Telegram Web Link
ለሞተ ወንድ የሚዳሩ ሴቶች
(ተስፋኣብ ተሾመ)
* * *

በደቡብ ኦሞ አከባቢ ካሉ ህዝቦች መካከል በናዎች ፥ ፀማዮች እና ኤርቦሬዎች ከሌላው ህዝብ የተለየ ልማድ አላቸው፥ ልማዳቸው ከእውነት ይልቅ አእምሮ ወለድ ለሆነ ምናባዊ ፈጠራ የቀረበ ይመስላል። ልብ-ወለዳዊ አልያም ተረት እንጂ መሬት ላይ ያለ የገሃድ አለም ልምምድ መስሎ አይታይም።

አንድ ወንድ ተወልዶ ሚስት ሳያገባ ቢሞት ለሟቹ ሚስት ይዳርለታል። ሟች እንደህያው ተቆጥሮ ከአከባቢው ሴቶች መካከል ሚስት የምትሆነው ትመለመላለች። ለሚስትነት ለተመረጠችው ሴት በባህሉ መሰረት ሽምግልና ይላካል።

ሟች ገና የተወለደ ጨቅላ አሊያም ለአቅመ አዳም የደረሰ ወጣት ሊሆን ይችላል። እድሜው ለውጥ አይፈጥርም። ዋናው ቁም ነገር ትዳር አለመመስረቱ ነው።
ወንድ ልጅ ሳያገባ እንዲሞት አይፈለግም። ትዳር አለመመስረት አይበረታታም። ድንገት ቤተሰብ ሳይመሰርት ይህችን አለም ትቶ ቢሰናበት ለሙት መንፈሱ ሚስት ትታጫለች።

ሟችን በመወከል የቅርብ ቤተሰቡ ለተመረጠችው ሴት ቤተሰቦች ሽምግልና ይልካሉ። "ልጃችሁን ለሞተው ልጃችን ዳሩልን" ብለው ይጠይቃሉ። የልጅቷም ቤተሰቦችም በወጉ መሰረት ልጃቸውን ሊድሩ ይስማማሉ።

ሰርግ ይደገሳል። ሟች ሙሽራ በሌለበት የሞቀ ድግስ ይደረጋል። ሙሽሪትም በይፋ የሟች ሚስት መሆኗ ይረጋገጣል።

ሴቷ የሚስትነት ወግ ጠብቃ መኖር ትጀምራለች። በተዘጋጀላት መኖሪያ የሴትነትን ሃላፊነቷን እየተወጣች ኑሮዋን ትገፋለች።
በተዘጋጀላት ቤት የሟች ሚስት ሆና በምትኖርበት ጊዜ እንግዳ የማስተናገድ ሃላፊነት ይጠብቃታል።
እንግዳው የሟች ወንድም ወይም የቅርብ ዘመድ ነው። በምሽት ወቅት ማንነቱ እንዳይታወቅ ተጠንቅቆ በጨለማ ወደ ሴቷ መኖሪያ ይገባል። የእንግዳው መምጫ ምክኒያት ምን እንደሆነ ስለምታውቅ ጭኗን ከፍታ ራሷን ትሰጠዋለች። ባህል ነውና ከሟች ዘመድ መካከል አንዱ እንደሚሆን ከሚገመተው ሰው ጋር ወሲብ ትፈፅማለች።

'አይሆንም' ማለት አይፈቀድላትም። ሰውዬውን አልፈልግም ለማለት የምትችለው በአንድ ልዩ ሁኔታ ብቻ ነው። ሰውዬው ሲመጣ አስቸጋሪ አመል ካየችበት 'ሂድልኝ' ብላ ልታበረው ስልጣን አላት። ነገር ግን በሱ ምትክ ሌላ ወንድ ሲመጣ ልታስተናግደው ትገደዳለች።

በዚህ መንገድ አብራው ከምትተኛው ወንድ ፅንስ የሚፈጠር ሲሆን የተወለደው ልጅ ህጋዊ አባት ተደርጎ የሚቆጠረው ሟች ነው። የተኛት ወንድ ለሚወለደው ልጅ እንደ አባት አይቆጠርም፥ ሴቲቱን እንደ ባል አይንከባከባትም፥ አንዳች ሃላፊነት አይኖርባት፥። ምሽት ሲሆን በስውር ወደቤቷ እየመጣ ይገናኛታል። ሴቷ ይሄን ሁሉ በፈቃዷ እንድትከውን ባህል ያስገድዳታል።
የሴቲቱ ሚስትነት ለሞተ ሰው ነው። ለተወለደው ልጅ አባት ተደርጎ የሚቆጠረውም ሟች ነው። "የማን ልጅ ነው?" ቢባል "የሟች ልጅ" ይባላል።

(ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ "ያልተቀበልናቸው" በሚለው መፅሐፉ 'የደቡብ ኦሞ ክራሞቴ' የሚል የጉዞ ማስታወሻ የፃፈ ሲሆን ይህን ያልተለመደ ልማድ በማስታወሻው አካቶታል።

Nb ፥ ይህ ፅሁፍ የዛሬ ሁለት አመት አጋርቼው የነበረ ሲሆን ዛሬ ድጋሚ እያጋራሁት ነው።


@Tfanos
👍2🤔2
በሰሞንኛው መጨቃጨቂያ ጉዳይ ይህ ፅሁፍ የመጨረሻዬ ነው።

የኔ ጥቅል አቋም ግልፅ ነው።

ሀ፥ ሰዎች መብታቸው ፥ ሰብአዊ ክብራቸው ሊጠበቅላቸው ይገባል። ከዚህ ተፃራሪ የሆነ ነገር በጣም ያሳስበኛል። ሴቶች ላይ የሚደርሰውም ጥቃት የሚያሳስበኝ "ሰብአዊ ክበር ሊደፈር አይገባም" ከሚለው መሰረታዊ እሴቴ ነው።

ለ፥ እዚህ ሐገር ባህል ፥ ፖለቲካ ፥ ሲስተሙ ወዘተ ሴቶች ላይ ከፍተኛ ጫና እና በደል ያደርሳል። ይሄ የማይካድ ሐቅ ነው። አንዳንድ የመብት ተሟጋች ነን ባዮች የሚሰሩት ጥቃቅን ስህተት ይሄን ሐቅ ሊጋርድብን አይገባም። መሰረታዊው ሐቅ ሴቶች ይበደላሉ።

ሐ፥ ማንም ሰው የፌሚኒዝምን እንቅሰቃሴ ቢቃወም ችግር የለብኝም። (በነገራችን ላይ እኔም ፌሚኒዝም ላይ ብዙም እምነት የለኝም) ነገር ግን አንድ ሰው ስለ ሴቶች ጥቃት ባወራ ቁጥር ፌሚኒዝምን እየታከኩ መብት ለመደፍጠጥ መሞከር የልብ ክፋትን ያሳያል።

ከላይ ያለውን ፖስት ያጋራሁት ባህል ሴቶች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በመጠኑ ካሳየ ብዬ ነው።

በዚህ ጉዳይ ድጋሚ ላለመጨቃጨቅ ቃል እገባለሁ!
👍71
"ፈረንሳያዊው የኢትዮጵያ ቅርሶች ጠበቃ"
(ተስፋኣብ ተሾመ)
* * *

ዣክ ሜርሲዬ ይባላል። ፈረንሳያዊ የስነ-ሰብዕ ተመራማሪ ነው።
ሰውዬው በ1964 ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ በመምህርነት አገልግሏል። ለ40 አመታት ያህል ኢትዮጵያን እና ባህሏን መርምሯል።
ስለደብተራዎች አጥንቷል፥ ስለክታብም መፅሐፍ ፅፏል፥ ኢትዮጵያዊ ስዕሎችን መርምሯል፥ ዛርና ውቃቢም የጥናቱን ትኩረት ማግኘት ችለዋል።

ከቀናት በአንዱ የጣና ሃይቅ ደሴቶችን ሲጎበኝ አንዳች ጉድለት እንደነበረ አስተዋለ። "መስቀሉ የት አለ?" ብሎ አስጎብኚዎችን ጠየቀ። ከአመታት በፊት ጣና ሃይቅ ያሉ ገዳሞችን የጎበኘ ጓደኛው እዛ የሚገኝ የቅዱስ ያሬድ መስቀልን ፎቶ አንስቶ አሳይቶት የነበረ ሲሆን በምስል የወደደውን ቅርስ በአካል ሊያገኘው ጓጉቶ የነበረ ቢሆንም አስጎብኚዎቹ "የምትለው መስቀል የት እንደሚገኝ አናውቅም" በማለት አረዱት። መስቀሉ ጠፍቷል !

ሌላ አጋጣሚ

ሰውዬው በሃዘን ወደ አውሮፓ ከተመለሰ በኋላ በአንድ ሐገር የሚገኝ የቅርሳቅርስ ስብስቦች እየጎበኘ ሳለ ትኩረቱን የሳበ ነገር ተመለከተ። ከኢትዮጵያ የተወሰደውን የቅዱስ ያሬድ መስቀልን አገኘ። ከዚህ በኋላ ያለው ሂደት ወስበሳቤ የድርድር መንገድን የፈለገ ነበር።

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የቅርሱ ባለቤት ብትሆንም ይህን በሕግ ፊት የሚያፀና የሰነድ ማስረጃ የለም። ዣክ ሜርሲዬ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ይዞት ቢሄድ በአጭር እንደማይቋጭ አውቆታል። ይህን በመገንዘብ መደራደርን እንደመፍትሄ ቆጠረ። ስለዚህ መስቀሉ የኢትዮጲያ መሆኑን በማሳወቅ እና ክፍያ በመፈፀም ማስመለስን አማራጭ አደረገ። ትውውቁን በመጠቀም እንግሊዝ ሐገር ወደሚገኝ በጎ አድራጊ አቀና። እርዳታ በመጠየቅ ያገኘውን ገንዘብ ክፍያ አድርጎ በመክፈል ቅርሱን ለኢትዮጵያ አስመለሰ።

(ቅርሱን ሲያስመልስ ወሳኝ ስምምነት ተደርጓል። ለኢትዮጵያ ቅርሱን የመለሰው ሐገር እና ግለሰብ ስማቸው እንዳይጠለሽ ሲባል እንዳይጠቀሱ ተዋውለዋል)

ፈረንሳያዊው ተመራማሪ ለአርባ አመታት ያህል የሚያውቃትን ኢትዮጵያ ይወዳታል። ቅርሷቿ ሲዘረፉም ቅር ከመሰኘት አልፎ እንዲመለሱ ይታትራል። ይሄን ሲያደርግ በባለቤትነት ስሜት ነው።

በአንድ ወቅት በአሮፓ የሚገኝ ሙዚየም ሲጎበኝ በቁጥር ብዙ የሆኑ የኢትዮጵያ ቅርሶችን ተመለከተ። ሐላፊዎቹን አናግሮ ካግባባ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጣ። "ተደራድረን ቅርሱን እናስመልስ'' አለ። ምላሹ ግን አሳዛኝ ነበር። ''ቤተክርስቲያን እንዴት ከሌባ ጋር ትደራደራለች?'' የሚል መልስ ተሰጠው። በዚህ የተነሳ የማስመለሱ ውጥን ከሸፈ።
''ሌቦችን በመስደብ የሚመለስ ቅርስ የለም፥ መፍትሔ መሆን ያለበት ብልሃትና ድርድር ነው'' የሚል አቋም አለው።

ሌላ ጊዜ ደግሞ ለጋሾችን አናግሮ 250 ሺ ዶላር ማስፈቀድ ቻለ። አላማው በትግራይ የሚገኙ ቅርሶችን ሰብስቦ በአንድ ሙዚየም ማስቀመጥ ፥ መንከባከብ እና ለጎቢኛዎች ክፍት ማድረግ ነበር። ሆኖም ግን በወቅቱ የባህል ሚኒስቴር ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ሹማምንት እቅዱ እንዳይሰምር አደረጉ። በግል መጠቀም ፈልገው የነበረ ሲሆን ይሄ ስላልሆነላቸው ''ከሱጋ መስራት አንፈልግም'' በማለት ነገሩን አበላሹት።

ሰውዬው "Ethiopia Church ፡ Treasure And Faith" የሚል ሐገራችንን የሚመለከት መፅሐፍ አለው።


@Tfanos
3👍3
Hiv በደሙ ውስጥ ያለበት ጓደኛ አለኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ HIv እንዳለበት ሲያውቅ የተሰማውን መጥፎ ስሜት አስታውሳለሁ። ድንጋጤ ፥ ሐዘን ፥ ፀፀት እና ተስፋ መቁረጥ እየተፈራረቁ በቡጢ ሲነርቱት ነበር።

ድንጋይ ላይ ቁጭ ብለን "ጨንቆኛል" አለኝ። ጭንቀቱን ከማስረዳቱ በፊት ማልቀስ ጀመረ።

አውቀዋለሁ። የልቡን ንፅህና አውቀዋለሁ፥ ታታሪነቱን አውቃለሁ ፥ ለሰው ያለውን ክብር አውቃለሁ ፥ ህልሙን አውቃለሁ። ያን ሰሞን በአንዳች አይነት ምክኒያት እንደተደበረ ገብቶኝ ነበር። ደጋግሜ የሆነውን እንዲነግረኝ ስጠይቀው ይሸሸኝ ነበር።

ድንጋይ ላይ ተቀምጠን ያወራን ምሽት አቀርቅሮ እያለቀሰ "HIV ኤዲስ ይዞኛል" አለኝ። ለቅሶው ውስጥ የልቡ ስብራት ታይቶኛል።

በማግስቱ መድሃኒት እንዲጀምር አግባባሁት።

ዛሬም ድረስ ከተሰወረበት የሚገለጥ ፀፀት ይለበልበዋል። ራሱን ይወቅሳል።

ህይወት እንዲህ ናት። ቀላል መስሎ የሚታዩ ግድ የለሽነቶች እድሜን የሚከተል ፀፀት ያስከትላሉ። ጥቂት ስሜታዊነት ህይወት ያስከፍል ይሆናል።

አንዳንዴ በቀላሉ ሊታረም የሚችል ስህተት በቀላሉ የማይስተካከል የህይወት ብልሽት ያስከትላል።

በHiv መያዝን የሁሉም ነገር መጨረሻ እያስመሰልኩ አይደለም።

ያ ጓደኛዬ ውጤቱን በሰማ ጊዜ ገብቶበት የነበረውን የተስፋ መቁረጥ አዘቅት አስታውሳለሁ። መሞትን ተመኝቶ ነበር። ማህበራዊ ግኑኝነቱ አደጋ ላይ ወድቋል።

ዋጋ የከፈልንበትን ነገር እንፈትሸው። ራሳችንን በሐቅ ሚዛን እንመዝን። ብዙዎቻችን በጥቂት ስሜታዊነት ብዙ ዋጋ ከፍለን ፥ ትንሽ ለመታገስ ባለመፍቀድ ግዙፍ ነገር አጥተናል ፥ ተራ በሚመስል ስህተት ታላቅ ነገር ተቀምተናል።

ማንንም መምከር አልፈልግም። ሰው ለመምከር የሚበቃ የህይወት ልምድ የለኝም። ይህ እንደተጠቀ ሆኖ ፥ ሁልጊዜም ጥቂት ስሜታዊነት ፥ ትንሽ ስህተት ብዙ ሊያስከፈል እንደሚችል ማሰብ አለብን እላለሁ።


@Tfanos
18👍4😢4🔥1
ጌታቸው ረዳ "የትግራይ ሊብራል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ" የሚባል ፓርቲ ሊያቋቁም ነው።

ያልገባኝ ነገር የብሔር ፓርቲ እና ሊብራሊዝም አብሮ ይሄዳል ወይ የሚል ነው? ማን ያውቃል ሊሄድም ይችላል። (ለሚያምን ሁሉ ይቻላል ቃሉ ስለሚል ይቻል ይሆናል

ብልፅግና ፓርቲ "ደሃ ተኮር ካፒታሊስት ነኝ" ብሎ ነበር። ብዙ ነገር የማይገባኝ ሰው ስለሆንኩ ደሃ ተኮር ካፒታሊዝም እስከአሁን አልገባኝም። (ማን ያውቃል ሀብታም ተኮር ሶሻሊዝም የሚባል ነገር ይኖር ይሆናል። እኔ አልገባኝም ማለት የለም ማለት ላይሆን ይችላል

ነገር ቶሎ የሚገባችሁ ሰዎች ብሔርተኝነት እና ሊብራሊዝምን ምን እንደሚያገናኘው አስረዱኝ 😎
🤔3
"ሜሲ እና ሮናልዶ"
(ተስፋኣብ ተሾመ)
* * *

ይህ ፅሁፍ እግር ኳሳዊ ትንታኔ አይደለም። በዚህ ተስማምተን እንጀምር

ሁለቱ በድምሩ 13 ጊዜ ባሎንዶር አሸንፈዋል። የእግር ኳስ ጣኦቶች ናቸው። ቁጥራዊ ስኬታቸው ከግለሰብ በላይ የላቁ አድርጓቸዋል። በእግር ኳስ ማሳካት ያለባቸውን ሁሉ አሳክተዋል ቢባል ግነት አይደለም።

ሁለቱ የምንግዜም ምርጥ እግርኳሰኞች ናቸው።

አልዓዛር አስግዶም "እግር ኳስ ቅሪላ ማልፋት ብቻ አይደለም" ይላል። መማር ለሚፈልግ ከእግርኳስ የሚመዘዝ የህይወት ትምህርት አለ።

ስኬት እና ዝና ጠልፎ ጣይ ነው። የአስተዳደር እውቀትን ይፈልጋሉ። ሰዎች ስኬታቸውን በአግባቡ ማስተዳደር ሲያቅታቸው በገዛ ስኬታቸው ይደናቀፋሉ። ዝና ወለድ ጣጣን የማያስተዳድሩ በዝናቸው ይደናቀፋሉ።

ዝና እና ስኬት የአደር ባይ ጭብጨባን እና ምክኒያት የለሽ ጥላቻን ያስከትላሉ። ሰዎች ስኬታማ በሆኑ ቁጥር ያለሰበብ ሊጠሉ እንዲሆም ያለ አግባብ የተጋነነ ጭብጨባን ያስተናግዳሉ። ሁለቱም አደጋን ያመጣሉ።

የአደር ባይ ጭብጨባ ግብዝ ያደርጋል። "ጨረቃ በቁጥጥሬ ነች" ያስብላል። ትምክህት ውስጥ ይከታል። ትምክህት ደግሞ ጠልፎ ይጥላል።
ምክኒያት የለሽ ጥላቻም ጣጠኛ ነው። ስኬታማ ሰዎችን ፥ ዝነኞችን ፥ ሀብታሞችን... ያለሰበብ የሚጠሉ አሉ። እንዲህ ያለ ነገር ሲደጋገም ስኬታማዎቹ ፥ ዝነኞቹ... ከህብረተሰቡ ፀብ ይገጥማሉ። ተናካሽ እና መራራ ይሆናሉ። ይህም ጠልፎ ጣይ ነው።

የነገራችን መነሻ ሮናልዶ እና ሜሲ ናቸው።

ሁለቱ ሰዎች ገና ወጣት ሳሉ ጀምረው ደምቀዋል። ከለጋነታቸው ዘመን ጀምሮ ስኬትን ሲጎናፀፉ ኖረዋል። ስኬታቸው ጥጋብ አልፈጠረባቸውም። የኋላቸውን እየረሱ ከፊታቸው ያለውን ለመያዝ ይዘረጉ ነበር። ጫና ውስጥ በሚከት ሁኔታ ውስጥ እንኳን ትኩረታቸው ስራቸው ላይ ነው።

በሚዲያ ዘመቻ ቢከፈት ፥ የአድናቆት ዶፍ ቢዘንብላቸው ፥ የትቸት መኣት ቢያስተናግዱ ከስራቸው አይዘናጉም። ተግተው ይሰራሉ።

የቀድሞው መድፈኛ እና ጀርመናዊ ተከላካይ ፔር ሜርት ሳከር የአለም ዋንጫን ያሸነፈው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አባል ነበር። ከአለም ዋንጫ ድል በኋላ ከአእምሮዬ የማይጠፋ ነገር ተናገረ። "አለም ዋንጫ ካሸነፍኩ በኋላ ለሌላ ድል መነሳሳት ከበደኝ" አለ። ትልቁን ድል ካሳካ በኋላ ለሌላ ድል መራብ አልቻለም። ተግቶ መስራት ከበደው።

ተወዳጅ መፅሐፍ ከፃፉ በኋላ ማንበብ ያቆሙ ስንት ናቸው? ተቀባይነታቸው ሲጨምር ከትጋት የጎደሉት ምን ያህል ናቸው?

በሐይማኖት መድረክ ፥ በኪነጥበብ አለም ፥ በቢዘነስ ወዘተ... የሆነ ስኬት ላይ የደረሱ ሲመስላቸው ከትጋት የጎደሉት ምን ያህል ናቸው?

ሮናልዶ እና ሜሲ ከእግር ኳስ ተጫዋችነታቸው በተጨማሪ የሚያስተምሩን የህይወት ትምህርት አለ። ያ ትምህርት "በገዛ ስኬት አለመደናቀፍ" ይባላል።

የቀደመውን እየረሱ ከፊት ያለውን ለመያዝ የመዘርጋት ትምህርት!


@Tfanos
👍11
አርሰን ቬንገር ፥ አርሰናልን እንድጠላ ያደረገኝ ሰው!
(ተስፋኣብ ተሾመ)
* * *

እግር ኳስ ማየት የጀመርኩት በልጅነቴ ነው። አባቴ ኳስ ሊያይ ሲሄድ ይዞኝ ይሄዳል። አባቴ የአርሰናል ደጋፊ ስለነበር በብዛት የሚያየው የአርሰናልን ጨዋታ ነበር።

በሂደት ሄነሪን ወደድኩት። ኳስ አገፋፉ ፥ አሯሯጡ ፥ አጨራረሱ ፥ ደስታ አገላለፁ ደስ ይላል። ከሄነሪ በላይ ተጫዋች የለም አልኩ። ሄነሪ የሚጫወትበትን ቡድን ወደድኩት።

ከሻንፒዮንስ ሊግ ምሽቶች በአንዱ የባርሴሎናን ጨዋታ ልናይ Dstv ቤት ከአባቴጋ ሄደን። ያን እለት ከሄነሪ በላይ ምታተኛ ሰው እንዳለ አመንኩ። ሮናሊዲንሆን ወደድኩ። ያኔ ከአርሰናል እና ከባርሴሎና በላይ ማንን መውደድ እንዳለብኝ ግራ ገባኝ።

እግር ኳስን እንድወድ ያደረጉኝ ሄነሪና ቬንገር ናቸው። ቬንገር ቡድኑን የገነባበት መንገድ እና የሄነሪ አጨዋወት በእግር ኳስ ፍቅር ጣለኝ።
ሮናሊዲኒሆ እና ሄነሪ ደግሞ ለባርሳ እና አርሰናል እኩል ፍቅር እንዲኖረኝ አደረጉ። በሂደት ግን ቀንደኛ የአርሰናል ደጋፊ ሆንኩ። ምክኒያቱ ደግሞ አይተኬው አርሰን ቬንገር ነበር!

ብዙ ሰው የጋርዲዮላን ባርሳ እንደሚያደንቅ አውቃለሁ። ከጋርዲዮላው ባርሳ በላይ የ2008ቱ አርሰናል ይበልጥብኛል።
ሂሌብ ፥ ፋብሪጋስ ፥ ትንሹ ሞዛርት (ሮዛ) ፥ ፍላሚኒ የነበሩበትን አርሰናል የሚያህል ቡድን አላየሁም።

ያ ቡድን ኳስን ዝም ብሎ በመቀባበል ብቻ አያሰለችም። ፈጣን ሽግግር አለ፥ ብዙ ይቀባለበላሉ ፥ ብዙ ኳስ ይሞከራል፥ የግል ተሰጥኦ እንደልብ ይታያል። በተለይ ሂሌብ እና ኤድዋርዶ እንደ ጎመን ሲተጣጠፉ ማየት ደስ ያሰኛል።

ሀይለኛ የአርሰናል ደጋፊ ነበርኩ።

ቬንገርን እንደ አሰልጣኝ ብቻ ሳይሆን እንደ ሰው እወደዋለሁ። የህይወት ፍልስፍናው ይገርመኛል። ለሰው ያለው ክብር ይደንቀኛል። ሰውን እንደ ሰው የሚያከብር ሰው ደስ ይለኛል። ቬንገር እንደዛ ነው።

ካርዞላ ፥ ትንሹ ሞዛርት ፥ ዲያቢ ፥ ዌልሻየር ፥ ቫንፔርሲ ፥ ቨርማለን... ጉዳት ይፈራረቅባቸው ነበር። በዛን ወቅት ቬንገር ተጫዋቾቹን እንደ ሰው ያከብራቸው ነበር። ስለሚጎዱ አውጥቶ ለገበያ አላቀረባቸውም። "ለእኛ ሲጫወቱ ነው የተጎዱት። እንደ ማይጠቅም እቃ አንወረውራቸውም" ይል ነበር። ማንንም በክፉ ቀን አውጥቶ አልጣለም።

ደግሞ አይኖቹ የንስር ናቸው። ከሄነሪ እስከ ፋብሪጋስ በንስር አይኑ ተመልክቶ መልምሏቸዋል። ከማንምነት ወደ ታላቅነት አሸጋግሯቸዋል።

ሃላፊነት ይወስዳል። አንድ ቀን አርሰናል በሊቨርፑል በአሰቃቂ ሁኔታ ሲሸነፍ "ሃላፊነቱን እወስዳለሁ" አለ። ያኔ ዋልኮት "እስከመቼ ሃላፊነቱን ሌላ ሰው ይወስዳል? ጥፋቱ የኛ የተጫዋቾች ነው" አለ። ቬንገር በውድቀት ወቅት ተጫዋቾቹን ለሚዲያ አያጋልጥም። ሲሸነፉ ራሱ ሃላፊነት የሚወስድ ታላቅ መሪ ነው።

አንድ ጊዜ ፔር ሜርትሳከር ቬንገርን "የምትወደው ቃል ምንድነው?" ብሎ ጠየቀው። ቬንገርም "ፍቅር" ብሎ መለሰ።

አርሰናል የፋይናንስ ቀውስ ነበረበት። በዛን ወቅት ከቬንገር የሚጠበቀው በ8 አመት 4ቴ ለሻምፒዮንስ ሊግ መሳተፍ ብቻ ነበር። የአርሰናል ሪሶርስ ከዛ በላይ የሚፈቅድ አልነበረም። የስታዲየም እዳ ለመክፈል በየአመቱ ከዋክብቱን እየሸጠ በ2 አመት አንዴ በሻምፒዮንስ ሊግ ቢሳተፍ እንደ ትልቅ ስኬት ይቆጠርለት ነበር። ቡድኑም ከቬንገር የጠየቀው ይኸን ብቻ ነው። ቬንገር ግን ከተጠየቀው በላይ ሰጠ። ቡድኑን ተፎካካሪ አደረገው።

ከዛስ?

ደጋፊው የቬንገርን ውለታ ካደ። የቬንገር ስራ ላይ ጥላሸት ተቀባ። አርሰናል ከቬንገር በፊት ቦሪንግ ቦሪንግ አርሰናል ይባል ነበር። ቬንገር ግን ብራንድ አጨዋወትን በውስን ሃብት አሳየ። ሆኖም ግን ተካደ።

ደጋፊው ስቴዲየም ውስጥ ታላቁን ሰው ሰደበ። ደጋግመው ተቹት። በየጫወታው ተሳለቁበት። ቡድናችንን ይልቀቅ አሉ።
በመጨረሻም ቬንገር ለቀቀ

የቨንገርን የመጨረሻ ጨዋታ ያየሁት ከእንባዬ እየታገልኩ ነው። የቬንገር ስንብት ፥ የክሎፕ ስንብት ፥ የኢኒየስታ ስንብት ፥ ሜሲ ከባርሳ ሲሰናበት ከእንባዬ ታግያለሁ።

ቬንገር ከአርሰናል እስኪለቅ የአርሰናል ወዳጅ ነበርኩ። ቬንገር ከለቀቀ በኋላ ቡድኑን ጠላሁት። አርሰን ቬንገር ተገፍቷል ብዬ ስላመንኩ አርሰናልን ጠላሁት።
ከቬንገር ስንብት በኋላ አርሰናል ላይ የምትቆጠር እያንዳንዷ ጎል ስታስደስተኝ ራሴን አገኘሁት።

አሁን በተለየ የምወግንለት ቡድን የለም። ባርሳ እና ሊቨርፑል ሲሳካላቸው ማየት ያስደስተኛል።

ቬንገር አርሰናልን ከለቀቀ በኋላ ዩናይትድን እንዲያሰለጥን ተመኝቼ ነበር። ምኞቴ ቢሳካ ኖሮ የዩናይትድ ደጋፊ እሆን ነበር።

ለማንኛውም ይሄ ፅሁፍ ስለ ቬንገር ከሚሰማኝ ውስጥ አንድ ፐርሰንት ብቻ ነው። አንድ ፐርሰንት ብቻ!! 99 ፐርሰንት የሚወራ ነገር ይቀረኛል።

ሜርሲ አርሰን


@Tfanos
ዛሬ በዩቲዩብ ቻናላችን ስለሴቶች ጥቃት እናወራለን።

የሴቶችን መጠቃት መቃወም ያለብን ለምንድነው? የተወሰኑ ጠቃሚ ሃሳቦችን እናነሳለን።

አስተያየት ያካፍሉ፥ ለሌሎችም ያጋሩ።


https://youtu.be/5EBgK2JXZOQ
👍3
የዛሬ የደርዘን ጥያቄ እንግዳ የቀድሞዋ ጋዜጠኛ የአሁኗ ፖለቲከኛ ሚስጥረ ስላሴ ታምራት ናት።

ሚስጥረ-ሥላሴ ከዚህ ቀደም በአሻም ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ የነበረች ሲሆን በአሁኑ ወቅት የኢህአፓ ዋና ፀሐፊ ናት።

ሚስጥረ በሚዲያው ውስጥ ባለው ችግር "ዋነኛው ጥፋት የጋዜጠኞች ነው" ትላለች። በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተወያየን ሲሆን ይህ ክፍል አንድ ነው።

በነገራችን ላይ የዛሬው ቆይታ በአዲስ ስቱዲዮ የተደረገ መሆኑ ለየት ያደርገዋል 😀

አስተያየት አካፍሉ ፥ ለሌሎችም አጋሩ።

https://youtu.be/hlKa1ZaNK8k?si=hnOP8FnetV1yV7Z3
ቲክቶክ ላይ "ቸርች አልሄድም" የሚል ቪዲዮ አንዲት ሴት ሰርታ አየሁ። ምክኒያት ብላ ያቀረበችው ደግሞ "ጌታን በግሌ አግኝቻለሁ" የሚል ነው። የገረመኝ ነገር ብዙ ሰው ሃሳቧን ደግፎታል።

Well እኔም ቸርች መሄድ ካቆምኩ አመታት ተቆጥረዋል። ቤተክርስቲያን ለመሄድ ተነስቼ በር ላይ ከደረስኩ በኋላ ትቼ የተመለስኩበት አጋጣሚ ብዙ ነው። መፀለይ ከተውኩ በትንሹ ሰባት አመት ያልፈኛል። አልፎ አልፎ ብቻ መፅሐፍ ቅዱስ አነባለሁ። መዝሙርን ለመልእክትነቱ ማድመጥ እየተወኩ ነው። ወዘተ...

ይህ ሁሉ ቢሆንም

ቤተክርስቲያን ላለመሄድ ሰበብ የሚመስሉ ነገሮች ቢኖሩም ራስን ልክ ለማድረግ ሌላ ጥፋት መፈፀም የለብንም።

ለአንድ ክርሰቲያን ህብረት ማድረግ መሰረታዊ ነገር ነው። ህብረት ማድረግ ፥ መፀለይ እና መፅሐፍ ቅዱስን ማጥናት መሰረታዊ ጉዳይ ነው። ከዚህ አንዱን መተው ጉድለት ይፈጥራል። ከመንፈሳዊ ህይወት የሚያጎድለው ነገር አለ።

አንድ ሰው ቤተክርስቲያን መሄድ ቢያቆም ልፈርድበት እቸገራለሁ። የትምህርት ችግር ፥ የአምልኮ ስርአቱ፥ የአገልጋዮች አስመሳይነት ፥ የቸርች ፖለቲካ፥ ከመፅሐፍ ቅዱስ የተጣላ ስብከት ፥ የአማኙ ግብዝነት... ወዘተ ልብ ያወርዳል። በዚህ የተነሳ የእምነት ተቋማት ለመሄድ ልባችን የዛለ ሰዎች አለን።

ቢሆንም ግን...

ቤተክርስቲያን መሄድ ማቆምን እንደ ትክክል አስመስሎ ማቅረብ ግልፅ ጥፋት ነው። "ቸርች እየሄድኩ አይደለም" ማለት አንድ ነገር ነው። ነገር ግን ያለመሄድ ምንም እንደማያጎድል አስመስሎ መናገር እና ነገሩን ትክክል ለማስመሰል ጥቅስ ማፈላለግ ስህተት ነው።

ክርስቲያን ነኝ የሚል ሰው ክርስቲያናዊ ህብረትን ማክበር አለበት። ህብረት ማድረግ ቢያቅተው እንኳን ሕብረት አለማድረጉን ትክክል አስመስሎ ማቅረብ የለበትም።

የገዛ ደካማነትን ለማዋዋብ መሞከር ሌላ ውድቀትን ይወልዳል። ደካማነትን ማማን ጥሩ ነው።

...

ምንድነው የፃፍኩት? ፀባረቅኩ ይሆን?


@Tfanos
🔥13👍4👎32
"አርበኛ ማሚቴ"
(ተስፋኣብ ተሾመ)
* * *

በጣሊያን ወረራ ዘመን 'አንገዛም' ያሉ የኢትዮጲያ ልጆች ከጠላት አንገት ለአንገት ተናንቀዋል። በዚህ ወቅት ወደ ውጊያ ሜዳ ከወረዱ የኢትዮጵያ ጦር መካከል አንዱ በጠላት ተከበበ፥ ይኼኔ ችግር መጣ። ከበባው ለቀናት የዘለቀ ስለነበር ስንቅ አለቀ። አርበኞቹ መብልና መጠጥ አጡ። የውሃ ጥምና ረሃብ ትጥቅ ሊያስፈታቸው ሆነ። 'እጅ መስጠት ወይም በረሃብ መሞት' የሚሉ ፈታኝ አማራጮች ተደገኑ። በዚህ የጭንቅ ወቅት አንዲት ሴት የመፍትሔ ሰው ሆና ተከሰተች።

"ማሚቴ" ትባላለች። ስዕል ከሚመስል ውበቷ በቀር ስለሷ ዝርዝር መረጃ የለም።ሽንጠ ረጅም እና ባለ ዞማ ፀጉር ነች። ቀጪን ወገብ እና ውብ መቀመጫ አላት። ጡቶቿ የተወደሩ ከንፈሮቿ ሞላ ያሉ ናቸው። ይህች ቆንጆ ወጣት አርበኞቹን ከጭንቅ ታድጋቸዋለች።

በጭንቅ ያለውን ሰራዊት "አይዟችሁ" ትላለች። በቃል ካፅናናች በኋላ ትታቸው ትሄዳለች። ከሄጀችበት ባዶ እጇን አትመለስም። የሚበቃ ምግብና መጠጥ ታመጣለች።
ከየት እንደምታመጣው ማንም አያውቅም። ነገር ግን በተደጋጋሚ አርበኞቹ በረሃብ ትጥቅ እንዳይፈቱ አድርጋለች። እርሷ ባትኖር አርበኞች በረሃብ እና በውሃ ጥም ያልቁ ነበር፥ ወይም በተስፋ መቁረጥ እጅ ይሰጣሉ። ነገር ግን በማሚቴ መኖር የተነሳ አርበኛው እንዳይፈታ ሆነ።

"አይዟችሁ" ትላለች በፈገግታ። ራቅ ብላ ትሄድና ከግማሽ ቀን በኋላ የሚበላ እና የሚጠጣ ታመጣለች። 'ከየት ነው የምታመጣው?፥ በጣሊያን ወታደሮች ከበባ የተነሳ ለአደጋ ያልተጋለጠችው ለምንድነው?' ይሄን የሚያውቅ የለም።

አንዴ ብቻ ለአደጋ ተጋልጣ ታውቃለች። በሞቀ ጦርነት መሓከል በድፍረት ወደ ውሃ ጉድጓድ ስታቀና ቦንብ ጣይ አውሮፕላን በቅርብ እርቀት ቦንብ ጥሎ በተአምር ተርፋለች። ከዚህ አጋጣሚ በቀር የከፋ አደጋ ሳይገጥማት አርበኞችን ስታገለግል ቆይታለች።

ይህች ሴት በአልሃንድሮ ዴልባዪ ከተፃፈላት ግማሽ ገፅ ፅሁፍ በቀር ሌላ የተፃፈ ታሪክ የላትም።


@Tfanos
4👎1
አያቶቻችን ዳር ድንበር አናስደፍርም ብለው አጥንቶቻቸውን ከሰከሱ። ደማቸውን አፈሰሱ። አምስት አመታት ሙሉ በዱር በገደል ሲፋለሙ ከቆዩ በኋላ ሀገር ነፃ ወጣች።

አያቶቻችን ዳር ድንበር ለማስከበር ተፋለሙ።

ዘሬ ጎረቤት ዳር ድንበራችንን ተከፋፍለውታል። ግዛታችን ተደፍሯል። ሚጢጢዋ ሐገር ጅቡቲ አፋር ውስጥ የአየር ጥቃት ያደረሰችው በቅርቡ ነበር። ትላንት ከኢትዮጵያ የተገነጠለችው ኤርትሪያ ዛሬም ድረስ ግዛታችንን ተቆጣጥራለች። ሻቢያ ትላንት የትግራይ ወጣቶችን በመደዳ ሲገ*ድል ከቆየ በኋላ ዛሬ ደግሞ የትግራይን መሬት ወስዷል።

የጎረምሳ እድሜ ያላት ደቡብ ሱዳን በአቅሟ ግዛታችንን ተዳፍራለች። ከደቡብ ሱዳን የሆኑ ታጣቂዎች 200 Km ወደ ግዛታችን ገብተው የተፈጥረው ሃብት ይዘርፋሉ ፥ ዜጎችን ይገድ*ላሉ።

ሱዳን አልፋሽጋን ከጠቀለለች ውላ አደረች። "ሱዳን የኢትዮጵያን ግዛት የወረረችው በጠቅላይ ሚኒስተሩ ግብዣ ነው" የሚል ዘገባ ከወጣ የቆየ ቢሆንም ከመንግሥት ወገን የረባ ምላሽ አልተሰጠም።

ዛሬ የጀግኖች አርበኞች ቀን መታሰቢያ ነው። አያቶቻችን ዳር ድንበር አናስደፍርም ብለው ከፋሽ*ሽት ተፋልመው ሉአላዊነታችንን ያስከበሩበት ቀን መታሰቢያ ነው።

ይህን ቀን የምናስበው ግዛቶቻችንን ለጎረቤት ሐገራት አከፋፍለን ነው....


@Tfanos
😢6
3ቱ መዝሙሮች የት ገቡ?
* * *

በመዝሙር ነው ያደግሁት። ወላይትኛ እና አማርኛ መዝሙሮችን አፈራርቄ በመስማት። ማንበብ ስችል ደግሞ የመዝሙር አልበሞች ላይ ያሉ የዝማሬ ግጥሞችን እያነበብኩ ከዘማሪው ጋር እዘምር ነበር።

ገና ህፃን ሳለው ጀምሮ የተለያዩ መዝሙሮች በቤታችን ይከፈታሉ። ቤታችን ባለው ቴፕ የኦዲዮ ካሴት መዝሙሮች ይከፈታሉ። ከወላይተኛ ዘማሪያን መካከል ዮሐንስ ባሰና ፥ ደስታ ቢራሞ ፥ ዮሐንስ ዳለቾ ከልጅነት እስከ ጉርምስና እድሜ ደጋግሜ የሰማኋቸው ዘማሪዎች ናቸው።

ከአማርኛ ደግሞ ተስፋዬ ጫላ ፥ ታምራት ሀይሌ ፥ ደረጀ ከበደ ዋነኞቹ ናቸው። እኛ ቤት ሊገባኝ ባልቻለ ምክኒያት የተስፋዬ ጋቢሶ የመዝሙር አልበም አልነበም።... ያሳዝናል!

ጥቂት መዝሙሮች ዛሬም ድረስ በአእምሮዬ የታተሙ ሆነዋል። "ያሻገረኝ በድል ያወጣኝ" "ገናናው የእኛ ኢየሱስ" "ዞር ብዬ ሳየው" "ኢየሱስ ነካኝ በድንገት" "ክብሩ ሰማያትን ሸፍኗል" ወዘተ ዛሬም ድረስ የሚነዝሩኝ መዝሙሮች ናቸው። ከወላይትኛ መዝሙሮች ደግሞ የሊዮን አልታዬ "ጦሳይ ኑጌ" የሚለው መዝሙር አይረሳኝም።

እናቴ ለፀሎት ስትንበረከክ የምትዘምራቸው ጥቂት መዝሙሮች አሉ። ወላይትኛ ናቸው። አባቴ ደግሞ ዮሐንስ ባሰናን ይወደዋል። የሱን የድሮ መዝሙሮች ደግሜ መስማት ፈልጌ አጥቻለሁ።

3መዝሙሮች አሉ። በጣም ደስ የሚሉኝ።

መዝሙር አንድ ፥ ልጅ ሆኜ ካለቀስኩ ዝም ማስበያ ፥ ሳምፅ ማስታገሻ ተደርጎልኝ የሚከፈት መዝሙር ነበር። ሰባት ወለደች መካኒቱ ይሰኛል።

"ሰባት ወለደች መካኒቱ
ሰባት ወለደች መካኒቱ
ጌታም አኖራት በቤቱ
ልጆች መንታ መንታ..."

የኦዲዮ ካሴት ታውቃላችሁ አይደል? መስማት የምትፈልጉበትን ቦታ በእስክሪብቶ በማጠንጠን ትከፍታላችሁ። ያን መዝሙር ከመውደዴ ብዛት እናቴና አባቴ ደጋግመው ይከፍቱልኝ ነበር። እያጠነጠኑ ይከፍቱልኛል። በዚህ የተነሳ የመዝሙሩን ትክክለኛ ቦታ ሸመደዱት። (ይህ አባባል ለዘመኑ ትውልድ አይገባም። በኦዲዮ ካሴት ዘመን የኖርን ሰዎች ክር ስለማጠንጠን ታውቃላችሁ አይደል? ይሄን ለሚሊኒየሙ ትውልድ አስረዱ

መዝሙር ኹለት ፥ መንሹ

"መንሹ በእጁነነው ፥ አውድማውን ፈፅሞ ያጠራል
ስንዴን በጎተራ ፥ ገለባውን ለእሳት ይሰጣል"

የዚህ መዝሙር ዜማው፥ የመዝሙሩ ጭብጥ ደስ ይለኝ ነበር። በልጅነቴ ደጋግሜ የሰማሁት ነው።

መዝሙር ሦስት ፥ ስለ መድህኔ

"ስለ መድህኔ ፥ ስለመድህኔ ፥ ስለመድህኔ
እኔም አለኝ የማወራው
እኔም አለኝ የምናገረው" እያለ ይቀጥላል።

የዚህ መዝሙር ዘማሪ ይመስለኛል ጎፈሬ ነው።

የሆነ ጊዜ የተወሰኑ የመዝሙር ካሴቶች ተበላሹብን። ምክኒያቱን አላስታውስም። ሦስቱ መዝሙሮችም ከተበላሹ የኦዲዮ ካሴቶቻችን ጎራ ሆኑ። በዚህ የተነሳ ደግሜ መስማት ሳልችል ቀረሁ።

ከላይ የተጠቀሱትን 3 መዝሙሮች የሰማሁት እድሜዬ ከአስር በታች ሳለ ነው። የሶስቱም መዝሙሮች ዜማ ዛሬም ድረስ ትዝ ይለኛል።

ካደግኩ በኋላ ሶስቱን መዝሙሮች ደግሜ መስማት ፈለግኹ። ሀይስኩል እያለው የዘማሪዎችን ስም እናቴን ጠይቄያት አታስታውስም።

3ቱ መዝሙሮች ብዙ ጊዜ ትዝ ይሉኛል። ደግሜ ብሰማቸው እመኛለሁ። የዘማሪዎቹን ስም ታውቁ ይሆን?

አዎ ፥የዚህ ረጅም ፅሁፍ ጥቅል ጭብጥ እኒያን 3 መዝሙሮች የሚያውቅ አለ ወይ ለማለት ነው።

የሚያውቅ ሰው በ @Jtesfaab ላይ ስማቸውን ቢነግረኝ አመሰግነዋለሁ
1👍1
ስለ #ነገን_ፍለጋ ፍለጋ ጥቂት...

"የራስን መፅሐፍ ማስተዋወቅ ከባድ ነው" ይላሉ እመው (በእርግጥ ብለው አያውቁም 😀

ነገን ፍለጋ የአጫጭር ልብ ወለድ ስብስብ ነው። 12 አጫጭር ታሪኮችን ይዟል። (መፅሐፍ ፆታው ወንድ ነው ሴት?)

በመፅሐፉ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ተዳሰዋል። በወላይታ የሚገኙ "አይሌ" የተሰኙ ማህበረሰቦች አሳዛኝ አኗኗር ፥ ራስን የማጥፋት ወረርሽኝ ከፖለቲካ ጋር ያለው ተዛምዶ ፥ ጦርነት እና ጦረኝነት በዘመናችን አውድ... በልብ ወለድ ተዋዝተው ተዳሰዋል።

የነገን ፍለጋ ጥቂት ኮፒዎች ቀርተዋል። ገርጂ ላላችሁ ታክሲ ተራ የሚገኘው "እውቀትን ፍለጋ መፅሐፍ ቤት" ይገኛል።

አንብቡት 😎
🔥51
እግር ኳስን የማይወድ ሰው እንዴት ያለ ጣፋጭ ነገር ቀረበት?

እግር ኳስ ምን ያህል ውብ ነገር ለመሆኑ ማስረጃ ካስፈለገ የዛሬው ጨዋታ ማስረጃ ሆኖ ይቀርባል።

ልብ ሰቃይ ድራማ ፥ ታለንት ፥ አልሸነፍ ባይነት ፥ አይገመቴነት ፥ አርት....

የዛሬውን ጨዋታ ማንም ቢያሸንፍ ፥ በታሪክ የማይረሳ ሆኖ ይመዘገባል።

እንኳን የእግር ኳስ ወዳጆች ሆንን!
🔥7👍3👎2😁1
ቅሪላ ማልፋት ፥ የፈረንጅ እርግጫ...
(ተስፋኣብ ተሾመ)
* * *

እግር ኳስን ለምን እንወዳለን?

እግር ኳስ ፥ጥጋበኛ ፈረንጆች ሜዳ ውስጥ ሲራገጡ ማየት የሚመስላቸው አሉ። እግር ኳስ ለእነሱ ቅሪላ ማልፋት ብቻ ነው።

"ማን እንደ ሆናችሁ የማያውቁ ሰዎችን ለምን ታያላችሁ?" ይሉናል። እኒሁ ሰዎች የሚያደንቁት የሐገር ውስጥ ጀግና አላቸው። የሚወዱት ኢትዮጵያዊ አለ። ሚኒሊክን አሊያም መለስ ዜናዊን ፥ ጥላሁንን ወይም አሊቢራን ፥ በአሉ ግርማን ካልሆነ ፀጋዬ ገብረመድህንን ይወዱ ይሆናል።

ፈረንጅ በማድነቅ እና ሐበሻ በማድነቅ መሐካል ያለው ልዩነት ዜግነት መጋራት ብቻ ሊሆን ይችል ይሆን?

ሜሲና ሮኒልዶ እኛን አያውቁንም። መለስ ወይም ሚኒሊክ ፥ ጥላሁን አሊያም ፀጋዬ ገብረመድህን እናንተን ያውቋቸዋል? የአድናቆት መሰረት ትውውቅ አይደለም!

ብዙ ችግር ባለባት ሐገር በእግር ኳስ አትመሰጡ የሚሉን አሉ።
አይተኬው ገጣሚ በእውቀቱ ስዩም "በነገ ያመነ፥ ልጁን ቀብሮ መጥቶ ፥ ሚስቱን ያስረግዛል" ይላል። የሰው ህይወት እንዲህ ነው። ከልጅ ሞት በኋላ ሌላ ህይወት ይቀጥላል። ለቅሶ ቤት ጭምር ሳቅ አለ። ካርታ እየተዋወቱ ደስታ ይፈጠራል። አንዳንዴ ደግሞ በዋልድባም ይዘፈናል።

ሐገር ጭንቅ ላይ ስለሆነች መደበኛ ህይወቱን ያቆመ ማነው? ሻይ መጠጣት አቆማችሁ? ሚስታችሁን ማቀፍ ተዋችሁ? ሙዚቃ አትሰሙም? ከወዳጅ አትገናኙም? ምነው ለእናንተ የተፈቀደ ደስታ ለሌላው የተከለከለ መሰላችሁ?

"እግር ኳስ ቁም ነገር የለውም" የሚሉ አሉ።

ባለፈው አንድ አንባቢ ፌስቡከኛ እግር ኳስ ወዳጆችን ከፍ ዝቅ አድርጎ ተሳደበ። እሱ መፅሐፍ አንባቢ ስለሆነ ራሱን እንደ አዋቂ ቆጥሮ ሲያበቃ ኳስ ተመልካቾችን ጭንቅላት የለሽ አስመሰለ።... እንዲህ አይነቱን ተርታ ሃሳብ አክብሮ መልስ መስጠት ያሳፍር ይሆናል። ግን መልስ እንስጥ!

ህይወት ቁም ነገር ብቻ አይደለችም። ሰው እውቀት ተኩር ፍጡር ብቻ አይደለም። ህይወት ቁምነገራም መሆን አለበት። በየእለቱ ከምክኒያት ሳንተላለፍ ለመኖር መጣር ፥ ደግሞም መርህ ተከል መሆን ያስፈልጋል። ይህ ግን የሳንቲሙ አንድ ገፅ ነው።

ሰው ስሜታዊ ፍጡር ነው። ደስታ ያስፈልገዋል። የምንወደው ፥ ስሜታችንን ከፍ እና ዝቅ የሚያደርገን ፥ የሚያስቀን ነገር ያስፈልገናል። ስሜታችን ሙት ከሆነ ያለ ጥርጥር ታመናል።
ስሜት የሰብአዊነት ከፊል ገፅ ነው። እግር ኳስ ለስሜት በልኩ የተሰፋ አገልጋይ ነው። እናም የአእምሮ ጅምናስቲክ የሚፈልጉ መፅሐፍትን እያነበቡም እግር ኳስን መውደድ፤ በእግር ኳስ ማበድም ይቻላል። ምክኒያቱም ሰው ምክኒያታዊ እና ስሜታዊ ፍጡር ነውና!

በእርግጥ እግር ኳስ ዝም ብሎ እርግጫ አይደለም። አንዳንዶች እንደሚያስቡት ኳስ እየተከተሉ እንዘጥ እንዘጥ ማለት አይደለም። በላቀ ደረጃ እግር ኳስን ለመጫወት የላቀ አእምሮ ይፈልጋል! አዎ አእምሮ ይፈልጋል!

እግር ኳስ የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት ነው። የግለሰቦች ተሰጥኦ ፥ የቡድን ስራ ፥ የአመራር ጥበብ ፥ ስነልቦናዊ ጥንካሬ ፥ የአእምሮ ፍጥነት ፥ የአካል ብቃት ፥ አልሸነፍ ባይነት... ወዘተ ተጣምሮ እግር ኳስን ይፈጥራሉ። ከላይ ከተጠቀሱት ያለ አንዱ ዘመናዊ እግር ኳስ የለም።

በእግር ኳስ ኒውትሬሽን አለ፤ በእግር ኳስ ዘመናዊ ህክመና አለ ፤ በእግር ኳስ ዘመናዊ አስተዳደር አለ ፤ በእግር ኳስ የሰለጠነ ማርኬቲንግ አለ ፤ በእግር ኳስ የጦርነት ጥበብ አለ።

ስመ ጥሩ የሱን ዙ መፅሐፍ የሆነው "Art of War" ከፈርጉሰን እስከ ሞሪኒሆ አንብበውት ለእግር ኳሳቸው ተስማሚ አድርገው ተግብረውታል። ቬንገር ቡድኑን ሲገነባ የሰው ልጅ ለመዝናናት ያለውን ስነልቦና ከግምት ባስገባ መንገድ ነበር።...

እግር ኳስ ቅሪላ ማልፋት ብቻ አይደለም።

እኛ እግር ኳስን ልንወድ ብዙ ምክንያት አለን!


@Tfanos
4👍4🤔1
የዛሬው አጀንዳችን ራስን ማጥፋት ነው። ራስን የማጥፋት ወረርሽኝ ለምን? በዚህ ጉዳይ እናወራለን።

አድምጡ ፥ አስተያየት አካፍሉ

https://youtu.be/NJgT7vIthqQ
2025/10/24 07:38:59
Back to Top
HTML Embed Code: