Telegram Web Link
ስሙ ታቦቱ "እግዚኣ ሰንበት ⇨ ጌታዋ ሰንበት" እየተባለ ይጠራል በሌላ መጠሪያ እግዚአ ሰንበት አልያም እግዚኣ ለሰንበት ቢልም የሰንበት ጌታ ራሱ ሰንበት ነውና የዘይቤ እንጂ የምሥጢር ተፋልሶ የለውም። መጽሐፍ "ለሊሁ ርስቶሙ ⇨ርስታቸው እርሱ ራሱ ነው" ባለው መምህራን ሰንበታችን ሥሉስ ቅዱስ ዕረፍታችን እርሱ ራሱ እግዚአብሔር ነው ይላሉ። «ሰንበት ለሊሁ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ» እንዲል፤
በመልክአ እግዚአብሔር አብ ላይም

እሰግድ ለመለኮትከ ዘአእረፎሙ ለአይሁድ
በዕለተ ሰንበት ሳብዒት እምተግባረ አእጋር ወእድ
እግዚአብሔር አብ ሰንበተ ክርስቲያን እሑድ
አግዕዘኒ እምቅኔ ሥጋ ለአብጽሖ ንስቲት ሰጊድ
ኀበ ኁልቆ ዕሥራ ወክልኤቱ ስሙያን አንጋድ

【ከእግርና ከእጅ ሥራ ፡ በሰባተኛው ቀን ሰንበት
አይሁድን ላሳረፋቸው ፡ ልስገድ ላንተ መለኮት
እሑድ የተባልክ እግዚአብሔር አብ ፡ የክርስቲያኖች ሰንበት
ለሥጋ ከመገዛት ነጻ አውጣኝ ፡ እንድሰግድልህ በጥቂት
‘ገናናው አባት አንተ ነህና’ ፡ ለሃያ ሁለቱም ፍጥረት】

ስለዚህ የሰንበት ታቦት/ጽላት የዕረፍት ታቦት ወደ ዕረፍት መግባትን ተስፋ በማድረግ ራሱ ማረፊያ!/ዕረፍት የሆነ የሰንበት ጌታ እንዳረፈባት የሚዘከርበት መታሰቢያ ነው።

የትኛው ሰንበት የሚለውን ለዕለተ ረቡዕ ባሳደርነው የመወያያ ነጥብ ላይ አንስተን የምንመካከር ይሆናል።

እግዚአብሔር ቢፈቅድ ብንኖር እንደቸርነቱ ነገ ማክሰኞ ደግሞ ለዚሁ ሠዓት ሰንበትና ስግደትን በሚመለከት ተከታዩን ጥያቄ እናያለን፦

☞ «በዕለተ ሰንበት የተከለከለው የጸጋ ስግደት እንጂ የአምልኮ ስግደት አይደለም» በሚል የሚሠጠው የጊዜው ‘ትምህርት’ እንዴት ይታያል ?

በቴዎድሮስ በለጠ መጋቢት ፲፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ·ም·
ክፍል ፪] ሰንበትና ስግደት
━━━━ ✦✿✦ ━━━━

ለዛሬው በክፍል ሁለት በያዝነው ቀጠሮ መሠረት እንደ እግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ከነገረ ሰንበት [Sabbatarianism] ትምህርታችን መኻል ተከታዮቹን ጥያቄዎች መነሻ አድርገን ጥቂት ሐሳቦችን እናነሳለን

☞ «በዕለተ ሰንበት የተከለከለው የጸጋ ስግደት እንጂ የአምልኮ ስግደት አይደለም» በሚል የሚሠጠው የጊዜው ‘ትምህርት’ እንዴት ይታያል ?

ዛሬ መጋቢት ፲፪ ቀን ሰጊድ ከሚከለከልባቸው የግዝት በዓላት መካከል የቅዱስ ሚካኤል ወርኃዊ መታሰቢያ በዓሉ ነው። እንኳን አደረሳችሁ 🙏

ወደ ሐሳቡ ከመዝለቃችን አስቀድሞ ትናንት የሰንበትን ታቦት በሚመለከት ካነሳነው መልእክት ሁለት ተጨማሪ ፍሬ ነገሮችን እናክል

«በሳማ ሰንበት» ታሪክ ውሥጥ ቤተክርስቲያኑ በ1026 ዓ.ም. የተመሠረተ የሰንበት ታቦት ያለውና በሰንበተ ክርስቲያን ስም የተቆረቆረ ቀዳሚና ብቸኛ ገዳም እንደነበረ የቦታው ታሪክ ይነግረናል፤ ክብረ በዓሉም በዕለተ ደብረ ዘይት እንደሚውልና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፓትርያርክና («ፕትርክና») አሁን ያለው አዲሱ ሕንጻ ተገንብቶ ቅዳሴ ቤቱ ሲከብር "ብሔረ ሕያዋን እግዚአ ለሰንበት" በሚል ተሰይሟል። 【የቤተክርስቲያን መረጃዎች ገጽ 95】ታቦቱ ግን እንደቀድሞ ታቦተ ሰንበት መሆኑን ልብ ይሏል።

ቤተክርስቲያናችን ቅዳሴ ማርያም ብላ የቅዱስ ሕርያቆስን ቅዳሴ እንደምትጠራው ሁሉ የቅዱስ አትናቴዎስን ቅዳሴ ደግሞ ቅዳሴ ሰንበት በማለት የሰንበትን ክብር ትገልጥበታለች ።

በዚህ ምስጋናም ልክ እንደ ሕያው ቅዱስ መስቀሉ ቅድስት ሰንበትን ለተማጽኖ ሕያውነቷን አምነን እንማጸናታለን ደጅ እንጠናታለን፤ መስቀሉን በመስተብቍዕ "ናስተበቊዖ ለዕፀ ቅዱስ መስቀል ጽኑዓ ሥልጣን" 【መጽሐፈ ሰዓታት】 እንዳልነው ሁሉ ሰንበትንም "ኦ ዛቲ ዕለት ሰንበተ ክርስቲያን ቅድስት ሰዓሊ ለነ አስተምሕሪ ኀበ እግዚአብሔር አምላክነ ⇨ ይህች ቅድስት የክርስቲያን ሰንበት ምን ትደንቅ ፤ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ዘንድ ለምኚልን፤ ስለእኛ አማልጂ" 【ቅዳሴ አትናቴዎስ】 እንላታለን፤ የሰንበት ጌታ ስለቅድስት ሰንበት ብሎ ይማረን 🙏

ወደ ዛሬው ጉዳይ እንሻገር ፦ የዕለተ ሰንበት የአምልኮ ስግደት።

በዘመናችን ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ከሚገዳደሩ ፈተናዎች መኻል ቀዳሚውን ቦታ የሚይዘው አዳስ ሕግ አርቃቂ ፣ ጠበል አፍላቂ ፣ ፈዋሽ አጥማቂ፣ ተኣምር አድናቂ ፣ ባህታዊ አጽዳቂ… መብዛቱ እንደሆነ ይሰማኛል።

ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ አንዳንድ ምዕመናን በግዝት በዓላትና ከቆረቡ በኋላ አብዝተው በመቅደስና በአውደ ምሕረት አካባቢ አብዝተው ሲሰግዱ ማየት እየተለመደ መጥቷል፤ የሚያስቆማቸው ሲገኝ ለማስተማር እየቃጣቸው «የአምልኮ ስግደት ነው በበዓላት ምክንያት የማይቋረጥ ነው» የሚል ሙግት ያቀርባሉ! ትምህርቱን ከመምህር እገሌ ከአጥማቂ እገሌ አገኘን ከሚል በቀር ማስረጃ እንኳ የላቸውም።

በሥርዓተ አምልኮ ውሥጥ ለመንፈሳዊ ተግባራችን ሁሉ ምንጭ የሚሆኑን መነሻዎቻችን ተከታዮቹ ናቸው
☆ መጽሐፍ ቅዱስ በተለይም ፰ቱ የሥርዓት መጻሕፍት ፣ የሕገ ቤተክርስቲያን ድንጋጌ/አዋጅ [እንደ ፍትሐ ነገሥት ፣ ቀኖና ጉባኤያት ፣ ሥርዓተ አበው፣ ሕንጻ መነኮሳት ፣ አንቀጸ ንሰሐ ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ የየዘመናት ውሳኔ ፣ ሕገ ቤተክርስቲያንና ቃለ ዓዋዲ] በዋናነት ይጠቀሳል ከቤተ ጉባኤ መምህራን [የቤቱ አብነት የሚያትታቸው ሥርዓቶች)] በየቦታው ሊለያይ የሚችል ሥርዓተ ገዳም።

ከዚህ ውጪ ግለሰባዊ መመሪያና በካህን የሚታዘዝ ቀኖናን በመቀበል እደወል ሕግና የጋራ ሥርዓት አድርጎ ክብረ ሰንበትን መሻር የሚያስቀጣ ነው።

በሰንበት የሚቻል ስግደት አለ ወይስ የለም? የሚለውን ከማብራራታችን በፊት ጥቂት ጉዳይ ስግደትን በሚመለከት እናንሳ

ሰጊድ ማለት በቁሙ መስገድ መዋረድ ማጐንበስ መንበርከክ መድፋት በግንባር መውደቅ ግንባርን ምድር አስነክቶ መሬት ስሞ መመለስን የሚገልጽ ሲሆን ጸሎት ለማቅረብ ፣ ክብር ለመሥጠት ፣ ሰላምታ ለመለዋወጥ ፣ ሰውነትን ለመቅጣት የምንፈጽመው ተግባር ነው።

ይኸውም የአምልኮና የአክብሮ ተብሎ በሁለት መንገድ ይቀርባል።

የአምልኮ ስግደት አምላክነት የባህሪ ገንዘቡ ለሆነ እግዚአብሔር ፈጥረህ የምትገዛን አንተ ብቻ ነህ ብለን አሐቲ ☞ አንዲት[የተለየች] ስግደት በፊቱ እናቀርባለን።
የአክብሮ ስግደት ግን በጸጋ ቅድስናን ገንዘብ ላደረጉ ሁሉ ሊቀርብ የሚችል ነው።

ፍትሐ ነገሥቱ በአንቀጽ ፲፭ ስለ ጸሎት ሲያስረዳ
"ሰጊድ ለእግዚአብሔር ልዑል በጊዜ ጸሎት" በሚለው ክፍል ተከታዩን ማብራሪያ ትርጓሜ ሊቃውንቱ ያስቀምጣል

የሚጸልይ ሰው በሚጸልይበት ጊዜ ሰጊድን ከሚያነሳ አንቀጽ ሲደርስ ለልዑል እግዚአብሔር ይሰግድ ፤ ጸሎቱን በአንድ ሰጊድ ወይም በሦስትም ይጀምር ። ጸሎቱን በጨረሰ ጊዜ አንዲህ ያድርግ በአንድ ጀምሮ እንደሆነ በአንድ በሦስት የጀመረም እንደሆነ በሦስት ይጨርስ [ወከማሁ ይግበር በተፍጻሜተ ጸሎቱ] ይላል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በዓላትን ምክንያት አድርጎ «ግዝት» ለመጠበቅ የተሠራውን የስግደት ሥርዓት መለያየት የአምልኮንና አክብሮን ስግደትን ለመፈጸም እንደ መለያ መጠቀሙ በምንም መንገድ ተገቢ አይደለም፤ ለምሳሌ አንዳንዶች ለእግዚአብሔር ሰጊድ ፣ ለእመቤታችን አስተብርኮ ለሌሎች ቅዱሳን አድንኖ እንደሚፈጸም ሲናገሩ ይሰማል።

ባይሆን ከአድኅኖና ከአስተብርኮ በቀር ግምባርን ምድር አስነክቶ ከመስገድ የሚከለክሉባቸው የታወቁ ጊዜያት አሉ፤ ፍትሐ ነገሥት "ወጊዜያት እሙራት ዘይኅድጉ ባቲ ስግደት እስከ ምድር ዘእንበለ አድንኖ ወአስተብርኮ ባቲ" የሚለው ይህን ነው።

እነዚህን ጊዜያት በዝርዝር ዕለት እሑድ ፣ በበዓለ ሃምሳ/ በበዓለ ጰንጠቆስጤ ፣ በጌታችን በዓል ፣ በእመቤታችን በዓል ፣ ሥጋውን ደሙን ከተቀበሉ በኋላ እያለ ተቀምጧል። በሌሎች የሥርዓት መጻሕፍት ወርኃዊ የግዝት በዓላትን ቅዱስ ሚካኤል ፣ እመቤታችንና በዓለ ወልድ [በ፲፪፣ በ፳፩ እና በ፳፱] በሚል ሲጨምር ይታያል።

ፍትሐ ነገሥቱ በዚኹ ክፍል ሰጊድ ሦስት ወገን ነው ይላል፤ ሰጊድ ፣ አድንኖና አስተብርኮ ፤ አድንኖ በጌታ በዓላት አስተብርኮ በእመቤታችን በዓላት ብሎ መለያው ለዚህ እንደሚነገር ይገልጣል እንጂ በደረጃ ለመለየት የአምልኮ የአክብሮ ብሎ ለመከፋፈል እንዳልሆነ ያስቀምጣል። በተለየ መንገድ ሰንበትን የሚመለከተውን ደግሞ የአምልኮና የአክብሮ የሚል መለያ ሳይደረግ በቀኖና ኒቂያ አንቀጽ ፳ ላይ "ወይከውን ጸሎት በሰንበት ዘእንበለ ሰጊድ ውስተ ምድር አላ በደኒን ወአትሕቶ ርእስ ⇨ በዕለተ ሰንበት የሚፈጸመው ጸሎት ወደ ምድር ወድቆ ያለ መስገድ ይሁን ነገር ግን ራስን ዝቅና አንገትን ዘንበል በማድረግ ይሁን" ይላል።

መልክአ ሰንበትም በዕለቱ ስግደት ብቻ ሳይሆን ጾምም እንደሚከለከል እንዲህ ሲል ያስረዳናል።

ሰላም ለኵነትኪ እምቅድመ ኵሉ ፍጥረት፡
በዕለተ ተፈጥረ ብርሃን እማእከለ ግሩም ጽልመት፡
ለሰንበተ ሙሴ ካልዕታ ሰንበተ ክርስቲያን ቅድስት፡
ላዕሌኪሰ ከመ ባዕዳን ዕለታት፡
አልቦ ፆም ወአልቦ ስግደት፡፡

【ከፍጥረት ሁሉ በፊት በአስፈሪው ጨለማ መኻል ብርሃን በተፈጠረበት ዕለት ለነበረው መገኘትሽ ሰላም እላለሁ። ለቀዳሚዋ የሙሴ ሰንበት ሁለተኛዋ የሆንሽ ቅድስቲቱ የክርስቲያኖች ሰንበት ሆይ እንደሌሎቹ ቀናት ፆምና ስግደት ባንቺ ላይ የለም】

የማይሰገደው ለምንድነው?
በግዝት በዓላት ዕለተ ሰንበትን ጨምሮ እንዲሁም ከቁርባን በኋላ የአምልኮ ይሁን የአክብሮ ስግደትን የሚከለክለው የቤተክርስቲያን ሥርዓት ምክንያቱን ሲነግረን ፦
✧ አክብሩ ያለውን ትእዛዝ ማፍረስ ስለሆነ፤
✧✧ በዚህ ቀን ዕረፍት ሥጋ አርፋችሁ ዕረፍተ ነፍስ ዕረፉበት ብሏል ያንን ተላልፈን ብንሰግድ በእመቤታችን ቃል ኪዳን ፣ በጌታ ካሳ … አልዳንም ስለሚያሰኝ፤
✧✧✧ የግዝት በዓላቱ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ናቸው በዚህ ቀን ሲሰግዱ መዋል መንግሥተ ሰማያት ከገቡ በኋላ ኃጢኣት ሠርቶ ንስሐ መግባት አለ ስለሚያስብል፤
✧✧✧✧ ሥጋውን ደሙን ከተቀበሉ በኋላ መስገድ የማይገባው ወዙ ይንጠፈጠፋልና በዚያውም ላይ በሥጋው ደሙ አልዳንም በትሩፋታችን ዳንን እንዳንል።

እንግዲህ ከዚህ በተለየ ለአምልኮ በሚል ሰንበትን በመሻር በእርሱ ካሳ አልዳንም በትሩፋታችን እንጂ ብሎ በሞኝ አዋጅ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ቀኖና መጻሕፍትን መሻር ምን ይሉታል?

፨ ተከታዩን ምክር በመለገስ የዛሬውን ሐሳብ እንቋጭ ፨

ሰግላዊው ሊቅ መምህራችን አባ ጊዮርጊስ እንዲህ ይላል "ወለእመሰ ፈቀድከ ታሥምሮ ለእግዚአብሔር አብዝኅ ጸሎተ ዘምስለ ሰጊድ ወጸዊም ዘምስለ ትሕርምት ወትሕትና ዘምስለ ትዕግሥት ወምንዳቤ ሥቃየ አጋንንት በውስተ ገዳማት ወምንዳቤ ሥቃየ ስምዕ በዐውደ ነገሥት ⇨ #እግዚአብሔርን_ለማገልገል _ከፈለግህ ጸሎትን ከስግደት ጋር አብዝተህ ጸልይ ጾምን ከቀኖና ጋር ትሕትናንም ከትዕግሥት ጋር በገዳመ ውስጥ በአጎንንንት መፈተንን በነገሥታት አደባባይ በሐሰት የመወንጀልን መከራ አብዛ"

ያን ማድረግ ባንችልስ ካላችሁ ደግሞ አባ ጊዮርጊስ ሌላም የተስፋ መንገድ አለ ይላል፦
"ወዘንተ ለእመ ኢክህልከ ግበር ተዝካሮሙ ለመስተጋድላን ከመ ትድኀን በኀይለ ጽድቆሙ ወበእንተዝ ንቤ ዘረከበ ሞገሰ አመ ፀአተ ነፍሱ ኢይረክብ ኀሣረ አመ ትንሣኤ ሙታን፡ ⇨ #ይህንን_ማድረግ_ባይቻልህ የሰማዕታትን መታሰቢያቸውን አድርግ በቃል ኪዳናቸው ትድን ዘንድ ስለዚህም ነፍሱ ከሥጋው በተለየች ጊዜ ክብርን ያገኝ በትንሣኤ ሙታን ጊዜ መከራ አያገኘውም"
【መጽሐፈ ምሥጢር】

እንደ ቅድስት ሥላሴ መልካም ፈቃድ ለነገው ደግሞ ክፍል ፫] ⚂ ረቡዕ መጋቢት ፲፫ በሠርክ ተከታዩን የቤት ሥራ ሠርተን ለመምጣት ያብቃን 🙏

ዕለተ ሰንበት የቷ ናት?
☞ በክብረ ሰንበት ዙርያ አንዳንዶች ሰንበት ዕለተ ‘ቀዳሚት’ ብቻ ናት ሲሉ ሌሎች ለክርስቲያኖች ‘እሑድ’ ሰንበት እንጂ ቀዳሚት ሰንበት ምናቸው ናት? የሚሉ አሉ፤ እኛስ ሁለቱንም በጋራ ለማክበርና ለመዘከር ማስረጃችን ከወዴት የተገኘ ነው?

በቴዎድሮስ በለጠ መጋቢት ፲፪ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም.
አቤቱ በእኔ በኩል እለፍ ፡፡

ተፆፋ  በሥነልቦና ባለሞያ Bini Girmachew


ጌታ ሆይ በኢያሪኮው መንገደኛ በኩል እንዳለፍህ ይህች ዐመት ከማለቋ በፊት እባክህን በእኔም በኩል እለፍ፡፡

የጠፋውን በግ አዳምን የፈለግኸው ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አቤቱ እኔንም ፈልገኝ፤ ባገኘኸውም ጊዜ እንደተሸከምኸው እኔንም ተሸከመኝ፡፡

የቀደመ ፍጥረትህን አዳምን ቸል እንዳላልከው ከእርሱ አብራክ የተገኘሁ እኔ ደካማ ልጁንም ቸል አትበለኝ፡፡ ይልቁንም ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አንድ ሰው የተባለ አዳምን እንደተሸከምከው እኔንም ተሸከመኝ፡፡
አዎን ጌታ ሆይ በመንገድ ላይ የወደቀው ስም የለሽ አንድ ሰው እኔ እንደሆንኩ አውቂያለሁ፡፡

ከኢየሩሳሌም ልዕልና ነፍስ ወደ ኢያሪኮ የኃጢአት ቁልቁለት የወረድሁት እኔ እንደሆንኩ ገብቶኛል፡፡ አንተ ለእኔ ድኅነት የሠራኸውን አሸቀንጥሬ ጥዬ እኔን ካስቀመጥክበት ከፍታ ተንደርድሬ ለእኔ ፍላጎት ወደሚስማማው ቁልቁለት የወረድሁት በወንበዴዎች እጅም የወደቅሁት የኢያሪኮው መንገደኛ እኔ ነኝ፡፡ በምሥጢራት ከሚኖርበት ተግባራዊ የክርስትና ከፍታ በማስመሰልና በውድድር ወደሚኖርበት ዝቅታ የወረድሁት ስም የለሽ መንገደኛ እኔ ነኝ፡፡ በእውነትና በፍቅር ከሚኖርበት የወንጌል ተራራ ጥቅሶችን ወደፍላጎታችን ወደሚለጥጥ ገደል የወረድሁት የተመታሁ መንገደኛ እኔ ነኝ፡፡

አንተን በሕይወቴ አሳድሬ አንተ በእኔ እንድትሠራ ከሚያደርግ ከፍታ እራሴን ለአንተ የሚሠራ ወታደር ወደሚያስመስል የሕይወት አዘቅት አውርጄ የጣልኩት የቁልቁለት መንገደኛው እኔ ነኝ፡፡

ሰለወደቀው በማዘን ስለእርሱም በመጸለይ እውነተኞቹ ልጆችህ ከኖሩበት ከፍታ ሁሉንም ወደሚያስንቅና ወደሚያስተች ዝቅታ የወረድሁት መንገደኛ እኔ ነኝ፡፡ ነገሮችን በመንፈስና በአስተውሎት ከመመርመር በስሜትና በግብታዊነት ወደማበላሽበት ጉድጓድ የወረድሁትም እኔ ነኝ፡፡ በእቅድና በጥበብ ከመሥራት በትችትና በነቀፌታ በእልህና በብስጭት ወደመናገር ብቻ የወረድሁት ከንቱ በእውነት እኔ ነኝ፡፡ ጥቂቶቹን ልዘርዝር ብዬ እንጂ ጌታ ሆይ እኔ ያልተውኩት ሰገነት፣ ያልወደቅሁበትም አዘቅት ምን አለና፡፡

ስወርድ ደግሞ እንደተጻፈው ወንበዴዎቹ አገኙኝና ደበደቡኝ፡፡ የነበረችኝንም ሁሉ ቀሙኝ፡፡ ጌታ ሆይ እየወረድኩም ይዠው ከነበረው ያልቀሙኝ ምንም የለም፡፡

መጀመሪያ የቀሙኝ ስንገዳገድ የምደገፍባትን፤ አቀበት ቁልቁለት የማቋርጥባትን፤ አራዊትን የማርቅባትን፣ ሰንቅና ጓዜን የምሸከምባትን አንዷን ዘንጌን ጸሎቴን ቀሙኝና ድጋፍ አልባ አደረጉኝ፡፡ ተነሥቼ ልጸልይ ስቆም አካሌ እንደ ሐውልት ቆሞ ነፍሴን ይዘዋት ይዞራሉ፡፡ አንዳንዴ ጥርሴን ያስነክሱኛል፡፡ አንዳንዴ ስለአንተ ተቆርቋሪ አስምስለው ጦርነት ውስጥ ይከቱኛል፡፡

ሌላ ጊዜ በአንተ በኩል ማግኘት የሚገባኝን ጥቅም ያሳስቡኛል፡፡ ሌላ ጊዜ አንተ የማያስደስቱ የሚመስሉኝን እንድትቆርጥ እንድትጥል ያሳስቡኛል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ የተረሳ ዘመድ ወዳጅ፣ የሞተ የጠፋ ቤተሰብእ ሳይቀር እያሳዩ ተመስጦ በሚመሰል ሕይወት ውስጥ ያጃጅሉኛል፡፡

የቀረ ሥራ የከሰረ ሀብትም አሳስበው ያናድዱኛል፡፡ ብቻ ነፍሴን የማይወስዱበት ቦታ የለም፡፡ ብሞት እንኳ መልአከ ሞት ነፍሴን ሊየንገላታት የማይችለውን ያህል ነፍሴን ያንከራትቷታል፡፡ ጸሎቴን ቀምተው ነፍሴን ማረፊያ ያጣች አሞራ አስመሰሏት፡፡

ስለዚህም የውስጥ ሰላሜ ተነጠቀ፡፡ እንኳን ከሌላው ከትዳር አጋሬ ከወላጅ ከቤተሰቤ በሰላም መነጋገሬን ሁሉ አከታትለው ቀሙኝ፡፡

ትዕግሥቴን ነጥቀዉ እንደ ፍየል ለፍላፊ፣ እንደ ጉጉት ጯሂ አደረጉኝ፡፡

ለሚናገረኝ ካልመለሰኩለት፣ የሚመለከተኝን ካልገላመጥኩት የተጠቃሁ እያስመሰሉ በመልካም የመመለስ ሀብቴን ዘረፉኝ፡፡ ይባስ በለው ልዩነቴን በእወቀት ከማስረዳት፣ ለመግባባት ከመወያየት አፋትተው የተለየለት ግልፍተኛ ተሳዳቢ አደረጉኝ፡፡

አሁንማ ካልተሳደብኩ ዐለም መሸነፌን አውቆ የሚስቅብኝ እያስመሰሉ እንኳን ይቃረኑኛል ለምላቸው በሀሳብ ይቀርቡኛል የምላቸውንም በእኔ መንገድ ስላልተናገሩ ብቻ የማላደላ ጀግና በማስመሰል እንድወርፋቸው ያደርጉኛል፡፡

ወደ ቀደመ ሕይወቴ እንዳልመለስም መንገዱን አጠሩብኝ፡፡ ጉባኤ ሔጄ እንዳልማር ጊዜ የማባክን ይመስለኛል፡፡

አንዳንድ መምህራንንም በትችት ስላስናቁኝ የመቀመጥ ትዕግሥቴ ራሱ የት እንደገባ አላውቅም፡፡ በጓደኛ ተጽእኖ ስቀመጥም ለእኔ ብሎ ከመስማት ይልቅ ይህ ለእነ እገሌ ነበር የሚያስፈልግ ያሰኘኛል፡፡

ሌላ ጊዜ ደግሞ ዛሬም ይህን ይሰብካል እንዴ ያሰኘኛል፡፡ እኔ በማዘወትረው ኃጢአት ሳላፍር መምህሩ የሚታወቅ ትምህርት አስተማረ ብሎ አያፍርም ወይ ያሰኘኛል፡፡

ሌላ ጊዜ ደግሞ የሚነገረውም አሽሙርና የማይረባ ያስመስልብኛል፡፡ እዚህ ከምማር በቃ ቤቴ ተቀምጬዬ አነብባለሁ ብሎ ካስተዋኝ በኋላ ቤቴ ስገባ ቴሌቪዥን ጋር ያፋጥጠኛል፡፡

እርሱ ሲሰለቸኝ ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ የወጣ ነገር እንድመለከት በጓደኞቼ በኩል ያስደውልብኛል፡፡ እንደምንም ታግዬ ላነብብ ስነሣ እንቅልፍ እንደበረዶ ያዘንብብኛል፡፡

በቃ በጎው ነገር ካመለጠኝ በኋላ አልያዝ አልጨበጥ አለኝ፡፡ ምክር እንዳልጠይቅ ትልቅና አዋቂ ሰው ነው በሚባል የገጸ ባሕርይ ካባ ሸፍነው አሳፍረውኛል፡፡ ከዚህ ሁሉ የተነሣ በነፍሴ ሕመም ሥጋዬም ታማሚ ሆነ፡፡

እንደወፈረኩ ደከማ፣ እንደጠገብኩ ልፍስፍስ አደረጉኝ፡፡ እንዳልጾም ሰውነቴ ሁሉ እንቢ አለ፡፡ እንዳልሰግድም ጉልበቴ ሁሉ ተብረከረከ፡፡ በሁሉ ባዶ ሆኜ ቁጭ አልኩ፡፡

የነፍሴ መድኃኒት ጌታዬ ሆይ አፍ ማብዛቴን፣ ነገር መውደዴን አይተህ ነው መሰል አፍን በማስክ የሚያስይዝ የተግሣጽ ደዌ ብታመጣም የእኔ ነፍስ ግን አሁንም አላስታዋለችም፡፡

እጆቼ ማስኩን አፌ ላይ ቢያደርጉም ምላሴን ሊያስቆሟት ግን አልቻሉም፡፡ አንተ ለደቀመዛሙርትህ እንዳልከው አፍን የሚያረክሰው ከውጭ የሚገባው ሳይሆን ከውስጥ የሚወጣው ነውና ከነፍሴ ቁስል የተነሣ በአፌ የሚወጣው የነገር ጠረን አካባቢውን አሸተተው፡፡

እንኳን ለሌላው ለእኔም እየተሰማኝ ቢሆንም ነፍሴን የደበደቧት ወንበዴዎች ግን እንድነቃ አልፈቀዱልኝም፡፡ ስለዚህ ጌታ ሆይ የአፍ ብቻ ሳይሆን የልብና የኅሊና ማስክ እዘዝልኝ፡፡ እንደ ዳዊት ወዳጅህ ለአፌ ጠባቂ ሹምለት፤ ከንፈሮቼንም እንደ ቤተ መቅደስህ በር በምሕረትና በእውነት የሚከፈቱ አድርግልኝ፡፡

ጌታ ሆይ አሁን ችግሬ ገብቶኛል፤ ማስክ የሚያስፈልገኝ ለውጨኛው ሳይሆን ለውስጠኛው የኅሊና አፌ ነው፡፡ ጸረ ተሐዋሲ መድኃኒትም ከሥጋዬ ይልቅ ለነፍሴ እጆች እንደሚያስፈልጋቸው ገብቶኛል፡፡

አቤቱ ሰነድ በመደለዝ፣ ደም በማፍሰስ የረከሱ እጆቻችን በምን ይነጻሉ? የሐሰት ትርክት በመተረክ፣ የበለው ግደለው ቅስቀሳ በመጻፍ የዋሆችን በማነሣሣት ደም ያፈሰሱ የምሁር እጅ ነኝ የሚሉ የነፍስ እጆቻችንስ ቤትኛው ሳኒታይዘር ይነጻሉ? ጌታ ሆይ ዘንድሮ ሁሉንም ችግሮቼን ነግረኸኛል፡፡

በተለይ ርቀት ያለመጠበቅ፣ ቦታዬንም ያለማወቅ ችግር አስታውሼው አላውቅም ነበር፡፡ የእኔማ የተለየ ነው፡፡ እንኳን በሾምካቸው በጳጳሳት በካህናት በአንተ ወንበር ተቀምጬ ስፈርድ፣ ስገድል ሳድን፣ ስሰጥ ስነሣ ነው የኖርኩት፡፡

በወንጌል አልገባ ቢለኝ በበሽታ አስመስለህ ርቀትህን ጠብቅ ብትለኝም ልመለስ አልቻልኩም፡፡ ግን ወድቄያለሁና ተነሥቶ መቆም ርቀቴንም መጠበቅ እንዳይቻለኝ ደርገው ወንበዴዎቹ አጋንንት ስወርድ አግኝተው ደብደበውኛልና ተመልሶ መቆም ተሣነኝ፡፡
ደጉ ሳምራዊ ሆይ እንደ መንገደኛው በወደቅሁበት በረሃ ማለፍህን እየተጠባበቁ አሁንም በኢያሪኮ ጎዳና ቁልቁለቱ መካከል ላይ ነኝና አትለፈኝ፡፡

ጌታ ሆይ ከእኔ ተሽለው ያልወደቁት ቢያዩኝም ትተውኝ አለፉ እንጂ ሊያነሡኝ አልቻሉም፡፡ እንደ ቀደሙት መንገደኞች ፈርተው አይመስለኝም፡፡ ይልቁንስ ሸተተን ብለው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ደጉ ሳምራዊ ሆይ መበላሸቴ እውነታቸውን ነውና እባክህን አንተ ወደእኔ ተመለከት፡፡ ከወደቅሁበት ዛሬም አንሣኝ፡፡

እንደ ወንጌሉ በፍጹም ትሕትናህ በአህያህ ላይ ጫነኝ፡፡ ሰው መሆንን ወድደህ ሰው አለመሆንን ጠልተህ ስለእኔም ጭምር ሰው ሆነህ እንደ አህያ ደካማ የሆነ ባሕርያችን ገንዘብ አድርገሃልና ከወደቅሁበት አንሣኝ፡፡

ጌታዬ ሆይ ስለእኔ ሰው ሆነሃልና በፈቃዴ ከሰውነት ባሕርይ ተራቁቼ ከእንስሳነትም ወርጄ በጠባዬ አውሬ የሆንኩትን እኔን ለሰውነት መዓርግ አብቃኝ፡፡

ናከደበነፆርን ግብሩን አይተህ አረአያውን ለውጠህ አውሬ ካደረግኸው በኋላ ወደስውነነት እንደመለስከው እኔንም በጠባዬ አውሬ የሆንኩትን ስለእኔ ሰው መሆንህን አስበህ ለሰውነት አብቃኝ፡፡

ስለእኔ በበረት ራቁትህን በብርድ ተወልደሃልና፤ የኃጢአት ብርዴን አርቅልኝ፡፡ ስለእኔም ጭምር ብለህ በከብቶች እስትንፋስ ተሟሙቀሃልና፤ በሙቀተ መንፈስ ቅዱስ እኔን ከኃጢአት ብርድ አላቅቀኝ፡፡

ስለእኔ ቅጠል ለብስሃልና አውልቄ የጣልሁትን ወንበዴዎቹም የዘረፉኝን የልጅነት ልብሰ ጸጋዬን መልሰህ አልብሰኝ፡፡

ጌታዬ ሆይ የጠፋነውን ወደመንጋህ ለመመለስ አንተ ስለእኛ ተሰደሃልና አቤቱ እኔን መልሰኝ፡፡ የጠፋ በግህን ከቅዱሳን ኅብረት ከቅድስና ጉባኤህ ከመንጋህ ደርበኝ፡፡

እንርሱን አንድ ጉባኤ አንድ አካል ላደረገ ለቅዱስ ሥጋህና ለክቡር ደምህም አብቃኝ፡፡

ጌታዬ ሆይ አቤቱ በአዲስ ዘመን ዋዜማ በአጠገቤ እለፍና አንሣኝ፡፡ ዘይትና ወይን ባልካቸው የመሥዋዕት ደምህ ቁስሌን ጥረግልኝ፡፡ ጨርቅ በተባለ ፍቅርህም ግጥም አድረገህ እሰርለኝና ከጥላቻ፣ ከከንቱነት፣ ከግብዝነት፣ ከለፍላፊነት፣ ከኩራትና ከትዕቢት፣ ከዝሙትና ከርኩሰት ቁስሌ ማገገምን ስጠኝ፡፡

በአገልጋይህ በኩል ስበህ የእንግዶች ማደሪያ ወዳልካት ቤትህ አስጠጋኝ፡፡ ጌታዬ ሆይ እባክህን ለእኔ ለምስኪኑ ዛሬም ዲናርህን ክፈልልኝ፤ አቤቱ ሁለቱ ዲናሮችህ በተባሉ በብሉይና በሐዲስ እጅግ የደከመች ቁስለኛ ነፍሴን መግበህ አድንልኝ፡፡

የነፍሴ እረኛ ሆይ በአንተ ዘንድ ዝለት መሰልቸት የለምና የእኔ መቅበዝበዝ አይተህ ቸል አትበለኝ፤ ጠባቂዬ ሆይ በኃጢአቴ ምክንያት ካገኘኝ ደዌ ሥጋ ደዌ ነፈስ ፈውሰህ ሰው አድርገህ አቁመኝ፡፡

ስለእኔ የእሾህ አክሊል የደፋኸው ጌታ ሆይ የአንተ ራስ ስለእኔ ተወግቷልና ኅሊናዬን ከሚወጋኝ የሀሳብና የኃጢአት እሾህ አድነኝ፡፡

በውኑ አንተ ለእኛ ብለህ ካልሆነ በከንቱ ተወግተሃልን? ስለዚህ ጌታ ሆይ ቤተ መቅደስ ውስጥ ቆሜ እየጸለይኩ እያስቀደስኩ ሳይቀር እሾህ ነገር እያሰወጋ ከሚያቆስለኝ ክፉ ሀሳብ ስለደፋህልኝ የእሾህ አክሊል ብለህ እኔን አድን፡፡

አቤቴ እረኛዬ ሆይ በዘመነ ሥጋዌህ ኃጢአትህ ተተወልህ፣ ኃጢአትሽ ተተወልሽ እንዳልካቸው ኃጢአትህ ተትቶልሃል የሚለውን ድምጽህን አዲሱ ዘመን ከመግባቱ በፊት አሰማኝ፡፡

የልጆችን ለውሾች መስጠት አይገባም እንዳልካት ሴት ፈውስ ባይገባኝ እንኳ ጌታ ሆይ ውሾችም ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ ስትለህ እምነቷን አይተህ እንደፈወስክላት እኔንም በእምነት ፍጹማን ከሆኑት የተረፈውን የፈውስ ፍርፋሪ አቅምሰኝ፡፡

ቤዛዬ ሆይ ስለእኔ ተገርፈሃልና በመገረፍህ ቁስል ፈውሰኝ፡፡ በሙሴ ፊት ብርሃን በሳልከበት በአንተ ፊት ላይ አይሁድ የረከሰ ምራቃቸውን ሲተፉብህ የተጋሰከው ቤዛዬ ሆይ ዛሬም እኔ በየቀኑ በአንተ ፍጡር ላይ የምተፋውን አይተህ አላጠፋኸኝም፣ ነገር ግን ርኩሱን ምራቅ በብርሃናዊ ፊትህ ላይ ስለመቀበልህ እኔን ከርኩሰቴ አንጻኝ፡፡

አንተ ስለእኛ ስለሁላችን ተከሰህ በጲላጦስ ፊትህ ቀርበህልናልና አቤቱ ጌታ ሆይ እኛ ስለኃጢአታችን አንከሰስ አንወቀስ፤ በአንተ መከሰስ እኛ እንፈወስ እንጂ፡፡ ጌታ ሆይ ስለአንተ መንገላታታ የምእመናን መንገላታት ይበቃ፡፡ ስለአንተ መናቅ እኛ በድነቁርናና ባለማሰብ፤ ባለማቀድና ባለመሥራት የገጠመን መናቅና መገፋት በአዲሱ ዐመት ይከልከልልን፡፡

ጌታ ሆይ ስለእኛ መስቀል ተሸክመህ ሦስት ጊዜ ወድቀሃልና፣ በግል በሠራነው ኃጢአት ከወደቅንበት ውድቀት፣ እንደተቋምም ተሰነካክለን ከወደቅንበት አዘቅት፣ የአባቶችን ገድልና ትሩፋት ይዘን ስለወደቅንበትም ታሪካዊ ውደቀት የአንተ መውደቅ ቤዛ ሆኖን እንነሣ፤ አቤቱ አንሣን፣ ቀጥ አድርገህም አቁመን፡፡

ተነሣ አልጋህን ተሸክመህ ተመላለስ እንዳልከው፤ ተነሡ ወንጌል እውነት ይዛችሁ፣ የተኛችሁበትን የታሪክ፣ የገድልና የፍቅር አልጋ ይዛችሁ በአገልግሎት ተመላለሱ ብለህ በኃጢአትና በድከመት የሰለሉ እግሮቻችንን አጽና፡፡

ጌታ ሆይ ስለእኛ ተቸንከረሃልና ከተቸነከርንባቸው የጎሰኝነት፣ የድንቁርና የጥቅመኝነትና የአድሎ ችንካሮች አልላቀን፡፡

አቤቱ ጌታ ሆይ ስለእኛ የሆምጣጤውን መራራ ጽዋ ቀምሰሃልና በምትኩ ከፍቅርና ከይቅርታ፣ ከዕወቀትና ከምሕረት ጽዋ እኛን አቅምሰን፡፡

ሳይገባህ ስለእኛ ተገንዘህ ተቀብረሃልና አቤቱ ከድንዛዜ መግነዝ ፍታን፣ ከጥልቅ የድንቁርና መቃብርም አውጣን፡፡ ስለ ልዩ ትንሣኤህ ትንሣኤ ልቡና ወኅሊና አድለን፡፡

ስለ ቅድስት ዕረገትህም ዕርገተ ኅሊናና አልዕሎ ልቡናን አሳድርብን፡፡ ስለ ዳግም ምጽአትህም በቀኝህ የሚቆሙ ወዳጆችህ የሚሠሩትን ምግባረ ሃይማኖት ለመሥራት አብቃን፡፡

ጌታ ሆይ በዚህች በዿግሜ ኢዮብን በዮርዳኖስ ወንዘህ አጥበህ እንደፈወስነው እኛን ኢትዮጵያውያንን ከሚያጸይፍ ቁስለ ነፍሳችን ፈውሰን፡፡ እጠበን እንጠራለን፤ አንጻንም እንነጻለን፡፡

ጌታ ሆይ ስለእኛ አይደለም መምጣትህን አስቀድመው ይነግሩ ዘንድ ስለነገርሃቸው አርእሰተ አበውና ነቢያት፣ መርጠህ አስተምረህ ሾመህ ዐለምን ወደአንተ ይመልሱ ዘንድ መስቀል መከራ ሞትን አሸክመህ ስለላክሃቸው ሐዋርያት፣ ኑፋቄ ዘርቶ መንጋውን ከአንተ ለመለየት የተጋውን የዲያብሎስን ሽንገላ ተቃውመው ሃይማኖትን በንጽህ ስለጠበቁ ሊቃውንት፣ ፍትወታትን ድል

ነሥተው በተጋድሏቸው ያለደም መፍሰስ ሰማዕትነትን ስለተቀበሉ ጻድቃን፣ የነገሥታትን ማስፈራራትና የሚያደርሱባቸውን መከራ ሳይሰቀቁ ነገሥታተ አሕዛብን ድል ስለነሡ ሰማዕታት፣ በንጽሕ እና በትጋት ሆነው ያለመታከት አንተን ስለሚያገለግሉ ሊቃነ

መላእከትና ሠራዊተ መላእክት ብለህ ይልቁንም ደግሞ ከሁሉም በላይ ስለሆነች ከእርሷ ሰው ትሆን ዘንድ ስለመርጥካት የንጽሕና መሠረት የባሕርየ አዳም መመኪያ ስለሆነች ስለንጽሕተ ንጹሐን ቅድስተ ቅዱሳን

ድንግል እናትህ ብለህ ጌታ ሆይ በወደቅሁበት አዘቅት እለፍና እኔን ምስኪኑን ቁስለኛ የዲያብሎስ ምርኮኛ ከወደቅሁበት አንሣኝ፤

በሚቀጥለው ዐመትና በመጪዎቹ ዘመናትም አንተን በመከተል ሕግህን በመጠበቅና ፈቃድህን በመፈጸም አንሣኝ፡፡

ለፈቃዴ አሳልፈህ አትሰጠኝ፣ ይልቁንም ለፈቃድህ የምገዛበትን ልቡና ሥጠኝ፡፡ አቤቱ አትተወኝ አትጣለኝም፣ አሜን፡፡
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - ‌🇴‌🇷‌🇹‌🇭‌🇴‌🇩‌🇴‌🇽 ‌🇹‌🇪‌🇼‌🇦‌🇭‌🇩‌🇴
https://www.tg-me.com/joinchat-AAAAAEILHwyFiBuqHNVyRw
አባ ጊዮርጊስ በሦስትዮሽ ስልት (Trio) ራሱን ከጌታና ከእናቱ
ጋር የሚያዛምድበት ውብ ሥነ ጽሑፋዊ ሦስት ማዕዘንም አለ ፡-

‘እኔ የተጠማሁ ነኝ ፤
አንቺ የወርቅ መቅጃ ነሽ ፣
ልጅሽ የሕይወት ውኃ ነው፡፡

እኔ ነጋዴ ነኝ ፤
አንቺ መርከብ ነሽ ፤
ልጅሽ ዕንቈ ነው፡፡

እኔ ገደል ተሻጋሪ ነኝ ፤
አንቺ ድልድይ ነሽ ፤
ልጅሽ የደስታ ሥፍራ ነው፡፡

እኔ ደሃ ነኝ ፤
አንቺ የክብር ማከማቻ ነሽ ፤
ልጅሽ የከበረ ጌጥ ነው፡፡

እኔ ቁስለኛ ነኝ ፤
አንቺ የመድኃኒት ብልቃጥ ነሽ ፣
ልጅሽ መድኃኒት ነው፡፡

እኔ ዕርቃኔን ነኝ ፤
አንቺ የሸማኔ ዕቃ ነሽ ፣
ልጅሽ የማያረጅ ልብስ ነው’

የግዮን ወንዝ ገጽ 27-28

https://www.tg-me.com/joinchat-AAAAAEILHwyFiBuqHNVyRw
በሌሊት ወደ ኢየሱስ

(ሽራፊ ሃሳብ 1 ከኒቆዲሞስ ምንባብ)

ኒቆዲሞስ በውድቅት ሌሊት ወደ ጌታችን መጣ። ሌሊት እንግዲህ በቂ ብርሃን የሌለበት ፣ እንቅፋት የሚበዛበት ፣ ጭልም የሚልበት ፣ ግራ ቀኝ ቢያዩ ሰው የሚታጣበት ፣ ማጅራት ከሚመቱ ወንበዴዎች በቀር በመንገድ ሌላ ሰው የማያጋጥምበት ፣ ብርድና ቆፈን ሰውነትን የሚያስጨንቅበት ሰዓት ነው። ይህ የአይሁድ መምህር በሌሊት የመጣበት ምክንያቱ ብዙ ሲሆን ለእምነት ማነስ ማሳያ የሚሆን ሰው ነው።

ዛሬ ደግሞ ለአፍታ ኒቆዲሞስን "በሌሊት ወደ ኢየሱስ በመምጣቱ" በጥቂቱ እናመስግነው። ብዙ እግሮች ወደ ኃጢአት በሚሮጡባት ሌሊት ወደ ክርስቶስ የሮጠውን ይህንን ሰው እስቲ እናድንቀው! ይህንን የሌሊት ግርማ ሳይበግረው ወደ ኢየሱስ የተጓዘ የጨለማ ተጓዥ ፣ ይህንን ሰዓታት ቋሚ ፣ ይህንን ማሕሌት ቋሚ በጥቂቱ ብናመሰግነው ምን አለ? ከጌታ ፊት ቆሞ ቅኔ የተመራውን ፣ ስለ ልደት እየተናገረ ስለ ጥምቀት የሚያመሰጥረውን የፈጣሪን ቅኔ ተቀብሎ ሊያዜም ከጀመረ በኋላ መቀበል ሲያቅተው ጌታችን "አንተ የአይሁድ መምህር ስትሆን ይህንን አታውቅምን?" ብሎ የገሠፀውን ኒቆዲሞስን እስቲ ዛሬ በበጎነቱ አርኣያ እናድርገው።

በሕይወታችን ውስጥ የተስፋ ብርሃን ጭልም ባለብን ጊዜ ፣ እንቅፋት በበዛብን ወቅት ፣ ግራ ቀኝ አይተን ሰው ባጣንበትና ብቸኝነት በዋጠን ሰዓት ፣ ክፉ ከማድረግ በማይመለሱ ጨካኞች በተከበብን ሰዓት እኛስ ወዴት እንሔዳለን?

ሕይወቱ "ሌሊት" የሆነበት ሰው ሁሉ ወደ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ቢሔድ እንደሚሻለው ከኒቆዲሞስ የተሻለ ምሳሌ የለም። ሕይወቱ የጨለመ ባይሆን እንኳን ልቡ የጨለመበት ፣ በኃጢአት ጠል የጠቆረ ፣ በበደል ብርድ ቆፈን እጅ እግሩ የታሰረ ከእኛ መካከል ስንት አለ?

እመነኝ ፣ ተስፋ ቆርጠህ ቁጭ ብለህ እስከሚነጋልህ ብትጠብቅ አይነጋም። ይልቅ ተነሥና "በሌሊት ወደ ክርስቶስ ሒድ" እርሱ ተስፋ ለቆረጠው ማንነትህ ዳግመኛ መወለድ እንዳለም ይነግርልሃል። ኒቆዲሞስ ጌታችንን ሊያየው ሔዶ ራሱ ታይቶ እንደመጣ አንተም ወደ እርሱ የቀረብህ እንደሆነ ራስህን ታያለህ።

በ"ሌሊት" ውስጥ ለሚኖር ሰው ነግቶ ፀሐይ ትወጣልኛለች ብሎ ከሚጠባበቅ ይልቅ በሌሊት እንደ ኒቆዲሞስ ተነሥቶ ወደ ጽድቅ ፀሐይ ወደ ክርስቶስ ቢሔድ ይሻለዋል። ወደ እርሱ ለሚሔድ ሰው ሌሊቱ ይነጋል ፣ ክርስቶስ ያለበት ሌሊት ከቀን ይልቅ ብሩሕ ነው ፣ እውነተኛው ብርሃን ያለበት ጨለማም ጨለማ አይደለም። ስለ እርሱ "ጨለማም በአንተ ዘንድ አይጨልምም" ተብሎ ተጽፎአልና።

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
መጋቢት 16 2010
ኒቆዲሞስ
ናይሮቢ ፣ ኬንያ

https://www.tg-me.com/joinchat-AAAAAEILHwyFiBuqHNVyRw
እንኳን አደረሳችሁ!

"ከሰውስ እንደኔ ኃጢአት የሚሠራ፤
ከመሐሪዎችስ እንዳንተ 'ሚራራ፤
አይገኝምና በዚያ የፍርድ ሥፍራ፤
ስለ ደምህ ብለህ ለኃጥኡ ራራ!"

"አልቦ ዘከማየ አበሳ ኃጢአት ገባሪ፤
ወአልቦ ዘከማከ እግዚአብሔር መሐሪ፤

አመ ለኮንኖ ዓለመ ትመጽእ ደኃሪ፤
ቀደመ ገቦከ ኃጢአትየ አስተስሪ!"

(መልክአ መድኃኔ ዓለም)

https://www.tg-me.com/joinchat-AAAAAEILHwyFiBuqHNVyRw
በደቡብ ምሥራቅ ትግራይ ሀገረ ስብከት በእንደርታ ወረዳ ለሰሰማት ትኩል ምዕራፈ ቅዱሳን ቤተ ደናግል ገዳም ሙሉ ገቢው የሚውለው "ከሞት ባሻገር" መጽሐፍ ሁለተኛ እትም

እና

ለኳታር ዶሃ ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ሕንፃ ማሠሪያ ሙሉ ገቢው የሚውለው አበረታች መድኃኒት መጽሐፎች በዘመነ ትንሣኤ በአዲስ አበባና በዶሃ ታትመው በገበያ ላይ ይውላሉ::

ሁለቱም መጻሕፍት ለሁለተኛ ጊዜ የታተሙ ሲሆን ከሞት ባሻገር በገጽ ብዛት ጭማሪ የተደረገበት ክልስ እትም (revised edition) ነው::
#ዘንባባ_እና_ሆሣዕና
✠.🌴🌴🌴.✠

ሙሽራይቱ የሆነችውን ቅድስት ቤተክርስቲያኑን መሠረት ሆኖ ያጸናት ፣ ራስ ሆኖ የሚገዛት ፣ በደሙም የዋጃትና አካሉ ሆና ያከበራት ክርስቶስ እንኳን ለዘንባባው በዓል አደረሳችሁ። 🙏 ሆሣዕና በአርያም 🙏

የቅዱስ ቀሌምንጦስ ዘሮምን ምስክርነት መነሻ እናድርግ "ቤተክርስቲያን እንቲአነ ፍሬሃ ከመ በቀልት እንዘ አሐቲ ለሊሃ ወብዙኃት ሕንባባቲሃ … የእኛ የሆነች ቤተክርስቲያን ፍሬዋ እንደዘንባባ ፍሬ ነው ለራሷ አንዲት ስትሆን ቅርንጫፎቿ ብዙዎች ናቸው" 【ቀሌ. ፰፥፷፯】

ዘንባባ የሚለው ቃል ሰሌን፣ ጸበርት/ፀመርት ፣ ተምር፣ በቀልት … የሚሉትን ሁሉ ተክቶ የተነገረ ነው። ይሆንና ግን በቀልት የሚለው ግንዱን ፀመርት ደግሞ ቅጠሉ ሲሆን ተምር ፍሬው እንደሆነ መተርጉማን ያስረዳሉ።
በዚህ መንገድ ዘንባባ የሚለው ፍሬው ተዘርቶ የሚበቅል ቁመታም ሰሌን የቴምር ዛፍ ግእዙ በቀልት እያለ የሚጠራው ነው።

በእብራይስጡ ደግሞ ተምር (תָּמָר) ወይም ቶሜር (תֹּמֶר) የሚለው የቴምር ዛፍ ዘንባባን ወክሎ የሚነገር ሲሆን በግሪኩም ፎይኒክስ (φοῖνιξ) የሚለው የዘንባባ ዛፍን ወክሎ ተነግሯል።

በምሥጢር ግን ዘንባባ ራሱ ሆሳዕና ተብሎም ተጠርቷል!

ለምሳሌ ለቅዱስ ማቴዎስ ክርስቶስ በአምሳለ ወሬዛ(ወጣት) ተገልጾለት ካህናተ ጣዖት ወዳሉበት ሀገር ሲገባ ምን ማድረግ እንዳለበት ሲነገረው ሆሣዕና በእጅህ ያዝ እንዳለው ስንክሳራችን ይነግረናል ይህንንም ዘንባባ ነው ሲል መልሶታል።

“አንተሰ ኢትክል ከመ ትባእ ውስተ ዛቲ ሀገር ዘእንበለ ትላፂ ርእሰከ ወጽሕመከ ወዘእንበለ ትእኅዝ ሆሳዕና በእዴከ … አንተ ግን ጽሕምህን (ፂምህን) ካልተላጨህ በእጅህም ሆሣዕና/ ዘንባባ ካልያዝክ መግባት አትችልም”【ስንክሳር ጥቅምት ፲፪ ቁጥር ፲፫ 】

ይህንንም ሊቁ አባ ጊዮርጊስ እየደጋገመ ለእመቤታችን ምሳሌ አድርጎ አስታውሶታል።
☆ በኆኅተ ብርሃን "ወደ ካህናቱ በገባ ጊዜ ለማስተማር የያዛት የማቴዎስ የሰሌን ዘንባባ አንቺ ነሽ… "
☆ በመዓዛ ቅዳሴም "የእንድርያስ የሕይወቱ መርከብ፣ ለያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ የስብከቱ መጽኛ፣ ብፁዕ ለሚሆን ለማቴዎስም የምልክቱ ዘንባባ የምትሆኚ ማርያም ሆይ ነዪ"

#ሆሣዕና ለሚለው ቃል የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍ ሆሳና (ὡσαννά) የሚለውን የጽርእ ቃል ቀጥታ ይጠቀመው እንጂ መነሻው የእብራይስጡ «ሆሺዓህናእ» የሚለው ጥምር ቃል ነው። ይህም ሆሺዓህ (יָשַׁע) ናእ (נָא) ከሚሉት ሁለት ቃላት የተገኘ ነው።
ትርጉሙም ሆሺዓህ= አድን፣
ናእ ደግሞ አሁን/እባክህ/አቤቱ በሚለው ይገለጻል።
☞ አሁን አድን ፣ እባክህ አድን፣ አቤቱ አድን ማለት ነው።

ዘንባባ በሕይወታችን ስላለው ትርጉም ውዳሴ አምላክ የቀዳሚት ምንባብ ይህን ይላል "መልካም ፍሬን እንደምታፈራ እንደ ሰሌን ሥር ጽናት በልቡና ጽናትና በነፍስ ዝምታ በቦታዬ ትከለኝ" ከዚህ ጸሎት በመንፈሳዊው ሕይወት የዘንባባን ሃይማኖታዊ መገለጫ በሥሩ ጽናት ከቦታ አለመናወጽ ለነፍስ አለመታወክ ምሳሌ ሆኖ መጠቀሱን እንረዳለን። ውኃ በሌለበት በረሐ እየበቀለ ባለ ፍሬ መሆኑ መከራ በበዛበት ዓለም እየኖሩ ፣ በተኩላዎች መኃል እንደበግ ተልከው ስለእውነት እየመሰከሩ ፣ በመልካም ምግባር ጸንተው ፍሬ ላፈሩ… ጽኑዓን መስተጋድላን ሁሉ ምሳሌ ሆኖ ይነገራል።

በቅዱስ መጽሐፍ ዘንባባ ያለውን ቦታ መረዳት እንድንችል ተከታዮቹን ተጨማሪ ታሪኮች እንመልከት ፦

✧ ታላቋ ባለቅኔ ሴት ዲቦራ በእስራኤል ላይ ስትፈርድ ትቀመጥ የነበረው ከዘንባባ በታች ነው። ዛፉም በስሟ ይጠራ እንደነበር መጽሐፍ እንዲህ ሲል ዘግቦልናል “እርስዋም በተራራማው በኤፍሬም አገር በራማና በቤቴል መካከል ካለው የዲቦራ ዛፍ ከሚባለው ከዘንባባው በታች ተቀምጣ ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እርስዋ ለፍርድ ይወጡ ነበር።” 【መሳ ፬፥፭】

✧ በኦሪቱ መቅደስ ጠቢቡ ሰሎሞን እንዲቀርጽ (እንዲሥል) ከታዘዙት ሦስት ሥዕላት ውስጥ ሥዕለ ኪሩብ የፈነዳ አበባ እና የዘንባባ ዛፍን ነው። 【፩ኛ ነገ. ፮፥፳፱–፴፯】

✧ ታላቁ የዜና አይሁድ ታሪክ ጸሐፊ ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን (Flavius Josephus / Yoseph Ben Mattithyahu) በዜና አይሁድ በሦስተኛው ክፍል በ፳፱ኛው ምዕራፍ ስለ ልማደ አይሁድ ሲዘግብ «በቂጣ በዓል ላይ የደስታና የክብር መገለጫ አድርገው በዘንባባ ዝንጣፊ የመማታት ጨዋታን እንደ ሕግና ልማድ ይፈጽሙት ነበር» ይላል።

✧ ሌላው በአይሁድም በሮማውያንም ዘንድ ዘንባባ ያለው ተምሳሌታዊ ሥፍራ ትልቅ ነው። ለድል አድራጊዎች በእምነታቸው ለጸኑትና ለሰላም አብሳሪዎች እንደ መገለጫ ሆኖ ያገለግላል። በተለይ ነቢያቱ የሰላም ዘመን እንዲመጣ ለሕዝቡ ለማብሰር በአሕያ ላይ ተቀምተው የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ወደ ከተማ ሲገቡ ይታዩ ነበር ፤

ቅዱስ መጽሐፋችንም ድል ነሺዎች የክብራቸው መገለጫ አድርገው በሰማዩ መቅደስ ዘንባባ ይዘው መገለጣቸውን እንዲህ ሲል ይመሰክርልናል።

“ከዚህ በኋላ አየሁ፥ እነሆም፥ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤” 【ራእ ፯፥፱】

በምሳሌነቱም ዘንባባ (በቀልት) የኢየሱስ ክርስቶስ ፣ የድንግል ማርያምና የሌሎቹም ቅዱሳን ጻድቃን ወኪል ሆኖ በየአገባቡ ሲመሰገኑበትና ክብራቸው ሲገለጥበት እንመለከታለን።

.🌴. ዘንባባ = ክርስቶስ

『 ስነ ቆምከ በቀልት ወመልክእከ ሕይወት ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ አምደ ሃይማኖት፣ ሥርግው ስነ ስብሐት በሰጊድ ስብሐት 』 ⇨ የቁመትህ ውበት ዘንባባ መልክህም ሕይወት የሆነ የሃይማኖት አምድ ክርስቶስ ሆይ ባማረ ምስጋና የተሸለምክ በመስገድ ላንተ ምስጋና እናቀርብልሃለን።

.🌴. ዘንባባ = ድንግል ማርያም

『 ለሕሊናኪ ንጽሕት እምነ ኵሉ ትውዝፍት፡ ለንጽሐ ሥጋኪ ዘአልቦ ርስሐት፡ ለቆምኪ ስነ በቀልት በሰጊድ ሰላም』 ⇨

.🌴. ዘንባባ = አቡነ ተክለሃይማኖት

『ተክለ ሃይማኖት በቀልት ወጽጌ ገነት ፡ ዘናቄርብ ለከ መዓዛ ስብሐት 』 ⇨

.🌴. ዘንባባ = አቡየ ገብረ መንፈስ ቅዱስ

『 ጻድቅሰ ከመ በቀልት ይፈሪ ወይበዝኅ ከመ ዘግባ ዘሊባኖስ አባ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፡፡ ኖመ ኖመ ኢየሩሳሌም በፍሥሓ ወበሐሴት፡፡ 』 ⇨

በይበልጥ ደግሞ "ጻድቅ እንደዘንባባ ያፈራል" በሚለው የነቢዩ ንጉሥ ዳዊት ቃል መነሻ በማድረግ 【መዝ ፺፪፥፲፪】በጽድቅ የኖሩ አያሌ ሰማዕታት መስተጋድላን መገለጫቸው ሆኖ ሲወሱበትና ሲወደሱበት ይታያል።

በኋላኛውም ዘመን ገዳማውያኑ መናንያን ሕይወታቸው ከዘንባባ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ሆኖ ታይቷል። ሥራቸው ሰሌን መታታት (ሠርቶ ሰፍቶ ለምንጣፍ ለቅርጫት፣ ለቆብና ለቀሚስ ማዘጋጀት) ፣ ለራሳቸውም የሚለብሱት ቆባቸውና ልብሳቸው ጭምር ከሰሌን የሚሠራ ነበር። ኋላም ዐረፍተ ዘመን ሲገታቸው የከበረ ሥጋቸው በሰሌን ተከፍኖ ግብኣተ መሬት ይፈጸምላቸዋል።

ከሰይጣን ውጊያ ለማረፍ እና ከስንፍና ለመለየት ከጸሎት ጋር መነኮሳት ሊተገብሩት ከሚገባ ተግባረ እድ ዋናው ሰሌን መታታት ሊሆን እንደሚገባ ቅዱስ መልአክ ለርእሰ መነኮሳት አባ እንጦንስ አስተምሮታል (ስንክሳር ዘጥር ፳፪) የባህታዊው አባ ጳውሊ ቀሚስ የአባ እንጦንስም ቆብ ከሰሌን የተሠራ ነበር መጽሐፈ መነኮሳቱና ዜና ገድላቸው ይነግረናል።
ገዳማዊው አባ ዳንኤል መታበይ ሲመጣበት ሔዶ ያየው ዘንድ እግዚአብሔር ወደ ንጉሥ አኖሬዎስ ልኮታል፤ ተወዳጁ ንጉሥ ሰሌን በመታታት በዘንባባ ቅጠል ምንጣፍ በመሥራት ይደክም ሸጦም ይመጸውት እንደነበር አይቶ ተምሯል (ስንክሳር ዘሕዳር ፲፮)

ታላቁ አባ ሙሴ ዘደብረ ሲሐት ልብሱ ከዘንባባ ቅጠል የተሠራ ሰሌን ነበር (ስንክሳር ዘመስከረም ፫)

በሌላ መንገድ ደግሞ በዘመነ ሰማዕታት ዘንባባው የክብር መቀበያ ከሥጋ ድካም የማለፋቸው ምክንያትም የሆነላቸውን ቅዱሳንም እናገኛለን። ከነዚህም ውሥጥ በሚያዝያ ወር የሚዘከሩ በሰማዕትነት ያረፉ ቅዱስ በብኑዳና ቅድስት ኮሮና (እሥጢፋና) በዘንባባ ላይ ተሰቅለው በዘንባባ መኃል ታሥረው ለክብር መብቃታቸውን የታሪክ መድብላችን ይመሰክራል።

🌴 ሰላም እብል ለበብኑዳ ሰማዕት፣… ሰቀልዎ ሎቱ መልዕልተ በቀልት 【ስንክሳር ዘሚያዝያ ፳】

🌴 ሰላም ለእስጢፋና እንተ ፃመወት በሕቁ፡
ለፊቅጦር ሰማዕት ተላዊተ ዐሠሩ ወጽድቁ፡
እለ ኰነንዋ ሐራ እስከ እምፍርሀት ወድቁ፡
በጒንደ በቀልት ዘአስተላጸቁ፡
ማኅፈቀ ሥጋሃ ለ፪ኤ ሠጠቁ፡፡ [የሰማዕቱ ፊቅጦርን ፍለጋና እውነት (ሕይወትና ሃይማኖት) የተከተለች የፈረዱባት ጭፍሮች ፈርተው እስከሚወድቁ ድረስ፤ በሰሌን ዛፍ በዘንባባ ግንድ ላይ አሥረዋት ሥጋ አካሏን ለሁለት እስኪሰነጥቁት ድረስ በእጅጉ ለደከመች ለእስጢፋና (ኮሮና) ሰላም ይሁን።] 【ስንክሳር ዘሚያዝያ ፳፯】

ወደ ሆሣዕናው ታሪክ ስንመለስ የዝክረ ቅዱሳን እስትግቡእ የሆነው መጽሐፈ ስንክሳር ስለዘንባባው የትመጣና ትርጉም ተከታዩን ሐሳብ ያስቀምጥልናል ።

«ማቴዎስና ማርቆስ የዘንባባን ነገር አላስታወሱም፤ ሌሎች ከዛፍ ላይ ቅርንጫፍ፡ ዘንጥፈው በመንገድ ላይ ጐዘጐዙ አሉ እንጂ ። ሉቃስም ዝንጣፊውንም ሆነ ዘንባባውን አላወሳም፤ ሲሄዱም ልብሳቸውን በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር አለ እንጂ ። ዮሐንስ ግን ብቻውን የሰሌን ዛፍ ዝንጣፊ ከኢየሩሳሌም ያዙ አለ ። ሰሌን በኢየሩሳሌም የለም ነበርና ጌታችን በሕፃንነቱ ከእናቱ ከክብርት ድንግል ማርያም ጋር ወደ ግብጽ ምድር በወረደ ጊዜ እስሙናይን ከተባለ አገር ደረሱ፤ በዚያም ሰሌን አገኙ ። ጌታችንም ከሥርዋ ተነቅላ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ትተከል ዘንድ አዘዛት ። ያን ጊዜም ወደ አየር ወጥታ በረረች በደብረ ዘይትም ላይ ተተከለች ። ከእርስዋም ዘንባባ ወስደው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ተቀበሉት፤ ሥርዓተ ሆሣዕናን እየዞረ አሳይቷልና ።»

ዘንባባው የመጣውና ደብረ ዘይት የተተከለው ከእስሙናይ (Eshmunen) ነው ያለውን ይዘን ታላቁ ሊቅ የእስሙናይ ሊቀጳጳሳት ቅዱስ ሳዊሮስ (Severus ibn al-Muqaffa) በበዓለ ሆሣዕናው ዙሪያ በመጽሐፉ የጻፈውን በድርሳኑ ፯ኛው ክፍል ላይ የምናገኘውን እናስታውስ

* እስከ ፴ ዓመቱ ድረስ በክርስቶስነቱ ማንም ሳያምንበት ኖረ ይህም ሮማውያንን ፈርተው እንደነበር በእሑድ ሰንበት በዕለተ ሆሣዕና ግን ሰማንያ አራቱ ደቀመዛሙርት (ሰባ ሁለቱ አርድእትና አስራሁለቱ ሐዋተርያት) ከደብረዘይት ይዘውት ሲወርዱ የሚነግሥና ከሮማውያኑ አገዛዝ ነጻ የሚያወጣቸው መስሏቸው በእብራይስጡ ሆሣዕና በአርያም በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው እያሉ ሲያመሰግኑት ህዝቡ ሁሉ የወይራ ዛፍ ከዘንባባ ዝንጣፊ ጋር ይዘው ልብሳቸውን እያነጠፉ እንደተቀበሉት ወደኢየሩሳሌምን ገብቶ ወደምኩራባቸውም አምርቶ እንደነገሥታቱ ተግባሩን ሲፈጽም ታየ እያለ እንደሚከተለው አስፍሯል። *

ወደ ምሥጢራዊው ትርጉም ስናልፍ ደግሞ ለምን በዕለተ ሆሣዕና በቦታው የተገኙት ዘንባባ በመያዝ ዘመሩ ለሚለው ተከታዩ አንድምታዊ ሐተታ በሊቃውንቱ ይነገራል ፦

☞ ዘንባባ ወይም ሰሌን እሾኻም ነው ትእምርተ ኃይል ትእምርተ መዊዕ (የኃይልና የድል ነሺነት ምልክት) አለህ ሲሉ እነርሱም ዘንባባውን ይዘው ታይተዋል ። (አንድም) ዘንባባን እሳት አይበላውም ለብልቦ ይተወዋል፤ ባሕርይህ አይመረመርም ሲሉ ከነዘንባባቸው እያጀቡት ወደ ኢየሩሳሌም ገብተዋል። (አንድም) ዘንባባ ረጅም / ልዑል/ ነው አንተም ባሕርይህ ልዑል ነው ሲሉ ዘንባባ ይዘው ተቀብለውታል፡፡

☞ የተምር ዛፍ ዝንጣፊ ነው ያሉ እንደሆነ ተምር ልዑል / ረዥም ነው ⇨ ልዑለ ባሕርይ ነህ ሲሉ። የተምር ፍሬውም በእሾህ የተከበበ ነው (ፍሬው በእሾህ የተከበበ ነው (በቀላሉ መለቀም አይቻልም) የአንተም ምስጢር አንተ ካልገለጠከው አይመረመርም ሲሉ) ⇨ በባሕርይህ አትመረመርም ሲሉ ነው፡፡ በዚያውም ላይ ፍሬው አንድ ነው ⇨ ዋህደ ባሕርይ ነህ ሲሉ ነው።

☞ ሰሌን ነው ያሉ እንደሆነ አብርሃም ይስሐቅን ይስሐቅ ያዕቆብን በወለዱ ጊዜ፤ እስራኤል ከግብፅ በወጡ ጊዜ፤ ዮዲት ሆሎፎርኒስን በገደለች ጊዜ፣ ሰሌን ቆርጠው ይዘው አመስግነዋልና በዚያ ልማድ።

(በዚያ ልማድ የተባሉትን ታሪኮች በአጭሩ ለማስታወስ እንዲረዳን ጥቂት ነገር እናውሳ… )

🌴 አብርሃም ላዳነውና በሔደበት ሀገር ደስ ላሰኘው ለእግዚአብሔር በዚያ መሠዊያን ሠራ… ደስ ብሎት አከበራት የዚህችን በዓል ስሟን የእግዚአብሔር በዓል አላት … የዘልዓለም ሥርዓት ሆኖ ተጽፏልና ለዚህ ሥርዓት የተወሰነ ዘመን የለውም፤ አብርሃም የሰሌኑን ጫፍ ለጋውን ያማረ የእንጨቱን ፍሬ ይዞ በየቀኑ ዘንባባውን ይዞ ሰባት ቀን የመሰዊያውን ዙርያ ይዞር ነበር" 【ኩፋ ፲፫፥ ፱,፲፯,፳,፳፩】

የሆሣዕናው ቅዳሴም የአብርሃምና የመልከጼዴቅን ነገር ሰፊ ቦታ ሰጥቶ ሲያወሳው እናያለን። ለዑደተ ሆሣዕና መነሻውም የአብርሐም ተግባር መሆኑን የመጋቢት ፳፪ቱ ስንክሳር እንደሚከተለው ይመሰክራል

« አብርሃምም ይቺን በዓል ደስታን የተመላች የእግዚአብሔር በዓል ናት ብሎ ጠራት፤ የሰሌን ዝንጣፊና ዘንባባን ይዞ መሠዊያውን ዙሮአልና»

🌴 መልከ መልካምና ደመግቡ የነበረች ታላቋ ሴት ዮዲት መቅደሱን ያሳደፉ ማደሪያውን ያረከሱ የእግዚአብሔር ጠላቶች ድል ስትነሳና የናቡከደነፆር ቢትወደድ የነበረውን ሆሎፎርኒስን ገድላ በበቅሎ ላይ ተቀምጣ ሠረገላ እየነዳች ወደ ሀገርዋ ስትገባ የእስራኤል ሴቶች ሊያይዋትና ሊመርቋት ሮጠው ወጡ "ደግ በዓል አደረጉላት ዘንባባም በእጇ ያዘች ከእርሷ ጋር ለነበሩትም ሠጠች" 【ዮዲ. ፲፭፥፲፪】

ለመቋጫ እንዲሆን ንጹሕ ክቡር የሚሆን ዐምዳዊው ስምዖን የደረሰው የሆሣዕና በዓል በተደረገ በከበረች የክርስቲያኖች ሰንበት የሚነበበውን ጸሎት ከግብረ ሕማማቱ በማስታወስ እንሰነባበት

[ … ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የዘይት (የወይራ ዛፍ) ዝንጣፊና የሰሌን ዘንባባ ተሸክሜ ከአርያም የተገኘ መድኃኒት መባል ለአንተ ይገባል እያልኩ ከሕፃናት ጋራ እጮኽ ዘንድ አድለኝ ። የዳዊት ልጅ ሆይ አማኑኤል እግዚብሔር ከእኛ ጋር ነው ማለት እንደሆነ ከአንተ ጋር አንድ አድርገኝ ። ወገኖችህ እንሆን ዘንድ አድርገን፤ በልቡናችን የጌትነትህን ብርሃን አብራ ። ከወገንህ ልጆች ውስጥ አድርገን ። እንተ ጠባቂያችን፣ መጋቢያችን፣ መሪያችን ነህ ። አንተም ንጉሣችን እኛም የወገንህ ልጆች፤ ንጉሣችንና አምላካችን ወደ እኛ መምጣትህ የተባረከች ናት፤ ከጨለማውም ግዛት አድነህ ብርሃንንና ክብርን ወደ ተመላች መንግሥትም አድርሰን ።በጨለማው ገዥ ከመረገጥ አድነን፤ ቃል ኪዳንህንና አምላካዊ ሕግህን በላያችን አጽና፤ በስምህ የሚያድን ሕይወትህን እንወርስ ዘንድ። ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ወደ ቤተ መቅደስ ገብተህ ርግቦች የሚሸጡትን ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል፤ እናንተ ግን የሌባና የወንበዴ ዋሻ አደረጋችሁት በማለት ያሳደድኻቸው ።
ከልቤና ከሰውነቴ የክፋት መንፈስን ሁሉና የተናቀ ነገር ማሰብን አስወግድ ። ልቡናዬንም የጸሎት ቤት አድርገው፤ ልቤንና ሐሳቤንም ስምህን ለማክበርና ለማመስገን አንቃቸው። …]

አሜን! 🙏 ሆሣዕና በአርያም 🙏

【 .🌴. ከቴዎድሮስ በለጠ Яερ๑รтεδ ƒя๑๓ ሆሣዕና ሚያዝያ ፱ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም. 】
2025/07/05 07:19:15
Back to Top
HTML Embed Code: