Telegram Web Link
ወርልድ ሊንክ ኮሌጅ ከዌስተርን ክሊፍ ዩኒቨርስቲ  ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ

ወርልድ ሊንክ ከተለያዩ አለም አቀፍ የትምህርት ተቋማት ጋር በመሆን በኦን ላይን እንዲሁም በውጭ ሀገራትና በአገር ውስጥ በማስተማር የትምህርት ማስረጃዎቻቸውን  በመስጠት ላይ እንደሚገኝ የኮሌጁ የኮሙኒኬሽን  ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዘላለም ደምስ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።

በተለያዩ ዓለም ሀገራት ላይ ከሚሰጣቸው የኦን ላይን የትምህርት ማስተማር ሂደት ውስጥ በእንግሊዝ አገር ብቻ ከ1000 በላይ ስልጠናዎችን ለተማሪዎቹና ለሰልጣኞቹ አገልግሎት መስጠቱ ተጠቁሟል። በአገር ውስጥ መምህራን እና ከግማሽ በላይ የሚሆነውን በውጭ ሀገራት ከፍተኛ ልምድና ትምህርቱ ባላቸው የውጭሀገር መምህራን ትምህርቱ እየተሰጠ ይገኛል፡፡

ከዚህም ጋር በተያያዘ ይህንኑ የትምህርት ስርዓት  ከፍ በማድረግና ለሁሉም የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ አሜሪካን ሃገር ከሚገኘው ታዋቂ ዩኒቨርስቲ እና ኮሌጅ ወርልድ ሊንክ ኮሌጅ ጋር በርቀት ትምህርት ስምምነት ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው ትምህርቱን በመከታተል የአሜሪካን ዲግሪ እንዲያገኙ ለማስቻል በሁለቱ ተቋማት መካከል የሚደረግ የመግባቢያ ስምምነት አካሂዷል።

በዚህም ተማሪዎች በቴክኖሎጂ፣ በአይሲቲ፣ በቢዝነስ ሙያ ትምህርታቸውን እዚሁ አገራቸው ውስጥ በመሆን በመማር ዓለም አቀፍ ደረጃ የአሜሪካን ዲግሪ ዕድል 75% ስኮላርሽፕ የመማርም ዕድል ይዞ ቀርቧል። በሁለቱ አገራትና በሁለቱ ተቋማት በሚደረገው ስምምነት ተማሪዎች ምቹ ዕድል፣ ጥራት ያለው ትምህርትና እጅግ በተመጣጣኝ ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ስምምነት መሆኑን አቶ ዘላለም ደምስ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል

በኤደን ሽመልስ
#ዳጉ_ጆርናል
በኦሮሚያ ክልል ኤጀሬ ማክሰኞ ማለዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ2 ሰዎች ህይወት አለፈ

ከሆለታ ከተማ መነሻውን በማድረግ ወደ ጊንጭ ሲጓዝ የነበረ የሕዝብ ማመላለሻ በመገልበጡ  በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የኤጀሬ ወረዳ ፖሊስ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

የኤጀሬ ወረዳ ፖሊስ ፅፈት ቤት የትራፊክ ደህንነት እና ቁጥጥር አስተባባሪ ምክትል ኢንስፔክተር  ከተማ በየቻ ለብስራት ሬዲዮ እንደተናገሩት ማክሰኞ ንጋት  አስራ አንድ ሰዓት ተኩል ላይ የሠሌዳ ቁጥር ኮድ 3-44080 ኦሮ የሆነ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ 15 ሰዎችን በማሳፈር ከሆለታ ከተማ በመነሳት ወደ ጊንጭ ከተማ ሲጓዝ ኤጀሬ ቢርብርሠ ለኩ የተባለ ቦታ መንገዱን ስቶ በመገልበጡ አሽከርካሪውን ጨምሮ በሁለት ሰዎች ሞት ተመዝግቧል።

ተሽከርካሪው ያለ መውጫ እንዳይነጋበት በፍጥነት ሲጓዝ መንገድን ስቶ እንደተገለበጠ የተናገሩት አስተባባሪው በአደጋው በአስራ ሶስት ሰዎች ላይ ከባድ አደጋ ደርሳል።

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ተጎጂዎች አዲስ አበባ እና ሆለታ ሆስፒታሎች የተላኩ ሲሆን አደጋው በአደጋ ቴክኒክ መርማሪዎች ሲጣራ ከፍጥነት በላይ መንገዱን ስቶ እንደተገለበጠ መረጋገጡን ምክትል ኢንስፔክተር ከተማ በዬቻ ጨምረው ለጣቢያችን ተናግረዋል።

በትግስት ላቀው
#ዳጉ_ጆርናል
የዶናልድ ትራምፕ የእርዳታ ቅነሳ በ2030 ከ14 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለሞት ሊዳርግ ይችላል ተባለ

በላንሴት ሜዲካል ጆርናል ላይ የታተመ ጥናት በዩኤስኤአይዲ የሚደገፉ መርሃ ግብሮች ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ በአለም ከ91 ሚሊየን በላይ ሞትን መከላከል ችለዋል ያለ ሲሆን አሃዙ በህፃናት ላይ 30 ሚሊዮን ሞትን ማስቀረት መቻሉን ያጠቃልላል ተብሏል።

ጥናቱ እንደሚያሳየው የዩኤስኤአይዲ የገንዘብ ድጋፍ ከኤችአይቪ/ኤድስ ሞት 65 በመቶ፣ 51 በመቶው ከወባ እና 50 በመቶው ከሌሎች የሐሩር ክልል በሽታዎች ቅነሳ ጋር ይያያዛል ብሏል። ነገር ግን እየተካሄደ ያለው ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ መቋረጥ በ2030 በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ ከ14 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለሞት ሊዳርግ እንደሚችል ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል። ይህም ከአምስት ዓመት በታች በሆኑ ሕፃናት ላይ 4.5 ሚሊዮን ሞትን ያስከትላል ተብሏል።

በተባበሩት መንግስታት ከተመዘገቡት መዋጮዎች ቢያንስ 38 በመቶውን የምትይዘው አሜሪካ በአለም ትልቁ የሰብአዊ እርዳታ ለጋሽ ነች። ባለፈው አመት 61 ቢሊየን ዶላር ለውጭ ዕርዳታ የሰጠች ሲሆን ከግማሹ በላይ የሚሆነው በዩኤስኤአይዲ በኩል መሆኑን የመንግስት መረጃ ያሳያል።

"የእኛ ግምት እንደሚያሳየው በ 2025 የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ የታወጀው ድንገተኛ የገንዘብ ድጎማ ቅነሳ ካልተቀየረ በ 2030 እጅግ በጣም አስደንጋጭ የሆኑ ሞት ሊፈጠር ይችላል" ሲል ጥናቱ አመልክቷል።

በሚሊዮን ሙሴ
#ዳጉ_ጆርናል
በደቡብ ወሎ ዞን የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈፅሞ ከህግ ተሰውሮ የነበረው ግለሰብ ከአራት ዓመት በኃላ በቁጥጥር ስር ዋለ

በደቡብ ወሎ ዞን ወረኢሉ ወረዳ በአስገድዶ መድፈር ተጠርጥሮ ከህግ ተሰውሮ የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን የወረዳው ፖሊስ አስታውቋል።

ተከሳሽ ጫኔ ታደሰ በለጠ ግንቦት 24 ቀን 2013 ዓ.ም 03 ቀበሌ ልዩ ቦታው ጎላ በተባለ ቦታ የ 18 አመት ወጣት ደፍሮ ከአካባቢው ይሰወራል የወረዳው ፖሊስም ወንጀሉ በተፈፀመበት ቦታ ተገኝቶ ታማሚዋን ወደ ህክምና ከላከ በኋላ ተጠርጣሪውን በመፈለግ የምርመራ መዝገቡን አጠናቆ ለሚመለከተው የፍትህ አካል ይልካል።

የወረኢሉ ወረዳ ፍረድ ቤትም ጉዳዩን ሲመረምር ቆይቶ ተጠርጣሪው ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ሐምሌ 06 ቀን 2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሌለበት በ 6 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ይወስንበታል ፤የወረዳው ፖሊስም ክትትሉን ሳያቆም ተጠርጣሪውን ለህግ ለማቅረብ ሲያፈላልግ ቆይቶ ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም የእስር ውሳኔውን እንዲፈፅም በቁጥጥር ስር አውሎ ለወረኢሉ ወረዳ ማረሚያ ቤት ማስረከቡን ብስራት ሬዲዮ ሰምቷል።፡

#ዳጉ_ጆርናል
ከዘንድሮው የኢ/ያ ፕሪሜርሊግ ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚወርድ ቡድን እንደማይኖር ታወቀ

👉 የ2018 ዓ/ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ20 ቡድኖች መካከል እንዲደረግ ተወስኗል


የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ/ም ባካሄዱት ስብሰባ የተለያዩ ወሳኔዎችን በማስተላለፍ ተቋጭቷል።

ከተወሰኑት ውሳኔዎች መካከልም፤ የሲዳማ ቡና ስፖርት ክለብ የታገዱ ተጫዋቾችን በማሰለፍ ያሸነፈው የኢትዮጵያ ዋንጫ በፎርፌ ተሸናፊ ሆኖ ዋንጫው ለወላይታ ድቻ ተመላሽ እንዲደረግ ውሳኔ ተሰጥቷል።

በዚህ መሰረትም የወላይታ ድቻ ስፖርት ክለብ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የ2025/26 የውድድር ዘመን ተሳታፊ እንዲሚሆን ተገልፆል።

ከዚህ በተጨማሪ የ2018 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በ2017 ተሳታፊ የነበሩ 18 ክለቦች እና ከከፍተኛ ሊግ ያደጉ ሁለት ቡድኖችን በማካተት በ20 ክለቦች መካከል እንዲካሄድ እና በ2018 የሊግ ውድድር አራት ክለቦች ወደ ከፍተኛ ሊግ እንዲወርዱ፤ 2 ክለቦች ከከፍተኛ ሊግ እንዲያድጉ እንዲደረግ ተወስኗል።

ዝርዝር ውሳኔዎች ከምስሉ መመልከት ይቻላል!

#ዳጉ_ጆርናል
ትራምፕ በሶሪያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ ትእዛዝ ሰጡ

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሶሪያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ እንዲነሳ የስራ አስፈፃሚ ትዕዛዝ ፈርመዋል።ይህ እርምጃ ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ከስልጣን ከተወገዱ ከስድስት ወራት በኃላ በሀገሪቱ የኢንቨስትመን በሮችን ለመክፈት ያስችላል ተብሎ ታምኖበታል። የትራምፕ የሰጡት አዲስ መመሪያ ለሶሪያ ልማት፣ ለመንግስት ስራ እና የሀገሪቱን ማህበራዊ መዋቅር መልሶ ለመገንባት ወሳኝ በሆኑ አካላት ላይ የተጣለው ማዕቀብ እፎይታ እንደሚሰጥ የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ኤእአ 2011 በሀገሪቱ የእርስ በእርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንድቶ የሶሪያ መንግስት በአሜሪካ ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት ተጥሎበት ቆይቷል። በኤክስ ላይ በተለጠፈው መግለጫ የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሳድ ሀሰን አል-ሻይባኒ የትራምፕን ውሳኔ በደስታ እንደሚቀበሉ በመግለፅ "ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው ይህ ማዕቀብ መነሳት የመልሶ ግንባታ እና የልማት በርን ይከፍታል" ብለዋል ። "በኢኮኖሚ ማገገሚያ ላይ ያለውን እንቅፋት በማንሳት ሀገሪቱን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ክፍት ያደርጋታል" ተብሎ ይጠበቃል።

ከቀድሞው መንግስት የሰብአዊ መብት ረገጣ ጋር የተያያዙ ድንጋጌዎችን ያካተተው ማዕቀብ በሀገሪቱ ውስጥ የመልሶ ግንባታ ጥረቶችን አበላሽቷል። በአል-አሳድ ዘመን የሶሪያን ኢኮኖሚ ወደ ውድቀት አፋፍ እንዲያደርስ ሲነገር ቆይቷል። ትራምፕ በግንቦት ወር በመካከለኛው ምስራቅ ባደረጉት ጉብኝት በሶሪያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንደሚነሳ ቃል ገብተው እንደነበር ይታወሳል። "ዩናይትድ ስቴትስ የተረጋጋች፣ የተዋሃደች እና ከራሷ እና ከጎረቤቶቿ ጋር ሰላም የሰፈነባትን ሶሪያን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነች" ሲሉ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት አዲስ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል
በደብረ ማርቆስ ከተማ የፖሊስ አመራርን  ገድሎ ለማምለጥ የሞከረው ግለሰብ በተወሰደበት እርምጃ ተገደለ

በደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር በንጉስ ተክለሀይማኖት ክፍለከተማ ቀበሌ 04 ልዩቦታው የትራፊክ መብራት አጠገብ የምስራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ ባልደረባ የሆኑት ምክትል ኮማንደር ዘላለም ጥላሁን በስራ ላይ እያሉ በስታር ሽጉጥ  በመምታት ህይወታቸው እንዲያልፍ ያደረገው ግለሰብ እርምጃ ተወሰደበት ።

ተከሳሾቹ ድርጊቱን ከፈጸሙ በኋላ  ባጃጅን ተጠቅሞ በመሸሽ ላይ እያሉ ህብረተሰቡ ለጸጥታ ሀይሉ በሰጠዉ ጥቆማ መሠረትተከታትለው በመሄድ እንዲቆም ሲጠየቅ ፍቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ  እርምጃ እንደተወሰደበት ብስራት ሬዲዮ ከደብረማርቆስ ከተማ ፖሊስ  መምሪያ ያገኘው መረጃ ያመላክታል። በዚህም ድርጊት ፈጻሚውን ለመያዝ በተከፈተ የጥይት ተኩስ ምክንያት  የደብረ ማርቆስ የጸጥታ ኃይል እና የምስራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ አባላት በወሰዱት  እርምጃ ባጃጇ ስትቃጠል ሲተኩስ የነበረው ግለሰብ ህይወቱ አልፎ 2 ስታር ሽጉጥ ከ 11 ጥይት ጋር እና አንድ ኤፍ 1 ቦንብ በቁጥጥር ስር ውሏል።

የከተማ አስተዳደሩ ሰላም እና ጸጥታን ለመንሳት የተለያዩ የዘራፋ ፣እገታ ፣ውንብድና የተለያዩ ተልኮዎችን እና ወንጀሎችን ሲፈጽም እንደነበረ አስታዉቋል።ተባባሪ ተከሳሾች በማህበረሰቡ  ጥቆማ ተገቢው እርምጃ ከመውሰድ ባለፈ በህግ አግባብም እስከ 21 አመት የእስራት ቅጣት ማስቀጣት መቻሉ ተገልጿል ።

ምክትል ኮማንደር ዘላለም ጥላሁን በምስራቅ ጎጃም ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በኃላፊነት ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን  በፖሊሳዊ ሙያቸው ህዝብን ሲያገለግሉ የነበሩ  የፖሊስ መኮነን የነበሩ መሆኑን  የደብረ ማርቆስ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ለብስራት ሬዲዮ የላከው መረጃ ያመላክታል ።

በኤደን ሽመልስ
#ዳጉ_ጆርናል
በእስር ላይ የሚገኙት የቻድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የረሃብ አድማ ማቆማቸው ተሰማ

የቻድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ሱሰስ ማሳራ ለአንድ ሳምንት ገደማ ከዘለቀው የረሃብ አድማ በኃላ አድማው ማብቃቱን ጠበቆቻቸው መናገራቸውን ፓርቲያቸው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ማስራ በዋና ከተማዋ ኒጃሜና ውስጥ ያለውን የእስር ጊዜያቸውን በመቃወም የረሃብ አድማ ማድረጋቸው ባለፈው ሳምንት አስታውቀዋል። የቻድ ዋንኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ለስ ትራስፎርማተርስ መሪ እና የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ማሳራ በሜይ 16 በዋና ከተማው የተያዙ ሲሆን በሎጎን ኦክሳይደንታል ግዛት ውስጥ በግንቦት 14 ቀን በተቀሰቀሰው እና 42 ሰዎችን ለገደለው ግጭት ተጠያቂ ናቸው ተብሏል።

ማሳራ “በአካል የተዳከሙ ቢሆንም በሥነ ምግባር የታጠቁ፣ የምግብ አድማውን አቁመዋል” ሲል የተቃዋሚው ፓርቲ መግለጫው ገልጿል። በተለይ ከእስር እንዲፈቱ ቅዳሜ እለት የተቃውሞ ሰልፎች ሴቶችን ጨምሮ አደባባይ በመውጣት የተደረጉ ሲሆን የአብሮነት ምልክቶች በስፋት በደጋፊዎች ዘንድ ታይቷል። እንደ ጠበቆቹ ገለጻ፣ ማሳራ በቅርቡ የመረመሩት የግል ሀኪማቸው የህክምና ምክር ተከትሎ የርሃብ አድማውን እንዲያቆሙ ወስነዋል። በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ጥላቻን እና ሁከትን ማነሳሳት፣ ከታጠቁ ቡድኖች ጋር በመተባበር እና በግድያ ወንጀል ተባባሪ በመሆን በተለያዩ ክሶች ተመስርቶባቸዋል።

ባለፈው ሳምንት ማስራ ከታሰሩ ከአንድ ወር በላይ በማስቆጠሩ እንደ ደጋፊዎቹ ሁሉ የታሰሩበትን ምክንያት ሲጠይቁ እንደነበር ተናግረዋል። እ.ኤ.አ በሜይ 2024 በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የተወዳደሩ ሲሆን በወቅቱ የሽግግር ፕሬዚደንት የነበሩት ማሃማት ኢድሪስ ዴቢ በምርጫው አሸንፈዋል። ባለፈው ወር ሂዩማን ራይትስ ዎች ማስራ “በትክክለኛ ወንጀል ካልተከሰሱ” በአስቸኳይ ከእስር እንዲፈቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኑ ጠይቋል።

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል
በ2017 ዓመት ሀረር ከ167ሺህ በላይ በሆኑ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች መጎብኘቷ ተነገረ

በ 12 ወራት ዉስጥ ክልሉን በማስተዋወቅ የውጪ ቱሪስት ቁጥርን 10ሺህ ለማድረስ ታቅዶ 11ሺህ 094 ቱሪስቶች ክልሉን የጎበኙ ሲሆን ይህም ከዕቅዱ አንፃር አፈፃፀሙ 100 ከመቶ  በላይ ለማሳካት የተቻለ ነዉ፡፡ አፈጻጸ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፃር በ36.4 በመቶ ብልጫ አሳይቷል ሲሉ የሀረሪ ክልል የባህል ቅርስ እና ቱሪዝም የእቅድ ዝግጅት ክትትል እና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አፈንዲ አብዲ    ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡

በውጭ ሀገራት  ቱሪስቶች በክልሉ የሚያወጡትን ወጪ ከ15 ሚሊየን ብር በላይ ለማሳደግ ታቅዶ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ክልሉን ከጎበኙ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ወጪ ተደርጓል፡፡ ገቢዉ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ22.4 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ገልፀዋል።የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 23 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ወጪያቸዉን በክልሉ ዉስጥ ከ159 ሚሊዮን ብር በላይ ማድረስ ተችሏል፡፡

በተጨማሪም በቱሪዝም ዘርፍ ለ 1ሺህ 760 ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር በታቀደው መሰረት በክልል ውስጥ አዳዲስ በሚገነቡ የሆቴል ግንባታዎች ስራ በጀመሩ ሆቴሎች፣በገስት ሀውስ በዕደ ጥበብ ስራ ላይ የስራ እድል በመፍጠር በአጠቃለይ ለ1ሺህ 331 ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር አፈፃፀሙ ከ75 በመቶ በላይ መድረሱን ገልፀዋል።

በከተማው በሚገኙ ሶስት ሆቴሎች ማለትም ሀረር ራስ ሆቴል፣ግራንድ ገቶ እና ወንደርላንድ ሆቴሎች ላይ ለቱሪስቶች የሚሆን የዕደጥበብ መሸጫ ክፍል ለይተው እንዲያዘጋጁ የተደረገ ሲሆን በዚህም ዕደ ጥበብ ዘርፍ ገበያ ትስስር በማድረግ የስራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል ሲሆን በቀጣይ ፍላጎት ያላቸውን በዘርፉ የተሰማሩ አካላትን ወደዚህ ዘርፍ እንዲገቡ ለማድረግ የሚሰራ ይሆናል ሲሉ አቶ አፈንዲ አብዲ ጨምሮ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።

በሰመኃር አለባቸዉ
#ዳጉ_ጆርናል
Forwarded from ዳጉ ጆርናል-ስፖርት (Beⓒk)
የሲዳማ ቡና ዋንጫ አንስቶ በነበረበት ወቅት ለተጨዋቾች በሀዋሳ የተሰጠዉ 200 ካሬ ሜትር መሬት እጣ ፈንታዉ ምን ሊሆን ይችላል...?

የሲዳማ ቡና እግርኳስ ክለብ ወላይታ ዲቻን በማሸነፍ የኢትዮጵያ ዋንጫ ባለቤት መሆኑን ተከትሎ ከሰሞኑ ለ 17 የቡድኑ ተጨዋቾች ሽልማት ሰጥቶ ነበር።

የሲዳማ ክልል ሲሆን ሽልማቱን የሰጠዉ 17 ተጨዋቾች እያንዳዳቸዉ መኖሪያ ቤት እንዲሰሩበት በሚል 200 ካሬ ሜትር ቦታ በሀዋሳ ከተማ በሲዳማ ክልል ፕሬዚዳንት ደስታ ሌዳሞ ተሰጥቷቸዉ ነበር። ክልሉ ለቀሪ ተጨዋቾችም 7 ሚሊዮን ብር ሽልማት ሰጥቶ እንደነበር ዳጉ ጆርናል ስፖርት ተገንዝቧል።

ታድያ በዛሬዉ እለት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ወላይታ ዲቻ ያቀረበዉን ቅሬታ ተከትሎ ባደረገዉ ምርመራ ሲዳማ ቡና ቅጣት ላይ የነበረ ተጨዋች በማሰለፉ ዋንጫውን ቀምቶ ለወላይታ ዲቻ እንዲሰጥ ወስኗል።

ይህ ዉሳኔ ከተሰማ በኋላ የዲቻ ደጋፊዎች ሶዶ ከተማ ላይ በዛሬዉ እለት ደስታቸዉን ገልጸዉ ነበር።

ታድያ የሲዳማ ክልል ለሲዳማ ቡና ተጨዋቾች የሰጠዉንስ መሬት ይነጥቅ ይሆን?

በበረከት ሞገስ

#ዳጉ_ጆርናል_ስፖርት
@Dagujournalsport
የግብፁ መሪ አል-ሲሲ ከሊብያው አዛዥ ካሊፋ ሃፍታር ጋር ከተወያዩ በኃላ በካይሮ ከአልቡርሃን ጋር መከሩ

ፕሬዝደንት አብደል ፈታህ አልሲሲ ከሊብያዊ ወታደራዊ አዛዥ ካሊፋ ሃፍታር ጋር ተገናኝተው በቀጠናዊ ውጥረት ዙርያ ውይይት ካደረጉ ከሰዓታት በኃላ ከሱዳን ሉዓላዊ ምክርቤት ሊቀመንበሩ ጀነራል አብደልፈታህ አል ቡርሃን ጋር በካይሮ ተገናኝተው መክረዋል።

ምንጮች እንደገለፁት ከሆነ አል ቡርሃን በስፔን ሴቪል የተካሄደውን የመንግስታቱ ድርጅት ኮንፈረንስ አቋርጠው የወጡ ሲሆን ከስፔን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ሊያደርጉት የነበረውን ውይይትም ሰርዘዋል። ከስፔን በቀጥታ ወደ ካይሮ ያቀኑት ጀነራሉ የሊቢያው ምስራቃዊ አዛዥ ሃፍታርም በካይሮ በነበሩበት ወቅት እዛ መድረሳቸው ተዘግቧል።

የሲሲ እና የሃፍታር ስብሰባ የውጭ ኃይሎችን እና ቅጥረኞችን ከሊቢያ የማስወገድ አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ መሆኑን የግብፅ መንግስት ሚዲያ ዘግቧል። ንግግሮቹ በሱዳን፣ በግብፅ እና በሊቢያ መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ የድንበር ትሪያንግል በፓራሚትሪ ፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች መያዙን ተከትሎ ነው። የሱዳን ጦር ለሊቢያ አዛዥ ከሊፋ ሃፍታር ታማኝ የሆነ የሳላፊስት ሚሊሻ አርኤስኤፍን ረድቷል ሲል ከሰዋል። በሊቢያ የአርኤስኤፍ ወታደሮች ማሰልጠኛ ካምፖችን አሉ በሚልም ዘገባዎች ይወጣሉ።

ውይይቱን የሚያውቁ ሁለት ምንጮች ሲሲ የድንበር ውጥረቱን ለማርገብ ቡርሃን እና ሃፍታር ለማስታረቅ ሊጥሩ እንደሚችል ተናግረዋል። የግብፅ ፕሬዝዳንት ባወጣው ይፋዊ መግለጫም ቡርሃን እና ሲሲ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ማጠናከር፣ የሱዳንን መልሶ ግንባታ እና የኢኮኖሚ ትብብርን ማጠናከር ላይ ተወያይተዋል።

ሲሲ ግብፅ የሱዳን አንድነት እና ሉዓላዊነት እንደምትደግፍ አረጋግጠዋል ሲልም መግለጫው አክሏል። ሁለቱም መሪዎች በሀገሪቱ ቀጣይነት ባለው ግጭት ለተጎዱት የሱዳን ዜጎች ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተስማምተዋል።

በሚሊዮን ሙሴ
#ዳጉ_ጆርናል
ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በትግራይ የሚገኙ ተፈናቃዮች ተንቀሳቃሽ የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበትን ሁኔታ እያመቻቸዉ መሆኑን አስታወቀ

በትግራይ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ መነገሩን ተከትሎ ጣቢያችን ብስራት ሬዲዮ ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ለእነዚህ ተፈናቃዮች እያደረገ ያለዉን ድጋፍ ለማጣራት ወደ ተቋሙ ደዉሏል ።

የዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ የህዝብ ግንኙነት ተቆጣጣሪ ስቴቨን አንደርሰን በግጭት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ተፈናቃዮች በመቀሌ በቋሚነት አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም መኖሩን ገልፀዉ በሽሬ ተንቀሳቅሰዉ ይህን አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች   እያመቻቸ መሆኑን ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል ።

ከዚህ በተጨማሪ የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት እና የተለያዩ እንደ ዊልቸር ያሉ የቁሳቁስ ድጋፎችን እንዲያገኙ እየተሰራ ይገኛል። ተፈናቃዮች ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገናኙበት እንዲሁም ለፆታዊ ጥቃት የተጋለጡትም ነፃ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉ ተገልጿል ።

ተቋሙ 20 የጤና መዋቅሮችን በህክምና ቁሳቁሶች እየደገፈ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ከትግራይ ዉጪ በተለያዩ አከባቢዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ስቴቨን አንደርሰን ጨምረዉ ለጣቢያችን ተናግረዋል ።

በመባ ወርቅነህ
#ዳጉ_ጆርናል
አሜሪካ ለእስራኤል የ510 ሚሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ሽያጭ አጸደቀች

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደገለጸው ሽያጩ ሁለት የተለያዩ የቀጥታ ጥቃት ፈንጂዎች እና ከ7,000 በላይ የቦምብ መቆጣጠሪያ መሳሪያዎችን ያካትታል። የቅርብ ጊዜው ሽያጭ የተወሰነው እስራኤል በቅርቡ በኢራን ላይ ባደረሰችው ጥቃት ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ካወጣች በኋላ ነው።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ሽያጩን ያፀደቀ ሲሆን የመከላከያ ደኅንነት ትብብር ኤጀንሲ አስፈላጊውን መረጃ ለአሜሪካ ኮንግረስ ሰጥቷል፣ ይህ የታቀደው ሽያጭ የእስራኤልን ድንበሮቿን፣ አስፈላጊ መሠረተ ልማቶችን እና የህዝብ ማዕከላትን የመከላከል አቅሟን በማሻሻል የአሁን እና የወደፊት ስጋቶችን የማሟላት አቅሟን ያሳድጋል። እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ የምታደርገውን አሰቃቂ ጥቃት በቀጠለችበት ወቅት ይህ እቅድ ተግባራዊ ሆኗል።

ከጥቅምት 2023 ጀምሮ በእስራኤል ጥቃት ከ56,500 በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ሲል የጋዛ የጤና ባለስልጣናት አስታውቀዋል። ሰኞ ዕለት ብቻ፣ የተፈናቀሉ ሰላማዊ ዜጎችን የሚጠለሉባቸውን ቦታዎች ጨምሮ እስራኤል በፈፀመችው የአየር ድብደባ እና የመድፍ ጥቃት በጋዛ በርካታ ቦታዎች ላይ ኢላማ በማድረግ ቢያንስ 97 ፍልስጤማውያን ሲገደሉ በርካቶች ቆስለዋል።

በጋዛ የዜጎች ሞት እያሻቀበ ባለበት ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ ለእስራኤል የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ በመቀጠሏ ከፍተኛ ትችት ገጥሟታል። ባለፈው ህዳር ወር የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትራቸው ዮአቭ ጋላንት በጋዛ በፈጸሙት የጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ ወንጀሎች የተነሳ የእስር ማዘዣ አውጥቷል። እስራኤልም ከአካባቢው ጋር ባደረገችው ጦርነት በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ ቀርቦባታል።

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል
2025/07/03 23:36:33
Back to Top
HTML Embed Code: