Telegram Web Link
ስለ ክቡር ዶ/ር አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን...

ቴዲ አፍሮ ዛሬ ሐምሌ 24/2013 ዓ.ም ከጎንደር ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬቱን ተቀብሏል። የክቡር ዶክትሬቱን በይፋ ከተቀበለበት ሰዓትም ጀምሮ የሙሉ ስም አጠራሩ "ክቡር ዶክተር አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን" ሆኗል። ይኽ አርቲስት ለዚህ ክብር የበቃው ለዘመናት በአገራዊ፣ በማህበራዊ፣ በፖለቲካዊ እና በሀይማኖታዊ ጉዳይች ላይ በጽኑ ተግቶ በመስራቱ እና የኢትዮጵያዊነት ስሜት ደብዝዞ እንዳይቀር ይልቁንም ኢትዮጵያዊነት እንዲገዝፍ ለአመታት በሙያው በመትጋቱ ነው። ይኼንንም እውነት የጎንደር ዩኒቨርስቲ በጽሁፍ አርቅቆ ለታዳሚያን ተርኳል። የውኃ ሚኒስቴር የሆኑት ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ለቴዲ አፍሮ ያላቸውን አክብሮት ሲገልጹ "ወንድሜ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/ እንኳን ደስ ያለህ.." በማለት ነበር።

ክቡር ዶክተር አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን በመርኃ ግብሩ ላይ ለቤተሰብቹ ለጓደኞቹ ለባለቤቱና የክብር ዶክትሬት ላበረከተለት ለጎንደር ዩኒቨርስቲ ምስጋናውን ያቀረበ ሲሆን አገራችን ኢትዮጵያ ያለችበት ወቅት ከባድ የጭንቀት ወቅት እንደሆነ ገልጾ ይኼ ወቅት እንደ እናቶች ምጥ ነው ከከባድ ምጥ በኋላ ነፍሰ ጡር ሴቶች ልጅ ወልደው እንደሚገላገሉ ሁሉ ኢትዮጵያም ከዚህ ጭንቅ በኋላ ፍጹም ሰላም ትሆናለች በማለት ምኞቱን ጭምር አስተላልፏል። አክሎም ለዘመናት ኢትዮጵያን በጎሳ እና በዘር ከፋፍሎ ያዳከማት ኃይል ዳግም የቀደመውን እድል እንዳያገኝ ሆኖ መሞቱን በመግለጽ ወጣት ተማሪዎች በተለይም በብዙ ልፋት ለተመረቁ አገር ተረካቢዎች የኢትዮጵያን ጉዳይ አደራ ብሏል።

ክቡር ዶክተር አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን በአድናቂዎቹ በጓደኞቹ እንዲሁም በዘመድ አዝማዶቹ ታጅቦ ወደ ጎንደር የገባ ሲሆን በከተማው ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል። የጎንደር ህዝብም ባገኘው አጋጣሚ ለክቡር ዶ/ር ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/ ያለውን ፍቅር እና አክብሮት ገልጾለታል። በዚህ እለት በመላው ዓለም የሚገኙ አድናቂዎቹ እና የመገናኛ ብዙኃን የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ ስነ-ስርዓቱን በሰፊው ሲያሰራጩ ውለዋል።

ማሳሰቢያ

ክቡር ዶክተር አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ወደ ፕሮግራሙ ስፍራ እንዲገኝ የተቀጠረለት ሰዓት 4:00 ሰዓት ሲሆን የመድረክ መሪው በተደጋጋሚ ስሙን ሲጠራ የቆየ በመሆኑ በአንዳድ ግለሰቦች ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ቴዲ አፍሮ እንዳረፈደ ተደርጎ ሊወራ ችሏል። እውነታው ግን አርቲስቱ ሰዓቱን ፍጹም አክበሮ በቦታው ተገኝቷል።

የግርጌ ማስታወሻ እና ምስጋና...!

ክቡር ዶ/ር አርቲስት ቴዲ አፍሮ በተበረከተለት የክቡር ዶክትሬት ፍጹም ደስተኛ የሆነ ሲሆን አድናቂዎቹ እና ቤተዘመዱ ሁሉ የጎንደር ዩኒቨርስቲን ከነመላው አመራሩ ያመሰግናል። በተጨማሪም በጎንደር ከተማ በቆየንበት ወቅት በማንኛውም ሁኔታ ለተባበራችሁን እና ለትብብር ዝግጁ መሆናችሁን ለገለጻችሁልን በጠቅላላ እንዲሁም ለመላው የጎንደር ህዝብ ልባዊ ምስጋናችንን ለመግለጽ እንወዳለን።

#ታታ_አፍሮ /ነፃ ብዕር/
ዓለማችን ላይ በየዘመኑ ድንቅ የተባሉ ጥቂት ሰዎች አሉ። በየዘመኑም ይፈጠራሉ። ለኔ በዚህ ዘመን ካንተ በቀር አንድ ሁለት ብዬ የምቆጥረው ሌላ ሰው የለኝም። አገሬ በጭንቅ ከተዋጠችበት ዘመን ጀምሮ የልጆቿን እና የሰንደቋን ነገር ችላ ሳትል እጅህን ወደ ነበልባል እሳት የሰደድክ አንተ ብቻ ነህ። አንተ "ለኔ" ብሎ አማርኛ አታውቅም። አንተ "ለኔ" ብሎ ግብዝነት አይነካካህም። በኪነ ጥበቡም ዘርፍ የዓለም የድል /የበላይነት/ ሰንጠረዥን በሩጫ ብቻ ሳይሆን በሙዚቃም አድቅቆ አንደኛ መሆን እንደሚቻል ብቻህን ታግለ፤ ድልንም አስመዝግበ አሳይተኸናል። አገሬ ከፍላ የማትጨርሰው የአንተ እዳ አለባት! ለወገኔ አመስግኖክ የማይፈጽመው ደግነትን አሳይተኸዋል። ኢትዮጵያ ባንተ ተግባር ለዘለዓለም ትኮራለች። ታሪኳን የዘከርክ፤ ክብሯን ያሳሰብክ፤ ድሏን ያበሰርክ ጀብዷንም የመሰከርክ ድንቅ እና ፍጹም ጥበበኛ ልጇ አንተ ነህ። ክቡር ዶ/ር አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን... እ...ን...ወ...ድ...ኃ...ለ...ን!

#ታታ_አፍሮ /ነፃ ብዕር/
ተሸንፌ የወደድኩህ...

እቺ ምስኪን አገሬ ሳይኖራት ሳይተርፋት መምህር ቀጥራ ትምህርት ቤት ገንብታ ያስተማረቻቸው ምሁሮች እውር ሆነውባት ያውቃሉ። ከትቢያ አንስታ እውቀት ዘርታባቸው ሰው አርጋቸው ስታበቃ ስጋዋን ሊበሉ ደሟን ሊጠጡ እያጋሱ ተነስተውባታል። አንተ ግን "የአባቶቼ አደራ የሆንሽ ቅድመ አያቶቼም የደም ዋጋ የከፈሉልሽ አገር ነሽና የኔም ነፍስ ለሉዓላዊነትሽ መረጋገጥ ቢገበር ደሜም ቢፈስልሽ ላንቺ የሚሰሰት አንዳችም የለኝም።" ብለኽ ዘለዓለማዊ ቃልኪዳን ያኖርክላት ይመስል በዚህ ጥልቅ ስሜት ውስጥ ሆነ ያለ በደልህ መከራ እንደ ጅረት ሲፈስብህ፤ አንዱ ቁስልህ ሳይሽር ሌላ ቁስል እያበጁብህ መቆም እንኳን እንዳትችል ፈተኑህ።

ፍጹም ሰላምን ለሌሎች ለሚመኘው ልብህ ከፉበት። ደግነትን እንደ ማህተሙ አጥብቆ የያዘውን ስብዕናህን ተጠየፉት። አንተ ግን አንደበትህ ክፉ ሳይናገር እግርህም ለስደት ሳይገሰግስ የደማ ልብህን በአገርህ አፈር አከምከው። የወገንህን መጎሳቆል እያየች በሀዘን የተዋጠች ነፍስህን እያባበልክ ጥሩ ቀን እስኪመጣ ታገስክ። የፍቅርህ የጥልቀት ልኬቱ አንተ እንጂ ለሌላ ሰው ለመረዳት ቀላል አይደለም። እግዚአብሔር ላንተ በስፋትም፣ በልህቀትም፣ በግዝፈትም ከሌላ ልቦች ሁሉ ለይቶ የፈጠረልህ እስኪመስለኝ ድረስ በኩራትና በትዕግስት የተሞላች ልብህን እደነቅባታለሁ።

ላንተ ከወርቅ የከበረ የኦፓል፣ የኤመራልድ፣ የዳይመንድ እና የሩቢ ፈርጥ ያለው ከነዚህም የተበጀ ዘውድ ቢጫንልህ ያንስሃል እንጂ በፍጹም አይበዛብህም። የኔ ኩሩ ለሰው ልጆች ሁሉ የሚሰጡ ሹመቶች ላንተ ይገቡኃል። የአገሬ አርቲስቶች አርቲስት በመሆናቸው እና በሙያቸው መኩራትም ካለባቸው አንተ በዘርፉ መገኘትህ ትልቁ ምክኒያታቸው ሊሆን ይገባል።

አይ እኔ በልቤ ያለን ሁሉ ለመጻፍ ስታገል ከዐይምሮዬ እየገዘፈ እጨነቃለሁ...! ብቻ እውነት በሆነ መውደድ እወድኃለው! ስላንተ በእጅጉ እጨነቃለሁ። ደስታህን መካፈል ሳይሆን መደሰት እችልበታለሁ። ዝም ብዬ እወድኃለው ብዬ ባወጋ መመጻደቅ ነው የሚሆንብኝ። አንተን ተሸንፌ ነው የወደድኩ! ጥበብህ፣ ሀሳብህ፣ ግጥምህ፣ ዜማክ፣ ደግነትህ፣ ትሁትነትህ፣ መልክህ፣ ቁመትህ፣ ኩራትህ፣ ወኔህ፣ አነጋገርህ፣ አሳሳቅህ፣ ቁምነገርህ ወዘተርፈ ባህሪያቶችህ እኔን አሸንፈውኝ ወድጄኃለው! ቅንጣት እንኳ የሚጠላ ነገር ባንተ ላይ ሳጣ እደነቃለሁ። ከፍቅሬ በላይ የምሸልምህ ውድ ነገር የለኝምና እ..ወ..ድ..ኃ..ለ..ሁ!

#ታታ_አፍሮ /ነፃ ብዕር/
ቴዲ አፍሮ ጎዳና

ለዘመናት ኢትዮጵያዊነት ላይ ትኩረቱን አድርጎ ማህበረሰቡን በአገር ፍቅር ሲያነቃቃ እና በመልካም ምግባሮች ሲቀርጽ የኖረው ክቡር ዶ/ር አርቲስት ቴዎድሮ ካሳሁን በጎንደር ከተማ ላይ ከጎንደር ዩኒቨርስቲ በር እስከ ኮሌጅ ማዞሪያ ያለው የአስፓልት መንገድ የክቡር ዶ/ር ቴዎድሮስ ካሳሁን ጎዳና ተብሎ ተሰይሞለታል። የመንገዱ ስም ከዚህ በኋላ ቴዲ አፍሮ ግዳና እየተባለ ይጠራል።

#ታታ_አፍሮ /ነፃ ብዕር/
Channel photo updated
2025/07/04 15:26:26
Back to Top
HTML Embed Code: