Telegram Web Link
ላለፉት ሀያ አመታቶች ከእኛ ጋ አብረኸን ተጉዘኃል። እኛም ካንተ ኋላ አልጠፉንም! አንጠፋምም። በዚህ የሁለት አስርት አመታት ጉዟችን እኛ ላንተ ከሆነው በላይ አንተ ስለ'ኛ የሆንከው ዕልፍ ነው። እኛ ጭብጨባና ፉጨት ብቻ ሰጠንህ አንተ ግን ጊዜህን፣ ብርህን፣ እንዲሁም በነፍስህ ተወራርደ እራስህን አሳልፎ ለመስጠት ወሰንክ። ለዚህም የ1997 ዓመተ ምህረት አልበምህ እማኝ ነው።

ስለ ወገንህ ተቆርቁረሃልና በምላሹ ታሰርክ፣ ኮንሰርት ተከለከልክ፣ ከአገር እንዳትወጣም ታገድክ፣ ብርህንም ተቀማክ! ይኼ ሁሉ በደል አንተ ክፉ ሆነህ አይደለም። አገርህን በመምረጥህ፤ ድሃ ወገንህን በመውደድህ ነው። ያ ሁሉ ግፍ ባንተ ላይ የሆነው ስለ እኛ መጨቆን በመሟገትህ ነው። እኛ ሩቧን ሳናደርግልህ ይኼን ሁሉ ሆነህልናልና ከምስጋና የዘለለ ቃል አጣን። ውለታህን የመክፈል አቅሙ የለንም። ቢቻለንማ ነፍሳችንም አታሳሳንም። አገሩን እና ወገኑን ወዶ በኢትዮጵያ እንዳንተ የተንገላታም ሆነ የተሰቃየ የለም። ያለ ጥቅም ስለወደድከን እናመሰግንሃለን።

ወዳጄ ሆይ ዛሬ ጠላቶችህ አቅመ ቢስ ሆነዋል። ተሽመድምደው ወድቀዋል! አንተ ላይ ለሰሩት ግፍ የቱም ቅጣት ያንሳቸዋል። ስለ ምህረት እና ስለ ፍቅር አስተምረኸኛል ግና የምወደውን ሰው ለነኩብኝ እንዴት ይቅር ማለትን ልለማመድ። አንተን ገፍተውብኛልና በደላቸውን ቆጠርኩ ለተከፈላቸው ቅጣትም ደስ ተሰኘሁ። የቱም ቅጣት በነርሱ በፈጸም አላዝንም። አትፍረድ ክፉ ሆኜ አይደለም። ብቻ አንተ ዛሬ ከእሳት ተርፈ፤ ከበደል አምልጠኽ በወዳጆችህ ፊት የንጉሥ ያህል ታፍረ እየኖርክ ነው። ይኼ ለኔ ዓለም ነው። ወዳጃችን እና መካሪያችን ሆይ ዘመንህ በወዳጆችህ እንደተከበበች ትፈጸም። በዓለም ያለን ክብር ሁሉ በቁምህ እየው። ልዑል እግዚአብሔር ለእኛ ለወዳጆችህ ሲል ጭምር እድሜ ከጤና ጋ ይስጥህ።
Forwarded from Amleset Muchie
መልካም አዲስ አመት🌻🌻
ቴዲ አፍሮ ትላንት እና ዛሬ /ድሮና ዘንድሮ/

ከስምንት ዓመት በፊት ይመስለኛል ቴዲ አፍሮ "አባይ" የሚል አንድ ነጠላ ዜማ ለቀቀ። /ከእስቱዲዮ  ተሰርቆ ወጣ/ በእውነት በወቅቱ ዘፈኑን ስሰማው እኔን የልቤን ያደረሰ ነበረ። የዘፈኑ አንጓዎች ደግሞ ማራኪዎች ነበሩ። ለምሳሌ
"በጊዮን ወንዞች ዙሪያ የሚኖሩ ህዝቦች
የያዕቆብ ድንኳን ቤተ ዳዊት
የፂዮን ተራሮች አናት መልከ ጻዲቅ ለዓለም
የነገደ ኖኅ ቅይጥ ቀለም.."

የሚል የፊተኛው አዝማች ላይ ያለ ውብ የግጥም አንጓ ነው። ለስለስ ባለ ሙዚቃ አባይን ቁም ሲል ተማፅኖታል። አንጀትን በሚበላ ዜማ አንተ እንባዬ አባይ አትቆምም ወይ ብሏል... አንተ እንባዬ አባይ ሲል  በመብራት እጦት አይኗ በጢስ ስለሚያነባ ድኃ እናት ላለመሆኑ ማረጋገጫ የለንም። ልጁ ጥበበኛ ነዋ...!

ሙዚቃው ሲጀምር በወኔ ነው። በወኔ ስልህ በጀብደኝነትም ጭምር..! እንደ ሐበሻ ልማድ በኩራትም። ሊያውም ታሪክን ከስሩ ነቅሶ አመጣጡን ጠቅሶ ነዋ...
እንዲህ ይላል...

"የወንዞች ሁሉ ራስ አባይ
የጣና ደሴት አዋይ
የኤደን ገነት ካባ
የገዳም ፀሎት እንባ
አትቆምም ወይ
አንተ እንባዬ አባይ...?"

በዚህ የመግቢያ ግጥም አቅምን አጎልብቶ በአይን እንባን አለመሙላት ከባድ ነው። አዎ እጅግ ከባድ ነው። የወንዞች ሁሉ ራስ ብሎ በምድራ ካሉ ወንዞች ሁሉ የላቀ ብሎ ሲጠራው ለጠላት ግጥም ለማሳመር አባይን ለማቆላመጥ የሚመስለው ቂል አይጠፋም እኮ ቅሉ ግን ወዲህ ነው። አባይ ከገነት ከሚፈልቁ አራት ትላልቅ የምድራችን ወንዞች አንዱ ነው ይላል መፅሐፍ ቅዱስ። ታዲያ እንዴት አባይ የወንዞች ሁሉ ራስ አይባል። እንዴት ያለውን ጥበብ ቢታደል ነው አባይን እንዲህ ባለ ረቂቅ ቃል መግለፅ የተቻለው..? አባይ በጣና ደሴት ገዳማቱን ስሞ በኩራት በረኃ እየሰነጠቀ ስለመውጣቱ ሲያወሳ ደግሞ...
👍1
"የጣና ደሴት አዋይ" ይለዋል... ኧረ የሱስ ለብቻው ነው ጃል። መጣፉን ጣፈው ዜማውንም አለው ከሙዚቃው አዋህዶም ዘፈነው። የጣናን ደሴት ጠቅሶ ገዳማቱ ውስጥ ያለን አገራዊ ጠሎት አለመጥቀስ በቴዲ አፍሮ ዘንድ ታሪክ ማጓደል ነውና
"የኤደን ገነት ካባ
የገዳም ፀሎት እንባ
አትቆምም ወይ
አንተ እንባዬ አባይ...?"
ሲል ስንኝ ቋጥሯል...

ታዲያ እንዲህ እያለ የተማጸነው አባይ ጩኸቱን ሰምቶ በትውልድ የላብ ጥርቅም አገሬን ልርዳት፤ የእናቶቼ እንባን ላብስ፤ በጨለማ አዳሪ ወገን አይኑረኝ። ኢትዮጵያዬ ትልማ ብሎ የአገር ልማቱን ሲጀምር ምስር "እኔ የማንን ጎፈሬ ሳበጥር ሐበሻ ግድብ ሊገድብ" ብላ ብትፈነጭ ጥበበኛው አገር ተነካ፤ ወገኔን ሰደቡብኝ፤ ባንዲራ ተደፈረ ሲል ብዕሩን መዘዘ! አበሻ ቼ በለው ካለ የአድዋ ሰንሰለታማ ተራሮች አፍ አውጥተው እስኪመሰክሩ ድረስ መራር መሆኑን ሊገልጽላቸው "ቼ በለው ኧረ ቼ በለው" እያለ አንጎራጎረ...! ቢገባቸው ይግባቸው ሲል በአረብኛ አስተርጉሞ ግጥሙን እንካቹ አላቸው።

"አባቱም ገዳይ እናቱም ገዳይ
ድርድር አያውቅም በአገሩ ጉዳይ"

ከዚህ የዘለለ ማስጠንቀቂያ ምን አለ..? ከዚህ በላይስ በምን ቋንቋ ስለ ጀብደኝነታችን ይናገራል። የቱስ ጥበበኛ ተነስቶ ዋ... ሲል ያስጠነቅቃል..? ነገ ግብጥ ሄዶ ኮንሰርት እንዳይሰራ ሊሆን ነዋ..! ነገ አረብ አገር ሄዶ ብር ላያገኝ ነዋ ምስርን ዋ ብሎ.. የኔው ሰው ግን በአገርነውና የመጡቱ "ዋ.." አላቸው! አይፈሬነቱን ሲያረጋግጥ ያ የነ ተፈሪ የነ ምኒልክ ልጅ "ሯ እኔ ማንንም አልፈራ.." ሲል አዜመ አበሻ እኮ ጀብደ ብዙ ነው። ከእናት ከአባቱ የወረሰው ጀብድ አሁንም አለ። ዳሩማ ባለ ቅኔው ሎሬት ቴዲ አፍሮ ስለ ጀብደኝነታችን ብቻ ከትቦ ዝም አላለም። ይልቁንም ከሁሉ ስለሚልቀው ደግነታችን እየራበን አጉራሽ ስለሆነ ማንነታችን አስረግጦ ተናግሮ ዳግም ደግሞ በማንነታችን የማንደራደር አልፈው ከመጡ እነሱ ጭድ እኛ እሳት ሆነን ልናጠፋቸው እንደምንችል ያስጠነቅቃል።

"አባይ የግሌን ባልኩኝ ለጋራ
ካቃራት ምስር ግፍም ሳትፈራ
የተቆጣ እንደው ፍቅር ታግሶ
የሚባላ እሳት ይሆናል ብሶ"

ስለዚህ ስንኝ ቴዲ አፍሮ ሲያወራኝ መፅሐፍ ቅዱስ ላይ "እግዚአብሔር የሚባላ እሳት ነው" ይላል እንዳለኝ አስታውሳለሁ። እርግጥ ይኼንን ቃል እኔ ዘዳግም እና ዕብራውያን ላይ አስተውዬዋለሁ። ከላይ ያለው ስንኝ በብዙ ይተረጎማል። ለምሳሌ እግዚአብሔር ለኛ ይፈርዳል ጦር ቢመዙ እንኳ ከእኛ ዘንድ ላለው እውነት ሲፈርድ እነርሱን እስከማጥፋት ነው የሚል ሌላ ሚስጥርም ይኖረዋል! /የግል እይታ ነው/ "ደሞ በአባይ" የተሰኘው የንጉሡ ሙዚቃ ይኼን ፅሁፍ እስከ ከትብኩበኩበት ሰዓት ድረስ በዩትዩብ አራት ሚሊየን ጊዜ ታይቷል።

የሆነው ሆኖ ቼ በለው የተሰኘውን ሙዚቃ ዘወትር ከፍ ባለ ድምፀት እያዳመጥኩ እውላለሁ። ሙዚቃው ለተዓመር የተቀናበረ ነውና ሙዚቀኞችም ቪዚክስ ሆኖባቸዋል... ይኼ እኔን ያስደስተኛል ብልህስ ጃል...😊 እስኪ ቼ በለው ወደ ንጉሡ ሙዚቃ...!

#ታታ_አፍሮ /ነፃ ብዕር/

#ቼ_በለው #ደሞ_በአባይ

https://youtu.be/btuC2IfwmfQ
👍1
@
"...️በሚያሳዝን ሁኔታ አፍሪካን አንድ ለማድረግ የሞከረ ህዝብ ለራሱ አንድ መሆን አቅቶት ስቃይ ውስጥ ነው ያለው!!
"...እኛ ኢትዮጵያውያን ከተባበርን አይደለም ለኛ ብቻ መሆን ይቅርና በፅኑ እንቅልፍ ለወደቀው ለሰፊው አፍሪካም ትልቅ አቅም እሚሰጥና ወደፊት የሚያፈናጥር ህዝብ ነው ኢትዮጵያዊ። ኢትዮጵያን ማዳን ደግሞ #የኔም #ያንተም #የሁላችንም ሀላፊነት ነው።

#ቴዲአፍሮ
1
@
በኢትዮጵያ ኪነጥበብ ውስጥ አንቱታን ያተረፈችው እና ለዘመናት በድንቅ የትወና ችሎታዋ በህዝብ ልብ የኖረችው አርቲስት አልማዝ ሐይሌ ዛሬ ጠዋት 1 ሠዓት ላይ ማረፏን ሰማን። ይኼ ለኪነ ጥበብ አፍቃሪያን እና ለአርቲስቷ ወዳጆች እጅግ የሚያሳዝን እና የሚያስደነግጥ ዜና እረፍት ነው። ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እና ለአድናቂዎቿ ብሎም ለእኛ መፅናናትን ፈጣሪ ያድለን። የዚህችን የተወደደች ባለሙያ ነፍስ በአፀደ ገነት ያሳርፍልን። የአርቲስቷ የቀብር ስነ ስርዓት ነገ /መስከረም 16/ ከቀኑ 6 ሠዓት ላይ በሥላሴ ቤ/ክርስቲያን ይፈጸማል።
@
#መስከረም_17_እና_የቴዲ_አፍሮ_ገጠመኞች

መስከረም 17 እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ ታላቅ በዓል ነው። ህዝበ ክርስቲያኑ ከሚያከብራቸው ታላቅ በዓላቶችም የመስቀል በዓል አንዱ እና ዋነኛው ነው።

ቴዲ አፍሮ በመስከረም 17 መልካምና አሳዛኝ ገጠመኞች አሉት። አስደሳቹ ገጠመኝ የሚጀምረው በጋሽ ጥላሁን የልደት ቀን ነው። የክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ መስከረም 17/1933 ዓ.ም ተወለዱ። ይኽ ቀዳሚው ክስተት ነው። ቴዲሻ ይኼን ቀን "የሞያ አባቴ የተወለደበት ቀን.." ብሎ ይጠራዋል።

ቀጣዩ እና አሳዛኙ ክስተት መስከረም 17/1993 ዓ.ም ቴዲ አፍሮ "አቦጊዳ" የተሰኘውን ተወዳጅ አልበሙን እያጠናቀቀ ባለበት ወቅት ወላጅ አባቱ አረፉ። ቴዲም እጅግ አዘነ ያለ እናት ያሳደጉት ደግ አባቱ በሞት ተለዩት። ካሳሁን ገርማሞ ለቴዲ እንደ አባት ብቻ አልነበረም። እጅግ የሚወደው እጅጉንም የሚያከብረው መመኪያውም ጭምር ነበር። ይኼ ክስተት ለቴዲ አፍሮ ቀላል አልነበረም። በሚዲያ ሳይቀር እንባ እየተናነቀው ስለ አባቱ አውርቷል። ቴዲ አፍሮ ግን በአባቱ ሞት አዝኖ ለሙት መንፈስ እጅ ሰጥቶ መቆዘም አልፈቀደምና
"በሞትክ ላይ ፎክሬበት በዳንኪራ
ትነሳለህ ከኔ ጋራ ትነሳለ ከኔ ጋራ..." የሚል ስንኝ ቋጥሮ ሌላ የመደሰቻ ቀን መፍጠር ቻለ።

ይኼውም መስከረም 17/2005 ዓ.ም በዕለተ ሐሙስ ሰርጉን ሰርጎ ሞትን ድል አድርጎ እሱ የአባቱን ቦታ ተክቶ ቀድሞ ባል ኋላም አባት በመሆን አባቱን ዳግም አነሳው። የአባቱ ስም የሚጠራበትን ዘር ዘራ። ዛሬ ሚካኤል ቴዎድሮስ ካሳሁን እና ማርያማዊት ቴዎድሮስ ካሳሁን እየተባሉ የሚጠሩ የዘር ሀረጎችን መዘዘ።

መስከረም አስራ ሰባትን ቴዲ አፍሮ ጠቅልሎ ሲገልፃት። "የሞያ አባቴ መስከረም 17 ተወለደ ወላጅ አባቴ ደግሞ መስከረም 17 ሞተ..." ይላል። እነሆ መስከረም 17 ለቴዲሻ የድል ቀን ነች። ቴዲዬ መጥፎ ትውስታዎችን በመልካም የመሻር ረቂቅ ተሰጥኦ አለው። አስበው እስኪ ማነው ለሰርግ ሐሙስን የሚመርጥ..? ሐሙስ የቀን ቅዱስ...ቴዲ እንጂ እንዲህ ያለ ቀንን የሚመርጥ! ሁሉን ምክኒያታዊ በሆነ ነገር ላይ በመንተራስ የሚያደርግ ታላቅ ሰው። መጥፎ ትውስታ ያዘሉ ቀኖችን በመልካም ትውስታ ቀይሮ በመስቀሉ ብርሃን ለበራው ለታላቁ ንጉሥ ለቴዲ አፍሮን እረጅም እድሜ እመኝለታለሁ። ሙሉ ጤና ላንተና ለቤተሰቦችህ።

በሐፁረ መስቀሉ የጠበቀን በደመ መስቀሉ የዋጀን አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን፡፡ ጌታን የወለደች ብጽዒት ድንግል ማርያም የትውልድ ሁሉ ምስጋና ይድረሳት።

ከዚሁ ጋ በተያያዘ ክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ እና አንጋፋው አርቲስት ካሳሁን ገርማሞ ነፍሳቸውን በአጸደ ገነት ያሳርፍልን። ለቴዲ አፍሮ እና ለባለቤቱም መልካም የትዳር ዘመን ያድልልን!

#ታታ_አፍሮ /ነፃ ብዕር/

መስከረም 16/2013 ዓ.ም ተለጠፈ
ይኸው የኔ ንጉሥ ድል ባለ ሰርግ የአገሩን ወግና ማዕረግ እንዲሁም ባህልና ስርዓቱን ሁሉ ጠብቆ ከተሞሸረ ስምንት አመታቶች ሞሉት። መቼም ከስምንት አመታት በፊት መስከረም 17/2005 ዓ.ም በቴዲ አፍሮ ሰርግ ጮቤ ያልረገጠ ወዳጅ ዘመድ እንዲሁም አድናቂ የለም። እኔም እራሴ የኔ ሰርግ እስኪመስለኝ ድረስ በልቤ የነበረው ደስታ በቃል የሚገለጥ አልነበረም! ቴዲዬ የኔ ልበ ቀና ሁሌም ደስተኛ ሆነህ አንዳች ሳይጎልብህ ኑርልኝ። ደስታህን መስማት ያስደስተኛል። ሁሉ ይሙላልህ ጌትዬ! በህይወትህ የሚያስፈልጉህን እና የሚበጁህን ነገሮች ሁሉ ከልብህ መሻት ጋ አጣጥሞ ልዑል እግዚአብሔር ይቸርህ ዘንድ እመኝልሃለሁ። ፍጹም ሰላምና የልዑል እግዚአብሔር ሀሳብ ብቻ የሚፈጸምበት ቅዱስ ትዳር ይሁንላችሁ!
2025/07/09 21:13:29
Back to Top
HTML Embed Code: