Telegram Web Link
Ťâťä Ä£ŕø
ቅዳም ስዑር
"ቅዳም ስዑር" /የተሻረች ቅዳሜ/

ክርስቲያኖች ቅዳሜ ጠዋት በቤተ ክርስቲያን ተሰባስበው ጸሎቱ ሲፈጸም “ገብረ ሰላመ በመስቀሉ፤ ክርስቶስ በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ፤ ሰላምን ፈጠረ፤ የምሥራች” ይባባላሉ። ለተሰበሰበ ሁሉ የምሥራች ምልክት የሚሆን ቄጤማ ይታደላል። ምእመናንም ይህን እየሰነጠቁ በራሳቸው ያስሩታል። ወደ ቤተ ክርስቲያን ላልመጡት ደግሞ ካህናት በየበኩላቸው ልብሰ ተክኅኗቸውን ለብሰው መስቀልና ቃጭል ይዘው ቄጤማውን “የምሥራች” እያሉ ይሰጣሉ።

ቄጤማው የምሥራች ምልክት መሆኑ ከታሪክ ጋር የተያያዘ ነው። ዓለም በንፍር ውሃ በተጥለቀለቀች ጊዜ ኖኅ ርግብን የውሃውን ሁኔታ ለመረዳት በመስኮት አሾልኮ ወደ ምድር ይልካታል። እርሷም በአፏ ቄጤማ ይዛለት መጥታለች። ኖኅ የውሃውን መጉደል በቄጤማው ተረድቶ ተደሰተ። መርከቢቱንም ለማሳረፍ ተዘጋጀ። ቄጤማው ለውሃው መጉደል ለኖኅ የምሥራች እንደሆነለት አሁንም ክርስቶስ የኃጢአትን ውሃ እንደደመሰሰው ለማስገንዘብ ምእመናን ቄጤማ አስረው፣ ቄጤማ ይዘው ይታያሉ። የምሥራችም ይባባላሉ።

ይህች ቅዳሜ በቅድስት ቤተክርስቲያናችን የተለያዩ ስያሜዎች አሏት። አንደኛው “ሰንበት ዓባይ” የሚል ነው። ይኸውም የፊተኛይቱ ቅዳሜ እግዚአብሔር ፍጥረታትን ፈጥሮ ከሥራው ያረፈባት ዕለት ስትኾን ይህቺ ግን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሦስት ዓመት ከሦስት ወር የማዳን ሥራውን በመስቀል ፈጽሞ በከርሠ መቃብር ዐርፎ የዋለባት ዕለት ስለሆነች ነው።

ዳግመኛም ይህቺ ዕለት “ስዑር ቅዳሜ” ትባላለች። ስዑር መባሏም በዓመት አንድ ቀን ብቻ ስለምትጾም የተሻረች ቅዳሜ ማለት ነው። በዚህች ዕለት ህዝበ ክርስቲያኑ እስከፈቀደ ይጾማል። ቄጤማውንም እስኪመገብ ብቻ አስሮት ይቆያል። በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ለፈቀደ ለሰላም አለቃ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ክብር የክብር ክብር ለእርሱ ይሁን አሜን!

በዚሁ ዕለት ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለ ዓዋዲ/ እየመቱ ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሳኤሁ አግሃደ የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር ጌታ በመስቀሉ ሰላም እንደሰጠንና ትንሳኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ። ምእመናኑም ገጸ በረከት ያቀርባሉ፤ ቄጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ። አንድም የምዕመናኑ በእራሳቸው ላይ ቄጠማ ማሰር አይሁድ ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሰሩበትን ድርጊት የሚያስታውስ ነው። በዚህ ዕለት ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲያቆናት ቄጤማ ተሸክመው፤ ቃጭል ሲያቃጭሉ መታየታቸው ዕለተ ትንሳኤውን ለሚናፍቁ ምእመናን ትልቅ ብሥራት ነው።

ለብርሃነ ትንሳኤው በሰላም ያድርሰን። አሜን!

#ታታ_አፍሮ /ነፃ ብዕር/
Ťâťä Ä£ŕø
"ክበር ተመስገን የኛ ጌታ
ከጠዋት አንስተ እስከ ማታ

አብ ልጁን ሰቅሎ ግብር ጠርቷል
በመድኃኔዓለም አዳም ድኗል..."

https://youtu.be/mDkSxDXiUoU
በመላው ዓለም የምትገኙ የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታይ ለሆናችሁ ኢትዮጵያውያን በሙሉ፤ እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤው በሠላም አደረሳችሁ። አደረሰን። ልዑል እግዚአብሔር ከጾመ በረከቱ እጥፍ ድርቡን ይክፈለን! ለአዳምና ለዘሩ ሁሉ በትንሳኤው የነፍስ ትንሳኤን ያደረገ ቸር አምላክ ክብርት ለሆነች ስሙንም ከፍ አድርጋ ለምትዘክር ለቅድስት አገራችን ኢትዮጵያ ዘለዓለማዊ ትንሳኤ ይስጣት። ዘወትር ፋሲካ ይሁንባት። ርሃብና ችግር ቸነፈርና ጦርነት ልዩነቶች ሁሉ ፈጽመው ከምድሯ ይወገዱ ዘንድ የእርሱ መልካም ፍቃዱ ይሁን።

መልካም የትንሳኤ በዓል!
Ťâťä Ä£ŕø
4ኛ አመት...😍
ኢትዮጵያ እና ቀሪው ዓለም... /፬ኛ አመት/

ኢትዮጵያ ከንጉሠ ነገሥቱ ስልጣን መውረድ በኋላ ስሟ ጠልሽቶ የድህነትና የርሃብ አውድማ መሆኗ በሁሉ ዓለም ተሰራጭቶ ኢትዮጵያዊያን በማንነታቸው እስኪሸማቀቁ ድረስ ከባድ ሆኖ ነበር። አፍሪካውያን ሳይቀሩ የኪነጥበብ ስራቸውን ከኛጋ ለመስራት ፍቃደኛ ባልሆኑበት ወቅት ቴዲ አፍሮ አፍሪካ ላይ ዝነኛ ከሆኑ አርቲስቶች ጋ በኮክ ስቱዲዮ የመድረክ ስራ በመስራት መንገዱን ከፍቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ከፍ ለማድረግ ቻለ።

በሚያዝያ 24/2009 ዓ.ም ለገበያ የቀረበው ኢትዮጵያ አልበም። የዓለምን ቀልብ ሳበ። ነጮች የማያውቁት ቃና ቢልቦርድ ላይ ደረጃውን ተቆጣጠረ። የቴዲ አፍሮ ሙዚቃ ከጅምሩም /ከአቦጊዳ ጀምሮ/ በዓለም አቀፍ የሙዚቃ ስልት የታጀበ ነው። የኢትዮጵያ ሙዚቃ ባለ አምስት ቤት የሚባለው ሲሆን ቴዲ አፍሮ ግን እስከ ሰባት ድረስ ሰብሮ የሄደ በአፍሪካ ምድር ሆኖ የአውሮፓውያንን ቅኝት የተፈታተነ አርቲስት ነው። ይኼ ጅምሩ ነው ዛሬ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ስልት ከአውሮፓ የሙዚቃ ስልት ጋ በማቀናጀት ጥበቡን አስደናቂ ያደረገለት። በኢትዮጵያ ሙዚቃ መራቀቅ የርሃብ እና የጦርነት ዜናዎቻችንን የዘገቡ CNN እና የBBC ጣቢያዎች የጥበብ ዜናችንን ለዓለም ዘገቡ። ኢትዮጵያ የተሰኘው አልበሙ ከመውጣቱ በፊት በዓለም ላይ ፈጥሮት የነበረው መነቃቃት እና የአድናቂዎቹ የሶሻል ሚዲያ ሰፊ ሽፋን አስደንጋጭ በመሆኑ ከመላዋ አፍሪካ ጥሶ በመውጣት የዓለምን ሪከርድ በመስበሩ ዝነኞች ሳይቀሩ "ኢትዮጵያ ማነች? ቴዲ አፍሮስ ማነው?" ሲሉ ጠየቁ።

ክንደ ብርቱ የሆነው ቴዲ አፍሮ ጀርባው ሲጠና የሰብዓዊ መብት ተሟጋችም ሆኖ ተገኘ። ዓለምም የትውልዱ ኮከብ አርቲስት ሲል አወደሰው። በአፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ ብቻውን በመፋለም ለህዝብ ለከፈለው መስዋዕትነት የአፍሪካ ወጣቶች ተምሳሌት በመባልም በዓለም ስሙ ገነነ የናቁን ነጭች ሳይቀሩ በግርማው ተማረኩ። ኢትዮጵያ የተባለች የጀግኖች አገር ዳግም ስሟ በመልካም ተነሳ። ቴዲ አፍሮ እግዚአብሔር ያክብርህ..!

CNN እና BBC በእንግሊዝኛ ሳይሆን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቋንቋ በሆነው የአማርኛ ቋንቋ ቃለ ምልልስ አደረጉ። ቃለ ምልልሱ በአገራቸው ሳይሆን የአፍሪካ መዲና በሆነችው በአዲስ አበባ ነበር። ሊያውም ሙሉ የድርጅት እቃቸውን ጭነው በደጁ ተገኝተው ነዋ። በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ የንግስና ዘመን የነገሥታቱ ህግ ከውጪ ዜጎች ጋ ለመወያየት ከአማርኛ ቋንቋ ውጪ አይፈቅድም ነበር! ስለሆነም ነገሥታቱ በቋንቋቸው ያወሩ ነበር። ይኼን ታሪክ ደገመው። የBBC እና የCNN ጋዜጠኞች በቴዲ አፍሮ ማናጀር በኩል የፖለቲካዊ ጥያቄዎች እንዳያነሱ ማስጠንቀቂያ የደረሳቸው ቢሆንም ቴዲ አፍሮ ግን በዓለም ነፃነት ስለሚያምን የጋዜጠኞችንም ሞያ ስለሚያከብር ያሻቸውን እንዲጠይቁ ፈቀደ ፖለቲካውንም ኪነ ጥበቡንም በወኔ በቂ ምላሽ ሰጠበት። ከዛ በኋላማ BBC Amharic የሚል የመረጃ ሰዓቱን ዘረጋ...

አልበሙ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱሰትሪ ላይ ትልቅ ነውጥ ፈጥሯል። የተኛ ሳይሆን የሞተውን የሙዚቃ ስሜት ቀስቅሷል። ባህል ዘመናዊ ሲሉ አላዋቂዎች አብኩተው የህዝብ ጆሮን ያሰለቹ ሙዚቃዎችን ወግዱ ብሎ በአፍሪካ እጅግ ልቆ በዓለም ላይ ሚሊየኖች የሚቃዡላቸውን ዘፋኞች ሁሉ አንዴ ተራው የኢትዮጵያ ነው በሚል አይነት ስሜት ኢትዮጵያ የተሰኘው ዜማው በሙዚቃ ሰንጠረዡ ፊት አውራሪ ሆነ። የተለያዩ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ትውልድ ይወቅህ የጥበብ አፍቃሪ ሁሉ አንተን ይማር ሲሉ የህይወት ታሪኩን እና የሙዚቃ ህይወቱን ብሎም የስራ ሂደቱን አንድ ላይ በማዋቀር ስለ አርቲስቱ ዘጋቢ ፊልም ለመስራት የአርቲስቱን መልካም ፍቃድ ጠይቀውም ነበር።

የዚህ አልበም የመጀመሪያ እትም 500,000 /500 ሺህ/ ኮፒ ሲሆን ይኼውም በመጀመሪያው ቀን ነበር ከአከፋፋዮች እጅ ላይ ያለቀው።

ይኽ አልበም ከወጣ እነሆ አራት አመታቶች ተቆጠሩ ግና ዛሬም ድረስ ትላንት እንደተለቀቀ አዲስ አልበም ዛሬም እንደ አዲስ ይደመጣል... እንደ አባይ ጅረት የማይነጥፍ ጥበባዊ የሆነ አቅሙን የገለጠ ዓለምን ያሳመነ ድንቅ የሙዚቃዎች ስብስብ ነውና ኢትዮጵያ "ኢትዮጵያ" በተሰኘው አልበሟ ዝንት ዓለም ትኮራለች።

#ታታ_አፍሮ /ነፃ ብዕር/
Ťâťä Ä£ŕø
በድጋሚ የተለጠፈ

ከቴዲ አፍሮ ስራዎች መሀል ለዛሬ አዲስ ቃል /ትርጓሜው በብዙሃኑ ዘንድ ግልፅ ያልሆነ ነው ብለን ያሰብነውን ከታላላቅ አባቶች ጠይቀን ለናንተ እንካቹ አልን። #ያምራል በተሰኘው ዜማው ላይ ከታች ዘርዘር አድርገን የምናቀርብላቹ ሁለት የግጥም መስመሮች አሉ። ስለ ሐምሌ ድንቅ ክስተትም እንዲሁ አክለን የምናካፍላቹ ቁም ነገርም አለን።

"እንዴት ታምሪያለሽ ሩቢ መሳይ
ውበትሽ ወቶ ላለም ይታይ"
እና....
"የደን አፀድ ጌጥ የሶሪት ላባ
ማን አበቀለሽ #ከአዲስ_አበባ..."

ሩቢ ለብዙ አይነት ነገሮች የተሰጠ ስያሜ ነው።

✔️ሩቢ፦ የድሮ የጦር መሪዎች ግንባራቸው ላይ የሚያረጉት ፈርጥ ያለው ሹመታቸውን አመልካች ጌጥ ነው።
✔️ሩቢ፦ ማለት ከእንቁ በላይ ውድ የሆነ የከበረ
ማዕድን ነው፡፡ ኦፓል፣ኤመራልድ፣ዳይመንድ እና ሩቢ በጣም ውድ እጅግም የከበሩ ማዕድናት ሲሆኑ ከሁሉም ሩቢ የበለጠ እና የከበረ ማዕድን ነው።
✔️ሩቢ፦ ባለ ቀይ ቀለም ብርቅዬ ወፍ መጠሪያ ስም ነው።
✔️ሩቢ፦አበባም ማለት ነው።
ከዚህም በተጨማሪ አንድ አባት የማይመረመር ምስጢራዊ ነገርን የያዘ ለምሳሌ እንደ ፅላት የከበረ ነገር ማለት ነው አሉኝ! ያ ማለት ግን ፅላት ራሱ ማለት እንዳልሆነም አስረግጠውልኛል። የቴዲያችን የግጥሞቹ ይዘት እና የሚገልፅበት መንገድ ረቂቅና ምጡቅ በመሆኑ ለመረዳት መፅሀፍ ማገላበጥ እና የታሪክ አዋቂዎችን መጠየቅ የግድ ይለናል!! ያም ሆኖ ከተሳካ ማለታችን ነው።

"የደን አፀድ ጌጥ የሶሪት ላባ"
የደን/ጫካ/ ውስጥ አጸድ/ፅድ/ አበቃቀሉ ከቁመቱ ጋር ሰው የከረከመው እስኪመስል ድረስ የተጌጠና ቀልብን የሚስብ ነው። ጥሩ መአዛም አለው። አፀድ ሌላ ትርጉሙ ማራኪ ሽታ ያለው /እጅግ ውብ/ እንደማለትም ነው።

#የሶሪት_ላባ

1፦ ሶሪት የምትባል የባለ ህብረ ቀለም ወፍ ስም ነው። ላባዋ ረዥም እና እይታን የሚስብ ቀለም ያለው ሲሆን መገኛዋ ከሰዎች መኖሪያ አካባቢ የራቀ ጫካ ነው። በበልግ ወራት ብቅ የማለት ባህሪ አላት።
2፦ሶሪት አበባ በመባል ይታወቅ የነበር አሁን ግን ወደ ሶሪት ላባነት ስሙ የተቀየረ አበባ አለ። ምክንያቱ ደግሞ አበባው ቀይ ሲሆን አበባውን ያቀፈው ላባው ደግሞ ነጭ ነው እናም ከአበባው ይልቅ ላባው ቀልብን ይገዛል ለዛም የሶሪት አበባ መባሉ ቀርቶ የሶሪት ላባ እየተባለ ይጠራል "እቴ አደይ አበባ የሶሪት ላባ" እየተባለም ተዚሞለታል.. ይኼ አበባ በስፋት ሐምሌ ወር ላይ ይበቅላል....! ሐምሌ ደግሞ እኔ በማስታውሰው ቀዳማዊ አጤ ኃይለ ሥላሴ እና ቴዲ አፍሮ በሳምንት ልዩነቶች ልደታቸው የሚከበርባት ውብ ወር ነች።

#ታታ_አፍሮ /ነፃ ብዕር/

#ኢትዮጵያ_አልበም_4ኛ_አመት
Ťâťä Ä£ŕø
ሰው አለ ወይ ውብ እንዳንቺ ፀባየ ሰናይ...
@
የዕርገት በዓል
በዐለ ዕርገት

እንኳን አደረሰን

ምስባክ፦ ዐርገ ውስተ አርያም ፄዊወከ ፄዋ ወወሀብከ
ጸጋከ ለእጓለ እመሕያው እስመ ይክሕዱ ከመ ይኀድሩ መዝ 67፥ 18
ትርጉም፦ ምርኮን ማርከህ ወደ ሰማይ ዐረግህ ጸጋህንም ለሰው ልጆች ሰጠህ።

የተነገረው ትንቢት የተመሰለው ምሳሌ ይፈፀም ዘንድ ጌታ በተቀበረ በሦስተኛው ቀን መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በኃይሉ ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ። ተነስቶ አርባ ቀን እስኪሞላው ለአባቶቻችን ሐዋርያት በጉባኤም ሆነው በተናጠልም ሳሉ እየተገለጠ እያስተማራቸው ቆየ። ልክ በተነሳ በ40ኛው ቀን ግን "ከሰማይ ኃይል እስክታገኙ ድረስ ባላችሁበት በኢየሩሳሌም ጸንታችሁ ቆዩ" ብሏቸው ወደ ቢታንያ አወጣቸውና እስከ ፓትርያርክነት ድረስ ያለውን ማዕረግ በአንብሮተ እድ ሾሟቸው እያዩት ከፍ ከፍ እያለ ዐረገ።

ጌታችን ዕርገቱን ከ40 ቀን ውጪ ዝቅ ብሎ በ39ኛው ከፍ ብሎ በ41ኛው ቀን ያላደረገበት ምክንያት አዳም አባታችን በ40 ቀን አግኝቶ ያጣትን ልጅነት እንደመለሰለት ለማጠየቅ ነው። ማረጉም በሚታይና በሚዳሰሰው ከእናቱ ከእመቤታችን በነሳው ሥጋ ነው። ለምን ቢሉ ተለየ ተለወጠ የሚሉትን መልስ ሲያሳጣቸው ነው። አንድም ልቡሳነ ሥጋ የሆኑ ቅዱሳን ማረጋቸውን ገነት መንግሥተ ሰማያት መውረሳቸውን ለማጠየቅ ነው። እንግዲህ ይህ ቀን በቤተ ክርስቲያናችን ከሚከበሩ የጌታችን ዐበይት በዓላት ውስጥ አንዱ ሆኖ ዘውትር በየዓመቱ ያረገበትን እለት ሐሙስን ሳይለቅ በታላቅ ድምቀት ይከበራል።

የጌታችን የኢየየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ማረግ ለክርስትና ሃይማኖት ታላቅ ድል ነው። በዓለማችን ብዙ የተለያዩ ሃይማኖቶች አሉ። የማናቸው ሃይማኖት መሥራች በድል አድራጊነት ወደ ሰማይ ያረገ አይገኝም። የሁሉም ሃይማኖቶች መሪዎች ሞተው በምድር ላይ ነው የቀሩት። የክርስትና ሃይማኖት መሥራችና መሪ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው ከሰማይ የወረደውና በመጨረሻም ወደ ሰማይ ያረገው። ክብር ምስጋና ይሁን ለአብ ለወለሰድ ለመንፈስ ቅዱስ!

እስከመጨረሻዋ ጠብቀን እንድንኖር ይርዳን።
ይቆየን።!
@
2025/07/04 20:37:15
Back to Top
HTML Embed Code: