Telegram Web Link
ፊቤላ ኢንዱስትሪያል በ30 ሚሊየን ብር ወጪ ያስገነባውን የመማሪያ ክፍሎች አስረከበ

በበላይነህ ክንዴ ግሩፕ ፊቤላ ኢንዱስትሪያል በ30 ሚሊየን ብር ወጪ በቡሬ ከተማ የዕድገት በህብረት መጀመሪያና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያስገነባቸውን 15 የመማሪያ ክፍሎች አስረከበ።

በ1971 ዓ.ም የተመሰረተው ትምህርት ቤቱ፤ በዕድሜ ብዛት የመማሪያ ክፍሎቹ ፈራርሰው ለመማር ማስተማር ሂደት ምቹ አልነበሩም።

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ አበበ አለማየሁ በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት፤ ባለሀብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ የመማሪያ ክፍሎችን ችግር በመረዳት በአጭር ጊዜ ውስጥ ባለ ሁለት ወለል 15 የመማሪያ ክፍሎች አስገንብተው አስረክበዋል።

የፌቤላ ኢንዱስሪያል ተወካይ ኃላፊ አቶ ዳዊት ገ/ስላሴ በበኩላቸው፤ ፊቤላ ኢንዱስትሪያል በከተማዋ ከፈጠረው  የሥራ እድልና የቴክኖሎጂ ሽግግር በተጨማሪ ማህበራዊ  ግዴታውን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ለዚህም የቡሬና አካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ከ200 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ወጭ አድርጓል ነው ያሉት።

የዕድገት በህብረት የመጀመሪያና መካከለኛ ደረጃ ት/ቤት የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ 30 ሚሊየን ብር ወጪ ማድረጉን ገልጸው፤ ለሁሉም ክፍሎች ደረጃውን የጠበቀ ወንበርና ጠረጴዛ አሟልቷል ብለዋል።

በላይነህ ክንዴ ግሩፕ በፋውንዴሽኑ አማካኝነት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ባለፉት አራት ዓመታት ከ900 ሚሊየን ብር በላይ ለማህበራዊ ኃላፊነት ወጪ አድርጓል።

የፍጻሜ ምዕራፍ ላይ ለሚገኘው የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ቀሪ ሥራዎች ማጠናቀቂያ የሚውል ከ60 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ  ተደርጓል።

#ዳጉ_ጆርናል
ኔታንያሁ ኢራን ለፈፀመችው የሚሳኤል ጥቃት 'ከባድ ዋጋ' ትከፍላለች አሉ

የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የኢራን የሚሳኤል ጥቃት በቢየር ሼቫ በሚገኘው የእስራኤል ሶሮካ ሆስፒታል ላይ ጉዳት ማድረሱን ተከትሎ "ከባድ ዋጋ እንደምትከፍል" ዝተዋል።

"ዛሬ ጠዋት የኢራን አሸባሪ አምባገነኖች በቢየር ሼቫ በሚገኘው በሶሮካ ሆስፒታል እና በሀገሪቱ በሚገኙ ሲቪሎች ላይ ሚሳይሎችን ተኩሰው ጉዳት አድርሰዋል" ሲሉ ኔታንያሁ በኤክስ ገፃቸው ላይ በለጠፉት ጽሑፍ ያስታወቁ ሲሆን "በቴህራን ውስጥ ያሉ አምባገነኖች ከባድ ዋጋ እንዲከፍሉ እናደርጋለን" ሲሉም አክለዋል።

የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዜም ጋሪባባዲ በበኩላቸው አሜሪካ ቀጥተኛ ወታደራዊ ጣልቃገብነት እንዳታደርግ ሌላ ተጨማሪ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

ጋሪባባዲ ለሮይተርስ የዜና ወኪል በሰጡት አስተያየት ኢራን ግጭቱ እንዲስፋፋ እንደማትፈልግ ነገር ግን አስፈላጊ ከሆነ እርምጃ ለመውሰድ እና ለአጥቂዎች ትምህርት ለመስጠት ዝግጁ ናት ብለዋል። የኢራን ወታደራዊ ውሳኔ ሰጪዎች "በጠረጴዛው ላይ ሁሉም አስፈላጊ አማራጮች" አሏቸውም ብለዋል።

በሚሊዮን ሙሴ
#ዳጉ_ጆርናል
ግሎው ኢትዮ-ቱርኪዬ የሚዲያ ባለሙያ ሊያ ሳሙኤልን በ3.5 ሚሊየን ብር ብራንድ አምባሳደር አድርጎ ሾመ

ግሎው ኢትዮ-ቱርኪዬ አጠቃላይ የጸጉር ንቅለ ተከላና የቆዳ ህክምና ማዕከል እና የሚዲያ ባለሙያ ሊያ ሳሙኤል አብረው መስራት የሚያስችላቸውን የፊርማ ስነ ስርዓት አከናውነዋል፡፡

የፊርማ ስነ ስርዓቱ የተከናወነው ሊያ ሳሙኤል፣ ግሎው ኢትዮ-ቱርኪዬ የሚሰራቸውን ስራዎች ህዝብ ዘንድ እንዲደርሱ እና እንዲተዋወቁ የብራንዱን አምባሳደርነት እንድትወክል ሲሆን የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ጨምሮ የተለያዩ ምርቶቹን በተለያዩ መንገዶች የምታስተዋውቅም ይሆናል፡፡

የሚዲያ ባለሙያ ሊያ ሳሙኤል ከግሎው ኢትዮ-ቱርክዬ የ3.5 ሚሊየን ብር ስምምነት እንደፈፀመች በተለይም ለብስራት ሬድዮ ተናግራለች።አሁን ላይ ለተለያዩ የጤና ምርመራ እና ህክምናዎች የጸጉር ንቅለ ተከላ እና ከውበት ጋር የተያያዙ ህክምናዎችን ጨምሮ  ከሀገር ውጪ መጓዝ በአለም አቀፍ ደረጃ እያደገ የመጣ ክስተት ሲሆን ቱርክ ለእንደዚህ አይነት የህክምና አይነቶች ቀዳሚ መዳረሻ ሆናለች።

ግሎው ኢትዮ-ቱርኪዬ አጠቃላይ የጸጉር ንቅለ ተከላና የቆዳ ህክምና ማእከል ይህንን ክፍተት ለመሙላት እና በሀገር ውስጥ መሰል አገልግሎቶችን ለመስጠት ሁሉን አቀፍ፣ በአንድ ማእከል ብቻ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቆዳ እንክብካቤ፣ የጸጉር ንቅለ ተከላ፤ የዋግምት ህክምና፤ የሰውነት ቅርጽን ማስተካከል እንዲሁም ከውበት ጋር የተያያዙ የውበት መጠበቂያ ፕሮዳክቶችን ከቱርክ በመጡ እንዲሁም ቱርክ ሰልጥነው በመጡ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ለማቅረብ አላማውን አድርጎ የተነሳ ማእከል ነው።

ግሎው ኢትዮ-ቱርኪዬ አጠቃላይ የጸጉር ንቅለ ተከላና የቆዳ ህክምና ማዕከልን ሲቋቋም ዋነኛ አላማው ከፍተኛ ችሎታ ባላቸው ባለሙያዎች፣ የላቀ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የእያንዳንዱን ደንበኛ ልዩ ፍላጎቶች በማሟላት ደንበኞች በራስ መተማመን፣ ውበት እና ምቾት እንዲሰማቸው በሚያስችላቸው አጠቃላይ የውበት፣ የፀጉር ንቅለ ተከላ እና የቆዳ እንክብካቤ መፍትሄዎች አማካኝነት መፍትሄ መስጠት እና የውጭ ምንዛሬን ከማዳን ባሻገር ሰዎች የትም ሳይሄዱ ሀገራቸው ላይ ውጪ ሀገር ሄደው የሚያገኟቸው የህክምና አገልግሎት እዚሁ ሀገራቸው ላይ እንደ አማራጭ ማቅረብ ነው፡፡

ሊያ ሳሙኤል እውቅ የማስታወቂያ ባለሙያ፤ ታዋቂ የቴሌቭዥን ፕሮግራም አቅራቢና የሶሻል ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪ በመሆኗ ግሎው ኢትዮ-ቱርኪዬ አጠቃላይ የጸጉር ንቅለ ተከላና የቆዳ ህክምና ማዕከልን እንድታስተዋውቅ እንደተመረጠች ብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቭዥን ሰምቷል።

በሰላማዊ ነጋሲ
#ዳጉ_ጆርናል
ወላይታ ሶዶ ከተማ የ8 ዓመት ህጻን አስገድደው ከደፈሩ በኋላ ገድለው የሰቀሏት  ሁለት ግለሰቦች በእስራት ተቀጣ

በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ፋና ወንባ ቀበሌ የአስገድዶ መድፈር እና የግድያ ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦች በእስራት መቀጣታቸው የከተማው ፖሊስ አስታወቀ።

ተከሳሾች ዳዊት ሻንቆ እና ታምራት ኦሳ የተባሉ ሲሆን የ8 ዓመት ህጻን የሆነችውን መሳይ አስናቀን ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም  ከአባቷ ቤት አታለው ወደ ጫካ በመውሰድ አስገድደው ከደፈሩ በኋላ ገለው 'ራሷን  ያጠፋች ለማስመሰል ጎረቤት በሚገኝ ባዶ ቤት በማስገባት አስክሬኗን በእንጨት ላይ በመስቀል ከአከባቢው  መሠወራቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት እና ገጽታ ግንባታ ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር አሸናፊ ኃይሌ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።

ፖሊስ ከአከባቢው ማህበረሰብና ከመንግስት አካላት ጋር በመሆን ባደረጉት ብርቱ ክትትል ለ4 ወራት ያህል ከተሰውሩበት መያዛቸው ተገልጿል።በፖሊስ የተጣራው የምርመራ መዝገብ የደረሰው የወላይታ ዞን ዐቃቤ ህግ  ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክሱን ያቀርባል።

የወላይታ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ተከሳሾች የቀረበባቸውን ክስ በአሳማኝ ሁኔታ መከላከል ባለመቻላቸው ጥፋተኛ በማለት  ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት በተከሳሽ ዳዊት ሻንቆ እና ታምራት ኦሳ በተባሉ በእነዚህ ግለሰቦች ላይ የዕድሜ ልክ ጽኑ አስራት እንዲቀጡ መወሰኑን  ምክትል ኮማንደር አሸናፊ ኃይሌ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።

በሳምራዊት ስዩም
#ዳጉ_ጆርናል
የእስራኤል ጦር የአራክ ሬአክተር ማጥቃቱን አረጋገጠ

የእስራኤል ጦር ተዋጊ ጄቶች የአራክ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫን ጨምሮ በደርዘን የሚቆጠሩ የኢራን ጣቢያዎችን በአንድ ሌሊት ማጥቃቱ ገልፆል። ጦሩ በተለይ "በፕሉቶኒየም ምርት ውስጥ ቁልፍ አካል የሆነውን የማብላያ ኮር መዋቅር" ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈፀሙ ገልፆል።

በናታንዝ የሚገኘውን "የኑክሌር ጦር መሳሪያ ልማት ጣቢያ" ለባለስቲክ ሚሳኤሎች የሚያስፈልጉ አካላትን የሚያመርቱ በርካታ ፋብሪካዎችን መምታቱም ተናግሯል።

የአራክ የውሃ ተቋም ከቴህራን በስተደቡብ ምዕራብ 190 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ተቋም ሲሆን በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ ግንባታው የተጀመረ የኢራን ሰፊው የኒውክሌር ፕሮግራም አካል ነው።በፍጥነት ጉልህ የሆነ አለምአቀፍ ትኩረትን የሳበ ነበር።

ቦታው የከባድ ውሃ ማምረቻ ፋብሪካን እና የ IR-40 ሬአክተርን ያካትታል።  የከባድ ውሃ ልከኝነት ለምርምር፣ አይሶቶፕ ለማምረት እና ፕሉቶኒየምን እንደ ተረፈ ምርት ለማምረት ያስችላል። የተባበሩት መንግስታት፣ የአውሮፓ ህብረት እና ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ አራክ ለኢራን የፕሉቶኒየም መንገድና የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ሊሰጥ ይችላል በማለት ስጋታቸውን ያለማቋረጥ ሲገልፁበት የቆዩ ተቋም ነው።

እ.ኤ.አ. በ 2015 የጋራ አጠቃላይ የድርጊት መርሃ ግብር (JCPOA) ፣ ኢራን ሪአክተሩን ለሰላማዊ አጠቃቀም እና የፕሉቶኒየም ምርትን ለመገደብ ተስማምታለች።

በሚሊዮን ሙሴ
#ዳጉ_ጆርናል
ባለፋት ዘጠኝ ወራት በአማራ ክልል በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ሳቢያ ለይስማ ንጉስ ሙዚየም የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ማሟላት አልተቻለም ተባለ

ባለፋት ዘጠኝ ወራት በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ለሚገኘው ይስማ ንጉሥ ቤተ መዘክርቅርሶችን ለማደራጀት የሚስፈልጉ ግብዓትን ለማሟላት በእቅድ ተይዞ እንደነበር የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።

የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ አበበ እምቢአለ ለብስራት ሬዲዮ እንደገለፁት ለሙዚየሙ ግብአት ለማሟላት በእቅድ የተያዘ ቢሆንም በአካባቢው ያለው የፀጥታ ችግር በቦታው ተገኝቶ ሙዚየሙ ያለበትን ደረጃ ገምግሞ መስራት አልተቻለም ፡፡

ነገር ግን የቅርስ ማሰባሰብ ስራ ለመስራት አንድ ጊዜ መድረክ በመፍጠር በደሴ ከተማ ውይይት መካሄዱን የገለፁት አቶ አበበ በቀጣይ በሀገር ደረጃ የሚመለከታቸውን ባለድርሻና አጋር አካላት ያሳተፈ መድረክ ለማካሄድ ታቅዷል ብለዋል።

ይህን እውን ለማድረግ የሚያስችች ቢጋር ተዘጋጅቶ ፀድቋል ሲሉ ተናግረው ከዚህ መድረክ በኋላ ቅርስ በማሰባሰብ የተለያዩ ግብዓቶችን የማሟላት ሰራ ይሰራል በማለት ጨምረው ለጣቢያችን ገልፀዋል፡፡25 ሚሊዮን ብር ወጪ ተመድቦለት የውጫሌ ውልን በሚዘክረው በታሪካዊው ቦታ (ይስማ ንጉስ) አካባቢ ሙዚየሙ መገንባቱ ይታወሳል።

በቅድስት ደጀኔ
#ዳጉ_ጆርናል
ኢራን መሳሪያዋን ተጠቅማ አጥቂዎችን ትምህርት ከማስተማር ወደኃሏ እንደማትል ዛተች

የኢራን ፕሬዝዳንት እያንዳንዱን የመንግስት አካል "ኢራንን እንዲያገለግል" በማህበራዊ ሚዲያ ድህረ ገጽ ላይ ባሰፈረት መልዕክት መመሪያ ሰጥተዋል። "ሁሉም ሚኒስቴሮች እና የመንግስት ኤጀንሲዎች ኢራንን በሙሉ ሃይላቸው እና ገንዘባቸው እንዲያገለግሉ ተልእኮ ተሰጥቷቸዋል።ከትዕግስት እና ድጋፍ ጋር ምንም አይነት አገልግሎት ሳያስቀሩ መስጠት አለባቸው ሲሉ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዝሽኪያን ተናግረዋል። "በፈጣሪ ቸርነት እና በመተሳሰብ እነዚህን አስቸጋሪ ቀናት እናልፋለን" በማለት ፔዝሽኪያን አክለው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ የምታደርገውን ጥቃት ለመቀላቀል በሚያስቡበት በዚህ ወቅት የኢራን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሜሪካን አስጠንቅቀዋል። የኢራን መንግስት ሚዲያ ካዜም ጋሪባባዲ እንደዘገበው “አሜሪካ እስራኤልን ለመደገፍ በንቃት ጣልቃ መግባት ከፈለገች ኢራን መሳሪያዋን ተጠቅማ አጥቂዎችን ትምህርት ከማስተማር እና ራሷን ከመከላከል ውጭ ሌላ አማራጭ አይኖራትም ብለዋል።

"ለአሜሪካ የምንሰጠው ምክረ ሀሳብ የእስራኤልን ጥቃት ለማስቆም ካልፈለጉ ቢያንስ ራሳቸውን ችለው እንዲቆሙ ነው" በማለት የኢራን "ወታደራዊ ውሳኔ ሰጪዎች በጠረጴዛው ላይ ሁሉም አስፈላጊ አማራጮች አሉ" ብለዋል ። የሩሲያእ ኢንተርፋክስ የዜና ወኪል የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭን ጠቅሶ እንደዘገበው በኢራን እና በእስራኤል ግጭት ውስጥ በአሜሪካ የሚፈጽመው ማንኛውም ጣልቃገብነት “አስፈሪ የሆነ የእርስ በእርስ ግጭት” ይፈጥራል ብለዋል። ትራምፕ አሁንም ጣልቃ በመግባት አማራጮችን እየገመገሙ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል
የትግራይ ትራንስፖርት ቢሮ የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት ማስጀመሩን አስታወቀ

የትራንስፖርት አሰጣጥ ስርዓቱን ለማዘመን የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በማስገባት የተፋጠነ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት እየሰራሁ እገኛለሁ ያለው ቢሮ አሁን ደግሞ BYT ከተሰኘ የቴክኖሎጂ አቅራቢ ድርጅት ጋር በመሆን በክልል ደረጃ የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት ወደ ስራ ማስገባቱ የትግራይ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ታደለ መንግስቱ ለብስራት ተናግረዋል።

አቶ ታደለ አክለው ቢሮው ያስጀመረ የኢ ቲኬትንግ አሰራር ትርፍ መጫን ለማስቀረት፣ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል ለመገደብ፣ ህብረተሰብ ከአላስፈላጊ እንግልት ለማዳን ያስችላል ያሉ ሲሆን ቲኬት በበይነ መረብ መቁረጥ የሚያስችል በመሆኑም የተሳፋሪዎችና የአሽከርካሪዎች ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው ብለዋል።

ቴክኖሎጂውን ወደ ስራ ለማስገባት 18 ወራት መፍጀቱ የሚገልፁት ኃላፊው አሰራሩ በክልሉ ውስጥ ባሉ ሁሉም መናሃርያዎች ተግባራዊ በሚሆንበት ሰዓት የተጓዦችና የአሽኸርካሪዎችን ያልተፈለገ እንግልትና ወጪ የሚያስቀር ይሆናል ተብሎ ተስፋ እንደተጣለበት ጨምረው ገልፀዋል።

በሰብል አበበ
#ዳጉ_ጆርናል
ኤሪክ አውሎ ነፋስ ወደ ሜክሲኮ እየተቃረበ ሲሆን 'እጅግ አደገኛ' መሆኑ ተነገረ

ኤሪክ አውሎ ነፋሱ ወደ ሜክሲኮ ፓሲፊክ የባህር ዳርቻ እየተቃረበ ሲሆን  “እጅግ አደገኛ” ሆኖ በምድብ 4 ደረጃ ተጠናክሯል ሲል የአሜሪካ ብሄራዊ አውሎ ንፋስ ማእከል (ኤን.ሲ.ሲ) አስታውቋል። ከፍተኛ ቀጣይነት ያለው ንፋስ 220 ኪሜ በሰአት ተመዝግቧል። ትንበያ ሰጪዎች በመጪዎቹ ሰዓታት ውስጥ "አውዳሚ የንፋስ ጉዳት" በአንዳንድ ግዛቶች ሊደርስባቸው ይችላል ብለው ይጠብቃሉ ።

የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሺንባም በአውሎ ነፋሱ መንገድ ላይ ያሉትን ሰዎች “ከይፋዊ መረጃዎች ጋር ግንኙነት እንዲያደርጉ ፣ ቤት ውስጥ እንዲቆዩ እና እንዳይወጡ” መልዕክት አስተላልፈዋል ።የአውሎ ንፋስ ማስጠንቀቂያ በፓስፊክ የባህር ዳርቻ 500 ኪሜ ድረስ  ከሪዞርት ከተማ ከአካፑልኮ እስከ ፖርቶ አንጄል ድረስ ተግባራዊ ሆኗል። በጌሬሮ እና ኦአካካ የሚኖሩ ነዋሪዎች ለሕይወት አስጊ የሆነ ጎርፍ እና የውሃ መጥለቅለቅ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ።

የሜክሲኮው ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሺንባም "በቆላማ አካባቢዎች፣ በወንዞች አቅራቢያ፣ በውሃ መስመሮች አቅራቢያ ያሉ ሰዎች ወደ ጊዜያው መጠለያ ማምራት አለባቸው" ብለዋል። በተራራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ሊደርስ ከሚችለው የመሬት መንሸራተት እንዲጠነቀቁ ተነግሯቸዋል።በቺያፓስ፣ ጓሬሮ እና ኦአካካ ግዛቶች ወደ 2,000 የሚጠጉ መጠለያዎች ተዘጋጅተዋል።

ከ18,000 በላይ የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ ሰጪዎች ለአውሎ ነፋሱ እንዲዘጋጁ መመሪያ ተሰጥቷል። በዚህ ወቅት ከሰኔ መጀመሪያ እስከ ህዳር መጨረሻ ባለው ጊዜ በሜክሲኮ ውስጥ የመሬት መንሸራተት ይከሰታል ተብሎ ይጠበቃል። እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2023፣ በአካፑልኮ ላይ በደረሰው አውሎ ንፋስ ኦቲስ፣ ምድብ 5 ቢያንስ 50 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተል። ኦቲስ በፍጥነት ጠንከረ ያለ አውሎ ንፋስ ሲሆን አደጋው ሲደርስ በርካታ ሰዎች ዝግጁ አልነበሩም።

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል
የአማኑኤል አእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከ102 ሺህ በላይ ተገልጋዮች ህክምና መስጠት መቻሉ ተገለፀ

ሆስፒታሉ በ2017 በጀት ዓመት ለ102 ሺህ 604 ተገልጋዮች በአእምሮ ህመምና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የህክምና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ መቻሉን የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህዝብ ግንኙነት አቶ ነብዩ የኔአለም ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።የአማኑኤል አእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በ9 ወራት ውስጥ በአስተኝቶ የአእምሮ ህክምና ለ1ሺህ 421 በተመላላሽ የአእምሮ ህክምና 98ሺህ 803 እንዲሁም በድንገተኛ የአእምሮ ህክምና 2ሺህ 380 በአጠቃላይ ለ102ሺህ 604 የአእምሮ ህመም ታካሚዎች ህክምናውን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም በመሆን ለአዕምሮ ህሙማን የህክምና አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከተመሰረተበት ከ1930 ዓ.ም ጀምሮ በተኝቶ፤ በተመላላሽ፤ በድንገተኛ ህክምና፤ በጭንቅላት ምርመራ ፤ በኤሌክትሪክ ንዝረት ህክምና ፤ በህፃናት የአዕምሮ ህክምና ፤ ከህግ ጋር የተያያዙ የአዕምሮ ህክምናና ምርመራ (ፎረንሲክ)፤ እንዲሁም የነርቭ ህክምናዎችን ጨምሮ እየሰጠ የሚገኝ ሆስፒታል ነዉ፡፡ ከህክምና አገልግሎቱ ጎን ለጎን በሃገራዊና በማህበራዊ አገልገሎት ዘርፍም የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡

ሆስፒታሉ አሁን ላይ የህክምና አገልግሎቱን፤ ምዝገባና መረጃ አያያዝ ስርዓቱን ከዚህ ቀደም ልማዳዊ ከሆነው ወረቀት ላይ የተመሰረተ አሰራር ሙሉ በሙሉ በመውጣት ወረቀት አልባ ወደ ሆነ የኤሌክትሮኒክ የህክምና አገልግሎት ምዝገባና መረጃ አያያዝ በመተግበር የተገልጋዩን የቆይታ ጊዜ ቀንሷል፡፡የካርድ መጥፋትና መበላሸትን በማስወገድ እንዲሁም የታካሚውን የህክምና መረጃ ደህንነቱ የተጠበቀ በማድረግና በተጨማሪም የታካሚውን እርካታ በማረጋገጥና በባለሙያው ላይ የሚደርሰውን ጫና በመቀነስ የአእምሮ ጤና ህክምናና ክብካቤውን ጥራቱንና ተደራሽነቱን ከመቼውም በላይ ማረጋገጥ ተችሏል ሲሉ አክለዋል፡፡

በዚህም ሆስፒታሉ የኤሌክትሮኒክ ሜዲካል ሪከርድ (EMR) ተግባራዊ በማድረግና አሁን ላይ የህክምና አገልግሎቱን ሙሉ በመሉ ዲጅታላዝድ በማድረግ ወረቀት አልባ የጤና ተቋም ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።የተመላላሽ ታካሚ የቆይታ ጊዜ ከ2016 በጀት ዓመት ከነበረው 49 ደቂቃ ወደ 38 ደቂቃ ማድረስ ተችሏል፡፡የፎረንሲክ ህክምና የወንጀልና የፍትሐብሔር ተመርማሪዎች በተመላላሽና በተኝቶ ለ570 ለሚሆኑ አገልግሎቱ ተሰጥቷል ፡፡

በሰመኃር አለባቸዉ
#ዳጉ_ጆርናል
በሶማሊያ የአየር ጥቃት ቢያንስ 25 የአልሸባብ ታጣቂዎች ተገደሉ

የሶማሊያ ጦር በታችኛው ጁባ ክልል በሚገኘው የታጣቂ ቡድን ቦታዎች ላይ በፈፀመው የአየር ድብደባ ቢያንስ 25 የአልሸባብ ታጣቂዎች መገደላቸውን የመከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል። "የሶማሊያ ብሄራዊ ጦር የዳናብ ጦር በአለምአቀፍ አጋሮች የሚደገፈው ኃይል በአልሸባብ ቦታ ላይ ትክክለኛ የአየር ድብደባ በማኩዋሃሃ ኪስማዮ፣ የታችኛው ጁባ" ላይ ፈፅሟል ሲል የመከላከያ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

የጥቃት ዘመቻው የሽብር ጥቃቶችን ለማቀድ ጥቅም ላይ የዋለውን ቁልፍ የዕዝ ማእከል መምታቱን እና ቦታው "ከፍተኛ መዋቅራዊ ጉዳት እንደደረሰበት" ገልጿል። ኪስማዮ በደቡብ ሶማሊያ የሚገኝ ዋና የወደብ ከተማ ሲሆን ከሞቃዲሾ ብሄራዊ ዋና ከተማ 500 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኝ የጁባላንድ ግዛት ዋና ከተማ ነች።

ሶማሊያ ለረጅም ጊዜ በፀጥታ እጦት ስትታመስ ቆይታለች፣ አልሸባብ እና አይ ኤስ (ዳኢሽ) ከፍተኛ ስጋት ለሀገሪቱ ፈጥረዋል። አልሸባብ ከ16 አመታት በላይ የሶማሊያ መንግስትን ሲዋጋ ቆይቷል፤ በተደጋጋሚ የመንግስት ባለስልጣናትን እና ወታደራዊ አባላትን ኢላማ አድርጓል።

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል
ጊፍት ሪል ስቴት እስከ 25 በመቶ የአፓርታማ ሽያጭ ቅናሽ ለደንበኞቹ ማድረጉን አስታወቀ

ጊፍት ሪል ስቴት የአዳዲስ ፕሮጀክቶች ግንባታ ርክክብ እና የበጀት አመቱ የማጠቃለያ ኤክስፓ መርሀ ግብርን በጊፍት ለገሀር መንደር በይፋ አከናውኗል።ጊፍት ሪል ስቴት በዛሬው እለት ለ4ኛ ጊዜ ባካሄደው ልዩ የሽያጭ ኤክስፓ የማገባደጃ ኤክስፓ መርሀ ግብርን አከናዉኗል፡፡

የጊፍት ሪል ስቴት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር ሰለሞን አሊ ለብስራት ሬዲዮ እንደተናገሩት ተቋሙ ባለፋት ጊዜያት ልዩ የጊፍት ሽያጭ አከናውኗል።በአሁኑ ወቅት 6 መቶ ሰራተኞች ያሉት ጊፍት ሪል ስቴት ባካሄዳቸው ሶስት ዘመቻዎች ከ4መቶ በላይ አፓርታማዎችን ለሽያጭ ማቅረቡ ተገልጿል።

እአአ በ2005 ላይ የተመሰረተው እና የንግድ ማእከላትና ዘመናዊ ሪል ስቴቶችን ገንብቶ በመሸጥ የሚታወቀው ድርጅቱ በለገሀር አካባቢ 84 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ 4ሺህ ቤቶችን እና ከ4 መቶ በላይ ሱቆችን ገንብቶ ለነዋሪው እንደሚያስረክብ የጊፍት ሪል ስቴት ሽያጭና ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ብርቁ ይርጋ ተናግረዋል።

ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ቀዳሚ እና ከምስራቅ አፍሪካ ተመራጭ ካምፓኒ እንዲሆን ራእይ ሰንቆ እየተጋ ይገኛል ያሉት አቶ ብርቁ ጥራት ያላቸውን መኖሪያ ቤቶችን እና የንግድ ማእከላትን መካከለኛና ከፍተኛ ገቢ ላላቸው ደንበኞቹ እየሸጠ ይገኛል።አያይዘውም በ2በመቶ ቅድመ ክፍያ እንዲሁም በ25 በመቶ ቅናሽ ሰዎች የቤት ባለቤት መሆን እንደሚችሉ ተናግረዋል።4ኛው ልዮ የሽያጭ ኤክስፓ እስከ ግንቦት 23 ቀን ድረስ እንደሚቆይ የተገለፀ ሲሆን ቤት ፈላጊዎች ይህን እድል እንዲጠቀሙ ጥሪ ቀርቧል።

በቅድስት ደጀኔ
#ዳጉ_ጆርናል
2025/06/28 20:45:13
Back to Top
HTML Embed Code: