ሽማግሌው ሲጠባበቁት የነበረው አውቶብስ ስለመጣላቸው ለመሳፈር ተጠግተዋል፡፡ እግራቸውን አንስተው ወደ ውስጥ ሲገቡ በአጋጣሚ የአንድ እግር ጫማቸው ተንሸራቶ ውጭ ይቀራል፡፡

መልሰው ጫማቸውን ማግኘት ሳይችሉ አውቶብሱ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡

በዚህ ጊዜ ሽማግሌው ምንም አይነት የብስጭት ቃላት ሳያሰሙ የቀሪ እግራቸውን ጫማ ያወልቁና በመስኮት በኩል አሾልከው ወደ ውጭ ይጥሉታል፡፡

የሽማግሌውን ድርጊት ውስጥ ሁኖ ይመለከት የነበረ ወጣት ተሳፋሪ ለሽማግሌው እንዲህ ሲል ጥያቄውን አቀረበላቸው፡፡

“አባት ሲያደርጉ የነበሩትን ነገር እያየሁ ነበር፡፡ ለምንድን ነው ቀሪውን ጫማ የወረወሩት?” አላቸው፡፡

ሽማግሌውም ወዲያውኑ እንዲህ ሲሉ መለሱለት

“ ይኸውልህ ልጄ ሾልኮ የቀረውን ጫማ ሊጠቀሙበት የሚችሉት ይሄኛውም አብሮ ሲኖር ነው፡፡ እናም ለማንኛውም ያገኘው አካል ጥቅም እንዲሰጠው ወይም ዋጋ እንዲኖረው ስል ነው ይሄኛውን ጨምሬ መወርወሬ” አሉት፡፡

“የማትጠቀምበት ነገር ሁሉ ያንተ አይደለም!”
@heppymuslim29
የሃይስኩል ተማሪ እያለች ነበር ኒቃብ የለበሠችው፡፡ ያውም በአንድ ቀን ደዕዋ፡፡ ቀኑና ጊዜውን ለማስታወስ በትዝታ ወደኋላ ርቃ ሄደች፡፡ ዕለቱ ጁሙዓ ነበር፡፡ ከሶላት በኋላ ስለ ሒጃብ ደዕዋ ያደረገው ኡስታዝ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይናገራል፤ በተለይ ሴቶች ጆሮ እንዲሠጡት ይወተውታል ‹ሴት ልጅ ዐውራ ናት፣ ፈፅሞ ፎቷ መታየት የለባትም፣ ፊት ያልተሸፈነ ምን ሊሸፈን!፣ ኒቃብ ግዴታ ነው፤ ሴቶቻችን አላህን ፍሩ፣ ኒቃብ ልበሱ፤ ወላጆችም እንድታለብሱ …› እያለ ይመክራል፡፡

እዚያው እያለች ወሠነች፡፡ ወደ ቤቷ ገባች፡፡ ለወላጆቿ ነገረች፡፡ ኒቃብ መልበስ አለብኝ አለች፡፡ ከብዙ ክርክር በኋላ አሳመነቻቸው፡፡ ትምህርት ብትጨርስም ዉጤት አልመጣላትም፡፡ በግል ኮሌጅ አካውንቲንግ ተማረች፡፡ ዉጤቷ ጥሩ ነበር፡፡ ሥራ ፈለገች፡፡ ግና በኒቃቧ ምክንያት ተገፋች፡፡ ተቆጨች፣ ተናደደች ….

ዕድሜዋ ሲገፋ ይታወቃታል፡፡ ከአሥራ ቤት ወጥቶ ሀያ ገብቶ ወደ ሰላሳም ተጠግቷል፡፡ በዚህ በኩል የሥራ ማጣት፣ በወዲያ ከትዳር መዘግየት አስጨነቃት፡፡ ወንድ አትቀርብም፤ ወንዶችም ሊቀርቧት ይፈራሉ፡፡ የለበሠችው በልጅነት በመሆኑ ቀይ ትሁን ጥቁር፤ ቆንጆ ትሁን መልከ ጥፉ በአካል አያውቋትም፡፡ ብቻ በሩቅ ይሸሷታል፡፡ አንድም ኢማናቸውን ንቀው አሊያም ታጠብቃለች፣ አክራሪ ናት ብለው በመፍራት፡፡ ሁለት ፈተና በአንድ ጊዜ ወጥሮ ያዛት፡፡ የለፋችበት ትምህርት ቆጫት፤ የምትመኘው ትዳር ራቃት፡፡ ብዙ ጓደኞቿ ሥራ አገኙ፡፡ በዕድሜ ታናሾቿ ተራ በተራ አገቡ፡፡ ሒጃብን ለሥሙ ብቻ ጣል የሚያደርጉት ጥሩ ትዳር ያዙ፡፡

አላህ እሱን ለማይፈሩት ነው እንዴ የሚያደላው! አለች፡፡ ጥሩዎች ሲጎዱ መጥፎዎች ሲጠቀሙ አየች፡፡ ታዘበች፣ አሰበች፡፡ ኢማኗ እየደከመ መጣ፣ በራስ መተማመኗ ቀነሰ፣ ሌሎች የሚያወሩላት ወሬ ሸረሸራት፡፡ ከራሷ ጋር ታገለች፡፡ ኡስታዞችንና ዓሊሞችን ጠየቀች፡፡ ‹ልጅ ሆኜ ስለ ዲን ብዙም ሳላውቅ ነበር በችኮላ የለበስኩት፤ አሁን ማውለቅ እችላለሁ ?› አለች፡፡ አውልቂ የሚላት ጠፋ፡፡ ወደ ራሷ ተመለሰች፡፡ ከሁለት ያጣች እንደሆነች ታወቃት፡፡ ኒቃብ ከሥራም ከትዳርም እየከለከላት እንደሆነ ሸይጧን ሹክ አላት፡፡ ደስ እያላት ባለመልበሷ ምክንያት ምንም አጅር እንደማታገኝም ነገራት፡፡

ወረደች፣ ተጠራጠረች፣ ግራ ታጋባች …. በጥርጣሬ ዉስጥ ከምዋልል ለምን አላወልቀውም አለች፡፡ ከብዙ ትግል በኋላ አወለቀች፡፡ የመጀመሪያ ሰሞን እርቃኗን የሆነች ያህል ተሰማት፡፡ ግና አንድ አድርጌዋለሁ ብላ ራሷን አበረታታች፡፡ ያዩዋትና የሚያውቋት ደነገጡ፡፡ እሷ ናት ወይስ ሌላ? አሉ፡፡ እሷነቷን ሲያረጋግጡ ብዙ አወሩ፣ ተሳለቁ በወሬያቸው ይበልጥ ባሰባት፣ እልህ ተጋባች፡፡ በዚያው ሄደች፡፡ ወደ ቀደመ ቦታዋ አልተመለሠችም፡፡ እሷ የድሮ ኒቃቧን ረሣች፡፡ እነርሱም አውርተው ሲደክሙ ዘነጓት፡፡


ኒቃብ የለበስሽ እህቴ ሆይ!
1- ኒቃብ ስትለብሺ ዒባዳ መሆኑን አስቢ፤ ኒያሽ ቀጥ ያለና የተስተካከለ ይሁን፣
2- ጊዜው ቢረዝምም፣ ቀኑ ቢቆይም አላህ መልካም ባሮቹን ጥሎ አይጥልም፡፡
3- ኒቃብ በማውለቅና ፎቶ በመለጠፍ የሚገኝ ትዳር የለም፤
4- በአላህ መመካትሽ እንደ ወፍ ይሁን፣ ባዶ ሆዷን ወጥታ ሆዷን ሞልታ ትገባለች፣
5- በአላህ አምኛለሁ በይና ቀጥ በይ፣
6- ጥሩ መጨረሻ አላህን ለሚፈሩና ለጥንቁቆች ነው፡፡
7- አላህ በመልካም ነገር ላይ ፅናት ይስጠን፡፡

@heppymuslim29
አንድ ጨዋ የምትባል ወዳጄ ናት ሰሞኑን ስለምታገባ ቤተሰቦቿ በደስታ ፍንጥዝ ብለዋል። የምታገባዋ ግን የከፋት ትመስላለች ምክንያቱን ባላዉቅም የሆነ የደበቀችኝ ሚስጥር ያላት ትመስላለች። እንዴት አወቅሽ እንዳትሉኝ የሆነ ሰአት ናፍቃኝ እዚች ወዳጄ ጋ መጥቼ አብሬያት ስጫዎት ቆይቼ በፌስቡክ ያወኩት ጓደኛዬ ብላ ብዙ ፎቶዎችን አሳይታኛለች። ምን የሱን ብቻ እኔ ነኝ ብላ ያሳየችኝ ፎቶ መቼም ልዩነቱ የሰማይና የምድር ነው። እኔ ለራሱ እኔ ነኝ ባትለኝ ፈፅሞ አላዉቃትም ነበር። እድሜ ለዘመናዊ ካሜራዎች አረብ አይደል እንዴ የሚያስመስሉት እያልኩ ሳስብ ያ ወዳጄ ነዉ ያለችኝ ወንድ ደዉሎ ለረዥም ሰአት " ማሬ ዉዴ " እየተባባሉ ሲያወሩ ቆይተዉ የት ሆቴል መገናኘት እንዳለባቸዉም ተቀጣጥረዉ ስልኩን ዘጉት...
ወደ ሰርጉ ልመለስ ሰርጉ በጣም በብዙ ወጪ እናትና አባት ደስ ብሏቸዉ ዳሯት ግን ያገባት ጓደኛዬ ብላ በፎቶ ያስተዋወቀችኝ ሳይሆን ሌላ ሰዉ ነበር። እናትና አባት ደስታቸዉን ሳይጨርሱ ባል ተብየዉ ለምላሹ እናትና አባቷ ፊት አምጥቶ " አንቺ ርካሽ.... " ምን ያላላት አለ። የፈለገዉን ያገኘ አይመስለኝም። ወይ ጉድ እሺ እሷንስ ቢያንስ በጥፋቷ ይሆናል እናትና አባት ምን በወጣቸዉ እያልኩ ሳዳምጥ ቆይቼ እሱም ጥሏት እልም። አባትም " ዉጭልኝ ከቤቴ እናትም አልይሽ እስከለተ ሞቴ " የሰፈሩ ሰዉም ልጂቷን አንቅሮ ተፏት። ልጂቷ ግራ ሲገባት የድሮ ጓደኛ ተብዬ ላይ ድዉል እሱም " ምን ፈለግሽ እሷም እርጉዝ ነኝ። " ከኔ ሀሀሀ አባቱን ፈልጊ እኔኮ ልጅ አለኝ ባክሽ አጨቅጭቂኝ"ምን???ነገርኩሽ ሴትዮ መቸም አታገኚኝ።😡ልጅቷም መድሀኒት በሌለዉ በልብ ስብራት ስብር.....


# አንዳንዴ አንድ ጊዜ ብቻ የምታገኙትን እድል ለተፈቀደለት ሰዉ ካልሆነ ለማንም በፍፁም በፍቃዳቹህ አሳልፋቹህ አትስጡ !!!
@heppymuslim29
አገልጋያቸው ሐቢብ እራት ሳያመጣላቸው በመዘግየቱ ምክንያት ኢማም አል-ሐሰን አል-በስሪ "ምነውሳ በረሃብ ገደልከን"አሉት። !

ሐቢብም "ኢማም ሆይ አንድ በጣም የራበው ሰው መጣና አሳዝኖኝ ያለንን ሁሉ አውጥቼ ሰጠሁት። በርግጥ አንቱ እንዲህ ሲሉ ሰምቼ ነበር እኮ
" ኢማን ማለት በእጅህ ካለው ነገር በላይ አሏህ ዘንድ ባለው መተማመን ነው።" አላቸው።

አል-ሐሰንም " አንተ ሰው ከዕቀትህ ይልቅ የእምነት እርግጠኛነትህ (የቂንህ) በዛ። እሺ ይሁን ግማሹን ለሱ ሰጥተህ ግማሹን ለኛ ብታስቀር ምናለበት።" አሉት።

እንዲሁ እያወጉ እያለ በር ተንኳኳ። ሐቢብ በሩን ከፈተ። የሆነ ሰው በምግብ የተሞላ ትሪ ይዞ በር ላይ ቆሟል። "አለቃዬ እዚህ ቤት እንዳደርስ አዞኝ ነው።" አለ። ሐቢብም ወደ አል-ሐሰን ዘወር በማለት ፈገግ ብሎ " አንቱ እኮ ዕውቀትዎ ብዙ፣ እምነትዎ ግን ትንሽ ነው።" አላቸው። አል-ሐሰንም ፈገግ በማለት " ከፊት ነበርን ግን ቀደምከን።" አሉት።


የቂን፣ የቂን፣ የቂን ... በማለት ይደጋግማሉ የደዕዋ ሰዎች።በአላህ ላይ ፍፁም በሆነ መልኩ እርግጠኛ መሆን ማለት ነው።

@heppymuslim29
..በረሱሉ ዘመን አንዲት እህትሽ በአዉድቅ በሽታ ትሰቃይ ነበር። ያቺ ሴትም የልብና የሰዉነት ሀኪም ወደሆኑት ወደ ረሱሉ በመምጣት ችግሯን ተናገረች። ረሱሉም ሁለት ምርጫ ሰጧት። አንድም ዱዓ አድርገዉላት ከበሽታዉ መዳን አልያም በበሽታዉ ላይ ታግሳ ጀነትን ማግኘት።ሙዕሚኖች ዘንድ ከጀነት በላይ ዉድ ነገር አልነበረምና ታግሳ ጀነትን ማግኘትን መረጠች። ላኪን ሌላ ችግር አለ። እቺ እህትሽ አዉድቁ በሚጥልባት ወቅት የተወሰነ አካሏ ይገለጣል፣ ፀጉሯ የተወሰነዉ ክፍት ይሆናል። ይህ እንዲቀረፍላት ረሱሉ ዱዓ እንዲያረጉላት ጠየቀች። ረሱሉም ዱዓ አረጉላት።

አይገርምም! እቺ ሴት ኮ አዉድቁ ጥሏት ሰዉነቷ ቢገለጥ እንደማትጠየቅ ታዉቃለች። ግን እቺ እህትሽ በክብሯ አትደራደርምና አዉድቅ ጥሏት እንኳን የትኛዉም የሰዉነቷ ክፍል እንዲታይ አትፈቅድም።

እህቴ! አደራሽን በመሸፈኛሽ አትደራደሪ! በሂጃብሽ አትደራደሪ! ፀጉርሽን ለወንዶች ክፍት አታርጊ! አደራሽን ወንዶች በአይናቸዉ በልተዉ ሚጨርሱሽ ተራ ዕቃ እንዳትሆኚ!
:
እህቴ! አላህ ዘንድ ትራክሺያለሽና ራስሽን አታርክሺ!

ሰሀቢያት እህቶችሽ የሂጃባቸዉ ጉዳይ በጣም ያስጨንቃቸዉ ነበር። የሆነ ጊዜ ኡሙ ሰለማ የሴት ልጅ ከእግሯ በታች ልብሷን ምን ያህል ማርዘም እንዳለባት ረሱሉን ስትጠይቅ ረሱሉ አንድ ስንዝር እንደሚበቃ ነገሯት። እሷ ግን አንድ ስንዝር ሴት ልጅን ሙሉ በሙሉ መሸፈን አይችልም ብላ ተሟገተች። ረሱሉም አንድ ክርን እንዲያረጉና ከዚያ እንዳያስበልጡ ነገሯት። አጀብ! ኡሙ ሰለማ የዚህ ዘመን ወንዶች ልብስ አንድ ክርን ወደታች ረዝሞ፣ በታቃራኒዉ የሴቶቹ ደግሞ አንድ ስንዝር ወደላይ አጥሮ ብትመለከት ምን ትል ይሆን?

@heppymuslim29
የቢላል የጥንካሬ ምንጭ ምን ነበር?

ሚሥጥሩ ከአንዲት ሀሳብ የተቀዳ ነዉ፡፡ የሰዉ ልጅ እኩል ነዉ የሚለዉ የነብዩ ሙሃመድ (ሰዐወ) መልእክት ድንገት ሲወራ ሰምቶ ነዉ፡፡ ከመጤፍ የማይቆጠር ማንነቱ ክብር እንዳለዉ የሚናገር ሰዉ መልእክት ሲሰማ ወዲያዉ ከዉስጡ ተዋሃደ፡፡ ለአመታት በባርነት የገረደዉን ኡመያ ከልቡ ጠላ፡፡ በአረቢያ ስለሚሰማዉ አዲስ እምነት ጥበባትም ልቡ ተዘነበለ፡፡

"አስተዉል"

የተልፈሰፈሰ ወኔ ነበረዉ፡፡ ኡመያን ሲበዛ ይፈራዋል፤ ቁጣው ሁለመናዉን ነበር የሚያናጋበት፡፡ አሁን ግን እንደኡመያ የሚንቀዉ ሰዉ አልነበረም፡፡ ስለሰዎች እኩልነት የሚያዉጀዉን አዲስ አብዮት ከልቡ ተቀበለ፡፡ ስለመቀበሉም ዑመያ ሲሰማ እጅግ በንዴት ናረ፡፡ እንደወትሮዉ በፍርሃት ካባ ተጀቡኖ እየተንቀጠቀጠ ይጠብቀኛል ብሎ ቢያስብም ቢላል ልበ-ሙሉ እንደሆነ ቆመ፡፡ እንግዳ ነገር ያየዉ ዑመያም ተደናበረ፡፡

ትኩር ብሎ አየዉ፤ በቢላል ፊት ላይ ግን አንዳች ለዉጥ ሳይታይ ቀረ፡፡ ስለሰብዓዊ ዘሮች እኩልነት የሚያስተምረዉን የረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ጥበበ-ብርሃን መቀበሉን ሳያመነታ ነገረዉ፡፡ ቀና ብሎ ለማየት እጅግ ይንቀጠቀጥ የነበረዉ ቢላል ዑመያን ፊት ለፊት እያየ በዉስጡ ስለያዘዉ አዲስ ማንነት ሳይደብቅ ገለጠለት፡፡ ይህም እጅግ የከበደ ቅጣት አስከተለበት፡፡ ከ40 ዲግሪ ሙቀት በሚልቀዉ የአረቢያ አሸዋማ ሜዳ ላይ የገዘፈ አለት ሆዱ ላይ በመጫን ዑመያና ግብረ አብሮቹ ይገርፉት ጀመር፡፡ የግርፋቱ ምክንያት አዲስ የተቀበለዉን አስተሳሰብ (እምነት) እንዲተዉ ነዉ፡፡ ቢላል ግን ፍጹም አዲስ ሰዉ ሆነባቸዉ፡፡

ለብዙ ሆነዉ ከሚገፉት አለት በላይ የጠነከረ አቋም ያዘባቸዉ፡፡ የግርፋታቸዉ መጠን ሲጨምር የርሱም አቋም ይበልጥ እየጠነከረ መምጣቱ ግራ አጋባቸዉ፡፡ በመጨረሻም መግረፋቸዉ ሲያደክማቸዉ ከበረሃዉ ድንጋይ ሆዱ ላይ እንደጫኑበት ጥለዉት ሄዱ፡፡ ሲመለሱም ግን አቋሙን አልቀየረም፡፡

አዲስ በገነባዉ የዉስጥ ማንነቱ ጠነከረ፡፡ በየትኛዉም ዉጫዉ ተፅዕኖም ላይቀረይዉ ጸንቶ ቆየ፡፡ በመጨረሻ ከሞት ተርፎ ነጻ ወጣ፡፡ በዓለም የኢስላም ታሪክ ቀዳሚዉ የአፍሪካ ጥቁር የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሙዓዚን በመሆን በወርቃማ ብዕር የታሪክ ቅጽ ላይ ሰፈረ፡፡
____

በወንድም ሙሐመድ አሊ ቡርሐን ከተፃፈው የስኬት ፈለግ ቁጥር አንድ መፅሐፍ የተቀነጨበ

@heppymuslim29
አንዲት ምሽት በዓኢሻ (ረዲየላሀ አንሃ) . ቤት

ነቢዩﷺ በተራዋ ቀን ወደ ዓኢሻ ቤት መጡ፡፡ መኝታቸው ላይ ከጎኗ ጋደም አሉ፡፡ መተኛቷን ሲያውቁ ቀስ ብለው ሕፃን ልጅ ከእናቱ ጉያ እንደሚሾልከው ሁሉ ሹልክ ብለው ተነሱ፡፡ ልብሣቸውን ለበሱ፤ ጫማቸውን ተጫሙ፡፡ ኮቴ ሳያሰሙ ወደ በሩ አቀኑ፡፡ ወጡና በሩንም ቀስ ብለው ዘጉት፡፡
ዓኢሻ(ረዲየላሀ አንሃ) እንቅልፍ በደንብ አልወሰዳትም ነበርና ነቃች፡፡ ተናዳ ብድግ አለች፡፡ በርሷ ተራ ቀን ወደ ሌላኛዋ ሚስታቸው የሄዱ መሰላት፡፡ በቅናት በግና ተነሳች፤ ልብሷን ለብሳ በጨለማው ፋናቸውን  ተከተለች፡፡  በርቀት ወዴት እንደሚሄዱ አየች፡፡

ነቢዩﷺ   በዚያች ሌሊት  ተወዳጅ ባልደረቦቻቸው ወደተቀበሩበት መካነ መቃብር ወደ አልበቂዕ ነበር ያመሩት፡፡ ወደመጨረሻው ዓለም የተሸጋገሩትን ሶሐቦቻቸውን ለመጎብኘት፡፡ በአካል ቢለዩዋቸውም በመንፈስ አብረዋቸው አሉ። ደርሰው ሰላምታ አቀረቡላቸው፡፡ ዱዓእ አደረጉላቸው፡፡ የአላህንም ምህረት ለመኑላቸው፡፡

ከዚያም ወደ ቤት ተመለሱ፡፡ ልብሣቸውንና ጫማቸውን አውልቀው ወደ ፍራሻቸው ወጡ፡፡ ዓኢሻን ሲያዩዋት ዐይኗን ጨፍና ተኝታለች፡፡ ሳትተኛ የተኛች ሆናለች። ሆኖም ግን አተነፋፈሷን ያጤኑት ነቢይ ከምር እንዳልተኛች አወቁ፡፡ ወደሷ ዘወር ብለው ጠየቋት፡፡ “ዓኢሹ ምንድነው እሱ?” አሏት፡፡ ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ሰው ሆና አየተንጠራራች ዐይኗን ከፈተች፡፡ ተወነች፣ አስመሰለች።
“ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ አረ ምንም የተፈጠረ ነገር የለም፡፡” አለቻቸው፡፡
“ንገሪኝ ካልሆነ ግን ዉስጠ አዋቂ የሆነው አላህ ሁሉንም ነገር እንደሚነግረኝ እንድታውቂ” አሏት፡፡

ሐቋን አወጣች። “ የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ተነስተው  ሲወጡ አየሆት እና ተከትዬዎ ወጣሁኝ፡፡ ወደ ሌላ ሚስትዎ ይሄዳሉ ብዬ ስለጠረጠርኩ ነው፡፡” አለቻቸው፡፡
ትክክል አልሠራሽም፣ እንዴት እንዲህ ትጠረጥርያለሽ የሚል በሚመስል ሀሳብ በፍቅር ደረቷን መታ አደረጓት፡፡

ቀጥለው እንዲህ በማለት ጉዳዩን ገለፁላት “ ጂብሪል ወደኔ መጣና ኃያሉና የተከበረው አላህ ሄደህ ለአል-በቂዕ ሰዎች ምህረትን እንድትለምን አዞሃል ስላለኝ ሄጄ የአላህን ምህረት ለመንኩላቸው፡፡”

ነብዩ ከሚስቶቻቸው ሁሉ አብልጠው ዓኢሻን ይወዳሉ፡፡ ይህንኑ በተደጋጋሚ በአደባባይ ተናግረዋል። እሷም ታውቀዋለች። ግና ፍቅር ካለ ሁሌም ቅናት፣ ስጋት፣ የኔነት፣ ...... አለ።

@heppymuslim29
በሆነ ስብስብ ላይ ነበርን። ከ አጠገቤ የነበረው ቦታ ክፍት ስለነበር እኔው ጎን ባለው ክፍት ወንበር ተቀመጠች።ፍልቅልቅ ናት። አለባበስ እና መልኳ የሰጠ ነው እድሜዋ ከ 29 ወይ 30 ባያንስም ነገር ግን በምቾት የፋፋች የ 24 ወይ 25 አመት ትመስላለች።ከለበሰችው ሂጃብ ጋር የሚመሳሰለውን ጥቁር ቡኒ ቦርሳዋን ፊት ለፊታችን ባለው ጠረጴዛ ላይ አኑራው ሰፊውን አባያውን ሰብሰብ አድርጋ ተቀመጠች። እንደማንኛውም አብሮ እንደተቀመጠ ሰው በ ዙሪያችን ከነበሩ ሰዎችም ጋር አንዳንድ ነገሮችን በመወያየት ጀምረን " አግብተሻል?"ወደሚል ጥያቄ ዘለልን።
" አይ አላገባሁም"
"እንዳትቸኩይ! የቸኮሉበት ነገር አካሄዱ አያምርም" አለችኝ። ጣቶቿን አየሁ። ባለትዳር ናት።
" ቸኩለሽ ነበር አንቺ?"
" በጭራሽ!" ፈገግ አለች። ፈገግታዋ፣ በነገሮች ላይ ያላት በሳል አመለካከት፣ ቁጥብነት እና እርጋታዋ እጅግ ስለማረከኝ ልቀርባት ፈለግኩ።ተቀራረብን።
" እኔ አልቸኮልኩም ነበር። እሱ ነው የቸኮለው። ባለቤቴ ። እኔ ገና ማትሪክ ተፈትኜ እንደጨረስኩ በ ቤተሰብ ነበር ትውውቁ። ከ ቀድሞ ፍቅረኛው ጋር የተጣላበት ወቅት ነበር እና በኔ ሊደበቅ አገባኝ። ከዛ ግን ትዳሩን እንዳልፈለገው እና በትክክለኛው ጊዜ እንዳላገባ ሲረዳ የልጅ አባት ሆኖ ነበር። ረፍዷል አይደል?" አሁንም ፈገግ እንዳለች ናት። አንዳንዴ በ ሳቅ የተደበቀን ሃዘን ማየት ይቻላል። ይሄን ግን ማንም አይለየውም። በየመሃሉ የሚያውቋት ሰዎች እየመጡ ሰላም ሲሏት እና ሲያወሯት በፍጹም ከ ደቂቃዎች በፊት መራር የህይወት ቁስሏን እያወራች የነበረች መሆኗን ለማመን ይከብዳል።
" ከዛስ? ተለያያሽ?"
"እንዲያውም ይቀየራል ብዬ 2ኛ አረገዝኩ እንጂ" ከት ብላ ሳቀች። የሆነ ቀልድ ያወራን ያህል። እንዳልቆሰለች
" 3ልጅ አለኝ። ምን እንደሚገርመኝ ታውቂያለሽ ፍቅሩን እንደጠፋበት፣ ያ አዲስ ሙሽራ የነበርን ጊዜ የነበረውን ስሜት እንዳጣ፣ ስሜን ማቆላመጥ እንደሚያንቀው እያወቅኩ ዛሬ ከ 12አመት በኋላም እታገላለሁ። "ይቀየር" ይሆናል። ዛሬም የ ቀድሞ ፍቅረኛው እንዳላገባች እያወቅኩ፣ ስልኩ ላይ የሷ ቁጥር እንዳለ እያየሁ አሁንም በጌታዬ ተስፋ አድርጌ ስለ ትዳሬ እታገላለሁ።"
"መንገዱ አያምም?"
"ስለ መንገድ አይወራማ! መንገድ መንገዱን ማን ያወራዋል መነሻ እና መዳረሻ እንጂ"
" ተናግረሽው ታውቂያለሽ?"
"አንዴ ተናገርኩትና ቤቴ እሳት ሆነ እንዳልተበደልኩ ያህል ቤቴን አተራመሰው። ዝምም ብቻ ነበር አቅሜ። ስንጋባ ጥሩ የሚባል የ ማስተዳደር ቁመና ላይ ነበር። አሁንስ? ያ የለም በደህና ጊዜ ባሰራነው ቤት እያከራየን ነው የምንተዳደረው። አልሃምዱሊላህ ማለት ነው ግን አይደል?"
አውጥታ ተናግራ አታውቅም መሰል አንድ ነገር ባወራች ቁጥር ቀለል የማለት እና የመረጋጋት ስሜት አይባታለሁ። ታድላ! ፈገግ ስትል የሆነ የሚነዝር ነገር አለው። ጥንካሬዋን ካየሁ በኋላ ይሁን እንጃ ብቻ ፈገግታዋ ውስጥ የሆነ ሃይል አለ። የሚጋባ። የሚያስቀና። አንድ ቀጠን ረዘም ያለ ሰው ስልኩን እየነካካ ወደኛ ሲመጣ አየሁት። "መርየም" አላት እዛው ስልኩ ላይ እንዳቀረቀረ ። ስሟን እንኳ እንዳልተዋወቅካት የገባኝ ሲጠራት እና ምላሽ ስትሰጠው ነው። "መጣሁ ሃቢቢ" ብላ ቦርሳዋን ብድግ አድርጋ ብድግ አለችና "ልክ እንደዛች እናታችን ዓዒሻ ዘንድ እንደመጣችው አንሷሪ ሴት " ወላሂ አልረሳትም"እንደተባለችው አንቺንም አልረሳሽም። ስሜቴን ሳወራ የመጀመሪያዬ ነስደመጥም የመጀመሪያዬ ነው መሰለኝ ቀሎኛል። አላህ መልካሙን ይወፍቅሽ" ብላ ግንባሬን ስማኝ ሄደች። ከምንም ያልቆጠራትን ሰው "ሃቢቢ" ብላ ልቡን ለማለስለስ እየጣረች ተከተለችው። አላህ ይከተላት። "ትዳርሽ እምር ብሎ አላህ ተደብቀሽ ያነባሽውን ይካስሽ" ብዬ በልቤ መረቅኳት

ይህ እውነተኛ ታሪክ ነው። ከስም እና ከ አንዳንድ ከነበሩት ነገሮች ውጪ ምንም ያልተቀየረ የ 12 አመት የትዳር ህይወት! አላህ ያስተካክልላት!

@heppymuslim29
ተጠንቀቂ ተጠንቀቅ‼️‼️

በኩፍር ለሞተ ሰው “RIP” አይባልም “አሏህ ይማረው” አይባልም “የጀነት ያድርገው” አይባልም፡!


አሏህ በባሮቹ ላይ ግዴታ ካደረገባቸው ነገራቶች ትልቁ ግዴታ አሏህን አውቀው እሱን ብቻ መገዛታቸው ነው፡፡
የትኛውንም የኩፍር አይነት የሚፈጽምና በዚሁ ላይ የሞተ የአሏህን ምህረት እና እዝነት አያገኝም፡፡ለዚህም አሏህ ሱረቱ አ’ኒሳእ አንቀፅ (48) እንዲህ ይለናል፦

إِنَّ اللَّهَ لَا يَغْفِرُ أَن يُشْرَكَ بِهِ وَيَغْفِرُ مَا دُونَ ذَٰلِكَ لِمَن يَشَاءُ
(48 سورة النساء)

ትርጉም፡
<አሏህ በእርሱ ላይ ያሻረከን አይምርም ከኩፍር ውጭ ያሉትን ወንጀሎች ግን ለፈለገው ይምራል>

አሏህ በሌላኛው አያህ ሱረቱል ፈትህ አንቀፅ (13) ላይ እንዲህ ይላል፦

وَمَن لَّمْ يُؤْمِن بِاللَّهِ وَرَسُولِهِ فَإِنَّا أَعْتَدْنَا لِلْكَافِرِينَ سَعِيرًا
(13 سورة الفتح)

ትርጉም፡
<በአሏህ እና በመልእክተኛው የማያምን ካፊር ነው ለካፊሮች የጀሀነም እሳት ተዘጋጅታለች>


እንዲሁም ከእስልምና ውጭ የሆነ ሰው ነገ ከጀሀነም ቅጣት እንደማይቀነስለት አሏህ በተከበረው ቁርኣን ሱረቱ አል‘ዒምራን አንቀፅ (88) ላይ እንዲህ ይለናል፦

خَالِدِينَ فِيهَا لَا يُخَفَّفُ عَنْهُمُ الْعَذَابُ
(88 سورة آل عمران)

ትርጉም፡
<ካፊሮች ጀሀነም ውስጥ ዘውታሪ ናቸው ቅጣቱም አይቀነስላቸውም>


የካፊሮች ቅጣት በጀሀነም እጅግ ከባድ መሆኑን ከሚያመላክቱ አንቀጾች አንዱ በሱረቱ አን’ኒሳእ አንቀፅ (56) የሚከተለው ነው፦

كُلَّمَا نَضِجَتْ جُلُودُهُمْ بَدَّلْنَاهُمْ جُلُودًا غَيْرَهَا لِيَذُوقُوا الْعَذَابَ ۗ
(سورة النساء -56)

ትርጉም፡
<ስቃይን ይቀምሱ ዘንድ ቆዳዎቻቸው በተቃጠሉ ቁጥር ሌሎችን ቆዳዎች እንለውጥላቸዋለን>

አሏህ ከጀሀነም እሳት ይጠብቀን፡፡አሏህ ሐቁን ያሳውቀን፡፡እባካችሁ ልቦናችንን ተከትለን ሸሪዐ ጋር የሚጋጭ ነገርን አንፖስት፣ ሸሪዐን የሚጋጭ ፖስትንም ላይክ አናድርግ እባካችሁ አሏህን እንፍራ!

@heppymuslim29
በቤትህና በሥራ ቦታህ መካከል ያለው ርቀት ምን ያህል ነው ተብሎ ተጠየቀ
"በመኪና ከሆነ 500 ተስቢህና ተህሊል። በእግሬ ከሆነ ደግሞ 1200 ተህሚድና ኢስቲግፋርን ያዘክረኛል" ሲል መለሰ።

(አላህን ሳያስታውሱ የማያመሹ ልቦች)🧡
@heppymuslim29
በታሪክ ትልቁ ይቅርታ
...

አቡ ዘር ቢላልን ‹አንተ የጥቁር ልጅ!› በማለት ወረፈው፡፡

ቢላል በአቡ ዘር ንግግር ተቆጣ፣ በእጅጉ  አዘነም፡፡ ይህን ጉዳይ ለአላህ መልዕክተኛ ነው የምናገረው በማለት ወደርሣቸው ሄደ፡፡

በሰሙት ነገር የአላህ መልዕክተኛ ፊት በአንዴ ተለዋወጠ፡፡ እንዴት በእናቱ ታነውረዋለህ!፣ አንተ ገና የመሃይምነት ቅሪት ከዉስጥህ አልወጣም፡፡› ሲሉ ወቀሱት ለአቢ ዘርን፡፡

አቢ ዘር የሠራው ስህተት ከባድ መሆኑ ተገለጠለት፡፡ አለቀሰም፡፡

የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! ‹አጥፍቻለሁ ምህረት ይለምኑልኝ!› አላቸው፡፡

እያለቀሠም ከመስጂዱ ወጣ፡፡

ሄደና ቢላል እግር ሥር ወደቀ፡፡ ጉንጩንም ከአፈር አገናኘ፡፡

‹አንተ የተከበርክ፤ እኔ ወራዳ ነኝ፡፡ በእግርህ ፊቴ ላይ ካልቆምክ በስተቀር ፈጽሞ አልነሳም› አለው፡፡

ቢላልም እንዲህ አለ ‹ በአላህ እምላለሁ፤ በእግሬ ለአላህ ብላ ሱጁድ ያደረገች ፊት ላይ አልቆምም፡፡›

አቡ ዘር ከተደፋበት ተነሳ፡፡ ተቃቅፈው አለቀሱ፡፡ ይቅርም ተባባሉ፡፡

እኛስ በወንድሞቻችን ላይ ስንቴ ድንበር አልፈናል! ስንቴስ አጥፍተናል!??

@heppymuslim29
በፈተና ፊት መፅናት

ዙለይኻ ሦስት ነገሮችን ያሟላች እመቤት ነበረች፡፡ ሃብት፣ ዝና እና ማራኪ ዉበት፡፡ በዉበቷ በቀላሉ የሁሉንም ትኩረት ትስብ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ አንድ በአጠገቧ የሚኖር ወጣት ሰው ግን ስመለኖሯ ያስተዋለ አይመስልም፡፡ ነቢየላህ ዩሱፍ ይባላል፡፡ በሷ ቤት አገልጋይ ሆኖ የሚኖረው። ዩሱፍ አይደለም ስለዉበቷ ሊደነቅ ቀርቶ ስለመፈጠሯም ትዝ ብሎት አያውቅም፡፡ እሷ ግን በዩሱፍ ፍቅር ክፉኛ ተይዛለች፣ በዉበቱ ተማርካለች፡፡ እናም ለፍለጋው ቆረጠች፡፡ ስሜት ከተነሳሳ ይሉኝታ አያቆመዉም፡፡

ጉዳዩ ሲብስባት ነው መሰል አንድ ቀን እርሱ እቤት ዉስጥ እያለ የክፍሉን በር ዘጋች፡፡ በጥልቅ ፍላጎትም ተነሳስታ “ሀይተ ለክ” ና ተዘጋጅቼልሃለሁኝ!፡፡› አለችው፡፡ አላህ የማይወደዉን መጥፎ ነገር እንዲሠራ ጋበዘችው፡፡ በዚህ የትኛውንም እኔ ነኝ ያለ ጎረምሳ በሚያልፈሰፍስ ገጠመኝ ፊት፣ በዚህ የወንድ ልጅን ቀልብ በሚያቀልጥ ክስተት ፊት ነቢየላህ ዩሱፍ ግን ፀኑ፡፡ በአይሆንም ተጋፈጡ፣ ወንጀልን እምቢኝ አሻፈረኝ አሉ፡፡ አላህ የሰጣቸዉን ብርታትና ኢማን ተጠቅመው ተቃወሙ፡፡ አላህ ብርታቱን ይስጠን፡፡

ወንድ ልጅ በህይወቱ ሊገጥመው ከሚችለው ፈተና ሁሉ ትልቁ ፈተና፣ በጣም ቆንጆ፣ ወጣት እና ሃብታም ሴት ጋብዛው፣ በዚያ ላይ ብቻውን ባለበት ሁኔታ “እምቢ” ማለቱ ነው ይላሉ ዑለሞች፡፡

ስሜትን ከሚያንበረክክ ጎታች ኃይል ፊት በአላህ ጥበቃ ሥር ተጠልሎ “መዓዘሏህ!” (በአላህ እጠበቃለሁ!) ማለት የሚችል ስብዕና ያለው ሰው ምን ያህል ያሥቀናል በረቢ!፡፡

ወዳጆቼ! መልካም ሠርተን ያልተደሰትንበትና ዉስጣችን ያልረካበት ጊዜ የለም፡፡ መጥፎ ሠርተን ዉስጣችን ያልተረበሸበት፣ ወደ ዉስጥ ያላነባንበት ጊዜ የለም፡፡ የአላህ ጥበቃ አይለየን፡፡

ዩሱፍ “መዓዘሏህ” አሉ፡፡ ወዲያውኑ ምንም ነገር ሊጥሰው የማይችል የአላህ ጥበቃ ሥር ሆኑ፡፡ “ሀይተለክ” “ወደ እኔ ና!” ስትለው “መዓዘሏህ!” እኔስ ወደ አላህ ተጠግቻለሁ” በማለት ወደ አምላካቸው ሸሹ፡፡ በዚህም ወንጀልን የሚያሸንፉበት ብርታት ተላበሱ፡፡

አላህ በፈተና ፊት መቆም የምትችል ልብ ይስጠን፡፡
@heppymuslim29
ከሁሉም ሙስሊም ቤት የሚዘልቀውን እንግዳ ለመቀበል ሰው ሁላ ሽርጉድ ይላል። እኛም ቤት የተለየ ነገር አልተፈጠረም። በግ፣ ተምር፣ ለሚጠባበሱ ምግቦች ዱቄት የመሳሰሉትን ፣ ለቤቱ ፍካት መጋረጃ መቀየር፣ የትራስ ልብስ ማሰፋት… ኢድ ነገ የሚሆን ይመስል ሁሉም ቦታ አዲስ ድባብ ይፈጠራል። ይህን ድባብ ከሌለ ረመዷኑ ረመዷን አይመስለንም፣ ከቤታችን የምናስፈጥረው እንግዳ ከሌለን ረመዷን አይመስለንም፣ ፊጥራ ላይ ሾርባ፣ አሳንቡሳ፣ ቡስኩትና ሌሎች ብዙ አይነት ምግቦች ካልቀረቡ ሸህሩ ራህማ የደረሰ አይመስለንም፣ እኔም ጭምር አይመስለኝም #ነበር… አዎ ነበር! አሁን ረመዷን ለኔ ይህ አይደለም። ይህን ሀሳብ ያስቀየረኝ የአንድ ሰው ንግግር ነው። ኡስታዝ ሙሀመድ ሆብሎስ… ማንኛውም ሰው እንደሚያደርገው ለረመዷን የምቀይረው የስልክ ጥሪ ነሽዳ በመፈለግ ላይ በስህተት የተከፈተ ቪድዮ ላይ፣ ስለ ረመዷን አጿጿማችን ነበር ስሜታዊ ሁኖ የሚናገረው። ሰላምታና በነብያችን ﷺ ላይ ሰለዋት አውርዶ የሚከተለውን ተናገረ።

< አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ ከሁሉም በጣም አዛኙ፣ ሀያሉ፣ ረዛቁ… ጌታ ነው። እኛ ነን እዝነቱን ሽሽት የምንሄደው፤ ምህረቱን ችላ ብለን የምንኖረው፣ እኛ ነን ምርጫ ተሰጥቶን ስህተት የሆነውን ምንገድ በምርጫችን የምንከተለው። ነብያት፣ መፅሀፍን አውርዶልና መመሪያ ይሆነን ዘንድ እኛ ችላ ብለን የተውነው። እርሱ ግን የተውበት በሮችን ክፍት አድርጎ እኛን በመጠበቅ ላይ ነው። መጪው ቀን ጥሩ እድልን ያመቻችልናል። ሱሀቦች ረመዷን በተቃረበ ጊዜ በጣም በጉጉት ይጠብቁ ነበር። ይህ ወር ዘንግተነው የኖርነውን ዲን ለማስታወስ፣ የደረቀ ልባችንን ለማርጠብ፣ ያመጸ ነፍሲያችንን ለማስተካከል የሚመጣ እዝነት የሚወርድበት የአመቱ ልዩ ወር ነው። የፆመ ሰው ሁለት ዒዶች ይኖሩታል። የመጀመሪያው ኢድ ቤተሰቦቹ ጋ ሁኖ የሚያከብረው ሲሆን የሁለተኛው ግን አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ ፊት ቁሞ የስራውን ውጤት(ሽልማት) ሲመለከት ነው። ታዳ ይህን ወር ሌላውን ወር እንደምናሳልፈው ማሳለፍ ትፈልጋላችሁን? ረመዷን የቁርአን፣ የሰደቃ፣ የተሀጁድ፣ የተራዊህ፣ የዱኣ፣ የኢዕቲካፍ ወር ነው። በረመዷን ከዱንያ በቻልነው ርቀን ወደ አላህ የምንቃረብበት ወር ነው። ነገር ግን አሁን ረመዷንን የበዓል ወር ካደረግነው ቆይተናል። የኢባዳውን ወር የመተኛ ፣ የፆሙን ወር ምግብ የሚደፋበት፣ ተሀጁድ የመስገጃውን ወርን ሌሊቱን የአመፅ አድርገነዋል። ለዚህ ነው ናፍቆናል የምንለው?
የጀነት በሮች ክፍት ሁነው በተዘጋጁልን ወቅት፣ የጀሀነም በሮች በተዘጉበት፣ ሸያጢኖች በታሰሩበት በዚህ ግዜ ወደ አላህ ካልተጠጋን መች ነው የምንጠጋው? ለኢፍጣር ቤተሰብ ጋ መሰባሰብ ደስ ይለናል፣ ፊጥራ ስንገባበዝ ደስ ይለናል፣ መጥፎ ነው እያልኩ አይደለም። ነገር ግን በዛን ወቅት ማነው መግሪብን መስጂድ ጀመዓ ለመስገድ የሚያስበው! ማነው ስለ ኢሻና ተራዊህ የሚጨነቀው? ለአስራ አንዱ ወር ያልተውነውን ለረመዷን ኢፍጣር ሲባል እንተዋለን! አንብያ፣ ሶሀቦች፣ ሰለፎች ሂወታቸውን ሰጥተው ለኛ ያስተላለፉትን ዲን ሌላው ቀርቶ ረመዷንን እንኳን እንዴት እንደምፆመው ቢያዩ ምን ይሉንስ ነበር? ወንዶሞቼ ይህ ነው እድላችን ከጀሀነም እሳት ነጃ የምንወጣበት።

ብዙዎቻችን ዘንድ የኢድ ጣዕሙ ጠፍቷል። ኢድ ላይ ያለን ጉጉት ጠፍቷል። ለምን ይመስላችኋል? ረመዷኑን ሙሉ በየአይነት ምግብ ስንበላ፣ ቤተሰብ ጋ ስንገባበዝ ስንዘያየር፣ እቃ ስንቀያይር ውለን ምኑ አዲስ ሁኖብን ኢድ ብርቅ ይሆንብናል? ውድ ሙስሊም ወንድምና እህቶቼ ወሩ የፆም ነው፣ ወሩ የኢባዳ ነው፣ ወሩ ያንተ፣ ያንቺ ነው። ፈተና በምትሆኑበት ጊዜ ቀናችሁን በፕሮግራም መድባችሁ ሰአት እንዳታባክኑ እንደምትጠነቀቁት ሁሉ የረመዷንንም ወር ተጠቅማችሁበት ይለፍ። አምና ያባከነው ረመዷን ቁጭቱ ይሰማን፣ ለኸይር እንሽቀዳደም ይህ እድል ዳግም ላይመለስ ይችላልና… ወሰላሙ አለይኩም ወራህመቱላሂ ወበረካቱሁ>
ይህን ደዕዋ ከሰማሁ በኋላ ነሺዳውን መፈለግ ትቼ እንዴት እቅድ ማውጣት እንዳለብኝ ፕሮግራም አወጣሁ። ኢንሻአላህ ቀኑ ተቃርቦ አንድ ብዬ ልጀምር ተቃርቢያለሁ። አላህ በትክክል የምሰራበት ወር ያድርግልኝ!
:
ስንት ረመዷን አባክነናል? ከቡሉግ በኋላ ስንተ ረመዷን ፁመናል? 3፣5 ፣10፣15 ስንት? ስንት ረመዷን ፁመን ሳንፆም አባክነናል? ስንት? አሁንም አንድ እንኳን የሳራንበት ረመዷን እንዲኖር አትፈልጉምን? አሁንም ምሽቱን በፊልም፣ ቀኑን በእንቅልፍ፣ ሌሊቱን በመብላት ብቻ አሳልፈነው እንዲያልቅ ትመኛላችሁን? ኑ በእድሜያችን ቢያንስ አንድ ጊዜ እንኳ በትክክል የፆምነው ረመዳን ይኑረን! ኑ አጅሩን በአግባቡ እንጠቀም! ኑ የእዝነቱን ወር ወደ አዛኙ እንቃረብነት!
<(እንድትጾሙ የተጻፈባችሁ) ያ በርሱ ውስጥ ለሰዎች መሪ ከቅን መንገድና (እውነትን ከውሸት) ከሚለዩም ገላጮች (አንቀጾች) ሲኾን ቁርኣን የተወረደበት የረመዳን ወር ነው፡፡>
(2:185)

@heppymuslim29
"رمضان مبارك، أتمنى لكم شهرًا مليئًا بالفرح والمحبة والبركات. أسأل الله أن يُعطيكم رحمته ويبارك لكم ولعائلتكم في هذا الشهر الفضيل.
REMEDAN MUBARAK 🤍
:
ዛሬ ጠዋት በጠዋት ተነስቼ የቤቴን ስራ በፍጥነት ለመጨራረስ እየተራሯጥኩ ነው። የሰፈራችን የሴቶች ጀምዓ ከጠዋት "ከይፈ ነስተቅቢሉ ረመዷን" ፕሮግራም ስላዘጋጀ እዛ ለመሄድ ጓጉቻለሁ። ብዙ ጓደኞቼ እንድሳተፍበት ቢጠይቁኝም ገና አዲስ ስለተቀላቀልኩም በቂርአቱም ስለሚቀረኝ አድማጭ መሆንን መረጥኩ። ነገር ግን በጊዜ ተገኝቶ ተጋባዦችን ማስተባበል ላይ ላግዛቸው ተስማምተናል። ለዛም ነው ጧት ጀምሬ የምዋከበው። ስራዬን እንዳለቀ ልብሴን ቀያይሬ ወደዛው አመራሁ። ወደ ውስጥ ስገባ እየተንቀሳቀሱ ነበር። ተቀላቅያቸው ሰዎቹን አስተበበብረን ስንጨርስ ለተወሰነ ጊዜ ውጭ ቁሜ አዲስ ለሚመጡት እያመላከትኩ ቆየሁና ሰው አይመጣም በቃ ብዬ ሳስብ ወደ ውስጥ ዘልቄ ዳዐዋወቹን ማከተተተል ጀመርኩ። አንድ እህታችን እየተናገረች ነበር።

<<… እናም እህቶቼ ረመዷን ላይ በሀይድ ወቅት ተኝተን እየዋልን ቀናችንን አናባክን። በሀይድ ወቅት ላይ የተከለከልነው መፆምና መስገድ ብቻ እኮ ነው። ከዚ በላይ ብዙ ልንሰራቸው የምንችላቸው ዒባዳዎች አሉ። ብዙ ዑለሞች በስልካችን ቁርአን መቅራትን እንደምንችል ነግረውናል። ቁርአንን እርግፍ አድርገን አንተወው። እኔ እንደማምነው በስልክም መቅራቱ አይቻልም ካላችሁም ቢያንስ ቁርአንን አድምጡ። ተፍሲሮቹን አንብቡ። ብዙ ሌሎች የምንሰራቸውም ዒባዳዎች አሉ። በፆም የሚውሉ ቤተሰቦቻችንንም እናታችንንም ማገዝ ትልቅ አጅር አለው። በኒያ እንተግብረው። በስራ በምንጠመድበት ወቅት ደግሞም ደዕዋዎችንን እንስማ። ውሏችንን በሙሉ ከአላህ ጋ የተገናኘ እናድርገው።

ብዙዎቻችን በሀይድ ወቅት ተራዊህ መስጂድ ባለመሄዳችን መስገድ ተከልክሏል ብለን ተኝተን ሌሎች ሰግደው እስኪመጡ የምንጠብቅ አለን። እህቴ ሆን አትሳነፊ ሁሉም ወደ መስጂድ ሂዶ ብቻሽን የምትቀሪባትን ሰአት ከኢላሂ ጋ በደንብ አውሪባት። ባንቺና በአላህ መካከል ብቻሽን የምታወሪበት ሰኣት ነው። ስለ ዱንያሽ ጠይቂው፣ ስለ አኼራሽ አደራ በዪው፣ የነብዪን ﷺ ጉርብትና፣ ከጀነቱም በጀነቱል አዕላ ጀነተል ፊርዲውስ ውስጥ ቦታን እንዲያኖርልሽ ለምኚው። አላህ ዱኣን ሰሚ፣ ሙጂብ የሆነ ጌታ ነው። ከዛም ደግሞ አላህን አወድሺው፣ ሱብሃነሏሁ ወቢሃምዲህ ሱብሃነሏሂል ዐዚም ማለትን አብዢ። የአላህ መልዕክተኛ ﷺ ለምላስ ቀላል የሆኑ ሚዛን ላይ ግን ከባድ የሆኑ ዚክሮች መሆናቸውን አስተምረውናል። እያንዳንዱ አዝካሮች ብዙ ጥቆሞችን ያዘሉ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም ደግሞ ካስቀመጣችሁት ሰንበት ያላችሁትን ኪታብ አንስታችሁ ሙራጀዓ አድርጉት። ሀዲሶችንን አንብቡ። ማንበብ የታዘዝነው ተግባር ነው። ስለ ኢስላም ህግጋት ማወቅ ራሳችንን የምናንፅበት መንገድ ነው። እውቀት ከመጥፎ ነገር የሚከለክለን መሳሪያ ነው። ስለዚህ በነብዩ ﷺ አስተምሮ ራሳችንን እንገንባ። ጎረቤቶቻችንን እኩል ማፍጠራቸውንና አለመራባቸውን እንመልከት። ሰደቃን እንስጥ፣ ደካሞችን እንርዳ፣ ህመሙ እስካልያዘን በቀር እነዚህን ሁሉ መተግበር እንችላለን። ገና አልፆምንም ብለን ተኝተን አንዋል። በቻልነው መጠን አንዘናጋ ለማለት ነው። እኔም በተናገርኩት እናንተም በሰማችሁት ተጠቃሚ ያድርገን። ወሰላሙ አለይኩም ወራህመቱሏሂ ወበረካቱሁ።>>

ተናግራ እንደጨረሰች ወደ ቦታዋ ተመልሳ ተቀመጠች። አንድም ቀን ሀይድ ላይ ሁኜ በዒባዳ ስለማሳለፍ አስታውሼ አላውቅም። እንዳለችው ምግብ ሲያበስሉ "ነይ ጨው ቅመሺ" ብለው ሲጠሩኝ ካልሆነ ተጋድሜ ጊዜዬን ሳባክን ነው የምገኘው። ያለፈውን ላለመድገም ለራሴ ቃል ገባሁ። ይሄን ሳሰላስል መድረክ መሪዋ ቀጣዩን ፕሮግራም አስተዋውቃ አቅራቢዋን እየጋበዘች ነበር። ዳግም ትኩረቴን ሰብስቤ ለማዳመጥ ተዘጋጀሁ።
:
እህቴ ሆይ የመጣው ወር የፆም ብቻ ሳይሆን የኢባዳ ወር መሆኑን አትዘናጊ። ይህ እድልሽ ወደ አላህ የምትጠጊበት እድል ነው። በመሳነፍ እድሉን አታስመልጪ! በቻልሺው እንደሌላው ቀን በኢባዳ ተወጠሪ። ኢስቲግፋር አብዢ፣ ተስቢህ ተህሚድ ተህሊል አድርጊ። በሀይድ ምክንያት የምትዳከም ሴት ከመሆን ራስሽን ጠብቂ!

@heppymuslim29
ስለ ፆም 7⃣0⃣ ጠቃሚ ነጥቦች.pdf
481.5 KB
↪️ ስለ ፆም 70 ጠቃሚ ነጥቦች
↩️ سبعون مسألة في الصيام

ትርጉም፦
📖 በሸይኽ አቡ ዘር ሀሰን አቡ ጦልሃ አላህ ይጠብቃቸው
📚 للشيخ أبي طلحة أبي ذر بن حسن الولوي «حَفِظَهُ اللَّهُ»

በዚች መልዕክት የሚከተሉት ነጥቦች ተዳሰዋል:-
✔️ የፆም ትሩፋት

✔️ የፆም ስርዓቶች እና ሱናዎች

✔️ የፆም ህጎች
  => ጉዞ ላይ መፆም
  => የበሽተኛ ፆም
  => የሽማግሌ የደካማ እና የአዛዉንት ፆም
  => ለመፆም ኒያ ማድረግ
  => ማፍጠር እና መከልከል
  => ፆምን የሚያበላሹ ነገሮች
  => ሴቶችን የሚመለከቱ የፆም ህጎች

አንብቡት ትጠቀሙበታላችሁ!!!
ደግሞ አንዲት ነፍስ አለች አምና ከምትወደዉ ቤተሰብ፣ ወይ ከሀያቷ ተጋሪ ባለቤቷ ጋር ፣ አልያም ከምትወዳቸዉ ሷሂቦቿ ጋር ወይም የኔ ከምትላቸዉ ከምትሳሳላቸዉ ፣ አለፍ ሲልም ከምትኖርላቸዉ ነፍሶች ጋር የነበረች፣ ያፈጠረች ፣ የሰገደች ፣ የሳቀች ፣ የተጫወተች፣ ሱሁር ያሰረች ፣ ቁርአን የቀራች። ምን አልባትም አመት ተተክቶ አዲስ ረመዳን ስንከፍት 'ዘንድሮ' ወይእሷን ወይ እነሱን አጉድሏል ።

ብቻ እንደምንም እዚህ ላደረሰ ረቢ አልሀምዱሊላህ።

@heppymuslim29
ከአጠገቤ የተቀመጠ ልጅ ነው። በግምት አስራ ሁለት / አስራ ሶስት አመት ይሆነዋል። የልጅ መዳፎቹን ዘርግቶ መለመን ይዞዋል። ጠበቅኩት። እንደ ልጅኛ ከማስበው በላይ ዱዐውን አርዝሞታል። ሲጨርስ ምን ብለህ ዱዐ አደረግክ? ብዬ ጠየቅኩት
.
በልጅነት ጥርሶቹ ፈገግታውን እያካፈለኝ " ለኔ እና ለእናቴ የሚለፋን ሰው ጠብቀው።" እያልኩኝ ነበር አለኝ።
የልጁ አባት ይህንን ጊዜያዊ አለም ተሰናብተው ከሄዱ አመታት አልፈዋል። የቲም ነው።
ልጅ የህይወት ሽንቁራቸውን ለመሙላት ለሚጥር ሰው የዱዐ መዳፎቹን ዘርግቶ ይለምናል።
:


በረመዳን ላይ የቲሞችን እናስታውስ። እንዘይር። ከተትረፈረፈው ምግብ እናካፍል። መስጠት ውስጥ ሰላምን መሰጠት አለ። የቲሞችን መንከባከብ የሀቢበላህን ጉርብትናን የሚያስገኝ ተግባር ነው። የቲሞችን እናስታውስ..
በፍቅር መዳፍ እንደባብሳቸው...
ባዶነትን፣ ብቸኝነታቸውን ገሸሽ እናድርግላቸው። ስለ ማፍጠሪያቸው እንዳይጨነቁ እናድርግ።

@heppymuslim29
የተራዊሕ ለቅሶ ይፈቀዳል ወይስ አይፈቀድም?

ቀናት እየነጎዱ ነው፡፡ ረመዷን በተለይ ከ15 ቀን በኋላ አትደርሱብኝም፣ አትይዙኝም…. በሚል መልኩ እየፈረጠጠ ነው፡፡ የረመዷን ወዳጆችም ረመዷን ከማለቁ በፊት በስስት እያለቁ ነው፡፡

የማታውን ተራዊሕ በሁለት በሁኔታቸው የተለያዩ የአላህ ባሮች መካከል ነበር ቆሜ የሰገድኩት፡፡ የቁኑት ዱዓእ ላይ ስንደርስ በቀኜ በኩል የነበረው ተንሰቅስቆና ድምፅ አውጥቶ ማልቀስ ጀመረ፡፡ በግራዬ በኩል ያለው ደግሞ አሁንም አሁንም የአልቃሹን ሁኔታ የጎሪጥ አሻግሮ ይመለከታል፡፡ አልተመቸው ይሆን? ምን ይነፋረቅብናል? እያለ ይሆን … ብቻ ዉስጡን ባላውቅም ሀሳቡ እንደተሰረቀና ተረጋግቶ መስገድ እንዳልቻለ በግልጽ ያስታውቃል፡፡

በሶላት ወቅት አላህ ዘንድ ያለን ደረጃ የሰማይ እና የምድር ያህል የሚራራቅበት ሁኔታ አለ፡፡ አልቃሹ ይሁን ዝም ባዩ በላጩን የሚያውቀው አላህ ብቻ ነው፡፡

ቁርኣንን ሰምቶ መልእክቱ እያስተነተኑ ማልቀስ ነቢያዊ ሱና ነው፡፡ በአንድ ወቅት ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ለዐብደላህ ኢብኑ መስዑድ “ቁርአንን አንብብልኝ” አሉት፡፡ “በርስዎ ላይ ወርዶ እንዴት አነብልዎታለሁ?” አላቸው፡፡ “ከሌላ ሰው መስማት ደስ ይለኛል” አሉት፡፡ ከአን-ኒሳእ ምዕራፍ አነበበላቸው፡፡ “ወጂእና ቢከ ዐላ ሃኡላኢ ሸሂዳ” የሚለው አንቀጽ ላይ ሲደርስ “ይብቃህ” አሉት፡፡ ዘወር ሲሉ ዐብደላህ የረሱሉን ሰ.ዐ.ወ. ፊት ተመለከተ፡፡ ዐይናቸው በእንባ ርሶ ነበር፡፡ ያለ ድምፅ እንባቸው ዝምብሎ ይፈስ ነበር።

በቁርኣን ማንባት የአላህ መልካም ባሮች ምልክት ነው፡፡ አላህ ሱ.ወ. ሲገልፃቸው  “የአልረሕማን አንቀጾች በነሱ ላይ በተነበቡ ጊዜ ሰጋጆችና አልቃሾች ኾነው ይወድቃሉ፡፡” ይላቸዋል፡፡ (መርየም ፡58)

ቁርኣን ሲነበብ ማልቀስ ሕያው ቀልብ መሆን ምልክት ነው፡፡ አልቃሾችም የአላህ ፍራቻ የሰረፀባቸው ናቸው፡፡ በሶላት ላይ ቁርኣንን ሰምቶ ማልቀስ የተከለከለ አይደለም፡፡ ሶላትንም አያበላሽም። የርሳቸው ለቅሶ ድምፅ ያወጣ አልነበረም፡፡ ሳቃቸዉም እንደዚያው ነው ይላሉ አንዳንድ ዑለሞች፡፡ ድምፅ የለውም።

ቁርኣንን ሲያነቡ አናቅፁን እያስተነተኑ የጀመሩትን መጨረስ የሚከብዳቸው ብዙ ነበሩ፡፡ አቡበክር ረ.ዐ. ለሶላት ሲቆሙና ቁርኣንን ሲያነቡ ከለቅሶ የተነሳ ድምፃቸው በትክክል አይሰማም ነበር ይባላል፡፡ ዑለሞቹ በቁርኣን እንደሚለቀሰው ሁሉ መልዕክቱን እያሰቡ በዱዓ ማልቀሱም ችግር የለውም ብለዋል፡፡

በሁሉም ዉስጥ ግን መጠንቀቁ ተገቢ ነው‼️ ነፍስያ እንዳትጫወትብን፣ ዒባዳችን ለይዩልኝና ይስሙልኝ እንዳይሆን ራስን መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ ቀደምት ደጋግ የአላህ ባሮች ለቅሶአቸው እንዳይታይባቸው በእጅግ ይጠነቀቁ ነበር፡፡ አንድ ቀን ሳይታወቅባቸው ዕድሜ ልክ ያለቀሱ ነበሩ። አላህን አስታዉሳ በድብቅ ማንም በሌለበት ያለቀሠች ዐይን ለጀነት የታጨች መሆኗንም ነቢዩ ሰ.ዐ.ወ. ተናግረዋል፡፡

የምንለምነው አምላክ ሰሚ፣ ተመልካች እና ሁለመናችንን አዋቂ ነው፡፡ ስለሆነም ብሶታችንና ሓጃችንን ለማሰማት የግድ መጮህ አይጠበቅብንም። ዱዓችንም ሆነ ለቅሶአችን በድብቅ ቢሆን ይመረጣል፡፡ አላህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ይላል “ ጌታችሁን ተዋርዳችሁ በድብቅም ለምኑት እርሱ ወሰን አላፊዎችን አይወድምና፡” (አል-አዕራፍ 55)

የአላህ ባሮችን አታልቅሱ ማለት ይከብዳል፡፡ ግና በተለይ በጀማዓ በሚሰገድበት ወቅት ለቅሶው ድምፅ የማይወጣበት ሌሎችን በማይረብሽና ትኩረት በማይሰርቅ ከራስ ጋር በሆነ መልኩ ቢሆን ይመረጣል፡፡  በለቅሶ የሚሸነፍና የማያስችለው ሰው ከሆነ ግን ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡
ወሏሁ አዕለም

@heppymuslim29
በአቀራሩ መላዕክት የተገረሙበት ሶሃባ
ኡሰይድ ኢብኑ ሁደይር (ረዲየሏሁ አንሁ)


ኡሰይድ ኢብኑ ሑዶይር በአንድ ምሽት የቤት ውስጥ ሥራዎቹን በመፈፀም ላይ ነበር። የሕያ የተባለ ልጁም ከጎኑ ተኝቷል።ጥቂት ፈንጠር ብሎም ለጂሃድ የተዘጋጀ ፈረሱ ታስሯል። ሌሊቱ ነፋስና ውሽንፍር የሌለበት ፀጥ ያለ ነበር። የከዋክብቶች ዓይን መሬትን በአትኩሮት የሚመለከቱ ይመስላሉ። ኡሰይድ ይህን ግርማ ሞገስ የተላበሰ ሌሊት ቁርኣን በማንበብ ሊያስጌጠው ፈለገ። ማንበቡን ጀመረ።

«አሊፍ ላም ሚም ዛሊከል ኪታቡ ላ ረይበ ፊህ… … ዩቂኑን።»

ፈረሱ ቁርኣን ሲሰማ የታሰረበትን ገመድ እስኪበጥስ ድረስ በደስታ ዘለለ። በሁኔታው የተገረመው ኡሰይድም ዝም አለ። ፈረሱም እንቅስቃሴውን አቆመ። ማንበቡን ቀጠለ፡-

«ኡላኢከ ዐላ ሁደን ሚን ረብቢሂም ወኡላኢከ ሁሙል ሙፍሊሑን።»

ፈረሱ አሁንም የደስታ እንቅስቃሴውን ቀጠለ። ካለፈው በበለጠ ሁኔታ። ኡሰይድ ዝም አለ። ፈረሱም እንዲሁ ይህንኑ ድርጊት ደጋግሞ ፈጸመ።
ፈረሱም ምላሽ መስጠቱ አልቀረም፡፡ ቁርኣን ማንበቡን ሲቀጥል ፈረሱም ደስታውን ይቀጥላል። ሲያቆም ደግሞ እርሱም እንቅስቃሴውን ይገታል። ልጁ የሕያን ፈረሱ እንዳይረግጥበት በመስጋቱም ሊቀሰቅሰው ተጠጋ። በቅጽበት ወደ ሰማይ እይታውን አቀና። ታይቶ የማይታወቅ ጽልመታዊ ዳመና አስተዋለ። በደመናው ላይ
የተንጠለጠለ የሚመስል ብርሃን መታየት ጀመረ። ከአድማስ አድማስ ብርሃን ፈነጠቀ። ይህ ብርሃን ግን ከእይታው እስኪሰወር ድረስ ወደ ላይ እየራቀው ሄደ።

🌅ሲነጋ ወደ መልዕክተኛው ﷺ በመሄድ ያጋጠመውን ክስተት አወሳላቸው።

«መላእክት ናቸው። አንተን ሲያዳምጡ ነበር ኡሰይድ ሆይ! ማንበብህን ብትቀጥል ኖሮ ለሰዎች ግልጽ በሆነ መልኩ በታዩ ነበር።»

አጂብ!!!
📒:سور من حياة الصحابة
@heppymuslim29
2024/05/03 18:30:21
Back to Top
HTML Embed Code: