Telegram Web Link
"+" ነገረ ሃይማኖት "+"

የነገረ ሃይማኖት ትምህርት አጠር ተደርጎ የቀረበ፡-
ክፍል ፫

"+" ሃይማኖት እንዴት ተገኘ? "+"

“ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ፡፡” ይሁዳ 3
ሃይማኖት፡-
1) የተሰጠ፣ የተቀበልነው ነው፡፡ እግዚአብሔር ሃይማኖትን ሰጠ፣ እኛ ደግሞ ተቀበልን፡፡ የእኛ ድርሻ መቀበል ነው፡፡ የሰው ልጅ ሃይማኖትን ይቀበላል እንጂ ሃይማኖትን ሊሠራ ወይም ሊያሻሽል አይችልም፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፣ እነርሱም ተቀበሉት፡፡” በማለት የገለጸው ይህን ነው፡፡ ዮሐ. 17፡8
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ያመነውንና የያዘውን ሃይማኖት ከጌታ የተቀበለው መሆኑንና፣ ያን የተቀበለውንም በወንጌል ትምህርት እንዳወረሳቸው ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሲያሳስባቸው እንዲህ በማለት ገልጾላቸዋል፡- “ወንድሞች ሆይ፣ የሰበክሁላችሁን፣ ደግሞም የተቀበላችሁትን፣ በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን፣ በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤ … እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ፡፡” 1 ቆሮ. 15፡1-3 እንዲሁም ስለ ምሥጢረ ቁርባን ባስተማረበት አንቀጽ ላይ “ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ደግሞ ከጌታ ተቀብያለሁና…” ብሏል፡፡ 1 ቆሮ. 11፡23
ወልድ ዋሕድ መድኃኒታችንም “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል?” ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም፡- “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎችም ኤልያስ፣ ሌሎችም ኤርምያስ፣ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት፡፡ እርሱም፡-እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው፡፡ ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፡- አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ፡፡ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፡- የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፣ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ፡፡ እኔም እልሃለሁ፣ አንተ ጴጥሮስ ነህ፣ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፣ የገሃነም ደጆች አይችሏትም፡፡” ማቴ. 16፡ 13-18
በሥጋና ደም አስተሳሰብ (በሰው ምርምርና ሐተታ) ሰዎች ስለ ጌታችን ሊሉት የሚችሉት ያን ጊዜ የነበሩት ሰዎች እንዳሉት ‘መጥምቁ ዮሐንስ፣ ወይም ኤልያስ ወይም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው’ ከማለት ያለፈ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ሰው ሆኖ እያዩት አምላክነቱን መረዳት በሥጋና በደም አስተሳሰብ ሊደረስበት የሚችል ምሥጢር አይደለምና፡፡ ጴጥሮስ ግን የወልድ ዋሕድ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰማያዊ አባቱ አብ የገለጠለትን ነገር -የኢየሱስ ክርስቶስን የአብ የባሕርይ ልጅነት - ስለ ተናገረ ጌታችን አመሰገነው፤ “ስምዖን ሆይ፣ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ” አለው፡፡
መቼም ቢሆን በሃይማኖት እግዚአብሔር የገለጠውን ትተን በራሳችን አስተሳሰብና በሚመስለን መንገድ እንሂድ ካልን ወደ እውነተኛው ሃይማኖት ልንደርስ አንችልም፡፡ በሐዋርያት ዘመን ከነበሩት ዓይነት ሰዎች የተሻለ ነገር ልንል አንችልም፡፡ ከዚያ ለመውጣትና ጴጥሮስ የመሰከረውን ለመያዝ ከሥጋና ከደም አስተሳሰብ መለየት የግድ ይላል፡፡ ጌታችን “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው፡፡” ያለው ለዚህ ነው፤ ስሙንም፣ ማንነቱንም ሊገባን በሚችለው መጠን የገለጠልን ራሱ ነው እንጂ ሃይማኖት የሰው ልጅ በምርምር የደረሰበት ግኝት አይደለም፡፡ ዮሐ. 17፡6

2) ሃይማኖት የተሰጠው አንድ ጊዜ ነው - “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት …” ይሁዳ 3 ምግብናው እንደየ ዘመኑ ይለያያል፣ ይዘቱ ግን ያው አንድ ነው፡፡ ለምሳሌ ሕፃን ልጅ በሕፃንነቱ ወተትና ፍትፍት፣ ሲያድግ ደግሞ ጠንከር ያለ ምግብ ይሰጠዋል፣ የሰውነት ባሕርዩ ግን ያው አንድ ነው፣ አይለዋወጥም፡፡ ሃይማኖትም በዘመነ አበው፣ በዘመነ ኦሪት፣ በዘመነ ወንጌል የምግብናው ሁኔታ እንደየ ዘመኑ የሰዎች የመረዳት ዓቅምና ሁኔታ ቢለያይም ይዘቱ (ጭብጡ) ግን ያው አንድ ነው፡፡ “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዘመናትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን” ያለው ይህን የሚገልጽ ነው፡፡ ዕብ. 1፡1-2 የቅዱሳን መላእክት፣ የአበው ቀደምት የእነ አዳም፣ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሙሴ፣ ዳዊት፣ የነቢያት፣ ኋላም የሐዋርያትና የሰማዕታት፣ የጻድቃንና የሊቃውንት ሃይማኖት አንድ ነው፡፡
ስለዚህ ሃይማኖት የተሰጠው አንድ ጊዜ፣ ያውም ፈጽሞ (ያለ መቀናነስና ያለ ቀረኝ) ስለ ሆነ ተሐድሶ ወይም ለውጥ አያስፈልገውም ማለት ነው፡፡ ሃይማኖትን ይቀበሉታል፣ ይጠብቁታል፣ ያወርሱታል እንጂ ላድሰው፣ ላሻሽለው አይባልም፤ እንዲያ ከሆነ መጀመሪያ የተሰጠው ሃይማኖት ሕፀፅ ነበረበት፣ ወይም ምሉዕ አልነበረም ያሰኛል፡፡ እግዚአብሔር የሰጣት፣ አባቶቻችን ከእርሱ ተቀብለው ኖረውባት ለእኛ ያወረሱን ሃይማኖት ግን ፍጽምትና አንድ ጊዜ የተሰጠች ናት፡፡ ብልየት እርጅና የለባትም፣ ተሐድሶ ወይም ማደስ የሚለው ቃል ብላሽና ለሃይማኖት ሊነገር የማይችል ጸያፍ ነው፡፡

3) ሃይማኖት ተጋድሎ ያስፈልገዋል በሃይማኖት ተጋድሎ የሚያስፈልገው በተሰጠን ሃይማኖት ለመጠቀም እና ለመጠበቅ ነው፡፡ ጌታችን “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው፡፡ የአንተ ነበሩ፣ ለእኔም ሰጠሃቸው፤ ቃልህንም ጠብቀዋል፡፡” ያለው ቃሉን መቀበል ብቻ ሳይሆን መጠበቅም እንደሚገባ ሲነግረን ነው፡፡ ዮሐ. 17፡6 የተሰጠንን አጽንቶ ለመያዝና የሕይወትን አክሊል ለማግኘት እስከ ሞት ድረስ መጋደልና ታማኝነትን በተግባር ማስመስከር የግድ ይላል፤ “ኩን መሃይምነ እስከ ለሞት ወእሁበከ አክሊለ ሕይወት - እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን፣ የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ” ተብሏልና፡፡ ራእ. 2፡10
እንዲሁም በሃይማኖት ለመጠቀምም ተጋድሎ ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁ በማመን ብቻ መጠቀም አይቻልም፤ ባመኑት ለመጠቀም ተጋድሎ ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እስራኤላውያን በደብረ ሲና ከራሱ ከእግዚአብሔር፣ ኋላም ከሙሴ በተደጋጋሚ የእግዚአብሔርን ቃል በጆሯቸው ቢሰሙም በሰሙት ለማመንና ባመኑትም ለመጠቀም ጥረት ስላላደረጉና ስላልተጋደሉ እንዳልተጠቀሙ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፡- “የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም፡፡” ዕብ. 4፡2

ስለዚህ፡-ሃይማኖትን ይቀበሉታል፣
ይጠቀሙበታል
ይጠብቁታል
ያወርሱታል
እንጂ ማደስ፣ ማሻሻል በሃይማኖት የለም፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ፡፡

ይቀጥላል...
------------------------------------
በየእለቱ አጥንትን የሚያለመልሙ መንፈሳዊ ጽሁፎችን ለማግኘት ይቀላቀሉን፡-
👉 @rituaH @rituaH
👉 @rituaH @rituaH
👉 @rituaH @rituaH
"+"ነገረ ሃይማኖት"+"
የነገረ ሃይማኖት ትምህርት አጠር ተደርጎ የቀረበ
ክፍል ፬

"+"ዶግማ እና ቀኖና"+"

ትምህርተ ሃይማኖት(የሃይማኖት ት.ት) በሁለት ይከፈላል። ይኸውም፦
1ኛ ዶግማ
2ኛ ቀኖና
.
ዶግማ፦ ቃሉ የግሪክ ሲሆን ፍቺውም እምነት ማለት ነው።
.
ቀኖና፦ ደግሞ ቃሉ የግሪክ ሲሆን ሥርአት ማለት ነው።
ከእነዚህ ከሁለቱ ዶግማ ወይም እምነት አይጨመርበትም፣ አይቀነስበትም ፣ አይሻሻልም ፣ችግርና ፈተና ቢመጣም እስከ ሞት ድረስ አጥብቀን የምንይዘው ነው። ለምሳሌ ያህል ይህን አለም ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ የፈጠረ ቢመረምር እንጂ የማይመረመር ሁሉን ችይ አምላክ የሚሳነው ነገር የሌለ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ የሰማይና የምድር ባለቤት ሕያው እግዚአብሔር ነው።
.
እግዚአብሔር የአካል ሶስትነት እለው። በመለኮት፣በመፍጠር፣ በስልጣን፣በአገዛዝ በፈቃድ ግን እንድ ነው። በሶስትነቱ አብ ወልድ መንፈስቅዱስ ሲባል በአንድነቱ አንድ መለኮት አንድ እግዚአብሔር ይባላል። በአዳም ምክንያት ከመጣው የዘላለም ሞትና ከዲያቢሎስ ባርነት ነፃ የወጣነው ከሶስቱ አካላት በአንደኛው አካል ማለትም በወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህ ዶግማ ወይም እምነት ይባላል፤ መቼም ቢሆን ሊቀየር እና ሊሻሻል አይችልምና። አሻሽላለሁ የሚል ካለግን ቅዱሳን አባቶቻችን በሰሩት ሥርአት መሰረት ከቤ/ክ ተወግዞ ይለያል ለምሳሌ መናፍቃን ይህን በመካዳቸው(ለማሻሻል ጥረት በማድረጋቸው) ከቤ/ክ ተለይተዋል።
.
ቀኖና ግን በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ያደጉ ክርስቲያኖች የሚመሩበት ሥርአት ስለሆነ በሃይማኖት አባቶች ወይም በቅዱስ ሲኖዶስ አማካኝነት እንደ ጊዜው ሁኔታ የሚሻሻል በመሆኑ የሚጨመርለት የሚቀነስለት ነው። ለምሳሌ ያህል እኛ ኦርቶዶክሳውያን የምንጠመቀው ሴት በሰማንያ ወንድ በአርባ ቀናችን ነው። ነገር ግን ቀኑ ሳይሞላቸው ቢታመሙ እና ሁኔታቸው አስጊ ከሆነ በ10፣በ20፣በ30… ቀናቸው መጠመቅ ይችላሉ ቀኖና ነውና። በቤ/ክችን የቀዳስያን ብዛት መነሻው አምስት ነው ምናልባት ከአምስቱ አነዱ ፣ሁለቱ፣ሦስቱ ቢታጡና ሌላም ተፈልጎ የማይገኝ ከሆነ ከአቅም በላይ ችግር ከገጠመ ሁለቱ ወይም አንዱ ቀድሰው ማቁረብ ይችላሉ።ቀኖና ነውና። ስለ ቀኖና ቅ.ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ጽፏል።
.
1. "ነገር ግን ሁሉን በአግባብና በስርአት አድርጉ" 1ኛ ቆሮ 14፥40
2. "ወንድሞች ሆይ በሰራንላቸው ስርአት ሳይሆን በተንኮል ከሚሄዱት ወንድሞች ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኃላን። እኛን ልትመስሉ እንደ ሚገባችሁ እኛም በእናንተ መካከል ያለስራ እንዳልኖርን ራሳችሁ ታውቃላችሁ " 2ኛ ተሰ 3፥6-7 ቀኖና(ሥርአት) የሚወሰነው በአባቶች እንደሆነና ወንጌልን የሚያስተምር ሰው ለሚያስተምራቸው ክርስቲያኖች በሃይማኖት አባቶች የተወሰነ ቀኖና ማስተማርና መሰጠት እንዳለበት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ያስረዳል።
በየከተማውም ሲሄዱ ሐዋርያትና ቀሳውስት በኢየሩሳሌም ያዘዙትን/የወሰኑትን/ ሥርአት አስተማራቸው። አብያተ ክርስቲያናትም በሃይማኖት ጸኑ እለት እለትም ቁጥራቸው ይበዛ ነበር።" ይላል ሐዋ 16፥4-5። በዚህ የእግዚአብሔር ቃል መሰረት ቅ.ጳውሎስ ደርቤንና ልስጥራን በተባሉ ቦታዎች ለነበሩ ክርስቲያኖች ወንጌልን ከሰበከ በኋላ ሐዋርያት የወሰኑትን ቀኖና(ሥርአት) እንደሰጣቸው እንረዳለን። ስለዚህ ቀኖና ወይም ስርአት ቤተ ክርስቲያንን ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። በነሆኑም ዶግማንና ቀኖናን ወይም እምነትና ሥርአትን ጎን ለጎን ይዞ መጓዝ ሐዋርያትን መከተል ነው። እንግዲህ ሥርአተ ቤ/ክያንን የሚቃወሙ ሁሉ ፤የሚቃወሙት በቀኖና(በሥርአት) የሚመሩትን ክርስቲያኖች ሳይሆን የእግዚአብሔር ቃል የሆነ መጽሐፍቅዱስን በመሆኑ እንዳይሳሳቱ አደራ እንላለን።
.
… ሁልጊዜም ክርስቶስን በማመን በጸናች በቅዱሳን አባቶቻችን ሃይማኖት ጠብቆ ያቆየን።
… ወስብሐት ለእግዚአብሔር።

ይቀጥላል...
-----------------------------------
በየእለቱ መንፈስን የሚያለመልሙ አጥንትን የሚያጠነክሩ ጽሁፎችን ለማግኘት ይቀላቀሉን፡-
👉 @rituaH @rituaH
👉 @rituaH @rituaH
👉 @rituaH @rituaH
"+"ነገረ ሃይማኖት"+"
የነገረ ሃይማኖት ትምህርት አጠር ተደርጎ የቀረበ
ክፍል ፭

"+"ቅዱስ ትውፊት(Holy Tradition)"+"

ትውፊት ማለት ስጦታ ፣ልማድ ፣ወግ ፣ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ሥርአት ፣ከጥንት ከአበው ሲያያዝ ቃልበቃል ሲነገር የመጣ ማለት ነው። በቤ/ክ ትርጓሜው ስንመለከተው፦ ትውፊት ማለት፦ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች በጠቅላላ በአበው በነብያት በሐዋርያት በጳጳሳት በሊቃውንት በካህናት በኩል የሚያስተላልፈው ሕያው (ሕይወትን የሚስጥ) ቃል ማለት ነው። ይኽ ህያው ቃል ቀደምት አበው ከእግዚአብሔር ይተቀበሉትና ለቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፉት ቤተ ክርስቲያንንም በየጊዜው እስከ አለም ፍጻሜ ድረስ የምትጠቀምበት ሕያው ት/ት ነው።

#ክርስቲያናዊ ትውፊት
(Christian Tradition)
በብሉይ ኪዳን ከአበው ወደ መሳፍንት ከመሳፍንት ወደ ነገስታት ወደ ነብያት ሲተላለፍ ቆይቶ ኋላም በሐዲስ ኪዳን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት የተገለጠ ከክርስቶስ ወደ ሐዋርያት፣ከሐዋርያት ወደ ሐዋርያት አባቶች እና ወደ ተከታዮቻቸው ሰማዕታት ከዚያም ለሊቃውንት በአፍ (oral) እና በጽሑፍ (writen) እየተሸጋገረ ሲወርድ ሲዋረድ እስከ ዘመናችንም የደረሰ የክርስትና ት/ት ነው።
በቅዳሴአችን ጊዜ ቄሱ "ነዋ ወንጌለ ነንግስት- መንግስተ ሰማያትን የምትሰብክ አንድም ወደ መንግስተ ሰማያት የምታገባ ወንጌል ይህቺ ናት" ብሎ ለንፍቀ ካሕኑ መስጠቱ ፤ ንፍቀ ካሕኑም " መንግስቶ ወጽድቆ ዘአወፈየኒ አወፈይኩከ - ጌትነቱንና ቸርነቱን የምትናገር የሰጠኝን ወንጌክ የምትናገር የሰጠኸኝን ወንጌል ሰጠኹኽ" ብሎ ለዲያቆኑ መስጠቱ ሐዋርያት ከሊቀ ካሕናችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልን ተቀብለው ለማስተማራቸው አምሳል ነውና ትውፊት ቅብብል፣ውርርስ መሆኑን በግልጽ ያሳያል /ሥርአተ ቅዳሴ 10፥53 አንድምታው/።
ትውፊት ሲባል ስላለፈ ነገር ብቻ የሚናገር ነገር ግን በእኹኑ ሰአት ምንም ሕይወት እንደሌለው ተደርጎ የሚታሰብ አይደለም። አኹንም ሕይወትን የሚሰጥ ነው። ለምሳሌ በኋላ የምንመለከተው መጽሐፍ ቅዱስ አንዱ የትውፊት አካል ነው ነገር ግን ስላለፈው ነገር ብቻ የሚናገር አይደለም። አኹንም ሕይወትን የሚሰጥ ነው። ስለዚሕ ትውፊትን መቀበል ያለፈውን ነገር የመጠበቅ ጉዳይ አይደለም ማለት ነው ፤ የሕይወት ጉዳይ እንጂ። በሌላ አነጋገር የምንጠብቀው የሐይወት ጉዳይ እንደሆነ ስለሚገን ነው።
እግዚአብሔር በዚሁ ቅዱስ ትውፊት ሲናገር ስላለፈው ነገር ብቻ ሳይሆን ስለአሁኑም ስለሚመጣውም ዘለአለማዊ ሕይወት ነው። ትውፊትን ቅዱስ ብለን መጥራታችንም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ስለማይለየው አንድም ከክርስቶስና ክርስቶስ አድሮባቸው ከሚኖሩ ከቅዱሳን ስለተገኘ ነው።
እንደ ኦርቶዶክሳዊ ተዋህዶ ቤ/ክ አስተምህሮ ፥እግዚአብሔር ከፍጥረት መጀመሪያ አንስቶ በጽሑፍም ያለጽሑፍም የገለጠውን እውነት የምናገኘው በቅዱስ ትውፊት ውስጥ ነው። በመሆኑም የተጻፈውና ይልተጻፈው ቅዱስ ትውፊት ለድህነታችን የሚሆን የእግዚአብሔርን መገለጥ የያዘ ስለሆነ እኩል አስፈላጊ ነው።
#መጽሐፍ ቅዱስ አንዱ የትውፊት አካል ነው!!!
ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያውን ስፍራ የሚይዝ (የመጀመሪያ ስፍራ ይይዛል ስንልም ካልተጻፈው ቅዱስ ትውፊት ይልቅ በቀላሉ ለስህተት የማይጋለጥ በመሆኑ ነው። ምክንያቱም በቀኖና አንዴ ተወስኖ የቀረበ ነውና። በዚሕም ያልተጻፈው ቅዱስ ትውፊት የሚመዘንበት ሚዛን ነው።) ቢሆንም ከሌላው የትውፊት አካል ግን ተነጥሎ የሚታይ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁ ጽሑፍ አይደለም። ሊብራራና በሕይወት ሊተረጎም የሚገባው ነው። ይኽም የሚሆነው የእውነት አምድና መሰረት በምትሆን በቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ ሕይወት ነው። 1ኛ ጢሞ 3፥15። የሊቃውንተ ቤ/ክ መጽሐፍት ይኽን መጽሐፍ በስፋትና በጥልቀት የሚተረጉሙ እንጂ እንደ ተጨምልሪ የሚታዩ አይደሉም። የቅዱሳኑ ገድላት በመጽሐፍ ቅዱስ የታዘዘውን እውነት በተግባር እንዴት እንደኖሩት የሚያሳይ ነው። ሌላ ወንጌል አይደለም ማለት ነው። ቅዱሳት ስእላቱ በሕብረ ቀለማትና በጥበባዊ መንገድ ነገረ እግዚአብሔርን ማንበብ ለማይችል ሰው የሚያብራሩ ናቸው። ቅዳሴው ስርአት ጸሎቱ ፣ የምስጢራተ ቤ/ክ አፈጻጸሙ ፣ ማዕጠንቱ፣ እና የመሳሰለው ሁሉ ሥርአት አምልኮው የሚፈጸምበት መንገድ ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስና ሌላው ቅዱስ ትውፊት ርስ በርሳቸው የሚደጋገፉ ናቸው። አንዳቸው አንዳቸውን የሚተረጉሙ እንጂ መናፍቃን እንደሚሉት የሚጣረሱ አይደሉም። በመጽሐፍ ቅዱስ ያልተጻፈው ሌላው ቅዱስ ትውፊት ነው የሚሞላው። በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው እውነት ትክክለኛ ትርጉሙን የምናገኘው በሌላው ቅዱስ ትውፊት ውስጥ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከሰፊው የቤተክርስቲያን ትውፊት ዋና ዋናውን የያዘ እንጂ ብቻውን የቆመ አይደለም። ወንጌል ከመጻፉ በፊት የነበረውንም ሁሉንም በጽሑፍ የያዘ አይደለም / ዮሐ 20፥30-31 "ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፤ ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎላችኋል።" ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ መናፍቃኑ እንደሚሉት ያለ ትውፊት ብቻውን ፍጻሜ የለውም። በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም አስተምህሮ ሌላውን ቅዱስ ትውፊት ከቅዱስ መጽሐፍ ጋር እኩል ሊቀበሉት የሚገባ የመለኮታዊ መገለጥ ምንጭ ነው ማለታችንም ከዚሁ የተነሳ ነው።
...ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ይቀጥላል...
-----------------------------------
በየእለቱ መንፈስን የሚያለመልሙ አጥንትን የሚያጠነክሩ ጽሁፎችን ለማግኘት ይቀላቀሉን
👉 @rituaH @rituaH
👉 @rituaH @rituaH
👉 @rituaH @rituaH
"+" ነገረ ሃይማኖት "+"

"+" የሃይማኖት ትምህርት አጠር ተደርጎ የቀረበ "+"
ክፍል ፮

ቅዱስ ትውፊት...የቀጠለ

"+" ቅዱስ ትውፊት በዘመነ ብሉይ"+"
ትውፊት የምእመናን የዘወትር ሕይወት ነው፡፡በመኾኑም ትውፊት ሰው ከመፈጠሩ አንሥቶ የነበረ ነው፡፡እግዚአብሔር አዳምን፡- “መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ከርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለኽና” ብሎ ሲነግረው በጽሑፍ አልነበረም /ዘፍ.2፡17/፡፡አዳምና ሔዋን በገነት ለሰባት ዓመታት ሲኖሩ ይኽን ቅዱስ ትውፊት ጠብቀው ነው፡፡እግዚአብሔር ስይቅርና፥ሰይጣን እንኳን አዳምንና ሔዋንን ያታለላቸው በጽሑፍ አልነበረም፤ቅዱስ ባልኾነውና ከራሱ ካመነጨው ሐሰት እንጂ /ዘፍ.3/፡፡
ቅዱሱ ትውፊት በአቤል በኵል ሲቀጥል፥ዲያብሎስ ያስተዋወቀው ቅዱስ ያልኾነው ትውፊትም በቃየን በኵል ቀጥሏል፡፡የአቤልና የቃየን ትውፊት ግን በቃል እንዲኹም በግብር እንጂ በጽሑፍ የወረሱት አልነበረም /ዘፍ.4/፡፡
ኄኖክ አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር አድርጐ ሞትን ሳይቀምስ የሔደው በቅዱሱ ትውፊት ሥርዓት መሠረት ስለኖረ ነው፡፡ኖኅ በዚያ ኀጢአት በነገሠበት ዘመን ጻድቅ ኾኖ የተገኘው፥ባልተጻፈው በቅዱሱ ትውፊት እንጂ ከእግዚአብሔር በጽሑፍ ያገኘው ነገር ስለነበረ አይደለም፡፡ኖኅ ንጹሐንና ንጹሐን ያልኾኑትን እንስሳት ለይቶ ያወቀው በጽሑፍ አልነበረም፡፡አብርሃም እግዚአብሔርን አምኖ ከቤተሰቡ ተለይቶ ሲወጣም በጽሑፍ አይደለም፡፡ኖኅ፣አብርሃም፣ይስሐቅና ያዕቆብ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ይሠዉ ነበር፡፡ነገር ግን በጽሑፍ የተሰጣቸው መመሪያ ስለ ነበረ አይደለም፡፡ዮሴፍ በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት ማድረግ እንደማይገባ የተማረው ከቅዱስ ትውፊት በቃል እንጂ በጽሑፍ አይደለም፡፡በአጠቃላይ፥ሊቀ ነቢያት ሙሴ በ1500 ከክርስቶስ ልደት በፊት ተነሥቶ መጽሐፍ እስኪጽፍ ድረስ፥የእግዚአብሔር ሰዎች ከ4000 ዓመታት በላይ ሲመሩ የነበረው በጽሑፍ ሳይኾን በቃልና በተግባር በሚገለጠው ቅዱስ ትውፊት ነበር፡፡
ቅዱስ ትውፊት በዘመነ ሐዋርያት

"+" በዘመነ ሐዲስ ያለውን "+" ስንመለከትም፥ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስት ዓመት በላይ ሕዝቡን ደቀ መዛሙርቱን ያስተምር የነበረው በጽሑፍ አልነበረም፡፡ቅዱሳን ሐዋርያትም ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበሉት በወረቀት የተጻፈ ነገር አልነበረም፡፡ወንጌላውያን ከጌታ በቃል ተምረው በተግባር አይተው ኋላ የሚጽፉትን እየዞሩ አስተማሩ እንጂ አስቀድመው ጽፈው ጠቅሰው አላስተማሩም፡፡መጻሕፍት መጻፍ የተዠመሩት፥ቤተ ክርስቲያን በይፋ ከተመሠረተች ከ8 ዓመታት በኋላ ነው (ከሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት መዠመሪያ የተጻፈው መጽሐፍ የማቴዎስ ወንጌል ሲኾን ይኸውም በ41 ዓ.ም. ላይ ነው)፡፡እስከዚኽ ጊዜ ድረስ ቤተክርስቲያን ስትመራ የነበረው በቃልና በተግባራዊ ምልልስ ሲተላለፍ በነበረው ቅዱስ ትውፊት ነው፡፡በሌላ አገላለጽ ወንጌል ከመጻፉ በፊት፥ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን በቅዱስ ትውፊት ታውቋለች፡፡ወንጌልን ስትኖረው ነበረች፡፡
ከጌታችን ጋር ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከዋለበት እየዋሉ፣ካደረበት እያደሩ ሲያስተምር፣ሲጸልይ፣ሰዎችን ሲያጽናና፣ድውያነ ሥጋን በተአምራት ድውያነ ነፍስንም በትምህርት ሲፈውስ፣ሙታነ ሥጋንና ሙታነ ነፍስን ሕይወት ሲሰጣቸውዐ ይተዋል፤ሰምተዋል፡፡ሥርዓተ ብሉይን አሳልፎ ሥርዓተ ሐዲስን ሲሠራ ተመልክተዋል፡፡ነገር ግን ይኽን ኹሉ በትውፊት ለተላውያነ ሐዋርያት (Apostolic Fathers - ተላውያነ ሐዋርያት የሚባሉት ከሐዋርያት በቀጥታ የተማሩ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡) አስረከቡት እንጂ፥እነርሱ ራሳቸው እንደነገሩን ኹሉንም አልጻፉልንም፡፡የጻፉልን እጅግ ጥቂቱን ብቻ ነው /ዮሐ.21፡25፣ 1ኛዮሐ.1፡1/፡፡ “እንድጽፍላችኁ የምፈልገው ብዙ ነገር ሳለኝ በወረቀትና በቀለም ልጽፈው አልወድም፡፡ዳሩ ግን ደስታችኁ ፍጹም እንደኾነ ወደ እናንተ ልመጣ አፍለ አፍም ልነግራችኁ ተስፋ አደርጋለኹ” እንዲል /2ኛዮሐ.12፣ 3ኛዮሐ.13-14/፥እንኳንስ የጌታችን ይቅርና እነርሱ ራሳቸው ያስተማሩትን ትምህርት ያደረጉትንም ተአምራት በሙሉ አልጻፉልንም፡፡በጽሑፍ የጻፉትም ቢኾን በቃል ያስተማርዋቸውን ምእመናን እንዲጸኑበትና አንዳንድ ቢጽሐሳውያን (ሐሰተኛ ወንድሞች) እውነቱን አዛብተው መጻፍ ስለዠመሩ እንዳይታለሉ ለመጠበቅ ጥቂቱን ነው /ሉቃ.1፡2/፡፡ዋናው መሠረታቸው ግን ከላይ እንደገለጽነው በቃልና በተግባራዊ ሕይወት የተማሩት ትምህርት ነው፡፡
ስለዚኽ ቅዱስ ትውፊት እያልነው ያለ ነው፥እንዲኽ ዓይነቱን በገቢርና በቃል ዕለት ዕለት በቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ሕይወት የሚገለጠውና አንድ ጊዜ ለቅዱሳን የተሰጠውን ሃይማኖት ነው /ይሁዳ ቁ.3/፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይኽን በማስመልከት ሲናገር እንዲኽ ይላል፡- “ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠኁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለኹና” /1ኛቆሮ.11፡23/፡፡ከዚኽ የሐዋርያው ቃል እንደምንረዳው፥ቅዱስ ትውፊት ማለት አንዳንድ የተሳሳቱ ሰዎች እንደሚሉት የአሮጊቶች ተረትተረት ወይም ከሰው የተገኘው ርስ ሳይኾን መለኮታዊ ስጦታ እንደኾነ ነው፡፡ “ትጸኑ ዘንድ መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችኁ ላያችኁ እናፍቃለኹና” /ሮሜ.1፡11/፡፡
#የቅዱስ ትውፊት ዋና ማዕከሉ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡በሌላ አገላለጽ ቅዱስ ትውፊት ወንጌል ነው፡፡በዘመነ ብሉይ ቢነገር ይወርዳል ይወለዳል ብሎ ነው፤በዘመነ ሐዲስ ቢነገር ደግሞ ወረደ ተወለደ ብሎ የምሥራችን ለትውልድ ኹሉ በቃልም፣በገቢርም፣በጽሑፍም የሚያውጅ ነው፤ቅዱስ ትውፊት፡፡ “ወንድሞች ሆይ! የሰበክኁላችኁን ደግሞም የተቀበላችኁትን በርሱም ደግሞ የቆማችኁበትን በርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለኹ፡፡በከንቱ ካላመናችኁ በቀር ብታስቡት በምን ቃል እንደሰበክኁላችኁ አሳስባችኋለኹ፡፡እኔ ደግሞ የተቀበልኹትን ከኹሉ በፊት ሰጠኋችኁ” እንዲል /1ኛቆሮ.15፡1/፡፡
ይቆየን
ይቀጥላል...
-----------------------------------
በየእለቱ መንፈስን የሚያለመልሙ አጥንትን የሚያጠነክሩ መንፈሳዊ ጽሁፎች እንዲደርሶት ይቀላቀሉን፡-
👉 @rituaH @rituaH
👉 @rituaH @rituaH
👉 @rituaH @rituaH
"+"ልደታ ለማርያም"+" እንኳን አደረሳችሁ!

"ከዕሴይ ሥር በትር ትወጣለች"

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግንቦት አንድ ቀን (የግንቦት ልደታ) የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ልደት የሚከበርበት ዕለት ነው፡፡ ይህ ዕለት ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ‹‹የመመኪያችን ዘውድ፣ የንጽሕናችንም
መሰረት›› ያላት ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም
የተወለደችበት ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ‹‹ድንግል ትጸንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች (ኢሳ 7፡14)›› ብሎ ትንቢት የተናገረላት ያቺ ድንግል በዚህች ዕለት ተወለደች፡፡
ይህች ቀን ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት ‹‹ የወርቅ ልብስ ተጎናጽፋ ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች (መዝ 44፡9)›› ብሎ የተናገረላት ንግሥት የተገኘችባት ዕለት ናት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በራዕዩ ‹‹ፀሐይን የተጎናጸፈች፣ ጨረቃን የተጫማች፣ አስራ ሁለት የክዋክብት አክሊል በራሷ ላይ ያላት
(ራዕ 12፡1)›› ብሎ የመሰከረላት የብርሃን እናቱ ድንግል ማርያም የተወለደችባት ቀን ናት፡፡ የእርስዋም ልደት እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ ድንገት የተከሰተ ሳይሆን አስቀድሞ በትንቢት፣ በምሳሌና በራዕይ የሰውን ልጅ ድኅነት
በጉጉት ሲጠባበቁ ለነበሩ ቅዱሳን ሲገለጽ የነበረ ነው፡፡

የድንግል ማርያም ልደት በነቢያት አንደበት

መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን፡ መሠረቶችዋ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው፡፡ መዝ 86፡1-7
እግዚአብሔር የዝማሬና የትንቢት ጸጋን ያበዛለት ክቡር ዳዊት ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥርወ ልደት አስቀድሞ በመንፈስ ቅዱስ መነጽርነት ተገልጾለት ‹‹መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን /መሠረቶችዋ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው/›› በማለት ትንቢት ተናግሯል፡፡ ‹‹የተቀደሱ ተራሮች›› ያለውም የእመቤታችን ሥርወ ልደት ከቤተ መንግሥትና ከቤተ ክህነት ከሆኑት ከተቀደሱት ከኢያቄምና ከሐና የመሆኑን ነገር ሲያመለክት ነው፡፡ ይህንን ትንቢትና እውነተኛውን የእመቤታችንን የትውልድ ሀረግ አስማምታ
ቤተክርስቲያን ‹‹የእመቤታችን ማርያም ትውልዷ ባባቷ በኩል ከንጉሡ ከዳዊት ወገን ነው፤ በናቷም በኩል ከካህኑ ከአሮን ወገን ነው፤ የአባቷ ስም ኢያቄም ነው፤ የእናቷም ስም ሐና ነው፡፡›› ብላ ታስተምራለች፡፡
"ትወፅእ በትር እምሥርወ ዕሴይ ወየዐርግ ጽጌ እምኔሃ፡" "ከዕሴይ ሥር በትር ትወጣለች፤ አበባም ከእርሷ ይወጣል፡፡" ኢሳ ፲፩፡፩
ቁጥሩ ከዐበይት ነቢያት ወገን የሆነው ነቢዩ ኢሳይያስም ጥበብንና እውቀትን በሚገልጽ ስለሚመጣውም ነገር ትንቢትን በሚያናግር በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ልደት ከነገደ ዕሴይ እንደሚሆንና
እርሷም ጽጌ (አበባ) የተባለ አካላዊ ቃል ክርስቶስን በሕቱም ድንግልና እንደምትወልድ ተገልጾለት ‹‹ትወፅእ በትር እምሥርወ ዕሴይ ወየዐርግ ጽጌ እምኔሃ /ከዕሴይ ሥር በትር
ትወጣለች፤ አበባም ከእርሷ ይወጣል/›› በማለት ታላቅ ትንቢትን ተናግሮ ነበር፡፡ ይህች በትርም ከእሴይ ዘር የተገኘችው በዚህች ዕለት ነውና ልደቷን በታላቅ ድምቀት እናከብራለን፡፡ ይህንን መሰረት በማድረግ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም
‹‹መልካሟ ርግብ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ፤ ከእሴይ ሥር የተገኘሽ መዓዛሽ ያማረ አበባ አንቺ ነሽ›› በማለት በውዳሴ አመስግኗታል፡፡ ‹‹በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ (መዝ
131፡13)›› የተባለልን የአባቶቻችን ልጆች እኛም እንዲሁ እያልን እናመሰግናታለን፡፡
ንዒ እምሊባኖስ መርዓት ንዒ እምሊባኖስ፡ ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ፡፡ መኃ 4፡8
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት መሰረት የእመቤታችን የትውልድ ስፍራ ሊባኖስ የተባለው ተራራማ ሀገር ነው፡፡ በሊባኖስ ስለመሆኑ አስቀድሞ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ንዒ እምሊባኖስ መርዓት ንዒ እምሊባኖስ ንዒ ወተወፅኢ እምቅድመ ሃይማኖት እምርእሰ ሳኔር ወኤርሞን አምግበበ አናብስት ወእምአድባረ አናምርት /ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ ከአማና ራስ ከሳኔር
ከኤርሞን ራስ ከአንበሶች መኖሪያ ከነብሮችም ተራራ ተመልከች/›› በማለት ተናግሮ ነበር፡፡ የዚህ ትንቢት ምስጢርም የእመቤታችን መካነ ልደት የሊባኖስ ተራራ ስለመሆኑ የሚያጠይቅ እንደሆነ ምስክርነታቸው የታመነ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡ ትንቢቱም ሲፈጸም ቅድስት ድንግል ማርያም ግንቦት 1 ቀን በ15 ዓ.ዓ ቅድመ ልደተ
ክርስቶስ በሊባኖስ ተራራ ተወልዳለች፡፡
ኢትዮጵያዊ ቄርሎስ የተባለው የነገረ ማርያም ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ እመቤታችን በሊባኖስ እንደምትወለድ አስቀድሞ ሰሎሞን የተናገረው ቃልም መፈጸሙን ሲገልጽ ‹‹….የአናብስት ልጅ አልኩሽ፡፡ ሰሎሞን እንዲህ ሲል እንደተናገረ፡- ሙሽራዪት ሆይ ከሊባኖስ ተራራ ነዪ፤ ከአንበሶች ጒድጓድ ወጥተሽ ነዪ፤ ከምርጥ ነገድነት የተነሣ ከሚመካ ወገን የመወለድሽ ዜና እጅግ ግሩም ነው፡፡›› በማለት አመስጥሮታል፡፡ እመቤታችንም በሊባኖስ ተራራ እንድትወለድ ምክንያት የሆነው በማሕፀን ሳለች የአርሳባንን ልጅ ዓይን በማብራቷና ሳሚናስ የሚባለውን የጦሊቅን ልጅ
ከሞት በማስነሳቷ አይሁድ በቅናት ተነሳስተውባቸው ስለነበር ሐናና ኢያቄም ወደ ሊባኖስ ተራራ እንዲሄዱ ታላቁ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ለኢያቄም ተገልጾ ስለነገራቸው እንደሆነ
የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡

የድንግል ማርያም ልደት በራዕይና በምሳሌ

ከትንቢቱ በተጨማሪም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ልደት በራዕይና በምሳሌም አስቀድሞ የተገለጸ ነበር፡፡ ከእነዚህም መካከል ከእርሷ ሰባት ትውልድ አስቀድሞ ለነበሩት ደጋግ ሰዎች እንዲሁም ለእናትና ለአባቷ የተገለጹት ምሳሌዎች በቅዱሳት መጻሕፍት በሰፊው ሰፍረው ይገኛሉ፡፡
ሰባተኛዪቱ እንቦሳ ጨረቃን ስትወልድ ጨረቃዋ ደግሞ ፀሓይን ስትወልድ አየሁ (ቴክታ) በቅድስና የሚኖሩ ነገር ግን መካን የነበሩት ቴክታና ጴጥርቃ ነጭ እንቦሳ ከበረታቸው ስትወጣ ፤ እንቦሳይቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ስድስት ስትደርስ፤ ስድስተኛዪቱ ጨረቃን ጨረቃዋም ፀሐይን ስትወልድ አይተው በሀገራቸው መፈክረ
ሕልም (ሕልም ፈች ሊቅ) አለና ሂደው ነገሩት፡፡ ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ፤ ጨረቃይቱ ከፍጡራን በላይ የምትሆን ልጅ ትወልዳላችሁ፡፡ የፀሐይ ነገር ግን አልተገለጸልኝም፤ እንደ ነቢይ እንደ ንጉሥ ያለ ይሆናል አላቸው፡፡ እነርሱም ጊዜ ይተርጉመው ብለውት ሄዱ፡፡ ከዚህ በኋላ ልጅ ወለዱ፡፡ ስሟንም ‹‹ረከብኩ ስእለትዬ፤ ረከብኩ ተምኔትዬ›› / የተሳልኩትን አገኘሁ፤ የተመኘሁትን አገኘሁ/ ሲሉ ‹‹ሄኤሜን››አሏት፡፡ ሄኤሜን ዴርዴን፤ ዴርዴ ቶናን፤ ቶና ሲካርን፤ ሲካር ሄርሜላን፤ ሄርሜላ ሐናን ወለደች፡፡ ሐና ለአካለ መጠን ስትደርስ ከቤተ ይሁዳ ለተወለደ ኢያቄም ለሚባል ደግ ሰው አጋቧት፡፡ ከኢያቄምና ከሐናም በጨረቃ የተመሰለች ድንግል ማርያም ተወለደች፡፡
ፀዓዳ ርግብ ሰባቱ ሰማያትን ሰንጥቃ መጥታ በማሕፀኔ ስታድር አየሁ (ቅድስት ሐና) ኢያቄምና ሐና መካን ስለነበሩ እግዚአብሔር ልጅ ይሰጣቸው
ዘንድ ጸልየው፤ ሲሰጣቸውም መልሰው ለእርሱ እንደሚሰጡ ስዕለትን ተስለው ነበር፡፡ ጸሎታቸው ሲደርስ ለሐና በሕልም ተገልጾላት ለባለቤቷ ለኢያቄም ‹‹ብእሴሃ አነኑ ርኢኩ በሕልምየ ርግብ ጸዐዳ መጽአት ኀቤየ ወነበረት ዲበ ርእስየ ወቦአት ውስተ እዝንየ ወኀደረት ውስተ ከርሥየ /ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብቶ በማሕፀኔ ስትተኛ አየሁ፡፡›› ብላዋለች፡፡ የዚህ ራእይ ምስጢርም ርግብ የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስትሆን፤ ፀዓዳ (ነጭ) መሆኗ ንጽሕናዋ
፣ ቅድስናዋ፣ ዘላለማዊ ድንግልናዋ ነው፡፡ ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማሕፀኔ ስትተኛ አየሁ›› ማለቷ ብሥራተ ገብርኤልን በጆሮዋ ሰምታ በግብረ መንፈስ ቅዱስ አምላክን የምትፀንሰውን ንጽሕት ርግብ የተባለችውን እመቤታችንን የምትወልድ መሆኗን ሲያጠይቅ ነው::
ከሰባተኛው ሰማይ ነጭ ዖፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ (ቅዱስ ኢያቄም)
በተመሳሳይ ኢያቄምም በሕልሙ ያየውን ለባለቤቱ ለሐና ‹‹እንዘ ይትረኀዉ ሰብዐቱ ሰማያት ዖፍ ጸዐዳ መጽአ ኀቤየ ወነበረ ዲበ ርእስየ /ሰባቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ዖፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ›› ብሎ በሕልሙ የተገለጸለትን ነግሯታል፡፡ የዚህም ራዕይ ምስጢር ዖፍ የተባለው አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን፤ ነጭነቱ ንጽሐ ባሕርዩ ነው፡፡ ኢያቄም ‹‹ከላይ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ›› ማለቱ የኢያቄምን ባሕርይ ባሕርይ እንደሚያደርግ የሚያጠይቅ ሲሆን ሰባቱ ሰማያት የተባሉ የጌታችን ልዩ ባህርይው፣ ምልአቱ፣ ስፍሃቱ፣ ርቀቱ፣ ልእልናው፣ ዕበዩና መንግስቱ ናቸው:፡

የድንግል ማርያም ልደት በሐዲስ ኪዳን ሊቃውንት

የሐዲስ ኪዳን ሊቃውንትም ትንቢተ ነቢያትንና ወንጌልን በማጣጣም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ልደት አመስጥረው አስተምረዋል፤ አመስግነዋል፤ ተቃኝተዋልም፡፡
የእርሷን ልደት እጅግ ብዙ ሊቃውንት በስፋትና በጥልቀት ያመሰጠሩት ሲሆን ለምሳሌ ያህል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡
ማርያምስ ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች (ቅዱስ ያሬድ) ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ስለእመቤታችን ልደት ‹‹ማርያምሰ ተኀቱ እምትካት ውስተ ከርሱ ለአዳም ከመ ባሕርይ ጸዓዳ/ ማርያምስ (ማርያም ግን) ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች፡፡›› በማለት እርሷ በደፈረሰው ዓለም በንጽሕና፣ በቅድስናና በድንግልና ስታበራ እንደነበርና ኋላም የዓለም ብርሃን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን መውለዷን አመስጥሮ ተናግሯል፡፡ በተጨማሪም ስለ ሥርወ ልደቷ ‹‹እንተ በምድር ሥረዊሃ ወበሰማይ አዕጹቂሃ…ሐረገ ወይን/ ሥሮቿ በምድር ጫፎቿም በሰማይ ያሉ…የወይን ሐረግ›› በማለት የተወለደችው በምድር ከነበሩት ኢያቄምና ሐና መሆኑን የወለደችው ግን ሰማያዊውን ንጉሥ እንደሆነ በማመስጠር ዘምሯል፡፡ በዚህም ሰውና እግዚአብሔርን ያገናኘች መሰላል መሆኗል ገልጾ አስተምሯል፡፡
ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም፤ በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐናና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ (አባ ሕርያቆስ) የብህንሳው ሊቀ ጳጳስ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም ‹‹ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ/ ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም፤ በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐናና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ›› በማለት የድንግል ማርያም ጽንሰትና ልደት እንዴት እንደነበር በድርሰቱ አስፍሮታል፡፡
ትውልድ ሁሉ ብፅዕት የሚላት የሁላችን እናት ድንግል ማርያም በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐናና ከኢያቄም ነሐሴ 7 ቀን ተፀንሳ ከዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በኋላ ግንቦት 1 ቀን ተወልዳለች፡፡ እርስዋም ስትፀነስ ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ ከጥንተ አብሶ (original Sin) ጠብቋታል፤ አበሳው
አልነካትም፡፡ ይህንንም ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ በኃጢአት በተከበበ፣ መርገም በሞላበት ዓለም ውስጥ ከኃጢአት ከበደል ርቃ (ተለይታ) እንደ ጌዲዮን ጸምር በንጽህና የጠገኘች ንጽህት ዘር መሆኗን ሲያስረዳ ‹‹የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ
ሰዶም በሆንን እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር (ኢሳ 1፡19)፡፡›› በማለት ተናግሯል፡፡ እንዲሁም ጠቢቡ ሰሎሞን ንጽህናዋን በትንቢት መነጽር አይቶ “ወዳጄ ሆይ፣ ሁለንተናሽ ውብ ነው፣ ምንም ነውር የለብሽም፡፡ ሙሽሪት ሆይ ከሊባኖስ ነዪ፡፡” (መሓልይ 4፡7-16) በማለት በንጽህና በቅድስና ያጌጠች፣ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ያልነካት፣ የድህነታችን ምክንያት፣ የንጽህናችን መሰረት የሰው ባህርይ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲዋሀድ ምክንያት የሆነች ንጽሕት የሰርግ ቤት ድንግል ማርያም በሊባኖስ የመወለዷን ነገር አስቀድሞ ነግሮናል፡፡
ይህች ዕለት ትልቅ ሕንፃ የታነጸበትና ፍጡር የፈጣሪ ማደሪያ ለመሆን የተዘጋጀባት ዕለት ናት (ቅዱስ እንድርያስ) የቀርጤሱ ቅዱስ እንድርያስ የከበረ ስለሆነው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት ታላቅነት ‹‹ይህ በዓል በሐዲስና በብሉይ ኪዳን መካከል መገኛ ሆነ፡፡
ምሳሌዎቹ በእዉነታ፣ አሮጌው በአዲስ ቃል ኪዳን ተተኩ፡፡ ፍጥረት ሁሉ በደስታ ይዘምራል፤ የዚህን ቀንም ደስታ ይካፈላል፡፡ ይህ ዕለት (ጌታ) መቅደሱን የሰራበት ዕለት ነው፡፡
ይህ ዕለት ትልቅ ሕንፃ የታነጸበትና ፍጡር የፈጣሪ ማደሪያ ለመሆን የተዘጋጀበት ዕለት ነው፡፡” በማለት ገልጾታል፡፡
በእውነት የእርሷ ልደት የልዑል ማደሪያው መቅደስ
የተሰራበት ዕለት ነውና ሁላችን እናከብረዋለን፡፡ በዚህም ዕለት ‹‹ዮም ፍስሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም/ እነሆ ዛሬ በእመቤታችን ልደት ደስታ ሆነ›› እያልን እንዘምራለን። ይህችን የልዑል ማደሪያ እናቷ ሐናና አባቷ ኢያቄምም በእጅጉ
ተደስተው በተወለደች በስምንተኛ ቀኗ ስሟን ‹‹ማርያም›› ብለው ሰይመዋታል፡፡

የእመቤታችን የልደት በዓል አከባበር

አባታችን አዳም በኃጢአት ከወደቀ በኋላ፣ ንስሃ በገባ ጊዜ አምላካችን ጌታ እግዚአብሔር የድህነት ቃል ኪዳን ገባለት፡፡ ቃል ኪዳኑም “ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ” የሚል ነበር፡፡ ስለሆነም አዳም 5500 ዘመን የሕይወት ምክንያት የሆነች የልጅ ልጁ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከአብራኩ ከተከፈሉ ቅዱሳን ልጆቹ የምትወለድበትን ቀን ተስፋ እያደረገ ኖረ፡፡ የእመቤታችንን የድንግል ማርያምን የመወለዷን ዜና ተስፋ በማድረግ “ሴት” ይላት የነበረውን ሚስቱን ሔዋንን በእመቤታችን ምሳሌነት “ሔዋን”፣ የሕያዋን ሁሉ እናት ብሎ ሰየማት፡፡ (ዘፍ. 3፡20) ዳግማዊ አዳም የተባለ ክርስቶስም የአዳምን ተስፋ በመስቀል ላይ በፈጸመ ጊዜ እውነተኛዋን
ሔዋን (ዳግሚት፣ አማናዊት ሔዋንን) ድንግል ማርያምን በዮሐንስ ወንጌላዊ በኩል ለሕያዋን ምዕመናን ሁሉ እናት አድርጎ ሰጠ፡፡ (ዮሐ. 19፡26) ይህን የከበረ ምስጢር የማይረዳ “ክርስቲያን” እንዴት ያሳዝናል!? እኛ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ግን የቀዳማዊ አባታችንን
የአዳምን፣ እንዲሁም በዳግም ተፈጥሮ ያከበረንን ዳግማዊ አዳም የተባለ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል ተቀብለን “የሕያዋን ሁሉ እናት” ድንግል ማርያምን ልደቷን በፍፁም ደስታ እናከብራለን፣ ከተወደደ ልጇ ምሕረትን ትለምንልን ዘንድም ወደ እርሷ እናንጋጥጣለን፡፡
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያለን ምዕመናን ከጌታችን ልደት ቀጥሎ በታላቅ ድምቀት የምናከብረው የልደት በዓል የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያም
የልደት ቀን ነው፡፡ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹በመወለዱ ብዙዎች ደስ ይላቸዋል (ሉቃ 1፡14)›› ከተባለ የድንግል ማርያም ልደት ምንኛ የሚያስደስት ይሆን?! የነቢያቱ ትንቢት የተፈፀመበት፣ የታየው ራዕይም በገሀድ የተከናወነበት፣ የብሉይ ኪዳን ማብቂያ የሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ ናትና ልደቷ
ለሰው ልጆች ሁሉ (ለሕያዋን ሁሉ) ታላቅ የደስታ ቀን ነው፡፡
ሰማያውያን ቅዱሳን መላእክትም በንጽህናዋ በቅድስናዋ ተደንቀው “እህትነ ነያ/እህታችን እነኋት” ብለው ያመሰግኗታል፡፡ በዘመናችን ያሉ የሰዎች ልደት በድምቀት የሚከበር ከሆነ ለሰው ልጅ
መዳን ምክንያት የሆነች የአምላክ እናት የተወለደችበት ቀን ምንኛ ሊከበር ይገባው ይሆን?! ቤተ ክርስቲያን የቅድስት ድንግል ማርያምን ልደት በታላቅ ድምቀት የምታከብረው ከዚህ ታላቅ በዓል በረከት ረድኤትን እንድናገኝበት ነው፡፡ የሕይወት ክርስቶስ እናት ዛሬ ተወልዳለችና፡፡
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትዉፊት መሰረት ሐና እና ኢያቄም ከአይሁድ ለማምለጥ ተሰደዉ በአድባረ ሊባኖስ ስር እመቤታችንን ወለዱ፡፡ በወቅቱ ከቤት የወጡት ለሽሽት ነበርና ስንቅ ስላልያዙ ምግባቸዉ ‹‹ንፍሮና ጥራጥሬ››
ነበር፡፡ይህንን ትዉፊት በመያዝ በዓሉ ከቤት ዉጭ ንፍሮ እየተበላ ይከበራል፡፡ነገር ግን በበጎ ነገሮች ሰበብ ክፉ ዓላማዉን ማስፈጸም የሚፈልገዉ ዲያቢሎስ በማር መካከል መርዝን ከሚጨምርባቸዉ መንፈሳዊ በዓላት አንዱ የግንቦት ልደታ (የእመቤታችን የልደት በዓል) ነዉ፡፡ በዚህ ዕለት አንዳንዶች ባለማወቅ ሌሎች ደግሞ በድፍረት ‹‹ለአድባር አዉጋር ነዉ፤ ቆሌዉን ለመለመን ነዉ›› እያሉ ለማያውቁት አምልኮ ንፍሮ የሚበትኑ፣ ቡና የሚረጩ፣ ቅቤ የሚቀቡ፣ የከብት ደም የሚያፈሱ አሉ፡፡ እውነታው እነዚህ በእርግጥም ጣዖት አምላኪዎች ናቸው፡፡ እኛ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ግን እነዚህን የሃይማኖት ለዋጮች ሥራቸውን እንጸየፋለን፡፡
ስለሆነም ከእንደዚህ ዓይነቱ ባዕድ አምልኮ በመለየት ይህንን ታላቅ በዓል በተገባና በተረዳ ነገር ልናከብረው ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በሠራችልን ሥርዓት መሰረት በቀናች በተዋሕዶ እምነት ሆነን፤ በምሕረቱ የጎበኘንን አምላካችንን
ብቻ እያመለክን፤ የድኅነታችን ምክንያት የሆነችውን ድንግል ማርያምንም እያመሰገንን ልናከብረው ይገባል፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር ከእመቤታችን ረድኤት በረከት ይክፈለን፡፡
አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
"+" ነገረ ሃይማኖት "+"

"+"የሃይማኖት ትምህርት አጠር ተደርጎ የቀረበ"+"

ቅዱስ ትውፊት...የቀጠለ

"+"ቅዱስ ትውፊት በሊቃውንት አስተምህሮ"+"
ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንም ስለ ቅዱስ ትውፊት ምንነት እጅግ ሰፊ የኾነ ትምህርትን አስተምረዋል፡፡ጥቂቶቹን ብቻ ለመጠቈም ያኽልም፡-
“በትወፊት አርባዕቱ ወንጌልን አወቅኁ፤እነርሱም እውነቶች ናቸው፡፡” / Origen, (cc Fr. Tadros Y. Malaty) Tradition and Orthodoxy, pp 18/
“ሐዋርያት ‘በቃል በመናገርም እንጂ በጽሑፍ ብቻ እንዳላስተማሩ በቃላችንም ቢኾን ወይም በመልዕክታችን የተማራችኁትን ወግ (ትውፊት) ያዙ’ በማለት ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረው ቃል ያመለክታል፡፡ኹለቱም ማለት የተጻፈውና ያልተጻፈው ለትምህርተ ሃይማኖትና ለድኅነት አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ስለዚኽ የቤተክርስቲያን ትውፊት መታመን የሚገባው መኾኑ እውነት ነው፡፡” /ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፥ 2ኛተሰ. 2፡15ን ሲተረጕም/
“በቅድስት ቤተክርስቲያን ተጠብቀው ካሉት ትምህርተ ሃይማኖትና ስብከቶች አንዳንዶች በጽሑፍ፥ሌሎች ግን በሐዋርያት ትውፊት የተሰጡን ናቸው፡፡ኹለቱም ተመሳሳይ ሥልጣን አላቸው፡፡ስለ ቤተክርስቲያን መቋቋም በጥቂቱም ቢኾን የሚያውቅ ሰው ይኽን ሊቃወም አይችልም፡፡ያልተጻፉትን ልማዶች ኹሉ ተገቢ እንዳይደሉ በቁጥር ብንጥላቸው በጣም አስፈላጊ የኾኑ የወንጌል ክፍሎችን እናጣለን፡፡ትምህርታችንም ባዶ ይኾናል፡፡” /አውሳብዮስ ዘቂሳርያ፣በእንተ መንፈስ ቅዱስ 27፡66/
“በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ኹሉ በትእምርተ መስቀል እንዲያማትቡ የትተጻፈ? በምንጸልይበት ጊዜፊታችንን ወደምሥራቅ ማዞር እንዳለብን የትተጻፈ? ወይኑንና ኅብስተ ቁርባኑን እንዲለውጥልን መንፈስ ቅዱስን ስለመጠየቅ (ስለቅዳሴ) ማንጻፈ? በዚኽ መሠረት ወንጌል ወይም የሐዋርያት መጽሐፍ በጠቀሱት ብቻ አንወሰንም፡፡በመስማትም የተማርነው ብዙ ነገር አለና፡፡” /ዝኒከማኁ/
“ለጥምቀት አገልግሎት ውኃን እንባርካለን፡፡ተጠማቂውን ለመቀባት ዘይት እንባርካለን፡፡ይኽ ኹሉ የትተጻፈ? ይኽን የተማርነው በምስጢራዊው ትውፊት አይደለምን? በሜሮን እንድንቀባ የት ተጻፈ? ተጠማቂው 3 ጊዜ ብቅ ጥልቅ ማድረግ የት ተጻፈ? ከጥምቀት ጋር ግኑኝነት ያላቸው ሌሎች ነገሮች፥ሰይጣንንና መላእክቱን መካድ የት ተጻፈ?” /ዝኒ ከማኁ/
እንደዚኹም መሠረተ ሐሳቡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቢኖርም ስለ ሕፃናት ጥምቀት የሐዋርያት ትውፊት ነው፡፡ስለ እመቤታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ዕረፍትና ትንሣኤ እንዲኹም ፍልሰት የምናስተምረው ትምህርት ኹሉ ከሐዋርያት ትውፊት የተገኘ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስን ስንተረጕም እንኳን የቅዱሳን አበውን አስተምህሮ የምንጠቅሰው የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ ትርጕም የምናገኘው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብቻ ስለኾነ ነው፡፡በዚኹ ዙርያ “ኦርቶዶክሳዊ ቅዱሳት መጻሕፍት አተረጓጐም ስልት” በሚል ርእስ በቀጣይ የምንመለስበት ይኾናል፡፡
ቅዱስ ትውፊት፥ቅዱስ ካልኾነው ትውፊት እንዴት ይታወቃል?
በቤተ ክርስቲያን ያለው ኹሉም በትውፊት የተገኘ ላይኾን ይችላል፡፡እያንዳንዱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኘው ነገርም የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪ መንፈስ ቅዱስ የሰጣት ነው ማለት አይደለም፡፡አንዳንድ ሰዋዊ ነገሮች ንልናገኝ እንችላለን፡፡ነገር ግን እነዚኽ ከሰው የኾኑ ነገሮች በራሳቸው ኀጢአት ወይም ስሕተት ላይ ኾኑይ ችላሉ፡፡ይልቁንም ለዋናው የቤተክርስቲያኒቱ ቅዱስ ትውፊት ማቀላጠፊያ ወይም ማስተላለፊያ መንገዶች ሊኾኑ ይችላሉ፡፡ለምሳሌ ድምጽ ማጉያ፣መቅረጸ ድምጽ፣ሲዲ፣ዲቪዲ፣እና የመሳሰሉት መጥቀስ ይቻላል፡፡ስለዚኽ ዋናውን የቤተክርስቲያኒቱ ትውፊትና ጊዜአዊው ማቀላጠፊያውን ለይተን ልናውቅ ይገባናል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች ጉባኤ እንደ መኾኗ መጠን፥እነዚኽ ክርስቲያኖችም በተለያ የግብረ ዓለም ሊያዙ ስለሚችሉ ይኽን የዓለም ሥራ ይዘው ቢመጡና ግብራቸውን በቤተክርስቲያን ውስጥ ቢያሠርፁ፥ይኽ ክፉ ግብር እንደ ቤተክርስቲያን ትውፊት ሊቈጠር አይገባውም፡፡
በመኾኑም ለቅዱስ ትውፊት ቀኖናዊ መመዘኛ እንዳለው ተረድተን ቅዱሱን ትውፊትና ቅዱስ ያልኾነውን ትውፊት ለይተን ልናውቅ ይገባናል /2ኛተሰ.2፡15/፡፡ትውፊት ኹሉ ከሐዋርያት ተያይዞ የመጣና ሐዋርያዊና ቤተክርስቲያናዊ ይዘት ያለው መኾን አለበት፤ከጥንት ዠምሮ በየትም ቦታ፥ኹልጊዜ በዓለም አቀፋዊት ቤተክርስቲያን የታመነ የተጠበቀና በተግባር ላይ የዋለ መኾን አለበት፤በዓለም አቀፋዊት ቤተክርስቲያን ዘንድ መለወጥና መቋረጥያልተደረገበትመኾንአለበት፡፡
እንደ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ሃይማኖት የሚቀበሉት ተቀብለውም የሚኖሩት ለቀጣዩ ትውልድም ሳያፋልሱ የሚያስተላልፉት እንጂ በየጊዜው የሚጨመርበት ወይም የሚቀነስበት አይደለም፡፡በፕሮቴስታንቱ ዓለም ደግሞ ከካቶሊካውያኑ ፍጹም ተቃራኒ በመኾን ቅዱስ ትውፊትን አንቀበልም ይላሉ፡፡መጽሐፍ ቅዱስ ብቻውን በቂ እንደኾነ ያስተምራሉ፡፡ነገር ግን ይኽም ቢኾን ፍጹም የተሳሳተ ትምህርትነው፡፡አንድ ቀላል ምሳሌ እናንሣና ትምህርታቸው ምን ያኽል ስሕተት እንደኾነ እናሳይ፡፡እሑድን እንደ ጌታ ቀን አድርገው ያከብራሉ፡፡በብሉይ ኪዳን እንዲከበር የታዘዘው ግን ቅዳሜ ነው /ዘጸ.20፡8/፡፡ቅዳሜን ትተው እሑድን ማክበር ከየት አገኙት? ዳግመኛም የጌታችንን ልደት፣ጥምቀት፣ትንሣኤ እንዲኹም በዓለ ኃምሳ አብረዉን ያከብራሉ፡፡ነገር ግን ይኽን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምንም አናገኝም፡፡ሌላ ጥያቄ እንጨምር፡፡ወደ ዓለም ኹሉ የተሰማሩት ሐዋርያት 12 መኾናቸውን ወንጌል ይነግረናል፡፡ነገር ግን ኹሉም ጽሑፍ አልጻፉም፡፡አላስተማሩም ማለት ግን አይደለም፡፡ታድያ ትምህርታቸው የት አለ? ትምህርታቸውን የምናገኘው በአንዲቱ ቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ሕይወት ውስጥ ብቻ ነው፡፡
ስለዚኽ ቅዱስ ትውፊት መቀበል ግድ ነው፡፡ለምን? የትናንቱን የቤተክርስቲያን ኹለንተናዊ ሕይወት ወደ ዛሬ የሚያመጣ፥ዛሬ ላይ ያለውንም ወደ ነገ የሚያሻግር ቅዱስ ትውፊት ነውና፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “የርሱን ግርማ ዐይተን እንጂ በብልሐት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችኁ” እንዳለ /2ኛጴጥ.1፡16/ ቅዱስ ትውፊት ሲባል እንዲኹ ከሰው የተገኘ ተረት ተረት እንዳልኾነ ልንረዳ ያስፈልጋል፡፡አለበለዚያ በትውፊት ያገኘነው መጽሐፍ ቅዱስም ተረት ተረት ማለታችን ነውና፡፡
ዳግመኛም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ወንድሞች ሆይ! በኹሉ ስለምታስቡኝና አሳልፌ እንደሰጠኋችኁ ወግን ፈጽማችኁ ስለያዛችኁ አመሰግናችኋለኹ” እንዳለን /1ኛቆሮ.11፡2/ የመጽሐፍ ቅዱስ አባት ራሱ ቅዱስ ትውፊት እንደኾነ ልናውቅ ይገባናል፡፡ “Sola Scriptura - መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” በሚለው የአንዳንዶች ስሕተትም ራሳችንንና ወንድማችንን ልንጠብቅ ይገባናል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ይቀጥላል..
--------------------------------
በየእለቱ መንፈስን የሚያለመልሙ አጥንትን የሚያጠነክሩ መንፈሳዊ ጽሁፎች እንዲደርሶት ይቀላቀሉን፡-
👉 @rituaH @rituaH
👉 @rituaH @rituaH
👉 @rituaH @rituaH
"+" ነገረ ሃይማኖት "+"

"+" የሃይማኖት ትምህርት አጠር ተደርጎ የቀረበ "+"

"+" ሀልወተ እግዚአብሔር /የእግዚአብሔር መኖር / "+"

ክፍል ፰

ስለ እግዚአብሔር መኖር ብዙዎቻችን እናምናለን፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ ስለ እግዚአብሔር መኖር የማያውቅ ማኅበረ ሰብእ ከቁጥር የሚገባ አይደለም፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲኽ መዝሙረኛው ክቡር ዳዊት፡- “ሰነፍ በልቡ አምላክ የለም ይላል” እንዳለ /መዝ.14፡1/ አንዳንድ ሰዎች የእግዚአብሔርን መኖር ጥያቄ ማንሣታቸው አልቀረም፡፡ በተለይም የምዕራቡ ዓለም የትምህርት ሥርዓት ከተስፋፋ ወዲኽ እንዲኽ ዓይነት ጥያቄዎች በአንዳንዶቹ ዘንድ የሚመላለስ ኾኗል፡፡
ኹሉም ባይኾኑም አብዛኞቹ ምዕራባውያን ስለ እግዚአብሔር መኖር ከተጠራጠሩና ከካዱ ሰነባብተዋል፡፡ ይኽ አካሔድም በሚገርም ፍጥነት ወደእኛ ሀገር እየተዛመተ ይገኛል፡፡ ከዚኽም በተጨማሪ አንዳንድ የውጭ ሀገር ዜጐች (ለምሳሌ ኦሾ የተባለው ሕንዳዊ ግለሰብ) የሚጽፏቸው ልበወለድ መጻሕፍት በሀገራችን ተርጓሚያን ጸሐፊዎች በብዙዎች እጅ ውስጥ መግባቱ በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ ግርታን መፍጠሩ አልቀረም፡፡
“እግዚአብሔር የለም” ብለው የሚያስቡ ሰዎች “እግዚአብሔር የለም” እንዲሉ የሚያደርጓቸው ምክንያት አሉ፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያኽልም፡-
• በኃጢአታቸው ምክንያት የሚጠይቃቸው አካል እንዲኖር ስለማይፈልጉ፤
• በዳሰሳና በሙከራ መንፈስ የኾነውን እግዚአብሔር ለማግኘት ስለሚሹ፤
• በአንዳንድ ቤተሰብ ውስጥ (በተለይ ሀብታም ቤተሰብ) ትምህርተ ሃይማኖትን ማስተማር እየቀረና እየቀነሰ ስለመጣ፤
• ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ ዘዴውን በረቀቀ መንገድ ሰውን ከእምነት እያስወጣ መምጣቱ (ለምሳሌ በስመ ዲሞክራሲና የነጻነትን ትርጕም አዛብቶ በመተርጐም)፤
• በብዙ ፈላስፎች ዘንድ “እግዚአብሔር አለ” ብሎ ማመን “በራስ ያለመተማመንና የፍርሐት ምልክት” ተደርጐ መወሰዱ፤
• ቁሳዊ አመለካከት እየተስፋፋ መምጣቱ፤
• ስለሌላም ብዙ ምክንያት፡፡
በመኾኑም ስለ እግዚአብሔር መኖር ማመን ለብዙዎቻችን ቀላል እንደኾነ ኹሉ፥ ለአንዳንዶች ግን ቀላል አልኾነምና መማማሩ ተገቢነት አለው፡፡
ሐልወተ እግዚአብሔር
ሀልወተ ማለት ሀለወ ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም መኖር ማለት ነው። ስለዚህ ሀልወተ እግዚአብሔር ማለት የእግዚአብሔር መኖር አኗኗርን የምንረዳበት ትምህርት ነው።
እግዚአብሔር የማይመረመር ረቂቅ፣በዚህ ጊዜ ተገኘ የማይሉት ቀዳማዊ፣በዚህ ጊዜ ያልፋል የማይሉት ድሃራዊ፣አለምን ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ የፈጠረ፣ዳግመኛም አለምን ከመኖር ወደ አለመኖር አሳልፎ የሚኖር ሃያል፣ፈጥሮ የሚገዛ ጌታ ነው። ሰውን ጻድቅ ቢሉት ሀሰት፣ሀብታም ቢሉት ድህነት ይሰማዋልና። እሱ ግን ሐሰት የሌለበት ጻድቅ፣ድህነት የሌለበት ባለጠጋ፣ድካም የሌለበት ኃያል ነው።
"መጠኑ ይኽን ያኽላል፤ መልኩ ይኽን ይመስላል" ብሎ ልክና መልክ ሊሰጠው አይችልም። ከነብያት እስከ ሐዋርያት፣ከሐዋርያት እስከ ሊቃውንተ ቤተ ክርስትያንም ይኽን እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሆነው ተናግረውታል።
ለምሳሌ፡-
1. “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ልትመረምር ትችላለኽን? ወይስ ኹሉን የሚችል አምላክ ፈጽመኽ ልትመረምር ትችላለኽን? ከሰማይ ይልቅ ከፍ ይላል፤ ምን ልታደርግ ትችላለኅ? ከሲኦልም ይልቅ ይጠልቃል፤ ምን ልታውቅ ትችላለኅ? ርዝመቱ ከምድር ይልቅ ይረዝማል፥ ከባሕርም ይልቅ ይሰፋል፤” /ኢዮብ.11፡7-11/፡፡
2. “የእስራኤል አምላክ መድኃኒት ሆይ! በእውነት አንተ ራስኽን የምትሰውር አምላክ ነኅ” /ኢሳ.45፡15/፡፡
3. “የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ ዕውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም። የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው? ወይስ አማካሪው ማን ነበር? ወይስ ብድራቱን ይመልስ ዘንድ ለርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው? ኹሉ ከርሱና በርሱ ለርሱም ነውና፤ ለርሱ ለዘለዓለም ክብር ይኹን፤ አሜን፤” /ሮሜ.11፡33-36/
፡፡
4. “ብቻውን አምላክ ለሚኾን ለማይጠፋው ለማይታየውም ለዘመናት ንጉሥ ምስጋናና ክብር እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን፤” /1ኛ ጢሞ.1፡17/፡፡
5. “ርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም፤ ለእርሱ ክብርና የዘላለም ኃይል ይኹን፤ አሜን፤” /1ኛ ጢሞ.6፡16/፡፡
6. “ሕሊናት የማይመረምሩትና (የሚረቅና) ያልተፈጠረ የፈጣሪን ምሥጢር እንደምን ማወቅ ይቻለናል?” /ጐርጐርዮስ ገባሬ መንክራት፣ ሃይ.አበ.13፡16/፡፡
7. “መላዕክትና የመላዕክት አለቆች ኹሉ በየወገናቸው በየሥርዓታቸው ፍጡራን ከኾኑት ኹሉ ጋር አንድ ላይ በአንድነት ቢሰበሰቡ የእግዚአብሔርን ህላዌ በጥቂቱ ስንኳ ሊያገኙት አይችሉም” /ባስልዮስ ዘቂሣርያ፣ ሃይ.አበ.33፡14/፡፡
8. “እግዚአብሔር በሰው ልጅ ሕሊና አይመረመርም፡፡ የሰው አስተሳሰብ መለኮትንና ህላዌ መለኮትን መርምሮ ማወቅ አይችልም፡፡ የመለኮት ህላዌ ከሰው ልጅ አስተሳሰብ የራቀ ነውና፡፡ ከሐሳቦች ኹሉ ይልቅ በጣም ከፍ ከፍ ያለ ነውና፤” /ቴዎዶጦስ ዘዕንቆራ፣ ሃይ.አበ.53፡2/፡፡
9. “አንደበት የርሱን ነገር እንደሚገባ አድርጐ መናገር አይቻለውም፡፡ አፈ ሕሊና (የሕሊና አንደበት) ሊጠራው እዝነ ልቡናም (የልቡና ዦሮ) ሊሰማው አይቻለውም፡፡ አንደበትስ ተወውና ከርሱ የሚበልጥ ሕሊና ልብ እንኳ ከጌታ ነገር ማናቸውንም ማወቅ መረዳት አይቻለውም፤” /ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ የዕብራውያን መልዕክት ትርጓሜ፣ ድርሳን 2፡6-9/፡፡
10. “ሰው ሆይ! ፍጥረታት ለማይመስሉት በምን ታመሳስለዋለኽ? የማይታሰበውንስ እንዴት አድርገኽ ልታስበው ትቃጣለኽ? በፍጡራን ሊያስተካክሉት የሚገባ አይደለም፡፡ በምንም በማናቸውም ስለ ግርማው በመብረቅ፣ ከፍተኛ ስለኾነው ብርሃኑ በፀሐይ፣ ስለ ልዕልናው በሰማይ፣ ስለ ስፋቱ በምድር፣ ስለ ጥልቀቱ በባሕር፣ እሳት ስለማቃጠሉ በእሳት፣ ስለ ርቀቱና (ረቂቅነቱና) ስለ ፍጥነቱ በነፋስ፣ ወይም በማናቸውም ቢኾን የእውነት አምላክን መለኮትነት ሊያስረዳ ይችላል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ይኽ ለፍጥረት ያልተሰጠውና፣ በምንም በማናቸውም ኹኔታውን ለመረዳት አይቻልም፡፡ ስለዚኽም ኹኔታውን ለመመርመር አይቻልም፤” /ርቱዐ ሃይማኖት /፡፡
11. “በመመርመር ያገኘው የለም፤ መርምሮ የሚያገኝኽ የለም፡፡ በባሕርይኽ መርምሮ የሚያውቅኽ የለም፡፡ በርቀት (በረቂቅነትኽ) አንተን ማየት የሚቻለው የለም፤ ባሕርይኽን አንተ ታውቀዋለኽ እንጂ፤” /ቅዳሴ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ፣ 1፡4-5/፡፡
12. “በሕሊና ተመርምሮ የማይገኝ ረቂቅ ነው፤ በልቡና ተመርምሮ የማይገኝ ምጡቅ ነው፡፡ በተልዕኮ የሚኖሩ መላዕክት የማይመረምሩት በተሰጥሞ (በተመስጦ) የሚኖሩ ጻድቃን የማይመረምሩት ረቂቅ ነው፤” /ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ፣ 1፡6/፡፡
“ፍጡር አስቦ ሊደርስበት አይችልም፤ መርምሮም ሊያውቀው አይችልም፤” ማለት ግን እግዚአብሔር የለም ማለት አይደለም፡፡ ወይም ደግሞ እግዚአብሔር ለሰዎች መገለጥን የማይወድ ዐይነ አፋር ነው ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም እግዚአብሔር ህላዌውን (መኖሩን) እንዲኽ የሰወረው ስለ ብዙ ምክንያት ነው፡፡
...ይቀጥላል
-----------------------------------
በየእለቱ መንፈስን የሚያለመልሙ አጥንትን የሚያጠነክሩ መንፈሳዊ ጽሁፎች እንዲደርሶት ይቀላቀሉን፡-
👉@rituaH @rituaH
👉@rituaH @rituaH
👉@rituaH @rituaH
"+" ነገረ ሃይማኖት "+"

"+" የሃይማኖት ትምህርት አጠር ተደርርጎ የቀረበ "+"
ክፍል ፱
"+" ሀለዎተ እግዚአብሔር... ካለፈው የቀጠለ "+"
ያለፈውን ለማንበብ 👉 http://www.tg-me.com/rituaH/251

እግዚአብሔር ህላዌውን (መኖሩን) ከሰወረበት ምክንያቶች
ጥቂቶቹን ለመግለጥ ያኽል፡-

1. ሰዎች ወድደውና ፈቅደው እንዲፈልጉት ፈቃዱ ስለኾነ፤
ለዚኽም ኹላችንም ርሱን እንድንፈልግ የምንገደድበት አዕምሮ በልቡናችን ውስጥ አሳድሯል /ሮሜ.2፡14-16/፡፡ የሥነ ፍጥረት ውበትና ሥርዓት እንዲኹም አቀማመጥ እየተመለከትን ይኽን ያደረገ ማን እንደኾነ እንድንመራመር የአዕምሮ ሕግ ሰጥቶናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው “አካላዊ አቋሜን ካለ መኖር ወደ መኖር ያመጣኹት እኔ ነኝ፤ እኔው ራሴ ራሴን ፈጠርኩ፤ ከሌላ ቦታ ይልቅ አኹን ባለኹበት ቦታ ለመኖር ራሴ መረጥኩ” ለማለት እስካልደፈረ ድረስ ፈጣሪውን ለመፈለግ ይገደዳል፡፡
እያንዳንዳችን ለአካላዊ አቋማችን አየር፣ ምግብ፣ ልብስ፣ ብርሃን፣ ጤና ማግኘት አለብን፡፡ ነገር ግን “እነዚኽን አስፈላጊ ነገሮች ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣኋቸው እኔ ነኝ” ለማለት እስካልደፈርን ድረስ ፈጣሪያችንን ለመመርመር እንገደዳለን፡፡
ዳግመኛም በሥጋችን የጤና ጕድለት፣ ረሃብ፣ ጥም፣ እርዛት፣ የተፈጥሮ መዛባት (ለምሳሌ ድርቅ፣ ውርጭ፣ በረዶ…)፣ እኛን የሚያጠቁ አውሬዎች ሲያስፈራሩንና ሲያሰቃዩን እናያለን፡፡ በደመ ነፍሳችንም ኀዘን፣ ጭንቀት፣ መከራ፣ ሥቃይ፣ ፍርሐት፣ ኃፍረት፣ ውርደት፣ ጥቃት ይደርስብናል፡፡ በመንፈሳችንም የኃጢአተኝነት፣ የበደለኝነት፣ ለኃጢአታችን የሚከፈል ዕዳ እንዳለብን እናስባለን፡፡ “ከዚኽ ኹሉ ማን ያስመልጠኛል? ማን ይታደገኛል?” ስንል ፈጣሪያችንን እንድንፈልግ እንገደዳለን፡፡
እነዚኽ ከላይ የጠቀስናቸው ምሳሌዎች በጭራሽ የማንክዳቸው እውነቶች ናቸው፡፡ ለዚኽም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደ ኾነ፥ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ኹሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ኹሉ ከአንድ ፈጠረ፥ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢኾንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም” ያለው /ሐዋ.17፡26-27/፡፡ ነገር ግን ኹሉም ሰው ፈጣሪውን አግኝቶታል ማለት አንችልም፡፡ ለዚኽ ዋና ምክንያቱ ደግሞ ብዙዎች አስተሳሰባቸውን ከትክክለኛው መንገድ ይልቅ በአሳሳችና ቅያስ ጐዳና ስለለወጡ ነው፡፡ አንዳንዶች ምንም ማድረግ በማይችሉ ፍጥረታት ይደገፋሉ፡፡ አንዳንዶች በአዕምሮአቸው በፈጠሩት ሌላ ፈጣሪ (ያውም ኅሊናቸው ውስጥ ካልኾነ በቀር ህልውናና አቋም የሌለው) ይደገፋሉ፡፡ “እግዚአብሔር ስለ ገለጠላቸው፥ ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው በነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና። የማይታየው ባሕርይ ርሱም የዘለዓለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ዠምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ኾኖ ይታያልና፤ ስለዚኽም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ኾኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ” /ሮሜ.1፡19-20/።
2. እግዚአብሔር በእግዚአብሔርነቱ የማይወሰን፥ የፍጡራን የተፈጥሮ አቋም፣
ዐቅምና ችሎታ ግን የተወሰነ ወይም የተመጠነ ስለኾነ፤
በግዘፍ ያለና በችሎታው ውሱን የኾነው የሰው አቋም የማይታየውንና የማይወሰነውን መለኮታዊ ባሕርይን መጨበጥና መወሰን አይችልም፡፡ ይኸውም ሊቁ አባ ሕርያቆስ፡- “ይኽን ባሰብኍ ጊዜ ሕሊናዬ ወደ ላይ ሊወጣና ተሠውሮም ወጥቶ ሕያው የኾነ ጌታ የሚሠወርበት መጋረጃን ሊገልጥ ይፈቅዳል፡፡ ወዲያውም ከሚነድ እሳት ይፈራና የአየራት ግማሽ እንኳ ሳያጋምስ (ሳይደርስ) ይቀራል፡፡ ይኽን ባሰብኍ ጊዜም ሕሊናዬ በነፋስ ትከሻ ሊጫንና ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ፣ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ፣ ወደ ዳርቻዎችም ኹሉ ሊበር ይፈልጋል፡፡ በኹሉም አከባቢና በኹሉም ዘንድ ሊጋልብ ይፈቅዳል፡፡ ዳሩ ግን መቀጠል ይሳነውና መዠመሪያ ወደነበረበት አቋም ይመለሳል” በማለት እንደመሰከረው ከዐቅምና ከችሎታ ማነስ የሚመጣ መሳን (አለመቻል) ነው /ቅዳሴ ማርያም፣ ቁ.85-88/፡፡ ካለመቻላችን የተነሣ እግዚአብሔርን ስላላወቅነው ግን፥ አስቀድመን እንደተናገርን የለም አንለውም፡፡ ይኸውም አንድ ማየት የተሳነው ሰው ፀሐይን ስላላያት የለችም እንደማይላት ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሔርስ ይቅርና የፍጡራንን ህላዌ ጨርሶ ሊመርምር የቻለ የለም፤ ደግሞም አይችልም፡፡ ስለ ፀሐይ ማን ያውቃል? ስለ ከዋክብት ማን ያውቃል? ሰው ስለነዚኽ ማወቅ ካልተቻለውማ ስለ ፈጣሪያቸው እንደምን ማወቅ ይችላል? ስለነዚኽስ ይቅርና ስለ ገዛ ሕሊናው ምን ያውቃል? ስለ ገዛ ሕሊናው ማወቅ ካልቻለ ሕሊናን ስለ ፈጠረማ እንደምን ይችላል?
3. ሰው ኹሉ በአዳም በደል ምክንያት ትክክለኛ የማሰብ ችሎታው ስለተበላሸበትና ስለወደቀበት፥ ራሱም ከሰይጣን ገዢነት ሙሉ ለሙሉ ስላልተላቀቀ በተጣራ አዕምሮ እግዚአብሔርን ሊፈልግና ሊመረምር ዐቅም የለውም፡፡
ታድያ የእግዚአብሔርን መኖር የምናውቀው እንዴት ነው?
ምንም እንኳን ነባቤ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ “ጌትነትኅ በአንተ ዘንድ የተሠወረ ነው፤ አንተ በአንተ አለኽ፤ ራስኽን ለራስኽ መጋረጃ አድርገኽ ትኖራለኽ፡፡ ራስኽን በራስኽ ትሠውራለኽ” እንዳለው እግዚአብሔር ከሕሊናት (ከምናስበው) በላይ ቢኾንም፥ ጭራሽ ልናገኘው አንችልም ማለት ግን አይደለም /ቅዳሴ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ፣ 1፡13/፡፡ አስቀድመን እንደተናገርን ሰው ልቡናው ውስጥ በተቀመጠለት የመሻት አዕምሮው ተመርቶ ፈጣሪውን ቢፈልግ ያገኟል፡፡ ሊቃውንቱ “እግዚአብሔር በመሔድ አይገኝም፤ ቢፈልጉት ደግሞ አይታጣም” ያሉትም ስለዚኹ ነው /ቅዳሴ ሠለስቱ ምዕት፣ ገጽ 291፣ ቁ.11/፡፡ በመሔድ አይገኝም ማለት በሳይንስ፣ በመመራመር፣ በፍልስፍና፣ በሙከራ፣ በዳሰሳ አይገኝም ሲሉ ነው፡፡ ታድያ እንዴት ነው የሚገኘው?
• እግዚአብሔር ራሱ ለሰው ከሚሰጠው የራሱን መገለጥ፤
ይኸውም “ሥጋና ደም ይኽን አልገለጸልኽም፤ ነገር ግን በሰማያት የሚኖር አባቴ ይኽን ገልፆልኻልና” እንዳለው ነው /ማቴ.16፡17/፡፡ ፍጥረት ኹሉ ለርሱ የተፈጠረ ነውና፥ ፍጥረት እንዲያውቀውም ራሱን ይገልጥለታል ማለት ነው (ኹሉ ከርሱ፣ በርሱ፣ ለርሱ የተባለውም ይኽንኑ ነው)፡፡ አዳም /ዘፍ.3፡9-10/፣ ኖኅ /ዘፍ.7፡1/፣ አብርሃም /ዘፍ.18፡27/፣ ሙሴ /ዘጸ.3፡6/፣ ነቢያት /ኢሳ.6፡1-6፣ ዕንባ.3፡2/፣ ሐዋርያት የእግዚአብሔርን መኖር ያወቁት በዚኹ መንገድ ነው፤ ራሱ ከሰጣቸው የራሱ መገለጥ፤ ቃል በቃል አነጋግሯቸዋል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት እንኳን የተጻፉት በዚኹ መንገድ ነው፤ በመገለጥ /2ኛ ጴጥ.1፡19-20/፡፡ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት “የእስራኤል አምላክ ተናገረኝ” ይላል /2ኛ ሳሙ.23፡2-3/፤ ነቢዩ ሳሙኤልም ይኽን መገለጥ ባገኘ ጊዜ “ባርያኽ ይሰማኻልና ተናገር” አለ /1ኛ ሳሙ.3፡10/፡፡ ስለዚኽ እግዚአብሔር ስለራሱ ካልገለጠ ማንም ሊያውቀው አይችልም፡፡ “የክርስትና ሃይማኖት የመገለጥ ሃይማኖት እንጂ ሰዎች በስምምነት ቃለ ጕባኤ ይዘው በጠረጴዛ ዙርያ ያጸደቁት አይደለም” የምንለውም ከዚኹ አንጻር ነው፡፡
----------------------------------
@rituaH @rituaH @rituaH
@rituaH @rituaH @rituaH
...-...-...-...-...-...-...-...-...-...-...-...-...-...
"+"ጳጉሜ ፫ - ርኅወተ ሰማይ እና የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል መታሰቢያ"+"
...-...-...-...-...-...-...-...-...-...-...-...-...-...

ርኅወተ ሰማይ በቤተ ክርስቲያናችን ከሚከበሩ ታላላቅ በአላት መካከል አንዱ ሲሆን የሚውለውም ጳጉሜ 3 በየዓመቱ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ቀን ነው፡፡ ርኅወተ ሰማይ የስሙ ትርጉም የሰማይ መከፈት እንደማለት ሲሆን በክርስቶስ ክርስቲያን የተባሉ ሁሉ ፀሎት፣ ልመናቸው ምልጃቸው የሚያርግበት ከአምላክም የሚወርድበት አለት ነው፡፡ በዚህች እለት ቅዱሳን መላእክት የምእመናንን ልመና መስዋእቱን የሚያሳርጉበት እና የአምላካችንን ምህረት ቸርነት ለሰው ልጆች የሚያወርዱበት እለት ፡:
በዚህች ቀን በሚዝንመው ዝናምም በእግዚአብሔር ቸርነት ብዙ ድውያን ፈውሰ ሥጋ ፈውሰ ነፍስን ያገኛሉ መካኖች ከማየ ፀሎቱ ጠጥተውም ማህፀናቸው ይከፈታል ሌሎች ብዙ ተዓምራትም ይደረግባታል፡፡
ጳጉሜ 3 የሊቃነ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል መታሰቢያ ነው ፡፡
ቅዱስ ሩፋኤል የጦቢትን ዓይን ያበራና ወለተ ራጉኤልን (የራጉኤልን
ልጅ) ተቆራኝቷት ከነበረው ጋኔን ያላቀቃት መሆኑ በመጽሐፈ ጦቢት በስፋት ተገልጿል፡፡
"የእግዚአብሔር ምሥጢር ግን በክብር ሊገለጥ ይገባል እንጂ ሊሰውሩት ስለማይገባ የእኔን ተፈጥሮና ስም ልነግራችሁ እፈልጋለሁ ተፈጥሮዬ መልአክ ነኝ፣ ሥራዬም የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ እኔ ሩፋኤል ነኝ› ሲል ገለጠላቸው፡፡ እነርሱም ወድቀው የአክብሮት ስግደት ሰገዱለት፡፡" መጽ. ጦቢት::
ጦቢት በፋርስ ንጉሥ በስልምናሶር ዘመን የተማረከ ከነገደ ንፍታሌም የተወለደ ጽኑዕ እሥራኤላዊ ነው፡፡ እግዚአብሔር በስልምናሶር ፊት የመወደድን ግርማና ባለሟልነትን ስለ ሰጠው አለቃ አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ ለወገኖቹ ምጽዋት በመስጠት ሕገ ርትዕን በመሥራት የተጋ ሰው ነበር፡፡ ሐና የምትባል ሚስት አግብቶ አንድ ልጅ ወልዷል፡፡ ስልምናሶር ሞቶ ሰናክሬም በነገሠ ጊዜ ከሹመቱ ስለሻረው ደግሞ ወደ ምድያም መሔድ አልቻለም፡፡
ሣራ ወለተ ራጉኤል ከፍተኛ ችግር ደርሶባት ነበር፡፡ ችግሯም ሕፃናት ወልጄ ቤት ንብረት ይዤ እኖራለሁ በማለት ባል አገባች ነገር ግን በዚች ሴት አስማንድዮስ የሚባል ጋኔን አድሮ ያገባችውን ሰው ገደለባት ሌላም ባል ብታገባ ሞተባት እንደዚህ እየሆነ በጠቅላላ ሰባት ድረስ ያሉትን ባሎችን ገደለባት፡፡
የራጉኤል ልጅ ሣራ በዚህ ሁኔታ በኀዘን ተውጣ ስትኖር በነበረበት ጊዜ ጦቢት ሸምግሎ ስለ ነበር ልጁ ጦብያን ጠርቶ በዚህ ዓለም እስካለ ድረስ ሊሠራው የሚገባውን መንፈሳዊ ሥራ እንዲሠራ በጥብቅ ከመከረው በኋላ በመጨረሻ ልጄ እኔ ሳልሞት የኑሮ ጓደኛህን ፈልግ፣ ስትፈልግም ዕወቅበት፣ እኛ የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብ ዘሮች ነን ስለዚህ ከእነርሱ ወገን የሆነችውን እንድታገባ ከዚህም ሌላ ከገባኤል ዘንድ በአደራ ያስቀመጥኩት ገንዘብ አለና እኔ በሕይወት እያለሁ ብታመጣው የተሻለ ነው አለው፡፡
ጦብያም ያባቱን ምክር ሁሉ በጽሞና ካዳመጠ በኋላ ‹አባባ የነገርከኝን ነገር ሁሉ በተቻለኝ መጠን እፈጽማለሁ ግን ከገባኤል ጋር ስላለው ገንዘብ እንዴት ለማምጣት እችላለሁ? ሀገሩን አላውቀውም› አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ነገሩ አሳሳቢ ሆኖ ስላገኘው ጦቢት ልጁ ጦብያን ‹አብሮህ የሚሄድ ሰው እስቲ ፈልግ ምናልባት አብሮ የሚሄድ ጓደኛ ታገኝ ይሆናል ደመወዝም ሰጥተን ቢሆን ካንተ ጋር የሚሄድ አንድ ሰው ግድ ያስፈልግሃልና ሂድ ሰው ፈልግ› አለው፡፡
አብሮት የሚሄደው ሰው ለመፈለግም ቢሄድ አንድ መልካም ጐበዝ አገኘ ይኸውም መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ጦብያ ግን መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል መሆኑን ፈጽሞ አላወቀም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጦብያ መልአኩን ሰው መስሎ እንዳገኘው ‹የሜዶን ክፍል ወደ ምትሆነውና ራጌስ ወደ ምትባለው ሀገር ከእኔ ጋር ለመሄድ ትችላለህን የድካምህን ዋጋ የጠየቅኸውን ያህል እሰጥሃለሁ› ሲል ጠየቀው ቅዱስ ሩፋኤልም ‹እሺ ካንተ ጋር ለመሄድ ፈቃኛ ነኝ መንገዱንም ሆነ ሀገሩን በሚገባ አውቀዋለሁ ከገባኤል ቤት ብዙ ጊዜ ኑሬአለሁና› አለው፡፡
ከዚህ በኋላ ጦብያ በል ከአባቴ ጋር ላስተዋውቅህ ብሎ ወደ አባቱ ወስዶ አስተዋወቀው ከእኔ ጋር የሚሄደው ሰው ይህ ነው በማለት ካስተዋወቀው በኋላ ጦቢትም ከወዴት እንደ መጣ ማን ተብሎ እንደሚጠራ ጠየቀው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልም የታላቅ ወንድምህ ወገን ከመሆንም ሌላ ስሜም አዛርያስ ይባላል አለው፡፡ ጦቢ. 5.12 ፡፡ ጦቢትም የወንድሙ ዘመድ መሆኑን ከሰማ በኋላ ‹አንተስ ወንድሜ ነህ በል የልጄ የጦብያን ነገር አደራ ከሀገር ወጥቶ አያውቅምና እንዳይደነግጥ ደኅና አድርገህ እንድትይዝልኝ› ብሎ ስንቃቸውን አስይዞ ሸኛቸው፡፡
አዛርያስ /ቅዱስ ሩፋኤል/ በመንገድ ይመራው ነበር፡፡ በዚህም ቅዱስ ሩፋኤል ‹መራኄ ፍኖት› /መንገድ መሪ/ ይባላል፡፡ እነርሱ ሲሄዱ ውለው ማታ ጤግሮስ ከተባለው ታላቅ ወንዝ ደረሱና ከዚያም ለማደር ወሰኑ፡፡ በዚህ ጊዜ ከድካሙ ጽናት የተነሣ ጦብያ ሊታጠብ ወደ ወንዙ ወረደና ልብሱን አውልቆ መታጠብ ሲጀምር አንድ ዓሣ ሊውጠው ከባሕር ወጣ፡፡ ወዲያውም መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን ያዘው ፤ ዓሣውን እንዳትለቀው አለው ፤ ጦቢያም ከዓሳው ጋር ግብ ግብ ገጥሞ እየጐተተ ወደ የብስ አወጣው ፡፡ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን እንዲህ ሲል አዘዘው፡፡ ዓሣውን እረደው ጉበቱንና ሐሞቱን ተጠንቅቀህ ያዘው ሌላውን ግን ጠብሰን እንበላዋለን አለው፡፡
ጦብያም መልአኩ እንዳዘዘው ዓሣውን አርዶ ሐሞቱንና ጉበቱን ያዘ፣ ሌላውን ሥጋውን ግን ጠብሰው ራታቸው አደረጉት፡፡ ጦብያም ያንን የዓሣውን ጉበትና ሐሞት ለምን እንደሚያገለግል ለመረዳት ‹ይህን ያዘው ያልከኝ ለምንድን ነው?› ሲል ጠየቀው ቅዱስ ሩፋኤልም ጋኔን ያደረበት ሰው ሲገኝ ይህንን ከዕጣን ጋር ቢያጤሱበት ጋኔኑ ይለቃል ሲል መለሰለት፣፡
በዚህ ሁኔታ አንድ ባንድ ሲነጋገሩ ከቆዩ በኋላ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን ‹ዛሬ ከራጉኤል ቤት እናድራለን፡፡ እርሱ ዘመድህ ነው፡፡ የእርሱም ልጅ ሣራ የምትባል ቆንጆ ልጅ አለችው፡፡ እሷን ለሚስትነት ይሰጥህ ዘንድ ለራጉኤል እነግርልሃለሁ› አለው፡፡
ጦብያም ‹ያች ልጅ ከዚህ በፊት ሰባት ሰዎች እንዳገቧትና ሰባቱም ባገቧት ሌሊት ደርቀው /ሞተው/ እንደሚያድሩ ሰምቻለሁ፡፡ ስለዚህ እኔ ላባቴና ለእናቴ አንድ ልጅ ነኝ እርስዋን አግብቼ ከዚህ በፊት እንዳገቧት ሰዎች እኔም የሞትኩ እንደሆነ አባቴንና እናቴን የሚረዳቸው የለም ቢሞቱም የሚቀብራቸው አያገኙምና እፈራለሁ› አለው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ግን ‹አባትህ ከዘመዶችህ ወገን ካልሆኑ በስተቀር ሌላ ሴት እንዳታገባ ሲል የነገረህን ረሳኸውን? በል ሰባት ባሎቿ ሙተውባታል ስለምትለው እኔ መድኃኒቱን አሳይሃለሁ ፤ አይዞህ አትፍራ አትሞትም የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ለምን መሰለህ ያዘው ያልኩህ ? እንግዲህ ሐሞቱንና ጉበቱን ከዕጣን ጋር ጨምረህ ስታጤስበት በሣራ አድሮ የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ወጥቶ ይሄዳል ፈጽሞም ወደ እርሷ በገባህም ጊዜ ሁለታችሁ ይቅር ባይ ወደ ሆነው እግዚአብሔር ጸልዩ እርሷም የተዘጋጀች ናት፡፡ ከእኛ ጋርም ወደ ሀገርህ ይዘናት እንሄዳለን› አለው፡፡ ጦብያም ይህንን ቃል በሰማ ጊዜ ደስ አለውና ከእርሷ በስተቀር ሌላ እንዳያገባ በሙሉ አሳቡ ወሰነ፡፡
... 👇👇👇
ከዚህ በኋላ ወደ ራጉኤል ቤት እንደ ደረሱ ሣራ በደስታ ተቀበለቻቸው የሣራ አባትም ጦብያን ገና እንዳለው ሚስቱ አድናን ‹ይህ ልጅ የእኔ ዘመድ ጦቢትን ይመስላል› አላት ከዚያም ጋር አያይዞ ‹ልጆች ከየት ሀገር መጣችሁ?› አላቸው፡፡ እነሱም ‹ከነነዌ ሀገር ነው የመጣን› አሉት፡፡ ‹ከዚያም ሀገር ጦቢት የሚባል ወንድም ነበረኝ ታውቁት ይሆን?› ሲል ጠየቃቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ጦቢያ አባቱን ሲጠራለት ‹እናውቀዋለን፡፡ እኔም ራሴ የጦቢት ልጅ ነኝ› አለው፡፡ ከዚያ በኋላ ራጉኤል ‹የወንድሜ ልጅ ነህን?› ብለ እቅፍ አድርጐ ሳመው፡፡ አድናም ሳመችውና ሁሉም ተያይዘው የናፍቆት ልቅሶ ተላቀሱ፡፡ ከወንድሙ እንደ መጡም ሲገነዘብ በግ አርዶ በጥሩ ሁኔታ ጋበዛቸው፡፡
ራትም ከበሉ በኋላ ጦብያ ቅዱስ ሩፋኤል በመንገድ የነገረውን በልቡ ሲያወጣ ሲያወርድ ስለ ዋለ ቅዱስ ሩፋኤልን ያንን በመንገድ የነገርከኝን አሁን ፈጽምልኝ ሲለው ሰምቶ ስለ ልጅቷ መሆኑን ስለ ገባው ራጉኤል ጦብያን ‹ልጄ ይህች ልጅ ላንተ የምትገባ ናት ሰጥቸሃለሁ አይዞህ አትጠራጠር አሁንም ብላ ጠጣ ለዛሬም ደስ ይበልህ አለውና ሣራ ካለችበት የጫጉላ ቤት አግብተው ዘጉት፡፡ ጦብያም ሣራን በይ እኅቴ ኑሮዋችን እንዲቃናልንና ጋብቻችን እንዲባረክልን አስቀድመን ወደ ፈጣሪያችን ጸሎት እናድርግ› አላትና አብረው ጸሎት ካደረጉ በኋላ ያንን የያዘውንና የዓሣ ጉበትና ሐሞት ከዕጣን ጋር ጨምሮ ቢያጤስበት በሣራ አድሮ ባሎችዋን ይገድልባት የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ከሣራ ለቆ ወጥቶ ሄደ ሁለተኛም ሊመለስ አልቻለም፡፡ እነርሱም በሰላምና በጤና አደሩ፡፡ የጦብያንና የሣራን ጋብቻ የባረከ ቅዱስ ሩፋኤል ስለሆነ ‹መልአከ ከብካብ› ይባላል፡፡
ከዚያ በኋላ የጤንነታቸውን ነገር ሲረዱ የሰርጉ ቀን የሚሆን የ14 ቀን በዓል እስኪፈጸም ድረስ ጦብያ ወደ ሀገሬ እሄዳለሁ ብሎ እንዳያውከው በማለት አማለው፡፡
የ14 ቀን በዓለ መርዓ ከተፈጸመ በኋላ ግን ጥሬ ገንዘብና የከብት ስጦታ አድርጐ መርቆ ወደ ሀገሩ ሰደደው፡፡ ወላጆቹ ጦቢትና አድና ግን በመዘግየቱ ልጃችን ምን አግኝቶት ይሆን? እያሉ ለጊዜው ሳያዝኑ አልቀሩም፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሚስቱንና ግመሎቹን ይዞ ሲመጣ በክብርና በደስታ ተቀበሉት፡፡ የጦብያ አባት ጦቢትም ልጅህ መጣ ሲሉት ዓይነ ሥውር ስለ ነበር እርሱን እቀበላለሁ ሲል ስለ ወደቀ ወዲያው ጦብያ የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ይዞ ስለ ነበር የአባቱን ዓይን ቀባው ወዲያውም ዓይኖቹ ተከፈቱ፡፡
በመጨረሻም ከጦብያ ጋር ሄዶ የነበረው መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልን የድካሙን ዋጋ ገንዘብ ለመስጠት ጠሩት እርሱ ግን ጦቢትንና ጦብያን ‹ፈጣሪያችሁን አመስግኑ እናንተ እስከ ዛሬ ድረስ ከየት እንደመጣሁ ማን እንደ ሆንኩ አላወቃችሁኝም፡፡
የእግዚአብሔር ምሥጢር ግን በክብር ሊገለጥ ይገባል እንጂ ሊሰውሩት ስለማይገባ የእኔን ተፈጥሮና ስም ልነግራችሁ እፈልጋለሁ ተፈጥሮዬ መልአክ ነኝ፣ ሥራዬም የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ እኔ ሩፋኤል ነኝ› ሲል ገለጠላቸው፡፡ እነርሱም ወድቀው የአክብሮት ስግደት ሰገዱለት፡፡ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት፡፡ /መጽ. ጦቢት/፡፡
የጳጉሜ ወር ዳግም ምጽአት የሚታሰብበትም ወር ነው፡፡ ይህም ጳጉሜ የዓመታት መሸጋገሪያ ጨለማው የክረምት ወቅት ወደ ማብቂያው የምናልፍባት እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ከጊዜያዊው ወደ ዘላለማዊ ከምድራዊ ወደ ሰማያዊ ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው መሸጋገሪያ ነውና ነው፡፡
አምላካችን ዳግም ሲመጣ በመንግስቱ እንዲያስበን ተግተን ልንፀልይ ሁሉን በስርአት እንድናደርግ ይገባል፡፡

ጦቢትን በሥራው ሁሉ የረዳ በችግሩም ያፅናናው ሊቀ መላእክት ሩፋኤል እኛንም ከመከራ ስጋ ከመከራ ነፍስ እንላቀቅ ዘንድ ይራዳን ያማልደን በረከቱ ሁሌም አይለየን አሜን፡፡
አዲሱ ዓመትም የሰላም የፍቅር የመከባበር አመት እንዲሆንልን አምላክ ይርዳን ፡፡
<<ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>
------------------------------------
@rituaH @rituaH @rituaH
@rituaH @rituaH @rituaH
+"+ ወርኃ ጽጌ +"+
(ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስርአት መሰረት ከመስከረም 26 ቀን እስከ ሕዳር 6 ቀን ያለው 40 ቀን የእመቤታችን ና የልጇን ስደት በማሰብ ወርኃ ጽጌን (ዘመነ ጽጌን) ታከብራለች፡፡ ይህ 40 ቀን የእመቤታችንና የጌታ ስደት ከቤተልሔም በግብፅ ወደ ኢትዮጵያ የተሰደደችበት የሚታሰብበት ዘመን ነው፡፡ ወቅቱ የአበባና የፍሬ ወቅት በመሆኑ እመቤታችን በአበባ ጌታን በፍሬ እየተመሰሉ ጌታችን በአምልኮት እመቤታችን በፈጣሪ እናትነቷ በተለየ ምስጋና ይመሰገናሉ ፡፡
ማኅሌተ ጽጌን ድርሰት አባ ጽጌ ድንግል ከአባ ገብረ ማርያም ጋር በአንድነት እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው የደረሱት እመቤታችንንና ፈጣሪ ልጇን በጎ መዓዛ ባላቸው አበባዎችና ፍሬዎች እየመሰለ የሚያመሰግነውን ይህንን ድርሰታቸውን በመዝሙረ ዳዊት መጠን 150 አድገው ደርሰውታል፡፡
ስለ ጽኑ የተጋድሎ ሕይወታቸውም 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾመው እጅግ ቢደክሙ የብርሃን እናቱ እመቤታችን ተገልጻላቸው ‹‹ወዳጄ ገብረ ማርያም ሆይ ይህን ያህል ገድል የምትጋደል ሰውነትህንስ የምትታስጨንቃት ለምንድነው?›› በማለት አጽንታ የደከመ ሰውነታቸውን አድሳላቸዋለች፡፡
ከአባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም አስከ ዕለተ ሞታቸው (ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6) ድረስ አንዱን አመት በደብረ በብስራት ሌላኛውን አመት በደብረ ሐንታ ገዳም እየተገናኙ ማሕሌተ ጽጌን በወረብ በሽብሻቦ ያገለግሉ ኑረዋል።
ዛሬ ይህ ሥርዐት ሕያው ሆኖ በኢትዮጵያ ገዳማት አድባራት አብያተክርስቲያናት በሙሉ በናፍቆት እየተጠበቀ በየመቱ በተመስጦ እያገለግል እንገኛለን ። ምዕመናንም በጾም በጸሎት በማሕሌት በዝክር ከእመቤታችን በረከት በፍቅር እየታደሉ ይገኛሉ።
በዚህ በወርኃ ጽጌ (በዘመነ ጽጌ) የሚጾሙ ክርስቲያኖች ሲኖሩ ጾሙን መንፈሳውያን ሰዎች ሳይታዘዙ በራሳቸው ፈቃድ የሚጾሙት ጾም በመሆኑ (የፈቃድ) የትሩፋት ጾም ይባላል፡፡ በቀኖና ቤተክርስቲያን ከታዘዙት ከ7ቱ አጽዋማት ውጪ የሆነ ትርፍ ጾም ማለት ነው፡፡ ከታዘዘው አትርፎ የጾመ ሰው የመጾሙን ዋጋ ያገኛል፡፡ ብዙ መንፈሳዊ ሥራ የሰራ ሰው ብዙ ክብር እንደሚያገኝ መጽሐፍ ይናገራልና፡፡ ‘’እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ሐጢአትዋ ተሰርዮላታል፡፡ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል’’ (ሉቃ. 7፡47) እንዲል፡፡
የጽጌን ጾም የሚጾሙ ሰዎች በክብርም ከእመቤታችን ጋር ይተባበራሉ፡፡ ነገር ግን የጽጌን ጾም የሚጾሙ ሰዎች ለመመጻደቅ መጾም የለባቸውም፡፡ የማይጾሙ ሰዎችንም መንቀፍና መክሰስ የለባቸውም፡፡ የጽጌ ጾም እንዲጾም በቀኖና ቤተክርስቲያን ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ተደርጎ ስላልተወሰነ የማይጾሙ ሰዎች ሕገ ጾምን እንዳፈረሱ አድርጎ መውሰድ ስሕተት ነው፡፡ ይልቁንም የሚጾሙ ሰዎች ቢችሉ መጾማቸው እንዳይታወቅባቸው ቢያደርጉ የተሻለ ነው፡፡ "ስትጾሙ እንደግብዞች አትጠውልጉ" (ማቴ. 6፥16) የተባለው ለዚህ ዓይነቱ ጾም ነው፡፡

ከእመቤታችን ረድኤት በረከት ያሳትፈን።
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን::
ጥቅምት 22-ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ዕረፍቱ ነው፡፡ ሀገሩ አንጾኪያ ሲሆን ቁጥሩ ከ72ቱ አርድእት ነው፡፡ ከአቴናና ከእስክንድርያ ሊቃውንት የሕክምና ሙያን አጥንቷል፡፡ ከሕክምና መያው በተጨማሪ የሥዕል ሙያም ነበረው፡፡ በይህ ምክንያት በወንጌሉና በሐዋርያት ሥራ መጽሐፉ ላይ ከሌሎቹ በተለየ ሁኔታ ሥዕላዊ አገላለጽን ሲጠቀም ተስተውሏል፡፡ በእጁ የሣላቸው ቅዱሳት ሥዕላትም በተለያዩ ሀገራት ይገኛሉ፡፡
ቅዱስ ሉቃስ የሣላቸው የእመቤታችን ሥዕላት በእኛም ሀገር እንደ ደብረ ዠመዶ፣ ዋሸራና ተድባበ ማርያም፣ ደብረ ወርቅ ማርያም… ባሉ ታላላቅ ቅዱሳት ገዳማት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ቅዱስ ሉቃስ የከበሩ ቅዱሳን ሐዋርያትን ጴጥሮስንና ጳውሎስን ያገለግላቸው ነበር፡፡ ለታኦፊላም ወንጌልንና የሐዋርያትን ዜና የጻፈው እርሱ ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ጴጥሮስና ጳውሎስ በሰማዕትነት ካረፉ በኋላ በሮሜ ወንጌልን በሰፊው ሰብኳል፡፡ መልእክቶችንም ይጽፍላቸው ነበር፡፡ ጣዖት አምላኪዎችም ከክፉዎቹ አይሁድ ጋር ተማክረው በሐሰት ከሰውት በንጉሥ ኔሮን ፊት አቆሙትና ‹‹ብዙ ሰዎችን በሥራዩ ወደ ክርስትና እምነት አስገብቷልና በሞት ይቀጣ›› ብለው ጮኹ፡፡ ቅዱስ ሉቃስም በሰማዕትነት እንደሚሞት አስቀድሞ ዐውቆ ወደ ባሕር ዳርቻ በመሄድ ዓሣ የሚያጠምድ አንድ ሽማግሌ ሰው አገኘና ወንጌልን ከሰበከው በኋላ መጻሕፍቶቹንና ደብዳቤዎቹን ‹‹ወደ እግዚአብሔር መንገድ ያደርሱሃልና እነዚህን መጻሕፍት ጠብቀቸው›› ብሎ በአደራ ሰጠው፡፡ ሽማግሌውም በክብር በዕቃ ቤቱ አስቀምጦአቸው ለቀጣዩ ትውልድ አስተላልፏቸዋል፡፡
ቅዱስ ሉቃስ በንጉሡ ኔሮን ፊት በቀረበ ጊዜ ንጉሡ ‹‹በሥራይህ ሕዝቡን ሁሉ የምታስት እስከመቼ ነው?›› አለው፡፡ ቅዱስ ሉቃስም ‹‹ለሕያው እግዚአብሔር ልጅ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ነኝ እንጂ እኔስ ሥራየኛ አይደለሁም›› አለው፡፡ ንጉሡም ‹‹እየጻፈች ሰዎችን የምታስት ይህችን እጅህን እቆርጣታለሁ›› ካለው በኋላ ቀኝ እጁን አስቆረጠው፡፡ ቅዱስ ሉቃስም የጌታችንን ኃይሉን ያሳየው ዘንድ ወደደና የተቆረጠች የቀኝ እጁን በግራ እጁ አንሥቶ ከተቆረጠችበት ቦታ ላይ በማገናኘት እንደ ድሮው ደኅነኛ እጅ አደረጋት፡፡ በዙሪያውም የነበሩ ሰዎች ሁሉ የንጉሡም የሰራዊት አለቃ ከነሚስቱ በአጠቃላይ ቁጥራቸው 477 ሰዎች ሁሉም በጌታችን አመኑ፡፡ ንጉሡም እጅግ ተናዶ ከቅዱስ ሉቃስ ጋር ራሶቻቸውን ይቆርጧቸው ዘንድ አዘዘ፡፡ እነርሱም ሰማዕት ሆነው የክብር አክሊልን ተቀበሉ፡፡ የቅዱስ ሉቃስንም ሥጋ በአሸዋ በተመላ ከረጢት ውስጥ አስገብተው ወደ ባሕር ጣሉት ነገር ግን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ አንድ ደሴት ደረሰና ምእመናን አግኘተውት ወስደው በክብር አኖሩት፡፡
የቅዱስ ሉቃስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!
እንኳን ለመድኃኔዓለም ዓመታዊ ክብረ በዓል ዝክረ ጥንተ ስቅለት አደረሳችሁ አደረሰን!!!
===================================
ከሁሉ አስቀድሞ ሃይማኖትን መመስከር እንዲገባ “ ከመዝ ነአምን ዘአልቦቱ እም በሰማያት፤ ወአብ በዲበ ምድር ” በሰማይ ያለእናት ከአብ መወለዱን፣ በምድርም ያለ አባት ከድንግል ማርያም መወለዱን እናምናለን። ይህንንም አባቶቻችን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ቅድመ ዓለም ከእግዚአብሔር አብ ያለ እናት፣ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ የተወለደ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አካላዊ ቃል ፤ ድኀረ ዓለም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት፣ መለወጥ ሳያገኛት ዘር ምክንያት ሳይሆን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ የተወለደ፤ ወልደ እግዚአብሔር በመለኮቱ ወልደ ማርያም በትስብእቱ ብለው አምልተው እንዲያስተምሩን “ከመ አሐዱ ውእቱ ባሕቲቱ ውእቱ አምላክ ወሰብእ ኅቡረ” ትርጉሙም እርሱ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው ማለት ነው። ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ ፴፭፥፳፩
መጋቢት ፳፯ በቃል መነገሩ በልብ መታሰቡ ከፍ ከፍ ይበልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሠቀለበት ጥንተ ስቅለቱ የሚታሰብበት ቀን ነው ፡፡ ይሁን እንጂ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በዲሜጥሮስ ቀመር መሠረት አጽዋማትን በጠበቀ መልኩ ከትንሣኤ በዓል በፊት ያለውን አርብ “ስቅለት” ተብሎ እንዲከበር ሥርአት ሠርተዋል፡፡መጋቢት ፳፯ ቀን በዓቢይ ጾም ስለሚውል በዓቢይ ጾም ሀዘን እንጂ ደስታ ስለሌለ በዓል ማክበርም ስለማይፈቀድ፤ ወደ ጥቅምት ፳፯ ተዛውሮ ደስ ብሎን እንድናከብረው ቤተክርስቲያን ሥርዓት ሰርታለች ።
ጥቅምት ፳፯ ዝክረ ጥንተ ስቅለቱን ቤተክርስቲያናችን ጌታችን በመስቀሉ ስለፈጸመልን የማዳን ስራ “ በመስቀሉ ወበቃሉ አዕበዮሙ ለአበዊነ ” ። በመስቀሉና በቃሉ አባቶቻችንን ከፍ ከፍ አደረጋቸው እያለች እየዘመረች ታስበዋለች። ከዚህም በተጨማሪ ጥቅምት ፳፯ በወርኀ ጽጌ ውስጥ ያለ በመሆኑ “ …እስመ ውእቱ ክብሮሙ ለቅዱሳን መድኃኒቶሙ ለጻድቃን አሠርገዋ ለምድር በጽጌ ሮማን ስብሐተ ዋህድ ዘምስለ ምህረት በመስቀሉ ወበቃሉ አዕበዮሙ ለአበዊነ ” እያለች የቅዱሳን ክብራቸው የጻድቃን መድኃኒት የሆነው ጌታ ምድርን በአበባ የሚያስጌጣት እንደሆነ በመመስከር ትዘምራለች ።
“እስመ አንተ ትክል አንጽሖትየ እግዚኦ ወበቃልከ እለ ለምፅ አንጻሕከ ወበጽጌያት ምድረ አሠርጐከ ወበመስቀልከ ለጻድቃን አብራህከ ” ልታነጻኝ ይቻልሃል አቤቱ ለምጻሞቹን በቃልህ እንጽተሃልና እያሉ አባቶቻችን በመስቀሉ ለጻድቃን ማብራቱን እያሰቡ በዓሉን በመዝሙር በደስታ ያከብሩታል
“ወበከመ ሙሴ ሰቀሎ ለአርዌ ምድር በገዳም ከማሁ ሀለዎ ለወልደ ዕጓለ እመሕያው ይሰቀል” ዮሐ ፫፥፲፬ ሙሴ እባብ በምድረ በዳ እንደሰቀለ የሰው ልጅ ክርስቶስ ይሰቀል ዘንድ አለው ብሎ እንደተናገረ የክብር ባለቤት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዓለም ድኅነት የተሰቀለው መጋቢት ፳፯ ቀን ነው ።
ክርስቶስ ስለስቅለቱ ሲናገር ምሳሌ የሚሆነውን፣ ሙሴ በምድረ ባዳ የሰቀለውን፣ የነሐሱን እባብ “ሙሴ እባብ በምድረ በዳ እንደሰቀለ የሰው ልጅ ክርስቶስ ይሰቀል ዘንድ አለው” ብሎ ምሳሌውን ተናግሯል።
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እስራኤልን ከደመና መና አውርዶ፣ከጭንጫ ውሀ አፍልቆ ቢመግባቸው ከዚህ ምድሩ ብቅ፣ሰማዩ ዝቅ ቢልለት፣ ከደጋ ላይ ቢሆንለት የውርጭ ሰደቃ እያበጀ፣ ውሀውን እያረጋ፣ መና መገብኳችሁ ይላል እንጅ ይክልኑ እግዚአብሔር ሠሪዓ ማዕድ በገዳም። ቆላ በሆነማ ባልተቻለውም ነበር ብለዋል ።ጌታም ሊያስተምራቸው ፣ የርሱን ከሃሊነት ሊያሳያቸው፣ የእነርሱንም ሀሰት ሊገልጥባቸው ፣ ሙሴን ነቅዓ ማይ የሌለበት በርሐ ይዘሀቸው ውረድ ብሎት ቢሄዱ መናው ወርዶላቸዋል፣ ውሀውም ፈልቆላቸዋል ።ነገር ግን ነዘር የሚባል እባብ እየነከሰ ይፈጃቸው ጀመር።ከዚህ በኋላ እስራኤል ሙሴ ዘንድ ሂደው ከጌታ ምህረት ቸርነት ከሰው ስሕተት ኃጢአት አይታጣም በእግዚአብሔርና በአንተ ላይ ተናግረን በድለናል እባቦችን ከኛ ያርቅልን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር አመልክትልን አማልደን አሉት።ሙሴም ስለሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ቢጸልይ ጽሩዩን ብርት አርዌ አስመስለህ ሠርተህ ከሚገናኙበት አደባባይ ከእንጨት ላይ ስቀልላቸው አለው። ሙሴም እባብን ሠርቶ በዓላማ ላይ ሰቀለ እባብም የነደፈችው ሰው ሁሉ የነሐሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ። (ኦሪ ዘኁ ፳፩ ፥፩፡፱)
ይህንም ምሳሌ አባቶቻችን በትርጓሜ ወንጌል ቅዱስ እንዳስቀመጡልን አርዌ ምድር የዲያብሎስ፤አርዌ ብርት የጌታ ምሳሌ ነው ። በአርዌ ምድር(እባብ) መርዝ እንዳለበት በዲያብሎስም ፍዳ ኃጢአት አለበት።በአርዌ ብርት መርዝ እንደሌለበት በጌታም ፍዳ ኃጢአት የለበትም ።አርዌ ብርት በአርዌ ምድር አምሳል መሰቀሉ ጌታ በአምሳለ እኩያን እንደወንጀለኛ ተቆጥሮ ለመሰቀሉ ምሳሌ ነው። ዳግመኛም “ተኈለቈ ምስለ ጊጉያን” ከዐመፀኞችም ጋር ተቈጥሯልና ኢሳ ፶፫፥፲፪ የሚለውን ትንቢት ፈጽሟል። ምሳሌውን አውቆ አስመስሏል ትንቢቱንም አውቆ አናግሯል ።
ጲላጦስ አይሁድን ከሁለቱ ማናቸውን ላድንላችሁ ትወዳላችሁ ቢላቸው በርባንን ፍታልን ክርስቶስ የተባለ ኢየሱስን ግን ስቀለው አሉ ።ጲላጦስም በዚህ ሰው ደም ከመጣ ፍዳ ሁሉ ንጹሕ ነኝ ብሎ ባደባባይ እጁን ታጠበ። አይሁድ ደሙ በኛም በልጅ ልጆቻችንም ይሁን አሉ። እርሱም በርባንን ፈታላቸው ጌታንም አሳልፎ ሰጣቸው። ማቴ ፳፯ ፥፳፭
ቅዳሴ ዮሐንስ አፈወርቅ “ሊቃነ መላእክት በመፍራትና በመንቀጥቀጥ ከፊቱ የሚቆሙለትን በአደባባይ አቆሙት፤ ኃጢያትን ይቅር የሚለውን ኃጥእ አሉት፤ በመኳንንት በሚፈርደው በርሱ ፈረዱበት” ፡፡ እንዲል ክርስቶስን አይሁድ ስቀለው ብለው ፈረዱበት።
አክሊልን የሚያቀናጀውን የነገሥታት ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስን አነገስንህ ብለውታልና ጭፍሮች በፍና ተሣልቆ የእሾህ አክሊል ታተው ደፉለት “ወጸፈሩ ሐራ አክሊለ ዘሦክ ወአስተቀጸልዎ ዲበ ርእሱ” ዮሐ ፲፱፥፪ ። ኢየሱስ ክርስቶስ የእሾኽ አክሊል በመቀዳጀቱ ዕፀ በለስን በልቶ “ምድር እሾኽንና አሜከላን ታበቅልብኻለች” ዘፍ ፫፥፲፰ ብሎ የፈረደበትን አዳም ስለርሱ ክሶ መርገሙን ደምስሶለታል ።
መጋቢት ፳፯ ቀን ክርስቶስ ኢየሱስ በመስቀል በተሰቀለ ጊዜ፤ የተሰቀለው የክብር ባለቤት ሰማይን የፈጠረ ነውና ፀሐይ ጨልማለች፣ ጨረቃ ደም ሆኗል፣ ከዋክብት ረግፈዋል። የተሰቀለው የክብር ባለቤት ምድርንም የፈጠረ ነውና በምድር የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለኹለት ተቀዷል፤ ምድር ተናውጣ ዐለቶች ተሠንጥቀዋል፤ መቃብራት ተከፍተዋል፤ ከ፭፻ በላይ ሙታን ተነሥተዋል (ማቴ ፳፯ )፡፡
ኦ አእዳው እለ ለሐኳሁ ለአዳም ተቀነዋ በቅንዋተ መስቀል ፤ ኦ አእጋር እለ አንሶሰዋ ውስተ ገነት ተቀነዋ በቅንዋተ መስቀል
አዳምን የፈጠሩ እጆች በመስቀል ቀኖት ተቸነከሩ ወዮ፤በገነት የተመላለሱ እግሮች በመስቀል ቀኖት ተቸነከሩ ወዮ፡፡ እንዲል ቅዳሴ ዮሐንስ አፈወርቅ ስቅለቱን በዲሜጥሮስ ቀመር አውጥተን የጌታን መከራውን አስበን በስግደት ህማማቱን እናስባለን በዝክረ ጥንተ ስቅለቱ በጥቅምት ፳፯ ደግሞ በመስቀል የተደረገልንን አስበን እናመሰግነዋለን፡፡
ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት መታሰቢያ ጋር ቤተ ክርስቲያን በ15ኛው መ.ክ.ዘ የነበሩትን አቡነ መብዓ ጽዮንን ታስባለች፡፡ አቡነ መብዓ ጽዮንን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን ‹‹ በዕለተ ዓርብ የተቀበልከውን መከራ ግለጽልኝ ››ብለው በጸለዩ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ የተቀበላቸውን መከራዎች ሁሉ አሳያቸው፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን
የኢየሱስ ከርስቶስን መከራ ካዩበት ቀን ጀምሮ ሕማሙን መከራውን ግርፋቱን እስራቱንበጠቅላላ አስራ ሦስቱን ሕማማተ መስቀል በማሰብ ጀርባቸውን በአለንጋ ይገርፉ ፤ ራሳቸውን በዘንግ ይመቱ ነበር፡፡ የጌታችንን ሕማማተ መስቀል እያሰቡ ዘወትር ስለሚያለቅሱ ዐይናቸው ጠፍቶ ነበር፡፡ ነገር ግን እመቤታችንቅድስት ድንግል ማርያም የብርሃን ጽዋ ይዛ መጥታ ዐይናቸውን ቀብታ አድናቸዋለች፡፡ በዚህ የተነሳ ‹‹በትረ ማርያም›› እየተባሉ እንደሚጠሩ ገድላቸው ያስረዳል፡፡ በዚህ መሰረት ጥቅምት ፳፯ ቀን ለአቡነ መብዓ ጽዮን ቃልኪዳን የገባበት ቀን በመሆኑ በየዓመቱ ጥቅምት ፳፯ ቀን ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዝክረ ጥንተ ስቅለቱ ጋር ይከበራል፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ይቅርታና ቸርነት፤የጻድቁ አቡነ መብዓ ጽዮን በረከትና ረድኤት ይደርብን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
” # ሕፃን ተወልዶልናልና፥ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይኾናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ኀያል አምላክ፥የዘለዓለም አባት፥የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” /ኢሳ 9፥6/።
"11 ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።
13 ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ።
14 ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ፡ አሉ።"
ሉቃ 2÷11-14
# ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በረቡዕ ውዳሴ ማርያም በጌታ ልደት የተደረገልንን ድንቅ የማዳን ሥራ በተናገረበት ድርሳኑ እንዲህ ነበር ያለው፦ “በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው፤ በቅዱሳን የሚያድር እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ልዩ ከሆነች ድንግል ሰዉ ሆኗልና ኑ ይህን ድንቅ እዩ፣ ስለተገለጠልን ምስጢር ምስጋና አቅርቡ # ሰው -የማይሆን-ሰው-ሆኗልና ቃል ተዋህዷልና ቅድምና የሌለው ሥጋ ጥንታዊ ቀዳማዊ ሆነ፣ ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ዘመን ተቆጠረለት”
ይህ የጌታ ልደት የቤተ ክርስቲያን አንድነት ነው። ሁሉ በአንድነት የተሰባሰቡበት በጋራ የዘመሩበት፤ በዚይች በበረት፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምሳሌ በሆነችው # ጌታችን ከመሀል # ከእናቱ ጋራ እንዲሁም # አረጋዊ ዮሴፍ ከማሕበረ ጻድቃን፣ ሰማያውያን
# መላእክት ፣ # እረኞች፣ ሰባሰገል # ነገሥታት፣ እንስሣትም ሳይቀሩ ባንድነት የተገኙባት የፍቅርና ያንድነት ቤት ናት።
ስለዚህ እኛም የክርስቶስ አባግዓ መርዔቱ፣ የመንጋው በጎች፣ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በፍፁም አንድነት መኖር እንዳለብን “ወንድሞች ሆይ፥ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ፤ ባንድ ልብና ባንድ ሃሳብም # የተባበራችሁ -እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ” የተባለውም ስለዚህ ነው /1ኛቆሮ 1፥10/።
እንኳን ለጌታችን ለመድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት መታሰቢያ ታላቅ በዓል በሰላም አደረሳችሁ።
የጌታችንና የአምላካችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱ በዓል በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን። አሜን።
2024/05/17 20:46:50
Back to Top
HTML Embed Code: