Telegram Web Link
የካቲት 5 ሰልፍ የጠራው ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ አይደለም:: ሰልፉን የጠራው ዛሬ ጠዋት ለቅድስት ቤተክርስቲያን ክብር በግፍ የተሠዋው ሰማዕት ደም ድምፅ ነው::

ዛሬ ቤታቸው ሳይገቡ እህል ሳይቀምሱ ቤተክርስቲያናቸው ውስጥ ውለው በስናይፐር የተመቱ ምእመናን ደም እኔና አንተ ክርስትና ለተነሣንባት ኃጢአታችንን በንስሓ ለምናራግፍባት የምንቆርብባት የምንዳርባት ስንታመም የምንጠመቅባትና ስንሞት የምንቀበርባትን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዳናጣ ብለው ነው::

ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ያልሆነችው የለም:: ትምህርት ሚኒስቴር ሆና ከድንቁርና ጤና ሚኒስቴር ሆና ከበሽታ መከላከያ ሚኒስቴር ሆና ከቅኝ ግዛት የቱሪዝም ሚኒስቴር ሆና ከተራነት ኢትዮጵያን የታደገች ቤተ ክርስቲያን ናት::

ውለታዋ ተረስቶ የተሳዳቢዎች አፍ መፍቻ የሐሰተኞች ትንቢት መለማመጃ ሆና በንዋየ ቅድሳትዋ ተቀልዶ በከበሮዋ ተጨፍሮ ዕረፍት እንድታጣ ሆና መቆየትዋ ሳያንስ አሁን ደግሞ በግልፅ ተዘምቶባታል::

ቅዱስ ሲኖዶስ በቀጣዮቹ የምህላ ቀናት ያቀረበው ቅድመ ሁኔታ ካልተፈጸመ እንደሚካሔድ ያወጀው የጾም አዋጅና የካቲት 5 የጠራው ሰልፍ አባቶቻችን አባት ሆነው የተገኙበት ነው:: ልጆች ሆነን መገኘት የእኔና አንተ ፋንታ ነው:: ሕጋዊነትዋን ይዛ በሰላማዊ መንገድ የጠራችው ተቃውሞ ነውና የተሻለው መንገድም ይኼ ነው:: ከዚህ ቀደም ተጀምሮ የቀረ ሰልፍ ምን ዋጋ እንዳስከፈለን እናውቀዋለን:: አሁን በምንም ወደ ኋላ ማለት የለብንም:: በጎበዝ አለቃ መመራት በተባራሪ ወሬ መነዳት ትተን ከቤተ ክርስቲያናችን ጎን እንቁም:: ጉዳዩ የሐዋርያዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና ጉዳይ ሆኖ ሳለ የዘርና የቋንቋ ጉዳይ ለማድረግ የሚጥሩ ሰዎችን ጆሮ ባለ መስጠት በማያምኑባት ቤተ ክርስቲያን ውድቀትዋን ተመኝተው የሚሳደቡ እነ "ብጥብጥ አማረኝ"ን በቻልነው ሁሉ ብሎክ በማድረግ ጆሮአችንን ለቤተ ክርስቲያን ብቻ እንሥጥ::

ድርድር ሽምግልና ወዘተ የሚሉ የማዘናጊያ ሃሳቦች ፈጽሞ ተቀባይነት የላቸውም:: ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች እጃችሁን አስገቡ ብትባሉም እንኳን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አክብራችሁ እጃችሁን ሰብስቡ:: መነጋገር ካለበት አካል ጋር ሊነጋገር መብት ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ ሲሆን ከሰልፉ በኋላ የሚለንን እንሰማለን:: የእኛ ድርሻ ቤተ ክርስቲያን ያለችንን ብቻ ማድረግ ነው::

#yekatit5
#one_patriarch
#አንድ_ሲኖዶስ
#eotc_one_holy_synod
#OrientalOrthodox
የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ የብዙኃን ጋብቻ በሰአሊተ ምሕረት ካቴድራል እየተካሔደ ነው::

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመከራ ውስጥም ሆና ልጆችዋን በሥርዓተ ተክሊልና በቅዱስ ቁርባን እያከበረችና ቀጣዩን ኦርቶዶክሳዊ ትውልድ እየገነባች ነው:: ለሁለት ወራት የጋብቻ ትምህርት ትምህርተ ንስሓ ትምህርተ ቁርባንና የልጆች አስተዳደግ ከማኅበራዊ ሕይወት ጋር ሲማሩ የሰነበቱት 23 ሙሽሮች በአሁኑ ሰዓት ሥርዓተ ጋብቻቸው እየተፈጸመ ይገኛል:: ሥነ ሥርዓቱን በAD Pictures በቀጥታ ይከታተሉ::
ወጣት መነኩሴ ወደ አባ እንጦንዮስ መጣ። እየተማረረ እንዲህ አለ "አባቴ ሆይ ከመነኮስሁ ዓሥር ዓመታት አለፉኝ። ነገር ግን የዲያቢሎስን ፈተናውን መታገስ አቃተኝ ፣ እጅግ እየታገለኝ ነው" አባ እንጦንስም ለዚህ መነኩሴ የሚገባውን ምክርና ተግሣፅ ሠጥቶ አሰናበተው። መነኩሴው ከወጣ በኋላ ዲያቢሎስ ወደ አባ እንጦንስ ቀርቦ እንዲህ አለ። "በሕያው እግዚአብሔር እምላለሁ ፣ ይኼ ሰው መመንኮሱንም አላውቅም"

እኛ በዲያቢሎስ ተፈተንሁ ለማለት ራሱ ገና ነን ፣ ምክንያቱም የራሳችንን ድካምና ምኞት ገና ድል አልነሣንም።

"ምንም እንደ መቅደሱ መንጻት ባይነጻ የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ለመፈለግ ልቡን የሚያቀናውን ሁሉ ቸሩ እግዚአብሔር ይቅር ይበለው" (2 ዜና 30: 19)
+ እኔንም አስበኝ +

ዮሴፍ በበደል ላይ በደል የበዛበት ሰው ነው:: ሆድ ብሶታል:: ከሀገሩ የወጣው ፈልጎ ሳይሆን የገዛ ወንድሞቹ ሸጠውት ነበር:: ከመሸጡ በላይ በሥጋ ወንድሞቹ መጠላቱ ልቡን አቁስሎታል:: ዐሥር ወንድሞቹ ጨክነው ተስማምተው መሸጣቸውን ማሰብ ደግሞ በጣም ከባድ ነበር::

ባይተዋሩ ዮሴፍ እንደተከፋ ወደ ግብፅ ሲወርድ እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር አብሮ ተሸጠ እንጂ ብቻውን አልተወውም:: በመከፋቱ አብሮት ተከፋ:: ስለኀዘኑም አብሮት አዘነ::

ዮሴፍ ጲጥፋራ በተባለ ሰው ቤት ባሪያ ሆነ:: በአባቱ ተወዳጅ ሆኖ ላደገው ቅምጥሉ ዮሴፍ በሰው ቤት ባሪያ መሆን እጅግ ከባድ ነበር::
ሆኖም በሰው ቤት ባሪያ በሆነ ጊዜ ግን የጌቶች ጌታ የሆነው እግዚአብሔር አብሮት ነበረ:: በጌታው ፊት ሞገስ ሠጥቶት ስለነበር የቤቱ አዛዥ ናዛዥ ሆኖ ተሾመ::

እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ከሆነ ባሪያ ሆነህ ብትሸጥም ባለ ሥልጣን ትሆናለህ::

እረፍት አልባው ዮሴፍ በተሾመበት ቤት ብዙም ሳይቆይ ግን የጌታው ሚስት ለዝሙት አስቸገረችው:: እግዚአብሔር ን ፈርቶ አሻፈረኝ ሲላት ራስዋ ገርፋ ራስዋ ጮኻ እስር ቤት ጣለችው::

መከረኛው ዮሴፍ እስር ቤት ወረደ:: የታሰሩ ሁሉ ወንጀለኞች አይደሉም:: የአንዳንዶችን ኃጢአት ለመሸፈን የሚታሰሩ ንጹሐን ብዙ ናቸው::

ዮሴፍ ያለ በደሉ ሲታሰርም ብቻውን አልሆነም::
እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር አብሮ ታሰረ:: በበደል ላይ በደል ደርሶበት በገባበት ወኅኒ ቤት "እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ነበረ ምሕረትንም አበዛለት፥ በግዞት ቤቱም አለቃ ፊት ሞገስን ሠጠው" ዘፍ. 39:21

እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ከሆነ እስር ቤት ውስጥም ትሾማለህ:: ዮሴፍ የወኅኒው ባለ ሥልጣን ሆነ::

ከዚህ በኋላ ዮሴፍ በወኅኒው ለሁለት ሰዎች ሕልም ይፈታላቸው ጀመር:: የአንዱ ሕልም ፍቺ "ተሰቅለህ ትሞታለህ" የሚል ሲሆን የሌላኛው ሕልም ፍቺ ደግሞ "በፈርኦን ፊት ዳግመኛ ትሾማለህ" የሚል ነበር::

ወደ ፈርኦን ቤተ መንግሥት ተሹሞ የሚሔደውን ሰው ዮሴፍ እንዲህ አለው :-

"ነገር ግን በጎ ነገር በተደረገልህ ጊዜ እኔን አስበኝ ምሕረትንም አድርግልኝ የእኔንም ነገር ለፈርዖን ነግረህ ከዚህ ቤት አውጣኝ:: እኔን ከዕብራውያን አገር ሰርቀው አምጥተውኛልና፤ ከዚህም ደግሞ በግዞት ያኖሩኝ ዘንድ ምንም አላደረግሁም።" ዘፍ. 40:14

ዮሴፍ "እኔንም አስበኝ ምሕረት አድርግልኝ" ብሎ የተማጸነው የፈርኦን ጠጅ አሳላፊ ግን "ዮሴፍን አላሰበውም፥ ረሳው እንጂ" ዘፍ. 40:23

ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ለሁለት ዓመታት በእስር ቆየ እንጂ ምንም የተፈጠረ ነገር የለም::

ባሪያ ሆኖ ሲሸጥ አብሮት የተሸጠው እግዚአብሔር
እስር ቤት ሲገባ አብሮት የታሰረው እግዚአብሔር
አሁን ግን ዮሴፍን ዝም አለው::

ለምን?

ዮሴፍ "እኔንም አስበኝ ምሕረት አድርግልኝ" ብሎ የለመነው የጠጅ አሳላፊውን ነበር:: በግፍ ከሀገሩ እንደወጣ ያለ በደሉ እንደታሰረ ያስረዳው ለፈርኦን ቤት ሹመኛ ነበር:: ስለዚህ እግዚአብሔር "ዮሴፍ ሆይ ጠጅ አሳላፊውን አስበኝ አልክን? በል እሱ ያስብህ" ብሎ ተወው::

በሕይወትህ ሰውን አደራ ያልክ ቀን እግዚአብሔር ይተውሃል:: "አውጣኝ" ያልከው ሰውን ከሆነ ፈጣሪ የሰውን ነገር እንድታይ ዝም ይልሃል::

ሁላችንም አደራ አስበኝ ብለን የተማመንንባቸው ጠጅ አሳላፊዎች አይጠፉም:: እንደ ዮሴፍ ቤተ መንግሥት ውስጥ ሰው አለኝ ብለን ተስፋ የጣልንባቸው ፣ ዘመድ አለኝ ብለን የሙጥኝ ያልናቸው ሰዎች አይጠፉም:: "በአንድ ስልክ ልጨርሰው እችላለሁ እኮ" ብለን የተመካንባቸው ሰዎች አናጣም::

ወዳጄ እመነኝ ሰው አደራ በላ መሆኑ አይቀርም:: ቃል የገባልህ ሰው ወደ ሹመቱ ሲገባ አያስታውስህም::
ሥጋ ለባሹን አደራ ብለህ ከፈጣሪህ አትጣላ::

ሰውን በቤተ መንግሥት አስበኝ ከማለት ፈጣሪን በመንግሥትህ አስበኝ ማለት ይሻላል::

"በሰው ከመታመን ይልቅ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል። በገዦች ተስፋ ከማድረግ ይልቅ በእግዚአብሔር ተስፋ ማድረግ ይሻላል" መዝ. 118:8

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጥቅምት 6 2015 ዓ.ም.
ዲላ ኢትዮጵያ

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን አጥብቃችሁ ስለ እኔ ጸልዩልኝ!
በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ [ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ ሌላ] ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)

ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like, Subscribe እና Share ያድርጉ :-

የፌስቡክ ገጽ :- https://www.facebook.com/officialHenokhaile/
የቴሌግራም ቻናል : https://www.tg-me.com/deaconhenokhaile
የዩቲዩብ ገጽ: https://www.youtube.com/channel/UCOaVsWC05aUjeqIEW3fWj7g
+ የዘኬዎስ ዛፍ +

ዘኬዎስ ቁመቱ አጭር ዝናው ግን ረዥም የሆነ ሰው ነው፡፡ ይህንን ሰው የምናውቀው በኢያሪኮ መንገድ የሚያልፈውን ክርስቶስ ለማየት በአንዲት የሾላ ዛፍ ላይ ወጥቶ ነው፡፡ ወደዚያች ዛፍ የወጣው ቁመቱ አጭር በመሆኑና በሕዝቡ መብዛት ምክንያት ክርስቶስን ሊያየው ባለመቻሉ ነው፡፡ መቼም ሰው በበዛበት ፣ ግርግርና በሆይ ሆይታ በሞላበት ቦታ ክርስቶስን ማየትም ሆነ ከአምላክ ጋር መነጋገር ለአጭርም ለረዥምም ሰው ከባድ ነው፡፡ እያንዳንዳችን ጌታን ለማየት ከጫጫታና ግርግር ተለይተን የምንወጣበት የየራሳችን ሾላ የሚያስፈልገንም ለዚህ ነው፡፡

ዘኬዎስ በሙያውም ከአመንዝሮችና ከወንጀለኞች ጋር የተቆጠረ ቀራጭ ነበር፡፡ በሰው ፊት ደፍሮ ‘ጌታን ማየት እፈልጋለሁ’ እንዳይል ፣ ከእርሱ ቀድሞ ዓይኑ እንደበራለት በርጤሜዎስ ‘የዳዊት ልጅ ሆይ ማረኝ’ ብሎ በሕዝብ ፊት እንዳይጮህ ‘አንተን ብሎ ጸሎተኛ! ትንሽ አታፍርም?’ የሚያሰኝ ሕይወት ስለነበረው ጌታን በሩቅ ማየት ብቻ ይበቃኛል ብሎ ከዛፍ ላይ ወጣ፡፡

ዘኬዎስ ወደ ዛፍ የወጣው ጌታን ለማየት እንጂ ለመታየት አልነበረም፡፡ የእርሱ ፍላጎት ከሰው መሃል ገብቶ ሳይከለል ጌታውን ማየት ነበር:: መታየት ከሚሹ ይልቅ እርሱን ማየት የሚሹትን ለይቶ የሚያውቀው ክርስቶስ ይህንን ቀራጭ ከሕዝቡ ለይቶ ተመለከተው፡፡

ጌታ ሲያየው ሕዝቡ ሁሉ ዓይኑን ወደሱ መለሰ:: በመድኃኔዓለም የምሕረት ዓይን ከታየህ በእርግጥም ዓለም ሁሉ ያይሃል፡፡ ክርስቶስ ስላየው ሁላችንም ዘኬዎስን አየነው ፣ ታሪኩም በምንሳለመው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተጻፈ፡፡

ጌታ በዓይኖቹ ይመልከትህ እንጂ ምንም ክፉ ብትሆን የሕይወት ታሪክህ ወንጌል ይሆናል፡፡ አንተ እርሱን የሚሻ ልብ ካለህ ድምጽ አውጥተህ ባትጠራውም ፣ ጸሎት ማሳመር ባትችልም የልብህን ጩኸት ሰምቶ ይጠራሃል፡፡ ለዘኬዎስ የሆነለት ይህ ነበር፡፡ እንደ አጋር ‘የሚያየኝን አየሁት’ ብሎ ሊዘምር የሚችል የሐዲስ ኪዳን ሰው እርሱ ሆነ፡፡ ጌታን ሊያይ ከዛፍ ወጥቶ በጌታው ታይቶ ወረደ፡፡ ወደ ቤታችን ለመግባት ጋባዥ የማይፈልገው ክርስቶስ የዘኬዎስን ልብ አይቶ ዛሬ በአንተ ቤት እሆናለሁ አለው፡፡

የቀራጮች መሰብሰቢያ የሆነችው የዘኬዎስ ቤት የጌታና የደቀ መዛሙርቱ ማረፊያ ቤት ሆነች፡፡ የግፍ ገንዘብ ማከማቻ የነበረችው የክፉዎች አዳራሽ የሰማያዊው እንግዳ የክርስቶስ ቤተ መቅደስ ሆነች፡፡ ሕሙማን ሊፈወሱ ከዚያች ቤት ዙሪያ ሰፈሩባት፡፡ ሐኪሙ ጌታ ገብቶባታልና የዘኬዎስ ቤት ሐኪም ቤት ሆነች::

በዚህ ደስ ያለው ዘኬዎስም ‘ካለኝ እኩሌታውን ለድሆች እሰጣለሁ ፤ በሐሰት የከሰስሁትን አራት እጥፍ እክሳለሁ’’ አለ፡፡ የሕይወት ለውጥ ከሌለ ደግሶ ማብላት ብቻውን ጽድቅ እንደማይሆነው አውቆ አለመታዘዙን በመታዘዝ ፣ ስርቆቱን በምጽዋት ሊበቀል ተነሣ፡፡ የመዳን ቀንድ ክርስቶስም ‘’ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል’ አለው፡፡

የዘኬዎስ ታሪክ ብዙ ምሥጢር ብዙ ምክር የሚወጣው ነውና ለዛሬ አንዱን ሰበዝ ብቻ እንምዘዝ ፤

እንደሚታወቀው የዘኬዎስ ከዚያ በኋላ ያለው ታሪኩ አልተጻፈም፡፡ ከሱ ታሪክ ጋር የተያያዘችዋ ቅርስ እርሱ የወጣባትና ጌታውን ያየባት የሾላ ዛፍ ነበረች፡፡ በኢያሪኮ መንደር የምትገኘው ይህች ዛፍ ለሌሎች ሰዎች ተራ ዛፍ ብትሆንም ለዘኬዎስ ግን ‘‘የሕይወት ዛፍ’’ ናት፡፡ ምናልባትም ዘኬዎስ ከመስቀል በፊት ጌታን ያየባት የከበረች ዕፅ ይህች ዛፍ ናት፡፡ ጌታው እርሱን ብሎ ሳይሰቀል በፊት እሱ ጌታን ብሎ የተሰቀለባትና መድኃኒቱን ያየባት ይህች ዛፍ ለዘኬዎስ ትልቅ ባለውለታው ናት፡፡

ዘኬዎስ ይህችን ዛፍ ባየ ቁጥር ምን ይሰማው ይሆን? ምንም እንኳን ትልቅ ዛፍ ብትሆንም እርሱ ግን እንደ ችግኝ በስስት ዓይን ሳይመለከታት የሚቀር አይመስላችሁም? ባለፈ ባገደመ ቁጥር በፍቅር የሚስማት ፣ ጌታውን ሲያስብ ለጸሎት የሚመጣባት : ቅጠሎችዋን በፍቅር እየነካካ ዙሪያዋን የሚያጸዳላት ጌታን ያየባት ክብርት ዛፉ ናት፡፡ 

አይበለውና ይህች ዛፍ ትቆረጥ ቢባል ዘኬዎስ ምን የሚል ይመስላችኋል? በእጆቹ ግንድዋን ታቅፎ "አንኩብኝ!" አይል ይሆን? ለማገዶ ትዋል ተብሎ ቢወሰንባትስ? እሳት ቢነድባትስ? የዘኬዎስ ልብ ምን ያህል ይቆስል ይሆን? ጌታውን ያየባት መሰላሉ ሕይወቱ የተለውጠባት የመድኃኒት ዛፍ ተቆርጣ ተማግዳ ቢያይ ዘኬዎስ ልቡ በኀዘን ይደማል::

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስትቃጠል ፣ ስዘረፍ ፣ ስትደፈር የሚሰማንም ይህ ነው! በኃጢአት ቁመታችን አጥሮ ፈጣሪን ማየት ሲሳነን በእርስዋ ላይ ወጥተን ጌታን ያየንባት ፣ የታሪካችን መስመር ተቀይሮ ለየቤታችን መዳንን ያገኘንባት ፣ ብዙ ዘኬዎሶችን ተሸክማ ከጌታ ያገናኘች እውነተኛዋ ዛፍ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡
እርስዋን የሚነኩ ሁሉ የመውጊያውን ብረት ይቃወማሉ ፤ ‘አይነኩ ከነኩ ያድሯል ሲታወኩ’ የተባለላት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ይህ ዘመን ስለዚህች የሕይወት ዛፍ ፣ የሰማይ ደጅ የምተጋበት ፣ ጌታን ያየንባትን ዛፍ ከበብን ከመቼውም ጊዜ በላይ በየመክሊታችን የምሠራበት ፣ ችግርዋን መፍታት ቢያቅተን ችግር ላለመሆን የምጥርበት ጊዜ ነው፡፡

ስለዚህች የኃጥአን ተስፋ ስለሆነችው የዘኬዎስ ዛፍ ገጣሚ ዳዊት ግርማ የአባ ጳውሊ ራእይ በተባለ የግጥም መድበል ላይ (paraphrased version) እንዲህ ብሎላታል ፦
ቤተ ክርስቲያን ደብረ ብዙኃን
ምነው እንደ ዳዊት ዘመን
ዛሬም በሆንሽ በድንኳን
ምቀኛ ሲገፋሽ ጠቅልዬሽ እንድሸሽ
ምቀኛ ሲተውሽ መልሼ እንድተክልሽ

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
አዲስ አበባ
ጥር 3 2012
EOTC_Television_አውደ_ስብከት_ታላቂቱ_ከተማ_
<unknown>
±±ታላቂቱ ከተማ±±

🌻በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ🌻

የእግዚአብሔርም ቃል ወደዐማቴ ልጅ፡ወደ ዮናስ እንዲህሲል መጣተነሥተኽ፡ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማወደነነዌ ኺድ ክፋታቸውም ወደፊቴ፡ወጥቷልና በርሷ ላይ ስበክ።{ት/ተዮናስ1÷1-2}
👉 @deaqonhanok 👈
👉 @deaqonhanok 👈
(ይህችን አመት ተወኝ ) ስነ ግጥም በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ)
የዲ'ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች
ይህችን አመት ተወኝ +
_
(በመ/ር ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ)
+

የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ ጸልዩ! ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like እና Share ያድርጉ
FB: https://www.facebook.com/officialHenokhaile/
Telegram: https://www.tg-me.com/deaconhenokhaile
Instagram: https://www.instagram.com/p/CBnMF0nnhcQ/?igshid=549jvl607bv4
Youtube: https://www.youtube.com/channel/UCOaVsWC05aUjeqIEW3fWj7g
ላለፉት ሦስት ሳምንታት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በታሪክዋ አይታው የማታውቀው ሐዋርያዊ ሰንሰለትዋን የሚበጥስ አንዳች ዱብ ዕዳ ገጥሞአት በብዙ ጭንቀትና መከራ ውስጥ አሳልፋለች፡፡ ከልሒቅ እስከ ደቂቅ በጉዳዩ ተደናግጦ ለእናት ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ አንድነት የሚችለውን ሁሉ ለመክፈል ታይቶ በማይታወቅ አንድነት ተረባርቦአል፡፡

የቤተ ክርስቲያንን ሰላም እስካይ ድረስ ለዓይኖቼ ዕረፍትን ለሽፋሽፍቶቼ እንቅልፍን አልሠጥም ብላችሁ ስለ ቅድስት ቤተ ክርቲያን በምትችሉት ቆማችኋል ፣ ብርድ ላይ አድራችኋል ፣ ለመሞትም ቆርጣችኋል፡፡ አሁን በሰማያዊትዋ የድል ነሺዎች ቤተ ክርስቲያን ሆናችሁ የምታዩን ፣ ዓይናችን እያየ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አትደፈርም ብላችሁ ሰማዕታት የሆናችሁት ልጆችዋም በረከታችሁ ይድረሰን፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ከብባችሁ አካላችሁ የጎደለ ፣ አሁንም ድረስ በአልጋ ላይ ያላችሁ ፣ ቤተሰቦቻችሁን ያጣችሁ ፣ ከቀዬያችሁ የተፈናቀላችሁ እስከ አሁንዋ ሰዓት ድረስ በወኅኒ ቤት ሆናችሁ ከእናንተ መፈታት ይልቅ የችግሩ መፈታት ያስጨነቃችሁ ወንድምና እኅቶቻችን ሥራችሁ በልበ ሥላሴ የተጻፈ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን ስለተገደሉ ልጆችዋ ስታለቅስና ማቅ ስትለብስም ከዳር ዳር ጥሪዋን ተቀብላችሁ ማቅ የለበሳችሁ ‘ቤተ ክርስቲያን ሆይ ማቅ ልልበስልሽ’ ያላችሁትን በአደባባይ በጥፊ የተመታላት የቤተ ክርስቲያን ራስዋ ክርስቶስ አይቶታል፡፡
ግራ ቀኝ የሚናፈስ ወሬ ነገሩን ሊያደፈርሰው ሲሞክርም በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ምእመናን ‘ከሲኖዶስ ሌላ ማንንም አንሰማም’ ብላችሁ ታዝዛችኋል፡፡ ከመቼውም ጊዜ በላይ የቤተ ክርስቲያን ክብርና የቅዱስ ሲኖዶስ ምንነት ሰምተው የማያውቁ ሰዎች ሳይቀር በዚህ የተነሣ የጉዳዩ መሠረታዊነት ግልፅ ሆኖላቸው ፣ ግድ የማይሰጣቸውና ሲኖዶስን ሲሳደቡ የነበሩ እንኳን ‘እኔ ነኝ ያስደፈርኩሽ ቤተ ክርስቲያኔ ይቅር በይኝ’ ሲሉ ሰንብተዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያኔን ነገር አደራ ብሎ ያነባው ፣ ንስሓ የገባው ሕዝበ ክርስቲያን እልፍ አእላፍ ነበረ፡፡ መተዳደሪያ ሥራቸውን ፣ ዝናቸውን ፣ ሙያቸውን አደጋ ላይ ጥለው ብዙዎች ለቤተ ክርስቲያናቸው ጮኸዋል፡፡ እምነታቸው ሌላ ሆኖ እንኳን ለቤተ ክርስቲያን የቆሙ ባለውለታዎችም ብዙዎች ናቸው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ምንም ዓይነት ማስፈራሪያና ጫና ያልበገራቸው ብፁዓን አበው ታሪክ በማይረሳው መንፈሳዊ ጥብዓትና ጽናት በአንድ ልብ ሆነው በመናገር የቤተ ክርስቲያኒቱ ጠበቆች ሆነዋል፡፡ ሁላችሁም ‘ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ እግዚአብሔር አመጸኛ አይደለም’ ዕብ. 6፡10

‘ይህ ሁሉ ለምን ሆነ?’ አንድ ፓትርያርክ ፣ አንድ ሲኖዶስ ፣ አንዲት ቤተ ክርስቲያን በሚል መርሕ የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና ለማስከበርና የቅዱስ ፓትርያርኩን አባትነት ለማጽናት ፣ በዚህም በሺህ ለሚቆጠሩ ዘመናት የተሻገረችውን ቤተ ክርስቲያን ሳትፈርስ እንድትቀጥል ለማድረግ ነው፡፡ ያ ሁሉ ዕንባና ልቅሶ ፣ ያ ሁሉ ሰማዕትነት አንድ ፓትርያርክ ፣ አንድ ሲኖዶስ ፣ አንዲት ቤተ ክርስቲያን የሚለውን ቀኖናዊ ዶግማ (Canonical Doctrine) ለማስከበር ነበር፡፡ በዛሬው ዕለት ከቅዱስ ሲኖዶስ እንደሰማነው በእግዚአብሔር ቸርነት ለሳምንታት ቤተ ክርስቲያንን እስከ ሰማዕትነት ድረስ ብዙ ዋጋ ያስከፈለው ችግር ተፈትቶ ‘አንድ ፓትርያርክ ፣ አንድ ሲኖዶስ ፣ አንዲት ቤተ ክርስቲያን’ የሚለው የቤተ ክርስቲያኒቱ መርሕ ተከብሮአል፡፡ ፓትርያርካችን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፤ ሲኖዶሳችን አንድ ፣ ቤተ ክርስቲያናችንም አንዲት ናት የሚለው ጸንቶአል፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ ስለ ክብሩ መደፈር ተቆርቁረን ብዙ የጮኽንለት ቅዱስ ሲኖዶስን የእውነት ማክበራችንና መውደዳችን በተግባር የሚፈተነው አሁን ነው፡፡ ከአባቶቻችን ጎን እንደነበርን ከዚህ በኋላ በሚመጣው ነገር ሁሉም አብረናቸው እንሆን ይሆን? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ ዛሬ በሰማናቸው መግለጫዎች ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና ተከብሯል ፣ ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ውጪ የነበረው ሹመትም መሻሩን ሿሚዎቹ ተቀብለዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ያቀረበውን የመመለስ ጥሪ ተቀብለው ይቅርታ ጠይቀውም የተወገዙት ሊቃነ ጳጳሳት ተመልሰዋል፡፡ ልባችንን ያደማው የቤተ ክርስቲያን መከፈል ጉዳይ ባልተጠበቀ ፍጥነት ተፈትቶ እግዚአብሔር ጸሎታችንን እንደሰማ አይተናል፡፡

በሒደቱ ላይ ነገሮች በጣም በፍጥነት ከመለዋወጣቸው የተነሣ ብዙ ጥያቄ የሚፈጥሩ ዝርዝሮችና ከልባችን ገና ያልወጡ ሥጋቶች መኖራቸው ግን የማይካድ ነው፡፡ ክስተቱ ተመለሱ የተባሉ ሰዎች ሲወላወሉ ባየንበት ማግሥት የሆነ ነገር እንደመሆኑም ለማመን የቸገረንና በሙሉ ልብ ለመደሰት የፈራን ብዙዎች ነን፡፡ ቤተ ክርስቲያን በውግዘት የለየቻቸውን አበው መልሳ የምትቀበልበት አካሔድ እንዴት ነው? ቀኖና ቤተክርስቲያን ምን ይላል? ከዚህ በኋላስ ምን ይፈጠር ይሆን? ፣ ወደነበርንበት ለመመለስ የከረምንበት ሁኔታ ይፈቅድልን ይሆን? መንግሥት በቃሉ ባይገኝስ? በፍርድ ቤት የታዩ ጉዳዮችስ? ይቅርታ የሚጠይቁ ሰዎች እያታለሉን ቢሆንስ ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች የቤተ ክርስቲያኑ ነገር እንደ እግር እሳት ሲያንገበግበው ከሰነበተ ምእመን የሚጠበቅ ውስጣዊ ጥያቄ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም ተግባራዊ ምላሽ እንደሚሠጥበት እንጠብቃለን::

መንግሥትን እንዴት ማመን እንችላለን? ለሚለው እኛ ሁልጊዜም የምናምነው እግዚአብሔርን ብቻ ነው፡፡ እርሱ ደግሞ አምነነው አሳፍሮን አያውቅም፡፡ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ስለ እግዚአብሔር ብቻ ነው:: በእግዚአብሔር መንፈስ ይመራሉ ብለን የምናምንባቸው አባቶቻችንንም እስከ አሁን ያዘዙንን ስናደርግ ሰንብተን ከዚህ በኋላ አባትነታቸውን ብንጠራጠርና በስሜታዊነት ብንሳደብ ‘ለሦስት ሳምንታት ቅዱስ ሲኖዶስ ክብርና ልዕልና ተነካ ብለን የጮኽነው ለምን ነበረ? ያስብላል፡፡

በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ከመንግሥት ጋር በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ሆነው ‘ቤተ ክህነቱ ሊወረር ነው ፣ አባቶች ሊታፈኑ ነው’ የሚል የሚያሸብር ዜና እየሰሙ በዚያ የጭንቅ ሰዓት ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው የሰነበቱ አባቶች ፣ ጠባቂዎች ቢነሡባቸው እግዚአብሔርን ጠባቂያችን ብለው ስለ ሕገ ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ በድፍረት የቆሙ ሊቃነ ጳጳሳት ዋናው ችግር ከተፈታ በኋላ በሚኖረው ሒደት ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን አሳልፈው ይሠጣሉ ብሎ መደምደም የሚያሳዝን ነው፡፡

አባቶችን ላታልላቸው ብሎ እንደ ሀናና ሰጲራ መንፈስ ቅዱስን ሊያታልል የሚሞክር ሰው የሚያታልለው ራሱን ነውና ይቀሰፋል፡፡ አርዮስ አባቶችን አታለልኩ ብሎ ሳያምን አምኛለሁ ብሎ የደረሰበትን ስንማር ኖረናልና ቤተ ክርስቲያንን ሊያታልል የሚሞክር ሁሉ በእርሱ እንደሚብስበት እናምናለን፡፡ ስለዚህ ተመለሱ በሚል ዜና እንደጠፋው ልጅ ወንድም አኩራፊ ፣ እንደ ሀናንያ ተጸያፊ ሳንሆን የእውነት ያድርገው ብለን በመጸለይ እንበርታ:: የነነዌ ለቅሶ መልስ ሲያገኝ ካኮረፍን ኩርፊያችን የዮናስ ኩርፊያ ይሆንብንና ትርፉ ቅላችንን ማድረቅና በፀሐይ መለብለብ ይሆናል:: (ዮና. 4:1-11) ልጅ ጠፍቶ ሲገኝ ደስ የሚል ከሆነ አባት ጠፍቶ ሲገኝ እንዴት ደስ አይልም? እንደ ልጅነታችን ዳግም አባት አልባ እንዳንሆን መለመን ነው እንጂ::
አባቶቻችን በኀዘን ተውጠው ስለ ቤተ ክርስቲያን ሲያለቅሱ አምነናቸው አብረን ካለቀስን ደስ ሲላቸውና ደስ ይበላችሁ ሲሉንም እንዲሁ ልናምናቸው ይገባል፡፡ ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት አልቅሰን ከጾምን አንድ ሆነች ሲባል ‘አይዋጥልኝም’ ማለትም ‘ታዲያ የጸለያችሁት ምን ይሁን ብላችሁ ነው?’ ያስብላል፡፡ ሊቃነ ጳጳሳቱ ‘አምላካችን ሆይ ስማን በሉ’ ሲሉ እንደተቀበልናቸው ‘ሰምቶናል’ ሲሉንም አብረን ማመስገን የልጅነት ግዴታችን ነው፡፡ ነገሩ ምንም ያልተዋጠልን እንኳን ብንሆን አባቶቻችንን አትንኩብን ስንል በከረምንበት አፋችን ለመሳደብ ብንነሣ እንኳንስ እግዚአብሔር ሶሻል ሚድያውም ይታዘበናል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስን ሌላው ሲያቃልለው ከተቃወምን እኛም የማቃለል መብት የለንም፡፡ ሁሉም ሰው መሪ ሊሆን ስለማይችል ጉዳዩን በትኩረት ለያዙት አባቶች ሥራቸውን እንደ ጀመሩት እንዲፈጽሙ እየጸለይን በምንችለው ማገዝ እንቀጥል፡፡

ከዚህ በኋላ ያለው ጊዜ የተሰበረውን የምንጠግንበት ፣ ቤተሰቦቻቸውን ያጡትን የምንደግፍበት ፣ ሰማዕታቱን የምንዘክርበት ፣ በመከራዋ ቀን ለጮህንላት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሁለንተናዊ ድጋፍ የምናደርግበት ነው፡፡ እስካሁን የገጠሙን ችግሮች ያልተሠሩ ሥራዎች ውጤት መሆናቸውን በማሰብ ሌላ ሰው አጀንዳ እስኪያቀብለን በመጠበቅ ሳይሆን እኛ አጀንዳ ሠጪ እየሆንን የተቀጣጠለውን ፍቅረ ቤተ ክርስቲያን ለወንጌል አገልግሎት የምናውልበት ዕድል አሁን ነው፡፡ መጪው ዐቢይ ጾም ነውና እያበጣበጠ ሲያፌዝብን የከረመውን ዲያቢሎስ በርትተን የምንቀጣበት እድልም ከፊታችን ነው::

አሁንም ደግመን እንላለን :-

አንድ ፓትርያርክ
አንድ ሲኖዶስ
አንዲት ቤተ ክርስቲያን

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
የካቲት 8 2015 ዓ.ም.
+ ጻድቅ ሆኖ ተመለሰ +

አባ ፕሮፎርዮስ እንዲህ ሲሉ ገጠመኛቸውን ያስታውሳሉ ፦

‘በጥምቀት በዓል ሰሞን ውኃው ተጸልዮበት ከተባረከ በኋላ ለካህናት ወደ ሰዉ ቤት መሔድና ጠበል መርጨት የተለመደ ሥርዓት ነው፡፡ የሆነ ዓመት ላይ ይህንን ጠበል እየረጨሁ ምእመናንን ለመባረክ ከቤተ ክርስቲያን ወደ መንደር ወጥቼ ነበር፡፡ በየቤቱ በር አንኳኳና ‘አመ ተጠምቀ እግዚእነ በዮርዳኖስ...!’ /ጌታ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ.../ እያልሁ እያዜምሁ እገባለሁ፡፡

ብዙ መኖሪያ ቤቶች ወዳሉበት መንደር እንደዘለቅሁ አንድ በብረት በር የተዘጋ ትልቅ ጊቢ ጋር ደረስሁ፡፡ ከፍቼ ዘልቄ ገባሁ ፤ ጊቢውን የሞላውን መንደሪን ፣ ሎሚና ብርቱካን የተተከለበት የአትክልት ሥፍራ አልፌ ቀጥ ብዬ ገባሁ፡፡ ሕንጻው ወደ ምድር ቤትና ወደ ላይኛው ፎቅ የሚያስወጡ ሁለት ደረጃዎች አሉት፡፡ ወደ ላይ ወጥቼ አንዱን በር ሳንኳኳ አንዲት ሴት ብቅ ብላ በሩን ከፈተች፡፡ ‘አመ ተጠምቀ እግዚእነ በዮርዳኖስ...!’ ብዬ ማዜም ስጀምር በፍጥነት አስቆመችኝ፡፡ ይሁንና ድምፄ በደንብ ተሰምቶ ስለነበር ከግራ ከቀኝ ካሉት ክፍሎች ውስጥ ወጣት ሴቶች ወደ ኮሪደሩ ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ ነገሩ ገባኝ ፤ ‘አሃ ዘልዬ የገባሁት ለካ መሸታ ቤት ከሚሠሩ ሴቶች ቤት ኖሯል?’ አልኩኝ በሆዴ፡፡

‘እባክዎን ይሒዱ አባ’’ አለች ቀድማ የወጣችው ሴት ‘እነዚህ ሴቶች መስቀል መሳለም የሚገባቸው አይደሉም ፤ እኔን ያሳልሙኝና ቶሎ ይሒዱ’ አለች በችኮላ፡፡

ኮስተር አልኩና ‘ካህን ነኝ ቤቱን ሳልባርክ አልሔድም’ አልኳት
‘እሱን ይችላሉ እነዚህ ሴቶች ግን መስቀሉን አይሳለሙም’ ብላ ፍርጥም አለች፡፡

‘መስቀሉን መሳም የሚገባው አንቺ ሁኚ እነርሱ በምን እናውቃለን? እግዚአብሔር መስቀሉን መሳለም የሚገባው ማን ነው ብሎ እኔን ቢጠይቀኝ ኖሮ መስቀል መሳለም የሚገባው ለአንቺ ሳይሆን ለሴቶቹ እንደሆነ በነገርሁት ነበር፡፡ ምክንያቱ ከምትመጻደቂው ከአንቺ ይልቅ የእነርሱ ነፍስ ትሻላለች’ ብዬ ገሠጽኋት፡፡ ደንግጣ ዝም አለች ፤ እኔም ሴቶቹን ወደ እኔ እንዲመጡ ጠራኋቸው፡፡

ከዚያም ‘‘አመ ተጠምቀ እግዚእነ በዮርዳኖስ...!’ እያልኩ ከመጀመሪያው በበለጠ ኃይል መዘመር ቀጠልሁ፡፡ እግዚአብሔር ወደ እነዚህ ምስኪን ነፍሳት እንድመጣ እንዳመቻቸልኝ ስላወቅሁ ውስጤ በደስታ ተሞልቶ ነበር፡፡

ሁሉም መስቀሉን ተሳለሙ፡፡ ሁሉም ያጌጠ ልብስ ለብሰው ሊወጡ ተዘጋጅተው ነበር፡፡ እንዲህ አልኳቸው ፦ ልጆቼ እግዚአብሔር ይባርካችሁ ፤ እግዚአብሔር የሚወደው ሁላችንንም ነው፡፡ እርሱ መልካም ነውና ለኃጢአተኞችም ለጻድቃንም ዝናምን ያዘንባል፡፡ እርሱ የሁላችን አባት ነውና ለሁላችን ይጨነቃል፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው ወደ እርሱ መምጣት እርሱን መውደድና መልካም መሆን ብቻ ነው፡፡ እርሱን ውደዱ ምንኛ ደስተኛ እንደምትሆኑ ታያላችሁ’’

በመደነቅ ይመለከቱኝ ነበር ፤ በተጨነቀች ትንሽ ነፍሳቸው ውስጥ የሆነ ነገር እንደቀረ ያስታውቅ ነበር፡፡

‘እናንተን ለመባረክ እግዚአብሔር ዛሬ ወደዚህ ቤት የመምጣትን ክብር ስለሠጠኝ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ’ አልኳቸው፡፡ ለመሔድ ስነሣ ‘እግዚአብሔር ለዘላለም ይባርካችሁ’ አልኳቸው ፤ ‘አሜን አባ’ ብለው በአንድነት መለሱ ፤ ጉዞዬን ቀጠልሁ፡፡
💒💒💒💒💒

ይህንን አጭር ታሪክ በኦርቶዶክሱ ዓለም እጅግ ተወዳጅ ከሆኑ እጅግ ውብ መጻሕፍት አንዱ ከሆነው ‘Wounded by Love ፤ The Life and the Wisdom of Saint Porophyrios’ ከተሰኘው የአንድ መነኩሴን ሕይወት የሚተርክ ድንቅ መጽሐፍ ነው፡፡

💒💒💒💒💒


ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ‘እግዚአብሔር በጽድቁ ከሚመካ ጻድቅ ይልቅ ስለ ኃጢአቱ የሚያለቅስ ዘማዊን ይወድዳል’ ይላል፡፡ በእርግጥም ራስን አጽድቆ የሌላውን ሰው ኃጢአት የማሰብን ያህል ኪሳራ በክርስትና ሕይወት የለም፡፡ ሰው ወደ እግዚአብሔር የሚቀርበው የሌሎች ሰዎችን ኃጢአት ሲቆጥር ሳይሆን የራሱን በደል ሲቆጥር ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት ‘እኔ መተላለፌን አውቃለሁና ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና’ እንዳለው እግዚአብሔር ኃጢአትህ ተሰረየችልህ የሚለው ሰው የራሱን ኃጢአት ዘወትር የሚያስብ ሰው ነው፡፡

የነነዌው ቅዱስ ማር ይስሐቅ ‘መላእክትን ከሚያይ ሰው ይልቅ የራሱን ኃጢአት የሚያይ ሰው ይሻላል’’ ይላል፡፡ ባለ በገናው ‘እባክህ ጌታዬ ሥጠኝ መስታወት ፤ የሰው ሥራ ትቼ የእኔን አይበት’ እንዳሉ የራሱን በደል ማየት ከሚችል በቀር ይቅርታን የሚያገኝ የለም፡፡ ለብዙዎቻችን ከራሳችን ይልቅ የሰው ጉድፍ ማውጣት ይቀልለናል፡፡ ሰው ሆኖ ሌላ ሰውን ኃጢአተኛ ነህ የማለትን ኃጢአትና ትዕቢት ግን የለም፡፡ የሰዎችን ድክመት ባየን ጊዜ ከመሳደባችን በፊት እኛ ከዚያ ሰው በኃጢአት ብዛት በምንም እንደማንሻል ማሰብ አንደበታችንን ይሰበስብልናል፡፡

አባ ሲድራስ የተባለ አባት አንድ ወጣት መነኩሴ የወይን ፍሬ ሰርቀሃል ተብሎ ከገዳም ሲባረር አይቶት ተከትሎት ወጣ፡፡ አባታችን ወዴት ትሔዳለህ ሲሉት ‘እሱ ወይን ሰረቆ ከተባረረ እኔ የሠራሁት በደል ብዙ ነውና አብሬው ብወጣ ይሻላል ብዬ ነው’ አለ፡፡ በዚህም ምክንያት መነኩሴውን ከመባረር አዳኖታል፡፡ ወዳጄ እኔና አንተ በወንድማችን የምንፈርደው ከእርሱ የባሰ የተሸሸገ በደል ተሸክመን መሆኑን አንርሳ፡፡ ‘እኔ እንኳን ብዙ ኃጢአት የለብኝም’ የምንል ከሆነ ግን በድሏል ካልነው ሰው የከፋ ለንስሓ መንገድ የሌለው በደል ውስጥ ነን፡፡ እግዚአብሔር ሊያድነን የሚችለው ከምናምነው ኃጢአታችን እንጂ ከመመጻደቃችን አይደለም፡፡

በወንጌል ጌታችን ከተናገራቸው ታሪኮች እጅግ የተዋቡት ምንባባት ኃጢአታቸውን ያልደበቁና ያልተመጻደቁ ኃጢአተኞች ታሪክ ነው፡፡ የዘኬዎስ ፣ የባለ ሽቱዋ ማርያም ፣ ልትወገር የነበረችው ሴት ወዘተ ታሪኮች ኃጢአታቸውን አምነው ይቅርታ ያገኙ ሰዎች ታሪኮች ናቸው፡፡ ከእነዚህ አንዱ ታሪክ ስለ አንድ ቀራጭ ይናገራል፡፡ በቤተ መቅደስ ፈሪሳዊውና ቀራጩ ጎን ለጎን ቆመው ይጸልያሉ፡፡

ፈሪሳዊው በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ እንኳን ራሱን ዝቅ አያደርግም፡፡ አፉን ሞልቶ ጽድቁን ያወራል፡፡ ጽድቅን ተናግሮ የሚገኝ ነገር ያለ ይመስል ‘እጾማለሁ ፣ ዐሥራት አወጣለሁ’ እያለ ይመጻደቃል፡፡ አልፎ ተርፎ ‘እንደ ሌላ ሰው ሁሉ፥ ቀማኞችና ዓመፀኞች አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ’ ብሎ የቀራጩን ኃጢአተኝነት ለእግዚአብሔር አሳሰበ፡፡ ወዳጄ ሺህ ጊዜ በጎ ብትሠራ እንዲህ አደረግሁ ያልህ ቀን ዋጋ ታጣለህ ፣ ስለ ሌሎች ሰዎች ኃጢአት ማውራትና ማሰብ እስካልተውህ ለእኔ ፈሪሳዊ ነህ እያለን ነው መሐሪው ጌታ፡፡

ቀራጩ ግን ‘‘በሩቅ ቆሞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳ አልወደደም፥ ነገር ግን። አምላክ ሆይ፥ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር እላችኋለሁ፥ ከዚያ ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ’’ ይላል ጌታችን፡፡ በእውነት እንዴት ያለ ቃል ነው፡፡
ብዙዎቻችን ቤተ ክርስቲያን እንሔዳለን ፤ ጸልየን ተሳልመን ወደ ቤታችን እንመለሳለን፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ስንመለስ ጻድቅ ሆነን ተመልሰን እናውቅ ይሆን? እውቀት ገብይተን ፣ የመንፈስ እረፍት አግኝተን ፣ በአገልግሎት ብዛት የሥጋ ድካም ሸምተን እንመለስ ይሆናል፡፡ ጻድቅ ሆኖ ተመልሶ የሚያውቅ ይኖር ይሆን? ምናልባትም ቤተ ክርስቲያን ሔደን ከሰው ተጣልተን ያም ባይሆን እንደ ፈሪሳዊው የሰው ኃጢአት በመቁጠርበ

ደል ሸምተን እንመለስ ይሆናል፡፡

እንደዚህ ቀራጭ ከቤተ ክርስቲያን ጻድቅ ሆኖ ተመለሰ የሚባልለት ይኖር ይሆን? ልብ በሉ ቄጤማ ገዝቶ ተመለሰ አይልም ፤ ነፍሱን አግኝቶ እንጂ! ይህ ቀራጭ ጻድቅ ሆኖ የተመለሰው የወንድሙን ኃጢአት ትቶ የራሱን በማየቱ ነበር፡፡ ጌታ ሆይ ከዚህ በኋላ ቤትህን ረግጬ ስመለስ ጻድቅ አድርገህ መልሰኝ ኃጢአቴን አይቼ ለማልቀስ ዕንባን አድለኝ ከማለት በላይ ምንም ጸሎት የለም፡፡ ይህ ቀራጭ ደረቱን ይደቃ ነበር ይላል ፤ በዝማሬ ተሻምተን ከበሮ ከምንደቃው በላይ ደረታቸውን በዕንባ የሚደቁ ትሑታን ለእግዚአብሔር ጎልተው ይታዩታል፡፡

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
አቃቂ ኢትዮጵያ
+ ትሞታለህና ቤትህን አስተካክል +

ንጉሥ ሕዝቅያስ በጠና ታምሞ ተኝቶአል:: ነቢዩ ኢሳይያስ ሊጠይቀው መጣ:: ሆኖም እንደ ልማዱ እግዚአብሔር ይማርህ አላለውም:: ለጆሮ የሚከብድ ቃል ጥሎበት ወጣ:: "ትሞታለህና ቤትህን አስተካክል!"

ነቢዩ ይህንን ብሎት ከወጣ በኁላ ሕዝቅያስ ወደ ግድግዳው ዞሮ ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ:: አምላኩ በንግግር ብዛት የሚሰማ አምላክ አይደለምና ፊቱን ወደ መቅደሱ አቅጣጫ አዙሮ አለቀሰ::

ከጥቂት ደቂቃ በኁዋላ ነቢዩ ኢሳይያስ ሌላ መልእክት ይዞ ተመለሰ:: እግዚአብሔር እንዲህ ይላል :- ጸሎትህን ሰምቻለሁ ዕንባህን አይቻለሁ በዕድሜህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምራለሁ" (ኢሳ 38:5)

ሕዝቅያስ ቤትህን አስተካክል ከተባለ በኁዋላ ፊቱን አዙሮ ከማልቀስ በቀር ምንም አላደረገም:: ሕዝቅያስ ሆይ ከአልጋህ ሳትወርድ ያስተካከልከው ቤት ምን ዓይነት ቤት ነው? ለባሪያዎችህ መመሪያ ሳትሠጥ የምታስተካክለው ቤትስ እንዴት ያለ ነው? በደቂቃዎች ውስጥ ትሞታለህ ከተባልክ በኁዋላ ዐሥራ አምስት ዓመት ያስጨመረልህ ምን ዓይነት ማስተካከያ አድርገህ ነው? ለእኛም ንገረንና ዕድሜ እናስጨምር::

ሕዝቅያስ ከአልጋው ሳይነሣ ያስተካከለው ቤቱ ልቡ ነበር::
ልብህን ካስተካከልህ ቤትህ ይስተካከላል:: እግዚአብሔር እንደሆን ትሞታለህ ቢልህም መሞትህን አይፈልግም:: እርሱ ካንተ ጋር ጸብ የለውም::

"በውኑ ኃጢአተኛ ይሞት ዘንድ እፈቅዳለሁን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከመንገዱስ ይመለስና በሕይወት ይኖር ዘንድ አይደለምን?" ይላል መሐሪው (ሕዝ 18:23)

እርሱ ትሞታለህ የሚልህ መኖርህን ፈልጎ ነው:: አንዴ ብያለሁ ብሎ አይጨክንብህም:: በንስሓ ተመለስ እንጂ ምሬሃለሁ ለማለት ይቸኩላል:: አሁን ትሞታለህ ብዬው አሁን ትድናለህ ብለው ይንቀኛል ሳይል ተመልሶ ይምርሃል:: ኃጢአትህንም ወደ ጥልቁ ይጥለዋል:: በጎ እንድትሠራም ዕድሜ ይጨምርልሃል:: አንተ ብቻ ተመለስና አሁኑኑ ንስሓ ግባ::
ከበደል አልጋ ጋር ያጣበቀህን ፈተናም ድል መንሻው ጊዜ አሁን ነው:: ሕዝቅያስ በደቂቃ ዕንባ ምሕረት አግኝቶ ዕድሜ ካስጨመረ በዐቢይ ጾም ሙሉ የሚያለቅስ ምን ያህል ዕድሜ ያገኝ ይሆን?
ወዳጄ አንተም ተነሣና በዚህ ወር ቤትህን አስተካክል::
እንደ ሕዝቅያስ ፈጣሪህ ይጠብቅሃል:: የተቀየምከውን ይቅር በል የበደልከውን ካስ የሚበቀልህን የማይተኛ ጠላትህን ዲያቢሎስ ተበቀለው::

የዐቢይ ጾም የወንጌል ምንባብ ስለ ዲያቢሎስ ፈተና ሦስቱ ወንጌላት የተናገሩትን ስናስተውል ሦስት ዓይነት ጥቅሶች እናገኛለን::

አርባ ቀን ከዲያብሎስ ተፈተነ። (ሉቃ 4:2)

በምድረ በዳም ከሰይጣን እየተፈተነ አርባ ቀን ሰነበተ (ማር 1:13)
የሚሉት ቃላት ጌታችን ዐርባውንም ቀን መፈተኑን ያሳያሉ::

አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ከጦመ በኋላ ተራበ። ፈታኝም ቀርቦ እንዲህ አለው (ማቴ 4:2)

የሚለው ደግሞ ከጾሙ በኁዋላ የቀረቡለትን ሦስት ፈተናዎች የሚያሳይ ነው::
ሦስተኛው ጥቅስ ደግሞ ከተፈተነ በኁዋላ ያለው ሲሆን

ዲያቢሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየ። (ሉቃ 4:13) ይላል:: ዲያቢሎስ ፈተናውን ቢጨርስም የሚተወው ለጊዜው እንጂ መፈተኑን አያቆምም:: የዲያቢሎስ ፈተና ስልቱ ይቀያየራል እንጂ ይቀጥላል::

ዐቢይ ጾም ዲያቢሎስ ድል የተደረገበት የጦር ዐውድማ ነው:: በዚህ ወራት ድል ያላደረግነውን ፈተና በሌላ ጊዜ አናደርገውም:: ሰነፍ ገበሬ በሰኔ ይሞታል እንደሚባለው በዐቢይ ጾም የተኛ ክርስቲያን መቼም አይነቃም:: ከነስሙ ሁዳዴ (ሰፊ እርሻዬ) የምንለው ይህ ጾም ለነፍሳችን ብዙ ዘር የምንዘራበት አጋንንት መድረሻ የሚያጡበት ጾም ነው:: በዐቢይ ጾም ያልተገራ አንደበት መቼም አይገራም:: በዐቢይ ጾም ያልተፈወሰ ቂም መቼም አይፈወስም::

ጌታችን በወንጌል አንዴ ወደ እሳት አንዴ ወደ ውኃ የሚጥል ጋኔን ያለበትን ልጅ ሲፈውስ "ይህ ዓይነቱ ጋኔን ያለ ጾምና ጸሎት አይወጣም" ብሎ ነበር:: ሀገራችንን አንዴ ወደ እሳት አንዴ ወደ ውኃ የሚጥላት የጥላቻ ጋኔንም ያለ ጾምና ጸሎት አይወጣም::

ወዳጄ ከቁስልህ የምትፈወስበት ወር እንደደረሰ ዕወቅ:: አንተስ ብትሆን ልትላቀቀው እየፈለግህ ያቃተህ ክፉ ልማድ የለብህም:: እንደ ቅዱስ ጳውሎስ "የምፈልገውን መልካም ነገር አላደርግም የማልፈልገውን ክፉ ነገር ግን አደርጋለሁ:: ምንኛ ጎስቋላ ለዚህ ለሞት ከተሠጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?" ብለህ ምርር እንድትል ያደረገህ ኃጢአት የለም? እንግዲያውስ እወቀው:: ይህ ዓይነቱ ወገን ያለ ጾምና ጸሎት አይወጣም:: ይህ ጾም ቁስል የሚሽርበት ጾም ነው:: ይህ ጾም ሸክም ማራገፊያ ጾም ነው:: እንደ ሕዝቅያስ በዚህ ወር ቤትህን በንስሓ አስተካክል::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
የካቲት 15 2012 ዓ ም
ዝዋይ ኢትዮጵያ
2025/07/12 22:32:23
Back to Top
HTML Embed Code: