሹ ልጁ ያደረገበትንም አወቀ። እንዲህም አለ፦ ከነዓን ርጉም ይሁን፤ ለወንድሞቹም የባሪያዎች ባሪያ ይሁን። እንዲህም አለ፦ የሴም አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ፥ ከነዓንም ለእነርሱ ባሪያ ይሁን። እግዚአብሔርም ያፌትን ያስፋ፥ በሴምም ድንኳን ይደር፤ ከነዓንም ለእነርሱ ባሪያ ይሁን። " 【ዘፍ ፱፥ ፳ - ፳፯】

እንግዲህ የተራቆተን ማየት በዚህ መጠን የሚያስነቅፍ ከሆነ ተራቁቶ የመታየት ቅጣቱ የከፋ ስለመሆኑ አያጠራጥርም መራቆት የዲያቢሎስ የክብር ልጅ መሆን ነውና ፤ ሰይጣን ማለት በትርጉሙ እሩቅ እም ስብሐተ እግዚአብሔር  【ከእግዚአብሔር ክብር የተራቆተ】ማለት ነውና።

የተፈቀደ የማያሳፍርም  ዕርቃን የተባለውና በጥንተ ተፈጥሮ በአዳምና በሴቲቱ ኑሮ የተገለጠው የትኛው ራቁትነት ነው?

① ራቁትነታቸው ከዚህ ዓለም ልብስ ነው አለማፈራቸው ብርሃን ለብሰው ስለነበር ነው

ዓለማችን የሚያለብሰን ምድራዊና ቁሳዊ ጊዜአዊና ኃላፊ ትጥቅ ነው መንፈሳዊ ትጥቃችን  ግን ኅልፈትና ውላጤ ከሌለው ሰማያዊ  አባታችን የምንቀበለው ነውና  “የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ።”  【ኤፌ ፮፥፲፩】

“እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትህትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ፤ … በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት ” 【ቆላ ፫፥፲፪- ፲፬】


የዓለሙ ልብስ ንፍገት ጭካኔ ቅሚያ ትዕቢት ብልጣብልጥነት ችኩልነትና ጸብእን ነው። ይህን ለብሰው የሚዋጉንን  ሥጋውያኑን በሥጋ ጦር ድል መንሳት እንዴት ይቻለናል? 

የሳውልን የጦር ዕቃ የታጠቀ ካባ የለበሰና በአመጽ ወደተመላው እግዚአብሔርን ወደተገዳደረው ጎልያድ  በሥጋዊ መሳርያ ውጣ የተባለው  ብላቴናው ዳዊት መታመኛ ትምክህቱ መከታ ጉልበቱ እግዚአብሔር ስለበር በበትርና በኮሮጆው ጠጠር ዘምቶ  አመጸኛውን ሰልፈኛ ሰው ድል ነስቶታል። 
“ዳዊትም ሰይፉን በልብሱ ላይ ታጠቀ፥ ገናም አልፈተነውምና መሄድ ሞከረ። ዳዊትም ሳኦልን፦ አልፈተንሁትምና እንዲህ ብዬ መሄድ አልችልም አለው። ዳዊትም አወለቀ።” 【፩ኛ ሳሙ. ፲፯፥ ፴፱】

② አእምሮ ጠባያቸው ያላደፈ በተፈጥሮ እንደ ሕፃን  ስለነበሩ በዕርቃናቸው አይተፋፈሩም

ሕጻናት በንጽሕና እንደ መላእክቱ ናቸው የእነርሱ አእምሮ ጠባይ ማደፍ ስላላገኘው ሊቁም «ንጽሖሙ ለሕፃናት በሥጋሆሙ ወነፍሶሙኒ ዘእንበለ ሕማም» ይላል።

በዘመነ ሥጋዌው ክርስቶስ አምላካችንም እንደ ሕፃናት መሆን ለክብረ መንግሥቱ እንደሚያበቃ ነግሮናል

“ እውነት እላችኋለሁ፥ ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም።” 【ማቴ ፲፰፥፫】
መልሶም እንደነርሱ ላሉቱ ስለምትሠጥነና እነርሱኑ ለመሰሉት ስለምትገባዋ ዘልዓለማዊ ርስት ይህን ደግሟል
“ነገር ግን ኢየሱስ፦ ሕፃናትን ተዉአቸው፥ ወደ እኔም ይመጡ ዘንድ አትከልክሉአቸው፤ መንግሥተ ሰማያት እንደነዚህ ላሉ ናትና አለ፤”   【ማቴ ፲፱፥፲፬】 

ያለቂም ያለበቀል የሚኖሩ ክፋትንና ተንኮልን አልመው አስበው ሌላው ይጎዳበት ብለው የማይፈጽሙ እንደወረቀት የሠጧቸውን የሚቀበሉ እንደውኃም ቅርጻቸው ያረፉበትን ሥፍራ የሚመስሉ ልጆች ሕጻናትን መስሎ መኖር የሚማሩትን መያዝ በበጎ አርያነት የሚመሩትን መምሰል በእጅጉ ይገባል ፤
“ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።”【፩ኛ ጴጥ ፪፥፪-፫】
እንዲህ ያለው የሕጻናት ንጹሕ አይምሮ መያዝ አያሳፍርም።

③ ከልብሰ ኃጢዓት  ተራቁተው ኃፍረተ ነፍስ ሳይኖርባቸው ይኖሩ ነበር

ሰው ኃጢዓትን ለብሶ በደል ደርቦ ከመኖር በንሰሐ ቢራቆት ተኮንና የምታፍር ነፍስ የለችውም፤  ይልቁንም የልብ ንጽሕና ማጣት የሕሊና ሞት እንደሚያመጣበት አውቆ በኃጢዓቱ ምክንያት ያገኘውን ቁስለት የልቡናው ሰንኮፍ በንሰሐ ከከከበረች ነፍሱ ቢያርቅ መንገዱን በጥንቃቄ ቢመራና በፍርሐትና በመንቀጥቀጥ ለአምላኩ ቢገዛ በግራ ከሚቆምና ተኮንነው ከሚያፍሩ በመለየት መክበር ይቻለዋል።

“እናንተ ዓለመኞች ሴቶች ሆይ፥ ተጠንቀቁ፤ ተማምናችሁም የምትቀመጡ ሆይ፥ ተንቀጥቀጡ፤ ልብሳችሁን አውልቁ፥ ዕራቁታችሁን ሁኑ፥ ወገባችሁንም በማቅ ታጠቁ።”
  【ኢሳ ፴፪፥፲፩】
ሸክም የሆነብንን ኃጢዓት አራግፈንና በደላችንን ከላያችን በማስወገድ ራስን አንጽቶ  ልብን አቅንቶ  ሕይወትን መምራት በዙፋኑ ቀኝ ሳያፍሩ ወደመክበር  ያደርሳል።

“እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።”【ዕብ ፲፪፥፩-፪】

በማያሳፍር ራቁትነት በፊቱ ለመክበር ያብቃን የአቡነ አዳም የእምነ ሔዋን በረከታቸው በሁላችን ይደር!

ትምህርቱን  ከታች ባለው "ሊንክ በድምጽ ማግኘት ይችላሉ
   https://youtu.be/s0ipUnYfRkA?si=pDknHqI_wLvUBx_P
#ፈራሁ

ቀኑ ከረፈደ ከመሸብኝ መጣሁ
ደጃፍህ ላይ ቆምኩኝ እንዳልገባ ፈራሁ
በደሌን ሳትመዝን ግቢ ብትለኝም
ኃጢያቴ ከበደኝ አላራመደኝም




የሰው ዕድሜው እኮ አጭር ነው ጥቂት ነው
እንዴት ነው ሳላውቅህ ዘመኔ ያለቀው?
ጉብዝናዬን ዓለም ስቃ ተጫውታበት
እንዴት ብዬ ልርገጥ ደጅህን በድፍረት?
ፈራሁ ልግባ ወይ አልግባ
እንዴት ይመዘናል የአንተ ደም በእኔ እንባ ?



እኔ ፈራሁ እንጂ አንተ እኮ አታስፈራም
መምጣቴ ነው ደስታህ ፍቅርህ አይታማም
ሽምቅቅ አለች ነፍሴ መስቀልህን ሳየው
በደሌን አሰብኩት ደምህን እያየሁ
ፈራሁ ልግባ ወይ አልግባ
እንዴት ይመዘናል የአንተ ደም በእኔ እንባ ?


በንጽህናህ ፊት እንዴት እቆማለሁ
እንደ መላዕክቱ በምን እጋረዳለሁ
ራሴን መሸፈኛ ክንፍ የለኝም እኔ
ይታያል ኃጢያቴ የበደል ዕርቃኔ
ፈራሁ ልግባ ወይ አልግባ
እንዴት ይመዘናል የአንተ ደም በእኔ እንባ ?



ጠዋት እና ማታ ለመጣው አንድ ነህ
አምሽቶ ለገባም እኩል ትከፍላለህ
አብርሃም ወይስሐቅ በድንኳንህ ቢያድሩም
በአንተ መንግሥት ግን ከወንበዴ አይቀድሙም
ፈራሁ ልግባ ወይ አልግባ
እንዴት ይመዘናል የአንተ ደም በእኔ እንባ ?



https://youtu.be/yZRhhLT74rY?si=TplnxdckbmIF7GG2
. መፃጉዕ እና ኒቆዲሞስ
【 ዮሐ ፫ / ዮሐ ፭ 】
✥ °°°°°°°°°°°°°°°°°°° ✥
የዐቢይ ጾም ሳምንታት ከ፶ ሚሊየን ሕዝብ በላይ ባላቸው ተዋህዶን በሚያምኑ በጽባሓውያኑ ኦርቶዶክሳውያት አብያተ ክርስቲያን ዘንድ [ Eastern Christian churches adhering to Miaphysite Christology; Oriental Orthodox Churches】እኛ ከዘወረደ እስከ ሆሳዕና እንደምንዘክረው ከሆሳዕና በቀር በስያሜ የተለያየት መታሰቢያ ተሠጥቶት ይዘከራል
በብዙዎቹ ① ከብካበ ቃና ☞ ② ለምጻሙን ማዳኑ ☞ ③ ሽባውን ማዳኑ ☞ ④የከነናዊቷ ሴት እምነት ልጇን ማዳኑ ☞ ⑤ እኩለ ጾም/ በዓለ መስቀል ☞ ⑥ ደጉ ሳምራዊና ጀርባዋ የጎበጠች ሴት ☞ ⑦ ዘእውሩ ተወልደ ☞ ⑧ ሆሳእና ይታሰቡበታል።

በዚህ ውሥጥ በየሳምንታቱ የእነዚህ ታሪኮች መጻፍና መዘከር ምክንያቱ ታሪክ ‘አዋቆች’ ብቻ እንድንሆን አይደለም። ለምሳሌ በቅዱስ መጽሐፍ የቅዱሳን እና የርኩሳን፣ የቡሩካንና የርጉማን ፣ የጻድቃንና የኃጥዓን ታሪክ ሁሉ ተዘግቧል ምክንያቱ ደግሞ በሁለት መንገድ መረዳት ይቻላል። እንድንታነጽና እንድንገሠጽ

፩) የመልካም ሰዎች ታሪክ ⇨ ለጽናት በተስፋ ለመጽናናት
“በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና።” 【ሮሜ ፲፭፥፬】

፪) የአመጸኞች ታሪክ ⇨ ለተግሳጽ
“ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፥ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ።” 【፩ኛ ቆሮ ፲፥፲፩】

በዚሁ መንገድ ሊቃውንትና መና**ፍቃን ፣ የካዱና የጸኑ ፣ በጎ ሠሪዎችና ክፉ አድራጊዎች … ግለሰቦችም ታሪካቸው ተዘግቦ ተነግሯል። ዐላማው እንደቀድሞው ለሁለት ጥቅም ነው ፤

፩) መልካም አድራጊዎች እንድናውቃቸው ምሳሌና አብነት እንድናደርጋቸው
☞ "ወአእምርዎሙ ለእለ ከመዝ ⇨ እንግዲህ እንደነዚህ ያሉትን እወቁአቸው”
【፩ኛ ቆሮ ፲፮፥፲፰】

፪) ክፉ አድራጊዎችን ግን እንድናውቅባቸው ለመጠንቀቅ
☞ "ተዓቀቡ አንትሙሂ ወዑቅዎሙ ለከለባት ወዑቁዎሙ ለገበርተ እኪት ⇨ ከውሾች ተጠበቁ፥ ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፥ ።” 【ፊል 3፥2】

መፃጉዕና ኒቆዲሞስም በ፫ ክፍል ታሪክ የዚህ መንገድ አስተማሪዎች እንዲሆኑ በዐቢይ ጾም ሰንበታት የሚታሰቡ ግለሰቦች ናቸው

✧ ክፍል 【፩】 በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፫ እና ምዕራፍ ፭

ኒቆዲሞስ ☞ ወሐሎ አሐዱ ብእሲ ዘስሙ ኒቆዲሞስ ወመልአኮሙ ለአይሁድ
ወውእቱ መጽአ ኀበ እግዚእ ኢየሱስ ቀዲሞ ሌሊቱ

መፃጉዕ ☞ ወሐሎ አሐዱ ብእሲ ዘሠላሳ ወሰመንቱ ክረምቱ እምዘደወየ ወኪያሁ ርእዮ እግዚእ እግዚእ ኢየሱስ ይሰክብ ውስተ ዐራቱ

ልዩነት
ኒቆዲሞስ ወደ ጌታው የመጣ
መፃጉዕ ጌታው ወደ እርሱ የመጣ
ኒቆዲሞስ ቀድሞ በሌሊት የሚገሰግሰው ከጌታው እግር ስር ሊማር (ለትምህርት)
መፃጉዕ ቀድሞ ወደ መጠመቀቂያው ውኃ ለመውረድ ደጅ የሚጠና ምኞቱ ሊማር (ለምሕረት)
ኒቆዲሞስ ምሁረ ኦሪት ፣ ባለ ሥልጣንና ባለሀብት
መፃጉዕ ምሁረ ደዌ ፣ ሰው የሌለው ፣ ድኃ (ንብረቱ አልጋው ብቻ)
ኒቆዲሞስ ስሙ የተጠቀሰ መፃጉዕ ግን በህመሙ ደረጃ መገለጫው እንጂ በስም ያልተጠቀሰ 【የመፃጉን ስም አልተጠቀሰም መፃጉዕነት የደዌ መጽናት እንጂ ስም አለመሆኑን ልብ ይሏል ፤ ልክ እንደ አልአዛርና ነዌ (ባለጠጋው) 】

ስሙ አለመጠቀሱ ባለመታመኑ ነው፤ የጻድቃን መንገድና የታመኑ ሰዎች ስም መታወቁ በመንግሥቱ እውቅና እንዳላቸው ያስገነዝባልና
“ኄር እግዚአብሔር ለእለ ይትኤገስዎ በዕለተ ምንዳቤሆሙ ወያአምሮሙ ለእለ ይፈርህዎ ⇨ እግዚአብሔር መልካም ነው፥ በመከራ ቀንም መሸሸጊያ ነው፤ በእርሱ የሚታመኑትንም ያውቃል።”።【 ናሆም 1፥7】
“እስመ እግዚአብሔር የአምር ፍኖቶሙ ለጻድቃን ወፍኖቶሙሰ ለኃጥኣን ትጠፍእ ⇨ እግዚአብሔር የጻድቃንን መንገድ ያውቃልና፥ የክፉዎች መንገድ ግን ትጠፋለች።”
【 መዝሙር 1፥6】

✧ ክፍል ፪
በአይሁድ ክስና ውንጀላ ውስጥ
☞ መፃጉዕ ወደ አይሁድ ሔዶ ክርስቶስን ከሰሰ ☞ ለክርስቶስ መገደል ምክንያትም ሆነ
በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፭ ከቁጥር ፻፫ ጀምሮ እንደተነገው
«ዳሩ ግን በዚያ ስፍራ ሕዝብ ስለ ነበሩ ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ነበርና የተፈወሰው ሰው ማን እንደ ሆነ አላወቀም። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በመቅደስ አገኘውና፦ እነሆ፥ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ አለው። ሰውዬው ሄዶ ያዳነው ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገረ። ስለዚህም በሰንበት ይህን ስላደረገ አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር።

☞ ኒቆዲሞስ ግን አይሁድ ወደእርሱ በመጡ ጊዜ ጥብቅና የቆመና እንዳይያዝ የሞገተ ሆኑ ተገኝቷል
በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፯ ከቁጥር ፶ ጀምሮ
« ከእነርሱ አንዱ በሌሊት ቀድሞ ወደ እርሱ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ፦
⁵¹ ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን? አላቸው።»

✧ ክፍል ፫

መጻጉዕ ፦ ጌታውን በዕለተ ዓርብ በጥፊ መትቶ የመታበት እጁ ሰሎ ቀርቶ ከደዌው የታረቀ
ቀድሞ እንዲህ ሲል አስጠንቅቆት ነበር "ናሁኬ ሐየውከ ዑቅ ኢትአብስ ዳግመ እንከ ከመ ዘየአኪ ኢይርከብከ ⇨ ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በመቅደስ አገኘውና፦ እነሆ፥ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ አለው።” 【ዮሐ ፭፥፲፬ 】
እርሱ ግን "በዚያ ቆሞ የነበረው ከሎሌዎች አንዱ፦ ለሊቀ ካህናቱ እንዲህ ትመልሳለህን? ብሎ ኢየሱስን በጥፊ መታው።” 【ዮሐ ፲፰፥፳፪】

ኒቆዲሞስ ፦ በከበረና ዋጋው ውድ የሆነ ሽቱ ገዝቶ ለአምላኩ የመግነዝ ሥርዓት ፈጸመ፤ ከስውሩ ደቀመዝሙር ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር ሆኖ አምላኩን ሥጋ ከመቃብር አውርዶ አካሉን በአዲስ በፍታ ሸፍኖ ወደ አዲስ መቃብር ያኖረ
【 ዮሐ ፲፱፥፴፰ እስከ ፵】
«ከዚህም በኋላ አይሁድን ስለ ፈራ በስውር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረ የአርማትያስ ዮሴፍ የኢየሱስን ሥጋ ሊወስድ ጲላጦስን ለመነ፤ ጲላጦስም ፈቀደለት። ስለዚህም መጥቶ የኢየሱስን ሥጋ ወሰደ። ደግሞም አስቀድሞ በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ።
የኢየሱስንም ሥጋ ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከፈኑት።»

ኒቆዲሞስ በልሳነ ጽርእ ኒኮዴይሞስ "Νικόδημος" ይባላል በትርጉሙ ኒኮስ (νῖκος) እና ዴይሞስ (δῆμος) አገናኝቶ መዋዔ እም ሕዝቡ ይለዋል ከሕዝቡ ድል ያደረገ "victorious among his people" ይለዋል

ቤተክርስቲያናችን ሦስት ጊዜ ትዘክረዋለች
፩) የዕረፍቱን መታሰቢያ ነሐሴ ፩ ቀን ሠይማ
፪) በዐቢይ ጾም ደግሞ የ፯ኛ ሳምንት መጠሪያን ሠጥታ
፫) ለሁልጊዜው ደግሞ የቤተመቅደሱን አጥር ቅጥር እንደመግነዙ በመቁጠር የመግቢያ በሩን አዕማድ ለዮሴፍና ኒቆዲሞስ መታሰቢያ እንዲሆናቸው በማውሳት

የቅዱሱን የማታ ሰው የኒቆዲሞስን በረከት በሁላችን ላይ ያሳድርብን!

መልእክቱን በድምጽና በምስል ለመከታተልና ለመስማት በተከታዩን ሊንክ ታግዘው ማግኘት ይችላሉ
https://youtu.be/jkIgQ87W4Zw?si=LRACYvXhUAYJDQkp
╔​✞═•┉✽✥✥✽┉•═✞╗
❀………#ነገረ_ናርዶስ ………❀
╚✞═•┉✽✥✥✽┉•═✞╝

“ማርያምም ዋጋው እጅግ የከበረ የጥሩ ናርዶስ ሽቱ ንጥር ወስዳ የኢየሱስን እግር ቀባች፤ በጠጕርዋም እግሩን አበሰች፤ ቤቱም ከናርዶስ ሽቱ ሞላ።” 【 ዮሐ ፲፪፥፫】

ሊቃውንት በትርጓሜ “ይትባረክ እግዚአብሔር ዘሰመየ ሕማማተ ወልዱ ክብረ ወስብሐተ ☞ የልጁን ሕማማት ክብርና ምስጋና ብሎ የጠራ እግዚአብሔር ይመስገን” ይላሉ!
ለዚህ መነሻውቸው አፈወርቅ ነው፤ እግዚአብሔር ዐለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ሰውን ሰው ያዳነበት ጥበቡ የረቀቀ መሆኑን በተናገረበት ክፍል የገለጠው ነው። እንኳን መክበሪያችን ለሆነው ሰሙነ ሕማማት አደረሳችሁ! ?

በመልካም መዐዛው ምሽት እስኪ ጥቂት ስለነገረ ናርዶስ እያነሳን ከመጽሐፍ እና ከመምህራን አፍ የተገኘውን እንማማር

#ናርዶስ / #ልጥረ_ናርዱ
°°°°°°°°•••°°°°°°°°°°°°°
የዕብራይስጡን ( נֵרְדְּ ) ኔርድ መነሻ ያደርጋል በግሪኩ ደግሞ (πιστικός) ፒስቲኮስ ይለዋል። አንዳንዶች ግን ከግሪኩ ናርዶስ (νάρδος ☞ nardos) ጋር ያምታቱታል ያ ማለት ግን በሳይንሳዊ ስሙ ናርዶስ ስትሪካ [Nardus stricta] የሚባለውን የሳር ዐይነት የሚወክል ሲሆን እንደስንደዶ ያለ የምንጣፍ ሳር (matgrass) የምንለው ነው

ይህኛው ናርዶስ ግን ከላይ እንደተመለከተው በእብራይስጡ ኔርድ የሚለውን መነሻ ይዞ ናርዲኖን ይላል በትርጉም ልጥረ ዘናርዱ ☞ የናርድ ንጥር (spikenard) ማለት ነው። 【የጠራ የነጠረ የበራ የተጠበቀ ንጥር / ልጥር ይባላል!】ባለመልካም ሽታ ስለሆነ መዓዛው የተወደደ ቅባት ወይም በከፍተኛ ገንዘብ የሚገዛ ስለሆነ ዋጋውም የተወደደ ሽቱ ነው ናርዶስ !

የእኛውም ግዕዛችን ለወንድ ናርዳዊ ለሴት ናርዳዊት ብሎታል ይህም ከናርድ የተገኘ/ች እንደማለት ነው። በእርግጥ ናርድ የሚባለው የሽቱ / የቅባት መገኛ ተክል ነው፤ ታዲያ ያንኑ መነሻ በማድረግ ናርዶስ ሲል ከቅጠሉ ከቡቃያው ከአበባው የተገኘ የነጠረው ወይም የጣፈጠው መረቅ ሽቱ ማለት ነው የናርድ ናርዳዊ/ት እንደማለት።

ናርዶስ የሚለውን ለሰዎች በስመ ተጸውኦና በማዕረግ ዘርፍ የመጠቀም ልማድ አለ፤ በቤተክርስቲያናችን በዚህ ስም ከሚጠሩ ቅዱሳን መኻል ጥር ፬ ቀን የሚከበሩ አባ ናርዶስ የሚባሉትን የደብረ ቢዘን ገዳም መስተጋድል ቅዱስ አባት እናገኛቸዋለን። እሊኽም ያለበትር በጥላቸው እባብ የሚገድሉ በጽናት የሚጋደሉ ቅዱስ አባት እንደ ነበሩ መጽሐፈ ስንክሳር ይነግረናል።

ከቅዱሳኑም መካከል በሚስበው መልካም የምግባር መዓዛቸው እና በጸና የተጋድሎ ሕይወታቸው አርአያ የሆኑ ምሳሌነታቸውም የተመሰከረላቸው ናርዶስ እየተባሉ በሊቃውንት የተወደሱ አሉ። ለአብነት ያኽል ቅዱስ ኡራኤል ፣ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ ፣ አቡነ ሀብተ ማርያም ፣ ንጉሡ ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስን… ከብዙ በጥቂቱ ማንሳት ይቻላል።

【መልክአ ዑራኤል ቁ ፳፮】
ናሁ ጸገየ ጽጌ ማኅሌት
ወናሁ ፈረየ ፍሬ ስብሐት
ዘእምጒንደ መስቀል ተረክበ በቀራንዮ ገነት
ዑራኤል ናርዶስ ዘመዓዛሁ ሕይወት
ስብሐቲነ ያምዕዝ መዓዛሁ ከመ ዘሱራፊ ማዕጠንት።
ቅድመ ገጸ ሕያው ክርስቶስ ወእሙ ቅድስት
【እነሆ በቀራንዮ የተክል ቦታ ከጉንደ መስቀል የተገኘ ጽጌ የምስጋና አበባ አበበ። የምስጋና ፍሬ አፈራ። ዑራኤል ሆይ፤ ሕይወትን የሚያድስ መዓዛው የጣፈጠ ተክለ ናርዶስ ነውና ጼና መዓዛው በሕያወ ባሕርይ በክርስቶስና በክብርት እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ፊት እንደ ሱራፊ ማዕጠንት ባለ መዓዛ መዓዛው የምስጋናችንን መዓዛ ያጣፍጥልን አሜን።】

【መልክአ ሀብተ ማርያም ቁ ፳】
ሰላም ለመዛርዒከ ለድኩማነ ልብ ብላዝ
እለ ስፉሐት እማንቱ ለገቢረ ሠናይ ትእዛዝ
ሀብተ ማርያም ናርዶስ ዘደብረ ሊባኖስ አርዝ
እምንዕስከ ዘተሠቀይኮ እም ተክለ ሃይማኖት ውኂዝ
ይኩነኒ ተስፋ ለወልድከ ትኩዝ

【መልክአ ኢየሱስ ሞዐ ቁ ፳፯】
ሰላም ለእራኅከ አርአያ ክርስቶስ አቡሁ
ዘኢአፀወ ምሕረተ በላዕለ ነዳያን አኃዊሁ
ኢየሱስ ሞዐ ናርዶስ ለጽጌ ጽድቅከ በመዓዛሁ
ምስካብ ሥጋከ ለእስጢፋኖስ ጽርሑ
አናስረ ዓለም ታስግድ ወታገኒ ናሁ

【መልክአ ይምርሃነ ክርስቶስ ቁ ፲፩】
ሰላም ለእራኅከ ጒንደ አጻብዕ ወአጽፋር
ካዕበተ ዐሥር
ይምርሃነ ክርስቶስ ናርዶስ ዕፀ ጽጌ ገነት ሥሙር
ሠውረኒ በጽላሎትከ ኢይልክፈኒ ሐሩር
ወኢያጽልሙኒ ነፋሳት ወቁር

ዛሬ የሕማማት ረቡዕ የመልካም መዓዛ ቀን ነው፤ በዚህ የከበረ ሽቱ ባለሽቱዋ ማርያም (ማርያም እንተዕፍረት ) ጠረንዋን የሚቀይረውንና መልካም መዓዛ የሚያጎናጽፋትን ጌታችንን በእንባዋ አጥባ በጸጉሯ አብሳ የቀባችው ይህን ሽቱ ነበር ።

“እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት በነበረ ጊዜ፥ በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የከበረ ጥሩ ናርዶስ ሽቱ የመላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ መጣች፤ ቢልቃጡንም ሰብራ በራሱ ላይ አፈሰሰችው።” 【ማር ፲፬፥፫】

አልባስጥሮስ የሚለው【ἀλάβαστρον ☞ alabaster】 በልማድ ራሱ ሽቱ እየተባለ ቢገለጽም የናርዶሱ ማስቀመጫ ሙዳየ ዕፍረት ወይም የሽቱ መያዣ ቢልቃጥ/ብልቃጥ (perfume vase) መሆኑን መረዳት ይገባል።

«ወመልአ ቤተ መዐዛሁ ለውእቱ ዕፍረት» የዚህ የናርዶስ ሽቱ መዓዛ ቤቱን ሲያውደው የማርያም ታሪኳ ተለውጦ የይሁዳ ሌብነቱ ተገልጦ ታየ፤ የትዕቢተኞችን በደል የሚገልጥ የትሁታንን ኃጢዓት የሚውጥ ሆነ ናርዶስ!

የናርዶሱ ከየት መጣ ታሪክ ዳዊት ሰሎሞን ከተቀቡት የተረፈ ከልጅነት ወዙ ጋር ተደባልቆ የተቀመመ መሆኑን መተርጉማን እንደሚከተለው ያትቱልናል

ይህች ሴት ከራስ ጸጉሯ እስከ እግር ጽፍሯ ይህ ቀራት የማትባል መልከ መልካም ናት። መላ አካሏን የሚያሳይ መስታወት አላት ልብሷን አኑራ መልኳን አይታ
«መፍረስ መበስበስ ላይቀር እንዲህ ማማር ምን ይረባል የዚያስ የዚያስ ኃጢአት የሚያስተሠርይ ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቷል አሉ ለሱ የምቀባው ሽቱ ገዝቼ እሄዳለሁ»
ብላ በዝሙት የሰበሰበችው ሦስት መቶ ወቄት ወርቅ አላት ይዛ ሄደች። ዲያብሎስ ታመልጠኛለች ይህን ጊዜ ላስታት ብሎ ቀድሞ ከምታውቀው አንዱን መስሎ በአምሳለ ወሬዛ ሠናየ ላህይ ከመንገድ ቆያት። «ወዴት ትሄጃለሽ ?» አላት፤ ዝም አለችው «አንች ባትነግሪኝ እኔ እነግርሽ የለም " እንግዳ ወንድ መጥቶብሽ ለእሱ ልትቀቢው ሽቱ ልትገዥ ትሄሻለሽ» አላት «አዎን» አለችው።
«ይህም አይደለም ፍቅሩ ያላለቀለት ወንድ መጥቶብሽ ለዚያ የምትቀቢው ሽቱ ልትገዥ ትሄጃለሽ» አላት ፤ ደግማ «አዎን» አለችው
«ይህም አይደለም በጥቂት ገንዘብ ብዙ ገንዘብ የሚሸጥ ነጋዴ መጥቶብሽ ለእሱ የምትቀቢው ሽቱ ልትገዥ ትሄጃለሽ» አላት፤ ለሦስተኛ ጊዜ መልሳ «አዎን» አለችው !
«ሁሉንም አዎን አዎን ትያለሽ ማናቸው ነው ?»አላት።
       «እንግዳ ወንድ መጥቶብሽ አልክኝ ከዚህ ዓለም ልዩ የሚሆን ጌታ መጥቷል። ፍቅር ያላለቀለት ወንድ መጥቶብሻል ላልክኝ ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት እንዲል። የሰው ፍቅር አገብሮት ሊሞት መጥቷል። በጥቂት ገንዘብ ብዙ ገንዘብ የሚሸጥ ባለጸጋ ነጋዴ መጥቶብሻል ላልከኝ አዎን በጥቂት ትሩፋት ብዙ ክብር የሚሰጥ ኢየሱስ ክርስቶስ መጥተልና ለእሱ የምቀባው ሽቱ ልገዛ እሄዳለሁ» ብላ ስሙን ብትጠራበት እንደ ትቢያ በኖ እንደ ጢስ ተኖ ጠፍቶላታል።
       ከዚህ በኋላ ሃድኖክ የሚባል ባለ ጸጋ ነጋዴ አለ ሄዳ
«ለነገሥታት የሚገባ ሽቱ አምጣ» ብላ ሦስት መቶ ወርቅ ሰጠችው በሀገራቸው ሐሰት የለምና «ይህን ያህልስ የሚያወጣ የለኝም» አላት እሱ የማያውቀው እናቱ የምታውቀው ዳዊት ሰሎሞን ተቀብተውለት የተረፈ «ዕፍረተ ናርዱ» ነበር ከእንዲህ ያለ ቦታ አለ ሽጥላት ብላው ሽጦላት አምጥታ ቀብታዋለች። ይህ ብቻም አይደል ጌታ ግብፅ ሲወርድ ሰሎሜም ፈያታይ ዘየማን ይዘውት ሳለ ከልብሱ ላይ ወዛ ቢያጽቡት ሰፈፈ ይህን በዕቃ አኑረውታል ይህም ተጨምሮበታል።

ናርዶስ ባለመልካም መዐዛ ቅባት ብቻ ሳይሆን በብዙ መንገድ ፍቱን መድኃኒት ጭምር ነው። መድኃኒትነቱንም  ከልማዳዊ የባህል ሕክሞና ዘርፍ አንስቶ  በአያሌ ጥናት በተደገፉ የዘመናችን ሳይንሳዊ የሕክምና ምርምር ጭምር  የተመሰከረለት ነው።

በእርግጥ የዓለም የጤና ድርጅት እንዳረጋገጠው 80እጅ የሚሆነው የምድራችን ነዋሪ ባህላዊ ህክምናን ለጤናው መጠበቅ ምርጫው ያደርጋል [About 80% of the world population totally depends on traditional medicine systems for their primary health care needs]

በቀደመው ልማዳዊ / ባህላዊ ህክምና ጥናት (Ethnomedical research) ሚናው ላቅ ያለው የናርድ ተክል በዘርፈ ብዙ ጥቅሙ  ለረቀቀው የሳይንስ ጥናት (Scientific ethnomedical studies)  እንደመነሻ ሆኖ በብዙ ጥናት የተደገፈ የጤና ችግሮች  ማቅለያ በመሆን ለነገረ ሰብእና   ለመድኃኒቶች ግኝት ጥናት እገዛው ከፍ ያለ ነው።

በሳይንሳዊ ስሙ Nardostachys jatamansi [ዕፀ ናርድ ☞ የናርዶስ ተክል] ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት አጥኚዎች ይመሰክራሉ በተለይ በህክምናው ረገድ  ✧ሥሩ (Root) ✧የሥሩ ግንድ (Rhizome) ✧ግንዱ (Stem) ✧ቅጠሉ (Leaves) ✧አበባው (Flower) እና ✧መላ ተክሉ (Whole plant) እየተቀመመ ከጭንቀት የአእምሮ ሕመም እስከ ነቀርሳ (ካንሰር) ድረስ በመድኃኒትነት በብዙ ዘርፍ ያገለግላል።

በክኒን (Tablet) በሽሮፕ (Syrup) በሚዋጥ ባለሽፋን እንክብል (Capsule ) በቅባት (Oil ) በዱቄት (Powder ) እንዲሁም በሌሎች መንገዶች (Granules & Paste) እየተዘጋጀ በዘመናዊ ሕክምናውም ረገድ ለዘርፈ ብዙ ጤና መታወክ መፍትሄ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

አፈወርቅ በድርሳኑ ፬ኛ ክፍል የጠቀሰውን መነሻ ያደረግነውን መድረሻ አድርገን እናብቃ

       «እስመ እግዚኣብሔር ይትባረክ ስሙ ሰመየ ሕማማተ ወልዱ ክብረ ወስብሓተ እስመ ተሠግዎቱ ለወልድ ወሕማማቲሁ በእንተ ፍቅረ ሰብእ የዓቢ ወይፈደፍድ እምተፈጥሮተ ዓለም ወአምጽኦቱ እምኀበ ኢሀልዎ ውስተ ሀልዎ»

☞ ስሙ ይክበር ይመስገንና እግዚአብሔር የልጁን ሕማምና ሞት ክብር ምስጋና ብሎ ጠራው ስለ ሰው ልጅ ፍቅር ብሎ  ሰው መሆኑና መከራ መቀበሉ ይህን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ ከመፍጠሩ በእጅጉ  ይበልጣል! 
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በምክንያት ሲያስረዳ
   «ፍጥረተ ዓለም ይኤምር ኀበ  አፍቅሮቱ ሰብአ አላ ሕማማቲሁ ባሕቱ ይከብር ፈድፋደ። ☞ ዓለሙን መፍጠሩ ሰውን መውደዱን ያስረዳል። የሕማሙ ነገር ግን እጅጉን ልቆ የከበረ ነው»

በምን አበላልጦት እንዲህ ይላል ቢሉ
☞ ዓለሙን በመፍጠሩ አልደከመበትም፤ በማዳኑ ደክሞበታልና። ☞ ዓለሙን በመፍጠሩ አላዳነበትም መከራ በመቀበሉ  አድኖበታልና።
☞ ሲፈጥር ያየው የለም፤ መከራ ሲቀበል ሁሉ እያየው ነው፤

ማኅየዊትና መድኃኒት በምትሆን ሕማሙ ጠረናችንን በመልካም መዓዛው ለውጦ ለቁስላችን መድኃኒት ለሞታችን ሕይወት የሆነን ክርስቶስ ከበረከተ ሕማማቱ አያጉድለን! 

🌴 በቴዎድሮስ በለጠ ሕማማት ረቡዕ ምሽት ሚያዝያ  ፳፫ ቀን  ፳፻፲፮ ዓ.ም.  
📍 የምድር ጌጥ ደብረ ሊባኖስ
2025/07/04 09:43:14
Back to Top
HTML Embed Code: