Telegram Web Link
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - ‌🇴‌🇷‌🇹‌🇭‌🇴‌🇩‌🇴‌🇽 ‌🇹‌🇪‌🇼‌🇦‌🇭‌🇩‌🇴
Photo
ሰበር ዜና
+++++++++++++++++++++++++++++++++++++
በሕገ ወጡ ቡድን የጵጵስና ልብስ አልብሶ ሾሜዎታለሁ ካላቸው መነኮሳት መካከል ከኢየሩሳሌም የመጡት "አባ" ንዋየሥላሴ አክሊሉ ቅዱስ ሲኖዶስ የሰጠውን ዕድል በመጠቀም በመንበረ ፓትርያርክ በመገኘት አስኬማቸውንና አርዌ በትሩን ለሕጋዊዋ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በማስረከብ ቤተክርስቲያንንና ምእመናንን ይቅርታ ጠይቀዋል።
በይቅርታ ደብዳቤያቸውም ሰሞኑን በቅድስት ቤተክርስቲያናችን ከቅዱስ ሲኖዶሱ እውቅና ውጪ አዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ሲካኼድ ከኢየሩሳሌም መጥቼ ከተሾሙት አንዱ ነበርኩ።

በዚህ ምእመናንን ባሳዘነ ቅዱስ ሲኖዶስ ቃለ ውግዘት ባስተላለፈበት ሕገ ወጥ ሢመት ውስጥ ባለማወቅና ነገሩን ሳላጣራ የገባሁበት በመሆኑ በእጅጉ የተጸጸትኩና በዚህም ተግባር ያዘንኩ መሆኔን በይቅርታ ልብ ለመግለጥ እወዳለሁ። በመሆኑም በዛሬው ዕለት ቅዱስ ሲኖዶስ በሠየመው አቀራራቢና በይቅርታ ኮሚቴ አማካኝነት በቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት በተከፈተው የይቅርታና የምሕረት በር ወደ እናት ቤተክርስቲያኔ እና የመንፈስ ቅዱስ አባቶቼ እንዲሁም ምእመናን ለይቅርታ የቀረብኩ ስለሆነ ቋሚ ሲኖዶሱ በምልዓተ ጉባኤው ውሳኔ መሠረት ይቅርታዬን በአባትነት መንፈስ ይቀበለኝ ዘንድ በታላቅ ትህትና እጠይቃለሁ ብለዋል ።

EOTC TV
#ሰበር_ዜና
በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዘው የተለዩት በቀድሞ ስማቸው እነ አባ ሳዊሮስ በዛሬው ዕለት በጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ ተገኝተው የይቅርታ ደብዳቤ ማስገባታቸው ተዋህዶ ሚዲያ ማዕከል ዘግበዋል።
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
“ሰው ሆይ፥ መልካሙን ነግሮሃል፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፥ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፥ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን?” ☞ ሚክ. 6፥8

ድምጹን በተመለከተ፦ ዝምታው ራሱ ስለሚጮህ ብዬ ነው!

ጌታችንን በምናወድስበት ጸሎትም በልቡናው ንጽሕና ተወዳጅነቱ የተመሰከረለትን አበ ልሳናት ባህረ ጥበባት ቅዱስ ዮሐንስን የሚያነሳ ይህን እጅግ ጠቃሚ ተማጽኖ እናገኛለን።

ሰላም ለአፉከ ለዮሐንስ ዘሰዐሞ፣
ንጽሐ ሕሊናሁ ወልቡ ለዓይነ ፍትወትከ ሶበ አደሞ፣
ኢየሱስ ክርስቶስ መፍቀሬ የዋሃት እምተቀይሞ፣
ጸግወኒ ማዕፆ አፍ እንተ ይእቲ አርምሞ፣
ለትዕግሥትከ ከመ አእምር ዐቅሞ።

ጌታዬ ኢየሱስ ሆይ፤ ዮሐንስን ለሳመው መለኮታዊ አፍህ ሰላምታ ይገባል። የልቡናው ንጽሕና በፊትህ ተወዳጅነትን አግኝቷልና። ፈጣሪዬ ክርስቶስ ሆይ፤ ቅያሜ በአንተ ዘንድ ቦታ የለውም ቸርነት ግን የባሕርይህ ነው። ስለዚህ የትዕግሥትህን መጠን (ጥቅም) አውቅ ዘንድ። አፌም ክፉ ከመናገር ይቆጠብ ዘንድ የዝምታ ቁልፍ ስጠኝ።【መልክአ ኢየሱስ】
እንግዲህ በጎ ዘመን፡ መልካም ቀን፡ የተሻለ ጊዜ ለማየት አሁን ክፋትን እንቢኝ ተንኮልን ወዲያልኝ ብለን ብዙ እንጸልይ ብዙ ዝም እንበል፤  ባለቅኔው ሎሬት ከቆቃ የላኩትን ምክር እየሰማን እንደው ዝም ብለን እስኪ አብረን ዝም እንበል።

አብረን ዝም እንበል
ከሰው መንጋ እንገንጠል
ለአንድ አፍታ እንኳ እንገለል
በእፎይታ ጥላ እንጠለል
ዝም ብለን አብረን ዝም እንበል።
·
·
·
ከሰው ኳኳታ እንነጠል
ለአንድ አፍታ እንኳ እንገለል
በእፎይታ ጥላ እንጠለል
ዝም ብለን አብረን ዝም እንበል።【ጸጋዬ ገብረመድኅን 1961 ቆቃ。】

✧ "ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፥ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤" 【፩ጴጥ· ፫፥፲】

በመጨረሻውም መጨረሻ የምናገረው ነገር ቢኖር አለመናገርን ነው።

"አርምሞሰ ተፍፃሜተ ፍፃሜ ውእቱ" ይላል መጽሐፈ መነኮሳት !
. ሰሙነ ሕርቃል “Heraclius Week”
⊙∗⊕━━✦༒༒✦━━⊕∗⊙
(መንደርደርያ ሐሳብ)

ሀገር ለቀው፣ ባህር ጠልቀው፣ ገደል ወድቀው የሚሰደዱትን መከራ ጸንቶባቸው የሚቸገሩትን በዓለም ሁሉ ያሉ ምእመናን ለስዱዳኑ ተስፋ፣ ለምንዱባኑ ረዳኤ፣ ለሕዙናን ናዛዜ፣ ለግዱፋን ዐቃቤ ፣ ለጽዑራን መጽንዔ የሆናቸው ክርስቶስ በቸርነት ይድረስላቸው🙏

እንኳን ለዐቢይ ጾም ቀዳሜ ሳምንት (ዘወረደ፣ ሙሴኒ፣ ሰሙነ ሕርቃል…) በሠላም አደረሳችሁ!

☞ «መገለጫውን ሲያይ ነው እንጂ የጾሙትስ ሐዋርያት ናቸው»

☞ «ምንም አንድ አካል ሁለት ባሕርይ በማለት ብንለያይ ወረደ ተወለደ በማለት አንድ ነንና መጥተህ አጥፋልን»

☞ «ሰሙነ ሕርቃል ዘትከውን እምቅድመ ጾም ዐቢይ …»

#ሰሙነ_ሕርቃል ለጾመ እግዚእ የመሰናዶ ሳምንት [Preparation Weekinitial week] ተብሎ ተገልጧል። ከስምንቱ የዐቢይ ጾም ሳምንታት ከቅድስት ቀድሞ ለሚጾመው የዘወረደ ሳምንት አንዱ ምክንያት ሕርቃል ንጉሠ ሮም እንደሆነ ይታወቃል።

፲፪ኛው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ቅዱስ ዲሜጥሮስ ድኅረ አስተርእዮ ያለውን ፵ ዕለት ዐቢይ ጾም (A 40 day fast post Theophany) በ250 ዓ.ም. አውጆ በሮም በኢየሩሳሌምና በአንጾክያ በነበረችው አሐቲ ቤተክርስቲያን ቅቡልነት አግኝቶ ጸንቷል። ይህ ህርቃል ግን የተጨመረ በ616 እንደሆነ ይነገራል። ነገር ግን መጠሪያው የመሰናዶ ሳምንት ቀድሞ የነበረ እንጂ ሕርቃል በሚል እንዳልነበር መረጃ በማቅረብ የሚሞግቱ ቅብጣውያን አሉ። ኋላ ከ13ኛው ምዕተ ዓመት ወዲህ በኢብን አል አሰል በኩል ጾመ ሕርቃል (ሰሙነ ሕርቃል) በሚል ተለይቶ እንደተጠራ አስረጂ ጠቅሰው ይገልጻሉ።

(We find mention, of this week being referred to as “Hercules Week” as late as AD 1245 by Al-Safawy Le Ibn Al-Assal as being a fast distinct from the Great Fast proper )

በእኛም ዘንድ የጾሙን ምክንያት ሊቃውንቱም መጻሕፍቱም በተለያየ መንገድ ገልጠውታል።

፩) ጥንቱን ሐዋርያት ዐቢይ ጾምን ከእሑድ በቀር ቆጥረው ቢጎድልባቸው ቀድሞ ያለውን አምስት ቀን ከቁጥር ጨምረውታል።

፪) በኢየሩሳሌም የበራንጥያው ንጉሥ ፎቃ [Flavius Phocas Byzantine emperor ] ያደረሰባቸውን መከራ እና ጥፋት ያራቀላቸው ንጉሠ ሮም ሕርቃልን ምክንያት አድርገው ምዕመናነ ኢየሩሳሌም ስለጦሙት።

፫) የፋርስ ንጉሥ ክስራ [Kessra the king of Persia] በግብፃውያን ላይ ያደረሰውን መከራ ለማቅለል ንጉሥ ሕርቃል ዘምቶ ድል ቢነሳላቸው ሊቀ ጳጳሳቱ አባ እንድራኒቆስ በአዋጅ ከአጽዋማቱ ገብቶ እንዲቆጠር አድርገውታል።

፬) ንጉሥ ሕርቃል ግዙራን መንግሥቴን ይወስዳሉ ብሎ ቢሰጋ አይሁድን ዘምቶ ለመውጋት መሐላውን ቢያፈርስ የሮም ሊቃነ ጳጳሳት ቀሳውስት ዲያቆናት ምእመናን አንድነት ጹመውለታል። …

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ምዕላድ የሆነው መጽሐፈ ስንክሳር በመጋቢት ፲ ምንባብ ሥር ነገረ መስቀሉ የሚከብርባቸውን ሁለት ምክንያቶች እንዳሉ ይነግረናል። አንደኛ ዕፀ መስቀሉ በኢየሩሳሌም ተቆፍሮ የተገኘበት ሲኾን ኹለተኛው ደግሞ ዕፀ መስቀሉ በፋርስ ንጉሥ በምርኮ ከወረደበት በሮሙ ንጉሥ ሕርቃል አማካኝነት ወደ ቆስጠንጥንያ የተመለሰበት ነው ይለናል። በአርኬውም የመጨረሻ አንጓ ላይ
"… መስቀል ተረክበ እምዘተኀብዐ ወገብረ መድምመ
በኢየሩሳሌም ቅድመ ወበፋርስ ዳግመ።" ይላል።

ከምርኮ የተመለሰበትን መንገድ በሚተርከው ክፍል ጥንተ ነገሩ እንዲህ ተቀምጧል።

✧ በሮሜ ንጉሥ በሕርቃል ዘመን የፋርስ ሰዎች በግብጽ አገር በበላይነት ኖረው ወደ አገራቸው ሊመለሱ ወደዱ። ከሹማምንቶቻቸው አንዱ የጦር መኰንን ተነጥሎ ወደ ኢየሩሳሌም አልፎ ደረሰ ወደ ከበረ መስቀል ቤተ ክርስቲያንም ገባ። መስቀሉም በላዩ በተተከለበት ግንድ ፊት ታላቅ ብርሃን ሲበራ አይቶ ሊያነሣው እጁን ዘረጋ። እሳትም ወጥታ እጁን አቃጠለችው። ከክርስቲያን በቀር ማንም ሊነካው እንማይችል የመስቀልን የክብሩን ነገር ሰዎች ነገሩት። ሁለት ዲያቆናትንም ይዞ የከበረ መስቀልን እንዲሸከሙ አዘዛቸው። ከኢየሩሳሌምም ብዙ ሰዎችን ማርኮ ወደ አገሩ ተመለሰ። የፋርስ ሰዎች ኢየሩሳሌምን እንዳጠፏት ብዙዎች ሰዎችንም እንደማረኩና የከበረ የክርስቶስንም መስቀሉን እንደ ወሰዱ የሮም ንጉሥ ሕርቃል በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ። ስለርሱም #እንዲጾሙ_ምእመናንን_አዝዞ ወደ ፋርስ ዘምቶ ወጋቸው ብዙዎችንም ገደላቸው የከበረ ዕፀ መስቀልንም እየፈለገ በአገራቸው ሁሉ ዞረ ግን አላገኘውም። ያ ዲያቆናቱንና መስቀሉን የወሰደ መኰንን ከቦታዎች በቤቱ አንጻር ባለ በአንድ ቦታ ላይ ወስዷቸው ጥልቅ ጉድጓድ እንዲቆፍሩ አዝዞ በዚያ የከበረ መስቀልን አስቀበረ እነዚያንም ዲያቆናት ገደላቸው። ነገር ግን ያ መኰንን የማረካት የካህናት ወገን የሆነች በእርሱ ቤት የምትኖር አንዲት ብላቴና ነበረች። እርሷ የከበረ መስቀልን ሲያስቀብርና ሁለቱን ዲያቆናት ሲገድላቸው በቤቱ ውስጥ ሁና በመስኮት ትመለከት ነበር ወደ ንጉሥ ሕርቃልም ሒዳ መኰንኑ ያደረገውን ሁሉ ነገረችው። ይህንም ንጉሥ ሰምቶ እጅግ ደስ አለው ያቺ ብላቴናም መራችው ከእርሱም ጋር ብዙ ሠራዊት ሁኖ ኤጲስቆጶሳትና ካህናትም ነበሩ። ወደ ቦታውም እስከምታደርሳቸው ያቺን ልጅ ተከተሏት ቆፍረውም የከበረ ዕፀ መስቀልን አገኙ ከዐዘቅቱም አወጡት ንጉሡና ሠራዊቱም ሰገዱለት። በልብስ መንግሥቱም አጐናጸፈው ታላቅ ክብርንም አከበረው ከሠራዊቱ ጋር እጅግም ደስ አለው ።

ይህንኑ በሚደግፍ ተወዳጁ ሊቅ የእስሙናዩ ቅዱስ ሳዊሮስ (Severus of El Ashmunein ﺳﺎﻭﻳﺮﺱ ﺍﻷﺷﻤﻮﻧﻴﻦ ‏) በድርሳኑ "ንሕነሰ ንጸውማ ንሥሓ በእንተ ሕርቃል ንጉሥ ሶበ ቀተሎሙ ለአይሁድ ወበልዐ ኪዳነ ዘተካየዶሙ ወዝንቱ ዕውቅ በዜና ሕርቃል ንጉሥ " ሲል ከነምክንያቱ አስረድቷል።

(እኛስ የምንጾመው ስለ ንጉሡ ሕርቃል ንስሐ ነው፤ አይሁድን በገደለ ጊዜ መኃላውን አፍርሷልና (ቃሉን በልቷልና) ይኽም በንጉሥ ሕርቃል ዜና የተነገረ ነው)

የመጽሐፈ ሕግ ወሥርዓት [ፍትሐ ነገሥት] ሐተታ ደግሞ መነሻው ከጥንት ሐዋርያት እንደሆነ በማውሳት ሌሎች እንደ ምክንያት የሚጠቀሱ ሁለት አጋዥ ታሪኮች አክሎ ያስቀምጥልናል።

በማከልም ከዐቢይ ጾምና ከረቡዕ ዓርብ (ጾመ ድኅነት) ውጪ የተጨመሩት አጽዋማት መነሻቸው የግብፃውያን ቀኖና እንደሆነም ፍትሐ ነገሥቱ ይጠቁማል።

«ወአጽዋምሰ አካልዓን እለ ተወስኩ ላዕለ ዝንቱ ወተሠርዑ በቤተ ክርስቲያን ቅብጣዊት። ወእምኔሆሙ ዘይከውን በአምሳለ ጾም ዐባይ በተጠናቅቆ። ወይእቲ ስሙነ ሕርቃል ዘትከውን እምቅድመ ፆም ዐቢይ»

(በዚህ ላይ የተጨመሩ ሌሎች ጾሞች ግን በግብፃውያኑ ቤተክርስቲያን የተሠሩ ናቸው፤ ከእነርሱም እንደ ዐቢይ ጾም በመጠንቀቅ የሚሆን አለ። ይህችውም ከዐቢይ ጾም ቀድማ የምትሆን የሕርቃል ጾም ናት)

በተለየ የሕርቃልን ጾም ሲያብራራ ደግሞ
⇨ ይህችውም ከዓቢይ ጾም አስቀድማ የምትሆን ስሙን ህርቃል ናት መገለጫውን ሲያይ ነው እንጂ የጾሙትስ ሐዋርያት ናቸው ሕልሙን ያየ ናቡደነፆር ሲሆን “ራእየ ዳንኤል” እንዲል
ታሪክ ጌታ ከቅድስት ሰኞ ጀምሮ እስከ ዓርብ ኒቆዲሞስ ከቆመ ሳያርፍ ከዘረጋ ሳያጥፍ ዓርባ ቀን በትህርምት ጾሟል ሐዋርያት እሑድ እሑድን አውጥተው ቢቄጥሩ ጎደለባቸው አስቀድመው አምስት ቀን ጹመው ለስብከተ ወንጌል ይፋጠኑ ነበርና …

የኋላውንም ሁለት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ታሪኮች ደግሞ እንዲህ ያብራራልናል።

① በኢየሩሳሌም ፎቃ በሮም ህርቃል ነገሠ ፎቃ በኢየሩሳሌም ባሉ ምእመናን መከራ አጸናባቸው ምንም አንድ አካል ሁለት ባሕርይ በማለት ብንለያይ ወረደ ተወለደ በማለት አንድ ነንና መጥተህ አጥፋልን እኛ ላንተ እንገዛለን ብለው ወደ ሕርቃል ላኩበት እሱም ከአይሁድ ጋራ ጨዋታ መሐላ ነበረውና ቸል ብሎ ተዋቸው ኋላ ግን "ግዙራን ይነሥእዋ ለመንግሥትከ" የሚል ራእይ አየ።

መንግሥቱን የሚወስድበት ኡመር ወልደ አድ እንደሆነ ባያውቅ "ግዙራን የተባሉ ሌላን እለ? አይሁድ አይደሉምን" ብሎ "ያን የላካችሁብኝ ነገር አልረሳሁትም ነገር ግን ሐዋርያት ነፍስ የገደለ መላ ዘመኑን ይጹም ብለዋል ጾሙን ብፈራ ነው እንጅ" አላቸው ያንድ ሰው ዕድሜ ቢኖር ሰባ ሰማንያ ዘመን ነው ይህንንስ እኛ እንጾምልሃለን አሉት መጥቶ አጥፍቶላቸዋል በኢየሩሳሌም ያሉ ምእመናን አምስት አምስት ቀን ተካፍለው ጹመውለታል ያላወቁት አንድ ጊዜ ጹመው ትተውታል ያወቁትን ግን ቀድሞም ሐዋርያት ጹመውታል ብለው ሥራት አድርገው በዓመት በዓመት የሚጾሙት ሁነዋል!

② የሮም ሊቃነ ጳጳሳት ቀሳውስት ዲያቆናት ምእመናን ጹመውታል የሮሙን ንጉሥ ከፋርሱ ንጉሥ ተጋብቶ ሲኖር ሚስቱን በድሎ ሰደዳት ሒዳ ለአባቷ አንተን ያህል አባት እያለኝ በድሎ ሰደደኝ አለችው። እሱም ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ብሎ ሒዶ እኔ ከሀገሩ ጠብ የለኝም ጠቤ ካንድ ሰው ነው ጠላቴን ስጡኝ ባትሰጡኝ ግን ጠቤ ከናንተ ጋራ ነው አላቸው ቢትወደዱ «ፎቃ» ይባላል ባንድ ሰው ምክንያት ብዙ ሰው እናስጠፋለን። አውጥተን እንስጥ እንጂ አላቸው። ማን ይነግሣል አሉት እኔ እነግሣለሁ አላቸው አወጥተው ሰጡት ፎቃ ነገሠ።

የጥጦስን የአስባስያኖስን ዘመን ለመመለስ በሮም ባሉ ምእመናን አገዛዝ አጸናባቸው ኋላ ባሪያውን ለማይገባ ገረፈው ህርቃልን ቢትወደድነት ሹሞት ነበረና ሔዶ በማይገባ ገረፈኝ ብሎ ነገረው አትገድለውም አለው ማን ይነግሣል አለው እኔ እነሣለሁ አለው ጊዜ አይቶ ገደለው ህርቃል ነገሠ። ከዚህ በኋላ የሮም ምእመናን መጥተው እኛም ከወገኖቻችን ካነገሥክልን ብድራችንን እንድንመልስ አይሁድን አጥፋልን ብለው አማሉት እሱም ከአይሁድ ጋራ ጨዋታ መሐላ ነበረውና ቸል ብሎ ተዋቸው ኋላ ግን ግዙራን ይነሥእዋ ለመግሥትከ የሚል ራእይ አየ ግዙራን የተባሉ ሌላ እለን አይሁድ አይደሉምን ብሎ ያን ያላችሁኝን ነገር አልረሳሁትም ነገር ግን ሐዋርያት ነፍስ የገደለ መላ ዘመኑን ይጹም ብለዋል ጾሙን ብፈራ ነው እንጂ አላቸው ያንድ ሰው ዕድሜ ቢኖር ስባ ሰማንያ ዘመን ነው። ይህነንስ #እኛ_እንጾምልሃለን አሉት መጥቶ አጥፍቶላቸዋል በሮም ያሉ ምእመናን አምስት አምስት ቀን ተካፍለው ጹመውለታል ያላወቁት አንድ ጊዜ ጹመው ትተውታል ያወቅቱ ግን ቀድሞውም ሐዋርያት ጹመውታል ብለው ሥርዓት አድርገው ባመት ባመት የሚጾሙት ሁነዋል።

ወደ እኛ የደረሰው እንዴት እንደሆነ ለማሳየትም ለመሰናዶው ሳምንት የሕርቃልነቱን ስያሜ ተቀብለው ከዐቢይ ጾም ቀድሞ ባለው ሳምንት እንዲዘከር በድንጋጌ ያጸኑ በዘመነ ሕርቃል በእስክንድርያ የነበሩ ፴፯ኛው ፓትርያርክ አቡነ አንደራኒቆስ መሆናቸውን ዜና ጳጳሳቱ ይነግረናል።

"Pope Adronicus, the 37th Patriarch of Alexandria, acknowledged this request. From that time, “Heraclius Week” began to be observed."

በአጋዥ የታሪክ ማነጻጸሪያ ደግሞ በስንክሳራችን ዕረፍቱ ጥር ፰ የሚዘከረው በቅዱስ ማርቆስ መንበር ፴፯ኛው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ቅዱስ አንደራኒቆስ በዘመኑ የፋርስ ንጉሥ ክስራ [Kessra the king of Persia] ከሮሙ ንጉሥ ህርቃል ጋር ስላደረገው ጦርነትና እስክንድርያ ባሉ ምእመናንም ላይ ይደርስ ስለነበረው መከራ ተከታዩን ታሪክ ይነግረናል።

«በሹመቱም ወራት ፀሐይን የሚያመልክ የፋርስ ንጉሥ ክስራ ተነሣና የሶርያንና የፍልስጤምን ከተሞች ወርሮ ዘረፋቸው፡፡ ወደ ግብጽም መጥቶ እስክንድድርያ ከተማ ደረሰ፡፡ በዙሪዋ በመነኮሳት የተሞሉ ሰባት መቶ ገዳማት ነበሩ፡፡ እነርሱም ገንዘብ ያላቸው በተድላ የሚኖሩ ነበሩ፡፡ ስለዚህም በእነርሱ ላይ እግዚአብሔር ሥልጣንን ሰጥቶት ገዳማቱን አፈረሰ፡፡ እነርሱንም ሸሽተው ካመለጡት በቀር ሁሉንም ገደላቸው፡፡ ገንዘባቸውንም ሁሉ ማረከ፡፡

የእስክንድርያ ሰዎችም ንጉሥ ክስራ ያደረገውን ባዩ ጊዜ የከተማውን በር ከፈቱለት፡፡ እርሱም ‹ይህችን አገር በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁ አታፍርሳት፣ በውስጧ ያሉትን ብርቱዎች ግደላቸው-ዐመፀኞች ናቸውና› እንደሚለው በሕልሙ አየ፡፡ በዚህም ጊዜ የሀገሩን ንጉሥ ይዞ ካሠረው በኋላ ለሀገሩ ሰዎች ‹‹በጦር ሠራዊት አደራጃቸዋለሁና ከ18 ዓመት ጀምሮ ያሉትን ብርታት ያላቸውንም ሁሉ ሰበስቡልኝ፣ ለእያንዳንዳቸው ደመወዛቸውን 20 የወርቅ ዲናር እከፍላለሁ›› አላቸው፡፡ ሕዝቡም ሁሉ እውነት ወርቅ የሚቀበሉ መስሏቸው 8 ሺህ ብርቱዎችን ቆጥረውና መዝግበው በሰጡት ጊዜ ንጉሡ ክስራ ሁሉንም በሰይፍ ገደላቸው፡፡ ወደላይኛው ግብጽ በመሄድም ኒቅዮስ ደርሶ ሰባት መቶ በሥራቸው ክፉ የሆኑ መነኮሳትን በሰይፍ ገደላቸው፡፡ የሮም ንጉሥ ሕርቃልም የፋርሱ ንጉሥ ክስራ ያደረገውን በሰማ ጊዜ ሠራዊቱን ሰብስቦ መጥቶ ንጉሥ ክስራን ከነሠራዊቱ ሀገሩንም ጭምር አጠፋቸው፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የአባ እንድራኒቆስ ገድሉ እጅግ ያማረ ነበር፡፡ … »

ሕርቃል ከአርመናውያን ቤተሰቦች በ575 ዓ.ም. በቀጰዶቅያ ተወልዶ በ641 ዓ.ም. በቁስጠንጥንያ ያረፈ በእምነቱም የመለካውያኑ (Chalcedonian Christianity) ተከታይ የነበረ የሮማውያን ንጉሥ ቢሆንም ካቶሊካውያኑ የእኛውን ንጉሥ አፄ ካሌብን [Saint Elesbaan] በቅድስና እንደሚዘክሩት «ምንም አንድ አካል ሁለት ባሕርይ በማለት ብንለያይ ወረደ ተወለደ በማለት አንድ ነንና መጥተህ አጥፋልን» ብለው ደጅ ለጠኑት በእስክንድርያ እና በኢየሩሳሌም ለነበሩ ምእመናን ባለውለታ በመሆኑ ኦርቶዶክሳውያኑ የልዩነት ድንበሩን ጠብቀው ሲያከብሩት ኖረዋል።

የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ሰላም ፣ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ወላዲተ አምላክ ማርያም ፍቅርና የኢየሱስ ክርስቶስ የረድኤቱ ሀብት የቅዱስ መስቀሉም ሞገስ ሁል ጊዜ ለዘለዓለሙ ከሁላችን አይራቅ!

ከሰሙነ ሕርቃል በረከት ያሳትፈን!

🌴 reposted from ቴዎድሮስ በለጠ መጋቢት ልደታ ፳፻፲፫ ዓ.ም. ተጻፈ
የንስሃ መንገዶች
በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

አምስት የንስሃ መንገዶች አሉ ። የተለያዩ ቢሆኑም ቅሉ ሁሉም የሚያደርሱት ግን ርስት መንግስተ ሰማያት ነው ። እነርሱስ ምን ምን ናቸው ? ያልከኝ እንደሆነ እንድህ ብየ እመልስልሃለሁ፦

፩ኛ • የመጀመሪያው መንገድ "የራስን ኃጢአት ማመን፣ መጥላትና ማውገዝ ነው።

ይኽውም ልዑል ቃል ኢሳይያስ "እንድትጸድቅ መጀመሪያ ኃጢአትህን ተናገር እንዳለው" (ኢሳ 43 ፥26 )፤ ክቡር ዳዊትም "በደሌን አልሸፈንኩም፤ ለእግዚአብሔር መተላለፌን እንግራለሁ አልሁ ፤ አንተም የልቤን ኃጢአት ተውኽልኝ" ብሎ እንደተናገረ መዝ 31፥5 ስለዚህ አንተም ስለ ሰራኽው ኃጢአት እራስህን ውቀሰው። በዚህ እግዚአብሔር ይቅር እንዲልህ ታደርገዋለህና። ይህ ብቻ ሳይሆን ስለ ኃጢአቱ እራሱን የሚወቅስና ኃጢአቱን የሚኮንን ሰው በተመሳሳይ ኃጢአት በቀላሉ አይወድቅምና። ስለዚህ በጌታ የፍርድ ዙፋን የሚወቅስህ እንዳይኖር ዛሬ እውነተኛ ወቃሽ በኾነው ሕሊናህን አንቅተህ በራስህ ላይ ወቃሽና ከሳሽ አድርገህ ሹመው። ይህ አንዱና ደገኛው መንገድ ነው ።

፪• ሁለተኛው የንስሐ መንገድ ደግሞ
የወገኖቻችንን በደል ይቅር ማለትና በበደሉህ ላይ ቅሬታና ቂም አለመያዝ ነው።

እንዲህ ስናደርግ "ለሰወች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ  እናንተንም ደግሞ ይቅር ይላችኋል" እንዲል እኛ በጌታችን ላይ ያደረግነውን በደል ይቅር እንባላለንና። ማቴ 6 ፡14

፫• ሦስተኛውን የንስሃ መንገድ መንበረ ጸባዖት የደርስ በትጋትና በጥልቅ ስሜት የሚደረግ "ከልብ የመነጨ ጸሎት ነው"

ጨካኙ ዳኛ እንዲርፈድላት ያደረገችው ያች መበለት እንዴት እንዲፈርድላት እንዳደረችገው አታያትም? ( ሉቃ 18፥3) አንተ ግን ሩኅሩኅና  መሐሪ የኾነ ጌታ ነው ያለህ። እርሷ በጠላቶቿ ላይ እንዲፈርድላት ነው የጠየቀችው፤ አንተ ግን እምትጠይቀው ስለራስህ ድኅነት ነው።

፬• አራተኛ መንገድ አለ እርሱም "ምጽትዋ ነው " ይህም እጅግ በጣም ታላቅ የኾነ ኃጢአትን የሚስተርይ ኃይል አለውና።

ናቡከደነጾር ኃጢትን ንቅስ ጥቅስ አርድጎ ወደ ክኅደት ሁሉ በገባ ጊዜ እንድህ ብሎታልና፦ "ንጉስ ሆይ ! ምክሬ ደስ ያሰኝህ ኃጢአትህም ለጽድቅ በደልህን  ለድኾች በመመጽወት አስቀር" (ዳ.ን 3፥27 ) ይህ ቸርነትና ሰውን መውደድስ ምንስ ይስተካከለዋል? እንዴት ያልከኝ እንደሆነ ስፍር ቁጥር የሌለውን ኃጢአት ከሰራ በኋላ ከዚያ ኹሉ በደል በኋላ እንደርሱ ለሆኑ ሰወች ርኅራኄን ቢያደርግ ከተገዳደረውና ከተጣላው አምላክ ጋር መታረቅ እንደሚችል ቃል ተገብቶለታልና ።

፭• አምስተኛው መንገድ "እንዲሁም ትሕትናና እራስን ማዋረድ ኃጢአትን ያደክማል"

ይህንንም ቀራጩ ያረጋግጥልናል አይኖቹን ወደ ሰማይ ለማንሳት እንኳንስ እስኪፈራ ድረስ በታላቅ ትሕትና ራሱን ባዶ ባደረገ ጊዜ "ጻድቅ ሆኖ ሄደ ተብሏልና ።(ሉቃ 18፥13) ስለዚህም ምንም ምግባር ቢኖርህም እንኳን በደልህን ከመናር በቀር በጎ ምግባርህን አታስበው። ያን ጊዜ እግዚአብሔር የበደል ሸምክህን ያራግፍልሃል።

ስለዚህ እነዚህን መንገደኞች ተመላለስባቸው እንጅ ሰነፍ አትኹን ።
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - ‌🇴‌🇷‌🇹‌🇭‌🇴‌🇩‌🇴‌🇽 ‌🇹‌🇪‌🇼‌🇦‌🇭‌🇩‌🇴
Photo
"የቤተ ክርስቲያን በዓል እንዲረበሽ እና ምእመናን ሕይወታቸውን እንዲያጡ እንዲሁም እንዲጎዱ ያደረገው ከመንግሥት የጸጥታ መዋቅር የተተኮሰው አስለቃሽ ጭስ እና ጥይት መሆኑ ለሁሉም የታወቀ ሆኖ እያለ ጉዳዩን ወደ ሌላ አካል ለማላከክ የተሄደበትን ርቀት ቤተ ክርስቲያን በፍፁም የምትቀበለው አይሆንም፡፡" ብፁዕ አቡነ ሄኖክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

በየካቲት ፳፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ላይ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች አማካኝነት የተፈጸመውን ሕገ ወጥ ድርጊት አስመልክቶ ከአዲስ አበባ ሀገረ ሰብከት የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሀገራችን ኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ ጀምሮ ያለችና መንግሥትን ያጸናች፣ የራሳቸው የጽሑፍ ቋንቋ ካላቸው ጥቂት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንድትሆን ፊደል ቀርፃ ያስተማረች፣ መንግሥት የአረንጓዴ አሻራን መርሐ ግብር ከማስጀመሩ ከሺህ ዓመታት በፊት የአካባቢ ጥበቃን ስትሠራ የኖረችና አሁንም በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፣ ገዳማትና አድባራት የአካባቢ ጥበቃ ሥራን የምትሠራ፣ ዘመናዊ ትምህርት ከመጀመሩ ከሺህ ዓመታት በፊት ሥርዓተ ትምህርት ቀርፃ ያስተማረችና የሀገር መሪዎችን፣ የስነ ህንፃ ባለሙያዎችን፣ የመድኃኒት አዋቂዎችንና ተመራማሪዎችን ያፈራች ቤተ ክርስቲያን ከመሆኗም በላይ ተቋም መሥርታ ለዘመናት የተቋምን ምንነት ያስተማረች ራሷ ሀገር የሆነች ናት፡፡

በተለይም ደግሞ መላው የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት በተያዙበት፣ አውሮፓውያን ኢትዮጵያንም ለመቀራመት ተስማምተው በፋሺስቱ የኢጣልያ መንግሥት አማካኝነት ሀገራችንን በወረረበት ጊዜ የንጉሱን የክተት አዋጅ ተከትሎ ሕዝቡ ለነፃነቱ እንዲዋደቅ የሀገር ፍቅር ለምእመኗ ያስተማረች በመሆኑ እና የንጉሱም ጥሪ ሀገራዊ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖትን የመጠበቅ ጥሪም የነበረ በመሆኑ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ንጉሱን እንዲከተል ከማድረጓም በላይ ታቦተ ቅዱስ ጊዮርጊስን በካህናቱ አጅባ የጦር ግንባር ድረስ በመዝመት፣ ምእመኑን እና ህዝቡን በማጽናናትና ጸሎተ ፍትሀት በማድረግ በዓድዋ ጦርነት ኢትዮጵያ ሀገራችን ድል እንድትቀዳጅና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም የነፃነት አርማ እንድትሆን በማድረግ ትልቁን የታሪክ ድርሻ እንደምትወስድ የታወቀ ሀቅ ነው፡፡
ከዚህ የድል በዓል በኋላም ኢትዮጵያ በነፃነት በቆየችባቸው ዓመታት ሁሉ ይህን የአድዋ የድል በዓል ቤተ ክርስቲያን የሰማእቱን ቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦተ ሕግ ከመንበረ ክብሩ ወጥቶ ሕዝቡን በመባረክ፣ ካህናቱና ምእመናኑ በታላቅ ምሥጋና እና መዝሙር በመላ ሀገሪቱ ስታከብረው የኖረች፤ ወደፊትም እየፈጸመች የምትጸናበት አኩሪ ታሪኳ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ይህ በዓል ላለፉት ጥቂት ዓመታት የድል በዓል መሆኑ ቀርቶ የጠብ እና የጥላቻ በዓል እየሆነ መምጣቱ ቤተ ክርስቲያንን በእጅጉ ያሳዘነ ተግባር ሆኗል፡፡ በተለይም ትላንት የካቲት ፳፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በተከበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ ክብረ በዓል በቤተ ክርስቲያን ላይ የአድዋ የድል በዓልን አስታኮ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተፈፀመው እጅግ አሳዛኝ ድርጊትን ግን ቤተ ክርስቲያን ሰምታና አይታ በዝምታና በሐዘን ብቻ የምታልፈው ጉዳይ አልሆነም፡፡

በየካቲት ፳፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም የቅዱስ ጊዮርጊስ ክብረ በዓል ለማክበር ህዝቡ ከየቤቱ ተሰባስቦ ከጠዋቱ ፫፡፲፭ ላይ ታቦተ ሕጉ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ የጆርጅያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት ከመንበረ ክብሩ ወጥቶ ዑደት ካደረገና ሕዝቡን ባርኮ በዐውደ ምህረቱ ላይ ከቆመ በኋላ ሊቃውንቱ ያሬዳዊ ወረብ በማቅረብ ላይ እንዳሉ ከመንግሥት የጸጥታ መዋቅር የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማዊ ልዕልናን ተላልፈው በሰሜን በኩል ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ፪ ጊዜ በተኮሱት አስለቃሽ ጭስ ምክንያት የንግሥ በዓሉ በመረበሹ በዓሉ ተቋርጦ ከጠዋቱ ፬ ሰዓት ላይ ታቦተ ሕጉ ወደ መንበሩ ተመልሷል፡፡ በዚህም ምክንያት እስከአሁን በደረሰን መረጃ መሠረት በቤተ ክርስቲያን ቅጥር ከፍተኛ ረብሻ በመፈጠሩ ምክንያት ፩ ምእመን በተተኮሰው አስለቃሽ ጭስ ታፍነው ሕይወታቸውን ማጣታቸውን፣ አገልጋይ ካህናት አባቶች፣ ምእመናን እና ምእመናት ከፍተኛ የሆነ አካላዊ እና ሥነ ልቡናዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ከ፲፭ ያላነሱ የሰንበት ትምህርት ቤት አገልጋይ ተማሪዎች በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል፡፡

ይህ ድርጊት ከተፈፀመ በኋላም መንግሥት የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብርና ልዕልና በመዳፈር በቤተ ክርስቲያን ላይ ይህን በደል የፈፀሙ የጸጥታ መዋቅር አካላትን ለሕግ ያቀርባል፣ እንደ መንግሥት ኃላፊነቱን ይወጣል ብለን ብንጠብቅም የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ቢሮ በዓሉን አስመልክቶ በዕለቱ ባወጣው መግለጫ ችግሩን የፈጠሩት አካላት ‹‹የአደባባይ በዓሉን ለመረበሽ ሲያቅታቸው በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሚደረገውን ሃይማኖታዊ በዓል ለመረበሽ ሞክረዋል፡፡ የጸጥታ መዋቅሩ ችግሩን ለመቆጣጠር በወሰደው እርምጃ ጉዳቱን ለመቀነስ ችሏል›› ሲል የችግሩን ሁኔታ ገልጧል፡፡

በዚህ መግለጫውም ላይ አሁንም ችግሩ የሌሎች ቡድኖች እንደሆነና የቤተ ክርስቲያኒቱን በዓል የረበሸው የእነዚህ አካላት እንቅስቃሴ ነው በማለት የሰጠው መግለጫ በቦታው ላይ ከነበረው እውነታ በእጅጉ የራቀ እና ድርጊቱ የተወሰኑ ግለሰቦች ሳይሆን የመንግሥት እውቅና ያለው መሆኑን እንዲሁም መንግሥት ችግሩን ለማረም እና መፍታት ፍላጎት የሌለው መሆኑን እንድንረዳ አድርጎናል፡፡ የቤተ ክርስቲያን በዓል እንዲረበሽ እና ምእመናን ሕይወታቸውን እንዲያጡ እንዲሁም እንዲጎዱ ያደረገው ከመንግሥት የጸጥታ መዋቅር የተተኮሰው አስለቃሽ ጭስ እና ጥይት መሆኑ ለሁሉም የታወቀ ሆኖ እያለ ጉዳዩን ወደ ሌላ አካል ለማላከክ የተሄደበትን ርቀት ቤተ ክርስቲያን በፍፁም የምትቀበለው አይሆንም፡፡

የመንግሥት የጸጥታ አካል በቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ምእመናን ላይ ጉዳት ሲያደርስ እና የቤተ ክርስቲያንን ክብር ሲያጎድፍ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ በጥር ፩ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም በቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን በተሰበሰቡ ምእመናን ላይ በቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ብዙ ምእመናን እንዲጎዱ የተደረገ ሲሆን በጊዜው መንግሥት ይህን ድርጊት በፈጸሙ አካላት ላይ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ልክ እንደአሁኑ ችግሩ የሕገ ወጦች ነው በማለት ለድርጊቱ እውቅና ሰጥቶት አልፏል፡፡ በዚህ ድርጊት መንግሥት በጸጥታ መዋቅሩ ውስጥ ያሉ እና መንግሥትንና ሕዝብን እንዲሁም ተገቢ ያልሆነ ያለመግባባት የሚያባብሱትን ግለሰቦች እና አመራሮች ለይቶ እርምት ከመውሰድ ይልቅ ሕዝብና መንግሥትን ሆድና ጀርባ የሚያደርግ ተግባሩን አስፋፍቶ ቀጥሏል፡፡

በመሆኑም መንግሥት ለዘመናት የኖረች እና ከግማሽ የሀገሪቱ ሕዝብ በላይ የያዘችን ቤተ ክርስቲያን ክብርና ልዕልና በሚዳፈር መልኩ በተፈጸመው ሕገ ወጥ ተግባር ላይ የተሳተፉ እና ይህን ድርጊት የፈጸሙ የጸጥታ አካላትና እንዲፈፀም ያዘዙ የመንግሥት ኃላፊዎችን በ፲፭ ቀናት ጊዜ ውስጥ ለይቶ በሕግ እንዲጠየቁ እንዲያደርግ እና ይህንንም ለቤተ ክርስቲያኒቱም ሆነ ለሕዝበ ክርስቲያኑ በግልጽ እንዲያሳውቅ እንዲሁም በተለመደው የሐሰት ውንጀላ በዓላችንን በማክበር ላይ እያሉ የመንግሥት የጸጥታ አካላት በፈፀሙት ሕገ ወጥ ተግባር ምክንያት በተፈጠረው ግርግር መነሻት የታሰሩ ምእመናንን ያለምንም ቅድመ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - ‌🇴‌🇷‌🇹‌🇭‌🇴‌🇩‌🇴‌🇽 ‌🇹‌🇪‌🇼‌🇦‌🇭‌🇩‌🇴
Photo
ሁኔታ እንዲፈቱ እየጠየቅን ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ቤተ ክርስቲያን መብቷን ለማስከበር ወደ ቀጣይ እርምጃዎች የምትገባ መሆኑን በአክብሮት እያሳወቅን ይህንንም ድርጊት ተከታትሎ የሚያሳውቅ እና የሚያስፈጽም የሕግ ባለሙያዎች ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደሥራ እንዲገባ የሚደረግም መሆኑን ጭምር እናሳስባለን፡፡

በዚህ ሕገ ወጥ ድርጊት የሊቀ ሰማዕቱን የቅዱስ ጊዮርጊስ ክብረ በዓል ለማክበር በመምጣት ሕይወቱን ላጣው ልጃችን እግዚአብሔር ነፍሱን በአብርሃም፣ በያዕቆብና በይስሐቅ እቅፍ ያኑር፣ ለቤተሰቦቹም መጽናናትን ያድልልን እያልን ቀላልም ሆነ ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባችሁ የቤተ ክርስቲያን የጭንቅ ቀን ልጆች ደማችሁን እና መከራችሁን እንደ ሰማእታት ዋጋ ይቆጥርላችሁ ዘንድ ጸሎታችን ነው፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
የካቲት ፳፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ኢትዮጵያ
፩. የዛሬዋ ምኩራብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፤

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የአምላክ ሥጋና ደም የሚፈተትባት፤ ሰዎች ዘለዓለማዊ ሕይወትን የሚያገኙባት የሐዲስ ኪዳን ምኩራብ ናት። ጌታችን በቅፍርናሆም ምኩራብ የሕይወት እንጀራ እርሱ ስለመሆኑ ያስተማረበት በዚህ በሦስተኛው ሳምንት በሰፊው ይነገራል። በዘመናችንም ‹‹የአባቴ ቤት የጸሎት ቤት ይሆናል።›› በሚል የድኾችና የምስኪኖች መጠጊያ እናት ተብላ የተነገረላት ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በዘመናችን የንግድ ቤትና የወንበዴዎች ዋሻ ወደ መሆን የተሸጋገረች ትመስላለች። በርካታ ድሆች፣ አረጋውያንና መበለቶች፣ እናት አባት የሌላቸው ሕፃናት፣ ድውያንና አካል ጉዳተኞች በደጇ የወደቁ ቤተ ክርስቲያን የእነዚህን ድሆችና ምስኪኖች ጩኸትና ዋይታ አላየኹም አልሰማውም በሚል የንግድ ቤት ግንባታ ውድድር ውስጥ ገብታለች። በኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምግባረ ሠናይ ድርጅትን በማጠናከር ረገድ እጅግ አነስተኛ ነው፤ ሌላው ቀርቶ በደጋጎቹ ነገሥታት የተቋቋሙ ምግባረ ሠናይ ድርጅቶች የሚከታተላቸው አካል በማጣታቸው የፈረሱ አሉ፤ በመፍረስ ላይ የሚገኙም አሉ፤ ለምሳሌ ከመቶ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረ ጥንታዊው የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ የአረጋውያንና የእጓለ ማውታ ድርጅት ‹‹አለ›› በማይባልበት ደረጃ እጅግ በመዳከም ላይ ይገኛል፤ ዛሬ የአዲስ አበባ አብያተ ክርስቲያናት ታላላቅ ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ገንብተዋል፤ የሚገርመው ሬስቶራንትና ሱፐር ማርኬት እንጂ ግን አንዳቸውም ላይ የምግባረ ሠናይ ተቋም አናገኝም። ይህ እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ መሄዳችንን ያሳያል፤ እውነቱን ለመናገር ከመቶ ዓመታት በፊት ያሉትን መሪዎችን እንኳን የመውቀስ ሆነ የማወደስም ሞራል የለንም፤ ምክንያቱም በዘረኝነት በነቀዘ በሙስና በቆሸሸ በእኛ አንደበት መወደሳቸው ለእነርሱ ውርደት እንጂ ክብር አይደለምና። እንደ ሕንድና እንደ ግብጽ ያሉ አኃት አብያተ ክርስቲያናትን ተሞክሮ ብንወስድ ለምሳሌ በሕንድ ከ፵፪ በላይ በቤተ ክህነት የሚተዳደሩ የምግባረ ሠናይ ድርጅቶች አሏቸው። በአሁኑ ጊዜ አረጋውያንን የሚጦር እጓለ ማውታ ሕፃናትን ተንከባክቦ የሚያሳድግ ምግባረ ሠናይ በቤተ ክርስቲያናችን ስም ተጠናክሮ መቀጠል ሲገባው ያሉትን ከማዳከም በላይ ምን ግፍ አለ፤ በተለይ በአንዳንድ አህጉረ ስብከት ያሉ የመምሪያ ኀላፊዎች በሙስና ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር እየተመቻመቹ ቤተ ክርስቲያን ለምግባረ ሠናይ ብላ ይዛ ያቆየችው ሀብትና መሬት በሌሎች አካላት እንድትነጠቅ ከፍተኛ ደባ ተፈጽሞባታል። የቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ዓላማ መሆን የነበረበት ሕንጻ እየገነቡ ለሆቴልና ለሸቀጣ ሸቀጥ መሸጫ ማከራየት ሳይሆን በሃይማኖታቸው ምክንያት ከቤታቸው ለተገፉ፤ ሃይማኖታችሁን ካለወጣችሁ ማደሪያችሁን ፈልጉ እየተባሉ በገዛ ልጆቻቸው ዛቻ ለሚፈጸምባቸው ከቤታቸው ለተገፈተሩ ጧሪ ቀባሪ ላጡ አረጋውያን መርጃ እንዲሆን ማድረግ ነበር። (ምንጭ ‹‹ሰቆቃወ ቤተ ክርስቲያን›› ታኅሣሥ ፳፻፲፪ ዓም)

ቤተ ክርስቲያን ዙሪያዋን በንግድ ቤትና በሱቆች ተንቆጥቁጣ በገንዘብ ባሕር ውስጥ እየዋኘች፣ ሀብትና ንብረቷ በአስመሳዮች፣ በወንበዴዎች፣ በሙሰኞችና በአጭበርባሪ ነጋዴዎች እየተዘረፈ ባለበት በዚህ ወቅት በደጇ ለወደቁ ድሆችና ምስኪኖች ምእመናኖቿ ከሚጥሉላቸው የሳንቲም ሽርፍራፊ የልብስ እራፊ በስተቀር ቤተ ክርስቲያኒቱ ለእነዚህ ድሆች ዘላቂነት ያለው ሥራ ከመሥራት ይልቅ የመቃብር ሥፍራ እንኳን ሁሉ ሳይቀር እያፈረሰች የንግድ ቤትና ሱቆችን እየገነባችና እያስፋፋች ትገኛለች። ለመሆኑ በከተማችን የትኛው ቤተ ክርስቲያን ነው ለአረጋውያን መጦሪያ፣ ለድኾች መርጃ የሚሆን ተቋም የገነባው። በጣት የሚቆጠሩ አብያተ ክርስቲያናት ለትውልድ ማፍሪያ የሚሆን የትምህርት ተቋማት መገንባታቸው እሙን ነው። እነዚህም ቢሆኑ በአብዛኛው በራቸው ክፍት የሚሆነው ኪሳቸው ዳጎስ ላሉት እንጂ ለድሆችና ረዳት ለሌላቸው አይደለም። ሆኖም ግን የቤተ ክርስቲያንን አጥር በንግድ ቤት ከሞሉት እነዚህኞቹ ሳይሻሉ አይቀርም፤ ቢያንስ ትውልድ እየቀረጹ ነውና።
በከተማይቱ እምብርት ባሉ አንዳንድ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የመዝናኛ ስፍራዎችና ጭፈራ ቤቶች እንኳን ለኻያ አራት ሰዓት የማይቋረጥ አገልግሎት በሚሰጡበት በዚህ ዘመን የዘመናችን ቤተ ክርስቲያን ግን እህል ውኃ የማያሰኝ ቆመጥና ነፍጥ ባነገቱ ዘበኞቿ በሯ ከምሽት ሰዓት በኋላ በትላልቅ ሰረገላና መሸጎሪያዎች ተቆልፈው ድሆች ከግቢዋ ተገፍትረው እየወጡ ለሌሊት ብርድና ቁር ተጋልጠው እንዲኖሩ ይፈረድባቸዋል። እናም እነዚህ ድኾችም በሺዎች በሚቆጠር ብር በሚከራዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ የንግድ ማዕከላት በረንዳ ላይ ወድቀው ኑሮአቸውን በምሬት ይገፋሉ።
ባሕረ ጥበባት ቅዱስ ያሬድ የዘመነ ሐዲስ ምኩራብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላዘነው መጽናናትን ለተጨነቀው መረጋጋትን የምትሰጥ፤ ደስታን የምታስታጥቅ ኀዘንን የምታርቅ እንደሆነች ሲዘምርላት እንዲህ አለ ‹‹በከመ ይቤ እግዚእነ በነቢይ ጊሥዋ ለቤተ ክርስቲያን እስመ ኵሉ ዘጌሠ ኀቤሃ ተአሥዮ ፍሥሐ። ጌታችን በነቢዩ አድሮ እንደተናገረው ቤተ ክርስቲያንን ገሥግሡባት፤ ማልዱባት ወደ እርሷ የገሠገሠውን ደስታ ትሰጠዋለችና›› በማለት ዘወትር ማልደው ወደ እርሷ የሚሄዱ ምእመናን ተጽናንተው ኀይል አግኝተው ተደስተው እንደሚመለሱ ተናግሯል። (ደብረ ዘይት ዘሐሙስ)
ሊቀ ጉባኤ ጌታሁን ደምፀ
2025/07/04 10:31:27
Back to Top
HTML Embed Code: