Telegram Web Link
አንዱ ሰውዬ ነው ... ለስላሴ ልጅ እንዲሰጡት ተስሎ ... ሚስቱ መንታ ወለደች ...
"ስላሴ መንታ ሰጡኝ" ብሎ ስለቱን አስገባ ...

በዓመቱም መንታ ደገመች...
"ስላሴ ደገሙኝ" ብሎ አሁን ስለቱን አስገባ

አሁንም በዓመቱ ሚስትየው መንታ ሰለሰች....
"ስላሴ ደጋገሙ!" ብሎ አሁንም ስለቱን አላጏደለም::

አሁንም ለአራተኛ ጊዜ ሚስትየው መንታውን ስታስታቅፈው...
"ኤጭ ስላሴ አበዙት" አለ አሉ..... 🤣🤣🤣

ትናንትና ጠዋት ኢምባሲ ቀጠሮ ነበረኝ ብዬ .... እኔን ብሎ ጠንቃቃ .... በቤቴ ኮ መንገድ ስለሚዘጋ ብዬ እነፀጊን ይዤ ... ሆቴል ይዘን ቀረብ ያለ ቦታ ለማደር መሄድ ... ማታ በየቦታው ስንገተር 6 ሰዓት ሆኖ ሆቴል ደረስን ..... ይሁን አልን.....

ጠዋት ኢምባሲዎቹ መንገድ ዝግ ነው ብለው ለሌላ ቀን ቀጠሩን .... ይሁን አልን ....

ማታ ነበር በረራዬ ቀኔን ቀያይሬ .... ወደ ቤት ልመለስ ብል በየት በኩል .... እዝህችው ቦታ ላይ ለ3 ሰዓት ቆምን .... (ፎቶውን የተነሳሁበት ቦታ) .... እንደሰውየው አበዙት አልልም ብዬ ቻልኩት 🤣🤣

ከቦሌ ጀሞ ለመድረስ ተጨማሪ አራት ሰዓት ሲፈጅብን "ኤጭ አበዙት" እያልኩ መንገድ ላይ ውዬ ማታ 2 ሰዓት የገባሁ ሰው ነኝ😜😜

እስቲ ንገሩኝማ ዛሬም ዝግ ከሆነ ቢያንስ በሶና ቆሎ ይዘን እንንቀሳቀስ.....
ይህቺ “አይመጥነኝም” “አትመጥነኝም” እያላችሁ ስለምትሰካከሷት ነገር እናውራ እስኪ ...

በቀደም አንዱ ሁለት ዓመት አብሯት ከቆየ ፍቅረኛው ጋር ተጣልቶ “ድሮም አትመጥነኝም!” አለኝ።

“በምን?” አልኩት ልጁ ቀውላላ ነገር ስለሆነ በቁመት ከሆነ ብዬ ነው። 😜

“በቃ አለ አይደል...” ምናምን ብሎ ከሷ የተሻለች ቆንጆ እጠብሳለሁ ዓይነት ነገር አለኝ። የሱ ሲገርመኝ እሷንም አሳምኗታልኮ እና እንደማትገባው ነው የምታስበው

ይሁን ደረጃችሁን መድቡ እንደው ግን የሚመጥነኝ ብለሽ የመደብሽው በምን ሚዛን ነው? በሀብቱ? በመልኩ? በዝናው? በማንነቱ?
በምላሱ? (አንዳንዱኮ የምር ከምኑን ሳይሆን በምላሱ ምስሉን ይስላል) በቁመቱ ( እቃ ጫኝ ነው እንዴ የፈለግሽው??)

አንተ ራሱ ራስህን በመልኳ ለክተኸው ነው? በትምህርት ደረጃዋ ለክተኸው ነው? (ይቅር ይበልህ በመቀመጫዋም የምትለካ እኮ አለህ ቱ 🙆🏻‍♀️🙆🏻‍♀️)

ጊቢ ተማሪ እያለሁ በእንግሊዝኛ አክሰንቷ በጣም የምንቀንባት አንድ ልጅ ነበረች። ስሟ ሲነሳ ሁሉም ሰው ወደ ጭንቅላቱ የሚመጣው የእንግሊዝኛ ችሎታዋ ነው። አንዱ ሸበላ ምኗ እንደማረከው ሳይገባው ብቻ ስለተወራላት ጠበሳት። በኋላ ስናወራ ቅዝቅዝ አለብን:: ደሞ እኔ ነኝኮ ስንቀለቀል

“አክሰንቷ ብቻ አይበቃም በናትህ?” እለዋለሁ

“አክሰንት ይነካል? አክሰንት ይሳማል? አክሰንት እንትን ይደረጋል?” አለኛ ኮስተር ብሎ 🤣🤣🤣

አትሰካከሱ በናታችሁ የራሳችሁን የይገባኛል ደረጃ በእገሊት ወይ በማህበረሰቡ መስፈርት ላይ ተንጠላጥላችሁ አታስምሩ። ሞዴል የጠበሰ ጀለስህን እያየህ መስፈርትህን አትለካ .... ይሄኔ እሱ አልነገረህም እንጂ መኝታ ቤት ገብቶ አረፍኩ አፈስኩ ሲል ፎቶ ማንሳት መሮታል 🤷🏽🤷🏽....

ያቺ ባለሀብት የጠበሰች ጏደኛሽን እያየሽ ደረጃሽን አትመድቢ .... ይሄኔ እሷም አልነገረችሽኝ እንጂ ሶዬው ፊልድ አለኝ ብሎ ስራ ለቀናት የሄደ ቀን ... 'ጌታ ሆይ ውለታህ በዛብኝ' ትላለች ...

እኔ እንደአንድ ግለሰብ ምንድነው የምፈልገው? (ከእውነታው የተዛመደ ነገር ፈልጊ ዓለሜ! ያ ስማርት ቆንጆ አመለ ሸጋ ከዛ ደግሞ ሀብታም ከዛ ደግሞ ደረቱ ሰፊ ከዛ ደግሞ ትከሻው ምናምን ከዛ ደግሞ ማብሰል የሚችል ከዛ ደግሞ ዝነኛ የሆነ ቢሆን .......የለም !! እማ እሱን ሶዬ ለፊልም ራሱ በመከራ ነው ያሰለጠኑት)

አንተ ራሱ የኔ ማር ቆንጆ ሰውነቷ የተስተካከለ ከዛ ደግሞ ሙያ ያላት ከዛ ደግሞ እንደእናቴ የሆነች ከዛ ደግሞ ወጪ የማታበዛ ከዛ ደግሞ ራሷን የቻለች እና የተማረች ......... ሶዬ እናትም ሚስትም ፍቅረኛም ሼፍም ...በአንድ ሴት ውስጥ አይከብድህም?)

ከለካህ አይቀር ራስህን ከፍ አድርገህ በማንነቷ ለካና እግባባታለሁ ብለህ ተመጣጠን። አንቺም እንደዛው። ልብ አድርጊ ራስሽን የምታስቀምጪበት ዋጋና ደረጃ አይኑርሽ እያልኩ አይደለም። ባክሽ ገብቶሻል!!!

ውብ ቀን ውብኛ አዋዋል ዋሉልኝማ❤️❤️❤️❤️❤️

https://www.tg-me.com/yemeri_terekoch
እውነት እናውራና

አንድ
በአብዛኛው በማህበረሰቡ የቁንጅና መስፈርት ቆንጆ የተባሉ ሴቶች ከቁንጅና እና ከመዋቢያ እቃ በላይ ምንም አንገብጋቢ ነገር በዓለም ላይ የሌለ የማይመስላቸው፣ ንባብ ጠል ፣ እነሱነታቸውን ለመገንባት ግድ የማይሰጣቸው .... አንድና አንድ ዓለማቸው እና ወሬያቸው የሚያጠነጥነው ስለሊፒስቲክ እና ስለሚጎመዥላቸው ወንድ ብዛት ፣ ዌል ስለአርቲስቶቻችን ጥልቅና ምጥቅ መረጃና እውቀት አላቸው።

ሁለት
(አሁንም በአብዛኛው) ሰውነታቸውን በስፖርት ገንብተው ጠብደል ጡንቻ ያካበቱ ወንዶች እነዚህም ያው ናቸው ዓለማቸውና ወሬያቸው ስለስፖርት ቤት፣ ስለምግብ ..... እገሌ ሲያየኝ መንገድ ሁላ ነው የሚቀይረው። ሽንቱን ነው የማሸናው አይነት ወሬ ነው ጨዋታቸው። እነዚህኮ ጡንቻቸውን ወጥረው ሴት ሁላ ያስፈራራሉ .... በጣም ምጥቀታቸው። "ነይ አንቺ!" ምናምን ብሎ ሴት ይጠራል መንገድ ላይ። 🤷🏽 ከጡንቻው በተጨማሪ ለጠቅ አድርጎ ትንሽዬ ከንፈርና አፈንጫ ጣል ካደረገበት ደግሞ የሰፈሩ ሴት ፈረደባት 🤣🤣

በአብዛኛው የሚለውን የደጋገምኩት ሁሉም አይደሉም ለማለት ነው!!

ሁላችንም የማህበረሰባችን እና ያስተዳደጋችን ውጤት ነን እኮ አይደል? በጣም ቀላል የየእለት ኑሯችን ሴትን ከውበት ጋር ወንዱን ከአቅም ጋር ያጋባ አስተሳሰብ ነው። (አቅሙ በገንዘብ፣ በጡንቻ ወይም በትምህርት ደረጃ ሊገለጥ ይችላል)

ለምሳሌ ከፀጊ እና ከፍቅር ጋር መንገድ ስወጣ የሚያገኘን ሰው። ፀጊን ቆንጅዬ ሆነች .... ፍቅርን ደግሞ ‘አንተ በጥባጭ ጎረመስክ!’ ያው እኔን አረጀሽ እንዳይሉኝም አፍረው ምንም አይሉኝም!🤣🤣🤣

እስኪ ዘፈኖቻችንን ስሟቸው ወላ ቁርጭምጭሚቷ ምናምን እያለ እኮ ለአካላዊ ውበቷ የሚያቀነቅንኮ አለ። ዳሌዋ ሲውረገረግ ፣ ዓይኗ ጉልላት ...ጥርሷ መብረቅ ምናምን ... ባቷ መቀመጫዋ .... ከዚህ እልፍ ካለ የጠመቀችው ጠላ ዓይነት ሙያዋን የሚያሞግስ ግጥም ይኖራል።

ክሊፖቹን ተዋቸው ወላ መቀመጫዋን ዙምምምምም ያደርገዋል 🤣🤣 የትኛው ዘፈን ነው እስኪ ይህቺ ነፍስ ስላላት ሴት የሚያወራው? በጣም ጥቂት!! እንደ “መልክሽ አይበልጥሽም” አይነት ዘፈን ....

ስለወንዱ ሲዘፈን በብዛት ምንሽር ያነገበ ሶዬ ይታይና ወይም ትከሻው ከፍ ያለ ምናምን ቅንድቡን እየሰቀለ (የዘንድሮ ወንድ እንኳን ለሜካፑ ከሴቱ ብሷል ) ግጥሙ ጀግና ተኩሶ ገዳይ የተከበረ የታፈረ ምናምን አይነት ..... ክብደት ሲያነሳም አለበት!!

ውበት ጥሩ ነው። በእስፖርት አካልን መገንባትም መልካም ነው። ስለውበት ማወቅና ውበትን መጠበቅ ደስ የሚል ነገር ነው። ምክንያቱም ሰውነትሽም ያንቺው ነው። ፊትሽም ያንቺው ነው። ተዋቢ (ስትተኚ ቢዮንሴን መስለሽ ተኝተሽ ስትነቂ ሜሪ አርምዴን የምትመስዪው ነገርም ቢሆን ላንቺ ከታረቀልሽ ይመችሽ)

ግን አስቢው ሰውነቷን የምትጠብቅ፣ ቆንጆ፣ ከዛ ደግሞ ነፍስ ያላት ሴት ስትሆኚ ......ሞላሽ ማለትም አይደል? እንደዛ ማለቴ ነው። ይቻላልኮ ቆንጅዬ ሆነሽ ከዛ ደግሞ ስታወሪ የምትጣፍጪ በሳል ነፍስ ያላት በራሷ የምትተማመን

(ልጆቼ እንዲሆኑልኝ የምፈልገው እንደዛ ነው። ይመስገነው እስካሁን ባለው በርትተናል!! ወደፊትም አያሳፍሩኝም! ያው እኔ መልኩ ተላልፎኛል ብዬ ነው 😜😜🤣🤣🤣)
(ለወንዱም ይሰራል)

ሶስተኛ እና አራተኛ መደቦችን ለጥቀን እንፅፋለን እስቲ እናንተ ደግሞ የራሳችሁን መንሽኑ

ሜዬ ለጋ ለጋውን ብናወራ ምን ነበረበት በቅዳሜው??? 🏃🏽‍♀️🏃🏽‍♀️🏃🏽‍♀️🏃🏽‍♀️🏃🏽‍♀️

ውብ ቀን ውብኛ አዋዋል ዋሉልኝማ ❤️❤️❤️❤️
ዲያስፖራው አጎትህ ከአሜሪካ ይመጣና ቁርጥ እየጋበዘህ የስደትን አስከፊነት ያብራራልሃል......

«እዚህ ሀገር ገና አልሰለጠናችሁም... ምንድነው ይሄ ሁሉ ቦርጭ?? ጂም አትሄድም እንዴ?? .... እናልህ ስደት ለጠላቴም አልመኘው!!..... "

"አስተናጋጅ እስኪ እጄን የምታጠብበት የታሸገ ውሃ አምጣልኝ?? ኤጭ እዚህ ሀገር ደሞ ፌክ ውሃ ታሽጋላችሁ አሉ ደግሞ እጄን ይቆራርጠኛል... አምቦውሃውን ሞቅ አድርገህ አምጣልኝ በቃ!!" ወዳንተ በቄንጥ ዞር ይልና ..

"እናልህ የወንድሜ ልጅ ስደትን እንዳታስበው...... "

ማታ ክለብ ይዞህ ይወጣና የ30 ምናምን ሺህ ብር ውስኪ ለሁለት ቆነጃጅት እየጋበዘ የስደትን አስከፊነት ይለጥቅልሃል... ለቺኮቹ ዘወር ይልና "ይገርምሻል LA የሆነ ቀን.... " ቺኮቹ በማያስቀው ሲገለፍጡለት እያየህ የስደት አስከፊነት ውስጥህ ሰርፆ ይገዘግዝሃል......

"እኔን አጎቴ እኔ ልሰቃይልህ!! ስደት እንዲህ ከመረረህ ለምን እርግፍ አድርገህ ትተህ ሀገርህ አትገባም?" ስትለው....

አሁንም በሀዘን ጭንቅላቱን እየነቀነቀ... "እኛማ አንዴ ገብተንበታል..... ስንት ሀላፊነት አለብን.... እናንተ ተሰብሰቡ እንጂ ...." 😜😜😜😜

Bilal ደግሞ አለልህ ቱርክን እያስጎበኘህ "የኩበት ሽታ ናፈቀኝ" 🎷🎷🎷🎷🎷 (ጠርታ ኩበት የምታጥንልኝ ልጣ??🤣🤣🤣🤣)

ኦንድሜ ስደትም እንደማንኛውም ህይወት ሁለቱንም የህይወት ፍሬዎች ያዘለ ነው:: ትርፍም ኪሳራም.... ሀገርህም ስትኖር እንደዛው .... በሀገርህ ድሎት ብቻ ቢሆንልህ ቀድሞውኑም ስለመሰደድ ባላሰብክ....

ለእገሌ ስለተሳካለት አይሳካልህም:: እገሌ ስለወደቀ አትወድቅም..... ያንተ የራስህ መንገድ ነው.... !! ስደት ይደላል ወይም ስደት ይከፋል አልልህም..... !! ምን እንደምታጣ እና ምን እንደምታገኝ ስሌትህን ራስህ ስራ!!

ሀገሩ ቁጭ ብሎ የተሳካለት ብዙ አለ:: (ወላ ለጉብኝት የሚወጣ) ሀገሩ ቁጭ ብሎም ያልተሳካለት ብዙ አለ:: .... እንዳልኩህ ነው ስሌትህን ራስህ ስራ... የእገሌ ውድቀትም ስኬትም መማሪያ ሊሆን ይችላል እንጂ ያንተ ሊሆን አይችልም:: ....

ዲያስፖራው አራት ወር ሀገር ቤት እየቀበጠ ከሚያስጎመዥህ ህይወት በፊት አራት ዓመት ኑሮ እንዴት እንደቀበጠችበት ይንገርህ ....(እርግጥ ቀብጦም ሊሆን ይችላል)

አንቦ ውሃ ከማስፈላቱ በፊት .... ደሙ ፈልቶ እንደነበር ጠይቅ!!!

እኔ ራሱ የኩበት ጭስ ናፈቀኝ 🏃🏽‍♀️🏃🏽‍♀️🏃🏽‍♀️

(ለ20ኛ ጊዜ ዲቪ ሞልተህ እንቢ ያለህ ሶዬ እዚህ ኮመንት ስር ገብተህ ማን እንደሀገር እንዳትል ባመዳናለም😜😜)

ውብ ቀን ውብኛ አዋዋል ዋሉልኝማ❤️❤️❤️❤️
እንደው በክፉ አትዩብኝና 😜 ከሙዚቃ ክሊፕ መጨረሻ "ምስጋና ለልዑል አምላክ እግዚአብሄር .... ማዳናለም ጌታ ክርስቶስ ..... " ምን ማለት ነው???

እኔ ሀይማኖተኛ ሆኜ ሳይሆን ግን 'ዘፋኝ መንግስተ ሰማያትን አይወርስም' ያለውን እግዜር ራሱን የዘፈኑ ተባባሪ /ፕሮዲውሰር/ ማድረግ ትንሽ አይዋቀጥም??....

ሰርቆ 'እንዳልያዝ ስለረዳኸኝ አመሰግንሃለሁ' እንደማለት አይደል?? ያው ሁለቱም ሀፅያት ነው ብዬ ነው.....

እንደው ነገሩን ነው... የሆነ ሙዚቃ መጨረሻው ላይ አንብቤው ተዋቅጦብኝ ነው....

ሜዬ ነገር እለፊ ተይ 🏃🏽‍♀️🏃🏽‍♀️🏃🏽‍♀️🏃🏽‍♀️🏃🏽‍♀️🏃🏽‍♀️
ስህተት ልክነት
ልክነት ስህተት

የእኔ ‘የልክነት ጥግ‘ ነው ብዬ ያመንኩበት ‘እውነት‘ ለወዳጄም ‘እውነቱ‘ መሆን አለበት ብዬ ወዳጄን በተሳሳች ሂሳብ መዳኘት ከቂልነቴ ባሻግር የጠበበ የሀሳብ ምህዳሬን ገልቦ አደባባይ ማስጣት ይመስለኛል።

ወዳጄ የቆመበትን ጫማ ‘ስህተት‘ ብዬ ለመዳኘት ለመሆኑ የእኔ ‘ልክ‘ በየትኛው ሚዛንና በማን ዳኝነት ተሰፍሮ ነው ልክነቱ የተረጋገጠው?

አይደለም ለሌላ ሰው ለራሴ እንኳን ‘ልክ ነው‘ ያልኩትን እምነቴን ጊዜ አላንጓለለብኝም? የዛሬ ምናምን ዓመት በፊት የእውነትና የእምነት ጫፍ የመሰለኝ ዛሬ አልተቀየረም? በጠበበም ወይ በሰፋ አስተሳሰቤ 'ልክነቴ'ን አልቀየርኩም?

እንዴት ነው በጊዜ፣ በመረዳቴ መጠን፣ በቦታና በበሽቃጣ የህይወት ክስተቶች እንደማይቀየር ዋስትና በሌለኝ ‘ልክነቴ‘ ወዳጄን በስህተት የምዳኘው?

ሊቀያየር ቢችልም እንደብዙዎች የራሴ አቋምና እምነት አለኝ። እንደራሴ ‘ልክ‘ እና ‘ስህተት‘ የምላቸው ሁነቶች አሉኝ። …… የኔ ‘ስህተት‘ ውስጥ ተዘፍቀህ ሳገኝህ… … ልልህ የሚገባው ‘ይመስለኛል‘ ብቻ መሰለኝ። ምክንያቱ ደግሞ የእኔ ልክ የልክ ጣሪያ ሊሆን አይችልም። የሆነ ቦታ……የሆነ ጊዜ… … ለሆነ ሰው ስህተቱ ሊሆን ይችላል።……

እኔና አንተ አንድ ቦታ ላይ በተለያየ አቅጣጫ ፊታችንን አዙረን ብንቆም የእኔ ቀኝ ያንተ ግራ ነው። …… ያንተ ግራ የኔ ቀኝ ነው። …… ቀኝ ይሄ ነው…… ግራ ይሄ ነው… … ብዬ ብከራከርህ ቂል ነኝ። …… እንዳንተ አቋቋም ያንተ እውነት ይሆናል። …… እንደ እኔ አቋቋም ደግሞ የእኔ እውነት ይሆናል። …… ባንተ እውነት ለማመን ያንተን ጫማ መዋስ አለብኝ።…… የቆምኩበት ሆኜ ለስህተትህ ሒሳብ እየሰራሁ ስዳኝህ እቀሽማለሁ። ………

በየራሳችን እውነትና እምነት መከባበርና እና መዋደድ በአብሮነት ብዙ ያስጉዘናል።

እየሆነ ባለው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ውብ ቀን ውብኛ አዋዋል ዋሉልኝ❤️❤️❤️❤️❤️
በቀደም አንዱ "ሚስቴ አኩርፋኝ ቁርስ ሳትበላ ወደ ስራ ሄደች" ብሎ ዓለም የተደፋበት አስመስሎት ከጠዋት ጀምሮ ያለቃቅሳል::

አንድ ከእኔ የባሰች ተንከሲስ ወዳጅ አለችኝ:: ማወናበድ ሆቢዋ ነው .... ጠቀሰችኝና ጀመረችው ...

"ይገርምሃል እኔ ባሌ የአሸባሪው ደጋፊ ሆኖ ዘመዶቼ ሲያልቁ አሸነፍኩ ብሎ ይጨፍራል:: ማንን ልሁን ?? ... ሀገሪቷ በጦርነት ቀውስ ግራ ገብቷታል... ቤተሰቦቼ የጦርነት ቀጠና ውስጥ ሆነው ስልክ እንኳን አይሰራም... ይሙቱ .. ይቁሰሉ ... በህይወት ይኑሩ አላውቅም... እዚህ ባል ያልኩት የልጆቼ አባት በቤተሰቦቼ ሞት እና ርሃብ ይደሰታል?? ልፍታው?? አብሬው ልኑር?? ከቤተሰቦቼ አንዱ ቢሞት አብሮኝ ያለቅሳል?? እያልኩ አስባለሁ:: ... እና ይገርምሃል ይሄ ሁሉ እየሆነ ስራ ቦታ መጥቼ ምንም ጭንቀት እንደሌለብኝ ፈገግ ብዬ ስራዬን እሰራለሁ:: .... " (ነገሩ የምሯን ነው!! )

የሚስቱን ቁርስ ሳትበላ መሄድ እረስቶት ጭራሽ ለሷ ማዘን ጀመረ 🤣🤪 እንባ እንባ ሁላ አለው:: እንደሀበሻ "ምፅ" ማለት ነበር የቀረው🤣🤪 ከዛ ቀን በኃላ የኢትዮዽያ ዜና አያመልጠውም:: ጭራሽ እጁ ላይ የኛን ባንዲራ (የኢትዮዽያን ባንዲራ) ጌጥ አድርጏል:: አካሄዱን ሳየው ልዝመት ማለቱ አይቀርም ...🤣🤪

እንላከውና "ሰራዊቱን የውጪ አካል እያገዘው ነበር" እናስብላቸው እንዴ??

እንዴት ናችሁልኝ በናታችሁ?? ❤️❤️❤️🤣
አታምጣው ስለው .... አምጥቶ ቆለለው (ርዕስ ነው)

የስልኬ ጥሪ ነው ከእንቅልፌ የቀሰቀሰኝ። ከንጋቱ 12:10

"ከሆስፒታል ነው የምንደውለው!! ዶክተር ፈቃደ እባላለሁ።"

"በየሱስም! እናቴ ምን ሆነች?" ብድግ ብዬ ቁጭ አልኩ:: ማታ ስኳሬ ከፍ ብሏል ስትለኝ ነበር።

"ወይዘሮ ሄለን አበራ አደጋ ገጥሟቸው ...."

"ሄለን አበራ? በስመአብ! (ልቤ ጉሮሮዬጋ ደርሳ ነበር ምልስ ብላ አቃፊዋ ውስጥ ስትገባ ታወቀኝ) ምነው እያጣራችሁ ብትደውሉ? በዚህ ጠዋት ያልታመምኩትን ሴትዮ በድንጋጤ ልትገሉኝ ነው እንዴ? ተሳስታችኋል!! እኔ ሄለን አበራ የምትባል ሴት አላውቅም! "

"ወይዘሮ ፌቨን አዳነ አይደሉም?"

"ነኝ!" አሁን ግራ ገባኝ። ስልኬን ቢሳሳት ስሜን ግን አስተካክሎ ሊጠራ አይችልም።

"የአደጋ ጊዜ ተጠሪ ተብለው የተመዘገቡት እርሶ ኖት!" ከአልጋዬ በደመነፍስ ወረድኩ

"እህ እኔ እንዲህ የምትባል ሴት አላውቅማ? ቆይ የሆነውን አስረዳኝ ምን አይነት ሴት ናት? ምን አይነት አደጋ ነው የገጠማት?"

"የመኪና አደጋ ነው። ለጊዜው conscious አይደለችም:: ቦርሳዋ ውስጥ ባገኘነው መታወቂያ ላይ የእርሶን ስልክና ስም ነው ያገኘነው።"

"እሺ መጣሁ!" አልኩኝ ነገሩ ምንም ስሜት ሳይሰጠኝ ..... አደጋ ደርሶ ነው እየተባልኩ ከዛ በላይ ጥያቄ ማብዛት ክፋት ነገር መሰለኝ። የእኔን ስም የአደጋ ጊዜ ተጠሪ ብሎ ሊመዘግብ የሚችል ዘመድ አሰብኩ ........ ምናልባት በቤት ስሟ የማውቃት ዘመድ ..... ጭንቅላቴ እዚህም እዛም እየረገጠ የተባልኩት ሆስፒታል ደረስኩ እና የተባለውን ዶክተር አገኘሁት። የተባለችው ሴት የተኛችበት ክፍል ወሰደኝ። ሰውነቷ በአብዛኛው በፋሻ ስለተጠቀለለ የማውቃት ሴት እንኳን ብትሆን መለየት አልችልም ነበር።

"የማውቃት አይመስለኝም!" አልኩት ግራ ገባቶኝ። ከጋውን ኪሱ መታወቂያዋን አውጥቶ ሰጠኝ። ሲገለባበጥ ሌላ ምስል ያሳየኝ ይመስል እያገለባበጥኩ አየሁት። በፍፁም አላውቃትም! ስሜና ስልክ ቁጥሬ ግን የመታወቂያው ጀርባ ላይ ቁልጭ ብሎ ተፅፏል። እድሜ 30 .... ቆንጅዬ ወጣት ናት። ፎቶዋ ላይ ጥርሷን ሳትገልጥ ፈገግ ብላለች። በወፋፍረሙ ተገምዶ ደረቷ ላይ የተዘናፈለ ፀጉር አላት ..... በፍፁም አይቻት አላውቅም።

"ማነው ሆስፒታል ያመጣት?" አልኩኝ ትክክለኛ ጥያቄ ይሁን ሳልረዳ

"አደጋ ያደረሰባት ሰው ነው ይዟት የመጣው። መጠበቂያ ክፍል ተቀምጧል ልታገኚው ከፈለግሽ? " ብሎ መልሴን ሳይጠብቅ በሩን ከፍቶ ወጣ ተከተልኩት የተባለው ሰው ከዶክተሩ ጋር ወደክፍሉ ስገባ ሲያየኝ ዘሎ ከመቀመጫው ተነሳ ..... አጠገቡ ተቀምጦ የነበረ በግምት የ4 ዓመት የሚሆን ህፃንም ተከትሎት ብድግ አለ።

"ቤተሰቧ ነሽ? ምን ማድረግ እንደነበረብኝ አላወቅኩም ነበር! እጄን ለፖሊስ ልስጥ? እሰጣለሁ በቃ! (መላ አካሉ ይንቀጠቀጣል።) ከየት መጣች ሳልላት ነው ዘው ብላ የገባችብኝ በቦታው የነበረ ሰውም አልነበረም። አልነጋምኮ .... የሞተች መስሎኝ ነበር !" ድንጋጤው እንዳለ ነው የለበሰው ጥቁር ሱፍና ነጭ ሸሚዝ በደም እንደተነከረ ነው። እጆቹ ላይ የቀረውን የደረቀ ደም ሊጠርገው ግድ ያለው አይመስልም ወይም ከነጭራሹ ደም እጁ ላይ መኖሩንም አላስተዋለውም። ግራ ገባኝ። ምንም በማላውቀው ክስተት ውስጥ የተነከርኩት እኔ ምን ልበል? አይኖቼ ህፃኑ ላይ መንቀዋለላቸውን ሲያይ

"ልጇ ነው። አብረው ነበሩ። እማ ብሎ ሲጮህ ነው ያየሁት እኔ እንጃ ምን እንደተፈጠረ። እሱ የእግረኛ መንገድ ላይ ነበረ። ቤተክርስቲያን እየሄዱ መሰለኝ ነጠላ ለብሳ ነበር። .... ቤተክርስትያን ለመሄድ ራሱ በቅጡ አልነጋም ነበር:: "

ምን እንደማደርግ ሳላውቅ ህፃኑጋ ተጠግቼ በርከክ አልኩ። ደነበረ። ትንንሽ እጆቹን ልይዛቸው እጄን ስዘረጋ ሰበሰባቸው።

"ስምህ ማነው?" አልኩት እናቱን መኪና ሲገጫት በአይኑ ካየ ሁለት ሰዓት ላልሞላው ህፃን የእኔ ጥያቄ ምኑ ነው? እኔስ ምኑ ነኝ? ዓለምስ ራሱ ምኑ ናት?

"ባባ" አለኝ የደረቁ ከንፈሮቹን እያላቀቀ

"ባባዬ እኔን ታውቀኛለህ?" አልኩት የማይጠየቅ ጥያቄ እንደሆነ እያወቅኩ። በአሉታ ጭንቅላቱን ነቀነቀ።

"አባትህ የት እንደሆነ ታውቃለህ?" አሁንም በአሉታ ጭንቅላቱን ነቀነቀ። ግራ ገባኝ! ይህቺ ሴት ማናት? ለምንስ ነው የማላውቃት ሴት መታወቂያ ላይ የእኔ ስም የሰፈፈረው?

"ዶክተር እሷ ያለችበትን ሁኔታ ንገረኝ? ትድናለች አይደል? " እንድከተለው ምልክት ሰጥቶኝ ወደ ቢሮ ይዞኝ ሄደ። ያለችበት ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ ለመገመት አልተቸገርኩም።

"ተጨማሪ ምርመራዎች አዝዣለሁ። ውጤቶቹ እስኪመጡ እርግጠኛ የሆነ ምላሽ ልሰጥሽ አልችልም። ጭንቅላቷ በሃይል ተጋጭቷል። እንዳልኩሽ ሁሉም ውጤት ሳይመጣ ብዙም ማለት አልችልም።"

"የምትድን ይመስልሃል ግን? የምትነቃ ይመስልሃል?"

"ይቅርታ ይሄን አሁን መናገር አልችልም።"

"እሺ እኔ ምን ላድርግ? አላውቃትምኮ? ህፃኑንስ ምን ላድርገው? ምን ጉድ ውስጥ ነው የገባሁት?"

"የማታውቂያት ከሆነ ሆስፒታሉ ለፖሊስ የማሳወቅ ግዴታ አለበት" አለኝ። አላውቃትም ያልኩትን ግን ያመነኝ አይመስልም።

"እሺ የገጫትስ ሰውዬ?"

"ቤተሰብ ቢገኝ ወይ በሽምግልና ያልቃል ወይ ይከሱታል። እንደምትዪው የማታውቂያት ከሆነ ጉዳዩን ለፖሊስ ማሳወቅ ግዴታችን ነው። ሰውየው የማምለጥ ሀሳብ የለውም። ሲገጫት ማንም አላየውም ጥሎ መሄድ ይችል ነበር። ይልቅስ ያላነሰ ብር ከፍሎ የግል ሆስፒታል ሊያሳክማት ፈቃደኛ ከሆነ በህግ ይዳኝ በሽምግልና ቤተሰብ ነው የሚወስነው።"

ሁሉንም ጥዬ መሄድ ፈለግኩ። ምን አገባኝ እና ነው እዚህ ጣጣ ውስጥ የምገባው ብዬ ..... ወደመጠበቂያው ክፍል ስመለስ ህፃኑ የምስራች የምነግረው ይመስል ከተቀመጠበት ዘሎ ተነስቶ በተስፋ አይን አይኖቼን ሲያየኝ እግሬ የሚቀጥለውን እርምጃ መራመድ አቃተው:: አጠገቤ ደርሶ ትንሽዬ ፊቱን ወደ ላይ አንጋጦ እያየኝ ሊያለቅስ ጉንጩ እየተንቀጠቀጠ

"እማዬስ?" አለኝ:: እንባው ከፊደሎቹጋ ከአይኑ እየወረደ..... ከሱ ብሼ እንደህፃን ማልቀስ አማረኝ:: አቅፌ ብድግ እያደረግኩት በዛች ቅፅበት አብሬው እማገዳለሁ እንጂ እሳት ውስጥ ጥዬው እንደማልሄድ አወቅኩ። ...

ይቀጥላል ........

እንዴት ናችሁልኝ ግን እናንተ? ❤️❤️❤️❤️
አታምጣው ስለው አምጥቶ ቆለለው #2

"የገጨሃት ቦታ ውሰደኝ ምናልባት ሰፈሯ ሊሆን ይችላል። ምናልባት ስልኳን እዛ ጥላው ሊሆን ይችላል። የሚያውቃት ሰው ሊኖር ይችላል!"

በውስጤ ምናልባት ጎዳና ላይ ቢሆንስ የምትኖረው ብዬ አስቤያለሁ ጮክ ብዬ አላወራሁትም እንጂ ምናልባት ከነአካቴው ስልክም አልነበራት ይሆናል። መታወቂያዋ ላይ ያለውን ቀበሌና የቤት ቁጥር ተከትዬ ቀበሌ ሄጄ ቤቷን ፍለጋ አስቤዋለሁ። ቀላል እንደማይሆን ግልፅ ነው። ቀበሌ አልወድም!!

"በፍፁም እኔ አልነዳም። ህም ...በጭራሽ መሪ አልይዝም። ታክሲ .....ራይድ ይጠራ" ሲል አሳዘነኝ ማንም ትኩረት ሰጥቶ እሱን ያየው የለም እንጂ እሱም ከባድ ድንጋጤ ላይ ነው። አሁንም እጆቹ እየተንቀጠቀጡ ነው። ሲያወራ መሸሻ ያጣ አይነት ዓይኖቹ መሬቱን ይምሳሉ። ይሄን እያለኝ ድርብብ ያሉ የሴት ወይዘሮ የሚያነክስ እግራቸውን በጌጠኛ ከዘራ እያገዙ የሚራመዱ ሰውዬ አስከትለው ወደ ክፍሉ ገቡ።

"ኪያዬ ......ደስ አላለኝም ! በለሊት አትጓዝ እያልኩህ ...." እያሉ እያገላበጡ ሲስሙት እና ደህና መሆኑን ሲያረጋግጡ ልጃቸው ተገጭቶ እንጂ እሱ ገጭቶ አይመስልም። እሱም እናቱን ሲያይ የሆነው የልጅ መሆን ካቀፍኩት ህፃን አይለይም ነበር። በኋላ እሱም ገብቶት ነው መሰለኝ ከእናቱ እቅፍ ወጥቶ በማፈር ሲያየኝ ነው ገና ሰው እንኳን መኖሩን እናትየው ያዩት።

"እባክሽ ልጄ አንድ ልጄ ነው በሽምግልና እንጨርሰው? (ባጌጠ ልብሳቸው እግሬ ስር ሲንበረከኩ ክብራቸው አላሳሰባቸውም። እናት ናቸዋ! ደንግጬ ደነዘዝኩ። ካሰብኩት በላይ ውጥንቅጥ ውስጥ እንደተዘፈቅኩ ገባኝ። ከተንበረከኩበት ላነሳቸው እየሞከርኩ ከአፌ ግን ቃል አይወጣልኝም።) ካሱ የምንባለውን እንክሳለን። እናትየው እስኪሻላት ህፃኑንም ቢሆን ወስጄ እንከባከባለሁ። እባክሽ ልጄን አሳልፈሽ አትስጪብኝ?"

ለደቂቃ ህፃኑን ሰጥቻቸው ጭልጥ ብዬ መጥፋት ሁሉ አሰብኩ። ባባ ቀልቡ የነገረው ይመስል ጭምቅ አድርጎ አቀፈኝ። የተገጨችው እህቴ ብትሆን ምንድነበር የምወስነው? ብትሞት የእነሱ ካሳ የህይወት ካሳ ይሆናል? እሺ ጥፋቱ የሷስ ቢሆን? እንዳለው እሷ ብትሆንስ ዘው ብላ የገባችበት? ኸረ ምን አይነቷ ሴት ናት ግን እዚህ ጣጣ ውስጥ ዘፍቃኝ ማን እንደሆነች እንኳን የማላውቃት

"እባኮትን ይነሱ። እኔ ለራሴ ዞሮብኛል።"

የተፈጠረውን አስረዳኋቸው። አባትየው መታወቂያው ላይ ባለው አድራሻ ቤቱን ሊያፈላልጉ ሀላፊነት ወሰዱልኝ። ማን እንደሆነች እና ከእኔጋር የሚያዛምዳትን ነገር እስክደርስበት ባባ እኔጋ እንዲቆይ ወሰንኩ። እነርሱም የሚያስፈልገውን ሊያሟሉለት እና ሊጠይቁት ቃል ገቡልኝ። አንድ ላይ በእነርሱ መኪና እናትየው እየነዱ አደጋው የደረሰበት ቦታ ሄድን:: ምንም ነገር የለም። ከአልፎ አልፎ ሂያጅ መንገደኛ ውጪ በአካባቢው ማንም አይታይም። የመኖሪያ ሰፈርም አይደለም። ዓይኔ መሬቱ ላይ ካለ አንድ ብር ሳንቲም ላይ አረፈ። ደም ነክቶታል። ለምን እንዳነሳሁት አላውቅም ግን አነሳሁት። የሷ ይሆን? በእጇ ይዛው ነበር? ወድቆባት ልታነሳ ስትል ይሆን መኪናውን ያላየችው? ወይስ ሌላ ሰው የጣለው ሳንቲም ነው? ስልኬ ሲጠራ ባላወቅኩት ምክንያት ደንግጬ ዘለልኩ

"አይዞሽ አይዞሽ" አሉኝ እናትየው መደንበሬን ሲያዩ

"እማ በጠዋት የት ሄደሽ ነው? " ልጄ ናት። ቤቴን ረስቼዋለሁ። ሰዓቱን ረስቼዋለሁ። ዛሬ ቅዳሜ መሆኑንም እረስቼዋለሁ።

"መጣሁ እናቴ! ለባብሰሽ ጠብቂኝ" አልኳት ቅዳሜ ጠዋት ሁል ጊዜ እናትና አባቴ ጋር ነው ቁርስ የምንበላው።

እነርሱ ስልክ ተቀያይረን እቤት አድርሰውኝ ተመለሱ። የማልዋሸው በዛው ቢጠፉስ ብዬ አስቤያለሁ። ሰው ለማመን ቅርብ አይደለሁም። የመኪና ታርጋቸውን መዝግቤ መታወቂያቸውን ፎቶ ኮፒ አደረግኩ።

"እማ ትልቅ ሰው የሚበላውን ምግብ ይበላል ኸረ ጥርስኮ አለው" ትለኛለች ልጄ ለባባ ምግብ ምን ልስጠው ብዬ ስባዝን እየሳቀችብኝ። ልጄ 15 ዓመቷ ነው። በስንት ዓመቷ ምን እንደበላች ጠፍቶኛል። ለመጨረሻ ጊዜ ገላዋን መች እንዳጠብኳት ረስቼዋለሁ ..... ባባን አጣጥቤ እነእማዬጋ ተያይዘን ሄድን::

"እግዚአብሄር የሆነ ነገር ሊያስተምርሽ ነው ይሄን ህፃን ወደ ህይወትሽ ያመጣው" አለችኝ እናቴ የሆነውን ሁሉ ከነገርኳቸው በኋላ። ከቤተሰቡ አንድ ሰው እንኳን ድንገት ቢያውቃት ብዬ አስቤ ነበር:: ማንም አያውቃትም። (እናቴ ምን ማለቷ እንደሆነ አውቃለሁ። ማግባት አለብሽ ልጅ መድገም አለብሽ ነው ቅኔው። ወንድሜ በሚያስቀና ትዳር ሶስተኛ ልጁን ሰልሷል። የእኔ ያለባል መቅረት ያሳስባታል:: )

"እማ ደግሞ እግዚአብሄር እኔን ስለሚወደኝ እኔን ለማስተማር ይሄን ህፃን አይቀጣም! የሆነችን ሴት በመኪና አስገጭቶ ለኔ ትምህርት አይሰጥም። እነርሱምኮ ፍጡሮቹ ናቸው እኔን ለማስተማር ህይወታቸውን የሚያዘባርቅባቸው አሻንጉሊቶች አይደሉም!!" አልኳት። ወንድሜና አባቴ ተያይተው ጨዋታውን ቀየሩት። ከእማዬጋ እንዲህ አይነት ወሬ ከጀመርን ማባሪያ የሌለው ጭቅጭቅ እንደሆነ ያውቃሉ:: እዛው ቤተሰቦቼ ቤት ሆኜ ወደ ከሰዓት ስልኬ ጠራ ባባ ኩርምት ብሎ ከተኛ ሰዓታት አልፈውታል።

"አብርሃም ነኝ"

"አብረሃም? አብረሃም?"

"የግሩም አባት! ልጅቷን የገጫት ልጅ አባት... "
"እእ ....እሺ "

"የምትኖርበትን ቤት አግኝተነዋል። አከራዮችዋን አናግረን የእሷ ቤት መሆኑን አረጋግጠናል።"

"በዚህ ፍጥነት? እንዴት? ያውም በቅዳሜ?"

"ብዙም አስቸጋሪ አልነበረም:: የቤት ቁጥሩ የአከራዮችዋ ቤት ነው:: ደግሞስ የልጄ ጉዳይ አይደል? ይልቅ መምጣት ሳይኖርብሽ አይቀርም። ከባሏ ውጪ ማንም ዘመድም ሆነ የቅርብ ሰው እንደሌላት ነው የነገሩን።"

"ታዲያ ባሏ እያለ እኔን ምን ቤት ናት ብላ ነው የፃፈችኝ?"

"ባሏ ከታሰረ ሁለት ዓመት አልፎታል።"

"እሺ እኔ ምን ቤት ነኝ መታወቂያዋ ላይ የተገኘሁት? ወይ ፈጣሪ ! "

"እኔ ምን አውቄው ብለሽ? (እኔ አልፃፍኩሽ የሚል አንድምታ ባለው ለዛ) ምናልባት በባለቤትዋ? እስር ቤት ያለ የቅርብ ሰው ወይ ዘመድ የለሽም?"

"በፍፁም ኸረ እኔ ጭራሽ የታሰረ የሩቅም ሰው አላውቅም። "

"ምናልባት አከራዮችዋ ከሚነግሩሽ ነገር ፍንጭ ልታገኚ ስለምትችዪ ብትመጪ መልካም ይመስለኛል:: ብዙ አመት ኖራለች አብራቸው.... እ.... ባለቤቷ ... አሸናፊ ይባላል ነው ያሉኝ .......እንደው ካወቅሽው "

ከጀርባዬ የሆነ ነገር ማጅራቴን በሀይል የደለቀኝ ነገር መሰለኝ .........ጭው አለብኝ። አይሆንም። እሱማ አይሆንም! ሊሆን አይችልም።... ስም ተመሳስሎ ነው.... ማሰብ ተሳነኝ!!

"ምነው ሴትየዋ ሞተች እንዴ?" ትለኛለች የወንድሜ ሚስት ......

ይቀጥላላ ምን ታፐጣላችሁ??? 🤷🏽‍♀️🤷🏽‍♀️🤷🏽‍♀️🤷🏽‍♀️
አታምጣው ስለው አምጥቶ ቆለለው #3

የእኔ አሸናፊ ሊሆን አይችልም! እሱ እንዲህ ሊደፍረኝ ድፍረቱ ሊኖረው አይችልም። የእኔ አሸናፊ ቢሆን ደግሞስ ለሚስቱ ማናት ብሎ ነው የሚነግራት? ምንስ ቢላት ደግሞ የአደጋ ጊዜ ተጠሪዋ አድርጋ ትፅፈኛለች? መቼም እህቴ ናት አይላትም ዘንድሮ ወንዱ ብሶበታል እናቴ ናትስ ብሏት ቢሆን? ወይ አክስቴ ………. አይሆንም እንዲሁ ራሴን ሳስጨንቅ ነው። አሸናፊ የሚባል ሀበሻ አሸን አይደል?

ለማንም ምንም ሳልተነፍስ ልጄንና ባባን እነእማዬጋ ትቼ ቦታው ደረስኩ። ለእነእማዬ ስሙን ብጠራባቸው ቄስ ጠርተው ነው እንዳልሄድ የሚያስገዝቱኝ። ልቤ ሲደልቅ በለበስኩት ሹራብ ላይ ይታያል። ሰዎቹን ምን እንደምጠይቃቸው አላውቅም። ብቻ መልሳቸው የእኔ አሸናፊ አለመሆኑን እንዲያረጋግጥልኝ አምላኬን እለምናለሁ። አብረሃምና ግሩም ሰዎቹ ቤት ተቀምጠው እየጠበቁኝ ነበር። አከራዮቹ ስገባ አስቀድመው ተነግሯቸው ስለነበር እንደሚያውቀኝ ሰው ሰላም አሉኝ። ‘ፈስ ያለበት’ ሆኖ ያውቁኝ ይሆን እንዴ ? ብዬ አሰብኩ።

“ይኸው እኛ ቤት መኖር ከጀመሩ አስራ ሁለት ዓመታቸው ነው። መጥቶ የሚጠይቃቸው ቋሚ ጓደኛ እንኳን የላቸውም እንኳን ቤተሰብ። ሁለቱም ቤተሰቦቻቸውን አያውቋቸውም። ምንድነው ስሙ ጠፋብኝ ……. ሁሌ ያወሩት ነበር ….. የሆነ የህፃናት ማሳደጊያ ነው አብረው ያደጉት።”

የውስጥ እጄን አላበኝ። አሸናፊ ማሳደጊያ ነው ያደገው:: ከዚህ በላይ እስኪነግሩኝ መጠበቅ ራሴን ማሰቃየት መሰለኝ።

"የአባቱን ስም ያውቁታል? አሸናፊ ማነው የሚባለው?"

"ማን ነበር አንቺዬ ? አሸናፊ ......" ብለው ሊያስታውሱ ሲታገሉ አባወራው ቀለብ አድርገው "አሸናፊ ታዬ ነው። እርግጠኛ ነኝ።"አሉ።

አፌ ውስጥ ሞልቶ የነበረው ምራቅ ደረቀ። ፀጥ አልኩ። የሰማሁትን እርስ በርሱ ሳጋባው ጭንቅላቴ ውስጥ ወዲያ ማዶ እጅግ ርቆ የተቀበረ ስም ትዝ አለኝ ሄለን!!

"ታናሽ እህቴ በያት! አብረን ስላደግን ሳናወራ እንግባባለን። በዚህ ምድር ላይ እንደርሷ የሚያውቀኝ ሰው የለም ነበር ያለኝ" ያኔ።

ራሷ ናት! አረብ ሀገር ነበረች ያኔ! በጠና ታማ ወደሀገር ቤት ስትመለስ ክንፏ እንደተሰበረች ወፍ እየተጥመለመለ በእንባ ሲነግረኝ አባዬን "ቤት ልገዛ ብር አንሶኝ ነው" ብዬ ዋሽቼ ብር ተቀብዬ ሰጥቼዋለሁ። ለአብሮ አደግ እህቱ ማን ያውቃል እኔንም ታላቅ እህቴ በያት ብሎ ይሆናል የነገራት። ምናለ ብትነቃ እና በጠየቅኳት

"ታውቂዋለሽ?" አለ ግሩም የፈሰሰ ፊቴን አይቶ

"መሰለኝ። አሸናፊ ታዬ የሚባል ሰው ከረዥም ጊዜ በፊት አውቃለሁ። የሚስቱ መታወቂያ ላይ ስሜን የሚያፅፍ አይነት መተዋወቅ አይደለም እንጂ ...."

"ምናልባት ቁልፍ ካላችሁ እቤታቸው የፎቶ አልበም አይጠፋ ይሆናል። እዛው እናንተ በቆማችሁበት ማየት ብንችል?" አለ አብርሃም

"የታሰረበትን እስር ቤት ታውቁታላችሁ?" ጭንቅላቴ ውስጥ ያሰብኩት ጥያቄ አይደለም። እኔም ከአፌ ሲወጣ ነው የሰማሁት። ብቻ ዓይኔን እያየ እንዲነግረኝ የምፈልገው ብዙ ነገር ነበረ

"እዚህ እያለ እንጠይቀው ነበር። ከ6 ወር በፊት ወደ ሸዋሮቢት ተዛውሯል። ከዛ በኋላ ጠይቀነውም አናውቅ። እሷም እግር ስናበዛ ደስ አይላትም።" አሉ ሰውየው የሆነ ቅሬታ ባለው ድምፅ

"የታሰረበትን ምክንያት ያውቁታል?" አልኩኝ መልሱ ምን እንደሚሰራልኝ ሳላውቅ

"ምኑን አውቀነው። ሚስጥር ነው እናቴ! እንድናውቅ አልፈለጉም። ሁለቱም እንደልጆቻችን ነበሩ። እሱ ከታሰረ በኋላ እሷ ጭራሽ ሌላ ሰው ሆነች። አንድ ጊቢ ሆነን የማንገጣጠም ሆንን" አሉ ሴትየዋ

"እንግዲህ ካላችሁ ቤቱን ልክፈትላችኋ!" አሉ ሰውየው ወሬውን መቀየር የፈለጉ ይመስላሉ።

እግሬ መቆም የሚችል ሁሉ አልመስልሽ አለኝ። አሁንም እሱ ባልሆነ እላለሁ ደጋግሜ

"ይቅርታ እኔ እዚህ ልቆይ እናንተ አልበም ካገኛችሁ አምጡልኝ እቤት አልግባ?" አልኩኝ ልምምጥ በሚመስል። የቤቱ አባወራ እና አብርሃም ሲሄዱ ግሩም አጠገቤ መጥቶ

"ይቅርታ በጥሩ የምታስታውሺው ሰው አይደለም መሰለኝ" አለኝ

"በጭራሽ!" ለጥሩ የቀረበ ምናምኒት ትዝታ እንኳን የለኝም። ..... ያልገባኝ ስሜን እንኳን ለማውሳት የሚያስችል ድፍረት እንዴት እንደኖረው ነው። እፍ እፍ ብሎ ቀብሮኝ የሄደ ሰው ነው:: " አልኩት ልክ ዛሬ የሆነ ይመስል እያርገፈገፈኝ። ለማያውቀኝ ሰው የማይነገር ስሜት እያወራሁ እንደሆነ ሲገባኝ

"ይቅርታ የማይባል አልኩ!" አልኩት መልሼ

"በፍፁም የማይባል አላልሽም። ማውራት ከፈለግሽ ጥሩ ሰሚ ነኝ::" አለኝ ትከሻዬን በአይዞኝ ደለቅ ደለቅ እያደረገ

"ማውራትስ የሚሆንልኝ ሰው አይደለሁም።" አልኩት። እነአብርሃም አንድ ያረጀ የፎቶ አልበም ይዘው ብቅ አሉ። ልቤ እሱ መሆኑን እያወቀ። ፎቶው ላይ ያለው ሰው ሌላ ሰው ቢሆን እላለሁ። እጄን ለመዘርጋት አልታዘዝልሽ እንዳለኝ ገብቶት ነው መሰለኝ ግሩም አልበሙን ተቀበላቸው። እንደማራገፍ ካደረገው በኋላ

"ዝግጁ ነሽ?" አለኝ ለመክፈት እጁን አዘጋጅቶ በጭንቅላቴ አይደለሁምና ነውን እንዳምታተሁ እየገባኝ። ወደላይም ወደጎንም ጭንቅላቴን ወዘወዝኩት። ገለጠው። ....... ራሱ ነው።

ትቶኝ ሲሄድ በአካል ሊነግረኝ እንኳን ያላከበረኝ አሸናፊ። ..... በብጣሽ ወረቀት እንደተወኝ : አብረን የገነባነውን ዓለም የኔ ዓለም አይደለም ያለኝ ..... አሸናፊ ! ትቶኝ ለመሄዱ ምክንያት እኔ ልጅ መውለዱን እናዘግየው ማለቴ መሆኑን አሳምኖኝ በፀፀት ያነደደኝ አሸናፊ ...... በብጣሽ ወረቀት የሶስት ዓመት ፍቅራችንን ....... ሙሽራዬ ተብዬ ደስታ እና ወዙ ሳይደበዝዝ የዓመት ትዳራችንን ....... እንደ ብናኝ ብትንንንን ያደረገው አሸናፊ !! ከሀገር ወጥቻለሁ አትፈልጊኝ ነበር ያለኝ። ...... ፎቶዎቹ ላይ ደስተኛ ይመስላሉ። ሰው እንዴት እንዲህ ክፉ ይሆናል? ሰው እንዴት እንዲህ ያለ ቅጥፈት ይቀጥፋል? እኔን ባይወደኝ ለእኔ ባያስብ ሰው የዘራውን እንደሚያጭድ እንዴት ነገውን አልፈራም? ትቶኝ መሄዱ ሳያንሰው ለትዳራችን መፍረስ ምክንያቷ እኔ መሆኔን አምኜ እንድተክን እንዴት ይፈርድብኛል?

"ሸዋሮቢት እሄዳለሁ!" አልኩኝ ሳላስበው። ማንም ምንም ሳይል ደቂቃ ከቆዩ በኃላ

"ዛሬ መሽቷል። ነገም ሰንበት ነው። ሰኞ በጠዋት እኔ አደርስሻለሁ ከፈለግሽ። እስከእዛ ድረስ ደግሞ ምን እንደሚፈጠር አይታወቅም። እናትየው ትነቃም ይሆናል።" አለኝ አብርሃም። እየሆነ ያለው ነገር ምን እንደሆነ ባያውቅም ሲኦል ነክ ነገር መሆኑ ሳይገለጥለት አልቀረም። ህመሜ እንደአዲስ ልቤን ሲሰቅዘኝ ታወቀኝ ልክ እንደያኔው ትቶኝ እንደሄደ ጊዜ ....... መንገር አፍሬ ብቻዬን ለወራት እንደቆሰልኩት ለማንም አገኘሁት ሳልል መታመምን በወደድኩ ......

"እቤትሽ እናድርስሽ?" አለ ግሩም መደንዘዜ ገብቶት። ያላለቀውን አልበም እየገጠመው። የእነእማዬ ቤት አቅጣጫ በየት መሆኑን ከማመልከት ውጪ ቃል ሳልተነፍስ እነእማዬጋ ደረስኩ። ባባ ከእንቅልፉ ነቅቶ ከጠዋቱ በተሻለ ነቃ ብሎ ከወንድሜ ልጆችጋ እየተጫወተ ነበር።
መጥፎ ሴት አይደለሁም። ግን ደግሞ መልዓክም አይደለሁም። የአሸናፊን ልጅ ልንከባከብ? ራሴን ፈራሁት። እኔ እኮ በእርሱ ምክንያት ማንንም የማላምን ደንባራ ሴት ሆኛለሁ። ሙሽራዋ ከአንድ ዓመት በላይ አብሯት ለመዝለቅ ያልፈለጋት ምንም የሆነች ዓይነት ሴት እንደሆንኩ እየተሰማኝ ታምሜያለሁ። እኔኮ በእርሱ ምክንያት ፍቅርንም ሰው ማመንንም ሰው መቅረብንም አጠገቤ እንዳይደርሱ አርቄ ቀብሬያቸዋለሁ። የእርሱን ልጅ ላሳድግ? እናቱ አይበለውና ብትሞት እናቱ እሆናለሁ? ራሴን ፈራሁት ......

"እማዬስ?" አለኝ ባባ ሳሎን ገብቼ የደነዘዘ ሰውነቴን ሶፋው ላይ እንደጣልኩት። 'እናትህማ እኔን ፍም ላይ ማግዳኝ ሆስፒታል ተኝታለች' ብለው ደስ ባለኝ።

"ምነው እማ? ምን ሆንሽ?" አለችኝ ልጄ ተከትላ ..... እንደአዲስ ክው ብዬ ደነገጥኩ .... ምንድነው የምላት???

ምንም ከማለቴ በፊት ባባ

"እማዬጋ ውሰጂኝ!" ብሎ እሪታውን አቀለጠው።

ይቀጥላል። ...........
አታምጣው ስለው አምጥቶ ቆለለው #4

ልነግረው ነበር እኮ ደስታ አቅሌን አስቶኝ እቤት የደረስኩት። "አርግዣለሁ እኮ" ልለው።

"ቤት ፣መኪና ፣ የተሻለ ስራ ...... ምናባቱ! አንተን ሙሉ የሚያደርግህ ልጅ መውለድ ከሆነ ሁሉንም ትቼዋለሁ።"ልለው ነበር እቤት ስደርስ

"የእኔ እቅድ አንተን ካስከፋብኝ ባላቅድስ ያንተን ፍላጎት ልኑርልህ" ልለው ነበር። ከመፈንጠዙ የተነሳ ምድር ትጠበዋለች ብዬ እያሰብኩ ከሀኪም ቤት እንደህፃን ዝግዛግ እየረገጥኩ መደነስ እየቃጣኝ እቤት የደረስኩት። እሱ አልነበረም! ብጣሽ ወረቀት አስቀምጦልኝ ሄዷል።

እስከዛች ቀን ድረስ የዓለምን ክፋት በመልካምነት መብለጥ እችላለሁ ብዬ የማምን ጅል ነበርኩ። ከሰዎች ውስጥ ጥሩነታቸውን ለማድመቅ የምጋጋጥ .... ለክፋታቸው ምክንያት እየፈለግኩ ይቅር ማለት የምችል ጀለገግ ነበርኩ። የማንም ክፋት እንዳይሰብረኝ ሆኜ በእድሜዬ በስያለሁ ብዬ የማምን ገልቱ !!! .... ክፋት በምሳሳለት ሰው ተመስሎ ሲመጣ ተሰብስቤ እንዳልገጣጠም ሆኜ ተሰባበርኩ እንጂ.... ለሰዓታት ቁጭ ብዬ እየደጋገምኩ ወረቀቱን አነበብኩት።

"ፌቪዬ አንቺ ቤተሰብ መመስረት እንዳያጓጓሽ በሚወዱሽ ቤተሰቦች ተከበሽ ነው ያደግሽው። መጉደልን አታውቂውም! እኔ የሌለኝን አባት ለልጄ መሆን እፈልጋለሁ። በህይወቴ የተመኘሁት ብቸኛ ነገር የራሴን ቤተሰብ መመስረት እንጂ ቤት መገንባት ወይም ሀብት ማጠራቀም አልነበረም። እንድትረጂኝ አልጠብቅም! አንቺ የተመቻቸ ህይወትም ቤተሰብም ኖሮሽ ስላደግሽ የተመቻቸ ህይወት ሳይኖረን መውለድ አትፈልጊም። ላስጨንቅሽ አልፈልግም! ደስተኛ እንደሆንኩ እያስመሰልኩ አብሬሽ መሆኑንም አልፈልግም። በራሴ ምክንያት በትዳራችን ደስተኛ አይደለሁምና ከሀገር ለመውጣት ወስኜ ፕሮሰሱን ጨርሻለሁ። እንዳትፈልጊኝ። ደስተኛ ሁኚ!

በቃ! በዝህች ሙንጭርጭር ነው 'ደስተኛ ሁኚ' ብሎ ተሳልቆ ደስታዬን ይዞት እብስ ያለው። እያንዳንዱን ዓረፍተነገር እየደጋገምኩ አመነዥካለሁ። ስለልጅ ያወራነውኮ ሁለቴ ነበር። 'ለልጃችን የተስተካከለ ህይወት አበጅተንለት ብናመጣው አይሻልም?' ነበር ያልኩትኮ።

ከመረዳት አልፌ እነማዬጋ ስንሄድ በዝምታ ስለሚያሳልፍ ይከፋው ይሆናል ፣ጉድለቱን ያስታውሰው ይሆናል ብዬ እነማዬን ላለማየት ሰበብ የምደረድር ሰው ነበርኩኮ። ትቶኝ ቢሄድ እንኳን ቢያንስ በአካል ቢነግረኝ ምን ነበረበት? ከእቅዴና ከፍቅራችን የቱ እንደሚበልጥብኝ ለመረዳት እድሉን እንዴት አይሰጠኝም?? ሰዓታት? ሰዓታት ታግሶኝ ቢሆን "ልጃችንን በሆዴ ይዣለሁ!" ልለው አልነበር?

ሁሉም ክስተት እንደአዲስ ውስጤ እየተገላበጠ ያምሰኝ ገባ! የወረቀቱ ሻካራነት እንኳን ጣቶቼ ላይ ይሰማኛል። በእንባዬ የተኮማተሩት ፊደላት .... ደብዳቤው የነበረበት ጠረጴዛ ..... እኔ የተቀመጥኩበት ረዥም ወንበር ...... ቀን ላይ ተሰርቶ የበላነው የነበረው ሳሎኑን ያፈነው የቀይወጥ ሽታ ....... ልክ እንደአሁን ይንጠኝ ጀመር። ረዥም ሳግ የቀላቀለው ትንፋሽ ተፈስኩ።

ወደ ሸዋሮቢት እየሄድን ነው። ከግሩም እና ከአባቱ ጋር ። ሳገኘው ምን እንደሚሰማኝ ማሰብ አልፈልግም። ትቶኝ የሄደበት ምክንያት ልጅ ያለመሆኑን ብቻ ነግሮኝ ራሴን ይቅር እንድለው ነው ጥድፊያዬ። ዓመታቱን እጎነጉናለሁ። ከመታሰሩ በፊት 10 ዓመት አብሯት ኖሯል። ልጅ የወለዱት ምናልባት ከ8 ዓመት በኋላ ነው። ፎቷቸው ያስታውቃል ደስተኛ ነበረ። ከሀገር ወጥቻለሁ ያለኝም ጭራሽ ውሸቱን ይሆናል አይደል? እንዳልወደደኝ ማወቅ ወይም ምክንያቱ ልጅ እንዳልነበር ማወቅ የቱ የበለጠ እንደሚሳምም ማመዛዘን አልቻልኩም።

ለማንም ምንም አልተናገርኩም። ሰኞ እስኪደርስ እንዳልፈነዳ ስፈራ ነበር ሰኞ የነጋልኝ። የዛን ቀን እነእማዬጋ ካደርኩ ጥያቄያቸውን ስለማልችለው ባባንና ልጄን ይዤ ወደቤቴ ተመለስኩ። ልጄ በእኔ ፈንታ አባብላ ዝም ባታስብልልኝ በነበርኩበት ሁኔታ ባባን ማረጋጋት ፈታኝ ነበር። እሁድ ቀን ወደሆስፒታል የሄድኩት ጥያቄዎቼን እንድትመልስልኝ ይሁን ወይም በጥሩነት እንድትድን ፈልጌ ይሁን ሳላውቅ ነው። እሷ እቴ! የትናንት ህመሜን ፣ ስድስት ማትሪክ የሚወጣቸው ዳሽ ሙላ ጥያቄዎች እና ባባን አስታቅፋኝ ....... ለሽሽሽ ብላለች።

ልጄ ለወትሮ ክፍሏ ከገባች ብጠራት የማትሰማኝ ከስር ከስሬ እያለች

"እማ ምንድነው የሆንሽው? እንደዚህኮ ሆነሽ አታውቂም ምንድነው?" ትለኛለች።

"ምንም አልሆንኩም!" እላታለሁ እየደጋገምኩ። ምልስ ብላ ያበረታችኝ መስሏት

"ባባ አሳስቦሽ ነው? አንቺ እንኳን ለአንድ ልጅ ለአንድ መዋዕለ ህፃናት ልጆችኮ እናት መሆን የምትችዪ ምርጥዬ እናት ነሽ!" ስትለኝ ሲንቀለቀል ዓይኔን የሞላውን እንባዬን እንዳታየው ዘልዬ ወደመታጠቢያ ቤት ገባሁ።

እንዴት ነው አይደለምኮ አባትሽን አገኘሁት!! ባባ ወንድምሽ ነውስ የምላት? ለእኔ ለትልቋ ሴት መሸከም ከብዶኝ እያንገታገተኝ ያለሁትን ጉድ በምን ለውሼ ብነግራት ነው ህመሟን የሚያለዝበው?

"አባቴን ማወቅ እፈልጋለሁ!፣ አባቴ ማነው? ለምንድነው የማይፈልገኝ?" ብላ ስትሰፋኝ

"አባትሽ አንቺን ማርገዜን ሳያውቅ ነው ተጣልተን ትቶኝ የሄደው። ቆይተን እንውለድ ስላልኩት ነው የተጣላኝ ..... አየሽ በተዘዋዋሪ አንቺን ስላልሰጠሁት ነው የተጣላኝ እንጂማ ልጁን ቢያውቅሽ ኖሮ ይኖርልሽ ነበር። ምርጥ አባት ይሆንሽ ነበር። ላልወለዳት ልጁ በፍቅር ያበደ ነበር" ብዬ ከነገርኳት ዓመት እንኳን አልሆነምኮ። ለራሴ እንኳን በቅጡ ያልገባኝን ትርምስምስ ምን ብዬ ልንገራት?

"ደህና ነሽ? የምትፈልጊው ነገር አለ?" አለኝ አብርሃም። ለካ መኪናው ቆሟል። ስሙን ለማወቅ ግድ ያልሰጠኝ የሆነኛው ከተማ ደርሰናል።

"አይ ደህና ነኝ። ምንም አልፈልግም" አልኩኝ።

የምፈልገው ግን ከቅዳሜ በፊት የነበሩት ቀኖቼ ላይ መመለስ ነበር።
ስራ ቦታ ...... የአንድ ባንክ ቅርንጫፍ ሀላፊ የሆነች ፣ ባል የሌላት ፣ 'ይህቺ ሴት ቆማ መቅረቷ ነው' እያሉ ሲያዝኑልኝ ..... ገሚሱም ሲመክረኝ ገሚሱም 'ችግር ቢኖርባት ነው' እያለ ሲያማኝ ከስራዬ ውጪ ከማንም በጥብቅ ሳልጋመድ የምትውለዋን ያቺን ሴት .......

እቤት ስመለስ .......ከልጄ ጋር የቤት ስራዋን ስንሰራ፣ ስለጓደኞቿ ስታወራኝ ፣ በሳምንት ሁለት ቀን ፊልም አብረን ስናይ፣ በሳምንት ሁለት ቀን ተራ በተራ መፅሃፍ ስናነብ፣ ክፍሏ ገብታ ስትቀርብኝ ለመጥራት ሰብብ ስፈልግ፣ የቀረውን ጊዜ ጓዳ እኔ ምግብ ሳበስል እየመጣች የእድሜዋን ጥያቄ እየጠየቀች ልቤን ድክም ስታደርገኝ የምታሳልፈዋን ያቺን ሴት.....

ቅዳሜና እሁድን ...... ከልጄ ጋር ቤተሰቦቼጋ ሄደን በቀን ለማይቆጠር ጊዜ ቡና ስናፈላ፣ ጉንጫችን እስኪዝል የባጥ የቆጡን ስናወራ፣ የእማዬን ጣፋጭ ምግብ ቁንጣን እስኪይዘን ስንበላ ፣ አባዬ በልጅ ልጆቹ ሩጫና ጩኸት ሲያማርር እየሳቅን የምታሳልፈዋን ሴት ......

ሁሉ ባይኖረኝም ባለኝ የማመሰግን። ህመሜን ባልረሳውም ከህመሜ ጋር እንዴት ተከባብረን ተላምደን መኖር እንዳለን የተማርኩኝ ያቺን ሴት......

አርብ ከመተኛቴ በፊት የነበርኳትን ሴት መሆን ነው የምፈልግ የነበረው። እንደብዙ ሰውኮ ብዙ አልጠየቅኩም አይደል እንዴ?

"ደርሰናል። ግን እርግጠኛ ነሽ ልታገኚው ትፈልጊያለሽ?" ሲለኝ ነው አሁንም መኪናው መቆሙን ያስተዋልኩት። ከኋላ ብቻዬን ነበር የተቀመጥኩት።
"እ? አዎ አይ እርግጠኛ ነኝ! ችግር የለውም!" አልኩኝ ደረቴን በርቅሳ ልትወጣ ይመስል የምትደልቅ ልቤን እንዳያዩብኝ ልብሴን እየነካካሁ። ምንም ባልናገርም ፊቱን ማየት እንደሞት እንዳስፈራኝ ከሁኔታዬ ገብቷቸዋል።

አባትየው ለአንደኛው ፖሊስ ሲያስረዳ ሲጨቃጨቁ አጠገባቸው ሆኜ እንደእሩቅ ድምፅ ነው የሚሰማኝ። የማስበው ሳየው ምን እንደምለው ነው! ሊመልስልኝ የሚችለውን መልስ መላ እመታለሁ። ልጅ እኔጋኮ ልጅ አለህ ስለው ይደነግጥ ይሆን? ይፀፀት ይሆን? እና? ቢለኝስ?

የሆነ ስም ጠርቶ እገሌ ይጠራልኝ ብሎ አባትየው ሲቀውጠው ፖሊሶቹ አልፈቅድ ብለው እንደሆነ ገባኝ። ከመምጣታችን በፊት አጣርቶ ነው ማለት ነው? ፍርሃቴ ከማየሉ የተነሳ እዚህ ድረስ ከመጣሁ በኋላ እንቢ ብለው ሳላገኘው ብመለስ ብዬ አስቤ ለቅፅበት ደስ እንደሚለኝ ተሰማኝ። ትልቁን ፍርሃቴን ተጋፍጬ ከእውነት ከመጋፈጥ መሸሽ!! የሰው ልጅ በብዙ እንደዛ አይደለ? ፍርሃቱን በመሸሽ ውስጥ ያለውን መንገድ ያውቀዋል። ቢወደውም ቢጠላውም ስለለመደው ይኖራል። ፍርሃቱን ሲጋፈጥ ከተራራው ጀርባ ያለውን ግን አያውቀውም። ሳያውቀው ይፈራዋል። አልለመደውማ! ስለዚህ ፍርሃቱን እሹሩሩ እያለ የለመደውን የተለመደ ህይወት ይኖራል።

የተባለው ሰው ተጠርቶ ተጨባብጠው። ሁኔታውን በእርጋታ ከተረዳዱ በኋላ ተስማሙ። ሰውየው አሸናፊ እንዲጠራ ትእዛዝ ሲሰጥ መሮጥ ሁሉ አማረኝ። ብቻ እነግሩም ስለተንቀሳቀሱ እግሬን ወደፊት እየዘረጋሁ ዘለቅኩ። ተጠርቶ ሲመጣ የሚቆምበት ቦታ የሆነ ፖሊስ ነገር እየመራ ወስዶ ሲያደርሰኝ እነ ግሩም ወደኋላ ቀሩ

ከጀርባው ለእኔ ከማይታየኝ ከሆነ ሰው ጋር እያወራ እየሳቀ ብቅ አለ። ሲያየኝ እንደመቆም አለ። ፊቱ ግን የገረመው አይመስልም ነበር። የሆነ ቀን እንደምመጣ የሚያውቅ ዓይነት መረጋጋት ነው ያለው። በረዥሙ ቢተነፍስ ትንፋሹ በሚሞቀኝ ዓይነት ርቀት ላይ ደርሶ ሲቆም ለምን ላገኘሁ እንደመጣሁ ፣ ምን ልጠይቀው እንደነበር ሀሳቤ ሁሉ ጭንቅላቴ ውስጥ ተደነባበረ። እልህ ፣እንባ ፣ላለመሸነፍ ትንቅንቅ ..... አፈነኝ። ወዲያው ደግሞ በራሴ ተበሳጨሁ። እንዴት ያለሁ ልፍስፍስ ነኝ ከዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ እንኳን የበደለኝን ሰው ሳየው ጎብዞ መታየት የሚከብደኝ? እኔ እስካወራ ድረስ ከንፈሩን አላላቀቀም። አይኖቹን እንኳን አልሰበራቸውም። ሳይነቅል ከማየቱ የተነሳ በአይኑ እየቦረቦረኝ ያለ ዓይነት ስሜት ሁላ ነው የተሰማኝ። ለደቂቃ ትንፋሼን ውጬ አይኖቼን አይኖቹ ውስጥ ዘፈዘፍኳቸው። አፌን ለቆ ሲወጣ የሰማሁት ዓረፍተ ነገር

"አብረን በነበርንበት ጊዜ ወደኸኝ ታውቅ ነበር?" የሚል ነው።

ይቀጥላል እንግዲህ......
አታምጣው ስለው አምጥቶ ቆለለው #5

አፌን ለቆ ሲወጣ የሰማሁት ዓረፍተ ነገር
"አብረን በነበርንበት ጊዜ ወደኸኝ ታውቅ ነበር?" የሚል ነው። ጥያቄዬ አፌን ለቆ ወጥቶ ሳያልቅ በፊት

"ባባ ደህና ነው?" የሚለው የእርሱ ጥያቄ ዓለሜን አዞረብኝ። ለመጠየቅ መልሱን ፈርቶ እያማጠ እንደያዘው ያስታውቅ ነበር። እኔ ሳየው የ15 ዓመት ቁስሌን ነው የጠዘጠዘኝ። ለካስ የእኔ መከሰት ለእሱ የቤተሰቡ ህልውና አደጋ ላይ መውደቅ ማመላከቻ መርዶ ነው። ራስ ወዳድ እንደሆንኩ ተሰማኝ።

"እሱ ደህና ነው። እኔጋ ነው!" አልኩት። በረዥሙ ከሆዱ እስከ ጭንቅላቱ የናጠው የመገላገል ትንፋሽ ተነፈሰ።

"እሷስ?" አለኝና መልሶ "ተይው አትንገሪኝ!" አለኝ። ለሆነ ደቂቃ ስረግመው የኖርኩት አሸናፊ መሆኑን ረሳሁት። የምመልስለትም የምጠይቀውም ተወነባበደብኝ።

"ሞታ ነው አይደል? በህይወት እያለች ላንቺ እንዲደወል አታደርግም።" አጠያየቁ እንድመልስለት የፈለገ አይደለም።

"በህይወት አለች!" አልኩት:: ሲቃ አይሉት ለቅሶ አይሉት ያለየለት ድምፅ አሰምቶ በዛ ቁመቱ ግንድስ ብሎ መሬቱ ላይ ዘፍ ብሎ ተቀመጠ። ላለማልቀስ እየታገለ ግን እንባ ሳይወጣው እያለቀሰ እንደሆነ ያስታውቅበታል። ዝም ብሎ ከማየት ውጪ ማድረግ የቻልኩት ነገር የለም። ድንገት የሆነ ነገር ትዝ እንዳለው ነገር በጥያቄ እያየኝ ከተቀመጠበት ተስፈንጥሮ ተነስቶ

"ቆይ ቆይ ታዲያ ህሉ በህይወት ካለች ባባ አንቺጋ ምን ይሰራል? እ ...እ ... በፍፁም! ህሉ ትንፋሿ እያለ ልጇን አሳልፋ አትሰጥም!" ተቁነጠነጠ። የተፈጠረውን ነገር ስነግረው ጭንቅላቱን በእጆቹ ይዞ ጀርባውን ሰጥቶኝ ቆመ። ምልስ ብሎ

"አንቺ ውሸት አትችዪበትም። እውነቱን ንገሪኝ! ትድናለች?" ሲለኝ የእኔ እንባ ምን ቤት ነው ከእርሱ ቀድሞ የተዘረገፈው?

"አላውቅም!! ሀምሳ ሀምሳ ነው የመንቃት እድሏ ነው ያሉት ሀኪሞቹ።"

እዚህ ደቂቃ ላይ ስለራሴ ምንም እንደማልጠይቀው አወቅኩ። ጥያቄዎቼን መልሼ አዝያቸው ልሄድ ወሰንኩ። ቤተሰብ ለእሱ ዓለሙ ነው። ዓለሙ ፈርሷል። የእኔን ህመም እርሱ ካለበት ሁኔታ ጋር ማነፃፀር አልፈለግኩም። ዝም አልኩ።

"ከሞተች። (ሲቃ እያነቀው ቃሉን ሲለው እንደዘገነነው ያስታውቃል።) ለልጄ እናቱ እንደሞተች አትንገሪው። ሲቆይ ይረሳታል። "

"እንዴ?" ብዬ ጮህኩኝ ሳላስበው።

"ልግባ?" አለኝ ለመሄድ ፊቱን እያዞረ። ግራ ገባኝ። እንዲህ ሁሉ ነገር እጄ ላይ ጥሎ እንዴት ነው የሚገባው? ባባን ምን ላድርገው? እሺ ልጄንስ ምን ልበላት? እሺ ሚስቱን የገጨበትን ሰው በህግ ልጠይቀው በሽማግሌ? እሺ ሚስቱንስ ምን ላድርጋት? ዥውውውው አለብኝ። ይሄን ሁሉ መከራ እላዬ ላይ ጥሎማ አይገባም! ግን የቱን አስቀድሜ የቱን እንደማስከትል እንጃ!

"አዎ እያንዳንዱን ቀን ወድጄሽ ነበር።" አለኝ ለመሄድ እየተንቀሳቀሰ። ማለት የምፈልግ የነበረው ብዙ ነበር። ለምን ብዬ የምጠይቃቸው እልፍ ጥያቄዎች ነበሩ። ፊቱ ላይ ካለው ስቃይ ጋር ሲነፃፀር የእኔ ጥያቄ ገለባ ሆነብኝ። መርዶ ይሁን የምስራች ሳይገባኝ

"እርጉዝ ነበርኩ። ያኔ ..... " ብዬ 'ትተኸኝ ስትሄድ' ልል ነበር። የምጎዳው ነገር መሰለኝና ሌላ የሚተካው ቃል ስፈልግ....

"እና? " አለኝ። ሊሄድ ከነበረበት ተመልሶ በጉጉት

"15 ዓመቷን ባለፈው ሰኔ 6 አከበረች::" አልኩት። ሳቅና ለቅሶ ፊቱ ላይ ተሳከረበት። ወደፊት ወደኋላ ከዛ ወደጎን ተንቆራጠጠ። እጁን አንዴ ጭንቅላቱ ላይ አንዴ ወደኋላ አንዴ ጉንጩ ላይ ያቅበዘብዘዋል።

"ታውቂያለሽ ....." ብሎ ዝም አለ

"አውቃለሁ። ብታውቅ ልጅህን ያለአባት እንድታድግ አታደርጋትም። ልነግርህ ነበር። ልነግርህ ስመጣ አንተ ሄደሃል።" አልኩት። ልክ እንደቅድሙ መሬቱ ላይ ዘጭ ብሎ ተቀመጠ። ግን እንደቅድሙ ለቅሶ ብቻ አይደለም። ፈገግ እያለ ነው የሚያለቅሰው። ቅስስ ብሎ ከመሬቱ ላይ ተነሳ መደሰት ይሁን ማዘን ያለበት ግራ የገባው ይመስላል።

"አባቷ ?...." ብሎ እንዴት መጠየቅ እንዳለበት ግራ ሲገባው

"ታውቃለች። እውነቱን ነው የነገርኳት። የአሁኑን እንዴት እንደምነግራት ነው ግራ የገባኝ።"

ሰዓታችን ማለቁን ደጋግመው እየገገሩን ነው። እንደማሰብ ካለ በኋላ ...... እስከአሁን የሆነውን መሆን እንዳልሆነ ...... ክፉ ዜና እንዳልሰማ ...... ምንም ዝንፍ ያለ ነገር እንዳልተፈጠረ ..... ተረጋግቶ ከፊቱ ላይ እንባውን ካበሰ በኋላ በሰከነ ዝግተኛ ድምፅ

"ጥያቄዎችሽን ሁሉ ብመልስልሽ : የሆነውን ሁሉ አንድ በአንድ ባስረዳሽ ደስ ይለኛል። ምናልባት እድሉን ካገኘሁ የሆነ ቀን ያደረግኩትን ለምን እንዳደረግኩ እነግርሻለሁ። ያ ማለት አንቺ ያ ይገባሻል ማለት አይደለም። እመኚኝ አንቺን ከጎዳሁሽ በላይ ባሰብኩሽ ቁጥር እቀጣበታለሁ። ይገባኛል ብዬም አይደለም የምጠይቅሽ ግን በዓመታት ብዛት ሊከፋ የማይችል ደግ ልብ እንዳለሽ አውቃለሁ። ልጄ ቤተሰብ እንዲኖረው እፈልጋለሁ። ካንቺ የተሻለ ብዙ ፍቅር ያለው ሰው አላውቅም!! እኔ የኖርኩትን ህይወት እንዲኖር አልፈልግም። የተፈረደብኝ ቀን ለሄሉ ድንገት የማትወጣው ነገር ውስጥ ከገባች ላንቺ እንድትደውልልሽ ነገርኳት። ታውቂያለሽ ሁለታችንም ቤተሰብ የለንም። 'በህይወት እያለሁ አላደርገውም ድንገት እኔ የሆነ ነገር ከሆንኩ ግን ልጄ በፍቅር የሚያድግበት ቤተሰብ ያስፈልገዋል።' አለችኝ:: ለዛ ነው መታወቂያዋ ላይ ያንቺ ስም የኖረው። "

ከዚህ በላይ መቆየት አይችልም ነበር። "እሺ አደጋ ያደረሰባትን ሰው ......" ብዬ ሳልጨርስ

"ምን እንደምታደርጊ አንቺ ታውቂያለሽ!! ካንቺ የተሻለ ምክንያታዊ ሆኖ የሚወስን ሰው አላውቅም !" አለኝ ፊቱን አዙሮ እየሄደ።

በቃ! ??? ስመጣ የሆነ ከባድ ሸክም ላራግፍ ...... የሆነ የሚስጥር መፍቻ ቁልፍ ላገኝ ........ የሆነ ያልኖርኩትን መኖር ልጀምር ....... የሆነ ከበሽታዬ የምፈወስ ........ የሆነ ጥያቄዬ ሁሉ የሚመለስ ዓይነት አልነበር የነበርኝ ስሜት?

ጥያቄዬ ግማሹ እንኳን መልስ ሳያገኝ ይባሱኑ ልሸሸው እንደማልሞክር የማውቀውን ሀላፊነት አሸክሞኝ ገባ! ተገተርኩ ለደቂቃ! ልክ እሱ መሬቱ ላይ ዘጭ ብሎ እንደተቀመጠው ንጥፍ ማለት አማረኝ። ራሴን ምን ውስጥ ነው የከተትኩት? ምኑን ከምኑ ነው የማዛምደው? ጭራሽ ልጠይቀው ያላሰብኩት ጥያቄ ትዝ አለኝ። ምን አድርጎ ነው የታሰረው? ምን ያህል ዓመት ይሆን የሚቆየው? ለልጄ እውነቱን ከነገርኳት ቢያንስ ይሄን ማወቅ አለብኝ። እንደገባኝ ከሆነ የግሩም አባት መረጃዎችን በአቋራጭ የማግኘት መክሊት አለው። እግሬ መሬቱ ላይ የተተከለ ይመስል ከተገተርኩበት ተስፈንጥሬ አጠገባቸው ደረስኩ። እንደሆነ ሊፈነዳ እንደተቀባበለ መዓት የምለውን ለመስማት ጠበቁኝ።

"አንድ ውለታ ዋሉልኝ!" ስላቸው ሁለቱም ግራ ገብቷቸው ያዩኛል።

"የታሰረበትን ምክንያትና ምን ያህል እንደተፈረደበት ማወቅ አለብኝ!" ስላቸው ፍፁም የጠበቁት ጥያቄ አለመሆኑ ያስታውቅባቸዋል። አባትየው ከድንጋጤው መለስ ብሎ

"ስልኮች እደዋውላለሁ። " አለኝ።

ወደአዲስአበባ እየተመለስን ጭንቅላቴን የጨመደደው ሀሳብ የታሰረው ክፉ ነገር አድርጎ ቢሆን ለልጄ እንዴት ብዬ እንደምነግራት ነበር። በመስኮቱ አሻግሬ እያየሁ ውስጤ ያለው ስሜት ቅድም ስሄድ የነበረው ዓይነት እንዳልሆነ ገባኝ ..... ምን አጊንቼ ነው የቀለለኝ??

"እርቦኛል:: የሆነ ቦታ ምግብ እንብላ?" አልኩኝ
"ባንቺ ሁኔታ ስለምግብ ማውራት ቅንጦት ስለመሰለኝ እንጂ ቁርስ እንኳን ሳንበላ ነውኮ ጠዋት የወጣነው!" አለኝ ግሩም!

ይቀጥላል ......

እኔ የምለው ዛሬኮ የአባት ሀገር ገና ነው!! በበዓል ግን ቁጭ ብዬ እንደፃፍኩላችሁ ታውቃላችሁ? ያው መውደዴን እንድታውቁት ታክል ነው። በዓሉ ለሚመለከታችሁ። ያማረ በዓል ከምትወዷቸው ጋር ይሁንላችሁ።❤️❤️❤️❤️❤️❤️🤣
አታምጣው ስለው አምጥቶ ቆለለው #6

“ማት? አንተ እኔን ብትሆን ምን ታደርግ ነበር ?" አልኩት ወንድሜን የሆነውን አንድ በአንድ ከነገርኩት በኋላ።

"እኔ አንቺን ልሆን አልችልም! ኸረ ማንም አንቺን ሊሆን አይችልም! እህቴ ማንም ያንቺ ልብ የለውምኮ!! ግን አያድርገውና ባንቺ ቦታ ብሆን ታውቂኛለሽ እዛው አንድ አይኑን በቦክስ ጠብቼው ሁለት ስንቅ ታመላልሺ ነበር።" አለኝ እየሳቀ።

"ማት የምሬን ጨንቆኝኮ ነው!"

"እህቴ ? " አለኝ ..... አለው የሆነ የሚያየኝ አስተያየት .... የስስት ዓይነት! በስሜ ጠርቶኝ አያውቅም። 'እህቴ' ነው የሚለኝ።

"ያለሽ እውነቱን ነው። ካንቺ የተሻለ ምክንያታዊ ሆኖ የሚወስን ሰው እኔም በአቅራቢያዬ አላውቅም! የሆነማኮ እነእማዬ ከእኔ ተደብቃው ያስተማሩሽ ጉብዝና አለ"

"አያድርገውና ብትሞትስ?" አልኩት

"ብትሞት ነው ወይስ ብትድን ይበልጥ ያስፈራሽ?"

"ማለት? "

"ማለትማ ገብቶሻል! ቅድም ከባባ ጋር ስትሆኚ የነበረውን አይቻለሁ። ውስጡ ካለነው በአንድ ጣት የማንሞላ ሰዎችሽ ውጪ ማንም እንዳይገባበት ደራርበሽ ያጠርሽውን አጥር ዘው ብሎ ገብቶብሻል። ያን አጥርሽን ሲያልፉ .... ስስት አታውቂም ነፍስሽንም : ያለሽንም ትሰጫለሽ! ከዛ ሲሄድብሽ ያለውን መሰበር ትፈሪዋለሽ!"

እሱ ክሽን አድርጎ በቃላት ሲያስቀምጠው የሆነ ያሳከከኝን ቦታ በትክክል ያገኘው 'አዎ !...እሱጋ' የሚያስብል አይነት ስሜት ተሰማኝ። የገለፀበት መንገድ ገርሞኝ

"አይገርምም! ፈሪ አድርጎኛል!" አልኩኝ

"እሱ ነው ፈሪ ያደረገሽ? እሱም በግድ አጥርሽን አልፎ አይደለም ውስጥ ያገኘሽው? ስታውቂው ውጣልኝ የማትዪበት ደረጃ ደርሶ አይደለም የተቀበልሽው? አስቢው እህቴ? መቼ ነው ከቤተሰብ ውጪ ለመጨረሻ ጊዜ ጓደኛ ኖሮሽ የሚያውቀው? ከአቢ በኋላ ሁሌም እንዲህ ነበርሽ። "

አቢ የአባዬ ታናሽ እህት የአክስቴ ልጅ ናት። እሷ እኛ ቤት ከመምጣቷ በፊት ምን ዓይነት ልጅ እንደነበርኩ አላስታውስም። አክስቴ በልጅነቷ ከትዳር ውጪ ነበር የወለደቻት። ጣሊያን ቪዛ አጊንታ ስትሄድ አቢ እኛ ቤት ስትመጣ 14 ዓመቴ ነው። በወራት ነበር የምትበልጠኝ። እህትም ጓደኛም አገኘሁ። እኔ የምማርበት ትምህርት ቤት ገባች። ለአራት ዓመት ከእርሷ ተለይቼ የሄድኩበትን ቦታ፣ ከእርሷ ተለይቼ የበላሁትን ምግብ፣ ሰምቼ ወይ አድርጌ እሷ የማታውቀው ነገር አላስታውስም። ውጤት አምጥተን የተለያየ ዩንቨርስቲ ሲደርሰን አይኖቼ እስኪፈርጡ አለቀስኩ። በዚህ መሃል እናቷ መጣች። እናቷ ስትመጣ በተደጋጋሚ ከእናቷ ጋር ለብቻ ማሳለፍ ሲጀምሩ የምሰራው ጠፋኝ። እሷ ሳትኖር ምንድነበር የማደርገው? ማሰብ አቃተኝ። የሆነ ቀን ግራ ሲገባኝ እማዬጋ ሱቅ ሄጄ ዋልኩ። ስመለስ አቢ አልነበረችም። ሻንጣዋን ይዛ ሄዳለች። ቻው እንኳን አላለችኝም። አባዬና ማት ሳሎን ቁጭ ብለው ነበር።

"አቢስ?" አልኩኝ

"አቢ ከእናቷ ጋር ሄዳለች!" አለኝ አባዬ

"ልታድር? " አልኩኝ ማደሯ እየከፋኝ

"አይደለም ልጄ! ተመልሳ አትመጣም! ከእናቷ ጋር ወደውጪ ሄዳለች። ዛሬ ነው በረራቸው !" አለኝ ምንም እንዳልሆነ ቀለል አድርጎ።

ያውቁ ነበር እንደምትሄድ። ራሷ ትንገራት ብለው ነበር ዝም ያሉኝ። እሷ ልትነግረኝም ..... ቻው ልትለኝም ግድ አልሰጣትም። ማልቀስ እየፈለግኩ ግን አላለቀስኩም። ዝም አልኩኝ። ለቀናት ዝም አልኩኝ። ለእኔ ብዙ ነገሬ ናት ብዬ ለማስባት ሴት ለሷ ምኗም አልነበርኩም ብዬ ሳስብ ልቤን ክብድ ይለኛል። እኔና እሷ የምንቀመጥበት የነበረ ካፌ ብቻዬን ቁጭ ብዬ 'የምሯን ነው ግን? አብረን የሳቅነውን፣ ያለቀስነውን፣ አብረን የሰራነውን ተንኮል፣ የተማከርነውን ....የምሯን ረስታው ነው?' እላለሁ። ከወር በኋላ ደውላ

"ቻው ያላልኩሽ ፈርቼሽ ነው!" ከማለት የተሻለ ማብራሪያ እንኳን አልሰጠችኝም። በቃ ህይወቷን ቀጠለች። እኔ ግን ጎደለችብኝ። የሆነ ቀን ከቤት ደወልኩላት። ከኢትዮጵያ ጣሊያን! በቅጡ ሰላም እንኳን ሳትለኝ "ፌቪዬ ልወጣ ስል ነው የደወልሽው እደውልልሻለሁ!" ብላ ዘጋችው። የእኔ በህይወቷ መጉደል ቁርስ የመዝለል ያህል እንኳን ሳይከብዳት ህይወቷን ቀጠለች:: ..... ጠበቅኳት። የሆነ ቀን 'ናፈቅሽኝ' ትለኛለች ብዬ ...... የሆነ ቀን የሄደችበት ሀገር የገጠማትን ልታወራኝ መልሳ ትደውላለች ብዬ ........ ጊቢ ሸበላ ወንድ አይቼ እንደው ደውላ ታበሽቀኛለች ብዬ ....... ቢያንስ ለልደቴ እንኳን አትረሳኝም ብዬ ......... ከዓመታት በኋላ ወደሀገር ቤት እስከተመለሰችበት ጊዜ ድረስ አልደወለችም። .....

"የህይወት አንዱ አካል ነው። ሰዎች ወደ ህይወትሽ ይመጣሉ ይሄዳሉ። የሆነው መንገድሽ ላይ መቀበልንም መሸኘትንም መልመድ የለብሽም?" አለኝ ማት በሀሳብ መጋለቤን እያስተዋለ። ስልኬ ሲጠራ አየውና በጥያቄ አየኝ

"ባክህ ባለመኪናው ነው። የገጫት!" አልኩት ግሩም የሚለውን ሲያይ ሌላ ነገር አስቦ እንደሆነ እየገባኝ።

"እኔ ተናግሪያለሁ!" አለኝ በተንኮል። ስልኩን አነሳሁትና ግሩም ሊያገኘኝ እንደሚፈልግ ነግሮኝ ልጄ ከትምህርት ቤት ከተመለሰች በኃላ ባባን ለሷ ትቼው ልንገኛኝ ተቀጣጥረን ዘጋሁት።

"አባቷ ምንም አድርጎ ቢሆን እውነቱን እንዳለ ማወቅ አለባት። ሳይዘገይ ብታውቅ ደግሞ ጥሩ ይመስለኛል።" አለ ማት ግሩም ስለአሸናፊ ሊነግረኝ በአካል ቢሆን ይሻላል እንዳለኝ ስነግረው።

"አውቃለሁ። ግን..."

"አንቺ አለሽላት ምንም አትሆንም! እያወቅሽ እንዳልነገርሻት ከምታውቅ እውነቱ ምንም ያህል ከባድ ቢሆን እሱን ብታውቅ ይሻላል። "

ማት ቤቴን ለቆ ከወጣ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ባባ ከእንቅልፉ ነቅቶ አጠገቤ መጣ። አይኖቹን እያሻሸ በቅጡ ሳይገልጥ የተቀመጥኩበት ሶፋ ላይ እግሮቹን አውጥቶ ጭንቅላቱን ጭኔ ላይ አስደግፎ ተጋደመ። ልምድ እንደሆነ ነገር ........ ብዙ ጊዜ አድርጎት እንደሚያውቅ ነገር.......ለቀናት ሳይሆን ብዙ ጊዜ እንደሚያውቀኝ ነገር። ሳላስበው ፈገግ አልኩ።

ሊሄድብኝ እንደሚችል እያወቅኩም ቢሆን ያለስስት ልወደው፣ ልጠብቀው፣ የእኔ እስከማይሆን ቀን ድረስ የእኔ ላደርገው ለራሴ ቃል ገባሁ። ቀኑ ደርሶ ትቶኝ ሲሄድ አምኜ እቀበላለሁ! አልኩ። ልጄ ስትመጣ እዛው እግሬ ላይ እሱ እንቅልፍ ወስዶት በተቀመጥኩበት ሶፋውን ደገፍ ብዬ ሸለብ አድርጎኝ ነበር።

"ነፍስ አጥፍቶ ነው!" አለኝ ግሩም አንዱ ካፌ በተቀመጥንበት ሊነግረኝ ሲታሽ ቆይቶ!

"አሸናፊ በሌላ በምንም ሊታሰር ይችላል። ነፍስ ማጥፋት? በፍፁም!" አልኩኝ የሰማሁትን እንኳን ለማብሰልሰል ሰከንድ ሳልወስድ እርግጠኛ ሆኜ :: መደንገጥ ነበር የነበረብኝ አይደል? እንደዛ አይደለም የተሰማኝ

"እኔ እንጃ! ሰዎች እኮ ይቀየራሉ! አንቺ የምታውቂው ሰው ላይሆን ይችላል አሁን"አለኝ

"ትናንት ያየሁት አሸናፊ ምንም አልተቀየረም! የዛሬ 15 ዓመት የማውቀው አሸናፊ ነው።" ካልኩት በኋላ ነው ዓይኖቹን አፍጥጦ በመገረም ሲያየኝ ስለእኔና ስለአሸናፊ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ያስታወስኩት።

"የልጄ አባት ነው!" ካልኩት በኋላ ለማስረዳት ብዙ እንደሚፈጅ ሲገባኝ ተውኩት። እሱም አልጠየቀኝም። "እሺ ስንት ዓመት ነው የተፈረደበት? "

"አስራ አራት"

"በፍፁም እርግጠኛ ሆኜ የምነግርህ አሸናፊ እንኳን ሰው ለመግደል ለጥፊ እጁን አያነሳም።"

"እኔ ስለማላውቀው ምንም ልልሽ አልችልም ሰዎች ግን አይደለም በ15 ዓመት በ15 ቀን ሊቀይራቸው የሚችል አጋጣሚ ይፈጠራል።"

"ሟች ምን አይነት ሰው ነው? መረጃ አለህ?"
"አብሮት ማሳደጊያ ያደገ ጓደኛው የነበረ ሰው እንደነበር ? ከሀገር ውጪ ነበር መሰለኝ ለእረፍት በመጣበት ነው የተገደለው።"

"ገደለው?" አልኩኝ ሳላስበው።

"ምነው ታውቂዋለሽ?"

"አዎ! ማለቴ አላውቀውም ግን አሸናፊ ሲያወራ ሰምቻለሁ:: እርግጠኛ ነኝ እሱ ነው!! " አልኩኝ ደሜ ቀዝቅዞ

ይቀጥላል እኮ ....
አታምጣው ስለው አምጥቶ ቆለለው #7

“ምን አድርጎት ነው የገደለው?” ነበር ያለችኝ።

በየትኛው ቃል፣ በየትኛው ዓረፍተ ነገር፣ በየትኛው ሰዓት፣ የት ቦታ ፣ እንዴት እንደምነግራት ስጨነቅ እና ሳምጥ ቀናት ካለፉ በኋላ ለልጄ ስለአባቷ ስነግራት!! ያልጠበቅኩት ምላሽ ስለነበር ፈራኋት። ምናልባት በጣም ደንግጣ ይሆን ምንም ዓይነት መረበሽ ያላሳየችኝ?

“የእኔ ልጅ ሁሉንም በአንዴ ስደራርብሽ ይበዛብሽል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ነገሮችን በሰከነ ጭንቅላት ሆነን እነግርሻለሁ። አንድ ነገር ግን በእርግጠኝነት ልንገርሽ አባትሽ መጥፎ ሰው አይደለም!” አልኳት

“እማ እኔ እንደምታስቢው ህፃን ልጅ አይደለሁም! ስለአባቴ እውነቱን የነገርሽኝ ትችለዋለች ብለሽ ስላመንሽብኝ አይደል? ከነገርሽኝ አይቀር ሁሉንም ማወቅ እፈልጋለሁ። እና ደግሞ እንኳንም ነገርሽኝ!” ብላ ጉንጬን ሳመችኝ። ከኔ በተሻለ ነገሩን በእርጋታ የተቀበለችበት መንገድ ጤነኝነት እስከማይመስለኝ ድረስ ተገረምኩ። ዝም ማለቴን ስታይ ቀጠል አድርጋ

“ቆይ በህይወቴ ሁሉ ጭራሽ ያልነበረ አባቴ ድንገት እስር ቤት እንደሆነ ከማወቅ ያውም ሰው ገድሎ፣ እናቴን ትቶ ሌላ አግብቶ የወለደው ወንድም እንዳለኝ ከማወቅ የባሰ አለው? የለውም እኮ እማ! ንገሪኝ ሁሉንም!!” እውነቷን ነው የባሰ የለውም!

“የለውም!” አልኳት እንዲህ መብሰሏ እየገረመኝ

“ንገሪኛ! ምን አድርጎት ነው የገደለው?”

“የአባትሽን ህይወት ያበላሸበት ሰው ነው። የእሱን ብቻም አይደለም። የባባን እናትም ህይወት ያበላሸ ሰው ነው። አባትሽ ያልኖረውን ህይወት ስኬታማ ሆኖ በመበቀል የሚያምን ሰው ነበር። በትምህርቱም ጎበዝ ተማሪ ነበር። ጥሩ ውጤት አምጥቶ ተምሮ ስራ ይዞ አግብቶ ወልዶ የሚኖርለት ቤተሰብ እንዲኖረው ነበር ምኞቱ። ስሙን ረስቼዋለሁ ……… ሟች ….. አብሯቸው ማሳደጊያ የነበረ ልጅ ነበር። በባህሪው ባለጌ በጉልበት የሚያምን ነበር። የባባን እናት ፍቅረኛዬ ካልሆንሽ ብሎ ያስቸግራት ነበር። የሆነ ቀን አባትሽ ‘ተዋት አትፈልግህም!’ ስላለው ይጣላሉ። ይደባደባሉ። የዛን እለት ማታ አባትሽ ወደማደሪያው ሲመለስ ሎከሩ ውስጥ መጠኑ ብዙ የሆነ አደንዛዥ እፅ በጥቆማ ተገኝቶበት ተከሰሰ። የአስራሁለተኛ ክፍል ትምህርቱን ሊጨርስ አንድ ዓመት ነበር የቀረው። ከዛ በፊት በጥሩ ስነምግባር : ልጆችን በማስጠናት : በቅን ልብ የሚታወቅ ልጅ በመሆኑ ቅጣቱ ቀሎለት 1 ዓመት ነበር የተፈረደበት። ከዛ ግን ህይወት ከቆመችበት አልቀጠለችለትም። እሱ ባልነበረበት ጊዜ ይሄው ልጅ የባባን እናት አታሎ ከጊቢ ውጪ አስጠርቶ ደፈራት። ለማንም መንገር ፈርታ ለአባትሽ የተፈጠረውን ነግራው ማሳደጊያውን ጥላ ጠፍታ አረብ ሀገር ሄደች። አባትሽ ከራሱ መታሰርና ህይወቱ እንደቀድሞ ካለመሆኑ በላይ እርሷን ሊጠብቃት ያለመቻሉ እኔ እስከማውቀው ድረስ ይጠዘጥዘው ነበር። አቅመ ቢስነት ይሰማው ነበር።”

“አባቴና እሷ ያኔ ፍቅረኛሞች ነበሩ? “

“እሱ እንደነገረኝ ከሆነ አልነበሩም። እንደእህትና ወንድም ነበር የሚጠባበቁት። ካምፑ ውስጥ ከነበሩ ልጆች በሙሉ ሁለቱ በተለየ ይቀራረቡና ይጠባበቁ ነበር። እንደታናሽ እህቱ ይሳሳላት እንደነበር ነው የነገረኝ።”

“እሺ ከዛስ?”

“ከዛ አባትሽ ቅጣቱን ጨርሶ ሲወጣ እሷም የለችም። ልጁም በህገወጥ መንገድ ከሀገር ወጥቷል። ከመታሰሩ በላይ ከፍተኛው ቅጣት ወደማሳደጊያ ጣቢያው መመለስ እንዳይችል የተጣለበት ማዕቀብ ነበር። ከዛ ጊቢ ውጪ ሰውም ህይወትም አልነበረውም። የትም ሆኖ ትምህርቱን መቀጠል አይችልም ነበር። ስራ እንኳን ለመቀጠር ተያዥ የሚሆነው ሰው የለውም ነበር። ብቻ እስር ቤት በነበረበት ጊዜ ተምሮ በነበረው የእጅ ሙያ አንድ ፈርኒቸር ቤት ስራ እስኪያገኝ ድረስ ብዙ አስከፊ ህይወት አሳልፏል።”

“እና ሰውየውን በመግደሉ ልክ ነው ብለሽ ነው የምታስቢው?” አለችኝ

“ልክ ነው ብዬ አላስብም ። አንዳንዴ ግን ሰዎች ሁሉ ልክ ያልሆነ ነገር እናደርጋለን። አባትሽ ያደረገው ልክ ባይሆንም። ያደረገበትን ምክንያት ግን በመጠኑም ቢሆን እረዳለሁ።”

“ትጠይዋለሽ? ማለቴ አባቴን ትጠይዋለሽ? ሰው በመግደሉ ሳይሆን አንቺን ባደረገሽ ነገር?”

“አልጠላውም የእኔ ልጅ!! ግን ተቀይሜዋለሁ። በጣም ብዙ ተቀይሜዋለሁ። ጥላቻ ሳይሆን መከፋት! ቅያሜ ነው ያለኝ!! ብዙ ቅያሜ!!”

“ይቅርታ ቢልሽስ?”

“ከይቅርታው ይልቅ ያደረገበትን ምክንያት መረዳት ብችል ምናልባት ቅያሜዬን እተወው ይሆናል። አላውቅም! እስከማውቀው ድረስ አባትሽ ያለበቂ ምክንያት ማንንም ሰው ቢሆን የሚጎዳ ነገር የሚያደርግ ሰው አልነበረም! ቢያንስ እኔ እንደዛ ነው የማስበው!”

“ስታገኚው አልጠየቅሽውም?”

“ከእኔ ጥያቄ የሚበልጥ መጎዳት ውስጥ ስለነበር መታገስን መረጥኩ የእኔ ልጅ!”

“አትናደጂም?” አለችኝ የእሷ እድሜ በማይመስል ጠንካራ ድምፀት

“በምኑ?”

“ደግነትሽን እንደጂልነት ሲቆጥሩብሽ? ምንም አድርጎሽ ቢሆን እንደምትረጂው ስለሚያውቅ ለምን ትቶሽ እንደሄደ እንኳን ምክንያቱን ሳይነግርሽ ጥሩነትሽን ይጠቀምበታል። እንቢ እንደማትዪው ያውቃል። ምክንያቱም ክፉ ልብ የለሽም አይደል?” ይሄን ያለችበት መንገድ ጉዳዩ ስለእኔ ብቻ እንዳልሆነ ገባኝ። የሆነ እያለፈችበት ያለ ነገር አለ ማለት ነው። የሆነችው ነገር። ንግግሯ የ15 ዓመት ልጅ ንግግር አይደለም።

“እንደዛ እንዲሰማሽ ያደረገሽ ሰው አለ? መልካምነትሽን እንደጅልነት የቆጠረብሽ ሰው አለ? ደግ ሆነሽለት ብልጥ ሆኖ የተጠቀመብሽ ዓይነት ስሜት እንዲሰማሽ ያደረገሽ ሰው አለ?”

“ብዙ ጊዜ። ጓደኞቼ የምላቸው የሆነ ነገር ከእኔ ሲፈልጉ የሚወዱኝ ይመስላሉ። እያወቅሁ የፈለጉትን የምችለው ከሆነ አድርግላቸዋለሁ። እነሱ ግን የሚመስላቸው የሸወዱኝ ነው።”

“ወይኔ ጉዴ!! መቼ ነው እንደዚህ ያደግሽው? በ15 ዓመት እንዲህ አይበሰልምኮ የእኔ ልጅ?”

“ያንቺ ልጅ አይደለሁ?”

“የውልሽ የእኔ ልጅ! ጥሩ መሆን፣ ለሰዎች ሁሉ ቅን ነገር ማድረግ፣ የቻልሽውን ሁሉ መርዳት ጥሩ ነገር ነው። የሰው ልጅ ሁሉ የሚያጭደው የዘራውን ነውና የዘራሽው ደግነት ባላሰብሽው መንገድ ጎተራሽን ሞልቶ ታገኚዋለሽ!! ያ ማለት ግን ቅን ልብሽን ተጠቅመው ባገኙት አጋጣሚ ሊጠቀሙብሽ ለሚፈልጉ ብልጥ ነን ብለው ለሚያስቡ ከንቱዎች ሁሌ መጠቀሚያ መሆን አለብሽ ማለት አይደለም። ዝምታ የሚገባው ብልህ ሰው ብቻ ነው። አንዳንዱ ሰው ከንቱነቱ ሊነገረው ይገባል። ለራስሽ ቁሚ! ‘እስከዛሬ ዝም ያልኩህ እንደእኔ ጥሩነት እንጂ እንዳንተ ከንቱነት አይደለም’ ማለት አለብሽ” ስላት ድክም ብላ ትስቃለች። ለዛሬ ንግግራችንን የጨረስን መሰለኝ። ውስጤ ሽጉጥ ብላ

“እወድሻለሁ እኮ! ምርጥዬ እናት ነሽ! እንዳንቺ ዓይነት እናት ባትኖረኝ እኔም ከከንቱዎቹ አንዷ እሆን ነበር።” አለችኝ

በሳል እንደሆነች ድሮም አውቃለሁ። ዛሬ ግን ከአዕምሮዬ በላይ ሆነችብኝ። እኔ በሷ እድሜ አባዬ እና እማዬ ሲጨቃጨቁ ሰምቼ እናትና አባቴ ተጣሉ ብዬ እንደ ተዓምር ለማቲና ለአቢ እያለቀስኩ መናገሬን አስታውሳለሁ። በእኛ ፊት አያደርጉትም እንጂ ለብቻቸው ሲሆኑ እንደማንኛውም ባለትዳር የሚጨቃጨቁበት ጉዳይ ሊኖራቸው እንደሚችል የገባኝ መቼ እንደሆነ እንኳን እንጃ ...... እሷ ከእኔ ተሽላ በእርጋታ ነገሮችን የተቀበለችበት መንገድ እየቆየ 'ሆ'ያስብለኝ ገባ።
ለተወሰኑ ቀናት ነገሮች እንደዛው ባሉበት ቀጠሉ። ልጄ ምንም እንኳን ስለአባቷ ያለውን ነገር ብትቀበልም ለጊዜው ልታገኘው እንደማትፈልግ አስረግጣ ነገረችኝ። እኔ ግን ላገኘው እፈልጋለሁ!! አሁንም የቀረኝ ነገር እንዳለ ነው የሚሰማኝ!! ባገኘው ፣ የሄለንን ያህል እንኳን ወዶኝ ባይሆን አብረን ያሳለፍነው ጊዜ በልቡ ውስጥ የሆነ ቦታ እንደነበረው ማወቅ ከሆነ መታሰሬ የሚፈታኝ ነገር ይመስለኛል። ለልጄ ያልኳት ከልቤ ነው። ይቅርታ እንዲለኝ አይደለም መሻቴ ምክንያቱ እኔን ትቶ ለመሄድ ውሃ ያነሳ እንደነበር ነው ማወቅ የምፈልገው። በሌላ ቋንቋ እሱጋ የነበረኝን ዋጋ ነው ማወቅ የፈለግኩት።

በቻልኩት አጋጣሚ እና ጊዜ የባባን እናት እየሄድኩ አያታለሁ። ምንም ለውጥ የላትም። እነግሩም የህክምና ወጪዋን እየሸፈኑ ቢሆንም ከዛ ባለፈ የተነጋገርነው ነገር የለም። ምንም ከመወሰኔ በፊት ሄለን ብትነቃ ውሳኔውን ለሷ ለመስጠት ፈልጌ ይመስለኛል በዝምታ ቀናት ያስቆጠርኩት።

አሸናፊ ለባባ ስለእናቱ እንዳልነግረው ቢነግረኝም ያን ማድረጉ ልክ መስሎ ስላልታየኝ ለባባ በእድሜው ሊገባው በሚችል መልኩ እናቱ ለጊዜው መታመሟን ነግሬው የተወሰነ ቀንም ይዤው ሄጄ አሳይቼዋለሁ። ምናልባት እሷ ብታልፍ እንኳን ዋሽቼው ልጄ አላደርገውም። እናቱ እንደሞተች አውቆ ከልጄ ለይቼ የማላየው እናቱ እንደሆንኩ አሳየዋለሁ። እናት እሆነዋለሁ!! የማትዋሸው እናት!! መጀመሪያ የወሰድኩት ቀን እንድትነቃለት ስሟን እየጠራ ሲያለቅስ እንደህፃን አብሬው አልቅሻለሁ!! የዛን ቀን እንቅልፉን ተኝቶ ሁሉ እየቃዠ ይጠራት ነበር። አልጋዬ ላይ አምጥቼው አጠገቤ አስተኝቼው በጭንቀት እና በላብ የተጠመቀ ትንሽዬ ፊቱን እያየሁት ለረዥም ሰዓት እንቅልፍ አልወሰደኝም። እቅፌ ውስጥ ሲሆን እንደምጠብቀው ልቡ ነግሮት ነው መሰለኝ ለጥ ብሎ ተኛ!!

ከተከታዮቹ ቀን በአንዱ ከስራ ተመልሼ ከልጄ እና ከባባ ጋር መክሰሳችንን እየበላን በሬ ተንኳኳ። የግሩም እናት ነበሩ። ከመጀመሪያው ቀን በኋላ አይቻቸው ስለማላውቅ እየገረመኝ ወደውስጥ እንዲገቡ ጋበዛኳቸው።

"ላናግርሽ ፈልጌ ነበር። በልጆቹ ፊት ባይሆን ጥሩ ነው!" አሉኝ ወንበሩ ላይ እየተቀመጡ። ልጄ እኔ ምንም ከማለቴ በፊት ባባን ይዛው ወደክፍሏ ሄደች።

"ምንድነው ሀሳብሽ? ውሳኔሽን ማወቅ እፈልጋለሁ! ልጄ ከዛ ቀን በኋላ ተረጋግቶ ምንም ነገር ማድረግ አልቻለም! ስራውን እንኳን በትክክል እየሰራ አይደለም! እሱ ዓመት ሙሉ ዝም ብትዪም እንደማይጠይቅሽ ስለማውቅ ነው ራሴ የመጣሁት! እየሆነ ያለው ነገር ምንም አልገባኝም! 'እሷ ለራሷም አልተረጋጋችም!' ይለኛል እሱ። መቼ ነው የምትረጋጊው? አንቺ እስክትረጋጊ ከዛሬ ነገ ፖሊስ መጥቶ በሬን አንኳኳ : ልጄን ወሰደብኝ እያልኩ መሳቀቅ ገደለኝ" አሉኝ ያነገቱትን ቦርሳ እንኳን ከትከሻቸው ሳያወርዱ

ይቀጥላል .......
2025/07/08 10:33:10
Back to Top
HTML Embed Code: