Telegram Web Link
የትግራይ ትራንስፖርት ቢሮ የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት ማስጀመሩን አስታወቀ

የትራንስፖርት አሰጣጥ ስርዓቱን ለማዘመን የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በማስገባት የተፋጠነ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት እየሰራሁ እገኛለሁ ያለው ቢሮ አሁን ደግሞ BYT ከተሰኘ የቴክኖሎጂ አቅራቢ ድርጅት ጋር በመሆን በክልል ደረጃ የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት ወደ ስራ ማስገባቱ የትግራይ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ታደለ መንግስቱ ለብስራት ተናግረዋል።

አቶ ታደለ አክለው ቢሮው ያስጀመረ የኢ ቲኬትንግ አሰራር ትርፍ መጫን ለማስቀረት፣ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል ለመገደብ፣ ህብረተሰብ ከአላስፈላጊ እንግልት ለማዳን ያስችላል ያሉ ሲሆን ቲኬት በበይነ መረብ መቁረጥ የሚያስችል በመሆኑም የተሳፋሪዎችና የአሽከርካሪዎች ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው ብለዋል።

ቴክኖሎጂውን ወደ ስራ ለማስገባት 18 ወራት መፍጀቱ የሚገልፁት ኃላፊው አሰራሩ በክልሉ ውስጥ ባሉ ሁሉም መናሃርያዎች ተግባራዊ በሚሆንበት ሰዓት የተጓዦችና የአሽኸርካሪዎችን ያልተፈለገ እንግልትና ወጪ የሚያስቀር ይሆናል ተብሎ ተስፋ እንደተጣለበት ጨምረው ገልፀዋል።

በሰብል አበበ
#ዳጉ_ጆርናል
ኤሪክ አውሎ ነፋስ ወደ ሜክሲኮ እየተቃረበ ሲሆን 'እጅግ አደገኛ' መሆኑ ተነገረ

ኤሪክ አውሎ ነፋሱ ወደ ሜክሲኮ ፓሲፊክ የባህር ዳርቻ እየተቃረበ ሲሆን  “እጅግ አደገኛ” ሆኖ በምድብ 4 ደረጃ ተጠናክሯል ሲል የአሜሪካ ብሄራዊ አውሎ ንፋስ ማእከል (ኤን.ሲ.ሲ) አስታውቋል። ከፍተኛ ቀጣይነት ያለው ንፋስ 220 ኪሜ በሰአት ተመዝግቧል። ትንበያ ሰጪዎች በመጪዎቹ ሰዓታት ውስጥ "አውዳሚ የንፋስ ጉዳት" በአንዳንድ ግዛቶች ሊደርስባቸው ይችላል ብለው ይጠብቃሉ ።

የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሺንባም በአውሎ ነፋሱ መንገድ ላይ ያሉትን ሰዎች “ከይፋዊ መረጃዎች ጋር ግንኙነት እንዲያደርጉ ፣ ቤት ውስጥ እንዲቆዩ እና እንዳይወጡ” መልዕክት አስተላልፈዋል ።የአውሎ ንፋስ ማስጠንቀቂያ በፓስፊክ የባህር ዳርቻ 500 ኪሜ ድረስ  ከሪዞርት ከተማ ከአካፑልኮ እስከ ፖርቶ አንጄል ድረስ ተግባራዊ ሆኗል። በጌሬሮ እና ኦአካካ የሚኖሩ ነዋሪዎች ለሕይወት አስጊ የሆነ ጎርፍ እና የውሃ መጥለቅለቅ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ።

የሜክሲኮው ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሺንባም "በቆላማ አካባቢዎች፣ በወንዞች አቅራቢያ፣ በውሃ መስመሮች አቅራቢያ ያሉ ሰዎች ወደ ጊዜያው መጠለያ ማምራት አለባቸው" ብለዋል። በተራራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ሊደርስ ከሚችለው የመሬት መንሸራተት እንዲጠነቀቁ ተነግሯቸዋል።በቺያፓስ፣ ጓሬሮ እና ኦአካካ ግዛቶች ወደ 2,000 የሚጠጉ መጠለያዎች ተዘጋጅተዋል።

ከ18,000 በላይ የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ ሰጪዎች ለአውሎ ነፋሱ እንዲዘጋጁ መመሪያ ተሰጥቷል። በዚህ ወቅት ከሰኔ መጀመሪያ እስከ ህዳር መጨረሻ ባለው ጊዜ በሜክሲኮ ውስጥ የመሬት መንሸራተት ይከሰታል ተብሎ ይጠበቃል። እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2023፣ በአካፑልኮ ላይ በደረሰው አውሎ ንፋስ ኦቲስ፣ ምድብ 5 ቢያንስ 50 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተል። ኦቲስ በፍጥነት ጠንከረ ያለ አውሎ ንፋስ ሲሆን አደጋው ሲደርስ በርካታ ሰዎች ዝግጁ አልነበሩም።

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል
የአማኑኤል አእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከ102 ሺህ በላይ ተገልጋዮች ህክምና መስጠት መቻሉ ተገለፀ

ሆስፒታሉ በ2017 በጀት ዓመት ለ102 ሺህ 604 ተገልጋዮች በአእምሮ ህመምና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የህክምና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ መቻሉን የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህዝብ ግንኙነት አቶ ነብዩ የኔአለም ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።የአማኑኤል አእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በ9 ወራት ውስጥ በአስተኝቶ የአእምሮ ህክምና ለ1ሺህ 421 በተመላላሽ የአእምሮ ህክምና 98ሺህ 803 እንዲሁም በድንገተኛ የአእምሮ ህክምና 2ሺህ 380 በአጠቃላይ ለ102ሺህ 604 የአእምሮ ህመም ታካሚዎች ህክምናውን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም በመሆን ለአዕምሮ ህሙማን የህክምና አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከተመሰረተበት ከ1930 ዓ.ም ጀምሮ በተኝቶ፤ በተመላላሽ፤ በድንገተኛ ህክምና፤ በጭንቅላት ምርመራ ፤ በኤሌክትሪክ ንዝረት ህክምና ፤ በህፃናት የአዕምሮ ህክምና ፤ ከህግ ጋር የተያያዙ የአዕምሮ ህክምናና ምርመራ (ፎረንሲክ)፤ እንዲሁም የነርቭ ህክምናዎችን ጨምሮ እየሰጠ የሚገኝ ሆስፒታል ነዉ፡፡ ከህክምና አገልግሎቱ ጎን ለጎን በሃገራዊና በማህበራዊ አገልገሎት ዘርፍም የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡

ሆስፒታሉ አሁን ላይ የህክምና አገልግሎቱን፤ ምዝገባና መረጃ አያያዝ ስርዓቱን ከዚህ ቀደም ልማዳዊ ከሆነው ወረቀት ላይ የተመሰረተ አሰራር ሙሉ በሙሉ በመውጣት ወረቀት አልባ ወደ ሆነ የኤሌክትሮኒክ የህክምና አገልግሎት ምዝገባና መረጃ አያያዝ በመተግበር የተገልጋዩን የቆይታ ጊዜ ቀንሷል፡፡የካርድ መጥፋትና መበላሸትን በማስወገድ እንዲሁም የታካሚውን የህክምና መረጃ ደህንነቱ የተጠበቀ በማድረግና በተጨማሪም የታካሚውን እርካታ በማረጋገጥና በባለሙያው ላይ የሚደርሰውን ጫና በመቀነስ የአእምሮ ጤና ህክምናና ክብካቤውን ጥራቱንና ተደራሽነቱን ከመቼውም በላይ ማረጋገጥ ተችሏል ሲሉ አክለዋል፡፡

በዚህም ሆስፒታሉ የኤሌክትሮኒክ ሜዲካል ሪከርድ (EMR) ተግባራዊ በማድረግና አሁን ላይ የህክምና አገልግሎቱን ሙሉ በመሉ ዲጅታላዝድ በማድረግ ወረቀት አልባ የጤና ተቋም ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።የተመላላሽ ታካሚ የቆይታ ጊዜ ከ2016 በጀት ዓመት ከነበረው 49 ደቂቃ ወደ 38 ደቂቃ ማድረስ ተችሏል፡፡የፎረንሲክ ህክምና የወንጀልና የፍትሐብሔር ተመርማሪዎች በተመላላሽና በተኝቶ ለ570 ለሚሆኑ አገልግሎቱ ተሰጥቷል ፡፡

በሰመኃር አለባቸዉ
#ዳጉ_ጆርናል
በሶማሊያ የአየር ጥቃት ቢያንስ 25 የአልሸባብ ታጣቂዎች ተገደሉ

የሶማሊያ ጦር በታችኛው ጁባ ክልል በሚገኘው የታጣቂ ቡድን ቦታዎች ላይ በፈፀመው የአየር ድብደባ ቢያንስ 25 የአልሸባብ ታጣቂዎች መገደላቸውን የመከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል። "የሶማሊያ ብሄራዊ ጦር የዳናብ ጦር በአለምአቀፍ አጋሮች የሚደገፈው ኃይል በአልሸባብ ቦታ ላይ ትክክለኛ የአየር ድብደባ በማኩዋሃሃ ኪስማዮ፣ የታችኛው ጁባ" ላይ ፈፅሟል ሲል የመከላከያ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

የጥቃት ዘመቻው የሽብር ጥቃቶችን ለማቀድ ጥቅም ላይ የዋለውን ቁልፍ የዕዝ ማእከል መምታቱን እና ቦታው "ከፍተኛ መዋቅራዊ ጉዳት እንደደረሰበት" ገልጿል። ኪስማዮ በደቡብ ሶማሊያ የሚገኝ ዋና የወደብ ከተማ ሲሆን ከሞቃዲሾ ብሄራዊ ዋና ከተማ 500 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኝ የጁባላንድ ግዛት ዋና ከተማ ነች።

ሶማሊያ ለረጅም ጊዜ በፀጥታ እጦት ስትታመስ ቆይታለች፣ አልሸባብ እና አይ ኤስ (ዳኢሽ) ከፍተኛ ስጋት ለሀገሪቱ ፈጥረዋል። አልሸባብ ከ16 አመታት በላይ የሶማሊያ መንግስትን ሲዋጋ ቆይቷል፤ በተደጋጋሚ የመንግስት ባለስልጣናትን እና ወታደራዊ አባላትን ኢላማ አድርጓል።

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል
ጊፍት ሪል ስቴት እስከ 25 በመቶ የአፓርታማ ሽያጭ ቅናሽ ለደንበኞቹ ማድረጉን አስታወቀ

ጊፍት ሪል ስቴት የአዳዲስ ፕሮጀክቶች ግንባታ ርክክብ እና የበጀት አመቱ የማጠቃለያ ኤክስፓ መርሀ ግብርን በጊፍት ለገሀር መንደር በይፋ አከናውኗል።ጊፍት ሪል ስቴት በዛሬው እለት ለ4ኛ ጊዜ ባካሄደው ልዩ የሽያጭ ኤክስፓ የማገባደጃ ኤክስፓ መርሀ ግብርን አከናዉኗል፡፡

የጊፍት ሪል ስቴት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር ሰለሞን አሊ ለብስራት ሬዲዮ እንደተናገሩት ተቋሙ ባለፋት ጊዜያት ልዩ የጊፍት ሽያጭ አከናውኗል።በአሁኑ ወቅት 6 መቶ ሰራተኞች ያሉት ጊፍት ሪል ስቴት ባካሄዳቸው ሶስት ዘመቻዎች ከ4መቶ በላይ አፓርታማዎችን ለሽያጭ ማቅረቡ ተገልጿል።

እአአ በ2005 ላይ የተመሰረተው እና የንግድ ማእከላትና ዘመናዊ ሪል ስቴቶችን ገንብቶ በመሸጥ የሚታወቀው ድርጅቱ በለገሀር አካባቢ 84 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ 4ሺህ ቤቶችን እና ከ4 መቶ በላይ ሱቆችን ገንብቶ ለነዋሪው እንደሚያስረክብ የጊፍት ሪል ስቴት ሽያጭና ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ብርቁ ይርጋ ተናግረዋል።

ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ቀዳሚ እና ከምስራቅ አፍሪካ ተመራጭ ካምፓኒ እንዲሆን ራእይ ሰንቆ እየተጋ ይገኛል ያሉት አቶ ብርቁ ጥራት ያላቸውን መኖሪያ ቤቶችን እና የንግድ ማእከላትን መካከለኛና ከፍተኛ ገቢ ላላቸው ደንበኞቹ እየሸጠ ይገኛል።አያይዘውም በ2በመቶ ቅድመ ክፍያ እንዲሁም በ25 በመቶ ቅናሽ ሰዎች የቤት ባለቤት መሆን እንደሚችሉ ተናግረዋል።4ኛው ልዮ የሽያጭ ኤክስፓ እስከ ግንቦት 23 ቀን ድረስ እንደሚቆይ የተገለፀ ሲሆን ቤት ፈላጊዎች ይህን እድል እንዲጠቀሙ ጥሪ ቀርቧል።

በቅድስት ደጀኔ
#ዳጉ_ጆርናል
እስራኤል ብቻዋን በኢራን የመንግስት ለውጥ ማምጣት አትችልም ሲሉ የሩሲያ የፖለቲካ ሳይንቲስት ተናገሩ

እስራኤል በኢራን ላይ ያደረሰችው ጥቃት ከሩሲያ እይታ አንጻር "በኢራን ውስጥ የአገዛዝ ለውጥን ለማስጀመር የተደረገ ግልጽ ሙከራ ነው" ሲሉ የሩሲያ የፖለቲካ ሳይንቲስት ኒኮላይ ሰርኮቭ ተናግረዋል። "ይህንን ለመከላከል ሩሲያ የተቻለውን ሁሉ ታደርጋለች፤ ምክንያቱም በመካከለኛው ምስራቅ ፣በባህረ ሰላጤ ሀገራት ላይ ብቻም ሳይሆን በደቡብ ካውካሰስ እና በካስፒያን ክልል ውስጥ በጣም ከባድ የሆነ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ያደርጋል ብለዋል።

ኢራን በበርካታ አካባቢዎች እና ክልሎች ውስጥ አስፈላጊ አጋር ናት ሲሉ ሰርኮቭ ለአልጀዚራ ተናግረዋል። የኢራን አለመረጋጋት ማለት ለሩሲያ አንዳንድ ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክቶች ይተዋሉ ማለት ሊሆን ይችላል ብለዋል ። "ለምሳሌ ሩሲያን ከባህረ ሰላጤው ሀገራት እና ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ ወደቦች እንዲሁም በአረብ ባህር ላይ በሰሜን-ደቡብ ኮሪዶር ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሰች ነበር" ብለዋል። ሰርኮቭ ሩሲያ በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የሽምግልና ሚና ልትጫወት እንደምትችል ተንታኙ አክለዋል።

ከሩሲያ እይታ አንጻር በዚህ ዘመቻ ላይ የአሜሪካ ንቁ ተሳትፎ ከሌለ እስራኤል ብቻዋን የስርዓት ለውጥ ማምጣት አትችልም ብለዋል።የሩሲያ የኒውክሌር ኢነርጂ ኮርፖሬሽን ኃላፊ እንዳሉት የሩሲያ ስፔሻሊስቶች በኢራን ቡሽህር የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ መስራታቸውን ቀጥለዋል፣ እናም እዚያ ያለው ሁኔታ መደበኛ ነው ብለዋል። አሌክሲ ሊካቼቭ እንደገለፁት ሞስኮ ጣቢያውን እንዳይጠቃ ለእስራኤል የሰጠችው ማስጠንቀቂያ በእስራኤል አመራር ዘንድ እንደተቀበሉት ተስፋ ተደርጓል።

የሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን ሃሙስ ዕለት እንዳሉት ከ200 በላይ ሩሲያውያን በኢራን ሩሲያ በተሰራው ቡሼህር የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ መስራታቸውን ቀጥለዋል። ከእስራኤል ጋር በደህንነቱ ዙሪያ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ከኢራን ጋር የስትራቴጂክ ትብብር ስምምነት ያላት ሩሲያ በእስራኤል ላይ በምታደርገው ጥቃት ዩናይትድ ስቴትስ እንዳትሳተፍ አጥብቃ አሳስባለች፣ ቀጣናውን አለመረጋጋት ውስጥ እንደሚጥለው እና የኒውክሌር አደጋን ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቃለች።

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል
በእስራኤል ኢራን ውጥረት ዙሪያ ትንታኔውን ከጋዜጠኛ ሚሊዮን ሙሴ እና ስምኦን ደረጄ ጋር ይከታተሉ

👇👇👇👇👇👇👇👇👇👇

https://youtu.be/d45g1548L5Y?si=lQAUN_d-D8cTHNQZ

#ዳጉ_ጆርናል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአልቤርቶ ቫርኔሮ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገለፁ


ከ1950ዎቹ ጀምሮ በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ፈር ቀዳጅ በነበሩት አልቤርቶ ቫርኔሮ ህልፈት የተሰማኝን ሀዘን ለመግለጽ እፈልጋለሁ። ስራቸው የሀገራችንን የግንባታ ከባቢ እና ታሪካዊነት ያላቸው ምልክቶችን ላቅ ባለ ደረጃ የቀረፀ ነው።

ከታሪካዊ ስራዎቻቸው መካከል የአፍሪካ አዳራሽ (የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን)፣ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት፣ ሂልተን ሆቴል፣ ሚሊኒየም አዳራሽ፣ የጅማ አባጅፋር አውሮፕላን ማረፊያ ማሻሻያ፣ የአብርሆት ቤተመጻሕፍት፣ የአንድነት ፓርክ እና የብሔራዊ ቤተመንግሥት እድሳት ሥራ ይገኙበታል።

የሥራ ውርሳቸው በነዚህ ብሔራዊ ምልክቶች እና በሚወክሉት የእድገት ትእምርት ሲታወስ ይኖራል። ለነፍሳቸው ረፍትን፣ በረፍታቸው ላዘኑ ሁሉ መጽናናትን እንመኛለን።

#ዳጉ_ጆርናል
ኤሌክትሪክ ተቋርጦ የሚቆይበትን ሰአት ቀድሞ ከነበረበት 365 ሰአት ወደ 152 ለማድረስ እየተሰራ ይገኛል ተባለ

የኤሌትሪክ ሀይል ተቋርጦ የሚቆይበትን ሰአት በ2012 ዓመት ከነበረው 365 ሰአት በ2017 ወደ 152 ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል።

በአገልግሎቱ የኮሚኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ አንዋር አብራር ለብስራት ሬድዮ እንደተናገሩት በሴክተሩ ከሚታዮ ዋነኛ ችግሮች መካከል የኤሌክትሪክ መቋረጥ ነው።በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱ  ለዜጎች የኤሌክትሪክ አገልግሎትን በአግባቡ ተደራሽ ለማድረግ ይህን ችግር ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ እየሰራ ይገኛል።

ለሀይል መቋረጥ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም እየዋሉ እንደሚገኙ የተገለፀ ሲሆን ሀይል ተቋርጦ የሚቆይበትን ሰአት ለመቀነስ ተቋሙ የአቅም ማሳደግና መልሶ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በስፋት እያከናወነ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

በሀዋሳ፣በአዳማ፣በድሬደዋ፣በመቀሌ፣በደሴ፣ባህርዳር፣እና በጅማ ከተሞች የሀይል መቆጣጠሪያ ማእከል ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ተብሏል።በዚህም ሀይል ጠፍቶ እንዳይቆይ ፣የመስመሮችን ጤንነት ከአንድ ማእከል ለመከታተል ትልቅ ሚና እንዳለው ተገልጿል፡፡

በቅድስት ደጀኔ
#ዳጉ_ጆርናል
የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ሂዝቦላህ ከኢራን ጋር ጥምረት እንዳይፈጠር አስጠነቀቁ

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ የሊባኖሱን ሂዝቦላህ ቡድን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አስጠንቅቀዋል፣ እስራኤልን በሚያስፈራሩ "አሸባሪዎች" ላይ ትዕግስትንችን ቀጭን ነው ሲሉ ዝተዋል። "የሂዝቦላህ ዋና ፀሃፊ ከቀደምቶቹ ትምህርት እየተማረ አይደለም እናም በኢራን አምባገነን ትእዛዝ መሰረት በእስራኤል ላይ እርምጃ እንደሚወስድ እየዛተ ነው" ሲሉ ካትዝ በኤክስ ላይ በለጠፈው ጽሁፍ አጋርተዋል።

የሂዝቦላህ የቀድሞ መሪ ሀሰን ናስራላህ ባለፈው አመት እስራኤል በሂዝቦላ ላይ ባካሄደችው ዘመቻ መገደላቸው ይታወሳል። "እስራኤላውያን በሚያስፈራሩ አሸባሪዎች ላይ ቴላቪቭ ትዕግስት እንዳጣች እንዲጠነቀቅ እና እንዲረዱት ለሊባኖሱ ሂዝቦላ ተግሳፅ አቀርባለሁ።" የሂዝቦላህ መሪ ናኢም ቃሴም ሃሙስ ዕለት እንዳሉት የሊባኖስ ቡድን በኢራን ላይ እየተወሰደ ያለውን "ጨካኝ የእስራኤል-አሜሪካዊያን ጥቃት" ላይ እርምጃ ቡድኑ እንደሚወስድ አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል የሊባኖስ ተደማጭነት ያላቸው የፓርላማ አፈ-ጉባዔ ናቢህ በሪ፣ በሀገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የሺዓ ፖለቲከኛ እና የሂዝቦላ የቅርብ አጋር ሲሆኑ ትናንት ምሽት ለሀገር ውስጥ ኤም ቲቪ ዜና ሲናገሩ ሊባኖስ በእስራኤል ግጭት ከኢራን ጋር እንደማትቀላቀል ያላቸውን ማረጋገጫ ገልፀዋል። “ሊባኖስ ወደ ጦርነት እንደማትገባ 200 በመቶ እርግጠኛ ነኝ” ሲሉ ቤሪ ለዜና ምንጩ ተናግረዋል፣ ምክንያቱም ይህን ለማድረግ ምንም ፍላጎት ስለሌላት እና ብዙ ዋጋ ስለሚከፍል ነው ብለዋል። አክለውም “ኢራን እኛን አትፈልግም። ድጋፍ የሚያስፈልገው ለእስራኤል ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል
ካቦድ ማርኬቲንግ ሶሉሽን   የመኖሪያ ቤት እጥረት መቅረፍ ያስችላል የተባለለትን ለሶስት ቀን የሚቆይ ኤክስፖ አዘጋጀ

ካቦድ ማርኬቲንግ ሶሉሽን ላለፉት 20 ዓመታት  የሪል እስቴት ቢዝነሶቹን በማደራጀት፣ በሽያጭ ፣ ገዢዎችን ከሻጮች በማገናኘት ፣ለሽያጭ ባለሙያዎች ነጻ ስልጠናዎችን በመስጠት የስራ እድል በመፍጠር የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱ የካቦድ ማርኬቲንግ ሶሉሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ወ/ሮ ኤዶም ዳምጠው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።

ካቦድ ማርኬቲንግ ሶሉሽን እና እህት ኩባንያው የሆነው ዶክሳ ቢዝነስ ትሬዲንግ የሪል እስቴቶችን ኤክስፖ በዓይነቱ ለየት ባለ መልኩ  የሚዘጋጅ  እንደሚሆን እና   ቤት ለገዢው ሱቅ ለነጋዴው በሚል መሪ ቃል  መዘጋጀቱ ነግረውናል።

ካቦድ ማርኬቲንግ በኮሪደር  ልማት ላይ የተገነቡ  ሱቆችን ለነጋዴዎች ያቀርባል ተብሏል። ኤክስፖ ዓላማውን ያደረገው   ሪል እስቴቶች ትክክለኛ ስራቸው እንዲያሳዩ  ቤት ፈላጊዎች ደግሞ የሚፈልጉት መርጠው ቤተሰብ እንዲሆኑ በማሰብ ነው ።

በተጨማሪም  የረጅም ጊዜ አከፋፈል እና ጥራት ያላቸው ቤቶችን ለመምረጥ ትልቅ እድል ይከፍታል ተብሏል። የኤክስፖው አዘጋጅና አስተባባሪ አቶ አሜን ዳንኤል እንደተናገሩት ካቦድ ሪልእስቴት 2025  ለሶስት ቀናት ማለትም ከሰኔ27 እስከ 29  የሚቆይ ሲሆን ቴምር ሪልእስቴት፣ፕራይም ሪል እስቴት፣ ካቮድ ኮሜርሺያል፣ ፓልም ሪል እስቴት ፣ጌት አስ ሪል እስቴት ፣ኦቪድ ሪልእስቴት፣  ላይፍ ታይም ፕሮፐርቲስ ፣ ቤዝ ሪል እስቴት  ይገኙበታል ተብሏል ።

በኤክስፖ ላይ ከሚገኙት ሪል እስቴቶች ፓልም ሪል እስቴት 10 በመቶ ቅናሽ ካቮድ ኮሜርሻል ከ 1.2 እስከ 1.4 ሚሊዮን ብር ቅናሽ ፣ ቴምር ሪልእስቴት ደግሞ ሙሉ ክፍያ ለሚከፍል 25 በመቶ  ቅናሽ እንደሚያደርግ ሌሎችም  ለደንበኞች ያዋጣል ያሉትን ቅናሽ  እደሚያቀርቡ የካቦድ ማርኬቲንግ ሶሉሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ኤዶም ዳምጠው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል ።

ይህ አይነት የሪል እስቴት ኤክስፖዋች የማማከር የማሰልጠን እንዲሁም በከተማው ውስጥ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት መቅረፍ የሚቻልበት ነው ተብሏል።

በኤደን ሽመልስ
#ዳጉ_ጆርናል
2025/07/05 04:56:24
Back to Top
HTML Embed Code: